ፋኖስ ቁጥር 2፣ 25.10 2023
ስልጣን በጠመንጃ ወይስ በምርጫ !
በመጀመሪያ የፋኖስ ዕትማችን በመግቢያው ላይ ለማብራራት እንደተሞከረው የፋኖስ ዋና ዓላማና ተግባር በተለይም በአገራችን ምድር በፖለቲካው ዙሪያ ያለውን ከፍተኛ ውዥንብር መልክ ለማሲያዝና ትክክለኛውን የትግል ፈር ለማሳየት ነው። ከታሪክ እንደምንማረው ዛሬ በአውሮፓ ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጸው ስልጣኔ ከመታየቱ በፊት በዚሁ በአውሮፓ ምድር፣ በ14ኛው ክፍለ-ዘመን በተለይም በኢጣሊያን ምድር ከፍተኛ ውዥንብር ስለነበር ሰፊው ህዝብ የሚሰራውንና የሚያደርገውን የሚያውቅ አልነበረም። አንድ የሚግባባትም ቋንቋ ስላለነበር እርስ በርሱ የማይግባባውንና ሃሳቡ የተበታተነውን ህዝብ ዕውነተኛውን መንገድ በማሳየት ራሱን እንዲያገኝ ዳንቴ የሚባለው ታላቅ ምሁር “የአምላኮች ኮሜዲ” በሚባለው መጽሀፉ ውስጥ ሰፊው ህዝብ ጭንቅላቱ እንዲያይ ከታገደበት ሁኔታ በመላቀቅ ብርሃንን በመጎናፀፍ አምላክ የሰጠውን የማሰብ ኃይል በመጠቀም ታሪክን እንዲሰራና እንደሰው እንዲኖር እጅግ በሚያምር ጽሁፉ የመጀመሪያውን ለጣሊያን ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለተቀረውም የአውሮፓ ህዝብም የሚሆን የዕውነተኛውን የስልጣንኔ መመሪያ መንገድ አሳየ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በብዙ ችግሮች የተወጠረው የጣሊያንም ሆነ የተቀረው የአውሮፓ ህዝብ ከገባበት ውዥንብርና መደናበር ቀሰ በቀስ በመላቀቅ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባትና የዕደ-ጥበብ ሙያን በማዳበር ለተከታታዩ የስልጣኔ መሰረት መጣል ቻለ።
በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ግብረ-ኃይል በየሁለት ሳምንቱ እየታተመ የሚወጣው ፋኖስ በመባል የሚታወቀው ዕትም እንደ ዳንቴው “የአምላኮች ኮሜዲ” ሊስተካከል ባይችልም በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ውዥንብርና መደነባበር መልክ ለማሲያዝ ይችላል የሚል ዕምነት አለን። የአገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ በብዛት የሚነሱና በቀላሉም መቋጫ ሊያገኙ የማይችሉ አርዕስቶች ቢኖሩም ለጊዜው በአብዛኛዎቻችን ጭንቅላት ውስጥ ከሚሽከረከሩትና ከሚብላሉት ከሁለት ቀናት በፊት ሶስት ሰዓት ያህል የፈጀውን ክርክራችንና ውይይታችንን አስመልክቶ የተነሳውን ስልጣን “በጠበንጃ ወይስ በምርጫ” በሚለው አርዕስት ስር አጠር መጠን ያለ ማብራሪያ እንደንሰጥ ተገደናል። ይህም የሆነበት ምክንያት የሽግግር መንግስት እያሉ የሚወተውቱ ስላሉ፣ ይህ ዐይነቱ ውትወታ አገራችን ውስጥ ከሚደረገው የብዙ እህቶቻችንና ወንድሞቻችንን ህይወት ከሚቀጽፈው ትግል ጋር እንዴት ሊጓዝ ይችላል? መቅደምስ ያለበት ጉዳይ የትኛው ነው? በአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታስ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይ? አስፈላጊም ነው ወይ? አገዛዙን የሚጋፈጠው የፋኖዎች ጥምር ኃይል በአሸናፊነት ቢወጣስ ለምርጫ ከመሽቀዳደም ይልቅ የጋራ ግምባር በመፍጠር በመጀመሪያ ደረጃ ቅድሚያ መሰጠት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ መረባረቡ የሚሻል አይደለም ወይ? ምርጫ ይካሄድ ቢባልስ ለውድድር የሚቀርቡ በማንኛውም ረድፍ የተዘጋጁ ፓርቲዎች አሉ ወይ? ምርጫ ቢካሄድና አንዱ ፓርቲ በአሸናፊነት ቢወጣስ ህዝባችን የሚፈልገውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሌሎችን የተወሳሰቡ ችግሮችን ቀስ በቀስ በመፍታት ለከታታይ ዕድገት የፀና መሰረት ሊጥል ይችላል ወይ? አገራችንና ህዝባችን አሁን ባሉበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በዚህም በዚያም ብለው ስልጣን ላይ ለመውጣት የሚፈልጉ ኃይሎች የህዝባችን አገልጋይ ከመሆንና ታሪክን ከህዝቡ ጋር ሆነው ከመስራት ይልቅ በውጭ ኃይል በመጠለፍና የእሱ አገልጋይ በመሆን የህዝባችንን የስልጣኔና የነፃነት ጥማት እያራዝሙበትም ወይ?
