መስከረም አበራ
ሀምሌ 2016
1-መንደርደሪያ
በአማራ ህዝብ ላይ የታወጀዉ የጠላትነት ጥንስስ የተጀመረዉ በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ቢሆንም አማራ ጠልነት ህገ-መንግስታዊና ተቋማዊ ቅርፅ ይዞ የሃገራችን ፖለቲካ ማጠንጠኛ የሆነዉ ግን ህወሃት ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ነዉ፡፡ ከዚህ ዘመን ጀምሮ በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰዉና እየደረሰ ያለዉ ከ “ጄኖሳይድ” እስከ “አፓርታይድ” የሚደርሰዉ መንግስታዊ ወንጀል የአማራ ብሄርተኝነትን አይቀሬ አድርጎታል፡፡ ይህ የአማራ ብሄርተኝነት በፕ/ሮ አስራት ወልደየስና ጓዶቻቸዉ የተጀመረዉ ቀደምቱ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ ቀደምቱ የአማራ ብሄርተኝነት ታድያ በወቅቱ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ የነበረዉን እና ወደፊትም ሊፈፀም ያለዉን ግልፅ አደጋ በመረዳትና ለተረዳዉ እዉነት ፀንቶ በመቆም ረገድ እንከን የማይወጣለት ነበር፡፡ ሆኖም እንቅስቃሴዉ በዋናነት ከህወሓት በመጣበት ምህረት የለሽ ተግዳሮት ሳብያ መሪዉን በመነጠቁ የታሰበዉን ያህል ለመራመድ አልቻለም፡፡ ብሄርተኝነቱ በፈጠረዉ መላዉ አማራ ድርጅት(መአድ) በተባለዉ ቀደምት አታጋይ ፓርቲ ዉስጥ የተፈጠረዉ ዉስጣዊ ችግርም ተደማምሮ እንቅስቃሴዉን እሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ አድርጎታል፡፡
ከመአድ በኋላ እስከ ፋኖ ትግል ድረስ ያለዉ ዘመን የአማራ ህዝብ ያለሁነኛ አታጋይ ፓርቲ አዉላላ ሜዳ ላይ ተጋልጦ ሲሳደድ እና በጅምላ ሲገደል የኖረበት ዘመን ነዉ፡፡ በዚህ ዘመን ብቅ ብሎ የነበረዉ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የተባለዉ ፓርቲ መሪዎች በስተመጨረሻዉ የአማራ ጠሉ ጎራ ሰልፈኛ ከሆነዉ ከብዓዴን/የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መሪዎች የሚለዩበትን ገፅታ ፈልጎ ማግኘት በሚቸግር መልኩ ሩጫቸዉን በጅምሩ የጨረሱ የአጭር ርቀት ተጓዦች ሆነዉ ቀርተዋል፡፡ “ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት” የተባለዉ ድርጅትም የበኩሉን ለማበርከት የሞከረ ድርጅት ነዉ፡፡ እነዚህ እና የመሳሰሉ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ቢሆንም የአማራን ህዝብ በህይወት የመኖር መብት ጨምሮ ሌሎችን መብቶች ማስከበር አልተቻለም፡፡ በመሆኑም አሁን በተስፋ ሰጭ ጎዳና ላይ እየተራመደ ያለዉ ፋኖነት የሆነዉ የአማራ ብሄርተኝነት እንዲወለድ ሆኗል፡፡
ይህ ብሄርተኝነት ከቀደምቶቹ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች በእጅጉ በተለየ መንገድ ህዝባዊ መሰረትና የትግል ቁርጠኝነት ይዞ የተነሳ ነዉ፡፡ ትግሉ በትክክለኛ ምክንያት ላይ የቆመ፣ እጅግ አስቸኳይ የሆነዉን በህይዎት የመኖር መብትና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ያለመ በመሆኑ አመርቂ ዉጤቶችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ እያስመዘገበ ያለ የህዝብ ትግል ነዉ፡፡ ሆኖም ፋኖነት የሆነዉን የአማራ ብሄርተኝነት ትግል በተመለከተ የትግሉ ወዳጅ ከሆኑም ካልሆኑም ጎራዎች በርካታ ጥያቄዎች እያነሱ ይገኛል፡፡ ከሚንሱ ጥያቄዎች ትልቁን ድርሻ የሚይዘዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጋር ያለዉ መስተጋብር እንዴት ያለ እንደሆነ የሚጠይቀዉ ነዉ፡፡ይህን ጥያቄ በተገቢ መንገድ መመለሱ ለአማራ ህዝብ ትግል ቁልፍ ሚና ያለዉ ስለሆነ ይህን ሰነድ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡ ሆኖም ሰነዱ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ የተዘጋጀ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከጥያቄዉ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሌሎች እሳቤዎችንም ለማንሳት ይሞክራል፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ “አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት” በሚል ሃረግ የተጠቀሰዉ ሃሳብ ከመአድ፣ ከአብን እና ሌሎች የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች ዉስንነቶች፣ ክፍተቶችና ስህተቶች ትምህርት ወስዶ በፋኖነት የተገለጠዉን የአማራ ብሄርተኝነት ለመግለፅ ነዉ፡፡ ሰነዱ እንደ መነሻ ሃሳብ ብቻ የሚወሰድ፣ በተከታታይ ፅሁፎችና ዉይይቶች ሊዳብር የሚገባዉ መሆኑን ከወዲሁ ማሳወቅ እወዳለሁ፡፡
2. አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የቆመባቸዉ መርሆዎች
2.1 የቀደሙ ስህተቶችን ማጤንና ማረም፡- በዚህ ሰነድ መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረዉ የአማራ ህዝብን ዘርፈ ብዙ የህልዉና አደጋዎች ለመቀልበስ ታሳቢ ተደርገዉ የተጀመሩ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሎች ከአደጋ መታደግ ሳይችሉ ቀርተዉ በተገላቢጦሹ የአማራ ህዝብ ወደ ሃገሩ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዳይገባ የሚከለከልበት የአፓርታይድ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የአማራ ህዝብ ለ30 በላይ አመታት በዘለቀ ጊዜ ማንነት ተኮር ግድያና መሳደድ የእለት ተዕለት ህይወቱ አካል እስከመምሰል ደረሰ፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ህጋዊ መስለዉ በግልፅ ሲፈፀሙ በአማራዉ በኩል አደጋዉን የሚመጥን ትግል ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ የሚያመለክተዉ ቀደምቶቹ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች ስህተቶች የበዙባቸዉ፣ ክፍተቶች የበረከቱባቸዉ እንደነበሩ ነዉ፡፡
አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሉን የጀመረዉ የቀደሙ ስህተቶችን በማረም፣ ክፍተቶቹን በመሙላትና ዉስንነቶቹን ለመመርመርና ለማሻሻል በማሰብ ነዉ፡፡ እነዚህ የቀደሙ ስህተቶች በርካታ ቢሆኑም ይህ ሰነድ ከተፃፈበት አላማ ላለመዉጣት ቀደምቶቹ የአማራ ብሄርተኝነቶች ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር በነበራቸዉ መስተጋብር አንፃር በታዩ ስህተቶችና ክፍተቶች ላይ ለማተኮር ይሞክራል፡፡ ከቀደምቱ መአድ ቢጀመር የአማራ ህዝብ ከአማራ ጠሉ ስርዓት የተጋረጠበትን አስከፊ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም የተቋቋመ ነበር፡፡ ሆኖም ፓርቲዉ የተፈጠረበትን በአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣ ማንነት ተኮር ጥቃት በማንነት ተደራጅቶ የመመከት ተገቢ ጅማሬ ከግቡ ሳያደርስ ይልቁንም በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ የነበረዉ መከራ እተባባሰ በሄደበት ሁኔታ በርካታ መሪዎቹ እና አባላቱ መኢአድ የተባለዉን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፓርቲ ማቋቋማቸዉ መአድን ወደ ሞት አፋፍ ያጣደፈ ጉልህ ስህተት ነበር፡፡
