ከላይ ሆነው እየጠጡ አታደፍርሺብኝ ማለት ምን ማለት ነው? – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ይህ የአያ ጅቦ ዓይነት ሰበብ ያመጣው መአቀብ ነው ፡፡

  • የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን በመግለጫቸው “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርምጃ መውሰድ ያለበት ጊዜ አሁን ነው” አሉ።
  • በኢትዮያ መንግስት ላይ የጉዞ እገዳ አደረገች ፡፡ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው የምጣኔ ሀብትና የደኅንነት ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ዕቀባ አደረገች ፡፡ይህንንንም በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ገለፀች።

የአያ ጅቦ ሰበብ በዚህ እጅግ በጥበብ በተራቀቀ ዘመን ከቶም አይሰራም ፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ብዙ ምርጫ አላት ፡፡ክብር ባለው ትብብር ፣ በፍቅር ፣ ሰጥቶ በመቀበል ፣ ከአሜሪካ ውጪ ከሌሎች ኃያላኖች ጋር ወዳጅነት ፈጥራ ለብልጽግናዋ ትሰራለች ፡፡ እየሰራችም ነው ፡፡

በዚህ በሠለጠነ 21 ኛው መ/ክ/ዘ  የአሜሪካ መንግሥት የ18 ኛውን መ/ክ/ዘ የቅኝ ገዢዎች አካሄድ መከተሉ ለአገራችን እና ለህዝቧ እጅግ አሥገራሚ ሆኖበታል ። የኢትዮጵያ ህዝብ የአሜሪካ የእጀራ አባታችሁ ልሁን ማለት  እና ከመሬት ተነስቶ ለመማታት ምክንያት መፍጠሩ አስገርሞታል ፡፡ ይህ የ18ኘው ክፍለ ዘመን የቅኝ ግዛት መንገድ ነው ፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የቅኝ ግዛት መንገድን በውጪ ፖሊሲው  መከተል ብቻ አይደለም ፤  በቅኝ ግዛት መንገድ ዛሬም እየተጓዘ ኢትዮጵያን የሚያሥተዳድራት እሥኪመሥለን ድረሥ በውሥጥ ጉዳይዋ ገብቷል ፡፡

እጅግ የሚሳዝነው ደግሞ ፣  በቁሟ ከቀበራት ፣ በዘር ከከፋፈለን እና ዛሬም ድረሥ የሚያጫርሰንን የቋንቋ አምልኮ ሥርዓት ከተከለብን ፣ “በህዝቦች ” ሥም አንድ የሆነውን ዳር ድንበር በአፈ ጮሌነት   በህገመንግሥት ሽፋን በክልል ሸንሽኖ  ፣ የቅኝ አገዛዝን መንገድ በመከተል  እየዘረፈ ፣ በአሜሪካ ውሥጥ ዶላሩን ሲረጭ ፣ ወርቁንም ሲነግድ የኖረውን እና በአገር ውሥጥ በጨካኝነቱ ፣ በአረመኔነቱ (ልብ በሉ ወገኖቼ የሚላቸውን የራሱን ጀነራሎችና ሹሞች አሥከሬን አንገታቸውን ቆርጦ  ጭንቅላታቸውን ሌላ ቦታ በመቅበር ፣ የሤጣን ወንድምነቱን ያሥመሠከረ ነው ። በበኩሌ ዛሬም ይህንን የናቡከደናፆር ጭንቅላት ያለውን የኢትዮጵያ ጠላት   ለሆዳቸው ሲሉ የሚደግፉ እንዳሉ አውቃለሁ ። እነዚህ ሰው ሆነው ተፈጥረው ሣለ ሰውነታቸውን የረሱ በመሆናቸውም አዝንላቸዋለሁ ።  ዞሮ፣ዞሮ ሞት ላይቀርላቸው ፣ ሰውነታቸውን ሸጠው  ፣ የባለገንዘቦች ዕቃ ሆነው መኖራቸው በእጅጉ ያሳዝነኛል ። )  ወደር በሌለው ፣ ኢ ሰብአዊ ተግባሩ ፣  ሉአላዊቷ ኢትዮጵያ አሸባሪ ብላ  ከፈረጀችው ፣ ህወሓት ጋራ ተደራደሩ ማለቱ ፣በፕሬዝዳንት ባይደን የሚመራው  የአሜሪካን መንግሥት ፣ለዴሞክራሲ ፣ ለሠላም ፣ለፍትህ ፣ ለህግ የበላይነት እና ለሰብአዊ መብት ደንታ እንደሌለው የሚመሠክር ነው ። ( በሶርያ ፣ በየመን ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በሊቢያና ትላንት በኢራቅ የአሜሪካ መንግስት በግልፅና በስውር ወታደሩን የላከው የየአገሩን ህዝብ ሊየበለፅግ ነው እንዴ ? )

የዛሬው የባይደን አሥተዳደር ፣አፍሪካን በተመለከተ ከትራፕ የተሻለ ፣ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ይኖረዋል ብለን    ብናስብም ፣ ይህ ተሥፋችን በወራት ዕድሜ  ውሃ በልቶታል ። የኢትዮጵያ ህዝብ በባይደን ዘመን ፣ አፍጦ ከመጣበት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ጋር ፈፅሞ  አይደራደርም ። በታሪኩ ለፍጡሩ ፣ ለአምሳያው ሰው ተንበርክኮ ባርነትን የተቀበለበት ጊዜ የለም ።

እርግጥ ነው ፤ በ1928 ዓ.ም (እኤአ በ1935 ) ፍሺስቱ ሞሶሎኒ  በማጨው በተሰባሰበው የኢትዮጵያ በሺ የሚቆጠር ሠራዊት ላይ ፣ በአውሮፕላን መርዘኛ  ጋዝ ፣ በበርሜል በመድፋትና ፣ ተቀጠጣይ ቦንብ በመጣል ፣በዘግናኝ ሁኔታ አባቶቻችን ፣አያቶቻችን ና ቅድመ አያቶቻችን ፣ያለርህራሄ  በመፍጀት ኢትዮጵያን በኃይል ለመግዛት ሞክሯል ። ይሁን እንጂ  እንዳሰበው አልተሳካለትም ። የጥቁር አንበሶቹ የኢትዮጵያዊያኑ አርበኝነት ፣ ኃያልነት  ፣ ለክብሩ ሟች የሆነው ህዝብ ፣ ለወራሪው የፋሺስት ጦር እንዳይገዛ ና በማንኛውም መንገድ ከአርበኞቹ ጎን እንዲቆም አድርጎታል ።

የወራሪውን የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊትን ፣ ፋታ በሌለው የደፈጣ  ውጊያ አሥጨንቀው ፣  በአምሥት ዓመቱ ያላሰለሰ ተጋድሏ ወራሪውን የፋሺስት አውሮፓዊ ጦር ድል በማድረግ ፣ በውጪ አገር  በሥደት የነበረውን በንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚመራውን የኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መልሰው ከዙፋኑ አሥቀምጠዋል።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሰው ፍጥረት ቃሚዎቹ እና ለአማልክት ቅርብ የሆንን ( መፀሐፈ ሄኖክን ይጠቅሷል )  በቅማቅመም ሐብታችንም የምንታወቅ ፤ ከዛሬ 4950 ዓመት በፊት ቀይ ባህርን ተሻግሮ ትልቅ ግዛት ያለን ” ሀበሻ ” ተብለን የምንታወቅ ፑንት የሚባል መንግስት የነበረን ነበርን ።

ከፑንት መንግሥት በኋላም የታወቀው የደአማት መንግሥት ታላቋን ኢትዮጵያን  አሥተዳድሯል ። ከ500 ዓ/ዓ እሥከ 100 ዓ/ዓ ። ከዛም  የአክሱም ዘመነ መንግሥት ተተክቷል ።  ይህ አኩሪ ታሪካችን ለአውሮፓና አሜሪካ አይጠፋቸውም ።