የህዝብ ብሶት ተነሳስቶ የአገዛዝ ለውጥ በተደረገባቸው የአፍሪካ አገሮችም ሆነ፣ ከ37 ዓመትታት በፊት ምርጫ በተካሄደባትና በፈርዲናንድ ማርኮስ ዲይናስቲ ስትገዛ በነበረችው ፊሊፒን በተከታታይ ምርጫ ቢካሄድም ስልጣን ላይ የሚወጡት ኃይሎች በሙሉ የፊሊፒንን ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን አላጎናጸፉትም፤ ከድህነትም በማላቀቅ የስልጣኔ ባለቤት እንዲሆን አላዳረጉትም። በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥም ከቅኝ-አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ሲባል ከረጅም ጊዜ የጠበንጃ ትግል በኋላ ነፃነታቸውን በተቀዳጁ አገሮች፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ዚምባብዌና ደቡብ አፍሪካ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ሁሉ የተትረፈረፈ የጥሬ-ሀብት ቢኖርምና መሬቶቻቸውም ለእርሻ ምርት የሚያገለግሉ ቢሆኑም ሀብትን የሚቆጣጠሩና ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመቆላለፍ የጥሬ ሀብቶቻቸውን የሚያዘርፉት፣ የየአገራቸውን የመንግስት መኪናዎችና የጥሬ-ሀብቶችን የግል ሀብታቸው በማድረግ እንደልባቸው የሚንደላቀቁት የየአገሩ አምባገነን አገዛዞች ብቻ ናቸው። ህዝቦቻቸው ዕውነተኛ ነፃነትን የተጎናጸፉና ከድህነት የተላቀቁ ሳይሆን በአገራቸው ምድር ባይተዋር በመሆን በፍርሃትና በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። አልፎ አልፎ ምርጫ በሚካሄድባቸው እንደናይጀሪያ በመሳሰሉትና በሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገሮችም ውስጥ አዳዲስ ገዢዎችን ከማፈራረቅ በሰተቀር የስርዓት ለውጥ በማምጣት ህዝቦቻቸው ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት የተላቀቁበት ሁኔታ የለም። ይህም ማለት የሰለጠኑ ተቋማት፣ ጥልቀትና ብሰለት ያላቸው ምሁራዊ ኃይሎች በሌሉበት አገር፣ የሲቪል ማህበረ-ሰብ በተደራጀ መልክ በማይገኝበት አገር፣ ውስጠ-ኃይሉ ጠንካራ የሆነና ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ አወቃቀር በሌለበት አገር ውስጥ ለይስሙላ ምርጫ ማካሄዱ በተዘዋዋሪ ላለው ጨቋኝ ስርዓት ዕውቅና እንደመስጠት ይቆጠራል። ለዚህም ነው በአገሮች ውስጥ አለመረጋጋት የሚታየውና በእስላም አክራሪነት ስም በሚካሄድ የርስ በርስ ጦርነት የውጭ ኃይሎች ሁኔታውን እናረጋጋለን በማለት ጣልቃ-በመግባት ሁኔታውን የሚያባብሱት። ለዚህም ነው አዲስ በተመረጡ አገዛዞች የማይደሰቱ ወጣት መኮንኖች ወይም ወታደሮች የአገዛዝ ግልበጣ እንዲያደርጉ የሚገደዱት። ቀደም ብሎ ማሊ፣ አሁን ደግሞ በቅርቡ በሐምሌ ወር በኒይጀር የተደረገው የመንግስት ግልበጣ የሚያረጋግጠው በምርጫ ስልጣን ላይ የሚወጡ መሪዎች የውጭ ኃይሎችን ከማገልገል በስተቀር ለሰፊው ህዝብ የሚሰጡት ግልጋሎት ባለመኖሩ ብቻ ነው።
ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ወያኔ 27 ዓመታት ያህል ስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር አገራችንን በጎሳ ከከለለ በኋላ በቀጥታ ትዕዛዝ በመቀበል ተግባራዊ ያደርግ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ አገዛዙንና ካድሬዎችን የሚጠቅም ብቻ ሲሆን፣ በዚያው መጠንም ህዝባችንን ወደ ድህነት ዓለም በመገፍተር አቅመ-ቢስ ያደረገ ነው። በነፃነት ስም ትግል ያደረገው ወያኔ የውጭ ኃይሎች ተገዢና ተጠሪ በመሆን በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ ጦርነት በማወጅና በጨቋኝነት በመፈረጅ ስቃዩን ሲያሳየው ከርሟል። የወያኔ የጎሳ ክልላዊ አገዛዝ ለራሱ የከፋፍለህ ግዛና የዘረፋ ፖሊሲ የጠቀመው በመሆኑ በተለያዩ ክልሎች የሚኖረው ህዝባችን የዕውነተኛ ዕድገትና የነጻነት ባለቤት ለመሆን አልቻለም። በተለይም በኦሮሚያና በበኔሻጉል ክልል የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመመሰጣጠር ወደ ውጭ ሊወጡ የሚችሉ ፍራፍሬዎችንና አበባዎችን በመትከል የየክልሉን ኗሪ ህዝብ ወደ ባርነት የለወጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን።
ወያኔ 27 ዓመታት ያህል እንደልቡ ከጨፈረና አገራችንን ከአዋረደ በኋላ ለህዝቡ የሚሰጠው ምንም ነገር ባለመኖሩ ከስልጣን መወገዱ የታሪክ ግዴታ ለመሆን በቃ። በአብዛኛው ህዝባችን ተስፋ የተጣለበት በአቢይ አህመድ የሚመራው የኦሮሙማ አገዛዝ ለጥቂት ጊዜያት ህዝባችንን ካታለለ በኋላ ስልጣኑን የሚያደላድልበትን ተንኮል መሸረብ ጀመረ። ለህዝባችን የሚፈልገውን ዕውነተኛ ስልጣኔ ከመለገስ፣ የነፃነቱን ፈለግ ከማሳየትና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ከመገንባት ይልቅ የበለጠ አምባገነናዊ በመሆን፣ አሁን እንደምናየው ሙሉ በሙሉ ፋሺሽታዊ ስርዓት ለመመስረት በቅቷል። ከስድስት ወራት ጀምሮ የአማራን ልዩ ኃይልና ፋኖዎችን ትጥቅ አስፈታለሁ በማለት የከፈተው እልክ አስጨራሽ ጦርነት በአማራው ወገናችን ላይ ከፍተኛ ዕልቂት እንዲፈጽም አድርጎታል። በአቢይ አህመድና በግብረ-አበሮቹ የተከፈተባቸውን ጦርነት ለመመከት ሲሉ በተለይም ፋኖዎች በመደረጃት በአገዛዙ በመገደድና የአማራውን ህዝብ ህልውናና ባህሉን ለማስጠበቅ ሲሉ ከፋሺሽታዊ አገዛዝ ጋር በመፋለም ላይ ይገኛሉ። አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹም እንደተመኙት የአማራውን ህዝብ ሊያንበረክቱት በፍጹም አልቻሉም። እንዲያውም በየቦታው ድል በድል በመሆን የፋሺሽታዊውን አገዛዝ ወታደሮች እየመቷቸውና መሳሪያዎቻቸውንም እየቀሙባቸው ነው። እንደምንከታተለው ከሆነ በፋኖዎች የሚደረገው ትግል መልክ እየያዘ በመምጣት ለአማራው ወገናችን ብቻ ሳይሆን፣ ለጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብም ተስፋ የሚጣልበት ለመሆን በመብቃት ላይ ነው። እንደሚታወቀው የፋኖ ትግል በመጀመሪያ ደረጃ የአማራውን ህልውና ለማስጠበቅ ሲሆን፣ በተጨማሪም የአገራችንን አንድነት ለማስጠበቅ ነው። የአማራውን ህልውናና የአገራችንን አንድነት ለማስጠበቅ ደግሞ የግዴታ በህዝብ የታገዘ አመጽ ለድሉ ወሳኝ ነው። ድል ሲባልም የአገዛዙን ቁንጮ ብቻ በማስወገድ እፎይ ተብሎ አርፎ መቀመጥ ሳይሆን፣ አገዛዙ እስካሁን ድረስ ሲመራበት የነበረውን በውሸት ትረካ ላይ የተመረኮዘውን የጥላቻ መርዝና የመጨቆኛ መሳሪያውን ቀስ በቀስ አኮንታኩቶ በመጣል ብቻ ነው ማረጋገጥና ማብሰርም የሚቻለው።
በአብዛኛዎቻችን ዕውነተኛ ነፃነትንና ስልጣኔን በምንፈልግ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይህ ዐይነቱ የትግል ስልት ከተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ ስንነሳ፣ ሎጂክንና አርቆ አሳቢነት የሌለውን አገዛዝ ከስልጣን ላይ ማስወገድ የሚቻለውና የሚገባውም በጠበንጃ ብቻ ነው። አንድ አገዛዝ ጦርነት አውጆ እንደልቡ ህዝብ ሲጨፈጭፍና አገር ሲያፈራርስ ዝምብለህ ተመልከት፣ ዕጣህም ነው የሚል የተፈጥሮም ሆነ የእግዚአብሄር ህግ የለም። አንድ አገዛዝም ስልጣን ላይ በአጋጣሚ ስልተቀመጠ አንድን ህዝብም ሆነ ግለሰብን እንደፈለገው የማሰር፣ ከቀዬው የማፈናቀል፣ ሀብቱን የመዝረፍና የመግደልም መብት የለውም። ማንኛውም አገዛዝ ከህዝብና ከህግ በላይ ሊሆን በፉጹም አይገባውም። ማንኛውም አገዛዝ በማንኛውም ጊዜ የህዝብ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን፣ አገሩንም በጸና መሰረት ላይ የመገንባት ግዴታና ኃላፊነት አለበት። አንድ አገዛዝ ከዚህ ውጭ ልዩ መብት የለውም፤ ሊኖረውም አይገባም። ስልጣንን የሚይዙ ኃይሎች ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ህገ-መንግስትን በመጣስ ከእያንዳንዱ ዜጋ በልጠው ሊታዩ አይችሉም፤ መብትም የላቸውም።
ከዚህ ዐይነቱ ተጨባጭ የአገራችን ሁኔታ ስንነሳና ፋሺሽታዊ አገዛዝ ሰፍኖ የአማራውን ወገናችንን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ህዝባችንን ፍዳውን በሚያሳይበት ወቅት የምርጫ ጉዳይ ብዙ ጥናትና ዝግጅትን የሚጠይቅ ቢሆንም ከረጂም ጊዜ አንጻር የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ የዛሬውን በአገራችን ምድር የሰፈነውን ፋሺሽታዊ አገዛዝና የውጭ ኃይሎች ተጠሪ በመሆን በአማራው ህዝባችን ላይ ጦርነት በመክፈት ህዝባችንን የሚገድለውንና በጠቅላላው በአገሪቱ ምድር ውስጥም የባህል ውድመትና ዘረፋ የሚያካሂደውን የአቢይ አህመድን የፋሺሽታዊ አገዛዝ ከስልጣን መወገድ ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ ዐይነቱ አገዛዝ ከቅኝ-ግዛት ባላነሰ ከወያኔ የወረሰውን የከፋፍለህ ግዛ ስልት ጥልቀትና ስፋት በመስጠት ህዝባችን በሰላም እንዳይኖርና አገሩን ቀስ በቀስ፣ ግን ደግሞ አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ እንዳይገነባ በማድረግ የድህነቱንና የጥገኘነቱን ዘመን እያራዘመው ነው።
ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ አገዛዝ በተቀነባበረ የጦርነት ትግል ስልጣኑን እንዲለቀቅ ከተገደደ በኋላ በሁሉም ዘንድ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ነገር ይህ ዐይነቱ ድል የጠቅላላው ትግል የመጀመሪያው ደረጃ ነው። እንደሚታወቀው ከእንደዚህ ዐይነቱ አረመኒያዊ አገዛዝ ጋር የሚደረግ ትግል ፖለቲካዊም እንደመሆኑ መጠን፣ በሁለተኛ ደረጃ በአገራችን ምድር የተረጋጋ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የሰላም፣ እንዲሁም የአንድነት ሁኔታና ስሜት ለመፍጠር ከተፈለገ የግዴታ የሽግግር ስርዓት/አስተዳደር በህዝብ ተወካዮች የመመስረቱ ጉዳይ አስፈላጊ ነው። ይህ እንደ ሸንጎ የሚቆጠር ስብስብ ሁሉም ተገዢ የሚሆንበት ሕገ-መንግስት የማርቀቅ ተግባር ሲኖረው፣ አርቃቂዎችም ከሁሉም ማህበረሰብ የተውጣጡ የህገ-መንግስት ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም የሚፈጠረውን የአስተዳደር ክፍተት የሚሞላ የፖለቲካ ኃይል ወይም ተወካይ መኖር መዘንጋት የለበትም። ይህ ዐይነቱ የሽግግር መንግስትም ለህዝቡና ለአገራችን በቆራጥነት የታገሉትን አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን የሚያካትትና የሽግግር ፍትህነትንም ተግባራዊ የሚያደርግ መሆን አለበት። የአስተዳደሩም ዘመን በተቻለ መጠን አጭር መሆን ይኖርበታል። ለምርጫ አስተማማኝ ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ በቁጥር ከሶስት በላይ የማይበልጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈጥረው ለምርጫ ሲበቁ ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊው የስልጣኑ ባለቤት ይሆናል። የስልጣን ዘመኑም በህግ ይደነገጋል። ይህ ዐይነቱ ሂደትም ለሲቪል ማህበረሰብ መመስረት አስፈላጊ ሲሆን፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ክፍተት እንዳይኖር በማድረግ ማንኛውም ኃይል በአመጽ ስልጣንን እንዳይዝ ለማገድ ይቻላል። እንደሚታወቀው የጦርነት ትግልና የህዝብ ዕምቢተኘት አስፈላጊ የሚሆኑት በህገ-መንግስት ውስጥ የሰፈሩት የመብት፣ ማለትም የዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎች፣ የህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎቶች፣ ማለትም የተመጣጠነ ምግብ፣ ንጹህ ውሃ፣ ቤት፣ የጤንነት መስክና ትምህርትን ለልጆት በተሟላ መልክ ማዳረስ በማይቻልበት ጊዜና፣ በተጨማሪም ደግሞ ለስራ ፈላጊው የህብረተሰብ ክፍል በቂ የስራ መስክ በማይከፈትበት ጊዜና ሰፊው ህዝብ በአጠቃላይ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ በሚወድቅበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ሃቅ ስንነሳ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ቀውሶች እንዳይፈጠሩ ከተፈለገ ለፖለቲካ ስልጣን እንወዳደራለን የሚሉ ፓርቲዎች በእርግጥም የህዝብን ጥያቄዎች የሚመልሱና የአገራችንንም ብሄራዊ ነፃነት ለማስጠበቅ የሚችሉና ኃላፊነትም የሚቀበሉ መሆን አለባቸው። የሞራል ብቃትም እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። የለውጡ ሂደትም ደረጃ በደረጃ የሚካሄድ ሲሆን ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው መደረግ አለበት፤ ወይም ጠቅላላውን የአገሪቱን ህዝብ የሚያሳትፍ የብሄራዊ ዲሞክራሲያዊ የለውጥ ሂደት ይሆናል። ምክንያቱም ሰፊው ህዝብ የማይሳተፍበት፣ ቅሬታውንም የማያሰማበትና መሻሻልም እንዲደረግ መብቱ በሚነፈግበት አገር ውስጥ ስለተሟላ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማውራት በፍጹም አይቻልምና። ሰፊው ህዝብ በአገር ግንባታ ውስጥ ሲሳተፍ፣ ተቋማት ሲገነቡና መብቱንም ሲጠቀም ብቻ ነው ስለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ተግባራዊነት ማውራት የሚቻለው።
