ፖለቲካ የማስተዳደር ጥበብ እንጂ ቁማር አይደለም – ከንገሤ አሊ

(Politics is not gambling, it is the art of governing) !!!

/

የጎሣ ብዝኃነት ባሉባቸው ሀገሮች ብሄርን መሠረት ያደረገ መንግሥታዊ ስርአትን ማዋቀር በብዙ ምሁራን ዘንድ እንደ አደገኛ አካሄድ የሚወሰድ የሀገርን ሉአላዊነትና የሕዝብን አንድነት የሚያናጋ ፣ የጎሳ ንቃተ-ህሊና ከመጠን በላይ እንዲገን ስለሚያደርግ በደም ግንኙነት ላይ ለተመሰረቱ (የጎሣ) መብቶች ብቻ ስለሚታገሉ የጋራ ማንነቶች እና የግለሰብ መብቶች ስፍራ ያጣሉ ።ያም የሚሆነው ራስን በራስ የማስተዳደር መርህን በማዛባት በጎሣው ስም መንበረ ሥልጣኑን የሚቆናጠጠው ኤሊት በሥልጣን ለመቆየት በምንግሥታዊና በኢኮኖሚ መዋቅሮች በሙሉ ችሎታን መሰረት ያላደረገ በዝምድናና በጎሣ ወሳኝ የሆኑ የሥልጣን እርከኖችና መሰረታዊ የሀብት ምንጮች እንዲያዙ ይደረጋል። ይህ ሊሆን ይችላል በሚል የሚቀርብ ግምታዊ ንድፈ ሀሳብ አይደለም ። የሌላውን ትተን በአገራችን ኢትዮጵያ ለሃያ ሰባት ዓመት ተሞክሮ የከሸፈና ጎራ ለይተን እርስ በርሳችን እንድንተላለቅ ያደረገንና አሁንም እስከ ዘር መጠፋፋት ያደረሰን ይሄው የጎጥ ፖለቲካ ነው ።

በጎሣ የተከለለ አስተዳደራዊ መዋቅር መሰረት በማድረግ የሚመሰረት መንግሥታዊ ስርአት በምንም ተአምር ዲሞክራሲያዊ ማድረግ አይቻልም የጎሣ ፖለቲካ አቀንቃኝ ጽንፈኛ ሊህቃን እንደሚሉት የአተገባብር ችግር አይደለም ። ያማ ቢሆን ኖሮ ትህነግ ተባሮ መቀሌ ሲከትም በትረ ስልጣኑን በበላይነት የተረከበው ኦህደድና ኦነግ (የኦሮሞ ብልጽግና) ነው። መልከጥፉ በስም ያወድሱ ካልሆነ በቀር ተህነግ የጀመረውን ከማስፈጸም በቀር በሶስት ዓመት የሥልጣን ጊዜ ያሳዩን የአተግባበር ጅማሮ እንኳን የለም ። ይባስ ብሎ ሥልጣኑን በበላይነት የጨበጠው ኦህደድ ኦነግ (የኦሮሞ ብልጽግና) በፌደራልና በክልል የስልጣን የበላይነት ኖሮት በተለይም በራሱ ክልል የታጠቀ የኦነግ ሰራዊት ከውጪ ከማስገባቱ በተጨማሪ ከ30 ጊዜ በላይ ልዩ ኃይል አሰልጥኖ ከኦሮሞ ውጭ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ በክልሉ እንዳይኖር የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ዘመቻ ማካሄድ እንጂ የጎሣ ፖለቲክን በተግባር ዲሞክራሲያዊ ማድረግ እንደሚቻል አላሳዩንም።

የዘር ፖለቲካ ድሞክራሲያዊ ማድረግ ያለመቻሉን ለማወቅ የግድ ጠበብት መሆን አያስፈልግም ከላይ በተግባር መሬት ላይ ያለውን ኃቅ ለማሳየት እንደተሞከረው ምሁር ንኝ ባይ የኦሮሞ ጽንፈኞች በአንድ በኩል የአተገባበር ችግር ነው እያሉ በሌላ በኩል የሚናገሩትን ስናስታውስ እግዚኦ መሀሬነ ክርስቶስ የሚያሰኝ ነው ለማንኛውም እስቲ በአጭር ትውስታችን (short memory) እናስታውሰው ፦

 

አቶ ለማ መገርሳ ስለ ዲሞግራፊ ማስተካከል ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን በክልሉ ውስጥ ቦታ የጠበባቸው ይመስል አዲስ አበባ አምጥተው በማስፈር የኦሮሞ ቁጥር በማብዛት የአዲስ አበባ ባለቤት የማድረግ ሙከራ የጎሣ ፌደራሊዝምን በአተገባበር ዲሞክራሲያዊ የማድረግ ጅማሮ አይመስለኝም።

 

አቶ ጃዋር መሀመድ የተጀመረው የዲሞግራፊ ማስተካከል ተግባር ሳይሳካ ቀርቶ በምርጫ ቢሸነፉ በሜንጫ ያም ካልሆነ አዲስ አበባን ለማንም የማትሆን(irrelevant) እናደርጋታለን ሲለ የኦሮሞ የግል ኃብት የማትሆን ከሆነ ማንም እንዳይኖርባት እናደርጋለን ሲሉ ባልበላው ጭሬ እበትነዋለሁ ነው እንጂ የነዋሪው ብሎም የኢትዮጵያውያን የጋራ ኃብት ነው ስላላሉ ምን አይነት አዲስ ዲሞክራሲያዊ አተገባበር ልሆን ይችላል ?

 

አቶ ሺመልስ አብዲሳ ብልጽግና ፓርቲን የመሰረትነው ለራሳችን ብለን ነው ሲሉ በተረኚነት እንደ ህወኃት ባንኩንም ታንኩንም ተቆጣጥረን ለመግዛት ነው ማለታቸው እንጂ የዘር ፖለቲካውን ዲሞክራሲያዊ እያደረግን ነው ማለታቸው አይደለም ። ቋንቋንም አስመልክቶ እኛ ስለ ቋንቋ የምንለው የሌላው አስጨንቆን ሳይሆን አማርኛን ተቀባይ ለማሳጣት ነው ያሉት የቋንቋ እኩልነት እንዳይኖር የሚታገሉት፤ ፖለቲካን ቁማር ነው የበላ ያሸንፋል ሲሉ የጎሣ ፖለቲካ ጸረ ዲሞክራሲ መሆኑን በተጨባጭ የመሰከሩት ፤ በኢሬቻ በዐል አከባበር ላይ ባደረጉት ንግግር የሰበሩንን ሰበርናቸው ሲሉ እኛና እነርሱ በሚል ጥላቻን መስበካቸው የሚያረጋግጠው የጎሣን ፖለቲካ አደገኝነት እንጂ የዘር ፌደራሊዝም ዲሞክራሲያዊ ሊሆን እንደሚችል እያሳዩን አይደለም።

 

ፕሮፌሰር መራራ ጉድና ቀሚሳችን በቁመታችን ልክ ይሁን የሚሉን በእነርሱ አባባል የብሔር ብሔረስቦችንና የሕዝቦች መብት እኩል ይከበር ሳይሆን ኦሮሞ በቁጥር ብልጫ ስላለው የአንበሳ ድርሻ የገባዋል ማለታቸው እንጂ ስለ ዲሞክራሲና ፍትህ እየተናገሩ አይደለም ።

 

አቶ በቀለ ገርባ አንድ ነጋዴ በንግድ ሥራ ላይ የሚሰማራው ምርቱን ሽጦ ያወጣውን ወጪ ከሸፍነ በኋላ ባገኘው ትርፍ ቤተሰቡንና ራሱን ያኖራል ። ነጋዴ ሸቀጡን ለመሸጥ ገዢ ያስፈልገዋል ስለሆነም የደንበኛ ፍላጎት ያጠናል ፣ የመግባቢያ ስልቶችን ያፈላልጋል ወዘተ ። እኚህ ጽንፈኛ ምሁር ግን የኦሮሞን ነጋዴ የጠቀሙ ይመስል ባሏን የጎዳች መስሏት ብልቷን በእንጨት ወጋች እንዲሉ በኦሮምኛ ካላወሩ ሸቀጡን እንዳትሸጡ ያሉት ግለሰብ ለዓለም ምሳሌ ይሆናል ያሉት የገዳ ዲሞክራሲ ካልሆነ በቀር በምንም መስፈርት ዘመናዊውን ዲሞክራሲ ሊሆን አይችልም ።

 

አቶ ሌንጮ ባቲ አሁን ሥልጣኑ በጃችን ገብቷል መቶ ዓመት መግዛት አለብን ሲሉ አንድ ጊዜ በአንድ ወቅት የተመረጠ መንግሥት በሚቀጥለው መርጫ ከተሸነፈ ሥልጣኑን እንደሚለቅ ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን የዘር ፖለቲካ ዲሞክራሲያዊ ሊሆን ስለማይችል ለመቶ ዓመት ለመግዛት የሚያስችል ቁመና መፍጠር እንዳለባቸው ሲያረጋግጡ በሌላ በኩል የጎሳ ፖለቲካ ዲሞክራሲያዊ መሆን እንደማይችል እየነገሩን ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የወያኔ ታጋዮችና የትግራይ ሕዝብ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ፖሊሲው በቀጥታም በተዘዋዋሪም የማይነጣጠሉ ትስስሮች አድርገዋል

 

ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ምንም እንኳን የውኃ ላይ ኩበት ቢሆኑም ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ የፖለቲካ ሞቅታ ሲይዛቸው ከሚናገሩት እንደምንረዳው ለአንድ ክልል ብለን ህገመንግሥት አንቀይርም ፤ በክልሎች ውስጥ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ለሚደርሱ ጥፋቶችና ወንጀሎች ትንሽ ሥጋ እንደ አጥንት ትወጋ እንዲሉ ለይቶ ደራሽነት ፤ ለሹመትና ለሽልማት የሚሰጡት ወገነተኚነትና ወዘተ የኦሮሞ ሊህቃን የማይቻለውን የጎጥ ፖለቲካ በተአምር ዲሞክራሲያዊ ሊያደርጉ ይቅርና ሁሉም ኦሮሞን እንወክላለን የሚሉት የሚስማሙበትን የኦሮሙማ አጀንዳ ለመተግበር አንድነት አጥተው እንደ አሜባ እየተባዙ እርስ በርሳቸው በመባላት ላይ ናቸው ።

የዘር ፖለቲካ በእኩልነት ምትክ ለይቶ ማጥቃትና ለይቶ መጥቀምን መርሁ ያደርጋል ምክንያቱም የተሰጠው የጎሳ ኃላፊነት በመሆኑ ለእኩልነት ፣ ለብሄራዊ አንድነት ፣ ለግለሰብ መብት እና ለክህሎት ቦታ አይሰጥም። ለዚህ ትክክለኛው ማረጋገጫ ካሁን በፊት ህወሓት መራሹ መንግሥት የጎሣ ፖለቲካን የሚያረጋግጥ ህገምንግሥት ቀርጾ በጎሣ ፌደራሊዝም ሕዝቡን ለያይቶ 27 ዓመት ሙሉ በበላይነት ለመግዛትና ቀሪውን ዜጋ ለመበዝበዝ በዘረጋው የጎሣ መዋቅር ከችሎታ ውጭ በደም ትስስርና በዝምድና የራሱን ሰዎች ወሳኝ በሆኑ የሥልጣን እርከኖችና የኢኮኖሚ አውታሮች ሰግስጎ ለምዝበራና ለህገወጥነት ዳርጎናል ። በዚህ ብቻ አላበቃም ለሃያ ሰባት ዓመት በጠላትነት ፈርጆ ሲቀሰቅስበት፣ ሲገልና ሲያስገድል በነበረው የአማራ ጎሳ ላይ የትግራይን ሕዝብ ልጅ አዋቂ ፣ ሴት ወንድ ሳይለይ አደራጅቶና አስታጥቆ በመውረር ወግን በወገኑ ላይ ሊያደርገው ይቅርና ባእድ ጠላት ያላደረገውና ሊያደርግ የማይችለውን ዘግናኝና ታሪክ የማይረሳውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል። ይህ የሚያሳየን የዘር ፖለቲካ አእምሮ ያለውን የሰውን ልጅ እንዴት ወደ አውሬንት እንደሚቀይር እንጂ ፍትህ ፣ እኩልነትና ዲሞክራሲን የሚያሰፍን አለመሆኑን ነው ።

በ1991 የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትን (ትህነግ) አጅቦ ለስልጣን የበቃው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አማራውን በማግለል ከትህነግ ጋር በማበር የዜጎችን መብት የማያውቅ፣ የማያስከብርና ሕዝብ ያልተሳተፈበትን „ህገመንግሥት“ በመቅረጽ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለዘመናት አብሮ የኖረውንና በደም የተቀላቀለውን አማራ ያለምንም ጥፋት በሀገሩ በህይወት የመኖር መብቱ ሳይቀር ተነፍጎ እንዲገደል አድርገውታል። እዚህ ላይ ትኩርት መስጠት የሚገባን በጎሣ በተከለለች ኢትዮጵያ ከክልሉ ብዙኃን የኦሮሞ ነዋሪ ውጭ የሚኖር የሌላ ጎሣ አባላት በተለይ አማራው ተለይቶ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል እየተፈጸመበት ይገኛል ።

የተለያዩ ምሁራን ከተለያዩ አገራት ልምድ በመነሳት ያካሄዱት የጥናትና ምርምር ውጤት እንደሚያስገነዝበው ህብረብሔራዊ በሆኑ አገራት በጎሳ መስፈርት የተደራጁ ድርጅቶችም ሆኑ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሁሉንም በእኩል ሊያገለግሉ እንደማይችሉ በመረጃና በማስረጃ ያረጋግጣሉ ። በጎሣ ተከፋፍላ በተከለለች አገራቺን የሚከተሉት የዜጊነት መብቶች አይከበሩም ፦

1 ህይወቱ እና ንብረቱ በሕግ የተጠበቀ ነው። 2 የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን መብቱ ነው።

  • ንብረትን በነፃነት ማፍራት መብቱ ነው። 4 ደህንነትና ሰላም በግዛቱ ማግኘት መብቱ ነው። 5 መመረጥ መብቱ ነው።

ማንኛውም የዘር ሐረግ መዞ በዝምድናና በደም ትስስር የተደራጀ የእኔ ነው ብሎ ከተሰባሰበው ጎሣ ውጭ አብሮት የሚኖረውን የሕብረተሰብ ክፍል እንደ ባእድና መጤ ተደርጎ ስለሚቆጥር በክልሉ ከላይ የተጠቀሱትን የዜጊነት መብቶችን ማግኘት አይችሉም ። ይባስ ብሎ ለሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽም ይሁን የተፈጥሮ ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ አድርገው ስለሚያዩ የማንኛውም ብሶት መወጫ ያደርጋሉ ድርጊታቸውም እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በህግ የሚጠይቃቸው መንግሥታዊ አካልም ስለለሌ የዘር ማጥፋትም ሆነ የዘር ማጽዳቱን ተግባር ያለ ከልካይ ይፈጽማሉ ። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነን በተለይ የዶክተር አብይ መንግሥት በትረሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ ጊዜ አንስቶ በራሳቸው የምርጫ ክልልና በሚወክሉት የጎሳ አባላት ከኦሮሞ ውጭ የሆነውን ዜጋ በተለይም አማራው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት እየተካሄደበት የኦሮሚያ መንግሥትም ሆነ የጸጥታ ኃይል ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለቱ የእኔ የሚለው አጥቂ ከሆነ እንደ እግር ኳስ ደጋፊ የሚፈነጥዝ ሌላው ካጠቃ ለገላጋይ እስኪታክት ያዙኝ ሊቀቁኝ ባይ ሲሆኑ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳት አቶ ሺመልስ አብዲሳን በተደጋጋሚ አይተናቸዋል ።

እኚህ ግለሰብ የተመረጡትና ተጠርነታቸውንም በህገ መንግሥቱ መሰረት ለኦሮሞ ሕዝብ ብቻ በመሆኑ በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ጎሳ አባላት ጊዴታቸውን እንዲወጡ ከመቆጣጠር በዘለለ መብታቸውን ማስከበር እንደ ሥራ ድርሻቸው አድርገው አያዩትም ። የሚያስጠይቃቸው የሕግ አግባብም ስለለሌ ማንኛውም የጋራም ሆነ የግለስብ ጉዳይ አይመለከተኝ የሚል እሳቤ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል። እንዲህ አይነቱ ኋላ ቀር አስተሳሰብ የተጠናወተው ግለሰብ ወይንም ቡድን የአመራር ቦታውን ከያዘ ለዘር ወይም ለዝምድና ትስስር ቅድሚያ መስጠቱን ተግባሩ ስለሚያደርግ በመቻቻልና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረት ሁለገብ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚያስቸግሩ እንቅፋቶችን ይፈጥራል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህሊና  እስረኞችን  ፍቱልን!!!! - ፊልጶስ

ጽንፈኛ የኦሮሞ ሊህቃን በሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ከስግብግብነታቸው ብዛት የተነሳ በጃቸው የገባውን ሥልጣን ተስማምተው በጥበብ ይዘውና መርተው አገር ማሳደግ ሲችሉ ከትህነግ ስህተት መማር ተስኗቸው የማስተዳደር ጥበብ የሆነውን ፖለቲክ ቁማር ነው ይላሉ። ያላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል እንዲሉ መቆመር ፣ ማደናገርና ማጭበርበር የቻለ ያሸንፋል እያሉ ይዘውን ወደ ገደል ቁልቁል በመውዘግዘግ ላይ ናቸው ። ፖለቲካ የማስተዳደር ጥበብ እንጂ ቁማር አይደለም (Politics is not gambling, it is the art of governing) ።

 

አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ፦

ዶክተር አብይ እንደ አገር መሪ ተቀዳሚ ተግባራቸው ህግና ስረአት ማስከበር መሆኑን ዘንግተው ወይንም አቅም አጥሯቸው አይደለም በሀገሪቱ ስርአተ አልበኝነት የሰፈነው ። ያቅም እጥረትማ ቢሆን ኖሮ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን አብዱ ኢሌን በቁጥጥር ስር ባላዋሉ ነበር ፤ ያቅም እጥረትማ ቢሆን ኖሮ የሰኔ 15ቱን የአማራ ክልል ኦፕሬሺን መርተው አርቆ አስተዋይ የሆኑ ንጹኃን ወገኖቻችንን ባል ፈጁ ነበር ፤ ያቅም እጥረትማ ቢሆን ኖሮ የሲዳማን ክልል ልሁን ህገመንግሥታዊ ጥያቄ ለማፈን የንጹኃን ደም በከንቱ ባልፈሰሰ ነበር ፤ ያቅም እጥረትማ ቢሆን ኖሮ ህጋዊ መብቱን የጠየቀውን የወላይታን ሕዝብ ለማስጨፍጨፍ የፌደራል ኃይልን ባላዘመቱ ነበር ፤ ያቅም እጥረትማ ቢሆን ኖሮ ትህነግ የሴምን እዝን መብረቃዊ ባለው ድንገትኛ ጥቃት አውድሞ መንበረ ሥልጣናቸውን ሲነቀንቅ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ወራሪ አሸንፎ በአጭር ጊዜ መቀሌን ባልተቆጣጠሩ ነበር ። ስለዚህ በሌላ ክልል ውስጥ ገብተው የፈለጉትን የማድረግ በቂ አቅም አላቸው ።

ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴሩ እንደሚሉን የማስታወስ ችሎታችን አጭር ካልሆነ በቀር ባንድ ወቅት ወደ ወለጋ ያልሄዱበትን መክንያት ሲናገሩ ኦሮሞ ኦሮሞን ገደለው እንዲባል ስለማልፈልግ ነው ብለውን ነበር ልብ በሉ የእርሳቸው ጭንቀት ህይወታቸውን ማጣታቸው ሳይሆን ኦሮሞ ኦሮሞን ገደለው መባሉ ነው ። ስለሆነም ነው ከነትጥቁ እንዲገባ የፈቀዱለት ኦነግ በክልሉ ውስጥ አማራን ለይቶ በየቀኑ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ዘመቻ እያካሄደ ህጋዊ እርምጃ ሊወስዱ ይቅርና መግለጫ ስጥተው የማያቁት ኦሮሞ ኦሮሞን ማስቀየም ነውር በመሆኑ እንጂ የአቅም እጥረት አይደለም ።

በኦሮሚያ ክልል ሰው ተዘቅዝቆ ተገድሎ ፣ ሀብት ንብረት ወድሞ አንድም ሰው ተፈርዶበት ኣልሰማንም ። ክቡር ጠቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ በትረ ሥልጣኑን ከጨበጡ በኋላ እርሳቸውን ለጠቅላይ ሚንስቴርነት ካበቃቸው ክልል ብቻ 20 ባንኮች ተዘርፈው እስካሁን የተጠየቀ የለም ፤ አሁንም እዚሁ ክልል ወጣት የደንቢዶሎ ዩኒቬርስቲ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ታፍነው ተወስደው መንግሥት ማስለቀቅ ባይችል ትክክለኛ መረጃ እንኳን ሳይሰጥ ሶስት ዓመት ሊሆን ነው ፤ ራሳቸው ጠቅላይ ሚንስቴሩ የሚመሩት የኦህደድ ፓርቲ ከሌሎች የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር ሆነው ስለ አዲስ አበባ ባለቤትነት የሰጡትን መግለጫ ሰምተው ጭጭ ያሉት ዝምታ መስማማት ነው ብለው ነው ፣ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ክልል ምክትል ፕሬዚድንት በነበሩበት ወቅት በኦሮምኛ ቋንቋ የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ለማስተካከል እየሰሩ መሆናቸውን መናገራቸውንና አሁንም ውስጥ ውስጡን እየተሰራ መሆኑ ከጠቅላይ ሚንስቴሩ የተሰወረ አይደለም ፣ ገሀድ የወጣው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳት የአቶ ሺመልስ አብዲሳ ሚስጥራዊ ንግግር ቪዲዮ ውስጥ ብልጽግና ለምን አላማ እንደተመሰረት ያወጡት ሚስጥር ጠቅልይ ሚንስቴሩን አልጎረበጣቸውም ፤ በገሀድ የምናየው የመሬት ወረራና የኮንድምኒዬም ቤቶች ዘረፋ ምንም ያልመሰለው መንግሥት በተቃራኒው የወንጀል ድርጊቱን የሚቃወሙና የሚያጋልጡትን የባልድራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላትን ለማሰር የፈጠኑት ውጥናቸው እንዳይደናቀፍ ነው ፣ አሁን ጠቅላይ ሚንስቴሩ ያካሄዱት መስፈርት አልባ ሹመት ፣ ሽልማትና ሌሎችን መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ብንመረምር የዶክተር አብይ ይሁንታና ተሳትፎ ሳይኖር የሚፈጸም አንዳችም ነገር አለመኖሩን የሚያረጋግጥ ነው ።

ግን ከዚህ ምን ያተርፋሉ ነው ጥያቄው መልሱ ተተንብዮላቸው በጾምና በጸሎት ማምሻም ዕድሜ ነው እንድሉ በስልጣን ለመሰንበት ካልሆነ ኦሮሙማን ወይንም ሌላውን በማጥፋት የኦሮሞ ቢቻ የሆነች ኢትዮጵያ መፍጠር አይችሉም የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎትም አይደለም ።

ጠቅላይ ሚንስቴሩ ስልጣን እንደጨበጡ ትልቅ ወንጀል በእርሳቸው ላይ ተደረገ የተባለው የግዲያ ሙከራ እውነት ይሁን ድራማ ከምን ደረሰ ? ታጥቀው እስከ ቤተመንግሥት ድረስ መጥተው በፑሻፕ የተሽኙ የሰራዊቱ አባላት በወንጀል ባይጠየቁ የዲስፕሊን እርምጃ ተወስዶ መች ለሕዝብ ይፋ ሆነ ፣ የኢንጂኔር ስመኜው ግዲያ ፣ የአማራ ክልል ባለሥልጣናትና የመከላከያ ሚንስቴር ሞት ፈቺ ያልተገኘላቸው ህልሞች ሆነው ያለ ተጠያቂ የሚቀሩ ወንጀሎች ለምን ሆኑ ?

ካሁን በፊት በኦሮሚያ ክልል የዘርና የሀይማኖት ተኮር ጌኖሳይድ ተካህዶ ሌላው ቢቀር እንደሰው ሀዘን ተሰምቷቸው በሚዲያ ወጥተው መግለጫ ሳይሰጡ ለሥልጣኔ አስጊ ነው ከሚል በመነሳት የተካሄደው ዘርና እምነት ተኮር ጭፍጨፋ ጌኖሳይድ እንዳይባል በሚል በሚዲያ ብቅ ብለው በእጥፍ የሞተው ኦሮሞ ነው ሲሉ እንደተለመደው ለሙታን ዘር ያከፋፍላሉ ይህ ደግሞ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ ሀጅ ከመሆን አያድናቸውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮሮና "ኩሩና" እና "ይህም ያልፋል" - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

አንድ መንግሥት ዲሞክራሲያዊ በሆነ ምርጭ ወይንም ከምርጫ ውጭ ስልጣንና የታጠቀ ኃይል ያለው የአንድ አገርን ሕዝብ የሚያስተዳድር ወይንም የሚገዛ ቡድን ሲሆን ተግባሩን ለማከናወን ይረዳ ዘንድ ህገመንግሥትና ሀግ ይኖረዋል ። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 8 ተራ ቁጥር 1 የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሊዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ይላል ። በአንቀጽ 9 በተራ ቁትር 2 ላይ ደግሞ ማንኛውም ዜጋ ፣ የመንግሥት አካላት ፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ሕገመንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው ይላል ፣

አማራ በሕገ መንግሥቱ በአእንቀጽ 8 ቁጥር 1 መሰረት እንደ ብሔር ፣ ብሔረሰብ ወይንም ሕዝብ ተቆጥሮ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅም ሆነ በማጽደቅ ተግባር አልተሳተፈም ። በአንቀጽ 9 ቁጥር 2 መሰረት እንደ ዜጋ ሕገ መንግስቱን የማስክበርና ለሕገመንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው ይላል ። በዚህ ሕገ መንግሥት መሰረት አማራው የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት አይደለም ነገር ግን እንደ ዜጋ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ለሕገ ምንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለበት ። በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ መሰረት አማራ በሰው ክልል ወስጥ ይቅርና ተሰፍሮና ተመጥኖ በተሰጠው ክልሉ ውስጥ እንኳን ግዴታን መፈጸም እንጂ የመብት ጥያቄ ማንሳት አይችልም ። ስለሆነም ነው መንግሥት ከነትጥቁ ፈቅዶ ባስገባቸውና አሰልጥኖ ባሰማራቸው የኦነግ ሽብርተኞች አማራው የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ዘመቻ ያለ ከልካይ ያሚፈጸምበት ።

በአንድ ወቅት ጥቅላይ ሚንስቴር ዶክተር አብይ ሕገ መንግሥቱ ለአንድ ክልል ተብሎ አይቀየርም ካሉ በኋላ የአማራ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው በአንድ በስብሰባ ላይ ይቀየራል እንጂ ለምንድነው የማይቀየረው ብለው ቁርጥ ያለ አቋማቸውን በመግለጻቸው ለህልፈት ተዳርገዋል ። ጀነራል አሳምነው ጽጌ አማራው ላይ አሁን እየተፈጸመ ያለውን እልቂት ቀድመው በመገንዘብ ዙሪያህን ተከበሀል ራስህን ለመከላከል አንድ ሁን ተደራጅ ብለው ልዩ ኃይል ማሰልጠን ሲጀምሩ ምርጥ የሆኑ ጀግኖችን በሴራ እርስ በርስ የተገዳደሉ በማስመሰል ርቆ ሀጅ እቅዳቸውን በአጭር ቀጩት የአማራን ሕዝብም ለእልቂት ዳረጉት።

አሁን በቅርቡ ደግሞ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን ሲሉን የነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳዉ የደቡብ ክልል ፕሬዘዳንት የጉራጌ ዞንን ክልል የመሆን ፍላጎት “….ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረን ውይይት ስንጠይቅ

እንኳን ክልል 83 ብሄሮችም ሃገር የመሆን (የመገንጠል) መብት አላቸው ብለዉናል…።” ነው ያሉት ታዲያ ይህ አባባላቸው አሁን መሬት ላይ እየተገበሩት ካለው በምን ተለይቶ ነው በአንክሮ የምናየው ? ሀገሪቱን 83 ሶስት ቦታ ቆራርጦ ሊያጠፋት ሌት ተቀን እየሰራ ያለውን ጠቅላይ ሚንስቴር ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ይሰዋል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ነው ። በኦሮሞ ሕዝብ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችም ሆኑ ጽንፈኛ ምሁራን መንግሥትን ጨምሮ ትህነግ አከርካሪውን ሰበርነው ያሉት አማራም ሆነ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጊዜ ለሰጠው ቅል ተሰባሪ ሳይሆን ሰባሪ መሆኑን በተግባር አሳይቷቸዋል

  • ከመምህራቸው ትህነግ ውድቀት የማይማሩት  በስም እንጂ ልዩነት የሌላቸው ኦነግ ፣ ኦህደድና የኦሮሞ ብልጽግና

82ቱንም ጎሳዎች በመዋጥና በመሰልቀጥ ኦሮሙማን ለመመስረት እንቅፋት ይሆኑብኛል ያላቸውን ሶስቱን የአማራ ፣ የአፋርና ተጋሩዎችን አቅመ ቢስ እስከሚሆኑ ድረስ የዶክተር አብይ መንግሥት ቆሞ በተመልካችነት እያጨራረሰን ይገኛል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጎሳም ሆነ ግለሰብ ነግ በእኔ ብሎ ከአማራና አፋር ወገኖቹ ጋራ ለሀገር ሏላዊነትና ለሕዝባችን አንድነት በጋራ መቆም ይኖርበታል እምነቱም ሆነ ኢትዮጵያ የአማራና የአፋር ብቻ አይደሉምና ። በተለይ የኢትዮጵያን መበታተን የማይፈልግ አገር ወዳድ የኦሮሞ ተወላጅ ጽንፈኞችን ለመታገል ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል ይህንን የምለው መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠሩት ኦሮሞን እንወክላለን የሚሉ ቡድኖች በመሆናቸው እንጂ የማንንም ጎሳ ጽንፈኛ ዘንግቼና የተሻለ ነው በማለት አይደለም የጽንፈኛ ደግ የለውም ። ጽንፈኝነት የበታችኝነት ወይንም የበላይ ነኝ ባይነት ስሜት ነው (Feelings of inferiority or superiority) ስለሆነም የእኔ አይደለም የሚለውን ሁሉ መጥፋት አለበት ብሎ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይፈጽማል ያስፈጽማል በኦሮሚያ ክልል የምናየው ይህንኑ ነውና በአንድነት ማስቆም አለብን ።

 

ፈጣሪ ሀገራችንና ሕዝባችንን ከጥፋት የመታደግ ኃይልና ጥበቡን ይስጠን መልካም ንባብ ገንቢ ሂስ ለመቀበል ዝግጁ ንኝ

ከንገሤ አሊ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share