ታሪካችን ታላቅ ቢሆንም ፣ በውስጥ አንድነታችና መላላት ተደጋጋሚ ሸንፈት በአገር መሪዎቻችን ትከሻ ላይ ሲወድቅ ፣ በታሪክ መነፅር ለማየት ችለናል ፡፡

ለምሳሌ ፣ ዓፄ ሱስንዮስ የአገር ግንባታ ውጥናቸው እንቅፋት እንዳጋጠመው ሁሉ ፣ በታላቅ ራእይ የተነሱት አፄ ቴዎድሮስም ፣ “በእኛ ትዕዛዝ የምትንቀሳቀሥ አሻጉሊት ንጉስ ትሆናለህ እንጂ ፣ በለ ኢንዱስትሪህ መንግስት በመሆን እንደ እኛ ሁለንተናዊ አቅም  ያላት  አገር አትገነባም ፡፡ ” በማለት ፣ በወቅቱ በነበረው ንቃተ ህሊና ዝቅተኝነት ና ኃይማኖታዊ ህሳቤ ፣ ከንጉሱ ጋር በተኮረፈው የህዝብ ክፍል ተተግነውና ለሥልጣን በሚሻኮቱ አፄዎች ተደግፈው ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ታላቁን ዓፄ  ቴዎድሮሥን እንግሊዞች ፣ በመድፎቻቸው ብርታት ድል በማድረግ ፣ የኢትዮጵያን የብልፅግና ራዕይ አሰናክለዋል ። ዛሬ ደግሞ ከአለው ብርቱ የብልፅግና ራእይ አንፃር ዳግማዊ ቴዎድሮስ የሆነውን የኢትዮጵያን መሪ ፣ ተንበርካኪ ባለመሆኑ ና ኢትዮጵያን አላሥበዘብዝም ፣ አላዘርፋትምም ፤ በማለቱ እና መበልፀግ እንደሚቻል ፣ ከቤተ መንግስት በመጀመር በማሳየቱ  ፣ ይህ የጭንቅላት የበላይነት ያላማራቸው ፤  የኃያላን አገራት መንግሥታትን በእጅ አዙር የሚመሯቸው ቱጃሮች ፤  በሰብአዊ መበት ሥም ፣ በዴሞክራሲ ሥም ፣ በፍትህ ሥም ፤ ኢ ሰብአዊ መብትን ፤ ፍርደ ገምድልነትን ፤ ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን ፤ ኃያላኑ የአውሮፖና አሜሪካ መንግሥታት እንዲተገብሩ እያሥገደዷቸው እንደሆነ እየታዘብን ነው ፡፡

ዛሬም እንደጥንቱ ፣ በቅኝ አገዛዛቸው መደፍ ውሥጥ እሥካልገባን እና ተዘራፊ እሥካልሆንን ድረሥ እርሥ በእርሥ እንድንጨራረሥ እኩይ ሃሳብ ከማዋጣትና የምንጋደልበት መሣሪያ ከማቀበል ወደኋላ አይሉም ።

በአገራቸው የህግ የበላይነት ፣ ሰብአዊ መብትና ዴሞክራሲ  የተከበረው በምግብ ችግር የሚሞት ሰው በለመኖሩ እንደሆነ እያወቁ እኛ ወርቅና አልማዝ ላይ ተኝተን ሥንዴ እየመፀወቱን በለውጡ ፣  ወርቅና አልማዛችንን ከትራሳችን ሥር ለመውሰድ ሲሉ ይህንን እነደሚደርጉም እናውቃለን ።

