በእንግሊዞች የተመራው የመቅደላው ዝርፊያ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ!!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

እንደ መንደርደሪያ

«በጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ በመቅደላ በንጉሡ በዐፄ ቴዎድሮስ ታስረው ከነበሩት እንግሊዛውያን እስረኞች መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው ከነበሩት ከአቡነ ሰላማ [በወቅቱ የኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ  የነበሩ ግብጻዊ ሊቀ ጳጳስ] መቃብር ዘንድ በመሄድ መቃብራቸውን ቆፍሮ፣ አስክሬናቸውን ጎትተው በማውጣት ብዙ ዶላር ሊያወጣ የሚችል ከአልማዝ የተሰራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበረ የሚያሳይ ነው፡፡

                            [ሄነሪ ስታሊን የአሜሪካው የኒዮርክ ታይምስ ሪፖርተር ... 1868.] 

the ethiopian ambassador visiting the looted manuscripts in britsh mueum (1)

ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ እ... 1868 በእንግሊዝ መንግሥት ከመቅደላ የተዘረፉ የተለያዩ ቅርሶችንና ታቦታትን ጨምሮ እንዲመልሱ የጻፉት ደብዳቤ በብሪቲሽ ሙዚየም ቦርድ በኩል በቀና መንገድ መታየቱን የሚገልጹ ዜና ሰምተናል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማርክ ብራውን የተባለ የእንግሊዙ ‹ዘጋርዲያን› ጋዜጣ ወኪል/Correspondent ‹‹UK urged to return sacred treasures hidden away for 150 years to Ethiopia›› በሚል አርእስት ባስነበበው ጽሑፉ፤ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያንና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት የሆኑ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው መመለስ እንደሚገባቸው አስነብቧ

crown lotted in the battle of meqedela

፡፡

እነዚህን ወቅታዊ መረጃዎች መሠረት በማድረግ በመቅደላ ወረራ ወቅት በእንግሊዞች ስለተዘረፉ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያንና የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆኑት ቅርሶቻችን ጥቂት የመወያያ ሐሳቦችን ለማንሳት ወደድኩ፡፡

የመቅደላን ዝርፊያ በጨርፍታ

ሙሐዘ ጥበባት፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፤ ‹‹ራእይ ዮሐንስ የዓለም መጨረሻ›› በሚል ከጥቂት ዓመታት በፊት ባስነበበው መጽሐፉ ገጽ 18 ላይ፣ ከመቅደላ ዝርፊያ ጋር በተያያዘ የሚከተለውን መረጃ አጋርቶን ነበር፡፡

እቴጌ ምንትዋብ ራእይ መጽሐፍን አስጽፈው ለጎንደር ደረስጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለእራሳቸውና ለልጃቸው ለኢያሱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ መስጠታቸውንና ይህም መጽሐፍ በመቅደላው ወረራ ጊዜ እንግሊዞች ዘርፈው ወስደው አሁንም ድረስ በብሪትሽ ቤተ መጻሕፍት በMS Or. 533 ተመዝግቦ ይገኛል፡፡

queen tirunesh necklace

የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብትና ኩራት የሆኑ ቅርሶቻችንና የቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ የብራና መጻሕፍቶችና ንዋያተ ቅድሳት ወደ አውሮፓ እንዲሻገሩ ምክንያት ከሆኑት መካከል የመቅደላው ጦርነት አንዱ እንደ ነበር የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎችና ሰነዶች አሉ፡፡ «የቴዎድሮስ አሟሟትና የመቅደላው ዘረፋ»  በሚል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባሳተመው የጥናት መጽሐፍ፣ ግርማ ኪዳኔ የተባሉ ምሁር ባቀረቡት ጥናታዊ ጹሑፋቸው ላይ በወቅቱ የጦርነቱን ሁኔታና የእንግሊዞቹን ዝርፊያ በማስታወሻው ላይ ያሰፈረው ‹‹የኒው ዮርክ ታይምስ›› ሪፖርተር የሆነው ሄነሪ ስታሊንን ጠቅሰው የወቅቱን ዝርፊያና ውድመት እንዲህ ገልጸውታል፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹የተመኘሁትንና የፈለኩትን ነው የሆንኩት›› ድምጻዊ አቤል ሙሉጌታ

ዐፄ ቴዎድሮስ እራሳቸውን ባጠፉበት ወቅት የተኩስ ድምጽ በሰሙበት አካባቢ ሁለት የአይሪሽ ዜግነት ያላቸው ወታደሮች የተኩስ ድምጽ ወደሰሙበት አቅጣጫ እየተሯሯጡ በመምጣት በሕይወትና በሞት መካከል ከነበሩት ከዐፄ ቴዎድሮስ ላይ ሽጉጣቸውን፣ የጣታቸውን የወርቅ ቀለበትና የአንገታቸውን መስቀል መውሰዳቸውንና እነዚህ ወታደሮችም እኚህ በጀርባቸው የተንጋለሉት ሰው ዐፄ ቴዎድሮስ መሆናቸውን በጭራሽ እንዳላወቁ በመግለጽ እነዚህ ወታደሮች በአጠገባቸው የተጋደሙት ሰው ዐፄ ቴዎድሮስ መሆናቸውን ያወቁት ሽጉጣቸውን እያገላበጡ በማድነቅ ሲመለከቱ በጎን በኩል ከብር ተቀርጾ የተለበደውን ጹሑፍ ካነበቡ በኋላ ነበር፡፡ ጹሑፉም እንዲህ የሚል ነበር፡ 

‹‹... 1854 ለአሽከሬ ለፕላውደን የአቢሲኒያው ንጉሥ ቴዎድሮስ ላደረጉለት ቅንነት የተሞላበት ደግነት ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ ከታላቋ ብሪታንያና አየርላንድ ንግሥት ቪክቶሪያ የተላከ ስጦታ፡፡››

artifacts returned (2)

የዐፄ ቴዎድሮስ መሞት ከተሰማ በኋላ የእንግሊዝ ወታደሮች በቀጥታ የተሰማሩት ወደ ዝርፊያ ነበር፡፡ ‹‹ይህ ደግሞ በወቅቱ በጣም የተለመደ ነበር ይላሉ›› ሪታ ፓንክረስት በአንድ ጥናታዊ ጽሑፋቸው፤ «The Capture of Maqdala was followed by an evening of looting in the best tradition of the British army at that time» እኚሁ እንግሊዛዊ ምሁር ‹‹The Maqdala Library of Tewodros ›› በሚል ባቀረቡት አንድ ጥናታዊ ጹሑፋቸው ላይ እንደገለጹትም፤

‹‹350 በላይ የሚሆኑ የብራና መጻሕፍቶች የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክና ክርስትና ሃይማኖቷን በሳይንሳዊ መንገድ ለማጥናት በሚል ወደ አውሮፓ መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህም መጻሕፍት ውስጥ እጅግ የተዋቡና በልዩ ሁናቴ የተጠረዙ የብራና መጻሕፍቶችን ለንግሥት ቪክቶሪያ በስጦታ መልክ ተሰጥቷቸው ዊንድሶር ካስል በተባለ በንግሥቲቱ ልዩ ቤተ መጻሕፍት በክብር እንደተቀመጠና እነዚህ ብርቅ ስብስቦች ለማየት ልዩ የሆነ የንግሥቷ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ ሪታ ፓንክረስት ጽፈዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዓለም ማንኛውም ታሪክ ፤ የግለሰቦች ሚና ትልቅ ሥፍራ አለው - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

prince alemayehu (1)

ይህን የመቅደላውን የእንግሊዞቹን ዝርፊያ አቶ ግርማ ኪዳኔ ከላይ በጠቀስነው ጥናታዊ ጹሑፋቸው ከእንግሊዝ ወታደሮች ከመቅደላ በጨረታ የገዛውን በርካታ ቅርሶች በመጫን ወደ አውሮፓ ስላሻገረው የኒዮርክ ታይምሱ ሪፖርተር ሄነሪ ስታሊን ሲያብራሩም፡

ስታሊን ከእንግሊዝ ወታደሮችና ሹማምንት በጨረታ የገዛውን በርካታ ቅርሶች በአምስት አጋሰስ ጭኖ ከመቅደላ ወደ ሰንዓፌ ከዚያም ወደ ዙላ ከምትባለው የቀይ ባሕራችን ጠረፍ ደረሰ፡፡ ከዚያም አምስት በቅሎዎች ላይ ጭነው ያመጣቸውን ቅርሶች በሣጥን አስገብቶ ካሸጋቸው በኋላ በቅሎቹን ሽጦአቸው በማግስቱ «ትራንስፖርት እስቲመር ኢንጂን» ተብላ በምትጠራው አነስተኛ መርከብ እርሱና የዐፄ ቴዎድሮስን አራት ዘውዶች ለንግሥት ቪክቶሪያ እንዲያደርስ ከተወከለው ከኮሎኔል ሚልወርድ ጋር በመሆን በስዊዝ ካናል በኩል አድርገው ቅርሶቻችን ከሀገር እንዲወጡ አደረገ፡፡

lotted cross of ethiopian church
lotted cross of ethiopian church

በተጨማሪም የእንግሊዝ ጦር አዝማች የነበረው ጄኔራል ናፒየር በርካታ ቅርሶችን በመዝረፍና በጨረታ በመሸጥ፣ እንዲሁም እጅግ ውድ የሆኑትን ቅርሶችን የግሉ ንብረት በማድረግና በመጨረሻም መቅደላንና አፄ ቴዎድሮስ የተቀበሩበትን የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ሳይቀር በእሳት በማጋየት የጦርነቱን ፍጻሜ እንዳበሰረ ጽፈዋል፡፡

የዐፄ ቴዎድሮስ እስረኛና ምርኮኞች ከነበሩት እንግሊዛውያን ሚሲዮናውያን መካከል አንዱ ስለፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊትና ዝርፊያ የኒው ዮርክ ታይምስ ሪፖርተር የሆነው ስታሊን በወቅቱ የታዘበውን ሲገልጽ፡ 

church in meqedela

‹‹…በጣም ከሚያስገርመውና ከሚያሳዝነው ነገር ሁሉ ከእስረኞቹ መካከል አንዱ ከስድስት ወር በፊት ተቀብረው ከነበሩት ከአቡነ ሰላማ መቃብር ድረስ በመሄድ አስክሬናቸውን ከመቃብሩ በማውጣት ከአልማዝ የተሰራ መስቀላቸውን ከአንገታቸው ላይ መንጭቆ መውሰዱ የቱን ያህል የተረገመ ሰይጣን እንደነበረ ነው…›› ሲል በሐዘኔታ የታዘበውን በመጽሐፉ አስፍሮታል፡፡

አቶ ግርማ ኪዳኔም በጥናት ወረቀታቸው እንደገለጹት የአቡነ ሰላማን ከወርቅ የተሰራ አክሊልና የቁርባን ጽዋ ከአንድ ጦር ሜዳ ከዋለ ወታደር የብሪትሽ ሙዚየም ተወካይ የሆነው ሆልምስ በአራት እንግሊዝ ፓውንድ ብቻ ገዝቶት እንደነበርና በኋላም እነዚህን ቅርሶች ሪቻርድ ሆልምስ ከኮሎኔል ፍሬዘር፣ ከኮሎኔል ሚልወርድና ከኮሎኔል ካሜሩን ጋር በመመሳጠር «ዘ አቢሲኒያን ፈንድ ኮሚቴ» በሚል ስም ለብሪትሽ ሙዚየም በሁለት የእንግሊዝ ፓውንድ እንዲሸጥላቸው ... ጁላይ 1/1868 አቅርበውት እንደነበር የተጻጻፏቸውን ደብዳቤዎች በዋቢነት በመጥቀስ ጽፈዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሻምቡ ጀግና የኦሮሞ ልጆች ፋሽስት ወያኔን በቃሪያ ጥፊ አጩለውታል!

censer from meqedela

እንደ ማጠቃለያ

በመቅደላ ወረራ ወቅትና በተለያዩ ጊዜያት ወደ አውሮፓና የተለያዩ ዓለማት የወጡ ታሪካዊና ብርቅዬ ቅርሶቻችንን በማስመለስ ረገድ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፣ እየተደረጉም ነው፡፡ በአንድ ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ እነዚህን በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የተወሰዱትን ቅርሶች ለማስመለስ የተቋቋመ AFROMET የተባለ ማኅበር ነበር፡፡ ይህ ማኅበር በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት በመቅደላ ጦርነት ተዘርፈው ከሄዱት ታሪካዊ ቅርሶቻችን መካከልም፤

የዐፄ ቴዎድሮስን የጸሎት ዳዊት፣ የአንገታቸው ክታብና ጎራዲያቸውንና ሌሎችንም ወድና ብርቅዬ የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶቻችንን በማስመለስ በአዲስ አበባ ዪኒቨርሰቲ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ቤተመዘክር ለሕዝብ እይታ ቀርበው እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡

በወቅቱም AFROMET ተባለውን ማኅበር በላይነት ይመሩ የነበሩት፣ ፕ/ር አንድሪያስ እሸቴ፣ ነፍሰ ኄር ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስትና ባለቤታቸው ሪታ ፓንክረሰት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ወዳጆች ማኅበር አባላት፣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ምሁራንና በቅርስ ዙሪያ ከሚሰሩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ እንደ ዩኔስኮ ካሉ ድርጅቶች ጋር እያደረጉት ባለው ጥረት ትልቅ ሥራን ሠርተዋል፡፡

በአሁን ወቅትም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር መስሪያ ቤት፣ በታሪክ፣ በባህልና በቅርስ ዙሪያ በሚሠሩ ኢትዮጵያውያንና የውጪ ሀገር ምሁራንና ተቆርkሪዎች አማካኝነት እየተደረገ ያለው ጥረት ለፍሬ እንደሚበቃ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ሂደትም ወደፊትም በእንግሊዝና በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ በርካታ ቅርሶቻችን እንዲመለሱልን ሁላችንም ኢትዮጵያውያንእነዚህ ቅርሶች የጋራ ሀብቶቻችንና ኩራታችን ናቸውና ድምፃችንን በአንድነት ልናሰማ ይገባናል እላለሁ፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

https://amharic.zehabesha.com/looted-maqdala-treasures-returned-to-ethiopia-after-150-years/

https://amharic.zehabesha.com/the-tragic-prince-of-abyssinya-in-malta/

https://amharic.zehabesha.com/the-last-day-of-emperor-tewodros-iis-life-and-the-loot-of-magdala/

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share