ሰሞኑን የአድስ አበባ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአድስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሠጠው ሽልማት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ ) የማይመለከተው መሆኑን እንገልፃለን !!
አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሠጠው ሽልማት
ፓርቲያችን የመላው ኢኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ ላለፉት ከ፫ አሥርት ዓመታት በላይ በሰላማዊ ትግል ላይ በፅኑ አቋም ተመሥርቶ እና ሰላማዊ ትግል የሚያስከፍለውን ዋጋ ተረድቶ ጉዞውን እስከ ቀራንዮ አደባባይ የሚያደርስ ፅናት ይዞ እየታገለና እያታገለ ያለ ፅኑ አቋም ያለው ፓርቲ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያውቀዋል። ለዚህም እማኛችን በትግሉ ሂደት ለዓላማቸው ሲሉ ውድ እና አይተኬ ሕይወታቸውን ቤዛ አድርገው ያለፉ ፣ በእሥር ሲሰቃዩ የቆዳቸው ቀለም ተቀይሮ አካላቸው የጎደለ ፤ ብሎም ዘር መተካትና ንብረት እንዳያፈሩ ሥራ የተከለከሉ በሕዝባችን በጉልህ የሚታወቁና የማይታወቁም ጭምር የትግሉን ሻማ ለኩሰው በአደራ የሰጡን እናት አባቶቻችንና እህት ወንድሞቻችን ሕያው ምስክሮቻችን ናቸው። በመሆኑም ዛሬ ሕዝባችን የበለጠ እንድንታገልና እንድናታግለው በሚፈልገን ጊዜ የምን መተጣጠፍና መለጣጠፍ!? በፍፁም መኢአድ ይሄንን ለማድረግ ሞቶ እንኳን እንደማያደርገው ሕዝባችን እንዲረዳልን፤
ታዲያ ሰሞኑን የተፈጠረው ምንድነው? ሰሞኑን የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምንን አስመልክቶ እንደሸለመ ባናውቅም ለብልፅግናዋ የአዲስ አበባ ከንቲባ ፎቷቸውን አሳትሞ (አስቀርፆ) ሲሸልም የሚያሳይ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ መዘዋወር አየን በዚህ ምስል ላይ የእኛ አመራር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አበበ በምስሉ ላይ ሽልማቱን ሲያበረክቱ ይታያል በዚህም የተነሳ የመላ አባላቱንና ደጋፊዎቻችንን ስሜት ለቁጣ ዳርጓል አስከፍቷልም። ይህ የመኢአድ አቋም ሊሆን መቼም አይችልም አይደለምም። ግለሰቡ በግላቸው ኃላፊነት ይወስዱበታል። በፓርቲ ውስጠ ደምብም በዲሲፕሊን የሚጠየቁበት ይሆናል። መኢአድ ግን በምንም ሁኔታ ከማንም ጋር አይሞዳሞድም!። ያሳለፈው ታሪኩም ይሄንን አይታገስም። አሁን እየመሩት ያሉት መሪዎቹም ያለፉትን ዓመታት በፓርቲው ውስጥ ቆዳቸው ተልጦ ሌላ ቀለም እስኪያወጡ ዋጋ የከፈሉ ቆራጥ ልጆቹ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ በታየውና በሆነው ነገር ለተበሳጫችሁ ደጋፊዎችና አባላት፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ስሜት በመዳረጋችሁ እጅግ የበዛ ይቅርታ እንጠይቃለን? እየደወላችሁ ቁጣችሁን ለገለፃችሁ በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን።
“አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!”
ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም
አዲስ አበባ
