`ዔርታ~ዓሌ`፡~በእንተ፡ነገረ፥`ድንቂቱ (ከ፡~ጃህእርሥዎ፡ሞትባይኖር፡ኪሩብ፡ዔል)

መስከረም፥፪፡ሺህ፡፲፬
ሎንዶን

 ከሰምና ወርቅ

ክፍል ፩

`ኣዲስ~አበባ`፡ከተማን፡ለቅቄ፡የወጣሁት፥የ፡`ቀይ~ሽብሩ`፡እሳት፡እየተንቦገቦገ፤ ንፁሃን፡ እና፡ፍትሕ፡ ፈላጊዎች፤ በእየ፡ ስፍራው፥ ከአለ፡ ፍርድ፡ በሚፈጁበት፣ አስከፊ፥የምድር፡ ሲዖል፡ወቅት፡ ነበር።  ወደ፡ ኋላዬ፡ ዘወር፡ ብዬ፡ የአለፈውን፣ ጥዬው፡ የወጣሁትን፡ ገሃነም፤ ለመገላመጥ፡ እንኳን፡ የሚያስችል፥የሰከነ፡ልቡና፡ አልነበረኝም።  የዘመናት፡ሥቃይዋን፡ ምድር፥ ጦርነት፣ ረኅብ፡ እና፡ሽብር፥ የምድራዊ፡ ገሃነም፡ መኻነ፡ መቃብር፡ አድርገዋታል።

ደጉ፡ሰው፡~`ኣባ~ሀገሩ`፡ናቸው፡~`እዚህ፥ኣይናችን፡እየ፡ አየ፥ እንደ፡ ጓደኞችህ፡ ከምትታረድ፥ነፍሥህን፡ እንደ፡ምንም፡ ብለህ፡ ለማትረፍ፡ ሞክር~ከቀናህ፥`ኣሎ`፥ወደ፡`ጅቡቲ`፡ጠረፍ ሊያደርስህ፤ ኮንትሮባንድ፡ ነጋዴዎች፡ጋር፡ ሊያገናኝህ፡ ይችላል።  እንደ፡ምንም፡ብለህ፡ብቻ፥`ኣይሻኢታ`፡ መንደር፡ለመግባት፡ሞክር`፡ ብሎ፥ በደፈናው፡ መራኝ።  በጭፍን፡፥ የዕውር፣ የድንብሬን፡ ከለገሃር፡ሰፈር፥` ሊዎንቺና`፡  ተሳፍሬ፤ሌሊቱን፡` ኣዋሽ`፡ ገብቼ፥ ከአንዲት፡ ትንሽ፡` ኣልቤርጎ`፡ ክፍል፡ ተከራይቼ፡ አደርኩኝ።

ጉዞዬ፡ሁሉ፥ጭለማ፡ለጭለማ፣በጭለማ፡ነበር። `ኣይሻኢታ`፡ከተባለችው፡መንደር፥ማን፡እንደሚጠብቀኝ፡አላውቅም። በስማ በለው፡እንዲሁ፡ብቻ፥`ኣባ፡ሀገሩ`፡የላኩኝ፡መንገደኛ፡ነኝ`፡ብዬ፥`ኣሎ፡የተባለውን፡ሰው፡ማፈላልግ፥ነፍስ፡አድን፡ሃሳብ፡መስሎኝ፤እሱውኑ፥ሙጥኝ፡ብዬ፡እያብላላሁ፥ከዓኖቼ፡ዕንቅልፍ፡የሚባል፡ሳይዞር፡ነጋልኝ።

ጥዱፍ፡ተሳፋሪው፣ችኩል፡መንገደኛው፣ወካባ፡ነጋዴው፣አላማ፡የለሽ፡ተጓዡ፣ወደ፡መሀል፡ሀገር፡የሚፈልሰው፣ከመሃል፡ሀገር፡የሚሸሸው፥ኢትዮጵያ፥የተነጎረ፡ምድር፡ሆናለች። ሁሉም፡ሰው፣ሁሉን፡ሰው፥በጥርጣሬ፡ዓይን፡ነው፡የሚመለከተው።

ተደልዞ፣ተሰርዞ፥በጉቦ፡የወጣልኝን፥የቀበሌ፡መታወቅያ፡ጨምድጄ፡ይዣለሁ። ጸጉሬን፡ተላጭቼ፣ቆዳ፡ሰንደል፡ጫማ፡ማጥለቄ፥የገጠሬ፡መሳይ፡ገጽታ፡ሰጥቶኛል። በእዚህም፡ላይ፥በከተማው፡ጦርነት፡ዓመታት፥የጠላትን፡ዓይን፤በዘዴ፡መሸሽን፡አስተምሮኛል።

ወደ፡`ዱብቲ`፡እና፡`ኣሻኢታ`፡የሚዘልቅ፡`ሊዎንቺና`፥ጠዋት፤የሚቆምበትን፡መሃጣ፡ስፍራ፥የ፡`ኣልቤርጎው`፡ሰራተኛ፡የሆነች፡ሴት፡ጠቆመችኝ። ሳላመነታ፣ሳልዘገይ፤ቀድሜ፡ሄጄ፡ስጠብቅ፤መንገደኞችን፡ሞልቶ፥በሰዓቱ፡ገጭ፡አለ።

`ኣብዮት~ጥበቃ`፡የታጠቁ፤ባለ፡ዋንዴዎች፤በእየ፡መንገዱ፥ላይ፡ታች፡ይላሉ። አንዱ፡የተጠራጠረ፡ጠባቂ፥አስቁሞ፡ሊፈትሽህ፣ከአልመሰለውም፡ሊያስርህ፣ከጨከነም፡ሊፈጽምህ፥የወታደሮቹ፡መንግሥት፥የዕብድ፡ፈቃድ፡ሰጥቶታል። ከተረፍክ፡ዕድለኛ፡ነህ፣ካልቀናህም፥`ኦሮማይ`*

ግራ፡ቀኙ፤አሽዋ፡እና፡በረኃ፡ሰንጥቀን፥`ኣይሻኢታ`፡መንደር፡ደርሰን፥በዘላኖች፡ከታመቀው፤የገበያተኞች፡መናኸርያ፡ሜዳ፡ስንራገፍ፤ወደ፡ቀትር፡ግድም፡ነበር። ደግነቱ፥የዘላኖቹ፡ትድረት፥ሁሉም፡ ሁሉን፡የሚያውቅበት፡ዕድር፡በመሆኑ፤የ፡`ኣሎን`፡ሥም፡ጠቅሼ፡መኖርያ፡ቤቱን፡ሳጠያይቅ፤የሚጠቁመኝ፡ሰው፡ለማግኘት፡ብዙ፡አልፈጀብኝም።

ከዘላኖቹ፡ማረፍያ፥ጭቃ፡ምርግ፡ቅጥር፡ስደርስ፥ሁለት፡የአገለደሙ፡ወጣቶች፤በጥርጣሬ፡ዓይን፡ቃኙኝ። ከመሃል፡ሀገር፡የመጣሁ፤የ፡`ኣሎ`፡እንግዳ፡እንደሆንኩኝ፡ሳስረዳ፥በገራም፡ዓይን፡ተመልክተው፥ወደ፡ግቢው፡እመቤት፡ዘንድ፡ወሰዱኝ።ከሁኔታቸው፥እንደ፡መሰለኝ፥ከኣዲስ፡ኣበባ፥ጠቃሚ፡ነገር፡ይዞ፡የመጣ፡መልዕክተኛ፡ሳይሆን፡አይቀርም፡ብለው፡ገምተው፡ነበር።

ከገበያ፡ውላ፡የተመለሰችው፥የቀዔው፡እመቤት፥በሦሥት፡ዘላኖች፡የተከበበች፤በአክብሮት፡እና፡መሽቆጥቆጥ፡የምትደመጥ፥`ኹልሱማ`፡የተሰኘች፤ደርባባ፤የዘላን፡ሴት፡ወይዘሮ፡ሆና፡አገኘኋት።

ገና፡ስታየኝ፤የርኅራኄ፡መንፈስ፡እንደ፡አደረባት፡እና፥ከ፡ከተማው፡ጦርነት፡ተዋክቤ፡የመጣሁ፤ኣሳዛኝ፡ፍጡር፡መሆኔን፥በዕንስታይ፡ነፍስዋ፡የተገነዘበችኝ፡ሆኖ፡ተሰማኝ። ጥያቄም፣ምርመራም፡ሳትለኝ፡~” ለመሆኑ፥ለእንግዳው፡የሚጎርሰውን፡ነገር፡አቀረባችሁለት!?”ስትል፥የቤት፡ረድ፡ሳዱሌ፣ባለንቅሳት፡ወሎዬ፡መሳይ፡ልጃገረድ፤ተፍ፡ብላ፤ወደ፡ጓዳው፡ገብታ፥በድልህ፡እና፡ቅቤ፡የተለወሰ፥የማሽላ፡እንጀራ፤በትሬ፡እና፤የግመል፡ወተት፡በጣሳ፡አምጥታ፡ሰጠችኝ። ለምን፡እንደሆነ፡እኔ፡እንጃ፥ነፍሴ፡እንደምትተርፍ፥በእዚህ፡ሰዓት፡ነው፡የታወቀኝ።

የበረሃ፡ግዜው፡ፍጥነት፡ሳይታወቀኝ፥ውጭው፡እንደ፡መጨላለም፡ብሏል።

(ክፍል~)

ድልህ፡በቅቤ፡የተለወሰውን፥የ፡ማሽላ፡እንጀራ፥ረኃብ፡እና፡እንግልት፡በበገበገው፡ሆዴ፥ጥስቅ፡አድርጌ፡በላሁት። የ፡ግመል፡ወተቱ፡ግን፥ገና፡ስቀምሰው፥በልጅነቴ፤ሞግዚታችን፡እትዬ፡`የሺ`፤የአጠጣችኝን፥ `እንገር`፡ወተት፡ቃና፡ስለ፡አስታወሰኝ፥የምንተ፡ሃፍረቴን፤ትንሽ፡አጉድዬለት፥ጣሳውን፡ከ፡ጎኔ፡አኖርኩት።

የ፡ባለ፡አደራዬ፥የ፡`ኣሎ`፡እህት፡እንደሆነች፡የነገረችኝ፥`ኹሉሱማ`፥ሠሌን፡ከደጅ፡ላይ፡እንዲነጠፍልኝ፥በደንከል፡ቋንቋ፡ትዕዛዝ፡ሰጥታ፤ወደ፡ጓዳው፡ገባች። ስጋት፣ሽብር፣ሰቀቀን፡ እና፡ፍርሃት፡የአጋሉት፡ኣኻላቴ፥እስከ፡አሁን፥የበረሃውን፡ወበቅ፡እና፡ቃጠሎ፡አልሰማ፡ኖሮ፥የቤቱን፡ጥላ፡አግኝቼ፥ትንሽ፡ጋብ፡ቢልልኝ፥ከውስጥ፣ከውጭ፤ይለብቀኝ፡ጀመር። አሰብ፡ባደርገው፥ለካስ፥ከ፡ሁለት፡ሺህ፡ጫማ፡ከፍታ፣ከ፡ደጋማዋ፡ኣዲስ~አበባ፥በጥቂት፡ሰዓት፡ጉዞ፡ወርጄ፥የባሕር፡ወለል፡ዝቅታ፡ውስጥ፡ነው፥እመር፡ብዬ፡የገባሁት።የበረሃው፡ሙቀት፥ የእራሱ፡የሆነ፥የኣርምሞ፡እና፡የ፡ማጉተምተም፡ንግግር፤የ፡አለው፡ይመስላል።የፊት፡ገጽን፡የሚጠፋ፡ሙቀት፡ይኖራል፡ብዬ፡ገምቼም፡አላውቅም።

ወደ፥`ኹልሡማ`፡ቅጥር፡የመሩኝ፥ሁለቱ፡ጎረምሶች፥ቀረብ፡ብለው፡ሊያነጋግሩኝ፡ቢሞክሩ፥ግራ፡የተጋብ፣ድንጉጥ፡ፍጡር፡በመምሰል፥በማይገባ፡ኣምኅርኛ፡ስንተባተብ፡ቢሰሙ፥እግር፡እራሴን፥ በኅዘኔታ፡ዓይን፡ተመልክተው፥እርቀውኝ፡ሄዱ።

ቅጥሩ፥ብዙ፡ዘላኖች፥ወጣ፡ገባ፡እየ፡አሉ፥የሚስተናገዱበት፣የሚያርፉበት፡ስፍራ፡በመሆኑ፥የኬሻ፡እና፡የጠፈር፡አልጋዎች፥በእየ፡ጥጋቱ፡ተዘርገተው፡ይታያሉ።`ማን፣ምን፡ይጠይቀኝ፡ይሆን!?፥ምን፡ ብዬስ፡ነው፡የማስረዳው!?~የ፡`ኣሎ`፡ወዳጅ፥`ኣባ፡ሀገሩ`፡ነው፡የላከኝ፤ከሚል፥እንጥልጥል፣ስንኩል፡ነገር፡ሌላ፤የያዝኩት፡አንዳች፡ተዓማኒ፡ታሪክ፡የለኝም።

`ኹሉሱማ`፥የ፡ቀዔው፡አስተዳዳሪ፡እመቤት፡እንደሆነች፡በቶሎ፡ተረድቼ፡አለሁ።የርኅራኄ፡አስተያትዋም፥የሚያጽናና፡ሆኖኛል። ገላዋን፡ተጣጥባ፥ሥሥ፡ሽብርቅ፡ቀለም፡መሃሙዲ፡አገልድማ፤በውሃ፡እንደ፡ራሰች፡ብቅ፡ስትል፥በ፡ሀገር፡ጎብኝዎች፡መጽሔት፡ላይ፡የሚወጡትን፥ሳያቸው፡የኖርኩትን፥ውብ፡የ፡ኣዳል፡ሴቶች፡ግርማ፡እና፡ጸዳል፡ተላብሳለች። አረማመድዋ፡ሳይቀር፥የዋላ፣የሣላ፡ኹራት፡ነበረው።

በ፡እስከ፡ዛሬው፡ጥቂቱ፡ዕድሜዬ፥ከ፡ቤት፡ውጭ፡የ፡አደርኩት፥ከ፡ትምህርት፡ቤት፡የ፡`ስካወት`፡ክበብ፡ጋር፥ለሣምንት፡`ሠበታ`ን፡ለመጎብኘት፡የሄድን፡ግዜ፡ብቻ፡ነው።እሱም፥ከ፡ብርዱ፡ትውስታ፡በስተቀር፥የተወልኝ፡ነገር፡አልነበረም። ይሄ፡ግን፡የተለየ፡ምኅዋር፡ነው። በኅራ፡ሠማዩ፡የተዘሩት፥ኅልቁ፡መሳፍርት፡ከዋክብት፥የምድርን፡ፀንፍ፡የለሽነት፡ይናገራሉ። ከተነጠፈልኝ፡ሠሌን፡ላይ፥በቀስታ፡ጎኔን፡ሳሳርፍ፥ልዩ፡ዕረፍት፡ተሰማኝ። ከ፡አሁን፡አሁን፤የኣብዮት ፡ጥበቃ፡ሰዎች፡መጥተው፡ይፈትሹኝ፡ይሆን*፣`ካድሬዎች`፥ድንገት፡ከተፍ፡ብለው፤በጥያቄ፡ቢያፋጥጡኝስ!?~ ከዘላኑ፡ነዋሪ፥በጉልህ፡ተለይቼ፡የምታይ፡ፍጡር፡ነኝ፣የከተማ፡ልጅ፡ለመሆኔም፥ ግንባሬም፣ውኃዬ፡ይነግራል!`~ይሄንን፡ሁሉ፡ሳብሰለስል፥`ኹሉሡማ`፡የሚሪንዳ፡ጠርሙስ፡አምጥታ፤እተኛሁት፡ቁልቁል፡ስታቀብለኝ፤አፈፍ፡ብዬ፡በመነሳት፤እጅ፡ነስቼ፡ተቀበልኳት። ቀምሼ፡የተውኩት፥የግመሉ፡ወተት፡እንዳልተስማማኝ፡አውቃልኝ፡አለች፡ማለት፡ነው።

“`ኣሎ`ስ~በትንሽ፡ቀን፡መቆየት፡ይመስለኛል~አንተውስ፡አትፍሩ፥በእዚህ፡ቤት፡መቆየት፡ነው~እሺ?”፡ስትል፤በወሎዬ፡ኣምኅርኛ፡ቃና፡ለዛ፡ብሥራት፡ስታሰማኝ፥የምመልሰው፡ተስኖኝ፤ እጅ፡ነስቼ፡እንደ፡ተገተርኩኝ፥በወተት፡የኖረውን፡በረዶ፡ጥርስዋን፡ፈልቀቅ፡አድርጋ፡~

” አንተውስ፥የግመል፡ወተት፥አታቁም ?”፡ብላኝ፥ለቅጥሩ፡ሰዎች፥ውጭ፡ላይ፡የተሰጣውን፡ድርቆሽ፡እህል፡ነገር፤ወደ፡ቤት፡እንዲያስገቡ፥በኣፋርኛ፡ትዕዛዝ፡እየሰጠች፡ሄደች። የዕድሌን፡ዕውንነት፡ ለማረጋገጥ፥የገጠመኝን፡እያብሰለሰልኩኝ፥የሠማዩን፡ከዋኽብት፡ስቆጥር፣ገና፡ትላንት፥ከ፡ኣዲስ፡አበባ፡ትቼው፡የመጣሁትን፥የጦርነት፡የሽብር፡መከራ፡ሳንገዋልል፥የበረሃው፡ጸጥታ፣ቁጢት፡ደመና፡የማይታይበት፤የሠማዩ፡ዝምታ፣የሰዉ፡እርጋታ፡እኔንም፤ወድያው፡አሰከነኝ።

ከቅጥሩ፡ጥጋት፥በ፡እየ፡ኣልጋቸው፡ላይ፡እንደ፡ተጋደሙ፥ማዶ፡ለ፡ማዶ፡እየተጯጯሁ፡የሚነጋገሩት፡ዘላኖች፥ድምጻቸው፡እየቀነሰ፡ሄደ። እኔንም፡እንደ፡ማንጎላጀት፡ሲያደርገኝ፥ቅድም፡የጎረስኩትን፡ የ፡ማሽላ፡እንጀራ፡የ፡አቀበለችኝ፤ትንስዬ፥ሣዱሌዋ፡ልጅ፥ሳላስተውላት፡መጥታ፤እግርጌዬ፡ቆማ፤የውስጥ፡እግሬን፤በዓውራ፡ጣቶችዋ፡ደንቁላ፥እየሳቀች፥ፉዲዲ፡ብላ፡ሮጠች። በእናት፡ዓይንዋ፤ ከእርቀት፡የነፀረቻት፡`ኹሉሡማ`፡~” አንቺ፡ቀበጥ፥እንግዳው፡ይተኛበት፡ተይው*~አንቺም፥ወደ፡ቤት፡አትገቢም?~አልመሸም?”~የሚል፡ቁጣ፡እንደተናገረቻት፡በደመ~ነፍስ፡ተርጉሜ፡ተረዳሁ። `ሣዱሌ`ም፤ከ፡እዝያ፡ በኋላ፡አልተመለሰችም።

(ክፍል~)

የደጅ፡ንጋት፡ብርኅን፤ዓይነ፡ቆቤን፡ዳሥሦ፤ከዕንቅልፌ፡ሲቀሰቅሰኝ፥በሕይወቴ፤የመጀመርያ፡ግዜዬ፡ነበር። ሰዓቱ፥በቤቱ፡ጥላ፡ልኪ፥ወደ፡ጠዋቱ፡አንድ፡ግድም፡ቢሆንም፥ወበቁ፡እና፡ግለቱ፥ከቀትር፡የተለየ፡አልነበረም። `ፋጡማ`፥የቂጣ፡ፍርፍር፡የሞላው፤ትንሽ፡ጣባ፥በግራ፡እጅዋ፣የብርጭቆ፡ሻይ፡በቀኝዋ፡እንደ፡ያዘች፥ዓይኖቼን፡እስክገልጥ፡ድረስ፡ቆማ፡ትጠብቀኝ፡አለች።`ኹሊሡማ`፥ሽቦ፡ላይ፡የምታሰጣውን፡ጨርቅ፡እያራገፈች፡~”ምን፡ይገትርሻል!?~አጠገቡ፡አስቀምጭለት፡እና፡መጥተሽ፡እርጅኝ!”፡ስትል፡ተቆጣቻት።

የቋንቋ፡ባይተዋርነቴ፥የሚሉትን፡ሁሉ፥በደመ~ነፍስ፡እንድረዳው፡አስገድዶኝ፡መሰለኝ፥ትርጉሜ፥እጅግም፡ከግምቴ፡የራቀ፡አልሆነም። ግቢው፡ጥግ፥በ፡በርሜል፡እና፡ላስቲክ፡ጎማ፡ከተሰራው፡መታጠብያ፥ፊቴን፡እና፡ክንዶቼን፡አባበስኩኝ። እዚህ፡ትድረት፡ውስጥ፥ውኃ፡ብርቅዬ፡መሆኑን፡ስለ፡አስተዋልኩኝ፥ትጥበቴን፤በልክ፡አደረግሁት።

በቅቤ፡የተለወሰው፡ቂጣ፡እና፥ስኳር፡የሞላው፡ሻይ፥ግሩም፡መዓዛ፡ነበረው። ኣጣጥሜ፡ተመገብሁት። የፀሃይቱን፡ሂደት፡ተከተሎ፥ሠሌኑን፥ከጥላው፡ጋር፡ማንፏቀቅን፥ቅጥሩ፡ውስጥ፡ከመኮለኮሉት፡ባለጉዳይ፡ዘላኖች፡አስተውዬ፥የእኔም፡ተግባር፡ይኸው፡ሆኖ፥ሠሌን፡ስጎትት፥ሳይታወቀኝ፥ቀትር፡እንደቀረበ፡ተረዳሁ። ዘላኖቹም፣ኹሉሡማም፥ክንዳቸው፡ላይ፤የአማሩ፡ሰዓቶችን፡አስረው፡ብመለከት፡ገርሞኝ፡ነበር፤ሳስበው፡ግን፥ሀገሩ፥ለ፡`ጅቡቲ`፡ጠረፍ፡ቅርብ፡እና፡የኮንትሮ፡ባንድ፡ነጋዴዎች፡መናኸርያ፡እንደሆነ፡አስታወስኩኝ። የእኔ፡ሰዓት፡መቁጠርያ፡ግን፡እስከ፡አሁን፥ጭቃ፡ምርግ፡ቤቱን፡በሚደግፉት፡ምሦሦዎች፡ጥላ፡ዑደት፡ነው።

ሲነጋ፡ጀምሮ፡እስኪመሽ፥ካለማቍረጥ፥ለመጪው፣ለሂያጁ፣ለሰራተኛው፣ለበላተኛው፡ትዕዛዝ፡እና፡ማብራርያ፡የምትሰጠው፡`ኹሉሡማ`ሠሌን፡እያንቆራጠጠ፤የ፡`ኣሎ`ን፥ከ፡ዛሬ፡ነገ፡መምጣት፥በ፡ተስፋ፡የሚጠብቀው፥የ፡ተሳዳጅ፡ምስኪን፡እንግዳዋ፡ሁኔታ፤እያሳሰባት፡እንደ፡ሆነ፥ከ፡አስተያየትዋ፡ያስታውቃል።

የ፡ትንስዬ፡`ፋጡማን`፡ክንድ፡ይዛ፡ወደ፡እኔ፡በመቅረብ፥የቀበሌ፡መታወቅያ፡ሥሜ፡ላይ፡በወጣልኝ፡መጠርያ፡ሥሜ፡~ “`ሡልዒማን`፥አንተውስ፥ከ፡`ፋጤ`፡ጋር፡ኣዋሽ፡ወንዝ፡ይወርዳሉ፡እና፡ያያል፡~በጥሩ፡ማማር፡ቦታ፡ኖ~እሺ?”

`ፋጡማ`፤እንጣጥ፡ቀበጥ፡እየ፡አለች፥እናትዋ፡የአስጨበጠቻትን፤የ፡`ፊዚዝ`፡ከረሜላ፤በግራ፡እጅዋ፣የ፡እኔን፡መዳፍ፡በቀኝዋ፡ጨብጣ፥እየመራችኝ፥ከቅጥር፡ግቢው፡ወጥተን፥ኣህያ፣ግመል፣በቅሎ፣ፈረስ፣ኣሮጌ፡ዱቅዱቄዎች፡በሚጋፉበት፡ኣዋራማ፡ጥርግያ፤መንደሩን፡ሰንጥቀን፡ስንጓዝ፥`ይህች፡ልጅ፤ወደ፡የት፡ልታደርሰኝ፡ይሆን?`፡እያልኩኝ፤በሆዴ፡ስገረም፡ቆይቼ፥የመንደርዋን፡ጥርግያ፡እንደ፡ጨረስን፥ኣፋፍ፡ላይ፡የተቀነበበች፡ኣምባ፡መሆንዋን፡የሚገልጥ፥ከስሩ፥ጅው፤ባለ፡ቁልቁለት፥ታላቅ፡ገደል፡ተከስቶ፥በእርቀቱ፥በዘምባባ፡ዛፎች፡የታጠረ፣ሰዎች፡ዉርዉር፡የሚሉበት፣በሰፊ፡ለምለም፡እርሻ፡የተከበብ፣ከጎኑ፥የ፡`ኣዋሽ`፡ወንዝ፤እየተጎማሸረ፡የሚፈሥሥበት፥የበረሃ~ገነት፥እንደ፡ሕልመ፡ራዕይ፥ፍንትው፡ብሎ፥በዕውን፥ከዓይናችን፡ፊት፡ተከሰተ።

(ክፍል~)

ቁልቁል፥ወደ፡ልምላሜው፡ምድር፡የሚወስደው፡አዘቅት፥በከብቶች፡እና፡ሰዎች፡እግር፡ዳና፡የተቦረቦረ፡ፉካ፡መረገጫ፡ስለ፡አለው፥እሱን፡እየተረገጥን፤ከ፡`ፋጤ`፡ጋር፤እጅ፡ለእጅ፡እንደተያያዝን፡ወረድነው።

እየሰገረ፡ከሚወርደው፥ድፍርሱ፡`ኣዋሽ`፡ወንዝ፡ዳራቻ፥ልብሳቸውን፡የሚያጥቡ፣የሚያደርቁ፡ዶቢዎች፡ዜማ፡ይሰማል፣በእግራቸው፡ተሽከርካሪ፡መዘውር፥ውኃ፡ከወንዙ፡እየቀዱ፤መስኖ፡የሚያጠጡትም፡ ያዜማሉ፣በጎመን፣ካሮት፣ቃርያ፣ቆስጣ፣ድንች፣ሽንኩርት፡አትክልት፡የተነጠፈው፡የእርሻ፡መደብ፥ህብረ፡ቀለም፡አለው። የዘምባባዎቹ፡ዛፎች፡ርዝመት፥ከስር፡የሚርመሰመሱትን፡ሰራተኞች፡አሳንሶ፡ይታያል።

ይሄ፥ከ፡ከባቢው፡ኣሽዋ፡በረኅ፡መሃል፡ልምላሜ፡ኣየር፡የሚተነፍስ፥ኣጸደ፡ሕይወት፥እዚሁ፡ሀገር፡ሳይሆን፥ከሌላ፡ምድር፥በ፡`ዓላዲን~ሥጋጃ`፡ተሰቅስቆ፡የመጣ፡መሰለኝ።

በትዕይንቱ፡መፍዘዜን፥የአስተዋለችው፡ህፃን፥መዳፌን፡ለቅቃ፡ሄደች፡እና፥ዘምባባው፡ዛፍ፡ስር፡ከሚቆፍሩት፡ሰዎች፡ጋር፡ተነጋግራ፥ብዙም፡ሳትቆይ፥በትንስዬ፡መዳፎችዋ፡ሙሉ፥ቅልጥልጥ፡የአለ፡የተምር፡ፍሬ፡አምጥታ፡ሰጥታኝ፡ተመልሳ፡ሄደች። ለእርስዋ፥እየመጣች፡የምትጫወትበት፡ስፍራ፡መሆኑንን፡ተረድቼ፥እኔም፥ወደ፡ወንዙ፡ዳርቻ፡በመሄድ፥ሱሬዬን፡አውልቄ፥እግሬን፡ከወራጁ፡ወንዝ፡ስነክር፥ የቅዝቃዜው፡ፈውስ፤ወደ፡ናላዬ፡ሲሰረጅ፡ተአወቀኝ።

ይሄ፥ኅመልማል፤የበረኅ፡~ገነት፥የተቀረው፡ዓለም፡ትርምስ፡የሚመለከተው፡አይመስልም። የእራሱ፡ሕይወት፣የእራሱ፡እንቅልፍ፡አለው። ከጥቂት፡ኪሎሜትር፡በኣሻገር፥ሃገር፥በጥይት፡ እና፡ቦምብ፡እየጋየች፡መሆኑ፡አይመለከተውም። ድርቅ፣ሀሩር፣ከምሲን፡እና፡ጥማት፡የሉም። `ፋጤ`፥ፈንጠር፡ብላ፡ሄዳ፤ከአገኘቻቸው፡ህፃናት፡ጋር፡መዛለል፡ስትጀመር፤እኔም፡ከወደ፡አትክልት፡ መደቡ፡ዳርቻ፥ለምለም፡ስፍራ፡ላይ፡ጋደም፡ብዬ፤ሃሳብን፡እፈልገው፡ጀመር።

ነፍሥ፡እና፡ስጋዬ፡ታድሰው፣ጥቂት፡ከአረፍኩኝ፡በኋላ፥`ፋጤ`፡መጥታ፥እግርጌዬ፡ግትር፡ብላ፡ቆመች፡~`በቃን፡እንሂድ`፡የ፡ኣኻል፡ቋንቋዋ፡እንደሆነ፡ገባኝ።

እንደ፡አመጣጣችን፥የውኃ፡ገረወይና፡ተሸካሚ፡ኣህዮቹን፡ዱካ፡ተከትለን፤ሽቅብ፡ተወጣጥተን፤አፋፉ፡ላይ፡ስንደርስ፥መለስ፡ብዬ፥የበረኃውን፡ገነት፥ቁልቁል፥በእርቀት፡ባየው፥`አሁንም፣በኋላም፣ነገም፡ እዚሁ፡ነኝ`፡የሚል፡የተስፋ፡ቃል፡ከውስጤ፡ስለ፡አሰማኝ፤ፈዝዤ፡እቆምኩበት፡ቀረሁ። `ፋጡማ`፡መዳፌን፡ሳብ፡ሳብ፡አድርጋ፥” ሡልዒማን!~ሡልዒማን!፥እንሂደው”፡ብላ፡ነው፡የአነቃችኝ።

(ክፍል~)

`ገኒኅተ፡በረሃው`ን፡አይቶ፣የኣዋሽ፡ወንዝን፥የሕይወት፡ውኃ፡ተነክሮ፡ስለተመለሰ፥የወዛውን፤የፊቴን፡ገጽ፡ላኅይ፡እና፥ለመኖር፡ተስፋ፡በማግኘቱ፡የተነቃቃውን፡ኣካላቴን፡የአስተዋለችው፥`ኹሉሡማ`፡~”`ሡልዒማን`፥አንተውስ፤በመደሰት፡ነህ፥`ኣዋሽ`፡ስታያት፡ግዜ!”፡በማለት፥`ጎ`፡የሚል፥ቀዝቃዛ፤የቆርቆሮ፡መጠጥ፡አስጨበጠችኝ።ጣሣው፥የታችኛውን፡ከንፈሬን፡ገና፡ከመንካቱ፥ትናጋዬ፤

ይሁን፡ላንቃዬ፤ወይ፡መላሴ፡የአጣጣመው፡ሳይታወቀኝ፥ፈሳሹ፡ከሆዴ፡ገብቶ፥`ቡርቡጭ`፡ሲል፡ሰማሁት። በሕይወቴ፤ለመጀምርያ፡ግዜ፥ውኃን፡እና፡ጥሙን፡እንደ፡አዲስ፡የተዋወቅሁት፤በአለፉት፡ጥቂት፡ቀናት፡ነው፥በማለትም፤ለእራሴው፡አረጋገጥኩኝ። የነጋ፣መሸውን፡ዕለት፡እንጂ፥ሰዓት፡መቁጠር፡ከአቆምኩኝ፡ሠነባብቻለሁ።የቤቱ፡ጥላ፡ምሠሦዎች፡የሚያመላክቱኝ፥`ቀትር`ን፡እና፡የምሽቱን፡መቃረብ፡ነው። የ፡`ኣሎ`ን፡መምጣት፡መጠባበቁ፤ተስፋ፡ቢሆነኝም፥ከ፡`ኹሉሡማ`፡አነጋገር፡እና፡ሁኔታ፥እኔን፡ለማጽናናት፡ስትል፡የምታደርገው፡እንጂ፥ሰውዬው፤በመንግሥት፡ተግባር፡ተጠምዶ፤ከወረዳ፡ወረዳ፡በመዟዟር፡ላይ፡እንደ፡አለ፡ገምቼ፡አለሁ። ደግሞም፥ከዘላኖቹ፡ሁኔታ፡እና፤የቅጥሩ፡ጭር፡ማለት፥የሡልጣን፡`ዓሊ፡ሜራህ`፡ሰዎች፤በወረዳው፡ላይ፡ሽብር፡መጀመራቸውን፡ያስታውቃል።`ኹሊሡማ`፡ግን፡ልትገለጽልኝ፡አልፈለገችምከመረበሽ፡ሌላ፡ምንም፡አይጠቅመውም፡ብላ፡መሰለኝ~ወይም፥ደንብሮ፤ድንገት፡ጥሎን፡እንዳይጠፋ፤ብላ፡አስባልኝ፡ይሆናል።

አንዱን፡ዓርብ፡ዕለት፡ሌሊት፡ነው።ቀኑን፡ሙሉ፥ከ፡`ኣዋሽ~ገኒኅት`፥እርሻው፡መደብ፡ጎን፡ተጋድሜ፥መንገዴን፡ስዓልም፣በምኞትም፡ስስለመለም፡ውዬ፥ደክሞኝ፡ጋደም፡እንደ፡አልኩኝ፤ዕንቅልፍ፡ወስዶኝ፡ስአለሁ፥ከ፡እግርጌዬ፥`ፋጤ`፡ግትር፡ብላ፡ቆማ፥የ፡ሠማይ፡ከዋክብቱ፡ላይ፡አፍጥጣ፡~

“`ዔርታ፡ዓሌ~ቦራ፡በሪቾ~ዳላ፡ፊላ~ጌዳ፡ዓሌ!”፡እየ፡አለች፤ለ፡እራስዋ፡ስትለፈልፍ፡ነቃሁ።

የሰውነትዋ፤እንደ፡እንጨት፡መድረቅ፡እና፡የዓይኖችዋ፡መፍጠጥ፥ልጅቱ፤በዕንቅልፍ፡ልብዋ፡ውስጥ፡እንደ፡አለች፡ተረዳሁ።`በዕንቅልፍ፡ልብ፡ሚሄዱ፡ሰዎችን፥በድንገት፡ከአባነኗቸው፥መጋኛ፡ይመታቸዋል`፥ማለትን፥ድሮ፡ሰምቼ፡ስለነበር፥የማደርጋት፡ቸግሮኝ፤እተኛሁበት፡ሠሌን፡ላይ፡ስገላበጥ፥እናትዋ፤ ከመጣችበት፡ሳላያት፤ድንገት፡ደርሳ፥እንደ፡ጭልፊት፡መንትፋ፤ክንድዋን፡አንጠልጥላ፡ስትወስዳት፡~

“`ሡልዒማን`፥አትደንግጠዋ፥`ፋጤ`፡በ፡መኝታዋ፡መሄዳት፡ህመም፡ነች!”፡ብላኝ፤ወደ፡ቤት፡ይዛት፡ገባች። በ፡ቀኑ፡ብርሃን፡ከማውቃት፤የማትጠገብ፡ሙና፡የተለየች፡ህፃን፡ማየቴ፡ቢያሳዝነኝም፤የበለጠውን፡የአስደነገጠኝ፥ከ፡ኣፍዋ፡የፈለቁት፥ስውርውር፡እና፡ባይተዋር፡ቃላት፡ናቸው።ዦሮዬ፤እየለመደው፡ከመጣው፤የ፡ኣፋርኛ፡ቋንቋ፡ዜማው፡የተለየ፡የባዕድ፡ልሣን፡ሆነብኝ።`በሌላ፡ቀን፡ትደግመው:ይሆን?`፤ብዬ፡ሳስብ፡ቆየሁ። ለቀጠሉት፥ማግሥት፣ሠልሥት፡ግን፡አልመጣችም። በቀን፡ብርኅን፡ስታየኝም፥ዓይኔን፡እንደ፡ማፈር፡አድርጓታል።

የደቃቁ፡አሸዋ፡አዋራ፡እና፡የሙቀቱ፡ላቦት፥ለብሼው፡የመጣሁትን፥ቡኒ፡ከፈይ፡ሱሪ፤ከአካሌ፡ላይ፡ተጣብቆ፥ልግም~በገላ፡ጨርቅ፡ሊያስመስለው፡እንደተቃረበ፡አስተውላው፡መሰለኝ፥አንዱን፡ቀን፥ከ፡`ገኒኅተ~በረኅ`ው፡ውዬ፡ስመለስ፥ከ፡ሠሌኑ፡ምንጣፌ፡እራስጌ፥የንግድ፡ምልክቱ፡እንኳን፡የአልተላጠ፥አዲስ፥ውኃ፡ኣረንጕዴ፡ቀለም፤ሥሥ፡ግልድም፡ጨርቅ፡ተሸጎጦ፡አገኘሁ።

የ፡ቸርነትዋን፣የማሰብዋን፡ፀጋ፡የምገልጽበት፡አንደበት፡ተስኖኝ፥ጨርቁን፡እንደያዝኩኝ፥ከጓሮው፥ማጠብያ፡ገንዳው፡ላይ፤አጎንብሳ፡ልብስ፡ከምታንቸፈችፍበት፡ደርሼ፥በምስጋና፡እጅ፡ስነሳት ፥በፍጹም፡ፈገግታ፡ተቀብላኝ፥ወደ፡የለበስኩት፡ሱሬ፡እየጠቆመች፡~”የለበሱትስ፡መታጠባት፡ይፈልጋሉ~እሺ?”፡አለችኝ።

እነሆኝ፤የ፡ኣዲስ፡አበባው፡ጎረምሣ፥ከተጫማሁት፡ሠንደል፡እና፡ማበጠርያ፡እና፡መቀስ፡ከረሳው፣በውኃ፡ርሰት፡ተጠምልሎ፤ወደ፡ትከሻዬ፡ከወረደው፡ጸጉሬ፡ጋር፥የሀገሩን፡ተወላጅ፥`ኣሣዊርታ`፡ ለመምሰል፤ብዙም፡አልፈጀብኝም!።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ (1931-2021)

የግቢው፡ጭር፡ማለት፡እና፡የ፡`ኹሉሡማ`፡ዝምታ፥በሀገሩ፡የገባ፡ችግር፡እንደ፡አለ፡አስታወቀኝ፤ወደ፡“ኣዋሽ~ገነት`፡መመላለሱን፤በልክ፡ማድረግ፡እንደሚገባኝ፡አሰብኩኝ።

የገበሬዎች፣የሠራተኞች፡መሰማርያ፡ዕድሞ፡በመሆኑም፥`ካድሬ`፡ወይ፡`ኣብዮት~ጥበቃ`፤ለሰበካም፡ይሁን፡ለወረራ፥በቅርቡ፤ወደ፡ስፍራው፡መምጣታቸው፡እንደማይቀር፡ገምቼ፡አለሁ። የሠማዩ፡ኣየር፡ሳይቀር፥አንዳች፥የሥጋት፡ውጥረት፡ድባብ፡ይታይበት፡ጀምሯል።

`ወደ፡`ጅቡቲ`፡የሚያሻግሩኝ፤የኾንትሮባንድ፡ነጋዴዎች፡ጋር፥`ኣሎ`፡እንዲያገናኘኝ፡ነው፡`ኣባ~ሀገሩ`፡የላከኝ፥እና፡እሱ፡ባይመጣም፤አንቺው: ከመሰለሽ፡ሰው፡ጋር፡አገናኚኝ`፡ብዬ፤ኣፍ፡አውጥቼ፤`ኹሉሡማን`፡ለመጠየቅ፥እስከ፡አሁን፡በአሳየችኝ፤ትኅትና፡እና፡የእናት፡ፍቅር፥እርስዋው፡እራሧ፤ችግሬን፡ለመረዳት፡እንደማይገዳት፡እና፡`ምክንያት፡ቢኖራት፡እንጂ፥ብትፈልግ፥ እስከ፡አሁን፡ታደርገው፡ነበር`፡ወደ፡የሚል፥የጭንቅ፡እሳቤ፡መደምደምያ፡ላይ፡ደረስኩኝ። ስለ፡እዚህ፥ዕጣ፡ፈንታ፡እንደሚያደርገኝ፡እስክሆን፥የተቸርኩትን፡በጸጋ፡ተቀብዬ፥የሚሆነውን፡ ለመጠባባቅ፡ወሰንኩኝ።

ከቅጥር፡ግቢው፡መዋሌ፤መሰልቸትን፡አስከትሎ፥አጉል፡መንፈራገጥ፡እንዳይገፋኝ፡እየሰጋሁ፤ምን፡ባደርግ፡ይሻላል፡ስል፥`ፋጤን`፡ፊደል፡ማስተማር፡ታስቦኝ፡ነበር፥ይሄም፥ተማሪነቴን፡ወደ፡ማጋለጥ፡ሊያመራ፡ስለሚችል፡ብዬ፡ተውኩት፡እና፥ከኣፌ፡የመጣልኝን፥ለህንድ፡ሙዚቃ፡በነበረኝ፡ጽኑ፡ፍቅር፥ከሸክላ፡ማዘፈኛ፡ላይ፥እየደጋገምኩኝ፡በማጫወት፤በጽሑፍ፡ገልብጬ፡በቃል፡የአጠናሁትን፥`ዋክት`፡ከተሰኘው፡ፊልም፡ሙዚቃ፡ሳዜምላት፥ህፃንዋ፤በደስታ፡ነፍስዋ፡እስክታብድ፡ድረስ፥በፍቅር፡ወደደችው። እየደጋገመች፥በኅሩሩ፡እና፡ቃጠሎው፡ዝዬ፡ከተጋደምኩበት፡ እየመጣች፤ትንስዬ፡መዳፍዋን፡ዘርግታ፥በልመና፡ድምፅ፡~

“~ሡልዒማን ሡልዒማን~እባኮህ፥`ኩቼማሉ”፡በለውማ`፡ትለኝ፡ጀመር። ግዜ፡ማሳለፍያ፡ዜማውም፥ዘላኖቹ፡ቅጥር፡ውስጥ፥እየተደጋገመ፡ያስተጋባ፡ጀመር፡~

“`ኩቼማሉ፡ሙነሂ!~ቱሃ፡ቢተክ፡ሄሃቲ !~ኣ፡ሜሪጆኣን !~ኩችካ፡ኹሩባ፥ሜዲጃ!~ሜዲጃ!”።

ቅጥሩ፡ውስጥ፥በሥራ፡ተጠምዳ፤ላይ፡ታች፡የምትለው፤`ኹሉሡማ`ም፥በ፡ውልብታ፡የምትሰማውን፥የህንድ፡ዘፈን፡ወድዳው፥አብራኝ፡በሆድዋ፡ስታንጎራጉር፤ከርቀት፥በጥቂቱ፡ይሰማኛል።

(ክፍል~)

የ፡ኣፋርን፡በረኅ፡ቃጠሎ፡እና፡ነዲድ፥ሰው፡ተብየው፡ፍጡር፤አይለመደው፡የለው፥እየለመድኩት፡ነው፡፡ ወደ፤`ጅቡቲ`፡የመሻገር፤ቀቢጸ፡ተስፋዬም፥እስከ፡አሁን፡ድረስ፤አልከሰመም~እጅግ፡አስቸጋሪ፡የሆነብኝ፡እና፡ኣንጎሌን፡እየተገዳደረው፡የመጣው፥ከጠዋት፡እስከ፡ማታ፥አንዳች፡ስራ፡ሳልሰራ፥ጥላ፡ፍለጋ፥ሠሌኑን፤ቤቱ፡ዙርያ፡እየ፡አሽከረከሩ፡መዋሉ፡ነበር።

ሰዓሊ – ጃህእርሥዎ፡ሞትባይኖር፡ኪሩብ፡ዔል

ኣዲስ~ኣበባ፡ውስጥ፡የኖርኩት፤ፋታ፡የለሽ፤የኣብዮቱ፡ተሳትፎ፡ሕይወቴ፡እና፡የቤተሰቤም፡ሰፊ፡ትድረት፡የፈቀደልኝ፡ሕይወት፥ድንገት፡በመትነኑ፥የአለፈውን፡ሕይወቴን፡በትውስታ፡እና፡ስጋት፡እየጎተትኩኝ፤ እንዳልረበሽበት፥ኣንጎሌን፥በብርቱ፤ሠረገላ፡ቁልፍ፡ከርችሜው፡አለሁ። ቢሆንም፡ባይሆንም፥የ፡አለኝ፡የመኖር፡ተስፋ፤የወደፊቱ፡ነው።

አብቅቶለታል፡ብዬው፡የነበረው፥የትንስዬ፡`ፋጡማ`፥የሌሊት፡ፊንታ፡እንደገና፡አገረሸ። የቁጥር፡ቀመር፡እንዳይረሳኝ፡የሠጋሁ፡ይመስልስ፥በስራ-ፈት፡ኣንጎሌ፥ተንጋልዬ፥ኅልቁ፡መሣፍርቱን፡ከዋክብት፡ስቆጥር፥እንደ፡ዓመልዋ፤ሹክክ፡ብላ፡እግርጌዬ፡ቆማ፥በዕንቅልፍ፡ልብዋ፡መነጋገርዋን፡ቀጠለች፡~” ካልዴሮ~ሃይሊ፡ጉቢ~ተት፡ኣሊ~ቱሉ፡ሞዬ”። የሌሊት፡ዓመልዋን፡እንደለመድኩት፡ የተገነዘበችው፡እናትዋም፤ቁጣዋን፡እና፡ማስጣልዋን፡ትታው፡አለች። ህፃኒቱ፥የዕንቅልፍ፡ልብዋን፡ንግግር፡ስትጨርስ፥ትንስዬ፡ባዶ፡እግርዋን፥ኣሸዋው፡ላይ፡እየጎተተች፤ተመልሳ፤፡ወደ፡ቤት፡ገባች።

`ከምሲን`፡የሚሉት፡ኣውሎ፡ነፋስ፡ሲነሳ፡በስተቀር፤በር፡እና፡መስኮቱ፡ስለማይዘጉ፥በድምፅ፡የለሽ፡ነኆላልዋ፡ሄዳ፡እናትዋ፡ጎን፡ክልትው፡አለች።ጠዋት፡ስነሳ፥ሌሊቱን፥ከ፡ኣፍዋ፡ሲፈልቁ፡የሰማኋቸውን፥ ኣስተናግር፡መሰል፡ቃላት፥ለፊደል፡ማስተማርያ፡እንዲሆን፡አስቤ፡ከሱቅ፡የገዛሁት፡ደብተር፡ላይ፥ሳልረሳ፡አስፈርኵቸው።

የእኔ፡ስራ፡ፈትነት፥ከተማው፡ውስጥ፡እየተፈጠረ፡ከአለው፡ውጥረት፡ጋር፡ተዳምሮ፥`ኹሉሡማን`፡እያስጨነቃት፡መሆኑ፥ከ፡አነጋገርዋ፡መረዳት፡ችዬ፡አለሁ።ይሄንኑ፡አሳብባ፡የዘየደችው፡መሰለኝ፥ዕሁድ፡ጠዋት፤ከተጋደምኩበት፡መጥታ፡~” እኔውስ፥ጨርቅ፤ለገብያት፡በመውሰድ፡ነኝ~በእኔ፡ጋር፡ይመጣል፡አንተው፥ሡልዒማን?”፡ብትለኝ፥አፈፍ፡ብዬ፡በመነሳት፥ጨርቅ፡የሞላውን ፡ዘምቢል፥ከእጅዋ፡ተቀብዬ፡ተከተልኳት። ከግራ፡ቀኙ፡መንገደኛ፥የአክብሮት፡ሰላምታ፡ሳይሰጣት፡አያልፍም። የጎሳ፡ወይዘሮ፡መሆንዋን፥በእርግጥ፡ተረዳሁ።

መሀል፡ከተማው፡የሚገኝ፥የጨርቃ፡ጨርቅ፡መደብር፡እና፡ልብስ፡ስፌትን፡ከአጣመረ፤መለስተኛ፡ሱቅ፡ስንደርስ፥ከትከሻው፡ላይ፡ሜትር፡መለክያ፡ዘንጠፍ፡የአደረገ፥ጸጉረ፡ሉጫ፡ቀልጣፍ፡ብጤ፡ጎረምሳ፤በፈገታ፡ተቀበለን።

በ፡ኣፋር፡ቋንቋቸው፡ከሰጠችው፥ረዘም፡የአለ፡ሀተታ፥`ሡልዒማን`፡ይባላል`፡ብላ፡እንደ፡አስተዋወቀችኝ፡ተረዳሁ። ሥሙን፥`ሙሄ`፡ነኝ፡የአለኝ፡ጮሌነቱ፡ከገጹ፡የሚናገር፡ጉብል፥ሰሃ፡በማይወጣለት፡የይፋቴ፡ኣምሃርኛ፡~

” ምንም፡ችግር፡የለም፥እዚህ፡እየመጣህ፡መዋል፡ትችላላህ~ጨርቃ፡ጨርቁን፡መሰንጠቅ፡እና፡መመተር፡ከረዳኸኝም፥የእጅህን፡ዋጋ፡አስብልሃለሁ~አረፍ፡በል፡አሁን”፡ብሎ፤ የ፡`ሚሪንዳ`፡ጠርሙዝ፤ከ፡`ፍሪጅ`፡ዉስጥ፡አውጥቶ፤ለሁለታችንም፡አደለን።

መደብሩን፤ለቅቀን፡ስንወጣ፥የ፡ኾንትሮ፡ባንድ፡ጨርቅ፡እና፡ሌሎች፡ሸቀጦችንም፡እየተቀበለ፡የሚቸረችር፡ቀና፡ልጅ፡እንደሆነ፡አጫወተችኝ። ዕድሌን፡ማመን፡ተሳነኝ። በሰሞኑ፥የመንፈሴ፡ውጥረት፤ ምን፡እንደማደርግ፡አላውቅም፡ነበር። ዋናውን፡መንገድ፡ጨርሰን፥ወደ፡ቅጥራቸን፡የሚያመራውን፡ጥርግያ፡ልንይዝ፡ግድም፥ከጥጉ፡ላይ፥ምድርን፡የሚደባልቅ፡ድቤ፡እና፡ጩኸት፡አይሉት፡ኹካታ፡ዓይነት፡ድምፅ፡ቢሰማ፥ወደ፡እኔ፡ዘወር፡ብላ፡~

~” ሡልዒማን፥አንተውስ፥`ኆፍርያት`፡ያውቃሉ?”፡ስትል፡ጠይቃኝ፤ወደ፡መስኮቱ፡ጠጋ፡አለች።እኔም፡ጠጋ፡አልኩኝ።

የ፡ኣታሞው፡ድቤ፡ምት፡ጣርያውን፡ሊያነሳው፡ተቃርቧል። አንዲት፥ጠና፡የአሉ፡ባልቴት፡ብጤ፥ላቦታቸው፤በእላያቸው፡እየጎረፈ፣ኣራት፡ሰዎች፤እንደ፡ኣጎበር፡ከኣናታቸው፡ላይ፡በአጠልሉላቸው፡ጨርቅ፡ ስር፥እንደ፡ዛር፡ውላጅ፡ይገዝፋሉ። እልልታም፣ጉሪም፣ጭብጨባም፡ተቀላቅሎ፡ይሰማል።

`ኹሉሡማ`፥የጨመደደችውን፡መዳፌን፡ጠበቅ፡አድርጋ፡~” አንተውስ፡መሳቃት፡የሉም~እሺ!?”፡አለችኝ።እኔ፥እንኳን፡ልስቅ፡ቀርቶ፥ድንጋጤዬም፡አላባራልኝም። `ዛር`፣ባለ~ዑቃቢ` ፡ወዘተ፡ሲባል፡መስማት፡እንጂ፥በኣይኔ፡ዓይቼው፡ስላማላውቅ፥በ፡ድንገት፡ስለተከሰተብኝ፤ዥው፡አድርጎኛል። አጠገባቸው፥ሳጠራ፡ሰደቅ፡ላይ፤ሰዎቹ፡የሚያቀርቡለትን፥ሰንደል፣ቂጣ፣እንጀራ፤ሽቱ፡ ከረሜላ፣በቆሎ፡ፈንዱሻ፡የሚሰበስብ፥ድምቡሽ፡የአለ፡ልጅ፡ቁጭ፡ብሏል፡~”`ኸዳሚ`፡መሆናቱ፡ነው፡እሱስ “፡አለችኝ። ብዙ፡ልንቆይበት፡የሚገባ፡ስፍራ፡ስለ፡አልመሰለኝ፤ፈቀቅ፡ማለቴን፡አስተውላ፥ወደ፡ቤት፡መንግዳችንን፡ቀጠልን።

“`ኣሎ`፡ይመጣል፡ቀን፡ድረስ፥አንተው፡በ፡`ሙሄ`፡ቤት፡መዋላት፡ነው~እሺ:`ሡልዓዒማን`?”። በፍጹም፤የልብ፡ምሥጋና፡~” እሺ~`ኹሉሡማ`~እሺ!”፡በማለት፡ሳመሰግናት፤ በ፥`አይዞህ`፡የሚያጽናኑ፡ዓይኖች፡ኣይታኝ፥መዳፌን፥የባሰ፡አጥብቃ፡ያዘችው።

ያንን፡ምሽት፥ደረቴን፡ሰቅዞ፡ይዞኝ፡የሠነበተ፤አንዳች፡ነገር፡ስለለቀቀኝ፥ጅው፡የአለ፡ዕንቅልፍ፤በቶሎ፡ወሰደኝ።`ፋጡማ`ም፥ሌሊቱን፡በነኆላል፡መጥታ፡አልጎበኘችኝም።

(ክፍል~)

