November 24, 2024
26 mins read

ትዉስታዎቼ ፡ ስለ መሬት ይዞታና የተለያዩ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች- ደራሲ፡ አለም አንተ ገብረስላሴ

Tiwustawoche Ethiopia Book Reviewየመፅሃፉ ርእስ፡ ትዉስታዎቼ ፡ ስለ መሬት ይዞታና የተለያዩ ፖለቲካዊና አገራዊ ጉዳዮች
ደራሲ፡ አለም አንተ ገብረስላሴ
አሳታሚ፡ ቀይ ባህር አሳታሚ (Red Sea Press)
የገፅ ብዛት፡ 268

ፕሮፌሰር አለም አንተ በህግ ትምህርት ተመርቆ ሙያዉ ከወጣትነቱ ጀምሮ ኢትዮጵያ እያለ ከመሬት ጋር የተያያዘ፤ አገር ጥሎ ከወጣም ወዲያ የህግ ትምህርት በማስተማር ላይ ያተኮረ ነዉ፡፡ ከሙያዉ ዉጭም የሃገርና የህዝብ ፍቅር ባሳደረበት ግፊት በተለያዩ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች ተሳትፏል፡፡ ራሱ የህግ ትምህርት ወደ ተለያየ የስራ ኣቅጣጫ ሊወስደዉ ቢችልም፤ መክሊቱ ከመሬት ስሪት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በመሬት ይዞታ የሚኒስትር መስሪያ ቤት በህግ ኣማካሪነት፤ ባስተዳደር በመጨረሻም በቋሚ ተጠሪነትና ዝነኛዉን የመሬት ይዞታን የህዝብ ያደረገዉን የ 1967 አም አዋጅ ካረቀቁትና ለባለድርሻዎች ገለፃ ካደረጉት ጥቂቶች ዋነኛዉ ለመሆን በቅቷል፡፡

እንዴት ወደ ህግ ትምህርትና ቆይቶም ወደ መሬት ስሪት ሊያዘነብል ቻለ? ብለን ስንጠይቅ መልሱን በገፅ 22 እናገኛለን፡፡ የግምጃ ቤት ሃላፊ የነበሩት አባቱ የዳኝነት ሂደትን እንዲከታተል አዘዉትረዉ ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ ያደርጉት ነበር፡፡ በኣባቱ ተፅእኖ የህግ ትምህርቱን ቢከታተልም፤ ወደ ዳኝነት ሙያ ያላዘነበለዉ ግን  በህግ ትምህርት የመጨረሻ አመቱ የንብረት ህግ አስተማሪዉ ፕሮፌሰር ሃሪሰን ዳኒንግ ስለ ኢትዮጵያ መሬት ስሪት መሻሻል አስፈላጊነት ጠቋሚ የትምህርት ብልጭታ ስለሰጠዉ መሆኑን ይነግረናል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ብሄራዊ ግዴታዉን ከመጨረሻ የትምህርት አመት በሁዋላ በመሬት ይዞታና ኣስተዳደር መስሪያ ቤት በመሬት ስሪት ጥናት መምሪያ ዉስጥ ተመድቦ ሰርቷል፡፡

በዚህ መፅሃፍ ደራሲዉ በኣራት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡

1-መሬትን የህዝብ ያደረገዉ አዋጅ ከመታወጁ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያና በሃረር ጨርጨር አዉራጃ ስለነበረዉ የመሬት ስሪትና በገበሬዉ ላይ ስለተጣለዉ የተለያየ ግብር-

ደራሲዉ በመጀመሪያ ከአዲስ አበባ ዉጭ ለስራ የሄደዉ ወደ ሃረር ጨርጨር አዉራጃ ነበር፡፡ የሃረር ምደባዉ በብዙ መልኩ የደራሲዉን ልብ ነክቷል፤ የፖለቲካ ዝንባሌዉንም አቅጣጫ ወስኗል፡፡ በዚሁ አዉራጃ የመሬት ፋይሎችን ከመመርመር ባሻገር፤ ከሽማግሌዎችና ከጭሰኞች ጋር ተወያይቷል፡፡ በርጫ በሚባል ስርአት ጭሰኞች መሬቱን ለቀጣይ አመት የማረስ መብት እንዲኖራቸዉ እርስ በርሳቸዉ የሚጫረቱበትና ለዚሁ ጨረታ ለባለርስቱ እንደመሬቱ ተፈላጊነት፤ መጠንና የተጫራቾች ብዛት የሚከፍሉት ክፍያ ነዉ፡፡  በዚሁ አዉራጃ ዳሮ ለቦ ወረዳ በሙሉ 22500 ጋሻ መሬት የራስ ብሩ ወራሾች መሬት መሆኑን ደራሲዉ ሲያዉቅና አብዛኛዉ የአዉራጃዉ ህዝብ በተወለደበት አገር መሬት ኣልባ መሆኑ ወደ ግራ ፖለቲካ እንዲያዘምም አስቻለዉ፡፡

በተጨማሪም በኤርትራ፤ በትግራይ፤ በጎጃም የተለያዩ የርስት ይዘቶችንና በህዝብ ላይ የተጣሉ ግብሮችን ለማወቅ ችሏል፡፡ በኤርትራ በቃለመጠይቅና በዉይይት ከጓደኞቹ ጋር ካገኙት መረጃ በሃማሴን በአዲ ተክለዛን ገበሬዎች የዘር ሃረጋቸዉ ከደምቢያና ከቋራ (ጎንደር) መሆኑን  ለጥናቱ ቡድኑ ገልፀዋል(40)፡፡እንደሚታወቀዉ ብዙ የኤርትራ ነፃነት ደጋፊዎች ከኢትዮጵያዉያን ጋር ምንም ግንኙነት የለንም የሚል የዉሸት ጋጋታ ያሰራጩ ነበር፡፡ ደራሲዉ በዚህ ጉዳይ ያገኘዉ ማስረጃ ይሀ ብቻ አልነበረም፡፡ ጠለምት በትግል በነበረበት ወቅትም አዝማች ያእቆብና ኪሮስ አገር የሚባሉ ሰፈሮች የሚኖሩት ዝርያቸዉ ከኤርትራ እንደሆነ መገንዘቡ ነዉ፡፡ በግብር መልክ ከሚከፍሉት የስንዴ ምርት የተወሰነዉን ከአስመራ ወጣ ብሎ ለሚገኘዉ ለደብረ ቢዘን ገዳም እንደሆነ ኗሪዎቹ ነግረዉታል (136)፡፡

በሰሜኑ ያገራችን ክፍል ያለዉ የመሬት ስሪት  “ርስት” ወይም በትግርኛ “ርስቲ” የሚባለዉ ተወላጅ ሁሉ መሬት የሚያገኝበት ሲሆን፤ ባንዳንድ ቦታዎች የወል የማህበረሰቡ መሬት ይኖራል፡ ለምሳሌ በትግራይ ጅራፍ ጎሰስ በሚባለዉ ስሪት የቀበሌዉ መሬት በሙሉ የጋራ ንብረት ነዉ፡፡

በሌላ በኩል ግን የሰሜኑንና የደቡብን ኢትዮጵያዉያንን በሙሉ ከሞላ ጎደል የሚያመሳስላቸዉ የሚከፍሏቸዉ የግብር አይነቶች ናቸዉ፡፡ ለምሳሌ ደራሲዉ አባቴ እንደነገሩኝ ብሎ እንደሚያካፍለን በበጌምድርና ሰሜን ብቻ እስከ 26 አይነት የግብር አይነቶች ነበሩ፡፡ (ለማስተርስ ትምህርቱ ወደ አሜሪካ በመታጨቱ የበጌምድርን የመሬት ስሪት ማጥናቱን አቋርጦ ነበር የሄደዉ) ፡፡ ከነዚህም ግብሮች መካከል – የሱሪ ማዉለቂያ፤ ወንበር መንሻ፤ የዳስ፤ የምልምል፤ ሁዳድ፤ የጨዉ፤ ለፈረሰኞች የሚከፈል አምሾ፤ በደምቢያ ብቻ የነበረና ቆይቶ የቆመ የአሞራ ግብር፤ ለቤተክርስቲያን የሚከፈል የድመት መሬት (መፅሃፍትናን የቤተ ክህነት ልብሶችን የሚበሉ አይጦችን በሚገድሉ ድመቶች ሰበብ)፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ወደቅ የሚባል ለየክፍለአገሩ በነፍስ ወከፍ የተጣለ (ጎጃም ብቻ በምንዝር ኣባቶች በወል የሚከፈል) ግብር ነበር፡፡

2- መሬትን የህዝብ ስላደረገዉ የየካቲት 1967 አዋጅ

በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ጉዳይ፤ በተለይም የባለርስትና የጪሰኛ ያልተመጣጠነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉልበት ቁልፍ ጥያቄ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ይመስላል ለዉጥ ሊያመጡ ይችላሉ ያሏቸዉን ሚኒስትሮች በየተራ አቶ በለጠ ገብረ ፃድቅንና ቀጥሎም አቶ በላይ አባይን ሹመዉ ነበር (75)፡፡ ነገር ግን የንጉሱ ሴት ልጅ ልእልት ተናኘወርቅና ራስ መስፍን ስለሺ የባለብዙ ጋሻ መሬት ባለቤቶች ስለነበሩና ለንጉሱ ጆሮ ስለሚቀርቡ በንጉሱ ዘመን የተሞከረዉ በዉጭ መንግስታት ግፊትም (ስዊድንና አሜሪካ) ይሁን ባገር ዉስጥ ሃይሎች ጥረቱ የትም ሊሄድ አልቻለም፡፡ ይህንን ከሁሉም በግልፅ የሚያሳየዉ  የመሬት ይዞታ ማሻሻያ ሃሳብ ለፓርላማ ቀርቦ ሊፅድቅ ትንሽ ሲቀረዉ የተከሰተዉ ክስተት ነዉ፡፡ ሚኒስትሩ አቶ በላይ አባይ በብዙ አከራክሮ ለፓርላማ ለድምፅ የደረሰዉን አዋጅ ፍፃሜ ለማየት ምክትላቸዉን ንጉሴ ፍርድ አወቅን፤ ደራሲዉንና ዘገየ ኣስፋዉን አስከትለዉ ወደ ፓርላማ ይሄዳሉ፡፡ ሰብሳቢዉ  ሰይፈ ታደሰ ድምፅ ሊያሰጡ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ከቤተመንግስት ስልክ ይደወልላቸዋል፡፡ አቶ በላይና ሰብሳቢዉ ባስቸኳይ ወደ ቤተመንግስት እንዲመጡ ታዘዉ፤ እዚያዉ ሆነዉ ፓርላማዉ እንዲበተን በሰብሳቢዉ ታዘዘ(74)፡፡ የመጨረሻዉ የማሻሻያ ተስፋ በዚሁ መከነ፡፡ ደራሲዉ ይህ የጪሰኛ  አዋጅ በጊዜ ታዉጆ ቢሆን ኖሮ  ደርግ ያወጣዉ አዋጅ በሌላ መልክ ሊወጣ ይችል ነበር ይለናል(76)፡፡ ነገር ግን ከዚያም በላይ ማሰብ ይቻላል- ምናልባትም የ66ቱን አብዮት የማዘግየትና ለዉጦች በዝግመተ ለዉጥ ብቻ እንዲመጡ ፈር ቀዳጅ ሊሆን ይችል ነበር፡፡

መሬትን የህዝብ ያደረገዉን የ67ቱን አዋጅ ያረቀቁት እነማን እንደሆኑ እስካሁን ለ24 አመታት ሃቅ ሆኖ የቆየዉ አንዳርጋቸዉ አሰግድ በመፅሃፉ በ”አጭር በተቀጨዉ ረጅም ጉዞ፤ መኢሶን በኢትዮጵያ ህዝቦች ዉስጥ (238)” ላይ ኣንዳርጋቸዉ ራሱን ጨምሮ ኣርቃቂዎች ያላቸዉ ሰዎች ነበሩ፡፡ሆኖም ፕሮፌሰር አለም አንተ የስም ዝርዝሩ ስህተት እንዳለበት እንዲያዉም አንዳርጋቸዉ ራሱም እንዳልነበረበት፤ አዋጁ ከወጣ በሁዋላ በብዛት ለኣፈፃፀም ከተቀጠሩት ኣንዱ እንደሆነ ይነግሩናል(86-89)፡፡ የ “ያ ትዉልድ” ደራሲ ክፍሉ ታደሰም ተመሳሳይ ስህተት እንደሰራ ደራሲዉ ይነግሩናል፡፡ በነገራችን ላይ ከአርቃቂዎች ዉስጥ የኢህአፓ አባል የነበረዉ ዳዊት ህሩይ አዋጁ ከመታወጁ በፊት ለኣፈፃፀም እንዲረዳ የገበሬ ማህበራት እንዲቋቋሙ ገፍቶ ነበር፤ ደርግ ግን አልተቀበለዉም፡፡

