እንጉርጉሮ ( ዘለስኛ )
ስማኝ ወዳጄ ምነው ?
ዛሬ በ21 ኛው ክ/ዘመን
የጥንቱን ሰው በመኮነን
የዛሬውን ትውልድ መክሰሱ.
ምን ይረባል መዋቀሱ ?
ሥማኝ ወዳጄ ምነው ?
ሰው የልብ ወደጁን ሲጠላ
እሳት ይሆናል የሚባላ
አለሁ፣አለሁ እያለው
ሥንቱ ጓዱን በለው ?
ስማኝ ወዳጄ ፣ ምነው ?
ዛሬ ጋኖች አልቀዋል
ምንቸቶች ጋን ሆነዋል
አያችሁ አይደል በጥበብ ልብስ
ድንቁርና አገር ሲያፈርስ ።
ስማኝ ወዳጄ ምነው ?!
በገንዘብ ገዝቶ ያንን ካባ
ወንበር ሲሰጠው በደባ
ይኸው ከላይ ተቀምጦ
መግዛት ጀመረ ደፍጥጦ ።
ስማኝ ወዳጄ ፣ ምነው ?
አንድ እብድ ሺ ጤነኛን
በመንጋ ሲነዳ አየን
ቀና ምክራችን ሰሚ ካጣ
ወይ ያኔ ነው የሚመጣ ።
ስማኝ ወዳጄ ፣ ምነው ?
የእውነት አንደበት ተዘግቶ
ኃቅ አውሪ ሰው ተፈንክቶ
ውሸታም ሰው ከበረታ
አገር በወሬ ነው የሚፈታ።
ሥማኝ ወዳጄ ምነው ?
በዝተዋል ጥላቻን ሰባኪዎች
በቋንቋ ጎሣ አጋጪዎች
በምለስ ጉልበት ብር ሊያፍሱ
እዩት ጥላቻን ሲያነግሱ ።
ስማኝ ወደጄ ፣ ምነው ?
በሬ አዋለጅ ሲበዛ
ይከተለናል ድንዘዛ
ተፈጥሮው ሳይሆን እርግዝና
ውለድ ይለዋል በሬውን ተኛና ።
( መጋቢት 2013 ዓ/ም መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ )
ግለሰቦች በአንድ አገር ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ና ዘመን የማይሽረው ሥም ሊኖራቸው የሚችለው ፣ ለመላው ዜጋ ጥቅም እና ለአገራቸው ክብርና ልእልና መወገናቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ድርጊት ሲፈፅሙ ና ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችን ሰርተው ሲያልፉ ነው ።
…ንጉሥ ቀዳማዊ ሚኒልክ ፣ንጉሥ ላሊበላ ፣ ንጉሥ ፋሲል ፣ንጉሥ ቴዎድሮስ ፣ ንጉሥ ዮሐንስ ፣ንጉሥ ዳግማዊ ሚኒልክ … ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ፣ ፕሬዘዳንት መንግሥቱ ፣ ጠ/ሚ መለሥ ፣ ሞተው እንኳን ታሪክ እና ትውልድ የማይረሳቸው ፣ በምድሪቱ ገፅ ላይ ና በየትውልዱ አትመው በሄዱት መልካም ና ክፉ አሻራ የተነሳ ነው።
የአገር መሪዎች ለሚመሩት ህዝብ ያበረከቱትን መልካም ሥራ እና በተቃራኒው ደሞ የፈፀሙትን እኩይ ተግባር ታሪክ በየጊዜው መዝግቦ ያሥቀራል ። በግልፅ አሥቀምጠው የሄዱትም አሻራ ማንነታቸውን ይመሠክራል።መሪዎች ለሚመሩት ህዝብ ፣ ምን እንደሰሩለት እና በተቃራኒው ህዝቡን እንደሽፋን በመጠቀምና በሥሙ በመነገድ ፣ ግፍ ሲፈፅሙበት እንዲኖሩ ፣ አገርን በዝብዘው እርሱን አደህይተው እነሱ እንደበለፀጉ ታሪክ ሳያዳላ መዝግቦ ያቆያል ። ሰዎች ታሪክን ሲፅፉ ሊያዛቡ ይችላሉ ።እውነተኛ ታሪክ ግን በትውልድ ቅብቡሎሽ በሰው ልብ ውሥጥ ታትሞ ለዘላለም እንደሚኖር መዘንጋት የለብንም ።
የሩቁን ትተን የቅርቡን የመለሥ አገዛዝን ቱሩፋት እና ከሞተ በኋላ የቀጠለውን ውርስ ሥራውን (ሌጋሲውን ) ብናሥተውል ፣ የምናዝንበት ክፉ ሥራ ከመልካሙ ሥራው በእጅጉ ልቆ በእያንዳንዳችን ልቦና ውሥጥ ታትሞ እናገኘዋለን ።
መለሥ በኢትዮጵያዊው ጥቁር አባይ መጠቀም መብታችን እንደሆነ በተግባር ማሳየቱ ከመልካሙ ሥራው በዋነኝነት ቢጠቀስም ፣ አገርን በጎሣ ሸንሽኖ የህዝብ ለህዝብ ፍቅር እንዲሸረሸር በማድረግ ፣ አገር እንድትፈራርስ መንገድ መጥረጉ ፤ ” ቤንሻንጉል ላይ የጀመረው ታላቅ ግንባታ ፋይዳው ምንድነው ? ” ያሰኘ ነበር ።ለዚህ ነው የመለሥ አገዛዝ ሲነሳ ዘረኝነቱ ና የጭካኔ ክፉ ድርጊቱ ደምቆ የሚታየን ።
ከመለሥ ዜናዊ ሞት በኋላ ፣ በቀጠለው የውርስ አገዛዝም ሲቀነቀን የነበረው ዋልታ ረገጥ ብሔርተኝነት ነው። ይህ ጠርዝ ላይ የቆመ ፀረ ፍቅር የሆነ ብሔርተኝነት ምን ያህል የአንድነት እና የህብረት ጠላት ፤ የግጭት ና የሰላም እጦት መንሥኤ ፤ እንዲሁም የደም ነጋዴዎች ማትረፍያ እንደነበረ ፣ ገጣሚ ና ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም ፣ ” ከአሜን ባሻገር ” በተሰኘ መፅሐፉ በገፅ 11 ላይ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል ።
” በዘመናችን ብሔርተኝነት ማለት ፣ሳይደክሙ ፣ የሌሎችን የድካም ውጤት መቀማት መሆኑንን አውቃለሁ ። አንድ ሰው በግሉ ስኬት መቀዳጀት ሲያቅተው ፣ በጥረታቸው ብልጫ ያስመዘገቡ ግለሰቦችን ስኬት ወደ ብሔር ስኬት ለውጦ ባዶነቱን ለመሙላት ይሞክራል ። ሌላው ፤ እልም የለ ፈሪ ሆኖ ሳለ “የበላይ ዘር ” እያለ ይፎክራል ። ብብቱ ውሥጥ ገብተው ካልደገፉት በቀር አልጋ ላይ መውጣት የማይችለው ሰውየ ፣ አበበ ቢቂላ በተነሳ ቁጥር “አበበ ኬኛ “ብሎ ይኩራራል ። በላይ ና አበበ ያስመዘገቡት ድል ፣ በላብና በደም የተገኘ የግለሰብ ጥረት ውጤት ነው። ድል በዘር አይተላለፍም ። የአባቶች ታላቅነት በዘር ወደ ልጆች የሚተላለፍ ቢሆን ኖሮ ግሪኮች በዛሬይቱ የአውሮፓ እግር ሥር እንደ ጉድፍ ወድቀው ባልተገኙ ነበር ። ብሔርተኝነት የግለሰብ ጥረትን ሰርቆ የራስን ድክመት ለመሙላት የሚደረግ መሰሪ እንቅስቃሴ ነው ።
ከውስጥ አዋቂ የሰማሁት አንድ ገጠመኝ ምሥክር ይሁነኝ ። የአንድ የብሔር ጎበዝ አለቃ የሆነ ሽማግሌ በኢትዮጵያ በአንዱ ክፍል ይኖራል ። ሀለት አርብቶ አደር ብሔሮች በግጦሽ ሳር ወይም በውሃ ምክንያት ይጣላሉ ። ይኼኔ ይኽ ሽማግሌ በዘመናዊ ላንድ ክሩዘር ወደ አዲስ አበባ ተጠርቶ ይመጣና ግጭቱን እንዲያቆም ትእዛዝ ይተላለፍለታል ። ለግጭት መቆጣጠሪያም ተብሎ ዳጎስ ያለ ብር በሰፊው ኪሱ ውስጥ ሻጥ ይደረግለታል ። ሽማግሌው ወደ ግጭቱ ቦታ ተመልሶ ከተቃራኒው ወገን የተሰለፉትን አቻ የጎሣ መሪዎች ይጠራና ከተመደበለት ጉርሻ ያካፍላቸዋል ። እነሱም በራሳቸው መንገድ የተቀሰቀሰውን ግጭት ያበርዱታል ።
የጎሣ መሪ ሽማግሌዎች ገንዘባቸው ሲያልቅ እንደገና ግጭቱን ይቀሰቅሱታል ። ጎበዛዝት ይዘነጣጠላሉ ። ጎጆዎች ይቃጠላሉ ። ያዲስ አበባው መንግሥት ባለሥልጣናት ሽማግሌውን እንደገና ጠርተው ይለማመጡታል ። የደም ገንዘብ የለመዱ ሰላምን አርቀው ይቀብሯታል ።… ”
በመለሥ ዜናዊ የአገዛዝ ዘመን እና ከሞተም በኋላ በቀጠለው ወራሴ መንግሥቱ በየክልሉ የቀጠለው ፣ ይህ አሳፋሪ ድርጊት ነበር ። ይህንን አሳፋሪ ድርጊት እና ሌሎች የዴሞክራሲ ና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመቃወም፣ወጣቶች ታላቅ ትግል አድርገው ፣ በመሰዋትነታቸው የዘረኞችን ወንበር ከተቸከለበት እንዲነቀል አድርገዋል ።
እነዚህ የአገራችን ወጣቶች ፣ የተደራጀ ፓርቲ ሥለሌላቸው …” ቤተኛ ባይተዋር ” (የመደመር መንገድ ገፅ 3 ) በመሆን በህቡ ሲታገሉ የነበሩት ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ነፃነት በመወገን ፤ የመለሥ ዜናዊ ሌጋሲን በታላቅ ጥንቃቄ እንዲቀበር በማደረግ ፤ የመሪነት መንበሩ ላይ ” የለውጡ አመራር ሰጪ ነን አገርን ወደ ሁለተናዊ ብልፅግና እናሻግራታለን ። ” በማለት መቀመጣቸውን አንዘነጋም ። እንሆ በመንበሩ ከተቀመጡ ሦሥት ዓመት ሆናቸው ። ( የለውጥ ኃይሎቹ መጋቢት 24/2010 ዓ/ም የመሪነት ሥልጣንን እንደያዙ ይታወቃል ። )
የመለሥ ዜናዊን የውርሥ መንገድ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ሲያሥቀጥሉ የነበሩት ( ኋላ ላይ ልማታዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ተብሎ ነበር ። ) ከአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ተላቀናል ፣ ለውጥን ፈላጊ የውሥጥ አርበኞች ነበርን በማለት በአደባባይ ምለውና ተገዝተው ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረጋቸውና የፈጠራቸውን እግዛብሔርን በባዓለ ሲመታቸው ወቅት በማክበራቸው ድፍን ኢትዮጵያ ልባዊ ድጋፉን የዛሬ ሦሥት ዓመት ገልፆላቸዋል ። ( ሙሉ ታሪኩን የመደመር መንገድ መፀሐፍን አንብበህ ተረዳ ።)
በነገራችን ላይ በዓለ ሲመት የሚለው ቃል ፣የሥልጣን የመጀመሪያ ቀን ማለት ነው ። ከዚህ የዘለለ ትርጉም የለውም ። ያሥልጣን መጀመሪያ ቀንን በተመለከተ አሜሪካ በህግ የተደገፈ ቀን ካላቸው ተጠቃሽ አገሮች ቀዳሚ ናት ።
በዓለ ሲመት የሚለው ቃል ተግባራዊ የሆነው ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያዚያ 30/1789 እኤአ ጆርጅ ዋሽንግተን ፕሬዝዳንት ሲሆኑ ነው። ከሦሥተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከቶማስ ጀፈርሰን ጀምሮም እሥከዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ የበዓለ ሲመት ፕሮግራም ይከናወናል ።
በ1857 ለመጀመሪያ ጊዜ የፎቶ ካሜራ በሥራ ላይ በመዋሉ ፤ ፕሬዝዳንት ጀምስ ቤክን በባዓለ ሲመታቸወ ወቅት ፎቶ በመነሳት የመጀሪያው ፕሬዝዳንት ናቸው ።
ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌቪዥን ሥርጭት በጥቁርና ነጭ ፊልም የታየው የ1949 (እአአ) የሃሪ ትሩማን በዓለ ሲመት ነው ።
የአሜሪካው ታላቅ የበዓለ ሲመት ክንዋኔ ከመጋቢት ሰባት ወደ ጥር 20 እኤአ እንዲሆን የተወሰነው ፣ከፍራንክሊን ሩዝቬልት ፕሬዝዳትነት ጀምሮ ነው ።
በአሜሪካ በዓለ ሲመት ታሪክ መፅሐፍ ቅዱስ ይዞ መማል የተለመደ ነው ። ይሁን እንጂ ሦሥት ፕሬዝዳንቶች መፅሐፍ ቅዱሥ ላይ እጃቸውን ጭነው አልማሉም ።
በአሣፋሪ መልኩ በሚተኳቸው ፕሬዚዳንት የሥልጣን መረከቢያ የመጀመሪያ ቀን ያልተገኙ ተሰናባች ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራፕ ብቻ ናቸው ።
ከዚህ እውነት አንፃር በአገራችን በህግ የተደነገገ ቁርጥ ያለ የሥልጣን ሽግግር ቀን የለም። ይህ ማለት ደግሞ በዓለ ሲመት የሚባል ህጋዊ ክንውን በኢትዮጵያ እንደሌለ ያረጋግጥልናል ።
መንግሥቱም መለሥም በጉልበት ነው ሥልጣን ላይ የወጡት ። በህዝብ ፈቃድና በምርጫ አይደለም። ኃይለማርያምም በኢህአዴግ ይሁንታ ነው ጠ/ሚ የሆኑት ። ሥልጣናቸውን በህዝባዊው ንቅናቄ አሥገዳጅነት በመልቀቃቸው ፣ በሳቸው እግር የተተኩት አብይ አህመድም በኢህዴግ ውሥጥ የተደረገውን የለውጥ ትግል ከጓዶቻቸው ጋር ሆነው በማሸነፋቸው ነው ፤ የአገር መሪነቱን መንበር በኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ የያዙት ።
በኢትዮጵያ ታሪክ በትከክለኛ ፣ ነፃ ፣ተአማኒ ፣ ዴሞክራሲያዊ ና ሰላማዊ ምርጫ ወደ መንበሩ ላይ የመጣ መሪ እና በህግ የበላይነት የሚያምን ነፃ የሆነ ጠንካራ ተቋማትን ያደራጀ መንግሥት አልነበረም።
ይህንን እውነት አሥመልክቶ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ፣በቅርብ ለህትመት ባበቁት የመደመር መንገድ መፀሐፋቸው በገፅ 357 ኢትዮጵያ የተዘፈቀችበትን ችግር ከግሪክ አፈታሪክ “ የዳናኢደስ የሽቁሩ እንሥራን እና የ50 ሴቶችን ፣ በሽቁር እንሥራ ውሥጥ ዘላለም ዓለማቸውን ውሃ በመገልበጥ እንዲሞሉ የተደረገበትን ትርክት “ በማሥቀደም ፣ በተቋማት ጥንካሬ የሚያምን መንግሥት ለመገንባት ቆርጠው መነሳታቸውን በገደምዳሜ አሳውቀውናል ። ነፍሥ ሄር ፕሮፊሰር መሥፍን ወልደማሪያም “እንዘጭ እንቦጭ ” በማለት ከገለፁት ፣ በህዝብ ሥም ከሚነግድ ሥርዓት ፣ ወደ ህዝብ አገልጋይ ሥርዓት በብልሃት መሻገር እንደሚያሥፈልግ ገልፀዋል ።
“…ብልህነት ሰለጎደለን በየጊዜው እሷን ይሞላልናል ያልነውን ውኃ ከማመላለስ በዘለለ ቆም ብለን እንሥራችን ሥለምን አልሞላችም ብለን አልጠየቅንም ።የማትሞላበትን ሽንቁሯን ዐውቆ ሊደፍንላት የሞከረ የለም ። በ1960ዎቹ አብዮት አካሂደናል ፤ እንስራው ውኃ እንዳልተጨመረበት ጎዶሎ ነው ። የ1997 ምርጫ ደግሞ ይሞላዋል ያልነው ቀርቶ ያለውንም አንጠፍጥፎ እንሥራውን ጭራሽ ባዶ አደረገው ።ኢትዮጵያን ለመገንባት ፣ ይህችን ለዘመናት የጎደለች እንሥራችንን ለመሙላት ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል ። ያደረግናቸው ሙከራዎችንሁሉ ግን እንደ አፈታሪኩ ሽንቁር እንሥራ መሙላት ሆኖብናል ።….
…ህጋዊነት ፣ ሞያተኝነትና ተቋማዊ አሰራር ሥር ይዘው በተቋቋሙባቸው አገሮች ፣የፓለቲካ መዋቅሩ ፣ሥርዓቱ ፣ ደንቡ ፣ መዓረጉና የመሳሰሉት አሠራሮች ቋሚና እንደመሬት ዘላቂ ናቸው ። የባንዲራቸው ዕድሜ በመቶና በሺ ለሚቆጠር ዓመታት ሊዘልቅ ይችላል። የህዝብ መዝሙሩ አያሌ ትውልድ አገልግሎ ገና የልጅ ፣ ልጅ ልጆች ሊዘምሩት ይችላሉ ። የከተሞች፣ የመንገዶች ፣ የትምህርት ቤቶች ፣ ሥምና ባለቤትነት በመካከለኛው ክ/ዘ የጀመረ ሊሆን ይችላል ። ባልታሰቡ አሥገዳጅ ሁኔታዎች ሳቢያ የሚለወጡ አንዳንድ ጉዳዮች ሊኖሩ ቢችሉም ፤ አብዛኛው ነገር ትውልድን በቋሚነት እንዲያገለግል ሆኖ ነተዘጋጀ ነው ።…”
ከዚህ የጠ/ሚ እይታ ተነስተን ፣ መፀሐፋቸውን በጥሞና አንብበን ፣ በለውጡ መሪ ህሊና ውስጥ ያለውን የታላቅ አገር የመፍጠር ራእይ መመልከት እንችላለን ።
ይህንን ሥል ፣ እያንዳንዱ ሰው ፣ ያለውን የግል ምልከታ በማክበር ነው ። ከህሊና እና ከገንዘብ ጋር የተሰለፈ ሰው ከቶም እንደማይጣጣምም አውቃለሁ ። … ለዚህም ነው ፤ ቅኔያዊ ግጥሜን “እጉርጉሮ ” በማለት ለፅሑፊ መግቢያ ያደረኩት ።
ለማንኛውም ከላይ ያነሳኋቸውን ጭብጦች በማሥተዋልና በታሪክ ውሥጥ የግለሰቦች ሚና ከፍተኛ መሆኑንን በማሥተዋል ነው ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት የመሪነት ዕድል ለጠ/ሚ አብይ አህመድ ቢሰጣቸው መልካም ነው የምለው ።
የጠ/ሚ አብይ አህመድ ሃሳብ ከአድማሥ ባሻገር በመሆኑ ብዙ ምሁራኖችን እንደሚያወዛግብ ይገባኛል ። ቢሆንም ግን አገር በደቦ ሳይሆን የተለየ ችሎታ ፣ ክህሎት ና ተሰጥኦ ባላቸው ግለሰቦች ሥትመራ ምን ያህል ለውጥ እንደምታመጣ ከአውሮፓ ና አሜሪካ መማር እንችላለን ።
የእሥታሊንን አገር ታላቅ የማድረግ ህልም የዛሬዎቹ ሶቬቶች አይረሱትም ። የጆርጅ ዋሽንግተንን የነፃነት ትግልና የአሜሪካ የመጀመሪያ ፕሬዝዳትነት አሜሪካዊያን ለዘላለም ያሥታውሱታል ። የሮማን ኢምፓየር ታላቅነትነ እና ጁሊየስ ሲዛርን ማን ይረሳል ። የግሪክ ጥበበኛ መሪዎችን እና ንጉሥ ላሊበላንም እዚህ ላይ መጥቀሱ መልካም ነው ። ደሞምም ህንድ እንደ መሀተመ ጋንዲ አይነት መሪ ፤ አፍሪካ ደግሞ እንደ ማንዴላ አይነት ይቅር ባይ መሪ እንደነበራት አሥታውስ ።
ብልህ ለሆኑ ፣ አሥቀድመው ነገሮችን በጥልቀት ለሚፈትሹ መሪዎች እድል መሥጠት ፣ የበዙ መልካም ነገሮችን እንዲፈጠሩና በሥራ ላይ እንዲውሉ እንደሚያደርጋቸው ይታመናል ። አገራችን የተፈራ የመከላከያ ኀይልና በመላው ኢትዮጵያ ህግን ማሥከበር የሚችል የፖሊሥ ኃይል ሊኖራት የሚችለው እንደ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ያሉ መሪዎች ፣በኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ በአደባባይ የተመሠከረ የመመራት ዕድል ሲሰጣቸው ነው ብዬ አምናለሁ