March 31, 2021
29 mins read

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የተንሸዋረረ እይታ – መላኩ ከኢትዮጵይያ

ግጭትና ጦርነት

ግጭቶች በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ይፈጠራሉ። ግጭቶች በአግባቡ ካልተፈቱ ወደ ጦርነት ያመራሉ። ጦርነት የመጨረሻውና ከፍተኛው የግጭት ደረጃ ሲሆን የጦር መሳሪያ ተይዞ በመገዳደል የሚከናወን ፍልሚያ ነው። ጦርነት በአጠቃላይ መደበኛ ወይም መደበኛ ያልሆኑ ወታደራዊ ሃይሎችን በመጠቀም ጽንፍ የለቀቀ አመጽን /extreme violence/፣ ባላጋራን መጉዳትን /aggression/፣ ጥላቻንና ደመኝነትን /hostility/፣ ማጥፋትንና ማፍረስን /destruction/፣ ሞትንና እልቂትን፣ መቁሰልንና የአካል ጉዳትን፣ መሰደድንና መፈናቀልን፣ ርሃብንና ጉስቁልናን የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚያስከትል ‘’አላስፈላጊ’’ና የማይወደድ፤ ነገር ግን በዕውኑ ዓለም አብሮን የሚኖር ሰይጣናዊ ክንዋኔ ነው። ጦርነት አይጀመር እንጂ ከተጀመረ አፈጻጽሙን መቆጣጠር በአብዛኛው አስቸጋሪ ነው።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ያልታጠቁና በጦርነቱ የማይሳተፉ ሰዎችን መግደል ክልክል ቢሆንም የጦርነቱ ባህሪ ይወስነዋል። ጦርነቱ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ከሆነ የሲቪሎች ጉዳት የማይቀር ነው። በተለይም ‘’ሲቪሎች’’ ወገንተኛ በሆኑበትና ለሚደግፉት ወገን መረጃ በመስጠት ወይም በውጊያው ወቅት ስንቅና ትጥቅ የሚያቀብሉ ከሆነ፣ ሌላው ወገን ጠላቱን ለማሸነፍ በሚያደርገው ፍልሚያ በነዚህ ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ይከብዳል።

ሌላው ደግሞ ጦርነቱ የሽምቅ ዉጊያ መልክ የያዘ ከሆነ ተዋጊዎች ጠላት ሲመጣባቸው መሳሪያቸውን አስቀምጠው ከህዝቡ ጋር ይቀላቀሉና ሁኔታው ሲያመቻቸው ዞር ብለው በመተኮስ ጉዳት ያደርሱና እንደገና ከህዝቡ ጋር ይቀላቀላሉ። በዚህ ወቅት ህዝቡን ከተዋጊው መለየት የተቸገረውና ጥቃት የደረሰበት ወገን ስሜታዊ ሆኖ ጅምላ እርምጃ ቢወስድ ትክክል ነው ባይባልም ድርጊቱ ከሰው ባህሪ ያፈነገጠ ተግባር ነው ሊባል ግን አይችልም። ሕዝቡም ተዋጊዎችን በማጋለጥ ፋንታ በወገንተኝነት በውስጡ ደብቆ ይዞ ጥቃት የሚፈጽምና የሚያስፈጽም ከሆነ፣ በዚህም ምክንያት ሌላው ወገን የትግል ጓዱ ከጎኑ እየወደቀ፣ የሚዋጋለት ዓላማ እየተሸነፈ፣ ጠላቱ የት እንዳለ አውቆ ግን ማን እንደሆነ ለመለየት ከተቸገረ ሁሉንም እንደተዋጊ በመቁጠርና ስሜታዊ ሆኖ ጦርነቱን “ያልተገደበ ውጊያ ” /Unrestricted total war/ ባህሪ ሰጥቶ ጅምላ ግድያ ቢያደርግ ትክክል ነው ባይባልም ስህተት ነው ለማለት ደግሞ በተጠቂው ቦታ ሆኖ መፍረድን የሚጠይቅ ይሆናል። ጦርነት ጥላቻ በሰዎች ላይ ሞልቶ በፈሰሰበት ሁኔታ የሚካሄድ በመሆኑ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት፣ በሰው ህይወት መጥፋት ከማዘን ይልቅ ድል አብሳሪነት፣ ከሰባዊነት ይበልጥ አሸናፊነት የበለጠ ዋጋ የሚሰጥበት በሆነበት ሁኔታ ለሕግ የመገዛት አቅም የተዳከመ መሆኑ ግልጽ ነው። ዓለም አቀፍ የጦር ሕግ ቢኖርም እልህ የተቀላቀለበት የሞት ሽረት ፍልሚያ በሰፈነበት ሁኔታ ስለ ሕግ ማሰብ አለበት ማለት የሰውአዊነት ባህሪን መካድ ነው።

 

የጦርነት ወንጀልና ሰብአዊ መብት ጥሰት ትስስር

የጦርነት ወንጀል ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ያስከትላል። ሁሉም የጦር ወንጀሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከሰብአዊ መብት ጋር የተያያዙ ናቸው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ይህን የሁለቱን ትስስር የሚመለከቱት አይመስለኝም። ትኩረታቸው በግጭት ወይም በጦርነት ውጤት ላይ ብቻ ነው። የጦርነትን ወንጀል /war crime/ እና ከዚያም ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የመብት ጥሰት ለመርመር ከመነሻውና ክምክንያቱ /cause of war or cause of human rights violation/ ለመነሳት አይፈልጉም። የሰብአዊ መብት ጥሰትን ከጦርነቱ ውጤት /effect of war/ አንጻር ብቻ ያዩታል። ለምሳሌ ግድያን ብቻ እንጂ ለምንና በምን ሁኔታ ግድያው ተፈጸመ የሚለውን መንካት አይፈልጉም፤ መፈናቀልን እንጂ ማን አፈናቀለ ለምን ተፈናቀሉ የሚለውን ይሽሹታል።

የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የሚወጡ ሪፖርቶች ወገንተኝነት የሰፈነባቸው ሆነው ታይተዋል። አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ፣ አንዱን ሞቅ ደመቅ ሌላውን ቀዝቀዝ ለዘብ ያደርጉታል። የጦርነት ወንጀሎች ተብለው ከተጠቀሱት ሶስት ነገሮች አንዱ “Crime against peace, which involved preparation and initiation of a war of aggression”1 ማለትም ለጦርነት ዝግጅት ማድረግን እና ጦርነት ማነሳሳትን የሚያካትት ስራ መስራት በሰላም ላይ የሚደረግ የጦር ወንጀል እንደሆነ ይገለጻል። በሰላም ላይ የሚደረግ የጦር ወንጀል ከሞላ ጎደል በሁሉም (በሰላሳዎቹም) የሰብአዊ መብቶች ላይ ችግር ይሚያስነሱ ናቸው።

በዚህ ረገድ ሕወሃት ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊት በከፍተኛ ደረጃ የጦርነት ዝግጅትና ቅስቀሳ ያደርግ እንደነበረ የኢትይጵያን ሁኔታ ሲከታተሉ የነበሩ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ጭምር የሚያውቁት ጉዳይ እንደሆነ እገምታለሁ። ከሁለት መቶ ሺ በላይ ሚሊሺያና ልዩ ሃይል ሲመለምሉና ሲያሰለጥኑ፤ “ትግራይ የኢትዮጵያ ወታደር መቃብር ትሆናለች” እያሉ ሲፎክሩ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ተጋሩ ወደ ትግራይ እንዲገቡ የክተት ጥሪ ሲያደርጉ፤ አክቲቪስቶቻቸው “ጦርነት ለትግራይ ሕዝብ ባህላዊ ጨዋታ ነው” ሲሉና ማአከላዊ መንግስት እየተጠናከረ ሳይሄድ ጦርነቱ ጊዜ ሳይሰጠው መጀመር እንዳለበት በሶሺያል ሚዲያው ሲቆሰቁሱ፤ በአጠቃላይ ከፍተኛ የጥላቻና የትንኮሳ ፕሮፓጋንዳ ሲያጮሁ ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነበር። ይህም የጦርነት ወንጀሎች ተብለው ከተጠቀሱት ሶስት የጦርነት ወንጀሎች ውስጥ ከላይ የተጠቀሰው የጦርነት ዝግጅት አንድም ቀን ወንጀለኝነቱ ሲነሳ አልሰማሁም። ጉዳዩን የተከታተለው የአለም አቀፉ የቀውስ ቡድን (International Crisis Group) ግን በትግራይ ውስጥ ያለውን የጦርነት ዝግጅት ከገመገመ በኋላ ግጭቱ ወደ ጦርነት እንደሚያመራ ተናግሮ ነበር።