መሬትን የህዝብ ያደረገዉ የ67ቱ አዋጅ ለዘመናት ችግር ሆኖ የቆየዉን የጭሰኝነት አባዜና የፍርድ ቤት ክምር ፋይል መፍትሄ አገኘለት (ሌሎች ችግሮች ተያያይዘዉ ቢፈጠሩም)፡፡ በተለይ ሌሎች ማሻሻያ ባደረጉ አገሮች የታየዉ የእርሻ ምርት መቀነስ በኢትዮጵያ አልታየም፡፡ ደራሲዉ ለምን ይህ እንዳልሆነ ሲያስረዳ በኢትዮጵያ ሰፋፊ እርሻዎች እንዳሉ በመቀጠላቸዉና ጭሰኞችና  አነስተኛ ይዞታ ያላቸዉ ወዲያዉኑ የመሬት ድልድል ትሩፋት ባለማግኘታቸዉ ነዉ(116)፡፡ ደራሲዉ በተጨማሪ በኣዋጁ ላይ ዛሬ የሚሰነዘርን መሬትን የህዝብ ሳይሆን የመንግስት ያደረገ የሚለዉ ትችትም አግባብ እንዳልሆነ፤ እንዲያዉም ይህ ጥያቄ በማርቀቁ ሂደት ላይ ቀርቦ ከአንድ ሰዉ በስተቀር (ታየ ጉርሙ) ድጋፍ ስላላገኘ ዉድቅ እንደተደረገና መሬትን የህዝብ ያደረገ አዋጅ እንደነበረ ይነግረናል(119)፡፡

አዋጁን ለማስፈፀም  ዘማቾች ከፍተኛ መስዋእትነት እንደከፈሉ ደራሲዉ በትክክል ያነሳል፡፡ ነገር ግን በኣዋጁ ምክንያት ከታዩት ጉድለቶችና ወንጀሎች ኣንዱ በብሄር ማንነታቸዉ ባንዳንድ ፅንፈኞች ኣንዳንዴም ከመሬት ጋር ባልተያያዘ ህይወታቸዉ ያለፉ ሰዎች ጉዳይ ነዉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያዉ የወላይታ ተወላጁና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ተራማጅ የነበረዉ የወላይታ ሶዶ አዉራጃ የመሬት ይዞታ አስተዳዳሪ የነበረዉ የሰለሞን ዋዳ ሚና ነዉ፡፡

ቦዘኔዎችንና አርሶ ኣደሮችን በማደራጀት ከተማ ዉስጥ የአቶ ተክሌ ኣብርሃ ሆቴልን ለማጥቃት ሲሞክሩ በባለቤቱና በቦዘኔዎች መካከል በተደረገዉ የተኩስ ልውውጥ አቶ ተክሌ ሲገደሉ የዘማቾች መሪም የነበረ ተገድሏል፡፡ ቀጥሎም አቶ ጥሩነህ ሙላት የሚባሉ ሰዉ  ሶዶ ከተማ ምግብ ቤት፤ ወፍጮ ቤት፤ የእንጨት መሰንጠቂያ፤ መጠጥ ማከፋፈያ ወዘተ ነበራቸዉ፡፡ ሆቴላቸዉ ጥቃት እየደረሰበት እንደሆነ ሲሰሙ ከነበሩበት ከአዲስ አበባ ሲመጡ፤ መንገድ ላይ እነዚህ ጥምር ሃይሎች እሳቸዉን፤ የሆቴላቸዉን ስራ ኣስኪያጅና ሹፌራቸዉን ገደሏቸዉ፡፡ ደርግ በዚህ በመበሳጨት ሰራዊት ልኮ የገበሬ ማህበሮችን ሁሉ አፈራረሱ፡፡ ሰለሞን ዋዳም ካካባቢዉ ተሰወረ፡፡

ሰለሞን አዋጁን ሽፋን አድርጎ የዘር ቅስቀሳ ሲያደርግ እንደነበር የወላይታ የዘማቾች መሪ ሻምበል ለሚኒስትሩ ለዘገየ ኣስፋዉ ደራሲዉ በተገኘበት ስሞታ አቅርቦ ነበር፡፡ በሰለሞን ላይ ግን ምንም አይነት ርምጃ ሳይወሰድ፤ ማስጠንቀቂያ እንኳን ሳይሰጠዉ ታለፈ፡፡ ከወላይታ ከተሰወረ በሁዋላ ሰለሞን፤ ሃይሌ ፊዳ ቤት ዉስጥ ተደብቆ እንደነበር ደራሲዉ ሚኒስትሩ እንደነገረዉ ያስታዉሳል፡፡ አክሎም  ዘገየ ለደራሲዉ እንደነገረዉ መንግስቱ ሃይለማርያም ራሱ ሰለሞን እንዲያመልጥ አድርጉ ብሎ እንደተናገረ ያወሳል፡፡ ሰለሞን ግን በጎንደር መተማ በኩል ሊያመልጥ ሲል ተይዞ ተገድሏል(109)፡፡ በዘር ቅስቀሳ  ተሳትፎ ጉዳቶች ያደረሰን ወንጀለኛ ከህግ ለመከለል ከርእሰ ብሄሩ ጀምሮ የተደረገዉ ጥረት አግራሞትን ያጭራል፡፡ ዛሬ ብዙ የኣማራ ብሄርተⶉች ኣማራዉ ለጥቃት ኢላማ የተዳረገዉ ላለፉት 50 ኣመታት ነዉ ሲሉ እንደነዚህ አይነት ማስረጃዎችን በማጣቀስ ሊሆን ይችላል፡፡

የተማሪዉ እንቅስቃሴ “መሬት ላራሹ” ብሎ የታገለለትን የፖለቲካ ጥያቄ፤ ደራሲዉ በሙያዊ ጥናትና ከህግ አንፃር ትክክለኛ መፈክር መሆኑን ማጠየቂያ ይሰጠዋል፡፡

3- በተለያዩ ድርጅቶች ደራሲዉ ስላደረጋቸዉ ትግሎች በጥቂቱ

ደራሲዉ በተለያዩ ድርጅቶች አንገብጋቢ ያገሩ ጉዳይን መፍትሄ ለማግኘት ከአገር ቤት ጀምሮ በስደት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ታግሏል፡፡በኢህአፓ፤ በአገር ወዳድ፤ በኢዲሃቅ፤ በህብረ ህዝብ፤ በጎንደር ህብረት ወዘተ

ኢህኣፓን እንዲለቅ ካስገደዱት ምክንያቶች ዋናዉ በጓዶች መካከል፤ በተለይም በመሪዎችና በአባሎች መካከል ሊኖር የሚገባዉ መተማመን ተጥሶ በማየቱ ነዉ፡፡  ሱዳን የአገር ወዳድ ድርጅትን የማስተዋወቅ ስራ እየሰራ እያለ የኢህአፓ ኣመራር አባሉ እዝያ መኖሩን የወደደዉ ኣይመስልም፡፡ ለሱ በቀጥታ ከመንገር ይልቅ በሱ በራሱ እጅ ደብዳቤ ኣስይዞ የሱዳን ከተማ ገዳሪፍ ወደ ነበሩት ሌሎች አመራሮች ይልከዋል፡፡ ደብዳቤዉን ያነበበዉ ሮባ በብስጭት  የደብዳቤዉን ይዘት ሲነግረዉ ደራሲዉ የተሰማዉን የሃዘን ስሜትና ዉሳኔ ይነግረናል (170-171)፡፡ መሬት ይዞታን ከመልቀቁ በፊት ደራሲዉ በኢህአፓነት ይጠረጠር ነበር፡፡  በኢህአፓነቱም፤ እድሜ ልኩን የታገለለትን የመሬት ስሪት ማሻሻል እንደሚቃወም  እንደ ተስፋየ መኮነን አይነት ወዶ ገቦች በስብሰባ፤ መኢሶኖች ደግሞ ሽሙጥ በምትባል ጋዜጣ ይጎነትሉት ነበር(112)፡፡

በተረፈ የአገር ወዳድ ድርጅት ዉስጥ በፀሃፊነት የተጫወተዉን ሚናና ስለ ድርጅቱ ያለዉን ኣንባብያን ስናነብ ይሀ ሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ታደለ ገዛሀኝ (ዘዉዴ በላይ) በፃፈዉ “ማእበል ጋላቢ” በሚለዉ መፅሃፍ የተገለፀ ነበር፡፡ጎንደር ህብረትም ዉስጥ የታገለዉ፤  ወያኔ በጎንደር ማህበረሰብ ላይ ያደረሳቸዉን ጉዳቶች – እንደ ወልቃይት አይነት ጥቃቶች፤ የኢኮኖሚ ድቀቶች፤ የሱዳን ድንበሩን መግፋት የመሳሰሉትን ለመመከት እንደሆነ ያስረዳናል፡፡

