መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ/ም
ቀሲስ አስተርአየ nigatuasteraye@gmail.com
እውነትን ይዞ በፊታቸው የቆመ ሰው ባለመኖሩ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ መርቆርዮስ አፋቸውን አፍነው በዝምታ ማረፋቸውን በሰማሁባት ወቅት አባቶቻችን ይህን የመሳሰሉትን ለዝክረታሪክ በሚያቀርቡበት ትውፊት መታሰቢያ ትሆን ዘንድ የተቀኘሁላቸው ታሪካዊት ቅኔ፡፡
እግዚኦ ፍታሕ ወተበቀል ላቲ በቀላ ለኢትዮጵያ!
እፎ አከየ ዘመነ መርቆሪ፦እምዘመነ ጽሑቅ ዳዊት ለኦርዮን ቀታሊሁ፡ አምጣነ ኩሉ ዐረየ ለቃኤል ምስሌሁ፡ ይስሐት በቃለዕዴሁ ወያብቁ አፉሁ፤
ይደለወሂ ከመ ያርምም መርቆርዮስ አብ ለመልከ ጼዴቅ እኁኁ፤ እስመ ተምኔቶ ኢኮነ ወኢተፈጸመ ናሁ፤ በከመ አበርሃም አብ ዘተፈጸመ ተስፋሁ፤ ወበቅድመ በልዓም ከመቆመ ወለዘካርያስ ከማሁ፤ አርኀዌልሣን ልዑክ እስመኢቆመ ቅድሜሁ፡፡ “ሀለወ ዘይጠበብ ወይጠናቀቅ እንዘ ይዔምጽ ወእንዘ ይመይጣ ለምክር፡ ወያስተርኢ ከመ ያድሉ ለቢጹ፡ ወከመ ያስተራትዕ ፍትሐ ለማኅፈሩ”(ሲራ 19፡22)፡፡
መግቢያ
ቅኔ የምንማረው በግእዙ የተጻፉትን መጻሕፍትና ከኛ በፊት የነበሩ ሊቃውንት ያለፉባቸውን ክፉወችንና ደጎችን ዘመናት የቃኙባቸውን ቅኔወች (ዝክረ ሊቃውንት) እንድንማርበት፤ እንድንመረምርበትና በዘመናችን የተከሰቱትን ደምረን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማቀበል ነው::
ሊቃውንት መምህሮቻችን፤ ቅኔን ከጽንስ፤ የባለቅኔን አዕምሮ ከናት ሰፋድል ጋራ ያመሳስሉታል፡፡ የናት ስፋድል ከውጭ የመነጨውን ተባዕታዊ ዘር ተቀብሎ ከናት የሚፈልገውን ንጥረ ነገር አዋህዶ ይጸንሳል፡፡ አርግዞ በመውለድ ያልነበረ አዲስ አካል ለህብረተሰቡ ያበረክታል፡፡ ባለ ቅኔም ከሕብረተ ሰቡ የሚፈልቁትን ክስተቶች በአዕምሮው ተቀብሎ፡ ከቀደሙ ክስተቶችን ጋራ በራሱ ጥበብ ቀምሮ ቅርጹን ይዘቱን አጠናቅሮ፤ ከዜማው ቅላጼ ጋራ አስታርቆ፤ በዕደ አዕምሮ ተዳሳሽ አድርጎ አዲስ ቅኔ ለህብረተሰቡ ያቀርባል፡፡
ባለ ቅኔ፦ቅኔው በፍርቅ ጸያፎች እንዳይበከል ይጠነቀቃል፡፡ማለትም ከሀሰት፤ ከማስመሰል ከሸፍጥ ካድርባይ አስተሳሰብ የጠራ እንዲሆን የመቀኘት አቅሙን ይጠቀማል፡፡ ቀድሞ የተከሰቱትን ታሪኮችንና ባህላውያን ትዝታወችን በሰምነት አዳዳሲ ክስተቶችን በወርቅነት አጉልቶ ያንጸባርቃል፡፡
“ተናገር ጽድቀ ውስቴታ በእንተ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንከ” (መስተብቁዕ በእንተ ሀገር ) የሚለውን ቀኖናችንን መመሪያ በማድረግ አቡነ መርቆርዮስ በጠቅላይ ምኒስቴርና ባካባቢያቸው በተደረደሩት ፊት ለምን እንዳልተናገሩ ይገልጹልኛል ብየ ያሰብኳቸውን ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ሰባት ምሳሌወችን በሰምነት ጠቅሻቸዋለሁ፡፡
1ኛ ዳዊት 2ኛ ሳሙ 11_ም 12፡ ከቁ 1 እስከ 19
2ኛ ቃኤል ዘፍ 4፡ 5_14፡፡ ዮሐንስ 8፤56
3ኛ ዐርከቃኤል ግብረ አበር ሰይጣን ዮሐንስ 8፡44
4ኛ አብርሃም ዘፍ12፡1_3፤ (8፡1_18) ገላ 3፡14_18
5ኛ በልዓም ዘኁ 22፤26_31
6ኛ ዘካርያስ ሉቃ 1፡62_65