የበለፀጉት የአውሮፓውያኑ  እና የኃያሏ አሜሪካ ቱጃር መንግሥታት  ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አፍሪካ በሙሉ  እንዲበለፅግ ከቶም እንደማይፈልጉ ከተገነዘብን ሰነበትን  ። በየትኛውም የአፍሪካ አገር ውሥጥ ህዝብን በልቶ እንዲያደር የሚያደርግ የልማት ሥራ እንዲከወንም አይፈልጉም ። የእነሱ ቱጃር ካምፓኒ ሥንጥቅ የሚያተርፍበትን እና ሀብቱን ወደ ትውልድ አገሩ የሚያሸሽበትን የፀረ  ልማት መንገድን ሲከተሉ ነው እሥከ ዛሬ የኖሩት ። በየትኛውም የአፍሪካ አገር ።

ይህ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን የተሰወረ አይደለም ። በብልፅግናቸው ሊረዱን እንደማይፈልጉ ከ18 ኛው መ/ክ/ዘ ጀምሮ በግልፅ ተረድተናል ። እጅና እግራችንን ጠፍረው በ1935 እኤአ በመርዝ ጋዝ በሥቃይ እንድንሟት መወሰናቸውን ና የሊግ ኦፍ ኔሽን ጩኸታችን ላይ መሣለቃቸውን ምንጌዜም አንረሳም ።…

ከዚህ እና ከዛሬው እውነት አንፃር ፣  በእኔ ግምገማ  ፣ አሜሪካም ሆነች ጥቂቶቹ የአውሮፓ አገራት ፣ የሰብአዊ መብት ፀር ከመሆናቸውም በላይ ፣ ፀረ ብልፅግና እና ሌብነትን አበራታች ናቸው ።…  በወያኔ ኢህአዴግ ፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጉሮሮ ተቀምቶ በየባንካቸው የተከማቸውን በቢሊዮን የማቆጠር ዶላር ሊመልሱልን ፍቃደኞች አይደሉማ ?! ይህን ደሃ ህዝብ ከድህነት ለማውጣት የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ፍላጎት ቢኖራቸው ኖሮ እኮ ፣ የአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የመንግሥት ሌቦች መሸሻና መደበቂያ ጎሬ አይሆኑም ነበር ።

እንግዲህ ይወቁን እኛ እንዲህ ነን ። ገመናቸውን የምናቅ ባለምጡቅ አእምሮ የሄኖክ ዘሮች ። ይህንን እውነት ሥለሚያውቁ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያዊያንን ፣ በዘር ና  በቋንቋ ሊከፋፍሉን የሚፈልጉት ፡፡ እኛ ግን ዛሬ ነቄ ብለናል ። የሰሜኑ የአገራችን የትግራይ ችግርም በቅርቡ ይፈታል ። እሥከዛሬም የሚጮኸው ገንዘብና ፕሮፖጋንዳ ነው ።

ዛሬ ይህንን ጮኺ የገንዘብና የፕሮፓጋንዳ ምርኮኛ ፣ ወደቀደመ ቀልባችን ተመልሰን ፣ ሤራውን የምናከሽፍበት አማራጭ በእጃችን ነው ፡፡…

አውሮፓውያኑም ሆኑ የተባበሩት አሜሪካኖች ፣ ዛሬ እና አሁን መገንዘብ ያለባቸው ፣ ትላንት ከእነሱ በፊት ትልቅ ነበርን ፡፡  ዛሬም ወደቀልባችን  ተመልሰን  ፣ በድህነታችን የሚሳለቁትን በማሳፈር ትልቅ እንሆናለን ።

እርግጥ ነው ፤ ሊነጋ ሲል ይጨልማል ፡፡ ፈተናችን ብዙ ነው ፡፡ ሆኖም እናልፈዋለን ፡፡ ዛሬም ፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆነ ያለማወቃቸውን የማይገነዘቡ ፤ ገንዘብና ወረት ሥላከማቹ እና ይህንን ገንዘባቸውን ለህሊና ቢሶቹ የኢትዮጵያ እንግዴ ልጆች በማደል ፣ ንፁሐንን ቃላት በማይገልፀው ጭካኔ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገድሉ እዛ ና እዚህ መሽገው እንዳሉ  እናውቃለን ፡፡  እነዚህን የሞሶሎኒ እና የሂትለር ልጆች ፣ ደግሞ  ፣ ትላንት የአሜሪካ መንግሥት አመራር በግልፅ ሲደግፋቸው እንደነበር አንዘነጋም ። ለዚህም ነው የአሜሪካ የአሁኑ መንግስት እና በእርሱ የሚመሩት የሰባዓዊ መብት ተቋማት ፣ ለዴሞክራሲ ፣ ለፍትህ ፣ ለሰብዓዊ መብት እና ለመሳሰሉት ደንታ የላቸውም የምንለው ። (በኢትዮጵያ ውስጥ ሽብርተኞች በንፁሓን ላይ ፣ ዘግናኝ ዕልቂት ሲፈጽሙ  ፣ የማይካድራን ጭፍጨፋ ጨምሮ ፤ አንድም ቀን የአሜሪካ መንግስት ይህንን የሽብርተኞችና የጨካኝ ዘረኞች ድርጊት አላወገዘም ፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ዛሬም በ21ኛው ክ/ዘ ፣ ለፍትህ እና ለእኩልነት ደንታ እንደሌለው የጆርጅ ፍሎይድ አሰቃቂ ግድያ ትላንት አረጋግጦልናል ። በነገራችን ላይ ፣  አንድ ጥቁር ፣ በአንድ ጥጋበኛ እና ህሊና ቢሥ ዘረኛ ነጭ ፖሊስ አንገቱ ተቆልምሞ እንደ እንስሳ ተረግጦ ፣ መተፈስ አቃተኝ እያለ ሲማፀን ፣  የክፉ ድርጊቱ ፈፃሚ የሥራ ባልደረቦቹ ፣ ምንም ሳይቃወሙት ፣ ለግፈና ድርጊቱ ተባባሪ በመሆናቸው ተጠያቂ አልሆኑም ፡፡   ሰወ በግፍ ና በጭካኔ ሲገደል ቆሞ እያየ ፣ ከሞት ያልታደገ ፖሊስን ተጠያቂ እንዲሆን ያላደረገ የፍትህ ሥርዓት ፣ የመጨረሻውን የፍትህ ከፍታ ይዞል ብዬ አላምንም ።  ከዚህ እውነት አንፃር ፣ የአሜሪካ መንግሥትን ህገመንግሥት የሚጠብቀው ሴኔት ፣  ይህንን እውነት ቆም ብሎ መፈተሽ እና ለ21ኛው መ/ክ /ዘ የሚመጥን  የወንጀል ህግ እንዲወጣ ሃሳብ ማዋጣት እንዳለበት አስባለሁ ።

ኢትዮጵያን በተመለከተም  ፣ የውጪ ግኑኝነት ፖሊሲውን ሴኔቱ መለሥ ብሎ እንዲቃኝ እና የአሜሪካ መንግስት ፣በደሀአገሮች ላይ ፣ ውሃዬን አደፈረሺብኝ በማለት የሚፈፅመው ፣  የማንአለብኝነት ድርጊት እዛው አገሩ ላይ ሊወጣ ከማይችለው ቀውሥ ውሥጥ ሊከተው እንደሚችል ሊያሳስበው ይገባል ። በአንድ ጆርጅ ፍልይድ ሞት ሚሊዮኖች በትራፕ አሥተዳድር ላይ ተቃውሟቸውን እንደሰሙ ሁሉ ፣ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነችውን አገር ፣ከላይ ሆኖ የወንዙን ውሃ እየጠጣ ከታች ሆና  ፣ እየጠጣች ያለችውን አህያ ለምን ውሃውን አደፈረሽብኝ በማለት ፣  እንደተቆጣው ጅብ አይነት መአቀብ ማድረግ ቢዘገይም ዋጋ ሊስከፍለው እንደሚችል ቢገነዘብ መልካም ነው ።