4- ስለ ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ኣከላለል ታሪክ

ደራሲዉ ካበረከተልን ሌላዉ በእንግሊዝ አገር ቤተ መፅሃፍት የሚገኙ የድንበር ማካለል መዛግብት መርምሮ ያቀረበልን ዉጤት ነዉ፡፡ በሱዳንና በኢትዮጵያ ያለዉን ድንበር የማካለል ሃላፊነት በእንግሊዝ መንግስት የተሰጠዉ ሻለቃ ግውይን  በ1902 ዉል መሰረት በጋራ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ክለላዉን ማከናወን ሲገባቸዉ ብቻዉን ያደረገዉን ስራ ዛሬ ሱዳን ተቀባይነት እንዲያገኝ ትከራከራለች፡፡ሻለቃዉ ኢትዮጵያንም ጭምር ወክሎ ነዉ ድንበሩን ያካለለዉ የሚል ኣስገራሚ ክርክርም ይደመጣል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ንጉሱና ፓርላማዉ ያላፀደቀዉ ስምምነት ኣይረጋም የሚል ህግ ቢኖርም ባንድ ወቅት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ምናሴ ሃይሌ  በ1972 እስካሁን የኢትዮጵያ መንግስት ይዞት የቆየዉን አቋም የቀየረ በሚመስል መልክ ለሱዳኑ አቻቸዉ ማስታወሻ ላኩ፡፡ በመሰረተ ሃሳቡ የኢትዮጵያ መንግስት ግዊይን ያካለለዉን ድንበር የሚቀበል መሆኑን የሚገልፅ ነበር፡፡ የሱዳን መንግስትም ሃሳቡን እንደሚቀበል ገለፀ(259)፡፡

ደራሲዉ የኢትዮጵያ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ሌሎችም የሰበሰቧቸዉን ሰነዶች የመመርመር እድል ስላልገጠመዉ ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ኣቋም፤ በተለይ የዶክተር ምናሴን ማስታወሻ ይበልጥ ለማጥናት አልቻለም፡፡ እንደ መለስ ዜናዊና ኣብይ አህመድ አይነት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ለማስከበር ግድ የሌላቸዉ መሪዎችን ያየች አገርና (መለስ ባንድ ወቅት ለፓርላማዉ ያደረገዉን አፍቅሮተ ሱዳን ንግግር ደራሲዉ ይጠቅሰዋል)(228) ዛሬም ኣል ፋሻግ የሚባለዉ ግዛቷ በሱዳን ተይዞ ያለች አገር የድንበር ዉሎችን ከስር መሰረታቸዉ ፕሮፌሰር አለም ኣንተ እንዳደረገዉ ከአለም አቀፍ ህግ አንፃር እያወዳደረ ሁኔታዉን የሚገልፁልን ምሁራን እንደሚያስፈልጉን አመላካች ነዉ፡፡

ምናልባት መፅሃፉ እንደገና ሲታተም ሊታሰቡ ከሚገባቸዉ ጉዳዮች አንዱ ገፅ 186/7 ያሉት ፎቶዎች ምን እንደሆኑ ላንባቢ ግምት ከመተዉ ገለፃ ቢደረግባቸዉ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም አንዳንድ በጣም አስፈላጊ ኩነቶችን ቀንና አመተ ምህረት  እስከታወቁ ድረስ ቢጠቀሱ፤ ለምሳሌ የፓርላማዉ ሰብሳቢ አቶ ሰይፈ ታደሰ ከቤተመንግስት ታዝዘዉ ስለ ጭሰኛ ማሻሻያ  የቀረበዉ ህግ ላይ ድምፅ ሊሰጥ የነበረዉን ፓርላማ  የበተኑበት አይነት መጥቀሱ ጠቃሚ ነዉ፡፡

በማጠቃለያ የደራሲዉ “ትዉስታዎቼ”ና የአቶ ሃይለ ልዑል “የመሬት ይዞታ ለዉጥ በኢትዮጵያ-ከቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ እስከ መንግስቱ ሃይለማርያም” አይነት መፃህፍት ተፈላጊ ናቸዉ፡፡  በኢትዮጵያ እስካሁን አወዛጋቢና በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሙሰኝነትን የሚያስፋፉበትን የመሬት ስሪትን በከተማም ሆነ በገጠር ስርአት ባለዉ ዴሞክራሲያዊ ኣሰራር መስመር ማስያዝ ለነገ የማይባል ትልቅ ስራ እንደሆነ አመላካች ናቸዉ፡፡

*መፅሃፉን ለመግዛት የሚፈልጉ ይሀን ማስፈንጠሪያ መጠቀም ይችላሉ፡ Africaworldpressbooks.com/mrec-pb

ሰሎሞን ገብረ ስላሴ

ህዳር 2017 ኣ. ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop