September 27, 2023
2 mins read

ትግስት አሰፋ የሮጠችበት ዐይነት አዲዳስ በ500 ዶላር መሸጥ ጀመረ

Tigist Assefa 1 1የአዲዳስ አዲሱ ጫማ የሆነውና፣ ባለፈው እሁድ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትግስት አሰፋ በበርሊን የማራቶን ሬከርድ የሠበረችበት ዐይነት ጫማ፣ ትናንት ማክሰኞ በ500 ዶላር ዋጋ ገበያ ላይ መዋል ጀምሯል።

የሩጫ ጫማ ገበያውን ለመቆጣጠር ከናይኪ ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ ላይ ያለው አዲዳስ፣ አዲስ ያቀረበው ‘አዲዚሮ ፕሮ ኢቮ 1’፣ ናይኪ ካቀረበው ‘አልፋ ፍላይ 2’ ዋጋው በ 225 ዶላር ይበልጣል። አማተር ሯጮች ጫማውን ለመግዛት ተጨማሪውን ዋጋ ለመክፈል ፍላጎት ያሳዩ እንደሁ ይታያል ሲል ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

አትሌቶች በተሻለ እንዲሮጡ ለማስቻል፣ ሶሉ ወፈር ያለ እና ለስላሳ እናዲሁም ከካርበን ፋይበር የተሰራ ንጣፍ ያለው ጫማ መመረት ከጀመረ አንስቶ፣ ሁለቱ የጫማ አምራቾች ከፍተኛ የንግድ ፉክክር ውስጥ ቆይተዋል።

አዲሱ የአዲዳስ ጫማ በጣም ቀላልና ክብደቱ 138 ግራም እንደሆነ እንዲሁም የሚያገለግለው ለአንድ ማራቶን ሩጫ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል። ሯጮች ለእያንዳንዱ ማራቶን አዲስ መግዛት እንዳለባቸው ኩባንያው አስታውቋል።

ጫማው ለፍጥነት እንጂ ለረጅም ግዜ ለማገልገል እንዳልተሰራ የገለጸው አዲዳስ፣ ትናንት ማክሰኞ 521 ጫማዎችን ለገበያ አቅርቧል። ተጨማሪ ጫማዎች በሕዳር ወር ለገበያ እንደሚቀርቡም አስታውቋል።

አዲዳስ ጫማው ሬከርድ ሰባሪ እንደሆነ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። ከትግስት አሰፋ ጋር አዲሱን ጫማ ይዘው የተነሱትን ፎቶ በኢንስታግራም ያጋሩት የኩባንያው ዋና ሥራ ስፈጻሚ ቢዮርን ጎልደን፣ “ትግስት አሰፋ እንኮራብሻለን!” የሚል ጽሁፍም አክለውበታል።

VOA

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop