fzqrxx wwamrwol
(ሁለቱም አካላት በጉልበት በሚቆጣጠሯቸው ሀገራት ምክንያት ጦርነቱ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም ሊባል ይችላል። ሕዝቡን ሳይወድ በግድ ወደ ጦርነት የማስገባት ችሎታ ስላላቸው፣ ጦርነቱ የሚጎዳውም በማዶና በማዶ ያለውን ሕዝብ ስለሆነ፣ የሚነሳውም ጦርነት በ”ዓለማቀፍ ማሕበረሰብ” ተብዬው እንደ ሀገራት ጦርነት ስለሚታይ፣ ስለሚወሰድ ማለት ነው። በሌላ በኩል የውጭ ላኪና አሰማሪ ቢኖራቸውም በነዚህ አገራት ውስጥ ግን ፈላጭ ቆራጮቹ ግለሰቦች ስለሆኑ ጦርነቱ የአቢይና የኢሳያስ ጦርነት ቢባልም ያስኬዳል።)
አንድ ታካሚ ሐኪም ለማየት ሲሄድ በወቅቱ የሚወስዳቸውን ሌሎች መድሐኒቶች፣ የጤንነቱን ሁኔታ፣ ሌሎች ተጓዳኝ ሕመሞችን፣ የአልኮልና ሌሎችም ደባል ሱሶችን እንዲዘረዝር ይጠይቃል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሚሰጠው ቅጽ ላይ ያለፈ ታሪኩን ይሞላል። ከዚያም አልፎ የወላጆቹን እና የአያቶቹን የጤና ሁኔታም ይጠየቃል። በዘር ስለሚተላለፉ በሽታዎች ስእል ለማግኘት ስለሚሞከር። የኛንም ግጭቶች ወይም ጦርነቶች መነሻ ሳንዳስስ ዛሬ ላይ ብቻ ተገድበን መንስኤውን ልናገኝ መፍትሔውን ልንጠቁም አንችልም። በዚሁ መንፈስ እንቀጥል።
እዚህ ላይ አንባቢ ድኅረ ፕሪቶሪያ ሕወሃት ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት እንድትፈጥር ለሕወሃቶች ሃሳብ ያቀረበም የፈቀደላትም አቢይ አህመድ የመሆኑን መረጃ እያስታወሰ ይጓዝ።
ይህ ጦርነት የሚካሄድበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? የትኛው መላምት ነው ለእውነቱ የሚቀርበው?
- ተፈጥሯዊ ጦርነት?በኤርትራ አፈጣጠር እና ተፈጥሮ ላይ ያተኮረ መላምት ነው። ኤርትራን ጣልያን ከፊል የኢትዮጵያን መሬት በወረራ ይዞ የፈጠራት ሀገር መሆኗ ይታወቃል። ከዚያ በፊት ኤርትራ የቀይ ባሕር ስም እንጂ የሀገር ስም አልነበረም። ይህ የመጀመሪያው መላምት ከመነሻውም ኤርትራ በጣልያን (እና እንግሊዝ) ስትፈጠር ራሷን የቻለች ሀገር እንድትሆን ታቅዶላት ሳይሆን ትልቋን ኢትዮጵያን ለማፈኛ፣ ለማወኪያና ከዚያ ተነስቶ ጠቅላላ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር ተብሎ የተመሠረተች ከመሆኗ ጋር የተያያዘ መላምት ነው። ለዚህም እንደ ማስረጃ ጣልያን አጋጣሚውን ሲያገኝ ኤርትራን እንደቤዝ ተጠቅሞ መላ ኢትዮጵያን በመውረር ኤርትራንም ቀላቅሎ ለመግዛት እንደሞከረ ማስታወሱ ይበቃል። ማፈኛ የሚለው አባባል ደግሞ የኤርትራ ጂኦግራፊ ሲፈጠር ለርሷ እንደትርፍ አንጀት የሆነውን አሰብን ጭምር አካትቶ እስከጂቡቲ ድረስ ባሕሩን እንዲዘጋ ተደርጎ መሆኑንን ለመጥቀስ ነው። እንግዲህ ኤርትራ በፊትም የጣልያን ገንዘብና ሃብት የሚያስተዳድራት የጣልያን የጦር ሰፈር ሆና የተቋቋመች ስትሆን በኋላም ከተቀረው ኢትዮጵያ ጋር ሆና እንጂ ብቻዋን ራሷን ችላ ለመኖር የሚያስችላት በቂ የተፈጥሮ ሃብት የላትም። ሕዝቡም በአርቲፊሻል የተለያየ እንጂ በአብዛኛው አንድ ላይ የኖረ አንድ ሕዝብ ነው። በሁለቱም ወገን ያለው ሕዝብ ሰፊ ከሆነው አገሩ ላይ ነው የተቀነሰው። ኤርትራ ሕዝቧ እንጀራና ሌላ ፍለጋ እየፈለሰ እስከመቼ ትኖራለች? በኢትዮጵያም በኩል ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር እስከመቼ ትኖራለች? ኢትዮጵያን ለማዳከም ለማፈን ሆን ተብሎ የተሠራ ነበር። ኤርትራም ራሷን እንዳትችል፣ ኢትዮጵያንም እንድታፍን፣ በዚህም ሁሌም ወደ ግጭት እንዲያመሩ ተደርገው የተቀመጡ ሀገሮች ናቸው የሚል ነው መላምቱ። ይህ እንግዲህ ወያኔ ካደረገው ሀገር የማስገንጠል ሂደት ጋር ተያይዞ አቢይ አህመድ በአብኖች አፍ በመናገር ጥያቄ ካነሳበት የኤርትራ መገንጠል (ነጻ ሀገር መሆን) ሂደትም በፊት ስለነበረው ታሪካዊ ጉዳይ የሚተነትን ነው። በዚህ መላምት የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪ ማንም ሆነ ማን ሁልጊዜ ወደ ግጭት ማምራታቸው አይቀርም። መስከረም አበራ (የነጻነቷን ቀን ያቅርበውና) የዲዛይን ችግር የምትለው ዐይነት ነገር ነውና።
- የጥቅሴ ጦርነት?ከላይኛው መላምት አኳያ ኤርትራ ራሷን ሙሉ በሙሉ የሚያስችላት ቁመና የላትም። በተለይ በምግብ። ኢትዮጵያም ወደብ ፈላጊ ናት። ሁለቱን ሕዝብና የሁለቱን ሕዝብ ፖለቲከኞች አሳምኖ ለኢትዮጵያ ወደብ ለኤርትራ ደግሞ የእርሻ መሬት መስጠት የሚቻል (በቀላል ተግባራዊ የሚደረግ) አይደለም። ስለዚህ መሪዎቹ ተጠቃቅሰው ጦርነት ያደርጉና ሻዕቢያ ወልቃይትን ሲይዝ አቢይ አሰብን ይይዛል። ዓለማቀፍ አስታራቂ፣ ሰላም አስከባሪ ወዘተ እንዲምቦጫረቅበት ያደርጉና ያም ወደቡን ያም ወልቃይትን ይዞ እንዲቀር “ያስማሟቸዋል”። ሕዝቡ እንዲቀበለው አንድ ሦስት ሚልዮን አበሻ እምሽክ ይደረጋል። ምናልባት ጎንደር፣ መቀሌና ባሕርዳርም እንደምርቃት (ተጨማሪ ማስደንገጫ) ይወድማሉ። በኤርትራም በኩል እንዲሁ።
- ኢሳያስ አፈወርቂን በአዲስ አሻንጉሊት ለመተካት?አሜሪካኖችና ምዕራባውያንን (ከ1970 እስከ 2025) ለሃምሳ አምስት አመታት ያገለገለው ኢሳያስ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ ስለማይታሰብ ወዲ አፈወርቂን የነሱን ጥቅም በሚያስጠብቅ ሌላ አዲስና ወጣት አሻንጉሊት የመተካት የቤት ሥራቸውን ለመሥራት ማለት ነው። ይሄን በሙሉ ልብ አልሄዱበትም እንጂ ፍላጎቱ እንዳላቸው ብዙ የሚያሳብቁ ነገሮች ነበሩ። በተለያዩ ሀገራት ደጋግመው የፈጸሙትም ተግባር ነው። እዚህ ላይ ኢሳያስ በሁሉም ጉዳይ ተላላኪያቸው፣ ታዛዣቸው ነው ለማለት ሳይሆን ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ በቀይ ባሕር ላይ ያላቸውን ጥቅም ማስጠበቂያ ሆኗቸዋል ለማለት እንጂ ብዙ የሚቆረቁራቸው አጋር መሆኑን ለመካድ አይቻልም። ይሁንና በተለምዶ ፍጹም ቢመቻቸውም እንኳን አጋራቸው ሲሸመግል በሌላ ባልጠበቁት ሰው እንዳይተካ የራሳቸውን አሻንጉሊት ለማስቀመጥ ይንቀሳቀሳሉ።
- ወታደራዊ አቅምን ለማንኮታኮት?ትንሽ ሀገርም ብትሆን በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ትልቅ ወታደራዊ ልምድ ያካበተችውን ኤርትራን ከዚህም ጋር ወታደራዊ ልምድ ያለውን ሕወሃትንም ዱቄት በማድረግ የምሥራቅ አፍሪቃ ቀጠናን መፋቂያ ብቻ በታጠቁ ነጭ መቼም ቢሆን መጥቶ በቀላሉ ሊቀዝንባቸው በሚችሉ እንኩቶዎች ለመተካት። (ይቅርታ ለቃላት አጠቃቀሜ) ይሄንን ስል አንባቢ ሊያስተውለው የሚገባው እያነሳሁ ያለሁት የኢኮኖሚ አቅምን ሳይሆን፣ ያለፈበትም ቢሆን የተለያየ መካናይዝድና ሽምቅ ውጊያን ማካሄድ የሚችል ከቀዝቃዛው ጦርነት ሲያያዝ የመጣን ወታደራዊ አቅም ዱቄት ማድረግ የመፈለጋቸውን ጉዳይ ነው። ምክንያቱ ደግሞ መሣሪያ አቅራቢ እስከተገኘ ድረስ ይህ ዓይነት እምቅ አቅም ያለው አካል ዘረፋቸውን ተቃውሞ ከቆመ/ቢቆም በአርጩሜ ብቻ እየገረፉ ለመግዛት እንቅፋት የመፍጠር እድል ስላለው ነው። ቡርኪናፋሶን መመልከት በቂ ነው።
- ምሥራቅ አፍሪካን አፍርሶ ለመሥራት?ይህ በእንግሊዞች ታቅዶ ጀብሃና ሕወሃት የተፈጠሩበት ኤርትራን በእስላማዊ ቆላ እና በክርስትያን ደጋ ከፋፍሎ ደረቁን ደጋ ከትግራይ ጋር ነጻ አገር የማድረግ፣ ለመስኖ ተስማሚውን ቆላ ደግሞ ገንጥሎ ከሱዳን ጋር ደርቦ ለእንግሊዝ የቀጥታም ሆነ የእጅ አዙር ቅኝ ማመቻቸትን ያለመው እሳቤ ነው። በተለምዶ ትግራይ ትግሪኝ የሚባለው ማለት ነው። ይህ እቅድ ኢትዮጵያንም ኤርትራንም እንደሚያፈርስ ልብ ይሏል። ባላፉት ሥልሳ አመታት ለዚህ ዓላማ የሚያስፈልጉ ግብአቶች ሁሉም በየደረጃ እየተሟሉ እዚህ ደርሰናል። ትልቁ እንቅፋትና ያልተሟላ የነበረው የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያዊነቱ ያለው ከፍተኛ ስሜት ነበር። ይህ ስሜት አሁን ካላፉት ሃምሳ አመታትም በተለይ ባለፈው ጦርነት በደንብ ተሠርቶበት ወደ ሚፈለገው ደረጃ ወርዷል ተብሎ እየታሰበ ነው። ለዚህ የምሥራቅ አፍሪካ ብተና ብልጽግና (ኦነግም) ተባባሪ እንደሚሆን እሱም ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ኦሮሚያ ሪፐብሊክን ለመገንጠያ እድል እንደሚያገኝ ይገመታል። ኢትዮጵያን ደጋግሞ በመካድና በመክዳት የሚታወቀው አቢይ አህመድ ለነገው ትውልድ የሚበጅ ለኢትዮጵያ ብሎ የሚያደርገው አንዳችም ነገር አይኖርም። አሰብ አሰብ እያለ የሚያላዝነበት ምክንያት ይሄንን ትንኮሳ በመፍጠር ቀጠናውን ወደ ጦርነት አስገብቶ የብተናውን መንገድ ለማመቻቸት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። አቢይና ኦሮሙማ ለኦሮሚያ የሚመኙላት ወደብ ሌሎች ሕዝቦችን ተጠቃሚ የማያደርግ ከባሕር ተነስቶ ኦሮሞ በሰፈረበት መሬት ላይ ብቻ በሚሄድ መንገድ ወይም ሃዲድ ብቻ የምትገናኝ ወደብን እንደሆነ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው።
- ለትራምፕ የኖቤል ሽልማት ለማስገኘት?ይቺ የምታስቀው ብዙ ሰው ይኖራል። ነገር ግን እንደሽመልስ አብዲሳ በፎልፏላነቱ የሚታወቀው ትራምፕ ባለፈው የፕሬዝዳንትነት ዘመኑ ለርሱ የሚገባውን የኖቤል ሽልማት ለአቢይ አህመድ እንደለቀቀለት ተናግሮ ነበር። ሁለት አገሮችን ከመተላለቅ በማስቆም ትልቅ ጦርነት አስቀርቺያለሁ አላለም! ገና እኮ አገሮቹ ወደ ጦርነት ቀርቶ ወደ ትንኮሳም ባልገቡበት ዘመን ነው። ሰውዬው ተደናብሮ ለወደፊት የተቀመጠለትን ቃል ነው አስቀድሞ የዘባረቀው ያስብላል። ምናልባት ኤርትራና ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት አፋፍ በመግፋት ከዚያም ትራምፕ ጣልቃ ገብቶ (ያው ብር ለቆባቸው) እንዲያስታርቅ በማድረግ ይሄንን የቋመጠለትን የኖቤል ሽልማት ለማሰጠት የምትደረግ ግርግርም ልትሆን ትችላለች። እውነት ትራምፕ የሽልማቱን እድል ለአቢይ ለቅቆለት ከነበረ አቢይም ውለታውን መመለስ ይኖርበታልና። የእነዚህን ሁለት በሽተኞችና ናርሲሲቶች የእብደት መጠን ማቃለል፣ ወይም ማናናቅ አይገባም።
- የአፍሪካን ሕዝብ ቁጥር የመቀነስ ዘመቻ አካል ይሆን?የአፍሪካ ትውልድ እየበዛ፣ እየበለጠንም ነው ብለው በሚቃዡ ግዙፍ ኃያላን፣ ሃብታሞች፣ ተቋማት ወይም መንግሥታት የሚደገፍ የሕዝብ ቅነሳ አጀንዳ አካል ሆኖ የሚከሰት ጦርነት ነው የሚል መላምት። ማብራሪያ አይሻም።
- የንቅለ ተከላ ዘመቻው አካል?በአፍሪካ ላይ ለመጫን የሚፈልጉትን አዲስ ባህልና ማንነት በበቂ ሁኔታ ለመጫን ያልተመቻቸው፣ ለሁለንተናዊ ፍልሰት (ባህላዊ፣ ቁሳዊ፣ ርስታዊ፣ ታሪካው፣ መንፈሳዊ) በመዳረግ ይሄንን አዲስ ማንነት የሚጭኑበት መደላድል ለመፍጠር የሚፈልጉ ኃይላት ዘመቻ አካል ይሆን? ይህ መላምት አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣ ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ የዋለውን እረፍት የሚነሳ የሾክ ቴራፒ (Shock Therapy) ዘመቻ የሚመለከትና መጪውን ጦርነት እንደተጨማሪ የዚህ ሽብር አካል አድርጎ የሚያይ ነው። የማፍለስና የመውረስን ተግባር በመብረቅ ፍጥነት ለማካሄድ ያለመ እንቅስቃሴ ነው። በዚህ የ7 አመታት የሾክ ቴራፒ ዘመቻ ላይ ሙሉ ራሱን የቻለ ጽሑፍ ማቅረብ ተገቢ ነው።
- ኦርቶዶክስን የማዳከም፣ ተቋማቷን የመዝረፍ፣ ሕዝቡን የማመናመን፣ አማኙን የመበተን እቅድ?ከመላምት ስምንት ጋር ተቀራራቢነት ያለው ነው። በጦርነቱ በዋናነት የሚዘምቱትም ሆነ የጦርነት ቀጠናው የሚያርፍበት አካባቢ የኤርትራ፣ ትግራይና አማራ ክልል ነዋሪዎች ቀጠና የተዋሕዶ ምእመናን ከፍተኛ ቁጥር ያለበት እንደመሆኑ ይህንን ሕዝብ ከማጥቃት አልፎ ዳግም ደም ለማቃባት እና ዘላቂ ቂም በቀል ለመተው ባጠቃላይ ለማዳከም ያለመ ጦርነት ነው። ይሄንን ዐይነት ጦርነት ለመደገፍ ከምእራቡም ሆነ ከቱርክና፣ ከአረቡ በኩል ችግር አይኖርም።
- ለቀሪው የሃብት ቅርምት(የንግድ መስመርም ይሁን፣ የማእድን ሃብትም ይሁን ሌላ) እንዲመች ሀገራትን ወደ የጎበዝ አለቆች መንደሮች የመቀየር ፍላጎት አካል? የካፒታሊስት ሥርዐቱ በዓለም ዙሪያ ለመቀራመት የሚችለውን ነገር ሁሉ ተቀራምቶ ያልተቆጣጠራቸው ጥቂት ነገሮች ይቀሩታል። የተቀረውን ለመቀራመት በመቅበዝበዝ ላይ ይገኛል። ለዚህም ፍላጎቱ 3ኛውን የዓለም ጦርነትን ሊያስነሳ ይችላል የተባለ ጦርነትን (የሩሲያ ዩክሬይን) እስከማቀጣጠል ድረስ በጭካኔ ሄዶበታል። ከዚያ ሁሉ እልቂት በኋላ ዋነኛ መዳረሻ ፍላጎቱ የዩክሬይንን ማእድን መመዝበር ሆኖ እንደተገኘ አንባቢ ልብ ይበል። በኤርትራ፣ በትግራይና በተቀረው ኢትዮጵያ ያሉ ወርቅና ሌሎች ማእድናትን በጎበዝ አለቆች አማካኝነት ለመበዝበዝ የሚደረግ የፍርሻ ጦርነት። ከመላምት አራት ጋር ይቀራረባል። በምዕራብ አፍሪካ እየታየ ያለው መነቃቃት በዝባዦቹ ምሥራቅ አፍሪካ ላይ እንዲረባረቡ ግፊት የፈጠረ ይመስላል።
- ኦህዴድና ሕወሃት ከገቡበት የቅቡልነት አጣብቂኝ ለመውጣት?ኦህዴድ ይሄንን ጦርነት ከፍቶ ፋኖ ከተነሳ ወዲህ ድምጥማጡ የጠፋውን ቅቡልነቱን እንዲያንሰራራ ለማድረግ፣ ፋኖን ደግፎ የቆመውን ኃይል ለማዳከም፣ ለመበታትን፣ ሀገር ማስተዳደር አቅቶት ያደረሰውን ድቀት በጦርነት ለመሸፈን፣ ባጠቃላይ ተቃዋሚዎቹን የበለጠ ለማጥቃት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር። በሕወሃት በኩል ደግሞ፣ ሕወሃትም ከገጠመው የፖለቲካ ኪሣራ መውጫ፣ ከተጠያቂነቱም የማምለጫ ሁከትን ፍለጋ። ይህ መላምት በሻዕቢያም በኩል ከተቃውሞ አኳያ ብርጌድ ንሃመዱን ለመምታት ከተጠያቂነት አኳያ ደግሞ ምናልባት ባለፈው ጦርነት ከመጣበት ተጠያቂነት በሕወሃት አማካኝነት ነፃ ለመሆን ሊያልም ይችላል። እንግዲህ ሦስቱም አካላት ቅቡልነት ለማግኘት፣ ተቃውሞን ለማፈን ከተጠያቂነት ደግሞ ለማምለጥ በመሻት ጦርነትን ይፈልጉታል ማለት ነው። [አቢይ አህመድ የወንጀል አቻ የመፍጠር ስልትን ይጠቀማል። ወንጀልን በወንጀል ያጣፋል። ለዚህም እሱ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ ሕወሃት በአማራና አፋር ላይ እንድታደርስ ሁኔታውን አመቻችቶላት ነጭ ጅብ ስትለው ጥቁር ጅብ ለማለት ተመችቶታል። አሁንም በትግራይ ሰዎች የሚከሰስበትን ባእድ አገር ጋብዞ ወገንን ማስፈጀት የሚል ክስ ሕወሃቶችም ያንኑ ባእድ ሀገር ጋብዘው ወገንን የሚያስፈጁበትን ቦይ ቀዶላቸው ባንዳ ሲሉት ባንዳ ብሎ ለመመለስ እያመቻቸ ይሆን? ድኅረ ፕሪቶሪያ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ የመከረና የፈቀደላቸው መጀመሪያውኑ እሱ እንደሆነ ልብ ይሏል።]
- ከነዚህ በተጨማሪ በውክልና ካልተዋጉ በስተቀር ኦህዴድም ሆነ ሻዕቢያ (ሕወሃትም ጭምር) አቅማቸው የተንኮታኮተ በመሆኑ ለጦርነት ከበሮ ድለቃቸው የቱርክና የአረቦችን ከቀይ ባሕርና ሕንድ ውቅያኖስ፣ ከወርቅ፣ ከእርሻ መሬትና ከመጠጥ ውሃ ጋር የተያያዙ ፍላጎቶችና ወቅታዊ አሰላለፎችን ያካተቱ ሌሎች ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። የተላላኪ ተላላኪ ሆነው ማለት ነው። አንድ እርግጠኛ ነገር ግን ግብጽን በተመለከተ በአባይ ነገር ከአቢይ አህመድ አሊ የተሻለ ጉዳይ አስፈጻሚ አገኛለሁ ብላ እንደማትደክም ነው። በቃልም በተግባርም ታይቷልና።
ብዙዎቹ መላምቶች ተመጋጋቢ ቢሆኑም በበኩሌ በእንግሊዝ መንጋጋ ውስጥ እንዳለች ነፍስ፣ ወይም በእንግሊዝ ባሕር ውስጥ እንዳለች ደሴት ለማያት ኢትዮጵያችን በአምስተኛ ተራ ቁጥር የሰፈረው መላምት (5) ዋናው የጦርነቶቻችን እና ግጭቶቻችን ማጠንጠኛ ይመስለኛል። ጦርነቱ ከመቶ አመት በላይ የዘለቀው ኢትዮጵያን ከቦና አድቅቆ የሚዋጠውን የመዋጥ፣ የሚጋጠውን የመጋጥ፣ አጥንት የሆነውን የመጣል ሤራ አካል መሆኑን በመረዳት። አንባቢ ሀገራችን ዙሪያዋን ድንበር የተዋሰነቸው ከየትኛው መንግሥት ጋር እንደነበር ያስተውል። የ’ኢትዮጵያ ቢቲኔስና’ው የኦነግ ኮንፈረንስም ሆነ የቀደመው የነኮህን የሀገር ብተና ኮንፈረንስ ለንደን ላይ መደረጉ ተራ አጋጣሚ አይደለም። የአፄ ዮሐንስ፣ የተፈሪ መኮንን፣ የመለስ ዜናዊ (የአቢይ አህመድ?) ሥልጣን በነዚህ ሰዎች መራጭነት የተደላደለ መሆኑንም አንዘንጋ።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ። በአቢይ አህመድ ላይ (እሱም ራሱ ጦርነት ነው) ሌላ ጦርነት? በዚህ ቁርቁዝናችን ላይ ቀጠናዊ ጦርነት? ከዚህ ይሰውረን፣ ሕዝባችንን ይሰውረው። ረሃብ፣ ስደት፣ የውክልና ጦርነት፣ ቁርቁዝና፣ ውድመትና ከባህል፣ ከእምነት፣ ከትውፊት መፈናቀል፣ ስደት ወዘተ ከበቂ በላይ ያደቀቀን ሕዝብ ነን። ይህ አዲስና ተጨማሪ ጦርነት እንዳይመጣ ምን ለማድረግ እንችላለን? በባርነት ቀንበር ውስጥ የሚገኘው ወገናችንስ ጌቶቹ ወዳዘመቱት ከመዝመት የተለየ ነገር የማድረግ አቅም አለው ወይ?