ሌላው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አልፎ አልፎ የሚያነሳውና መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርገው በመተከል፣ በኦሮሚያና በደቡብ የሚካሄዱ ዘርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ነው። እነዚህ ግጭቶች የሽምቅ ውጊያ ባህሪ ያላቸው በመሆናቸው ለመከላከል አስቸጋሪ ናቸው። የሽምቅ ውጊያ በሚካሄድበት ማንኛውም አገር መንግስት ወንጀለኞችን ይዞ ለሕግ ለማቅረብ ወይም ሕዝቡን ከጥቃት ለመከላከል ያለው ችሎታ ውስን ነው። የመንግስት ወታደር በየመንደሩ ተሰማርቶ ጸጥታ ማስከበር በተለይ እንደኢትዮጵያ ባለ ሰፊ ሀገር አስቸጋሪ ነው። የችግሩን መነሻ ወደጎን በመተው የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን መንግስት ማውገዝ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተቀዳሚ ተግባር ሆኖ ቆይቷል። ተዋጊዎችን በማሰልጠን፣ በቁሳቁስና በገንዘብ በመርዳት ግጭቱን የሚያቀጣጥለው ሕወህት መሆኑን መንግስት በተለያየ ጊዜ ቢገልጽም፣ በዚህ መነሻነት ለሚደርሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት ጥናት አድርጎ የችግሩን መነሻ ለማወቅ ሞክሮ አያውቅም። በአንጻሩ በነዚህ የመብት ጥሰት በሚፈጽሙ ሃይላት ላይ መንግስት እርምጃ ሲወስድ እንደገና ኡኡታውን በመንግስት ላይ ያሰማል።ምንድን ነው የሚፈለገው?!!

  • War crimes _United Nations Office on Genocide prevention

የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሰዎች በማንነታቸውና በሚከተሉት ሃይማኖት ምክንያት ሲጨፈጨፉና ከፍተኛ ንብረት ሲወድም የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ልፍስፍስ ያለ መግልጫ ለይስሙላ ከማውጣት ውጪ እንዲህ እንዳሁኑ (እንደትግራዩ) አለም አቀፍ ትኩረት እንዲስብና የውጭ መርማሪዎች አላስፈለጉትም ነበር። እውነት እንነጋገር ከተባል ከሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ የተካሄደው ጭፍጨፋ ዛሬ በትግራይ ደረሰ ከትባለው የመብት ጥሰት በስፋቱም በይዘቱም የበለጠ ነው። ንጹሃን ሰዎች በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው “በህይወት የመኖር” መብታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ሲነጠቅ፣ የሰዎች መተዳደሪያ ሙሉ በሙሉ ወድሞ ያለመጠለያ ሲቀሩ፣ በአንድ ቀን ሌሊት ከድህነት አልፈው የሚልሱትና የሚቀምሱት ሲያጡ፤ የኛው ኮሚሽንም ሆነ የአለም አቀፉ የመብት ተከራካሪዎች ነን የሚሉ ሁሉ የለበጣ ሪፖርት ከማውጣት ያለፈ እንዲህ እንዳሁኑ አልዘመሩለትም፡፡ ያንዱ ሕይወት ከሌላው ሕይወት የበለጠ በሚመስል መልኩ!!!

በትግራይ ለተፈጥረው ቀውስና የመብት ጥሰት ማንንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳስብ ይገባል። ከኢትዮጵያዊያን ሌላ የበለጠ ተቆርቋሪ ሊኖር አይችልም። ጥያቄው የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ወጥ ያልሆነ አሰራር ፍትሃዊነትና የመረጃው ተዐማኒነት ነው። በትግራይ የመብት ጥሰቱ መሰረታዊ መነሻውና ተጠያቂው በግልጽ መታወቅ አለበት። ይህም ሕውሃት በሰሜን እዝ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ነው። አቶ ፍስሃ ተክሌ (የአሜንሲቲ ኢንተርናሽናል “የሕወሃት ወኪል”) ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በሰጠው ቃለ ምልልስ ወያኔ በወታደሩ ላይ ያደረገው ጭፍጨፋ ከስብአዊ መብት ጉዳይ ጋር እንደማይገናኝ ሲናገር ሰምቻለሁ። በርግጥ በውጊያ ላይ የሚገኝ ወታደር (combatant) በመሞቱ ወይም በመቁሰሉ ሰብአዊ መብቱ ተጣሰ እንደማይባል ይገባኛል። ነገር ግን ሁኔታው ይህ አልነበረም። ሕወሃት ወታደሮችን በጨፈጨፈበት ወቅት ጦርነትም ሆነ የጦርነት ሁኔታ ጨርሶ አልነበረም፤ የታጠቁም አልነበሩም። ካምፕ ውስጥ ባሏቸው የወያኔ አባላት መሰሪነት መሳሪያ እንዳይዙ የተደረጉ እንደነበሩም ሰምተናል። ጥቃቱ በሁሉም ወታደሮች ላይ በእኩል አልተፈጸመም፤ ትግርኛ ተናጋሪዎች አልተጠቁም። በተወሰኑ የብሄር አባላት ላይ ትኩረት ያደረገ ግድያም ነበር። ሰራዊቱ ቀን የትግራይን ገበሬዎች ሲያግዝ የነበረ፣ ግብዢያ ሲደረግለት የዋለ ሰራዊት አገር ሰላም ነው ብሎ በተኛበት ሁኔታ በተቀነባበረና በአንድ ጊዜ በትግራይ ባሉ የወታደር ካምፖች በሙሉ የተደረገ ፍጅት የሰላማዊ ሰዎችን በህይወት የመኖር መብት የጣሰ መሆኑ በማያወልዳ መልክ መታመን አለበት። በሙያቸው ወታደር ቢሆኑም በዚያን ጦርነት ላይ ባልነበሩበት፣ ባልታጠቁበትና በተኙበት ሁኔታ ሰላማዊ ሰዎች እንጂ combatant ተብለው ሊፈረጁ አይችሉም። ስለሆነም የሰብአዊ መብት ጥሰት አልተፈጸመም ብሎ ማለት የወታደር ልብስ የለበስ ሰው ከሆነ “ስብዕና የለውም” እንደማለት ነው። የሰብአዊ መብት ይዘት ይህ ሊሆን አይችልም። ከተዘረዘሩት 30 መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ውስጥ ቢያንስ ሶስቱን “the Right to life. Everyone has the right to life, liberty and security of person.” በሕይወት የመኖር መብት፤ “No discrimination. Everyone is entitled to all the rights and freedoms, without distinction of any kind, …..” ያለአድሎ ማንኛውንም መብትና ነጻነት የማግኘት መብት እና “Human rights can’t be taken away.

Nothing in this Declaration may be interpreted as implying for any State, group or person any right to engage in any activity or to perform any act aimed at the destruction of any of the rights and freedoms set forth herein” የሰብአዊ መብቶች በማንኛውም ሁኔታ ሊነጠቁ አይችሉም፤ የሚሉትን መብቶች የጣሰ ነው።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ያለውን ሁኔታ እንመልከት፤

  • ወያኔዎች ማረኳቸው ያሏቸውን ወታደሮች በባዶ እግራቸው አሰልፈው በከተማ እየነዱ ደጋፊዎቻቸውን እልል እያሰኙ፣ እያሰደቡና እየተፉባቸው ሲያሸማቅቋቸው በቴሌቪዥን አላዩም? ይህ በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነት አያስጠይቅም?

 

  • ያሰሯቸውና መቀሌን ሲለቁ አብረው ይዘዋቸው ይሄዱትን ወታደሮች መልቀቅ ግድ ሲሆንባቸው መኪና መንገድ ተከትለው ብቻ እንዲሄዱ ከተነገራቸው በኋላ ቀደም ብለው ባሰሉትና በአመቻቹት ዘዴ በጣም ጠባብና በግራም በቀኝም ገደል በሆነና መሸሻ በሌለው ቦታ ሲደርሱ በሲኖ ትራክ ሲጬፈልቋቸው በአጋጣሚ ቆስለው የተረፉ ወታደሮች እያለቀሱ አሰቃቂነቱን ሲገልጹ የመብት ተሟጋቾች አላያችሁም? ለማጣራትስ ምን እርምጃ ወሰዳችሁ? ቢያንስ በሚዲያ የታዩትንና ጉዳት የደርሰባቸውን ወታደሮች ለማነጋገር እንኳ አልሞከራችሁም።

 

  • የተያዙ ሴት ወታደሮችስ የደረሰባችውን የመብት ጥሰት እያነቡ ሲናገሩ፤ ጡታቸው የተቆረጠ ሴቶች እንዳሉ ሲናገሩ ጉዳዩን ለመመርመር ምን እርምጃ ወሰዳችሁ?