በእኛ ዕምነት በመጀመሪያ ደረጃ የዛሬው አገዛዝ አስተማማኝ በሆነ መንገድ በግዴታ ከስልጣኑ መወገድ አለበት እንላለን። ብዙ ማዋከብም ሳይበዛ ከውጭ የሚመጣውን ግፊት በስርዓትና በብልህነት ለመቋቋም ከተፈለገ ተገደው ወደ ጫካ እንዲገቡ ለተገደዱት ፋኖዎች ለሽግግር መንግስት መመስረት አመቺ ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ የጠቅላላውን የፖለቲካ ሁኔታ ረጋ ባለ መልክ መመልከትና አገር ወዳድ ምሁራንም ሊሳተፉ የሚችሉበት የስትራቴጂ ጥናትና ቅየሳ መደረግ አለበት። ይህ ዐይነቱ የስትራቴጂ ጥናት አስፈላጊነትም የአገራችንን የተመሰቃቀለ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ፣ እንዲሁም የሰላም እጦት መንሰኤዎች በማጥናት ደረጃ በደረጃ መፍትሄ ለመፈለግ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ድረስ በአገራችን ምድር ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይሰፍንና ዕውነተኛ ለህዝቡ አለኝታ የሚሆን ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን በአገራችን የውስጥ ፖለቲካ በመግባት የሚፈተፍተውንና ለዚህም አመቺ ሁኔታ የሚፈጥሩትን ጠጋ ብሎ ለማጥናት ነው። በተለይም አሜሪካን አገር በአማራውም ሆነ በሌላው ብሄረሰብ ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ስላሉና፣ አንዳንዶችም የአሜሪካንን አገርን የማመሰቃቀል አጀንዳ ለማስፈጸም ደፋ ቀና የሚሉ ስለሆነ እነዚህ ዐይነት እርኩስ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች ሰርገው በመግባት የትግሉን ዓላማ እንዳያሰናክሉ ከአሁኑ መጠንቀቅ ይገባል የሚል ዕምነት አለን። በአገር ቤትም ሆነ በውጭው ዓለም በአማራዎችና በፋኖዎች፣ እንዲሁም ደግሞ በጠቅላላው ህዝባችን ስም የሚደረገው ትግል በከፍተኛ ደረጃ በምስጢር የሚካሄድ መሆን አለበት። ዲፕሎማሲያዊ ትግል እናደርጋለን እያሉ እዚህና እዚያ የሚደረገው መቅበዝበዝ የህዝባችንን የነፃነት ፍላጎት ድምጥማጡን የሚያጠፋው መሆኑን መታወቅ አለበት። በአሁኑ የዓለም ሁኔታና አገራችንም ተዳክማ በምትገኝበት ዘመን ዲፕሎማሲ የሚባል ነገር አይሰራም። የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለምም በዲፕሎማሲ የሚያምን አይደለም። የምዕራቡ ካፒታሊስት ዓለም ዲፕሎማሲ ሲል የእኔን የበላይነት ተቀበል፣ የምልህንም ዝምብለህ ተግባራዊ አድርግ ማለቱ ብቻ ነው። በተለይም ግሎባል ካፒታሊዝም አገሮችን በሚያተረማምስበት ዘመን ትግሉ የግዴታ ምስጢራዊና በከፍተኛ ምሁራዊ ብቃትነት የታጠቀ መሆን አለበት እንላለን።