ደግ፡ነገር፡ሲመጣ፥አብረው፡እንዲያጅቡት፡የታዘዙ፡እኩያን፡ይኑሩ፤ተብሎ፤በጠዋት፡የተደነገገብን፡ይመስል፥`ኹልሡማ`፡ቅጥር፡ግቢ፡ውስጥ፡መወሰኑ፡ኣንጎሌን፡ማደንዘዝ፡ጀምሮት፡የነበረውን፡ስቃይ፥ የ፡ኣዋሽ፡ወንዝ፡፥`ገኒኅተ~በረኅ`፡መከሠት፡ሲፈውሰው፥በእግሩ፡ተከትሎ፡`የ፡ሡላጣን፡ዓሊ~ሚራህ`፡ሰርጎ፡ገቦች፥ከብበዋል፥የሚለው፡ጭምጭምታ፥በከተማይቱ፡የፈጠረው፡ውጥረት፥ ያሰጋኝ፡ጀመር። እዚህ፥የዘላን፡ትድረት፡ውስጥ፡ደግሞ፥`ጭምጭምታ`፡የ፡`ስልክ`፡ጥሪ፣የ፡`ራዲዮ`፡ዜና፡ማለት፡ያህል፡ነው።

በማለዳ፡ተነስቼ፤ወደ፡`ሙሄ`፡መደበር፡በማምራት፥ጨርቃ፡ጨርቁን፡መመተር፣ጣቃውን፡እየቀደድኩኝ፡አጣጥፌ፡ማስቀመጥ፡ተግባሬ፡ሲሆን፥ደምበኞች፡በሌሉበት፡ሰዓት፡እንጨዋወታለን፤ ሰው፡ሲመጣ፡ግን፡ወደ፡ዝምታዬ፡በማቀርቀር፥ጎንበስ፡ደፋ፡በማለት፡ሰራተኛ፡እመስል፡አለሁ።

የቆዳዬ፤በፀሃዩ፡ሃሩር፥በፍጥነት፡መጥቆር፡እና፡የጸጎሬ፡ሽብልል፡ማለት፥ፈጽሞ፤ከሃገሬው፡የሚለየኝ፡ባለመሆኑ፥ገና፡እንደገቡ፥`መሃፈዳ`፡በማለት፥በ፡ኣፋርኛ፡ማነጋገር፡ሲጀምሩ፡ መልስ፡ባለምስጠቴ፥`ሙሄ`፡በቶሎ፡ደርሶ፡~`~ከ፡ኣሰብ፡የመጣ፡ዘመዴ፡ነው~ጉሮሮውን፡ስለታመመ፤መርፌ፡ላይ፡ነው፡እና፥ሃኪም፡እንዳይነጋገር፡ከልክሎታል`፡ሲላቸው፤በኅዘኔታ፡እና፡ጥርጣሬ፤ በጎን፡ተመልከተውኝ፤ጉዳያቸውን፡ጨርሰው፡ይወጣሉ።

የ፡ዕለት፡ውሎዬን፡ጨርሼ፣`ሙሄ`፥ለ፡እጄ፡የ፡አሰበልኝን፥ሦሥት፣ዓራት፥ሙቀት፡እና፡ላቦት፡የአሳሳቸው፡ብሮች፡ቍጥሬ፡እንደወጣሁ፤በቶሎ፡የምገዛው፤ከ፡ጅቡቲ፥`በኮንትሮ፡ባንድ`፡የሚመጣው፥`ጎ`፣`ኦራንጂና`፣`ሲናልኮ`፡ወዘተ፥የለስላሳ፡መጠጥ፡አይነት፥ውኃ፡ጥሜን፡እየ፡አባሱብኝ፡ተቸገርኩኝ።

በተረፉኝ፡ሳንቲሞች፥ለፋጤ`፤`ሜንታ፡ከረሜላ`፡እና፡`ፊዚዝ`፡የተሰኘ፡ቀዝቃዛ፡የበረዶ፡ከረሜላ፡ገዝቼላት፡ስመልስ፥ሰዓቱን፡ጠብቃ፤ከቅጥሩ፡በር፡ላይ፡ይዛኝ፥ጣፋጩን፡ከነጠቀችኝ፡በኋላ፤ እየጮኸች፤ወደ፡እናትዋ፡ስትሮጥ፡ማየት፥ከእርስዋም፡ይበልጥ፡እኔን፡ያስደስተኝ፡ነበር።

ሣምንት፡እንደሞላኝ፥ወደ፡`ሙሄ`፡መደብር፡የሚመጡት፡ደምበኞች፡ቁጥር፡ቀነሰ። `ዲቺ~ኦቶ`እና፡`ኤሊ~ዳአር`፡የተሰኙት፥ድንበር፡መንደሮች፡ላይ፥`ደርግ`፡የፍተሻ፡ቡድን፡ እንደተከለ፡እና፤በኣሰብ፡ወደብ፡በኩል፡የሚያስገባውን፥ከሩስያ፡የጦር፡መሣርያ፡እንደሚያግዝ፡ተሰማ። የኣፋር፡ሕዝብ፥በመንቀሳቀስ፡መብቱ፡ላይ፥አንዳች፡ገደብ፡ስላማያውቅ፡እናም፥አብዛኛው፥ የ፡`ዓሊ~ሚራህ`፡ደጋፊ፡በመሆኑ፥ነገሩ፡እየተካረረ፡በመሄድ፡ላይ፡እንደሆነ፥`ሙሄ`፥በኅዘኔታ፡ገጽ፡እንደተከዘ፡አወጋኝ።

የ፡`ዓሎ`፡መምጣት፡ተስፋ፥የ፡በረኅ~ውኃ፡ሽታ፡ሆኖ፡እየራቀ፡ሲሆን፥የእኔው፤የውኃ፡ጥም፡ነገር፡ደግሞ፥ቀን፡በገፋ፡ቁጥር፡እየበረታብኝ፡ነው። ማለዳ፡ዓይኖቼ፡ሲገለጡ፡የማያት፡ ፀሃይ፥ወደ፡ምድር፡እየቀረበች፣ወደ፡እኔው፡እየተጠጋች፤ስለሚመስለኝ፥ለሰው፡ላካፍለው፡የማልችለው፥ልዩ፡ጭንቀት፡እየተፈጠረብኝ፡ነው።

`ኹሉሡማ`፥`ሙሄ`፡መደብር፡ውዬ፣ለ፡`ፋጤ`፡`ፊዚዝ፡ይዤ፡መምጣቴ፥የቀድሞውን፡ጭንቀቴን፡የቀነሰልኝ፡እየመሰላት፡~"ኣሎ`ስ፤በሠሞናት፡መምጣት፡ይመስለኛል፥እሺ~፡ `ሡልዒማን`!”፥በሚሉ፡የማጽናኛ፡ቃላት፡ታበራታኛለች። ከ፡እርስዋም፡ማበረታታት፡ይበልጥ፥በ፡ከተማውም፡ሆነ፤በ፡ዓለሚቱ፡አንዳች፡ችግር፡አለ፡ብላ፡የማታስበውን፥የ፡`ፋጤን`፡የ፡ገመድ፡ዝላይ፡ማየት፡እና፡ግድ~የለሽ፡ሳቅዋን፡መስማቱ፥ተስፋ፡ይሰጠኝ፡ነበር።

የ፡`ኹሉሡማ`ን፡ግቢ፡መቀዝቀዝ፡እና፤የ፡`ኣሎን`፡መዘግየት፡ጉዳይ፥ለ፡`ሙሄ`፡አጫወትኩት። የ፡ይምሰል፡ማጽናኛ፡ሊሰጠኝ፡ስለ፡አልፈለገ፥በጽሞና፡አድምጦኝ፥ጭንቅላቱን፡ እየነቀነቀ፥የሚመትረው፡ጨርቅ፡ላይ፡አጎነበሰ። ስለ፡ፀሀይቱ፥ወደ፡እኔ፡መቃረብ፡ግን፥ለምነግረው፡ሰው፡ቸገረኝ።

የበረኅ፡ውኃ፡ጥም፤ሰውን፡እንደሚያሳብድ፥ከ፡ልጅነታችን፡ጀምሮ፡ስንሰማው፡የአደግነው፡ታሪክ፡ነው።`እገሌ፡የተሰኘ፡ወታደር፥ጠረፍ፡ጥበቃ፡ኦጋዴን፡በረኅ፡ተደልድሎ፥በውኃ፡ጥም፡ ኣብዶ፡ተመለሰ`፡ሲባል፤እንደ፡ተረት፡ነበር፡የምንሰማው። ተረት፥ዕውን፡ሊሆን፡እንደሚችል፥የትኛው፡የልጅነት፡ኣእምሮ፡ገምቶት!?

“ዖሞዒሳ!”~”ኣፈሌራ!”~”ዳንዲ!”~”ጎቢ፡ለማ`!”~”ቁሩብ፡ረጲ!”፥የሚሉ፡ድምጾች፡እንደ፡ሠመመን፤ዕዝነ፡ልቡናዬ፡ውስጥ፡ሲንሾካሾኩ፥ከተኛሁበት፥በቀስታ፡ነቃሁኝ። `ፋጡማ`፡ግትር፣ድርቅ፡እንደ፡አለች፥ሽቅብ፡ከዋክብቱ፡ላይ፡አፍጥጣ፡እየለፈለፈች፥እግርጌዬ፡ቆማለች።

ከ፡እራስጌ፡ኬሻ፡ስር፥እርሳስ፡እና፡ደብተሩን፥በቀስታ፡ስቤ፡በማውጣት፥የሠማኋቸው፡ቃላት፡ሳይዘነጉኝ፤በቶሎ፡ስቸከችክ፥ለ፡እርሧ፥ፈጽሞ፤ከ፡ዓይኖችዋ፡እይታ፡አልገባም፡ነበር። ኣሥተናግሯን፥ድንገት፡ቁርጥ፡አድርጋ፡አብቅታ፥እግርዋን፤አሸዋው፡ላይ፡እየጎተተች፥በጕሮው፡ጭለማ፡በኩል፡ተሰወረችብኝ።

(ክፍል~)

በማለዳ፥ግመሎች፡እየጎተቱ፡የመጡት፡ዘላኖች፥`ኹልሡማ`፡ን`ወደ፡ቅጥሩ፡ጥጋት፡ወስደው፥ዝግ፡በ፡አለ፡ድምፅ፤ሲያነናግርዋት፡አርፍደው፤ለ፡አድማ፡እንደ፡ተሰደረ፡ጋንታ፥አንገታቸውን፡አቀርቅረው፡ተመልሰው፡ሄዱ።

`ኹልሡማ`፥የቁርሴን፡ሻይ፡ብርጭቆ፡ሳታቀብለኝ፡~`ሡልዒማን`፥የ፡ደርጉስ፡ሰዎች፡ለመፈተሻት፡መምጣት፡አሉ፡~አንተውስ፤ወደ፡`ሙሄ`፡ሱቅ፡በመሄዳት፡ይሻላል`፡ብላኝ፡ተመለሰች። ልታስበረግገኝ፡አልፈቀደችም፡እንጂ፥ነገሩ፤የከረረ፡እና፡አስፈሪ፡እንደሆነ፥ከሰውነትዋ፡መረበሽ፡ያስታውቃል። ወደ፡`ሙሄ`፡መደብር፡ሳመራ፥የ፡`ኣሻዒታ`፡መንደር፥ፍጹም፡ጭር፡ማለቷን፡አስተዋልኩኝ። ኣዋራ፡መንገዶቹን፥የ፡በረሃ፡ንፋስ፡ብቻ፡ነበር፡የሚያፏጭባቸው። የ፡አሸረጥኩት፡ግልድም፡እና፤የጸጉሬ፤መሸብለል፤ባይከልለኝ፤በቀላሉ፥ከ፡አንዱ፡የቀበሌ፡ጀሌ፤ዓይን፡እንደምገባ፡አያጠራጥርም።

ከሁሉም፡ሁሉም፡የባሰብኝ፡ግን፥የፀሃይቱ፡ሀሩር፡እና፥ምጣድዋ፤በ፡እየ፡ደቂቃው፤ወደ፡ጭንቅላቴ፡እየቀረበ፡መምጣቱ፡ነው። በዦሮዬ፡የምታንሾኮሹክብኝም፡ይመስለኛል።ቃላቱ፡ግን፡በጥራት፡አይሰሙኝም። የ፡`ፀሃይቱን`፡ነገር፡ኣቅቤ፥የውኃ፡ጥሜ፡እየባሰብኝ፡ስለመሄዱ፡ብቻ፥ለ፡`ሙሄ`፡ባማክረው፡~`የ፡ለስላሳ፡መጥጦቹን፡በልክ፡አድርገው~ስኵሩ፡ሳይሆን፡አይቀርም፡የሚያብስብህ`፡ሲል፡መከረኝ። ወደ፡ደጅ፡ወጥቶ፥ፀሀይቱን፡ማየት፡እያስፈራኝ፡መጣ። `ሙሄም`፡በከተማው፡ሽብር፡በመታወኩ፥ከ፡ወደ፡ንግግሩ፡ቆጠብ፡ብሏል።

ከ፡`ኹሉሡማ`፡ቅጥር፡ስመለስ፥በ፡ኣዛውንት፡መሳይ፡ሰዎች፡ተከብባ፡ሲወያዩ፡ደረስኩኝ። ነገራቸውን፡ጨርሰው፡እንደ፡ወጡ፥ወደ፡የ፡ተጋደምኩበት፡ጥጋት፡መጥታ፡~`እኔውስ፤ለ፡ዓይን፡መታከማት፥`ጃቡቲ`፡መሄዳት፡ነኝ፥አንተውስ፡ከ፡እኔም፡አብረውት፡ይመጣል~እሺ~`ሡልዒማን`፡ብትለኝ፤በደስታ፡ዘልዬ፡ላቅፋት፡ቃጥቶኝ፥ሁኔታዬን፡አስታውሼ፡እራሴን፡ገታሁት።

ከ፡ቅጥር፡ግቢዋ፡የተፈጠረውን፡አስጊ፡ሁኔታ፥በግልጽ፡የ፡አብራራልኝ፡ግን፥`ሙሄ`፡ነበር፡~`፡የ፡ሡልጣን፡ዓሊ፡ሚራህ`፡ዘመድ፡ስለ፡ሆነች፥የ፡ደርግ፡ሰዎች፡ጠርጥረዋታል፥ለ፡እዚህ፡ነው፤በ፡ህክምና፡ሰበብ፥ወድ፡`ጅቡቲ`፡መሸሽ፡የፈለገችው~ለ፡አንተ፡ግን፡ጥሩ፡ሆነልህ፥`አየህ~ዓላህ`፡ሊረዳህ፡ፈለጎ፡የ፡አደረገውን*`አለኝ።

ይሄንን፡መስማቱ፥ትልቅ፡ተስፋ፡ቢሆነኝም፥`ኹሉሡማ`፡ቅጥር፥የደርግ፡ሰዎች፡ድንገት፡ከተፍ፡ብለው፤ይዘው፡ቢመረምሩኝ፥አንዳች፡ማምለጫ፡ቀዳዳ፡እንደማይኖረኝ፡አስቤ፥የባሰውን፡ተረበሽኩኝ። ወደ፡`ኣዋሽ`፡ወንዝ፡ገኒኅቱ፡አልጠጋ፡ነገር፥የሰራተኞች፡እርሻ፡መስክ፡በመሆኑ፥`እናንቃችሁ`፣`እናስታጥቃችሁ`፡የሚሉ፥ካድሬዎች፥በቅርቡ፡ደርሰው፡እንደሚወሩት፡ግልጽ፡ነው። በ፡ውኃ፡ጥም፡ኣራራ፡ላይ፡ሽብር፡እና፡`የ፡ፀሃይቱ፡ማጉረምረም`፡አብረው፥ሁኔታዬን፤በቅጡ፡ለማሰብ፡እንኳን፥ለእራሴው፡አስፈሪ፡ሆነበኝ።

የ፡`ፀሃይቱን`፡ነገር፥ለ፡አንዳቸው፡ትንፍሽ፡ብል፥`ኣብዷል`፡ብለው፡ሊሸሹኝ፡እንደሚችሉ፡አስብኩ። ወይም፥ሲለፈልፍ፤ኣጋልጦ፡አደጋ፡ላይ፡ይጥለናል፡ብለው፥አሳልፈው፡ቢሰጡኝስ*~ደግሞስ፡እስከ፡መቼ፥`ሙሄ`፡ሱቅ፡ተሸሽጌ፡እዘልቃለሁ*~የምተነፍስበት፡በኩል፡ተሳነኝ። `ሙሄ`፡የ፡አለኝ፡`ዓላህ`፥የ፡`ኹሉሡማን`፡የ፡`ጅቡቲ`፡መንገድ፡እንዲያፋጥን፡መመኘት፡ብቻ፡ነው።

`እንደ፡አየኸው፥`ከ፡`ዱብቲ`፡እና፡ከ፡`ኣሰብ`፡የሚመጡ፡ሰዎች፤ከመደብሬ፡ስለሚመላለሱ፥ትንሽ፡ፍንጭ፡ቢያገኙ፥ለ፡ደርግ፡ሰዎች፡እንዳያሳብቁብኝ፡እየፈራሁ፡ነው~ሁሉም፡ነፍሱን፡ለማዳን፡ሲል፥ወሬ፡አቀባይ፡ሆኗል~እና፥ለጥቂት፡ቀናት፡ሱቄን፡ለመዝጋት፡እየ፡አሰብኩኝ፡ነው~ከ፡ኹልሡማ`፡ጋር፡መንገድ፡እስክትጀምሩ፡ድረስ፥እስቲ፡እዚሁ~ጎንበስ፡ጎንበስ፡እያልን፡እናሳልፈው*`አለኝ።

የ፡እናትዋን፡ስጋት፡መጨመር፡እና፤የግቢውን፥ከ፡አለ፡ወትሮው፡መርመስመስ፡ማየት፡የጀመረችው፡`ፋጤ`፡ሳትቀር፡ተደናግጣ፥ትንስዬ፡ፊትዋ፡ተራብሾ፡ብመለከት፤እጅግ፡አዘንኩኝ።አላጽናናት፡ነገር፥እኔም፡እራሴ፡ነፍሴ፡ተናውጻብኝ፡አለች። የ፡ሌሊት፡ነኆላልዋ፡እና፡ኣስተናግሯም፡ቆሟል፥የቀኑ፡ሕይወትዋ፡እራሱ፥የቁም፡ቅዠት፡ስለ፡ሆነባት፡ይሆል፤ብዬ፡ገመትኩኝ።

ጠዋት፡ስንነቃ፥`የ፡ሡላጣን፡ዓሊ~ሚራኽ`፡ሰዎች፤ፈንጂ፡ጠምደው፡ሽብር፡ጀምረዋል፡የሚለው፡ወሬ፤ከተማይቱን፣የኅሙስ፡ገበያ፡ጭምር፥ሰጥ፡ለጥ፡አድርጕት፡ዋለ።ከ፡`ዱብቲ`፡የመጡ፤ጂፕ፡ሙሉ፡ወታደሮች፤ሲሽከረከሩባት፡ውለው፡ተመለሱ።ሁሉም፡በ፡እየ፡ማደርያው፡እንደተከተተ፡ውሎ፤አመሻሽ፡ላይ፥ጥግ፡ጥጉን፡እያልኩኝ፤ወደ፡`ሙሄ`፡ሱቅ፡አመራሁ።

ፍርሃት፡እና፡ስጋቱን፡ለመደበቅ፡ይመስል፥አግዳሚውን፡ሰደቅ፡ተደግፎ፥`ጂታን`፡የኮንትሮባንድ፡ሲጃራ፡እያጤሰ፥`ናሽናል~ጂኦግራፊ`፡የሚል፡መጽሔት፡ሲያገላብጥ፥ዘው፡ብዬ፡ገባሁ። ገና፡ሲያየኝ፡~ `አንተ፡ደፋር፡ልጅ*~እንዴት፡ብለህ፡መጣህ*`፡ሲል፡አነከረ። የ፡`ኹሉሡማ`ን፡ግቢ፡ውጥረት፡ሁኔታ፡አወሳሁት።

(ክፍል~)

” የዛሬ፡ዓመት፡ግድም፥`ደንከል~በረኅን፡ለማጥናት፡ብለው፡የመጡ፡ፈረንጆች፥ድንኳናቸውን፡ከምሲን፡በታትኖባቸው፤ለማሰፋት፡በሰዎች፡ተመርተው፡ሱቄ፡የመጡ፡ግዜ፥ስጦታ፡ትተውልኝ፡ የሄዱት፡መጽሔት፡ነው”፡ ብሎ፥እያገላበጠ፡አሳየኝ። ገጾቹን፡ስገላልጥ፥አንደኛው፡ገጽ፡ላይ፡ያየሁት፡ጽሑፍ፤ቀልቤን፡ነጠቀኝ። አተኩሬ፡ማንበብ፡ስጀምር፥ኣንጎሌ፡ውስጥ፡እንደ፡የገደል፡ማሚቴ፡ድምፅ፡ይጮህብኝ፡ጀመር። ጽሑፉን፤ደጋግሜ፡ማንበብ፡ስቀጥል፥በሰንጠረዥ፡የተዘረዘሩት፥ኢትዮጵያ፡ምድር፡የሚገኙት፡የ፡እሳተ~ገሞራ፡ስሞች፡ዝርዝር፡በሙሉ፥`ፋጤ`፡በእንቅልፍ፡ልብዋ፡ ስታስተናግራቸው፡የነበሩት፡ቃላት፡ሆነው፡አገኘኋቸው።

የከንፍሮቼን፡መንቀጥቀጥ፡እና፡መርበትበቴን፡የአስተዋለው፡`ሙሄ`፡~” ምነው?፤ምን፡ጉድ፡አገኘህበት፥ይሄንን፡ይአክል፡የደነገጥከው!?”፡ሲል፡ጠየቀኝ። ኣፌ፡ላይ፡የመጣልኝን፡~” አይይ፥ከትምህርት፡ቤታችን፡ሲያስተምሩን፡የነበረ፡ነገር፡ስለ፡አገኘሁበት፥ተገርሜ፡ነው”፥ስል፡ቀጠፍኩት።የተጠራጠረ፡አልመሰለኝም፥ሲጃራውን፥በኩራት፡ማቦለቁን፡ቀጠለ። የአነበብኩትን፡ለማመን፥ ሰሌን፡ምንጣፌ፡ራስጌ፡የሸጎጥኩትን፡ሉክ፡ማመሳከር፡እንደሚገባኝ፡አሰብኩኝ። ጉሮሮዬ፥በ፡ድንጋጤ፡ሲሰነጣጠቅ፡ተሰማኝ፡~ ” እባክህ፡`ሙሄ`፥የምጠጣው፡ነገር፡ስጠኝ!?”፡ብዬ፡ስማጠነው፥በጥድፍያ፡ፍሪጁን፡ከፍቶ፥ቀዝቃዛ፡የሲናልኮ፡ጠርሙዝ፡እየ፡አቀበለኝ፡~” በአንዴ፡አትገሽረው፥ቀስ፤ብለህ፡ጠጣው”፡ሲል፡መከረኝ። የ፡`ፋጤ`ን፡ኣስተናግር፥ነገር፥ቁም፡ነገር፡ብዬ፡ባጫውተው፥ይሄ፡ምስኪን፡ተሳዳጅ፥ውኃ፡ጥሙ፥አእምሮውን፡ነክቶታል፤ብሎ፡እንደሚደመድም፡ታሰበኝ፡እና፡ ” አንብቤ፡ልመልስልህ?”፡ብዬ፡ብጠይቀው፥ሳያመነታ፥በኣዎንታ፥ጭንቅላቱን፡ነቀነቀልኝ። ወድያው፤በተደጋጋሚ፥ከተማው፡ውስጥ፡ተኩስ፡ሲሰማ፥የሱቁን፡በር፡ዘጋግቶ፤ማሾውን፡ ለኮሰ፡እና፡~” ዛሬ፥እዚሁ፡ማደር፡ሊኖርብህ፡ነው!~ጣርያው፡ሰቀላ፡ላይ፥ትርፍ፡ሰሌን፡አለኝ” ብሎ፥በእንጨት፡መሰላሉ፡እየመራኝ፤ ሽቅብ፡ይዞኝ፡ወጣ። ገና፥ጎናችንን፡ከማሳረፋችን፥ `ሙሄ`፡ማንኳረፍ፡ሲጀምር፥እኔ፡እየተገላበጥኩኝ፥በእየ፡ሩብ፡ሰዓቱ፤ወደ፡ጓሮው፡በመሄድ፡ሽንቴን፡ስሸና፡ነጋልን።

ቀድሞኝ፡ተነስቶ፥ወደ፡መንደሩ፡ዳቦ፡መጋገርያ፡ቤት፡ሄዶ፥ሽልጦ፡እና፡`ፓስቴ`፡ቁርስ፡ይዞልን፡ተመለሰ። ፊቱ፡ክፉኛ፡ገርጥቷል፣ የወትሮ፡ፈገግታውም፡አይታይበትም፡~” እዚህ፡ከተማ፥ወሬ፥ከንፋሱ፡ይፈጥናል!~`የ፡ዓሊ፡ሚራኽን`፡ሰዎች፡ለማደን፤የደርግ፡ወታደሮች፤ወደ፡ከተማ፡እየመጡ፡ነው፡እና፥ተጠንቀቅ`፡ነው፡የሚሉኝ~እኔም፥መንገዴን፡ማበጀት፡ይኖርብኛል”፡አለኝ፤ “ታድያ፥እኔስ፤ምን፡ባደርግ፡የሚሻለኝ፡ይመስልሃል~`ሙሄ`?”። ሰደቁ፡ጀርባ፡እየተንጎራደደ፡~” እኔ፡ምን፡አውቄ!~ምናልባት፥`ኹሉሡማን`፥መቼ፡ለመንቀሳቀስ፡እንደ፡አሰበች፡ልጠይቃት፡እና፥ከሁለት፣ሦስት፡ቀናት፡የበለጠ፡የማይዘገይ፡ከሆነ፥ወደ፥`ዔርታ~ዓሌ`፡አካባቢ፡እየሄዱ፥ጨው፡ኣሞሌ፤ከሚጠርቡት፡ኅማሎች፡ጋር፡አገናኝቼህ፥ባይሆን፤ከ፡እነሱ፡ጋር፥ጥቂት፡አድፍጠህ፡ቆይተህ፥ሰዎቹ፥የሚያደርጉትን፡አድርገው፡ከሄዱ፡በኋላ፤ብትመልስ፡ይሻላላ~ታድያ፥ሌላ፡ምን፡ማድረግ፡እንችላለን፡ብለህ!?”:ሲል፡መከረኝ።

ቀኑን፡ሙሉ፡ሲደንቀኝ፡የዋለው፥የ፡ኩሉሡማ፡እንክብካቤ፡ሲገርመኝ፥የእዚህ፡ልጅ፥ለእኔ፡ነፍስ፡መትረፍ፡መትጋት፡እና፥ሕይወቱን፡አሳልፎ፡መስጠት፡ነበር!። ወደ፡አመሻሽ፡ ላይ፥የከተማው፡ነዋሪዎች፡ለመምሰል፥መልስ፡በማልሰጠው፤የኣፋር፡ቋንቋ፥እሱ፡እየ፡ተናግረ፤`ኹሉሡማ`፡ቅጥር፡ግቢ፡ደረስን።

(ክፍል~)

ቅጥሩ፥መርዶ፡እንደሰማ፡ቤት፥ኩም፣ኩርምት፡ብሎ፡አገኘነው።`ፋጤ`፤ሃገሩን፡ማየት፡የፈራች፡ይመስል፥እናትዋ፡እግርጌ፥ሽቦ፡አልጋው፡ላይ፥ለሽ፡ብላ፡ተኝታለች። `ኹሉሡማ`፡እና፡`ሙሄ`፡ ሲነጋገሩ፥ልክ፥ከተማይቱ፤በጠላት፡ተወርራ፤ማምለጫ፡የሚዘይዱ፡ይመስላሉ። ነገራቸውን፡እንደ፡አበቁ፥በሚገባኝ፡ጥሩ፡ኣምኅርኛ፥ውሳኔአቸውን፤በደንብ፡እንዲያስረዳኝ፡ነገረችው።

በመሰረቱ፥ቀደም፡ብሎ፥`ሙሄ`፡እራሱ፡ከነገረኝ፡ብዙም፡ተጨማሪ፡አልነበረበትም። ግመል፡እየተሰናዳላት፡እንደ፡ሆነ፡እና፥የአሳሾቹ፡ቡድን፥ከተማዋን፡በርብሮ፡እስኪጨርስ፡ድረስ፥ ሙሄ`፡ዘንድ፡አድፍጬ፡እንድቆይ፣`የ፡`ኣሎ`፡መጥፋትም፥ከጥርጣሬ፡ውስጥ፡እንደከተታት`፤አስረዳኝ። ከጨው፡ጠራቢዎቹ፡ጋር፤ወደ፥`ዔርታ~ዓሌ`፡አከባቢ፡ዘወር፡ሊያደርገኝ፡እንደ፡ወጠነ፡ሲነግራት፥ለእኔ፡አዲስ፡ተስፋ፡በመስማትዋ፥ገጽዋ፡ወለል፡ሲል፡ታየኝ።

ጎሕ፡ከመቅደዱ፡በፊት፥እንደ፡አመጣጣችን፤እየተንሾካሾክን፤ወደ፡`ሱቁ`አመራን። እኔ፤ወደ፡ጣርያው፡ወጥቼ፡ዕንቅልፌን፡ስወጣ፥`ሙሄ`፤ጫቱን፡ጎስሮ፥የንፋስ፡ራዲዮውን፡ሲያዳምጥ፡ነጋለት።

ቀኑን፤በሩን፡ሳይከፍት፥ሱቁን፡ዘግቶ፡ዋለ። አመሻሽ፡ላይ፥በጥድፍያ፡የ፡አዘጋጀውን፥የባቄላ፡ንፍሮ፣የፍየል፡ኣይብ፣የቃርያ፡እና፡ቲማቲም፥በ፡ኑግ፡ዘይት፡~`ፉል~መደመስ`፡ነው፡ብሎኝ፥ እየጣፈጠኝ፡ስመገብ፥በሩ፡ተቆረቆረ፡እና፡ሲከፍት፥እራሰ፡በራ፡ሽማግሌ፥ዘው፡ብለው፡ገብተው፥ቁና፡ቁና፡እየተነፈሱ፥ወደ፡እኔ፡በመጠቆም፤አንዳች፡አጣዳፊ፡ነገር፡ነግረውት፥ተመልሰው፡እንደ፡ወጡ፥ወደ፡እኔ፡ዘወር፡ብሎ፡~ “`ሡልዒማን`፥ነገሩ፡አልቍል~ማን፡እንደነገራቸው፡አልታወቀም፥`ኩሉሡማ`፡ግቢ፥የ፡አረፈ፥የ፡ዓሊ~ሚራህ`፡ሰው፡አለ፡ተብሎ፡ተወርቶ፥ፍተሻ፡ሊሰማሩ፡ነው፥ነው፡የሚሉኝ~ ወደ፡`ዔርታ~ዓሌ`፡የሚጓዙት፡ኅማሎች፤ምሽቱን፡ነው፥ጓዝ፡የሚጭኑት፥አሁኑኑ፡ይምጣ፡ብለዋል~በል፡በቶሎ፡ሂድ፡እና፡ተቀላቅለህ~ዓላህ፡እንደሚያደርግ፡ያድርግህ!”፡ሲለኝ፥ጨለማዋ፡መንደር፡ላይ፤በኣናትዋ፡በርኖስ፡ሲደረብባት፡ተአየኝ፡~ ” አይይ!~`ፋጤን`፡እና፡`ኹሉሡማ`ን፡ሳልሰናበት!?”፡ብል፥በግርምት፡ዓይን፤በጎን፡ተመለከተኝ፡እና፡~

” ወይ፡ጉድ!~ምን፡የአለኸው፡ኑርሃል፥አንተየዋ!~እስኪ፡ቀድሞን፤የእራሥህን፡ነፍስ፡አትርፍ!”፡ሲል፡ገሰጸኝ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንጋፋዋ ድምጻዊት ጠለላ ከበደ አረፈች! (1931 - 2014 ዓ.ም)

`ኣያ~መክኑን`፡እየ፡አለ፡የሚጠራቸው፥ቀልጣፋ፡ሸበቶ፡ሽማግሌ፡ተመልሰው፡መጡ፡እና፤በጎን፡ተንሾካሹከው፡ሲያበቁ፥በካኪ፡ጨርቅ፡ከረጢት፡የሞላ፡ቂጣ፡እና፤ኾዳ፡ውሃ፡አስታጥቀውኝ፥ ትከሻዬን፡ስመው፡~” ዓላህ፡ይከተልህ!”፡ብለውኝ፤ወደ፡ጓዳው፡ገቡ።

`ኣያ~መክኑን`፥አንዳች፡ቃል፡የማልሰማውን፡ቋንቋ፡እየለፈለፉ፥ከፊት፡ከፊቴ፥ኩስ፡ኩስ፡እየ፡አሉ፡እየተራመዱ፡ወስደው፥ከመንደሯ፡መውጫ፡ግድም፥ጥቂት፡ግመሎችን፤ከተንበረከኩበት፡የሚያስነሱ፡ዘላኖች፡ጋር፡አገናኝተውኝ፥ዘወር፡ብለው፡እንኳን፡ሳያዩኝ፥ተመልሰው፥ኩስኩስ፡እየ፡አሉ፥በጭለማው፡ውስጥ፡ተሰወሩ።

በጨረቃዋ፡ብርሃን፡እየተመራን፣ጭለማውን፡ሰንጠቀን፡መጓዝ፡እንደ፡ጀመርን፥ኣንጎሌን፡የ፡ወጠረው፡ስጋት፥የ፡አለፈው፡ሕይወቴ፡እና፡ለወደፊቱ፡የመኖር፡ተስፋዬ፡ሳይሆን፥ነግቶ፥ፀሃይቱ፡ስትበራ፡ምን፡ሊውጠኝ፡ይሆን?~የሚለው፥የቁም፡ቅዠት፡ነበር። `ቅዠት`፡መሆኑን፡መካድ፡አልችልም፤ብክደውስ፥ለማን፡እክደዋለሁ!?

መንገድ፡የሚያካሂዳቸው፡አንዱ፡ነዳጅ፥መነጋገር፡ሳይሆን፡አይቀርም። ድምጻቸው፥ለ፡ትንፋሽ፡ፋታ፡የለውም።ከኣምሥቱ፡ጠራቢዎች፡አንደኛው፤ወጣት፡ብጤው፥አልፎ፡አልፎ፥በ፡ሚያበረታታ፥ በጎ፡አስተያየት፡ይመለከተኛል። የተጫሙት፡ሰንደል፥ከ፡ጎማ፡እና፡ከ፡መጫኛ፡የተቀፈፈ፡ሲሆን፥ተረከዝ፡እና፡ፊት፡ቅርጽ፡እንደሌለው፡አስተዋልኩኝ። መሄድ፡መመለሳቸውን፡ማወቅ፡እንዳይቻል፡ ሆኖ፡የተሰራ፤የዘላን፡ጦረኞች፡ዘዴ፡እንደሆነ፥`ሙሄ`፡የአጫወተኝ፡ታወሰኝ።

ኣሸዋው፡እየሳሳ፡መጥቶ፥የሚረገጡትን፡መጠንቀቅ፡እንደጀመሩ፡አስተዋልኩኝ። ብዙም፡ሳንርቅ፥ኣየሩም፣ምድሩም፡እየበጨጨ፡ታይቶ፥ኣንጎል፡የሚፈጠርቅ፤የድኝ፡ሽታ፥ኣፍንጫችንን፡ሰነፈጠን።

የጨው፡መፈልፈያው፡ስፍራ፡እንደ፡ደረስን፡አየሁኝ። `ሙሄ`፥`አይመልስም፡እንጂ፥መስማቱን፡ይሰማል`፡ብሎ፡ስለ፡ዋሸልኝ፥ዘወር፡እየ፡አሉ፡የሚነግሩኝን፥ጭንቅላቴን፡ብቻ፡በመነቅነቅ፡አጸድቃለሁ።

ቆም፡ብለው፥ዙርያውን፡እየተመለከቱ፥የንጋትን፡ብርሃን፡ስርቀት፡በመጠባበቅ፥ከግመሎቹ፡ጭነት፡ላይ፡በአወረዱት፡ጀበና፡እና፡ፊንጃል፤ሻይ፡አደሉን። እዚህ፡ቃጠሎ፡ውስጥ፥ትኩስ፡ሻይ፡አልጠጣም፡ ለማለት፡የሚያበቃ፡መግደርደርያ፡ኅሊና፡ስለ፡አልነበረኝ፥ተቀብዬ፤ገና፡ፉት፡ከማለቴ፥`ኣብሩክ`፡ብለን፡የተቀመጥንበት፡አሽዋማ፡ስፍራ፡ምድሪቱ፤ከስራችን፡ማጉረምረም፡ስትጀምር፥ግመሎቹ፡ እየተወራጩ፡ኣስገመገሙ፣ ዘላኖቹም፡እየተቀባበሉ፡~`ዔርታ~ዓሌ`፣`ዔርታ~ዓሌ`፡ተባባሉ። በዓይነ-ገብ፡እርቀት፥ሠማዩ፥ፍም፡የጋለ፡ምጣድ፡መስሎ፡ይታያል።

የእሳተ~ገሞራው፡እሳት፡ነጸብራቅ፡እና፡ወላፈን፥ሠማዩ፡ላይ፡የጸፈጸፈው፡ቅላት፡መሆኑን፡ተረዳሁ።እሳተ~ገሞራ፤እንዲህ፤በ፡እረዥም፡እርቀት፡ሲያስገመግም፡ይሰማል፡ብዬ፡አልገመትኩም፡ነበር፡እና፡ፈራሁ። በዕውነቱ፡ለመናገር፥ለመጀምርያ፡ግዜ፥የፍርሃት፡ስሜት፡አደረብኝ። ውጋጋኑ፡ይሄንን፡ከመሰለ፥ገሞሩ፡ምን፡ቢሆን!?።

በዝምታ፡መለጎም፣በሥጋት፡መወጠር፡እና፡በፍርኅት፡መያዝ፥ድንዙዝ፣ግዑዝ፡እያደረጉኝ፡ነው። ከተሰነቀልኝ፡የውኃ፡ኮዳ፤ጎንጨት፡ማለቴን፡አላቍረጥኩም፡ነበር፡እና፥ይሄንን፡ይአክል፡መበርከቱ፡ ገርሞኝ፥ኮዳውን፡ከፍቼ፡ብዘቀዝቀው፥ለካስ፡ባዶውን፡አየር፡ነበር፡ስልስ፡የቆየሁት!!።

በእዚሁ፥የጭንቅ፡ጣዕር፡እና፡ነዲድ፡ላይ፡ታክሎ፥አንደበቴ፡ተለጉሞ፡ስለቆየ፡ነው፡መሰለኝ፥መጮህ፡መጮህ፡አሰኘኝ። ማን፡ይሰማኛል?ማንስ፡ይታዘበኛል?፣ማንስ፡ይቆጣኛል?~`የ፡አስጠለሉህን፡ዘላኖች፡መንፈስ፡ግን፥ልትረብሽ፡ትችላለህ~እና፡ይቅርብህ!`፥የምትል፥የተረፈች፡ትንስዬ፡የውስጥ፡ኅሊና፡አከላከለችኝ።

መቼም፥~`አትንጊብኝ!`፡አይባል፡ነገር!~~እና፡ፀሃይቱ፡ልትደርስብኝ፡ነው፡ማለት፡ነው!። እዚህ፥የ፡`ኹሉሡማ`፡ቤት፡ጥላ፡ጥግ`፡የሚባል፡ነገር፡የለ!። ከባሰብኝ፥ግመሎቹ፡ስር፡ እንድሸሸግ፡እጠይቃቸው፡አለሁ`~ይሄም፡እንደማይሆን፡አሰብኩኝ~~`ከደርግ፡ነፍሰ~ገዳዮች፡ብቻ፡ሳይሆን፥ከጸሃይቱም፡የሚሽሽ፡ሰው፡ከሆነ፥ይሄ፡ፍጡር፥ችግሩ፡ሌላ፡ነው`፥ብለው፥ቢያባርሩኝስ?።

ጕዛቸውን፡እንደገና፡ጭነው፥ተነስተው፥ወደ፡ዋናው፤የጨው፡ማዕድን፡ማምራት፡ሲጀምሩ፥የምድሪቱ፡እሩምታ፡እና፡ማጉረምረም፡እየጎላ፡መጣ። የ፡ሠማይ፡ከዋክብት፡ብርሃን፡እየከሰመ፡ሲሄድ፥ የፀሀይ፡ሥርቀት፡እንደቀረበ፡ተረዳሁ።

በጎንዮሽ፡ሲመለከተኝ፡የቆየው፡ልጅ፥ምን፡እንደታሰበው፡እኔ፡እንጃ፥ቀረብ፡ብሎ፡~”የኣሰብ፡ልጅ፡ነኝ፥ ኣምሃርኛ፡መናገር፡እችላለሁ”፡ቢለኝ፥ደረቴን፡አንኳኩቶ፡ልቤን፡የከፈታት፡መሰለኝ፡እና፡ግትር፡ብዬ፡ቆምኩኝ።

“እየተራመድን፡ይሻላል~አይዞህ!~ችግርህን፥`ሙሄ`፡ነግሮኝ፡ነበር፤ከ፡መንደር፡እስክንርቅ፡ብዬ፡ነው፤ዝም፡የአልኩህ”

” አመሰግን፡አለሁ~በነፍስ፡ነው፡የደረስክልኝ~ከ፡አልለመድኩት፡ሙቀት፡ቃጠሎ፡ጋር፡ተዋህዶ፥መንፈሴ፤ሊታወክ፡ተቃርቦ፡ነበር~ይሄንን፡አልደብቅህም!”፡ስል፥በግልጽ፡ተናዘዝኩለት።

“~ችግርህ፥በደንብ፡ይረዳኛል~ከ፡ከተማ፡የሚመጡ፡ሰዎች፡የማይገጥማቸው፡የ፡ፈተና፡ዓይነት፡የለም~`ጨረቃ፥ገጽ፡ለገጽ፡እያጨዋወተችኝ፡ነው`፡ብሎ፤ሸሽቶ፥ወደ፡`ወልድያ`፡የተመለሰም፡ ሰው፥አውቅ፡አለሁ~አንዱማ፥ኣራራው፡ሲብስበት፥ከኣውራ፡ጎዳና፡የቆመ፥የናፍጣ`፡ቦቴ`፡መኪና፡ላይ፡ወጥቶ፥ውኃ፡መስሎት፡ተግቶ፣ተግቶ፡እዝያው፤ፍንግል፡ብሎ፡ቀረ~አይዞህ።” ምንም፡ምን፡ቢለኝ፥የ፡እኔን፥`የፀሃይቱን፡ድምፅ፡መስማት`፡ፍራቻ፡ግን፡አውጥቼ፡ልነግረው፡አልደፈርኩም።

ሰሌናቸውን፡አነጣጥፈው፥`ሶላት`፡ለማድረግ፡መስገድ፡ሲጀምሩ፥ግትር፡ብዬ፡ቢያዩኝ፤እርስ፡በእርስ፡ተያዩ፡~

” አይዞህ፥የመሃል፡ሀገር፡ልጅ፡እንደሆንክ፡ያውቃሉ፡አትሥጋ!” አለኝ።

(ክፍል~፲፩)

“`ዔርታ~ዓሌ`ን፡ወደ፡ጎን፡ትተን፥ጥቂት፡ከተጓዝን፡በኋላ፡ነው፥የጨው፡ማዕድኑ፡መፈልፈያ፡የሚገኘው~ፀሃይቱ፡መበርታት፡ሳትጀምር፡ብንደርስ፥ጓሉን፡ለማፈራረስ፡ይቀልልናል”፡አለኝ፥`ሃሚድ`።

የሚፈላ፣የሚፍለቀለቅ፡የእሳት፡ሐይቅ፣የፍም፡ኩሬ፡ገሞራ፥ማጉረምረም፥ምድሪቱን፡እየናጣት፡ነው። የነበልባሉን፡ወላፈን፡እየገላመጥነው፡ስንጓዝ፡~”ቁፋሮው፤በደህና፡ከሆነልን፥የ፡`ኣይሻዒታ`፡ሽብር፡መለስ፡ሲልለት፤በሰላም፡ወደ፡ቤታችን፡እንመለሳለን~”፡እያለ፤የተስፋ፡ቃላት፡ሲያሰማኝ፥ግመሎቹ፤ድንገት፡መራወጽ፣ማስገምገም፡ቢጀምሩ፥ዓራቱም፡ዘላኖች፥አካፋ፡እና፡ መሰቅሰቅያ፡ዲጂኖኣቸውን፡ሸጓጉጠው፥መሬቱ፡ላይ፡ዦሮኣቸውን፡ደፍተው፡ማዳመጥ፡ሲጀምሩ፥ከምድሪቱ፡ገላ፡የሚሽቱ፥አንዳች፡ነገር፡የአላቸው፡ይመስሉ፡ነበር።

`ሃሚድ`፤ከ፡አንደኛው፡ወደ፡ሌላኛው፡እየተዛለለ፥በነገር፡ሲያጣድፋቸው፡ቆይቶ፤ወደ፡እኔ፡መለስ፡አለ፡እና፡~”`ከ፡አንድ፡ኪሎ፡ሜትር፡በማይሞላ፡እርቀት፡የመኪና፡መንኮራኾር፡ይሰማል፡ነው፡የሚሉት~የደርግ፡ወታደሮች፥የ`ዓሊ~ሚራህ`፡ሠርጎ፡ገቦች፡መስለናቸው፥እየተከተሉን፡ነው!”፡አለኝ። ” ምን፡ልንሆን፡ነው፡ታድያ?”። በመዳፉ፡ዓይኖቹን፡አጥልቶ፥ዙርያውን፡እየቃኘ፡~” በ፡ባህላቸው፥እጅ፡ሰጥቶ፡መታሰርን፡አያውቁም~መንፈሰ፡ነፃ፡ህዝቦች፡ናቸው~እና~ወታደሮቹ፥`እንያዛችሁ` ፡ብለው፡ከቀረቡ፥ተታኩሰው፡የሚሆኑትን፡መሆን፡ነው!”፡ብሎኝ፥ተመልሶ፡ወደ፡እነሱው፡ሄዶ፥ጭንቅላታቸውን፡ገጥመው፡መጨቃጨቅ፡ጀመሩ።

ጠብ፡መንጃ፡እና፡ካራ፡ከኣካላቸው፡ላይ፡የማይወርድ፡ጦረኛ፡ሕዝቦች፥ለደርግ፡ጀሌዎች፡ይማረካሉ፡ብሎ፡ማሰብ፡ዘበት፡ነው። ዓራቱም፥ፈንጠር፡ፈንጠር፡ብለው፥ጎንበስ፡ቀና፡እየ፡አሉ፥በ፡እየ፡አግጣጫው፡ሲመለካከቱ፡ቆይተው፥አመጣጣቸውም፥በእርግጥ፡ወደ፡እኛው፡እንደሆነ፡እና፤እየቀረቡን፡መሆናቸውን፡ነገሩት።

በ፡ቅርባችን፥ምድር፡ለምድር፡የሚያስገመግመው፥የ፡`ዔርታ~ዓሌ`፡ገሞር፥ንዝረት፥በመላው፡ኣካሌ፡ይሰማኝ፡ጀምሯል። ከእነዚህ፡የታጠቁ፡ዘላኖች፡ጋር፡ተይዤ፡ብታሰር፥የሚጠብቀኝን፤ማሰቡ፡ ከንቱ፡ነው።

የፀሃይቱ፡ጨረር፡እና፡ቃጠሎ፡እየ፡አየለ፥የቀድሞው፡ህሥሥታ፡ንግግርዋ፥አሁን፥ልክ፥ኣንጎሌን፡እንደ፡የሚዳሥሱ፡ቃላት፥ቀርበው፡ይሰሙኝ፡ጀመር። ውኃ፡አልቋል፣ተስፋም፡አልቋል፣መሸሻ፡ መንገዱም፡አልቋል። የከበቡኝ፡~ጽንፍ፡የለሹ፡ሃራ፡ሠማይ፣አድማስ፡የለሹ፥የ፡ኣፋር፡በረሃ፣የ፡`ዖዔርታ~ዓሌ`፡እሳተ፡ገሞራ፡እና፥የጦርነት፡ባሩድ፡ናቸው።

አግጣጫው፡ካልታወቀ፡በኩል፥ድንገት፡አከታትሎ፡ተኩስ፡ሲሰማ፥ዓምሥቱም፥ግመላቸውን፡አብርክ፡አድርገው፣ጠብመንጃቸውን፡እየ፡አቀባበሉ፥ከግመሎቹ፡ጀርባ፡ተከልለው፥እኔም፡ እንድከለል፥የ፡እጅ፡ምልክት፡ሰጡኝ።

ለማድመጥም፣ለማሰብም፡የሚችል፡አእምሮ፡አልነበረኝም። የ፡`ዔርታ፡~ዓሌ`፡ገሞር፡ውጋጋን፡ወደሚታይበት፡አግጣጫ፡መሮጥ፡ስጀምር፥”`ሡልዒማን!~`ሡልዒማን!~እሳት፡ ነው!~ሡልዒማን!`”፡የሚለው፥የ፡`ሃሚድ`፡ድምጽ፥ፊቴን፣ዦሮዬን፡በሚጋረፈው፡ትኩስ፡አየር፡እየተቆራራጠ፡ይሰማኛል።

የሚፍለቀለቀው፥የጭቃ፡እሳት፡ኩሬ፡አፋፍ፡ስደርስ፥መላው፡ሰውነቴ፥የጋለ፣የፈላ፥ፍም፡ብረት፡ሆኖ፡ተሰማኝ። የሚፍለቀለቀው፡ገሞር፡ሠማይ፡ላይ፥እንደ፥ኣዋሽ፡ወንዝ፡ዳር፡~የነበርኩበትን፥ ገኒኅተ~በረሃ፡ተሥዕሎ፡ተጸፍጽፎ፡ሲታየኝ፥የ፡`ፋጤ`፡አስተናገር፡ድምጽ፡ማሚቴው፥ከመላው፡ሰውነቴ፡ማስተጋባት፡ጀመረ፡~ ~”`ዓሞ~ኢሳ!ደንቲ~ታሳ!~ሱጫ!ሳቦ~ቤሬ!`”።

የተኩስ፡ልውውጥ፡እንደጀመሩ፤በመሃሉ፥እንደ፡ፉጨት፡እርቆ፡ይሰማኛል። የሰው፡ኣንጎል፡አብቅቶለት፡ሲከስም፤ልብ፡በፈንታዋ፡

ማሰብ፡ትጀምር፡ይመስል፥`ከ፡እሳተ፡ገሞራው፡ሠማይ፡ላይ፡ተጸፍጽፎ፡የማየው፡`ገኒኅተ~በረሃ`፥የ፡እስትንፋሴ፡የመጨረሻ፡ሥርቅታዋ፡ሥዕል፡እና፥የውሃ፡ጥሜ፡ዕብደት፡መለያ፡ይሆን?`፡አልኩኝ።

በተኩስ፡ልውውጡ፡መሃል፥ጩኸት፡እና፡ማጓራትም፡እየቀረበኝ፡ሲመጣ፥እየተሳደዱ፡እንደሆነ፡ገመትኩኝ። የገሞሩን፡እሳት፤ፍም፡የሚፍለቀለቅ፡ጭቃ፡ኩሬ፥ዙርያ፤ቁልቁል፡ስመለከት፥ እኔም፡ፍም፡የሆንኩኝ፡መሰለኝ።

ወደ፡ኋላ፡ጥቂት፡አፈግፍጌ፥እየተንደረደርኩኝ፥ጅው!~፡ብዬ፡ወደ፡ገሞር፡ውስጥ፡ስዘልል፥ቦታ፡እና፡ግዜ፡የማትመርጠው፥የፀሃይቱ፡ድምጽ፡”አለሁልህ!”፡ስትል፥በ፡እዝነ~ነፍሴ፡ሰማኋት።

ማስተዋወቂያ፤

ይህን ለመጀመሪያ ጊዜ የምናትምለትን “ዔርታዓሌ ወበእንተ ነገራ ለድንቂቱ” በሚል ርዕስ ባቀረበው ትርክት `ጃህእርሥዎ፡ሞትባይኖር፡ኪሩብ፡ዔል`፡~ በሚል መጠሪያ ቢጠቀምም ፣ በተለምዶ ስሙ “ጃርሶ ኪሩቤል”ተብሎ የሚታወቀው ይኸው ደራሲ፣ ፀሐፊና ተራኪ፣ በኪነ~ጥበብ ሙያ እና በ( ዔዞቴሪክ~ሳይንስ)ኅቡዕ የነገረ-ሰብ ጥናት እና ምርምር ላይ የተሰማራ ሰው ነው። በርካታ ጽሑፎቹ በ `ጀርመን ራዲዮ`ጣብያ እና በ`ሸገር ራዲዮ` ተተርከው ለአድማጭ የቀረቡ ሲሆን `ሩኅ` እና ሌሎችም መጽሔቶች ካተሟቸው በርካታ ተረክዎቹ በተጨማሪ ሁለት የተረክዎች መድብል ማለትም`አስኮ ጌታሁን` እና`ከደመናው በላይ` የተሰኙትን መጻሕፍት ለኅትመት አብቅቷል።

ቀደም ባሉት ዘመናት የ `ኢህአፓ` ድርጅት አባል ሆኖ በየተለያዩ ደረጃዎች አገልግሏል። በአብዪቱ ዘመን ባቀረባቸው ቀስቃሽ ሥነ ጽሑፎች ከተጠቀመባቸው የብዕር ስሞች አንዱ “ዲማ” የሚል መጠሪያ ነበር። በርካታ የሥዕል፣ የማኅሌት፣ የሥነ~ጽሑፍ እና ጥናታዊ ስራዎቹ እና የእንግሊዝኛ ጽሑፎቹ ቀናቸውን እየጠበቁ ይገኛሉ። አሁን ነዋሪነቱ በሎንደን ከተማ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዝክረ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ - ቀሲስ አስተርአ

አንባቢ እንዲገነዘብ የምንሻው ጃርሶ ባቀረበልን በዚህ ጽሑፍ የተጠቀመባቸውን የነጥብ ሥርዓቶች በተለይ ሁለት ነጥቦችን በየቃላቱ መጨረሻ ላይ የማስገባት ዘዴ፣ ጥንት ጽሑፎች በእጅ ይጻፉ በነበረ ጊዜ (አሁንም ባንዳንድ ቦታዎች እንደሚደረገው) ጥቅም ላይ የዋለ ነው። ደራሲው ለምን ይህን ዘዴ መረጠ የሚለውን እርሱ ራሱ እንዲመልስ እንተወዋለን።

“`ዔርታ፡ዓሌ፥ወበእንተ፡ነገራ፡ለ`ድንቂቱ`ተረክ ጭብጡ ዕውን ላይ የተመሠረተ ታሪክ ነው” ሲል ደራሲው ገልጾልናል፤ “መታሰብያነቱ፥ታሪኩ፡~በነፍሥም፣በስጋም፤ለሚመለከታቸው፥ሕያዋን፡እና፡ሰማዕታት፡ኢትዮጵያውያን፡ሁሉ፡ይሁንልኝ” በማለትም ጽፎልናል። መልካም ንባብ።

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share