 

  • በማይካድራ መታወቂያ እየታየ በማንነታቸው ብቻ ሰላማዊ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት እንደተዘለዘሉ ሁሉም ያውቃሉ። እንደ አክሱሙ የተደራጁ የወያኔን ሰዎች ጠይቀው ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰራተኞች ያስከሬን ሽታ እየተነፈጋቸው ቢያረጋግጡም እንዲህ እንደ አክሱሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ አላስተጋቡትም። በድርጊቱ አፈጻጸምና በተጎዱ ሰዎች ብዛት የማይካድራውን የሚስተካከል የለም። በአክሱሙ የመብት ጥሰት ሪፖርት ዉስጥ መረጃ ሰጭዎቹ ኤርትራዊያንን “አስከሬን እንቅበር ብንላቸው የኛ አስከሬን ሳይቀበር የናንተ አይቀበርም” አሉን በማለት ሲናገሩ ሰማሁ። ይህ ማለት ገደሉ ከሚባሉት የኤርትራዊ ወታደሮች ጋር ውጊያ ነበር ማለት ነው። በውጊያ ጊዜ የተደረጉ መገዳደሎችን አግዝፎ የዘገበው የኮሚሽኑ ሪፖርት በጦርነት ላይ ያልነበሩ አማሮችን ከቤታቸው እያወጡ ያረዷቸውን ንጹሃን ዜጎች የመብት ጥሰት ለአክሱሙ ከተሰጠው ትኩረት እጅግ ያነሰ ነው።

 

  • ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ከተሳፈሩበት አውቶቡስ አስወርደው ወያኔዎች ሲግድሏቸው የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ጉዳያቸው አይደለም።

 

  • የእርዳታ ሰራተኞች በወያኔ ታጣቂዎች ሲረሸኑ የመብት አስጠባቂዎች አይናቸው አያይም፤ ጆሯቸውም አይሰማም።

 

  • ወያኔ የቴሌኮሚኒኬሽንና የመብራት ሃይልን መሰረተ ልማት ሲያወድም፣ የጤና ተቋማትን ሲዘርፍ፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ሲያቃጥል፣ የአክሱም አይሮፕላን ማረፍያን ምንም ስጋት ሳይኖረው ሲያርስ፣ ድልድዮችን ሲያፈርስ አንድም ዓለም አቀፍ ድርጅት ሃይ ያለ የለም። በሌላ በኩል ይሄው ዓለም አቀፍ ድርጅት ተብየው የህዝብና የግል ንብረትን ማውደም የጦርነት ወንጀል አድርጎ ፈርጆታል፤ “Plunder of public or private property” is war crime ብሎታል።

 

  • የዓለም አቀፉ ሕግ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆችን በወታደርነት መመልመልን እንደጦርነት ወንጀል ይቆጥረዋል፡፡ ወያኔ በጦርነቱ ያሰለፋቸውን ህጻን ልጆችን አይተናል፤ መብት ተከራካሪዎችም አይተውታል፤ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አንድም ቃል ትንፍሽ ሲሉ አልተሰሙም።

 

  • ሌላው በትልቁ አጉልተው የሚያጮሁት የሰቶች መደፈር ነው። በእርግጥ ይህ በማንኛውም መልኩ የሚኮነን ነው። በዚህ ረገድ በሰላሙ ጊዜም የወያኔ ካድሬዎች ሴቶችን ሲደፍሩ ተቃውመናል። የትግራይ ሴቶች ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱም በአካል አብረናቸው ባንገኝም ሁላችንም ጮኸናል። ወያኔ በአዲስ አበባ እስር ቤቶች ከሴት እስረኞች

በተጨማሪ በባህላችን አጸያፊ የሆነውን ወንድንም ጭምር ደፍረዋል። ። የተደፈሩ ሴቶች ቁጥር የተጋነነ ቢሆንም ድርጊቱ የሚወገዝ ነው። ግን የድርጊቱ ፈጻሚ ማነው? በክልሉ ብዙ ተዋናዮች አሉ፤ በደረቅ ወንጀል ታስረው የነበሩ ከ10ሺ በላይ እስረኞች ተለቀው በወንጀል ሥራ ላይ መሰማራታቸው በስፋት ይነገራል። እነዚህ ወንጀለኞች በዚህ ተግባር አይሳተፉም ማለት ያስቸግራል። የወያኔ ሴቶችን የመድፈር የቆየ ባህሪ በዚህ ጦርነት ጊዜ አይከሰትም ማለት አይቻልም። እነዚህ እውነታዎች ሳይመረመሩ የወያኔ ደጋፊዎች ከሰጡት መረጃ በመነሳት ወንጀሉን በወታደሮች ላይ ብቻ መደፍደፍ ፍትሃዊ አይደለም።

መረጃ የሚሰጡት በአብዛኛው ወያኔዎች ወይም የወያኔ ሚሊሽያዎች ወይም ወያኔ ያደራጃቸው የወያኔ ደጋፊዎች ናቸው። ወያኔ የሚታወቅበት ዋና መለያው ውሸትና ደባ ወይም ሴራ ነው። በርካታ ዉሸቶቹ ተጋልጠዋል፤ ቦኮሃራም የገደላቸውን የናይጀሪያ አስከሬኖች ምስል ወስዶ አክሱም የተገደሉ አስመስሎ አቅርቧል፤ ያልሞቱ ሰዎችን እንደሞቱ ያቀረበው መረጃ ተጋልጧል፤ አሜሪካ ሆኖ አክሱም እንደሚኖር ቄስ ሆኖ መረጃ የሰጠው ተጋልጧል፤….. ሌላ ሌላም። በቅርቡ በአሜሪካ

ድምጽ ሬድዮ በተደረገ ውይይት ላይ አንድ ተወያይ እንደገለጹት፣ ሴቶችን “አስራ ስድስት ሆነው ደፈሩን በሉ ..ማንም አያጣራውም”፤ “የውጭ ጎብኝወችና ጋዜጠኞች ሲመጡ ባሌ፣ ልጄ ወዘተ ተገደለ ብላችሁ ጩሁ፣ አልቅሱ” የሚሉ ወያኔ ያሰራቸው የቅስቀሳ ቪዲዮች አሉኝ ሲሉ ሰምቻለሁ። ይህን እንደሚያደርጉ አልጠራጠርም። ገጠር ውስጥ በነጭ ወረቀት ላይ በእንግሊዝኛ የተጻፉ መፈክሮችን (እንኳን እንግሊዝኛ በራሳቸው ፊደል መጻፍ የማይችሉ) እናቶች ይዘው ለውጭ ሰዎች ሲያሳዩ ተመልክቻለሁ።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ሴራ አለ፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን ከተርጂነት ሊያወጣ ስለሚችል ምእራባዊያን አልወደዱልንም፤ ተላላኪ የሆነ መንግስት ስለማይኖር ወያኔን ለማስገንጠልና አገሪቱን ለማዳክም አስቀድመው አቅደዋል። ወያኔንም የማይሸነፍ ሃይል አድርገው ወስደውት ስለነበር ተደናግጠዋል። የሰብአዊ ድርጅቶች ነን የሚሉትን ሁሉ (በአገር ውስጥ ያሉትንም ጭምር) አምንስቲ ኢንተርናሽናልንና ሂውማን ራይትስ ዋችን፣ እንድሁም ሌሎች የምእራባውያን አፈቀላጢዎችን አሰልፈው ተነስተውብናል። በግብጽና በሱዳን ሊያስጠቁን እየተዘጋጁ ነው። በዚህ ጊዜ ነው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአንድ መቆም ያለብን። ልዩነቶች አሉ፤ ግን በሃገር ላይ አንድ ሆነን መነሳት የግድ ነው። ጠላቶቻችን በመካከላችን የሉም ማለት አይቻልም። ዘርን ሃይማኖትን እየተጠቅሙ ሊያባሉን የሚፈልጉ የውስጥ ሰርጎ ገቦች ወይም ባንዶች ይኖራሉ። የኢትዮጵያ ልጆች የሆኑ ሁሉ ይህን ሴራ ማወቅ አለባቸው። በውስጣችን ሆነው በአሁኑ ጊዜ መነሳት የሌለበትን የሚያራግቡ ተላላኪዎችን እምቢ ማለት ስንችል አገራችን ባሸናፊነት ከፍ ትላልች። ፈጣሪ ከኛ ጋር ነውና እንወጣዋለን።

 

መላኩ

ከኢትዮጵይያ

መጋቢት 23 2013

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop

Don't Miss