ይህ መሰረታዊ ስህተት ሌላ ከሃገራችን ህገ-መንግስት ጋር የሚጋጭ ስህተት ወልዷል፡፡ የሃገራችን ህገ-መንግስት የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነዉ በሃገሪቱ በሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ስምምነትና በጎ ፍቃድ ላይ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ የአማራ ህዝብ ጥብቅ ፍላጎት የሆነዉን የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት ለማረጋገጥም ቢሆን የአማራ ህዝብን በብሄር አደራጅቶ እንደማንኛዉም ሌላ ብሄረሰብ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት እጣ ፈንታ ላይ የሚወስንበትን ፖለቲካዊ አቋም እንዲይዝ የሚያደርግ አታጋይ ፓርቲ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህን ሲያደርግ ብቻ ወቅቱ የሚጠይቀዉን የፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ እየተናገረ፣ በብሄር ተደራጅቶ የራሱን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር ይችላል፡፡ መአድ ያለጊዜዉ ወደ መኢአድነት ሲቀየር የሰራዉ ስህተት የወቅቱን የፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ ይዞ ሲጓዝበት የነበረዉን ተገቢ አካሄድ ትቶ ህገ-መንግስታዊም መሰረትም ሆነ የወቅቱ የፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ በሌለዉ የትግል ዘይቤ ለመሄድ መምረጡ ነዉ፡፡ መኢአድ በዚህ አካሄዱ ያለመርከብ በዉቅያኖስ ዉስጥ ተጉዞ አንድ ከተማ ለመድረስ የተመኘ ተጓዥ ይመስላል፡፡
በአሁኑ የሃገራችን የፖለቲካ ዘይቤ አንድ የፖለቲካ ተጓዥ ብሄረሰቡን መርከብ አድርጎ፣ የብሄረሰብ መብት ማስከበርን ቀዳሚ አላማዉ አድርጎ ነዉ ከኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ጋር መስተጋብር የሚፈጥረዉ፡፡ ስለ ሃገረ-ኢትዮጵያ ቀጣይነት
መምከር ተገቢ የሚሆነዉ ደግሞ ከሌሎች አቻ የብሄር መርከበኞች ጋር በመታደም ብቻ ነዉ፡፡ ባጭሩ ወደ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚኬደዉ ተገቢ ጉዞ የሚባለዉ በብሄር በኩል ሲያዘግሙት ብቻ ነዉ፡፡ በመሆኑም ጥሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን በመጀመሪያ ጥሩ ትግሬ፣ጥሩ ኦሮሞ፣ጥሩ ሲዳማ፣ ጥሩ ኮንሶ፣ ጥሩ አማራ፣ ጥሩ ከምባታ ወዘተ… መሆን ያስፈልጋል ሲሉ የብሄር ፖለቲካዉ የዘመኑ ቀሳዉስት ሊያስረዱ ሞክረዋል፡፡ “l’m Oromo first” የሚለዉ ዝነኛ አባባል የተነገረዉ ይህንኑ ወቅታዊ የፖለቲካ መንፈስ እጥር ምጥን አድርጎ ለመግለፅ ነበር፡፡
በብሄርተኝነት መርከብ ተሳፍረዉ ከሚያደርጉት ጉዞ ዉጭ ወደ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚደረግ ጉዞ በትምክህተኝነት የሚያስፈርጅ፣ የራስን ብሄር ፍላጎት በኢትዮጵያ ስም በሌሎች ላይ በመጫን የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት ለመስጠት የመሞከር እብሪተኝነት ሲያስወርፍ የኖረ “ስሁት” አካሄድ ነዉ፡፡ ይህን ወቅታዊ ሁኔታ ባላገናዘበ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የሚፀና የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትም ሆነ የሚከበር የአማራ ህዝብ መብት የለም፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሃገረ-መግስት ቀጣይነትም ሆነ የአማራ ህዝብ ህልዉና ጥያቄ ዉስጥ ይገኛል፡፡
የመአድ ያለጊዜዉ መኢአድ መሆን ያመጣዉ ሌላ ስህተት የአማራ ብሄርተኝነትን በአማራ ህዝብ ዘንድ የማስረፅና ህዝቡ በአማራ ጠሉ ስርአት የተጋረጠበትን በዉል ለማስረዳት የሚያስችል ፋታ ያሳጣ መሆኑ ነዉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የአማራ ህዝብ አማራ-ጠሉ ስርዓት የሰነቀለትን አደገኛ ስንቅ ቀምሶት ብቻ እንዲረዳዉ አስገድዷል፡፡ በአንጻሩ መአድ መዒአድ ለመሆን ሳይቸኩል ተገቢዉን ፋታ ወስዶ ቢሆን ኖሮ የአማራ ህዝብ በማንነቱ የተቃጣበትን አደጋ በተገቢዉ ሁኔታ መቀልበስ በሚያስችል የፖለቲካ አቋም ላይ ቆይቶ እራሱንም ኢትዮጵያንም ለመታደግ የሚያስችለዉን ትግል ቀደም ብሎ መታገል ይችል ነበር፡፡
ከመአድ መዳከም በኋላ የመጣዉ በአብን የሚመራዉ የአማራ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ አብን እንደተመሰረተ ሰሞን የአማራ ብሄርተኝነት እና የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት መስተጋብር አስመልክቶ በዋነኛ አመራሮቹ በኩል በአደባባይ ይገልፀዉ የነበረዉ ንግግር ዉጤቱ በዉል ያልታሰበበት ስለነበረ ፓርቲዉ ገና በሁለት እግሩ ሳይቆም ከአማራ-ጠሉ ጎራ ከፍተኛ ትችትን እንዲያስተናግድ አድርጓል፡፡ ይህ ማስተዋል የጎደለዉ የአብን አመራሮች ንግግር ከአማራ ልሂቃን በኩል የሚሰማዉን ማንኛዉም የፖለቲካ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ጥርጣሬ እና ስጋት የሚያየዉ የአማራ-ጠሉ ጎራ አማራዉን ትምክህተኛ እያለ ለማብጠልጠል አዲስ የፕሮፓጋንዳ ግዳይ እንዲያገኝ ያደረገ ነበር፡፡ ሌላው በአብን በኩል ሲቀነቀን የነበረው የትግላችን መንታ ነው መርሁ፣ ማለትም የአማራ ብሔርተኝነት እና የሀገረ-ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት በእኩል ትግል አሳካለሁ ማለቱ በሁለት ያጣ ውጤት እንዲደመደም አድርጎታል፡፡
በዚህ ስህተት ሳቢያ የአብን እንቅስቃሴ የአማራ ብሄርተኝነትን እንደጠላት ከሚያዩ ኢትዮጵያዉያን ጎራ ጭምር በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የአብንን ስህተት በማጤን የአማራ ህዝብ ትግል የአማራ-ጠሉ ጎራ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ እንዳይሆን ጥንቃቄ የተሞላበት የህዝብ ግንኙነት ስራን ለመስራት ይሞክራል፡፡ በመሆኑም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር ምንም አይነት ጠብ የሌለዉ መሆኑ አበክሮ ለማስረዳት ይሞክራል በይበልጥ ደግሞ በተግባር ለማሳየት ይሰራል፡፡ ይህ ትግል ከኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ጋር ጠብ ሊኖረዉ ቀርቶ የሚታገለዉ ሀገረ-ኢትዮጵያ የአማራን እና የሌሎች ወንድም እህት ህዝቦችን መብት አክብራ በጥንካሬ እንድትጓዝ ነዉ፡፡ በተጨማሪም የአማራ ህዝብ የፋኖነት ትግል በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ምንም አይነት የበላይነትና የበታችነት ግንኙነት እንዲኖር እንደማይፈቅድ፣ እየታገለ ያለዉም የእራሱንም ሆነ የሌሎች ወገን ህዝቦችን መብት የምታከብር ኢትዮጵያን እዉን ለማድረግ እንደሆነ ለማሳወቅ ይጥራል፡፡
2.2. ባልተሄደበት አዲስ የትግል ስልት የሚጓዝ
ባለፉት ከሰላሳ በላይ አመታት የአማራ ህዝብ በከፍተኛ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች ዉስጥ የሚገኘዉ የወቅቱን የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በዉል አጢኖ ህዝቡን ከእልቂት የሚታደግ ጠንካራ የአማራ ብሄርተኛነት ማምጣት ስላልቻለ ነዉ፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ይህን የሽንፈት ታሪክ ለመቀየር አልሞ የተነሳ እንቅስቃሴ ነዉ፡፡ ስለሆነም ከዚህ ቀደም የተሞከሩ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ዉጤት አልቦ ያደረጉ ስህተቶችን ላለመድገም በከፍተኛ ጥንቃቄ በአዲስ ስልት የሚጓዝ ነዉ፡፡ በአንድ አይነት የስህተት መንገድ እየተመላለሱ የተለየ ዉጤትና ድል መጠበቅ ስለማይቻል አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሉን በአዲስ መንገድና ስልት ለማስኬድ ወስኗል፡፡
እነዚህ አዲስ መንገዶች በርካታ ቢሆኑም በዚህ ሰነድ ሁኔታ ከአማራ ብሄርተኝነት እና ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት አንፃር የተተለሙ አዲስ የትግል ስልቶችን በመቃኘቱ ላይ አተኩራለሁ፡፡
ከዚህ አኳያ ቀዳሚ የተደረገዉ አዲስ የትግል ስልት መአድ ወደ መኢአድ ለመቀየር የፈጠነዉን ስሁት ፍጥነት ባለመድገም ይልቅስ ሙሉ ሃይልን የአማራ ብሄርተኝነትን በማጎልበት ላይ በማድረግ በቂ ጊዜን መዉሰድ ነዉ፡፡ በዚህ እጅግ አስፈላጊ የጊዜ ፋታ ዉስጥ በርካታ አስፈላጊ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ የመጀመሪያዉ የአማራ ህዝብ ከአማራ-ጠሉ ስርአት የተቃጡበትን አደጋዎች በዉል እንዲረዳ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ህዝቡ የተጋረጠበትን አደጋ ለመቀልበስ የሚያስችሉ ማታገያ ጥያቄዎቹ በህዝቡ ዘንድ የሚታወቁ ቢሆንም በተቀራራቢ ሁኔታ መግባባት ላይ የተደረሰባቸዉ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ይሰራል እየተሰራም ነዉ፡፡ ብሄርተኝነቱን በላቀ ግንዛቤና በጠንካራ የትግል ስነ-ምግባር መርተዉ ዳር ሊያደርሱ የሚችሉ መሪዎችን ማፍራትም ሶስተኛ አስፈላጊ ስራ ነዉ፡፡ ሌላዉና አራተኛ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለዉ ስራ የአማራ ብሄርተኛነት ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስፋ እንጅ ስጋት እንዳልሆነ በተጨባጭ የማሳየት ስራ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ሙሉ ትኩረቱን በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ለማድረግ የሚወስደዉ ጊዜ የራሱን ዉስጠ–ብሄር የፖለቲካ የቤት ስራ ሰርቶ አጠናቆ ከሌሎች ወንድም እህት ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ስለ ኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመምከርና ለመወሰን የሚያስችል ጥንካሬን ይዞ ለመዉጣት የሚያስፈልግ አስፈላጊ ጊዜ ነዉ፡፡
አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ይህን ያልተሄደበት አዲስ መንገድ ለመተግበር የወሰነዉ አማራ-ጠሉ ጎራ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን የአማራ ብሄርተኝነት መደበቂያ ዋሻ አድርጎ የመቁጠርና ሁለቱንም በአንድ ድንጋይ በማጥቃት የማሽመድመድ የቆየና የተካነበት ዘዴ ስላለ ከዚህ በተቃራኒ በመጓዝ ሁለቱንም ብሄርተኝነቶች ለማዳን በማሰብ ነዉ፡፡ በሌላ አባባል የኢትዮጵያና የአማራ ብሄርተኝነትን በዉል ያልነጣጠለ የትግል ስልት ለአማራ-ጠሉ ጎራ ጥቃት ምቹ ሆኖ መቅረብ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ቀላቅሎ የመጣን የአማራ ብሄርተኝነት አማራ-ጠሉ ስርዓት ከመቅፅበት በትምክህተኝነት፣ በጨፍላቂነት እና በጠቅላይነት ፈርጆ አማራዉን የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በትግላቸዉ ያመጡትን የብዝሃነት ፖለቲካ ለመቀልበስ የሚሞክር የብሄረሰቦች ብሄራዊ ጠላት አድርጎ ያቀርባል፡፡
ይህ አደገኛ ፍረጃ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በየብሄራቸዉ ጎራ ገብተዉ ስለ ብሄራቸዉ መብት መከበር ብቻ ሲሰሩ የኢትዮጵያን ሃገረ-መንግስት የማስቀጠሉ እዳ በአማራ ህዝብ ጫንቃ ላይ ብቻ የወደቀ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የራሱን ብሄርተኝነት ያላሳደገዉ የአማራ ልሂቅም ይህን አደገኛ ሃላፊነት የሚቀበለዉ የአማራን ህዝብ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት መስዋዕት በማድረግ ሆኖ ኖሯል፡፡ አማራዉም ለኢትዮጵያ ቀጣይነት የሰራ መስሎት ይሄን እጅግ አደገኛ ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነትም ቢሆን ያልጠቀመ ሃላፊነት በመቀበሉም የሚተርፈዉ ምስጋና እና ሽልማት ሳይሆን “ከሌሎች ብሄረሰቦች የበለጡ ኢትዮጵያዊነት አለኝ የሚል ትምክህተኛ” የሚል ማሸማቀቂያ ነዉ፡፡ ይህ አስጠቂ የትግል ስልት የመአድና የመኢአድን ጉልበት ያዛለ ብቻ ሳይሆን አንድነት እና ሰማያዊ በሚባሉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፓርቲ ጥላ ስር ገብተዉ ይታገሉ የነበሩ የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኞችን በግል ሳይቀር ግራ ሲያጋባ የኖረ፣ዳግመኛ ሊኬድበት የማይገባ የሽንፈት መንገድ ነዉ፡፡
በአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ የአማራ ህዝብ ትግል ሩቅ መንገድ በመጓዝ እራሱንም ኢትዮጵያንም ለመታደግ ከፈለገ በትግሉ የመጀመሪያዉ ወሳኝ አመታት (Formative Years) ሙሉ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት በአማራ ብሄርተኝነት ጉዳዮች ብቻ ነዉ፡፡ በእነዚህ ወሳኝ ጊዜያት ስለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት እጣ ፈንታ የሚበይን ሆነ የሚያወሳ የትግል ስልት ለመተለም መሞከር “እራስ ሳይጠና ጉተና” ከመሆኑም ባሻገር ከአማራ-ጠሉ ጎራ በኩል በተለመደዉ ዱላ ተደጋሞ ለመመታት በተለመደዉ የስህተት መንገድ መመላለስ ነዉ፡፡ ስለሆነም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት መነሻዉን በአማራ ህዝብ ጥያቄዎችና በደሎች ላይ አድርጎ፣ በዛዉ ላይ በቂ ጊዜ ወስዶ ቆይቶ ዉስጠ ብሄር የቤት ስራዉን በስኬታማ መንገድ ፈፅሞ መዳረሻዉን ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጋር በመመካከር የፀናች የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስትን እዉን በማድረግ ላይ ያደርጋል፡፡ ፋኖነት የሆነዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሉን ከዚህ ቀደም ባልተኬደበት መንገድ ማድረጉ ገና ከጅምሩ በርካታ አበረታች ዉጤቶችን እያስገኘለት ይገኛል፡፡
ከላይ የተገኙት ዉጤቶች የመጀመሪያዉ አዲሱ የትግል ስልት የአማራ ብሄርተኝነትን ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ነጥሎ _ ማቅረቡ አማራ-ጠሉ ስርዓት እንደለመደዉ የአማራብሄርተኝነት እና የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን አዳብሎ ለማሽመድመድ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይልቅስ የአማራዉ የብቻ ሃላፊነት መስሎ የኖረዉ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትን የማስቀጠል ሃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን እንዲታወቅ ሆኗል፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያን በአማራ በኩል ሲጠላና የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትን ሲያንቋሽሽና አፈርሳለሁ እያለ ሲገለገል የነበረዉ አማራ-ጠሉ ጎራ የኢትዮጵያ ቀጣይነት የሚያስጨንቀዉ ሃገር ወዳድ መስሎ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አማራ-ጠሉ ጎራ ከዚህ ቀደም በትምክህተኝነትና ጨፍላቂነት ዘለፋ አድበስብሶ ሲያልፋቸዉ ከነበሩ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች እና ሲፈራዉ ከኖረዉ እዉነተኛዉ የአማራ ብሄርተኝነት ጋር በግላጭ ለመፋጠጥ ተገድዷል፡፡ ይህ አካሄድ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነትም ሆነ ለአማራ ህዝብ መብት መከበር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነዉ፡፡ ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ላይ ሙሉ ትኩረቱን ማድረጉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ቸል ማለቱ ወይም ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አደጋ መሆኑን ሳይሆን የኢትዮጵያንም የአማራንም ህልዉና ለመታደግ የሚያስችል የድል መንገድ መሆኑን ነዉ፡፡
2.3 ስህተት መሰራት የሌለበት ነዉ
አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ስህተት መስራት የለበትም የሚለዉ መርሆ ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጋር ካለዉ መስተጋብር አንጻር ሲታይ የሚሰጠዉ ትርጉም በኢትዮጵያ ብሄርተኝነትና በአማራ ብሄርተኝነት መካከል ሊኖር የሚገባዉን ጤናማ ሚዛናዊነት በትክክል አስጠብቆ መራመድ መቻል ነዉ፡፡ የአማራ ህዝብም ሆነ ልሂቅ በታሪኩ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነትን በእጅጉ የሚፈልግ ለዚሁም በአፍ ሳይሆን በተግባር በርካታ መስዋዕትነትን የከፈለ ነዉ፡፡ ይህ አካሄድ በራሱ ጥፋት ያለዉ ነገር ባይሆንም የወቅቱን የሃገሪቱን የብሄር ፖለቲካ የጨዋታ ህግ ተረድቶ የአማራ ህዝብ እንደ ብሄር ያሉበትን አደጋዎች በማጤን በሁለቱ ብሄርተኝነቶች መካከል ሊኖር የሚገባዉን ጤናማ ሚዛናዊነት ለማስጠበቅ አለመሞከሩ ግን ዉድ ዋጋ ያስከፈለ ስህተት ነዉ፡፡
የቀደመዉ ያልተመጣጠነ አካሄድ ስህተት ስለነበረ ብሎ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኝትን እርግፍ አድርጎ መተዉም ሌላ አዲስ ስህተት መፍጠርም ይሆናል፡፡ ይህ ስህተት ከሚሆንባቸዉ በርካታ ምክንያቶች ሁለቱ ዋነኞች ናቸዉ፡፡ የመጀመሪያዉ የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ስሪት ዉስጥ የማይተካ ሚና ያለዉና የፖለቲካ ስነልቦናዉም ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በመላዉ ኢትዮጵያ ተበትነዉ የሚኖሩ በመሆናቸዉ ነዉ፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነትም እነዚህ የአማራ ተወላጆች በሃገራቸዉ ላይ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸዉ ተከብረዉላቸዉ እንዲኖሩ ማስቻልን አልሞ የተነሳ ነዉ፡፡ ይህ የሚሳካዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት ሲኖረዉ ነዉ፡፡ ስለሆነም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስትን መቀጠል በእጅጉ የሚፈልገዉ ነገር ነዉ፡፡
2.4 ማሸነፍን ብቻ ታሳቢ አድርጎ የሚሰራ
አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ቀዳሚ አላማዉ በመላ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን በህይወት የመኖር መብት የማስከበር ነዉ፡፡ የሰዉ ልጆች በህይወት የመኖር መብትን ማክበርና ማስከበር የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መግባቢያ ቋንቋ መሆን ያለበት ጉዳይ ነዉ፡፡ ዜጎች በሃገራቸዉ እንደልባቸዉ ተንቀሳቅሰዉ እንደልባቸዉ የመስራት ሰብዓዊ መብታቸዉ መጠበቅ ብቻ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትን ህልዉና ቀጣይነትን ያረጋግጣል፡፡ ዜጎች በገዛ ሃገራቸዉ የሆነ ቦታ ላይ መገኘታቸዉ የወንጀል ወንጀል ሆኖ በጭካኔ ሞት የሚያስቀጣ ከሆነ ኢትዮጵያ አለች ማለት አይቻልም፡፡ የዘር ማጥፋትን ማቆምና ማስቆም ያልቻለ መንግስት ህገ-መንግስታዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ሰብዓዊ ነኝ የማለት ብቃት የለዉም፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በዋናነት ለአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብት የሚታገል ቢሆንም በአጠቃላይ እሳቤ ደረጃ ግን የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ሰብዓዊ መብት ያለ ቅድመ ሁኔታ መከበር መቻሉ ያገሪቱ ፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ እንዲሆን አጥብቆ ይሻል፡፡
ይህ አይነቱ የዜጎችን የሰብዓዊ መብት የማስከበር ትግል ደግሞ አሸናፊነትን ብቻ አንግቦ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ምክንያቱም ትግሉ አሸናፊ መሆን ካልቻለ ዘር ማጥፋትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሃገራችን መንግስታዊ አስተዳደር ዘይቤ ሆኖ መቀጠሉ ነዉ፡፡ ዘር ማጥፋትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደ አዘቦት ተግባር የሚቆጥር መንግስታዊ አስተዳደር ደግሞ ሃገረ-መንግስት ሊያስቀጥል ከቶ አይቻለዉም፡፡ ስለዚህ የሰብዓዊ መብቶችን የማስከበርን ክቡር አላማ ይዞ የተነሳዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አሸናፊ ይሆን ዘንድ ግድ ነዉ፡፡
3 በአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 3.1 “ከሌሎች ንዑስ ብሄርተኝነቶች በምን ይለያል?”
ይህ ጥያቄ በሁለት አበይት ምክንያቶች ይነሳል፡፡ የመጀመሪያዉ ብሄርን ፖለቲካ ማድረግ በሃገራችን ላይ ያስከተለዉን ዉድመት ከመገንዘብ የሚነሳ ስጋት አዘል አጠያየቅ ነዉ፡፡ ይህ በራሱ ችግር ያለበት ነገር ባይሆንም በዉስጡ ያዘለዉ ስህተት ግን አለ፡፡ ስህተቱም ሃገራችን በብሄር ፖለቲካ ምክንያት የተጋረጠባትን የመፍረስ አደጋ ለማስቀረት አማራዉ በብሄር መደራጀት የለበትም፤ አማራዉ በብሄር መደራጀት ከጀመረ ሃገሪቷ መፍረሷ ነዉ የሚለዉ ነዉ፡፡ የዚህ እሳቤ ሌላዉ ገፅ ኢትዮጵያ የቆመችዉ ወይም ልትቆም የሚገባት በአማራ ትከሻ ላይ ብቻ ነዉ የሚል ከእዉነታ የተፋታ አመክንዮ ነዉ፡፡ አስተሳሰቡ አደገኛ ዉጤት ያለዉ ስህተት ያዘለ ቢሆንም በአብዛኛዉ የአማራ ልሂቅና የኢትዮጵያን መቀጠል በሚሹ የሌሎች ብሄሮች ልሂቃን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ለረዥም ዘመናት ገዥ ሃሳብ መስሎ የኖረ እሳቤ ነዉ፡፡
ይህ እሳቤ ስህተት ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ መሆኑን በዚህ ሰነድ 2.1 እና 2.2 ላይ በአጭሩ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ሃሳቡን እጅግ በአጭሩ ለማስታወስ ያህል አማራ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ተደራጅቶ የብሄር ፖለቲካዉን ሊታገል የሞከረበት አደገኛ አካሄድ ለአማራ-ጠሉ የብሄር ፖለቲካ ቀሳዉስት የምቾት ከባቢ (Comfort Zone) ሆኖላቸዉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እና የአማራ ህዝብ አዳብለዉ በመቀጥቀጥ ሁለቱንም ለማሽመድመድ ያስቻላቸዉ የተካበት መንገድ ነዉ፡፡
በተጨማሪም ይህ ስልት ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አይነተኛ ጉልበት የሆነዉ የአማራ ህዝብ እያለፈበት ያለዉን አሰቃቂ ጥቃት እና የህልዉና አደጋ እንደሌለ አድርጎ በመካድ እዉነተኛ ባልሆነ የደህንነት ስሜት ዉስጥ እራሱን እያታለለ ሲጓዝ የኖረ አካሄድ ነዉ፡፡ በመሆኑም የትግል ስልቱ ከእዉነት የተጣላ እና ፍሬ ቢስ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ይህ የትግል ስልት በሃገራችን ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ፖለቲካ ዉስጥ እዚህ ግባ የሚባል ተጽኖ የሌለዉ ሆኗል፡፡ የዚህ የትግል ስልት መንገደኛ ከሆኑ ድርጅቶች ዋናዉ የሆነዉ ኢዜማ የተባለዉ ፓርቲ ደግሞ ስልጣን ላይ ያለዉ አማራ-ጠል ዘረኛ ስርአት ገባር ሆኖ ከመግባቱ ባሻገር በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለዉን ግልፅ ዘር ማጥፋት በአደባባይ ክዷል፡፡ የኢዜማ ለብሄር ፖለቲካዉ ግብር መግባት የኢትዮጵያ ብሄርተኝነቱን ጎራ መጠጊያ አልባ ከማድረጉም በላይ ስልጣን ላይ ያለዉ ዘረኛ ስርዓት “ተፎካካሪ” ፓርቲን ስልጣን እስከማጋራት የደረሰ “ዲሞክራሲያዊነት” እንዳለዉ እያነሳሳ ሰሚን የሚያሰለችበት የፕሮፓጋንዳ ሲሳዩ ሆኗል፡፡
“የአማራ ብሄርተኝነት ከሌሎች ብሄርተኝነቶች በምን ይለያል?” የሚለዉ ጥያቄ የሚነሳበት ሁለተኛዉ ምክንያት ሸር የማያጣዉ፣ አዉቆ ማደናቆር እና ፍርደ-ገምድልነት የተጣመሩበት ነዉ፡፡ በዚህ ጥያቄ ዉስጥ ያደፈጠዉ የፖለቲካ ሸር በአማራ ህዝብ ላይ ዘር ማጥፋት ወንጀል እየሰራ ያለዉን አማራ-ጠል ስርአትና ይህንኑ ለመከላከል የተፈጠረዉን የአማራ ብሄርተኝነት በእኩል የጥፋተኝነት ወንበር የሚያስቀምጥ ነዉ፡፡ በሌላ አባባል ጥያቄዉ ገዳይና ሟችን በአንድ ላይ
አዳብሎ፣ በዉስጠ ታዋቂ ለገዳይ የሚወግን ነዉ፡፡ ይህ እሳቤ የረሳዉ ነገር የአማራ ብሄርተኝነትን እና ሌሎች ንዑስ ብሄርተኞችን የፈጠረዉ ምክንያት ሰፊ ልዩነት ነዉ፡፡ በርግጥ ይህ እሳቤ እንደሚለዉ የአማራ ብሄርተኝነት ንዑስ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ ነገር ግን ዋናዉ ነጥብ አማራዉን ለንዑስ ብሄርተኝነት የጋበዘዉ የተደቀነበት የዘር ማጥፋን የሚያክል የሞት ሽረት ጉዳይ እንጂ እንደሌሎቹ በፋሽት ጣሊያን አማራ-ጠል ፕሮፓጋንዳ ላይ ተሸፍኖ በቀላሉ ስልጣን ላይ የመፈናጠጥ የስልጣን ጥም አይደለም፡፡
እነዚህ ጠያቂዎች ግን የመነሻዉን ልዩነት አዉቀዉ ትተዉ መጨረሻዉ ከብሄርተኝነት ስለሆነ የአማራም፣ የህወሃትም፣ የኦነግም ብሄርተኝነት ያዉ ብሄርተኝነት ነዉ ሲሉ ያደናቁራሉ፡፡ ይህን ሲሉም አማራዉ ንዑስ ብሄርተኛ ላለመባል ዝም ብሎ የማለቅን አማራጭ ብቻ ያቀርቡለታል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ጥያቄ የመነጨበት እሳቤ አንድ ክፉ ድርጊት (Action) አፀፋዊ እራስን የመከላከል ድርጊት (Reaction) የማስከተሉን አይቀሬ ሃቅ የካደ የጠላት በለሃ ልበልሃ ነዉ፡፡ ይህን በማድረግ ወይ ዝም ብሎ እንዲሞት እታገላለሁ ካለ ደግሞ ግልፅ የሆነዉን የትግሉን ምክንያት አዉቆ ለተፃፈና ጆሮ በማስረዳት እንዲባዝን የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡
በአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች ምንጫቸዉ ምንም ይሁን ምን ጥያቄዉ እስከተነሳ ድረስ ቢያንስ አንድ ጊዜ ለዋነኛ ጥያቄዎች መልስ መስጠቱ ለአማራዉ ትግል ብርታት ይሆናል እንጅ ጉዳት ስለሌለዉ ወደዛዉ እንለፍ፡፡ የአማራዉ ብሄርተኝነት ከሌሎች ንዑስ ብሄርተኞች የሚለይበት በርካታ ሃቆች አሉ፡፡
የመጀመሪያ- የአማራ ብሄርተኝነት ግልፅ ከሆነ መንግስታዊ ዘር ማጥፋት ወንጀል የተነሳ የታለፈባቸዉ ተጨባጭ የህይወት ተሞክሮዎች (lived experiences) በመነሳት የተተለመ እራስን የመከላከል የአፀፋ ብሄርተኝነት መሆኑ ነዉ፡፡ ስልጣን የያዘዉ አማራ-ጠል ስርዓት የብሄረ-ኢትዮጵያ ርዕዮትን ከማበሻቀጥ አልፎ የብሄረ ኢትዮጵያ መድህን አድርጎ ሰፈዉን የአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብት እስከመግፈፍ የደረሰ፣ግዴታን ያላገናዘበ የመብተኝነት አዉዳሚ ጉዞ ላይ ይገኛል፡፡ የአማራ ብሄርተኝነትን ወለዱ ይህ አዉዳሚ ጉዞ በመግታት እራስን የመከላከል ተገቢ ፍላጎት ነዉ፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ንዑስ ብሄርተኝነቶች በተለይ ህወሃትና ኦነግ በብሄር መደራጀት በቀላሉ የህዝብን ስሜት አገንፍሎ ለስልጣን ስለሚያበቃ የመረጡት መንገድ እንደሆነ መሪዎቻቸዉ በግልፅ የተናገሩት ሃቅ ነዉ፡፡ በአማራ ህዝብ አንፃር ህዝብን በብሄር ማደራጀት ቀላል እንዳልሆነ የአማራ ብሄርተኝነትን እዉን ለማድረግ የፈጀዉ ረጅም ዘመን ምስክር ነዉ፡፡
በአጠቃላይ የአማራ ብሄርተኝነት በግልፅ እየደረሰበት ያለዉን አደጋ ለማስቆም ሲባል በጣም ከረጅም ዘመን በኋላ የተጀመረ እንጂ እንደ ህወሃትና ኦነግ ንዑስ ብሄርተኝነቶች በፍጥነት የስልጣን ማማ ላይ ለመሰየም ቀላሉ መንገድ ነዉ ተብሎ ተመርጦ እዉነቱንም ዉሸቱንም እየተደበላለቀ የተሸመነ የሀሰት ሸማ አይደለም፡፡
ሁለተኛዉ የአማራ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት መፈጠርም ሆነ መቀጠል ጋር ምንም ጠብ የሌለዉ መሆኑ ነዉ፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት የብሄር-ኢትዮጵያ ርዕዮትን አንግቦ ለሃገረ-መንግስቱ ቀጣይነት በሙሉ ልቡ የሚሰራ ነዉ፡፡ የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የአማራ ህዝብ ከብሄረ-ኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ጥብቅ የስነ-ልቦና ቁርኝት ስለሚያዉቅ ከህዝብ ስነ-ልቦና በተቃራኒ የመሄድ እብሪት ስለሌለዉ ነዉ፡፡ በተጨማሪም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አንዱ አላማዉ በመላ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን መብት ማስከበር ስለሆነ ነዉ፡፡ ይህን አላማ ለማሳካት የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት ጥያቄ ዉስጥ የማይገባ ነገር ነዉ፡፡
አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከብሄር ኢትዮጵያ ርዕዮት ጋር የማይጣላ ይልቅስ ተደጋግፎ የሚሄድ ነዉ ሲባል የሚነሳ ሌላ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸዉም የንዑስ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች ግራ ዘመም ስለሆኑ የአማራ ብሄርተኝነትም ግራ ዘመም መሆን አለበት፤ግራ ዘመም ሆኖ ደግሞ ስለ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት አስባለሁ ማለት አብሮ አይሄድም የሚል ነዉ፡፡ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ አካላት በአመዛኙ የህወሃትና የኦነግ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ ደጋፊዎችና ወዳጆቻቸዉ ናቸዉ፡፡ ኦነግና ህወሃት ትግላቸዉን የጀመሩት ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥነት በመክሰስ ነበር፡፡ ትግላቸዉን ሲያጣጡፉ የነበረዉም ኢትዮጵያን መፍረስ ያለባት የአማራ ስሪት እንደሆነች በመደስኮር ነዉ፡፡
ይህን ሲሉ በነበረበት አንደበታቸዉ ደግሞ ስልጣን ሲይዙ ኢትዮጵያ ተጠብቃ መኖር ያለባት ዉብ ሃገር እንደሆነች መለፈፍ ጀመሩ፡፡ ስልጣን ላይ ቁጭ ብለዉ ሲያዩዋት ብቻ የምታምራቸዉን ኢትዮጵያን በተመለከተ ትላንት ምን እያሉ ሲያበሻቅጥዋት እንደነበር የሚያስታዉቸዉ ሲገኝ ደግሞ ያንን የተናገሩት ብስለት በማጣት እንደሆነ ሲያስረዱ ይገኛሉ፡፡
ይህንን አቋም የለሽ የፖለቲካ ዘይቤያቸዉን ነዉ የግራ ፖለቲካ ተከታይነት አድርገዉ የሚያስቡት፡፡ የሆነዉ ሆኖ ስልጣን ከመያዛቸዉ በፊት በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ላይ ሲያወርዱት የኖሩት የጥፋት ዉርጅብኝ የግራ ዘመምነት የፖለቲካ ዘይቤ ነዉ ከተባለ እንኳን ያንን አቋማቸዉን ይዘዉ አልዘለቁ፡፡ አሁን ላይ ከስልጣን ጥፍጥና የተነሳ የቀኝ ፖለቲካ መንገደኛ ነን እያሉ ጭራሽ አማራዉ ሃገር እዳያፈርስ እንሰጋለን እያሉ ነዉ፡፡ በአንፃሩ አማራዉ የእራሱን ብሄር-ተኮር ጥያቄ ለማስመለስ ኢትዮጵያን ማበሻቀጥ ግድ እንዳልሆነ ከበፊትም ጀምሮ ያዉቅ ነበር እና ዛሬም ድሮም ኢትዮጵያን ሳያዋርድ፣ ክፏን ሳያወራ በነበረበት ትክክለኛ መንገድ ላይ ቆሞ ከገዛ ሃገሩ ሊያገኘዉ የሚገባዉን መብቱን ብቻ እየጠየቀ ይገኛል፡፡
ሶስተኛዉ- የአማራ ብሄርተኝነት የትኛዉም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ በጠላትነት ያልፈረጀ መሆኑ ነዉ፡፡ በህወሃት ኦነግ የተመሰረተዉና በሌሎች አማራ-ጠል ብሄርተኞች የተጠናከረዉ አማራ-ጠሉ ስርአት በአማራ ህዝብ ላይ የማይነገር በደል ቢያደርስም የአማራ ብሄርተኝነት በስርዓትና በህዝብ መካከል ያለዉን ልዩነት ከጅምሩ ያጤነ ስለሆነ ምንም አይነት የበቀልተኝነት ዝንባሌ የሌለዉ እንደሚሆን መግባባት የተያዘበት ነገር ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ አማራ-ጠሉ ስርዓት በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰዉን ወንጀል ሁሉ እንዲያደርስ በብአዴን/አማራ ብልፅግና ፓርቲ ዉስጥ የተሰገሰጉ የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኞች ያበረከቱት ሚና ከህወሃትና ኦነግ ፖለቲከኞች የማያንስ ነዉ፡፡ ይህ በመሆኑም የአማራ ብሄርተኝነት የአማራን ህዝብ በጠላትነት ለመፈረጅ እንደማይችል ሁሉ ሌላዉ ኢትዮጵያ ህዝብም በጠላትነት ሊፈርጅ አይሞክርም፡፡
3.2 “የአማራ ብሄርተኝነት ጠመንጃ ያነሳ ስለሆነ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነዉ”
ይህን ሃሳብ ለመሞገት ቀዳሚ ሆኖ መምጣት ያለበት ነገር አማራዉ ለምን ጠመንጃ አነሳ? ጠመንጃ ከማንሳቱ በፊት ለሩብ ምዕተ ዓመት መታገሱ ምንን ያሳያል? የሰዉ ልጅ ህይወቱን ከዘር ማጥፋት ስጋት ለማዳን እራሱን ባገኘዉ መንገድ ሁሉ መከላከል ሌላ ሊያደርገዉ የሚችለዉ ሌላ አማራጭ አለ ወይ?
እራሱን ለመከላከል ጠመንጃ ካነሳዉ የአማራ ብሄርተኝነትና በሰላማዊ ሰዎች ላይ አማራ በመሆናቸዉ ብቻ ዘር ማጥፋን ከሚፈፅመዉ ስርኣት የትኛዉ ነዉ ቀድሞ ዲሞክራሲን የገደለዉ የሚሉ ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት እራሱን ለመከላከል ጠመንጃ ማንሳቱ የማይካድ ሃቅ ነዉ፡፡ እራስ መከላከል ደግሞ ተፈጥሮአዊ መብት ነዉ፡፡ ዋናዉ ጥያቄ መሆን ያለበት ጠመንጃ የተነሳበት ምክንያት ነዉ፡፡ በአንድ ዘወትራዊ ተጠያቂነትና በአንድ ስርዓት የሁልጊዜ አጥቂነት መስተጋብር የሚፈጠር ዲሞክራሲ የለም፡፡ ስለዚህ አማራዉ ያነሳዉ ጠመንጃ ዲሞክራሲን ለመግደል ሳይሆን እራስን ለመከላከል መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡
3.3 “የአማራ ብሄርተኝነት በአዉራጃዊነት የተከፋፈለ ነዉ”
አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ዋነኛ ማንነቱ የፋኖ ትግል ነዉ፡፡ ፋኖነት የሆነዉ የአማራ ህዝብ ትግል የተፋፋመዉ አማራ-ጠሉ ስርዓት በአማራ ህዝብ ላይ ሲያደርስ የኖረዉ በደል እያደር ቅጡን አጥቶ፣ ሊታገሱት የማይቻል ደረጃ ላይ በመድረሱ ከዚህ በኋላ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ የሚያስከትለዉን በመረዳት ነዉ፡፡ አንገት ላይ በደረሰዉ ስርዓታዊ ግፍና በደል በአስቸኳይ መፍትሄ ለማምጣት ቆርጦ የተነሳዉ የፋኖ ታጋይ ትግሉን የጀመረዉ በየአካባቢዉ በመሰባሰብ ነበር፡፡ ይህ የፋኖ ትግል ለህወሃት የትግል ዘይቤ በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል፡፡
በህወሃት ሁኔታ በመጀመሪያ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጅ ልሂቃን ከየዩንቨርሲቲዉ አቋርጠዉ በመዉጣት የትግሉን አስኳል በመመስረት የመሪነቱን ሚናም አብረዉ ወሰዱ፡፡ ቀጥለዉም ለትግሉ ሰራዊት የሚሆኑ ታጋዮችን ከመላዉ ትግራይ መመልመል ጀመሩ፡፡ በመሆኑም ትግሉ በአንድ የእዝ ማዕከል የሚመራ፣ከሞላ ጎደል የእዝ ተዋረዱ የሚታወቅ ነበር፡፡ በአማራ ፋኖ ትግል ሁኔታ ግን ትግሉ እራሱ የተጀመረዉ ስርዓታዊዉ በደል አማራ በተባለዉ ህዝብ ቤት ሁሉ በነፍስ ወከፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመግባቱ ህዝቡ ባልተጠበቀ ሁኔታ በጅምላ የተነሳበት ነዉ፡፡ በመሆኑም እንደ ህወሃት በመጀመሪያ ሰባት ስምንት ሰዎች ጫካ ገብተዉ የሆነዉንም ያልሆነዉንም የሚያወሳ የማታገያ ማኒፌስቶ ፅፈዉ ህዝቡን ጎትተዉ ወደ ትግል ማስገባት አላስፈለገም፡፡
ይህ የሚያሳየዉ የአማራ ፋኖ ትግል ከፕሮፖጋንዳና ከልሂቃን ጉትጎታ የመነጨ ሳይሆን ከህዝብ እዉነተኛ ምሬት የተነሳ በራሱ በህዝቡ ተፈጥሮአዊ የነፃነት ፍላጎት እየተገፉ በስተመጨረሻ የማይቀለበስ ሙላት ላይ የደረሰ ፍትሃዊ ትግል እንደሆነ ነዉ፡፡ በመሆኑም የአማራ ፋኖ ትግል ከመላዉ አማራ ግዛት በተነሱ ታጋዮች የተጀመረና ቀስ በቀስ ወደ መያያዝ የሚመጣ የትግል አይነት ነዉ፡፡
የአማራ ፋኖ ትግል ከማእከላዊ እዝ የሚመራ አለመሆኑ ትግሉ ህዝባዊ እንጂ መንግስት እየለፈፈ እንዳለዉ የልሂቃን ብቻ እረብሻ እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡ ትግሉ ከማእከላዊ እዝ የማይነሳ ይልቅስ ህዝቡ በየአካባቢዉ በመሰባሰብ ለህልዉና ለመታገል የወጣበትና መሪዎቹንም ከዚያዉ ከስብስቡ ቀስ እያለ እየመረጠ መሄዱ በአንዴ ማዕከላዊ አመራር ለማምጣት የማያስችለዉ መሆኑ አዉቆ ላልተኛ ሁሉ ግልፅና ቀላል ሃቅ ነዉ፡፡ ስለዚህ የፋኖ ትግል ከአንድ ማእከላዊ ዕዝ የማይመራ መሆኑ ከትግሉ _ አጀማመር ተፈጥሮ የሚመነጭ እንጂ አማራ የተለየ የአዉራጃዊነት ፍቅር ያለበትና አንድ መሆን የማይችል ህዝብ ስለሆነ አይደለም፡፡ ይህም ማለት የሰዉ ልጅ ከአካባቢዉ ጋር ያለዉ ጥብቅ ትስስር በአማራ ህዝብ ዘንድ የለም ማለት አይደለም፡፡ አካባቢያዊነት ድል አድርጎ ስልጣን ለመያዝ በቻለዉና ከዉጭ ሲያዩት ፍፁም አንድነት የሚያሳይ በሚመስለዉ፣ በትግል አጀማመር ዘይቤዉም በመጀመሪያ ማዕከላዊ እዙን አዘጋጅቶ ትግሉን በጀመረዉ ህወሃት ዉስጥም ይንፀባረቅ የነበረ የሰዉ ልጆች ሁሉ ዝንባሌ ነዉ፡፡ ዋናዉ ነገር አካባቢዊነት ዋናዉን የትግል አላማ ማስረሳት መቻል ያለመቻሉ ጉዳይ ነዉ፡፡ የአማራ ፋኖ ትግል ከዚህ አንፃር ሲገመገም መነሳት ያለበት ምክንያታዊዉ ግምገማ ትግሉ ከተጀመረበት እስከዛሬ ባለዉ በጣም አጭር የሚባል ጊዜ ትግሉን በመሪዎች ስር የማሰባሰቡ አኳያ እየተወሰደ ያለዉ እርምጃ ምን ያህል አበረታች ነዉ የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ ተስፋ ሰጭ እርቀቶችን የሄደ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡
አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከሚመራባቸዉ ጥብቅ መርሆዎች አንዱ የቀደመ ስህተትን መድገምም ሆነ አዲስ ስህተት መሰራት የለበትም የሚለዉ ነዉ፡፡ ከአማራ ብሄርተኝነት የቀደሙ ስህተቶች አንዱ ደግሞ የተሸከሙትን የህዝብ አደራ በጠንካራ ታማኝነትና ዲስፕሊን ዳር የማድረስ ሁለንተናዊ ብስለትና ጥንካሬን የተላበሱ መሪዎችን የማግኘት ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህ አደገኛ ስህተት ለማረም ትግሉ በሁነኛ መሪዎች እጅ እንዲገባ ጊዜ ወስዶ በከፍተኛ ጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነዉ፡፡ ስለዚህ ትግሉ ማዕከላዊ አመራር አለዉ እንዲባል ብቻ ሲሮጡ የመታጠቅ ስራ ከመስራት መቆጠቡ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ ትግሉን ከቀደሙ ክሽፈቶች ለመታደግ ሲባል የሚደረግ የጥንቃቄ ጉዞ ብአዴን ስፖንሰር እያደረገ ሲያራግበዉ ከኖረዉ አላማ ቢስ መንደርተኝነት ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡
አማራ-ጠሉ ስርዓት የአማራ ፋኖ ትግል የተበጣጠሰና መሪ የሌለዉ እንደሆነ እየለፈፈ እራሱን የሚያፅናናበት አካሄድ መሪዎቹን ካወቀ በኋላ ህወሃት በጀግናዉ ጎቤ መልኬ ላይ ያደረገዉን አይነት እና ሌሎች ሸሮች ተጠቅሞ መሪዎቹን በማጥፋት ለመበተን ካለዉ ፍላጎት አንፃርም መታየት አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ትግሉ መሪ እንኳን የሌለዉ ተራ ረብሻ ነዉ ብሎ ለማጣጣል ሲባል የሚደጋገም ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ለማንም ሊሰወር አይገባም፡፡ የሆነዉ ሆኖ የአማራ ፋኖ ትግል ከተጀመረበት ጊዜ ይልቅ ዛሬ በተሻለ የመሰባሰብና የመናበብ ፈለግ እያያዘ ያለ፣በቅርብ ጊዜም የህዝብን ትግል በምስር ወጥ የማይሸጡ ሁነኛ መሪዎችን ይዞ የመምጣት ጥንቃቄ የተሞላበት ስራ ላይ ያለ ተስፋ ሰጭ ትግል ነዉ፡፡
መቋጫ
ለአንድ ህዝብ መብት መከበር ተብሎ የሚደረግ ትግል የሚታገልለትን ህዝብ ፖለቲካዊ ስነልቦና ባገናዘበ መንገድ በተነደፉ የትግል መርሆዎች መመራት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ትግሉ በልሂቃን ስሜት ተደምሮ የእነሱን የግል ጥቅም በማርካት ፍሬ-ቢስ መደምደሚያ ይጠቀማል፡፡ በዘመናዊት ኢትዮጵያ የተነሱት ትግል መሳይ ነገሮች መጨረሻ ከዚህ የራቀ አልነበረም፡፡ እነዚህ ትግሎች የህዝቡን ማህበረ-ፖለቲካዊ ስነ-ልቦና ያገናዘበ የሁኔታ ትንተና ሳይሰሩ ወደ ትግል የገቡ በመሆናቸዉ ብዙ ስህተቶችን ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ስህተቶችን ዋነኛዉ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ላይ ይነገር የነበረዉ አደገኛ ማጣጣል፣ዉርጅብኝ እና በቀኝ ገዥነት እስከመፈረጅ የደረሰ አዕምሮ የጎደለዉ የአዉዳሚነት አካሄድ ነዉ፡፡ ይህን አደገኛ አካሄድ በማራመዱ ረገድ ህወሃትና ኦነግ ዋነኞቹ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሃይሎች በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ላይ የመዘዙት አዉዳሚ ፍላፃ ቀድሞ ያገኘዉ የአማራን ህዝብ ነዉ፡፡ እነዚህ በአማራ በኩል ኢትዮጵያን የሚጥሉ ንዑስ ብሄርተኞች ዋኖቻቸዉን ህወሃትና ኦነግን አስቀደመዉ በአጠቃላይ ግን እራሳቸዉን “የፌደራሊስት ሃይሎች” ብለዉ ይጠራሉ፡፡
እነዚህ ሃይሎች በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሱት በደል ማቆሚያ ማጣቱ ነዉ አዲሱን የአማራ ብሄርተኝነት የፈጠረዉ፡፡ ሆኖም የአማራ ህዝብ አዲሱ የትግል ዘይቤ የእነዚህ ሃይሎች ስህተት መድገምን አልመረጠም፡፡ ይልቅስ ከዚህ አዉዳሚ ጎራ ስህተቶች ትምህርት በመዉሰድ ትግሉን በታሰበበትና በሰከነ መንገድ ማስኬድን መርጧል፡፡ በመሆኑም የሚታገልለት የአማራ ህዝብም ሆነ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በረዥም ዘመን የሃገረ-መንግስት የታሪክ ዘመኑ ያዳበራቸዉ ሃይማኖታዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስነ-ልቦናዎች በማክበር እንጅ ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ ሃገርን በማጣጣል የህዝብን አብሮ የመኖር ፍላጎት በመናቅ የሚደረግ ትግል የትም እንደማያደርስ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በዉል ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም የአማራ ህዝብ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር ያለዉን ጥብቅ ቁርኝት ማስቀጠል የአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት መርህ ነዉ፡፡
ሆኖም ይህ ቁርጠኝነት ከዚህ ቀደም እንደነበረዉ የአማራን ህዝብ ብሄር-ተኮር ጥያቄዎች ለማዳፈን፣በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሱ ግልፅ በደል ለማጥፋት የሚዉል የአማራ-ጠሉ ስዓት ዋሻ እንዲሆን አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አይፈቅድም፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግም እንደ ዋነኛ የትግል ስልት የወሰደዉም የአማራ ብሄርተኝነትን ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ነጥሎ በማዉጣት የአማራን ህዝብ አንገብጋቢ የህልዉና ጥያቄዎችን ጥርት ባለ መንገድ ግልፅ ማድረግና ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት የሚያስችል ጠንከር ያለ የአማራ ብሄርተኝነት ትግል ማድረግ ነዉ፡፡ ይህ ሲደረግ የአማራ ብሄርተኝነትን በተገቢዉ መንገድ ማጠናከር የሚቻልበትን በቂ ትኩረትና ጊዜ መዉሰድ በምንም ሊተካ የማይገባዉ የትግሉ አንጓ መሆኑ ታምኖበት ነዉ፡፡ ይህ አዲስ የትግል ስልት በአማራ ልሂቃን ሲደረግ የተለመደ ስላልሆነ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ሙሉ ትኩረቱን አድርጎ መሰራቱ ኢትዮጵያን በመካድ ሊያስከስስ እና በፅንፈኝነት ሲያስፈርጅ መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ችላ ብሎ በዋናዉ አላማ ላይ ማተኮር ሊያነጋገር የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አማራዉ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ፅናት ያለዉን ታማኝነት የደም ዋጋ እየከፈለ አሳይቷልና ዛሬ ገና እንደ አዲስ ኢትዮጵያን ምን ያህል እንደሚወድ ለማሳየት የተደቀነበትን የህልዉና ስጋት ለመቀልበስ የጀመረዉን ትግል መተዉ የለበትም፡፡ በምትኩ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ፅናትና ቀጣይነት ያለዉን ታማኝነት ማሳየት ያለበት ኢትዮጵያን ሲያበሻቅጥ የኖረዉ አማራ-ጠሉ የፌደራሊስት ሃይል ነኝ የሚለዉ ጎራ ነዉ፡፡ ይህ ጎራ ኢትዮጵያን የዘረኝነቱ መሸፈኛ የማድረግ አደገኛ ዝንባሌ ያለዉ ከመሆኑም በተጨማሪ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚለዉ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ሲዘርፋት ብቻ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር ያለዉ መስታግብር ምን ያህል ጤነኛ እንደሆነ በተግባር ማስመስከር ያለበት ይህ የማይታመን ሃይል እንጅ የአማራ ህዝብ አይደለም፡፡
ይህ ሰነድ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ከፃፍኳቸዉ ሰነዶች አራተኛዉ ነዉ፡፡ ሰነዶቹ የሃሳብ ተያያዥነትና ተከታታይነት ስላላቸዉ አንባብያን በጉዳዩ ላይ የተሻለ መረዳት እንዲኖራቸዉ ይህን ሰነድ ከማንበባቸዉ በፊት ቀዳሚዎቹን ሶስቱን ሰነዶች ቢያነቡ የተሻለ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ሰነድ “የአማራ ህዝብ ትግል ዳራና ቀጣይ አቅጣጫዎች” የተፃፈ ሲሆን፣ ሁለተኛዉ ሰነድ “የአማራ ህዝብ ትግል እንዴት ይመራ?” የሚል ርዕስ ይዟል፡፡ ሶስተኛዉ “የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች” በሚል ርዕስ የተፃፈ ነዉ፡፡
ሰነዶቹን አንባብያን እዚህ ላይ ሊንኩን ይጫኑ