ስለሆነም በጠበንጃ ስልጣን ላይ ከወጡ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች አገዛዞች ፋኖዎች መማር ያለባቸውው ጉዳይ ከራሳቸው ባሻገር ለህዝባቸውና ለአገራቸው የቆሙ መሆን ያለባቸው መሆናቸውን ቀስ በቀስ ማረጋገጥ አለባቸው። የአገራችንንም ሆነ የአብዛኛዎችን የአፍሪካ አገሮች ሁኔታ ታሪክንና የህብረተሰብ አወቃቀር ስንመለከትና ስንመረምር በሚገባና በሁሉም አቅጣጫ የሰለጠነና የዳበረ ምሁራዊ ኃይል ባለመኖሩ ስልጣን ላይ የሚወጡት ኃይሎች ክመጀመሪያውኑ በቅደም ተከተል መወሰድ ያለባቸውን ተግባሮች አያውቁም። ባለው የበሰለና የሰለጠነ ምሁራዊ ኃይል ክፍተት የተነሳ ስልጣንን በጠበንጃ የተቀዳጁና የሚቀዳጁ ኃይሎች በካፒታሊስት አገሮችና ኤክስፐርቶች ነን በሚሉ በቀላሉ የሚታለሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም ማለት ለነፃነት የተደረገውና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል የመጨረሻ መጨረሻ የውሃ ሽታ ይሆናል ማለት ነው። ከዚህ ዐይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ስንነሳ ከበሰሉና አገር ወዳድ ከሆኑ ምሁራን ምክር በመቀበል ስፈው ህዝብ የሚነቃበትና የሚደራጅበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። ሰፊውንም ህዝብ ሊያገለግሉና ለአገርም መሰረት ሊሆኑ የሚችሉ ትላልቅና ትናንሽ ተቋማት በየቦታው መገንባት አለባቸው። ሰፊውንም ህዝብ በአገር ግንባታ ላይ ለማሳተፍ ሰፋ ያለ ስትራቴጂ መቀየስ ያስፈልጋል። ከዚህ ዐይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ስንነሳ ቅድሚያ የሚሰጠውና ከአንዳንድ የኃያልነትን ደረጃ ላይ ከደረሱ አገሮች የምንማረው ነገር አንድን አገር በጋራ ለመገንባትት ከተፈለገ ለጊዜውም ቢሆን የጋራ-ግምባር የሆነ በአገር ወዳዶች፣ በሰለጠኑና በዕውቀት በዳበሩ ኃይሎች የሚመራ አገዛዝ መመስረቱ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በአስቸኳይ ምርጫ እያሉ መወትወት የአገራችንን ተጨባጭ ሁንታ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ውዥንብርም እንደመንዛት ይቆጠራል። አገር ወዳድ ነኝ የሚል ካለ ስልጣን አካባቢ ሳይደርስም ወይም ለስልጣን ሳይታገል በዕውቀቱ ለአገሩ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት ይችላል የሚል ዕምነት አለን። ይሁንና ምርጫ ይካሄድ የሚባል ከሆነ ደግሞ ልዩ የአሰራር መካኒዝም በመፍጠር አንድ ሰው ከስምንት ዓመት በላይ ስልጣን ላይ እንዳይቆይ በማድረግ የሰለጠነ ስራ መስራት ይቻላል። በየሎካሎች ቀስ በቀስ ህዝቡ ሊሳተፍ የሚችልበትና ህዝባዊ ኃላፊነትም ሊቀበሉ የሚችሉ ኃይሎች የሚሳተፉብት ምርጫ ሊካሄድ ይችላል። ያም ሆነ ይህ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው በምን መንገድና እንዴትስ ነው በአገራችን ምድር ዘላቂነት ያለው ሰላም ማስፈን የሚቻለው? በምን ዐይነት መንገድና የገንዘብ ምንጭ ዘዴ ነው አገርን በጋር መገንባት የሚቻለው? የሚሉት ከፍተኛ አትኩሮ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። ምክንያቱም ስልጣንን ከመያዝ ባሻገር ህዝባችን የመጀመሪያ መጀመሪያ አስተማማኝ ሰላምን ስለሚሻና፣ ከድህነት የሚላቀቅበትን ዘዴ ስለሚመኝ ብቻ ነው።