7ኛ መላክ ሉቃ 1፤19
የቅኔው ይዘት ሐተታ
ቅኔዬን ለማስረዳት አስረጅና ሰም አድርጌ የጠቀስኳቸውን ከዚህ በታች
ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ ቅኔ ከሀሰት ከማስመሰልና አጠይሞ ከማቅረብ ፈጽሞ መራቅ አለበት፡፡ አዳዲስ ክስተቶች በወርቅነት ቀደም ብለው የተፈጸሙ በሰምነት ይጣመራሉ፡፡ ያልተፈጸሙትንና ያልሆኑትን ነገሮች ለተፈጸሙ ነገሮች ሰም (ፈጠራወች) አርጎ አለመጥቀስ በታሪካዊ ቅኔ ትውፊት ይመረጣል፡፡
ቅኔውን በጀመርኩበት ስንኝ “እፎ አከየ ዘመነ መርቆሪ“ በማለት አቡነ መርቆርዮስን የገጠማቸውን ክፉ ዘምን ዳዊትን ከገጠመው ክፉ ዘመን ጋራ ለማነጻጸር ዳዊትን ጠቅሻለሁ፡፡ መከራን ከመከራ ለማነጻጸር እንጅ በዳዊትና በአቡነ መርቆርዮስ ላይ ለደረሰባቸው መከራ ምክንያቶቻቸው አንድ አይነት ናቸው ማለት አይደለም፡፡
ለዳዊት “ለዘላለም ሰይፍ ከቤትህ አይርቅም ” 2ኛ ሳሙ 12፤10 እንደተባለ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱም በኋል በኢትዮጵያውያን በተለይም በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የተመዘዘው ሰይፍ እየባሰና እየከፋ ሲቀጥል እንጅ ሲቀንስ አልታየም፡፡
ዔሊን የጠቀስኩት ልጆቹ በፈጸሙት ስህተት ባባትነቱ ንክኪ በልጆቹ ላይ ከደረሰው መከራ እንዳላመለጠ ቅዱስ አባታችንም ተመልሰው በመግባት ወገናቸው በፈጸመው የበደል ንክኪ ከደረሰበት መከራ ከመሳተፍ አላመለጡም፡፡
ዓሊ “ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ ክንድህንም ያባትህንም ቤት ክንድ የምሰብርበት ዘመን ይመጣል”(1ኛ ሳም 2፡ 31) እንደተባለ፤ በአቡነ መርቆርዮስ ዘመንም በቤተ ክርስቲያናቸውና በኢትዮጵያ አገራቸው አስታራቂ ሽማግሌ የለም፡፡ በዘመናቸው ያሉት ሁሉ የአባቶች የማስተዋል አቅም የላሸቀበት የሽምግልናና የክህነት ኃይላቸው የተሰበረበት ክፉ ዘመን ነው፡፡
አብርሃምንም የተጠቀስኩት “አሕዛብ በዘርህ ይባረካሉ” ተብሎ የተነገረውን ተስፋ አሻግሮ አይቶ እንደተናገረ በወንጌል ተገለጿል፡፡ አቡነ መርቆርዮስ ግን ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውና በክርስቲያን ልጆቻቸው ላይ የደረሰው እልቂት እጅግ በከፋ መልኩ ቀጠለ እንጅ ያዩት የተሻለ ነገር ስላልነበረ አልተናገሩም ፡፡
በለዓምን የጠቀስኩት፡ የተቀመጠባት አህያ መናገር የማትችል ነበረች፡፡ መናገር የቻለችው ከእግዚአብሔር የተላከው መላክ ከፊቷ ሲቆም ብቻ ነበር፡ በለዓምን እውነት እንዲናገር የረዳው የመልአኩ በፊቱ መቆም ነበር፡፡ አቡነ መርቆርዮስ ግን በፊታቸው እውነት ይዞ የቆመ ሰው ባለመኖሩ አለተናገሩም፡፡
ዮሐንስ ተጸንሶ እስኪወለድ ዘካርያስ ዲዳ ሆነ፡፡ ዮሐንስ ማለት ደስታ ነው፡፡ ዘካርያስ ዮሐንስ ተወልዶ ደስታ በቤቱ ሲከሰት ደስ ብሎት ጻፈ፡፡ ባንደበቱም ተናገረ፡
