የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን
ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን
ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ
ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ
ምግቧንም ተጋርቶ
ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ
ማን ይኖራል ከቶ?
በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት
ልሳኑ እንደ ቀዳሽ የተሞረደለት
አእምሮዉ ተነክቶ ለካስ ልቡም ታሟል ቂም የቋጠረበት።
እንደሙሴ ባህር ላሻግራችሁ ብሎ
ከጭንቅ ሊያወጣን ተገዝቶ ምሎ
አስበላን ባሞራ ቀብር አስከልክሎ።
ጸልዩልኝ ብሎ እኛን እናቶችን
እድሜ ስንለምን ጌታ ፈጣሪያችን
ሆዳችንን ቀዶ ጣለ ልጆቻችን።
እያየ እንዳላየ አይኑ ተከልሎ
ጆሮውም ደንቁሮ
ሰው እንደበግ ታርዶ ተበላ ዘንድሮ።
ሩህሩህ መሪ ነው ጥላ እንዲሆን ብሎ አስተከለ ዛፍ
ነፍስ እንድትደሰት እሬሳም እንዲያርፍ።
ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ
ብለህ አልነበረ
ያ ሁሉ ቃል ኪዳን ወዴት ተቀበረ።
ምሁሩ ደንዝዞ ነብይ ሙሴ ብሎህ
ፈላስፋው ታዉሮ በጭፍን ሲያመልክህ
ወጣቱ ተሳክሮ ከንፎ ሲከተልህ
ቀሳዉስት በጸሎት ጌታን ለመኑልህ።
ነፃ ወጣን ብሎ ሁሉም ዘር በሞላ እልልታ አስተጋባ
ይሉኝታ፤ ምንይሉኝ፤ ያገራችን ባህል እሴቱ የት ገባ?
ህዝብ እየተራበ ጎዳና አብለጭልጮ ሕንጻ እሚያስገነባ።
ቤትን አፈራርሶ ቤተሰብ በትኖ ጅብ ህጻንን በልቶ
የጎረቤት ጬኸት የናት ለቅሶን ሰምቶ
ለሱ ልጆች ሰላም ዘበኞቹን ጠርቶ
ምን አይነት ጨካኝ ነው የሚያድረው ተኝቶ።
ህዝብ እየለመነ ጎዳና ላይ ወጥቶ
በራብ ተቆራምቶ
ምን አይነት መሪ ነው?
ቤተመንግሥት ሰርቶ የሚሽሞነሞነው ።
በምንሽር ነበር ወይም ባውቶማቲክ የጀግና ሰው ሞቱ
እንደ ጣሊያኖቹ እንዴት ባይሮፕላን
በቱርክ ሰራሽ ድሮን
በገዛ ሀገሩ በገዛ ወገኑ ይቃጠላል ቤቱ
ገላዉ ከሰል ሆኖ ይነዳል ንብረቱ።
\የድሮ መሪዎች ጠብቀውን ነበር ከሱዳን ከጣሊያን
መከላከያችን ኩራት ነበር ለውጭ እንኳን ላገራችን
ምነው ተገልብጦ አረደው ህዝባችን።
ትምህርት ቤት ተከብረዉ
ቤተምነት ተፈርተው
በኖሩበት ሀገር
በመድፍ በድሮን ያቃጥለው ጀመር።
ጀግና ጀግናን ገጥሞ ሲያሸንፍ ሲሸነፍ ነበር የምናዉቀዉ
እናቶችን መግደል ክምርን ማቃጠል ከወዴት አመጣዉ
ህጻናትን መድፈር ቄሶችን መሰዋት ያረመኔ ጨካኝ የፈሪ ሥራ ነዉ።
እየነደደ እሳት ባራቱ ማእዘን
አገራችን ጭሳ ነዳ ሳትበተን
ፋኖ አንድነት ፍጠር
መሪህንም መርጠህ ትግልህን አጠንክር።
ከትግራይ ኦሮሞ እዲሁም ከሐረር
ወላይታው ጉራጌው ሌላም ሌላም ብሔር
ተባብረን እንኑር በሰላም በፍቅር።
ሁሉም ዘር ወርቅ ነው እኔ ዘር አልመርጥም
አንዱን ዘር ከሌላው አላበላልጥም።
እንደ ዱር አበባ ልዩነትም ዉብ ነው
ለሁሉ እሚበቃ ሀገሩም ሰፊ ነው
አብሮ መኖር እንጅ የተከለከለዉ።
መርጦ አልተወለደ ልሁን ብሎ አማራ
ኦሮሞ ጉራጌ ዶርዜ ወይ ጊሚራ
ጎንደር ልሁን ብሎ ወይ ሀረርን መርጦ
ወለጋን ከወሎ ከትግራይ አብልጦ
ሰው አልተወለደ በገዛ ፈቃዱ ከግዜር ቃል አምልጦ።
እግዜር በፈቀደዉ በተወለደበት
ሰው በሰውነቱ መከበር አለበት።