የአሜሪካ መንግስት ሰከን በማለት እውነትን ቢገነዘብ እና ከእውነት ጋር ቢታረቅ ደስ ይለናል ፡፤ ዛሬ ዓለም በሥልጣኔ ጎዳና እየተራመደች ከመሆኖም በላይ   ሰው ሁሉ አንድ መሆኑንን የሚመሰክሩ የሣይንሥ እውነቶችም ለመላው የዓለም ህዝብ በኢንተርኔት አማካኝነት ግልፅ ሆነውለታል ።

ዘመነኛው ቴክኖሎጂም ዓለምን ለማጥፋትም ሆነ ለማልማት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ዝግጁ እንደሆነ ይታወቃል ። እናም በዚህ በዘመነ ክ/ዘ ኢትዮጵያን በ18 ኛው ክ/ዘ መንገድ እንግዛ ማለት ያዋጣልን ?

እኛም እንደ ቻይና ሁለንተናዊ ብልፅግና በአገራችን እንዲመጣ ፣ ከዓለም አገራት ጋር በትብብር ለመሥራት እንፈልጋለን ።የሥጋ ዘመዳችን ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር ይቅርና ከመላው አፍሪካ ጋር  ህብረታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን እንፈልጋለን ። የአውሮፓ ህብረትን ነጮች በተግባር ህብረት አርገው ህዝባቸውን የበለጠ ካበለፀጉ ፤  ጥቁሮቹ  የአፍሪካ አገራት የአፍሪካ  ህብረትን ፣ ወደ ላቀ ትሥሥር እና ድንበር የማይገድበው  የህዝቦች መቀራረብ በመፍጠር ፣  እንዴት ታላቋን አፍሪካ መመሥረት ይሳናቸዋል  ?  ከተባበሩ  የሚሳናቸው ነገር አይኖርም ። የዚህን ህብረት ጅማሬም የሚያረጋግጡት ዛሬ ና አሁን ፣ የአፍሪካ ህዝቦች ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሲቆሙ ነው ።አፍሪካዊያን ለአፍሪካ ነፃነት መስዋት ከከፈለቸው ኢትዮጵያ ጎን ሲቆሙም  የዓለም ጥቁር ህዝብ በሙሉ ፣ ከኢትዮጵያ ነፃነትና የብልፅግና ዓላማ ጎን በጽናት ይሰለፋል ። ልማት ፣ እውቀት ፣ ጥበብና ሠላም በአፍሪካ እውን ይሆናል ።

እኛ አፍሪካውያን ከተባበርን የማንወጣው ተራራ የለም ።  በትብብራችን እና በጠንካራ ህብረታችን ፣ ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንችላለን ። ውሃዬን አደፈረሽብኝ በሚል ሐሰተኛ ትርክትም የሚያሥፈራራን አይኖርም ። ድር ከአበረ አንበሳን ያሥራልና !!

 

1 Comment

  1. አሜሪካ ተሳስታለች የሚለው ያስማማናል። የኢትዮጲያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም “ጥሩ” የሚባል መግለጫ አውጥቷል። ነገር ግን በቴዎድሮስ፤ በአድዋና በማይጨው እየፎከሩ አሜሪካንን “መሳፈጥ” ለመንግስቱ ኃ/ማርያምም አልበጀም፣ እሱንም ወደ ዚምባብዌ ኤርትራንም ነጻ ሃገር አደረጋት። ቁርጡ ሲመጣ የሚሆነው “እየማቀቁ መፎከር” ነው። ቻይናና ሩሲያ አንድም ሃገር ከአሜሪካ ጥቃት ሲያተርፉ አላየንም። ምናልባት የሲሪያውን መሪ በግለሰብ ደረጃ! አቶ ደረጀ ደምሴ የተባሉ [የጄነራል ደምሴ ቡልቶ ልጅ] ከሄኖክ አለማየሁ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ማዳመጡ ይጠቅማል። በአባት የጀግንነት ዉርስ ላይ እውቀትና ብልሃት እንዴት መጨመር እንዳለበት ጥሩ ማሳያ ነው።
    ሠላሙን ያውርድልን
    በምርጫ ብቻ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.