አቡነ መርቆርዮስ በአገራቸውና በቤተ ክርስቲያናቸው የሚያሰደስት አዲስ ተስፋ ባለመከሰቱና ዘላቂ ተስፋና ደስታ ባለማየታቸው አልተናገሩም፡፡ ተምሮ፤ ወይም አርሶ ነግዶ ለመኖር ያቃተው ሁሉ አገር አተራማሽ ጎረምሳ፤ ከቅልጥሙ የሚፈላውን ሥጋዊ ስሜቱን የሚያረካበትን ገንዘብ ከየዋሁ ህዝብ ለመዘረፍ “ነቢይ ነኝ ሰባኪ ነኝ፤ ባህታዊ ነኝ” በማለት ህዝባቸውን ያወናበደበት ክፉ ዘመን በመሆኑ አቡነ መርቆርዮስ ዝምታን መምረጣቸው ጠጠር ጎርሶ ከሞተው ከአጋቶን ጋራ ማነጻጸር ሕጸጽ ይመስለኛል፡፡ ”ውስተ ኩሉ ዘተነገርክ ተዘከራ ለድኅሪትከ ወኢተአብስ ልዝሉፉ ”(ሲራ 7፡36) ማለትም፦ በምትናገረው ነገር ሁሉ ከመናገርህና ከተናገርክም በኋል ስለምትመዘንበት መመዘንህን አትርሳ” የሚለውን የሲራክን ምክር ተረድተው ዝምታን መረጡ ማለት የሚሻል ይመስለኛል፡፡
ገዳዮችና አስገዳዮች ሳይወገዱ የተገደለው ሕዝብም ተገቢውን ፍትሕ ሳያገኝ፡ ይልቁንም በባሰ ጭካኔ ህዝቡ በሚታረድበትና በሚጨፈፍበት ወቅት አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ዘመናቸውን እጅግ የከፋ አድርጎባቸዋል፡፡ ወደ ሀገር መግባታቸው ያመጣው መርጋጋትና ሰላም ስለሌለ መግባታቸውን እንደ በረከት የቆጠረ ካለ፡ የነእንጦንስን መነኮሳዊት ተልእኮ የማገናዘብ ድክመት ይመስለኛል፡፡
“ወሥጋሆሙኒ ለጻድቃኒከ ለአራዊተ ገዳም” እንዲል፦ ጻድቃን ከዚህ ዓለም ሲሰናበቱ የሚሸኙት በመንግሥት ሠራዊት ማርሽና ተልእኳቸውን ባልፈጸሙ ካህናት በመታጀብ አይደለም፡፡ መንግሥት ባለውለታወቹን በሚቀብርበት ቦታም አይቀበሩም፡ መቃብራቸው ከርሰአራዊት ነው፡፡ አቡነ መርቆርዮስ በብልጽግና ወታደር ማርሽ ስለተቀበሩ ጻድቅ አያደርጋቸውም፡፡ ስለተቀበሩባትም ለኢትዮጵያ በረከት ወይም ሰላም አያተርፍላትም፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ አትድከሙ፡፡ ከኃጢአተኞች በደረሰበት ባለ ጋራ ከኃጢአት ጋራ እየተጋደላችሁ ገና ደማችሁን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፡፡ ልጆች እንደመሆናችሁ የተናገራችሁትን የማበረታች ቃል ረስታችኋል” (ዕብ 12፡4_5) እንዳለው፦ እኛ ካህናት ይልቁንም መነኮሳት ያጠመቅናቸው ክርስቲያኖች ባረመኔወች ከመሞታቸው በፊት፡ አረመኔወች ደማችንን እስኪያፈሱ ድረስ ካልታገልን ተልእኳችን የተሟል አይደለም፡፡
አቡነ መርቆርዮስ በነበሩበት ዘመን የነበርን፡ አሁንም በሕይወት ያለን ሁላችን ኦርቶዶክሳውያን ካህናት ገለልተኛ ዳኛ ተሰይሞ ከመጀመሪያ ጀምሮ ደሙ ለፈሰሰው ዜጋ አማራ ትግሬ አፋር ሳንል ፍትህ ይፈጸም እያልን ለሁሉም እኩል ድምጻችንን ማሰማት ይጠበቅብን ነበር፡፡ ግማሾቻችን ከእነ ዶክተር ደብረ ጽዮን ጋራ ግማሾቻችን ከነ ዶ/ር ዓቢይ ጋራ በመሰለፍ፡ የተጨፈጨፈውን ሁሉ፤ ከጨፍጫፊወች ጋራ ደምረን የምንከስ ግፈኞች ጳጳሳትና ቀሳውስት ከተከሰትንበት ዘመን ለአቡነ መርቆርዮስ ምን የከፋ ዘመን ይኖራል? አቡነ መርቆርዮስ ወደኢትዮጵያ በመመለሳቸው ሊደሰቱ ይቅርና የተመለሱባትን ቀን የረገሙ፡ እንዲመለሱ ባደረግናቸውም ተማረው የሞቱ ይመስለኛል፡፡ በፊታቸው ከቆምነው መካከል እውነትን የያዘ ስላለነበረ በብዙ ትዝብት ታፈነው የሞቱትን አቡነ መርቆርዮስን ጠጠር ጎርሶ ከሞተው ከአጋቶን ጋራ ማነጻጸር የሁለቱንም ታሪክ ያዛባ ነውና ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡
እግዚአብሔር ካባታችን አቡነ መርቆርዮስ ጋራ በሰማያዊቷ ጽዮን ያገናኘን!
ቀሲስ አስተርአየ
http://amharic-zehabesha.com/archives/179791