ግንቦት 25 ቀን 2017ዓም(02-06-2025)
በዚህ ዐምድ ስር ከ1997-2009 እአአ ድረስ ከሰላሳ በላይ ተከታታይ ጽሁፎችን በማውጣት በአገራችን በኢትዮጵያ ዙሪያ በፖለቲካ፤በኤኮኖሚና በማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ በዓይን ያዬዃቸውንና በዜና የሰማዃቸውን በማስረጃ የተረጋገጡ ክንውኖችን ለአንባብያን ሳቀርብ እንደነበረ የሚያውቁ ብዙዎች ናቸው።የመጨረሻዋን የትዝብት መጻጽፌን ኢትዮጵያ በሄድኩበት በ2019 እአአ ካቀረብኩ በዃላ በልዩ ልዩ ምክንያትና በሌላ አቅጣጫና በተለያዩ እርዕሶች ስር በመጻፍ የተነሳ በትዝብት አምድ ስር ከመጻፍ ተቆጥቤ ነበር።ይህ ማለት ግን ለትዝብት የሚበቁ ጉዳዮች ሳይኖሩ ቀርተዋል ማለት አይደለም።እንዲያውም ብዙ የሚያስተዛዝቡ ጉዳዮች ከቀን ወደ ቀን ተፈጥረዋል፣ እዬተፈጠሩም ነው። የትዝብትን መቋረጥ ተከትሎ ለምን ተቋረጠ ብለው የሚጠይቁኝ ጥቂቶች አይደሉም።
አሁን ባለንበት ወቅት በአገራችን በኢትዮጵያ ሊታለፍ የማይችል የሚገርም፣ የሚያሳፍር፣ብቻም ሳይሆን አስጊ ሁኔታ በመከሰቱ ይህንን በሚመለከት የታዘብኩትን ለመግለጽ ትዝብት ካለችበት ማረፊያ ቤት ጎራ ብዬ በተለመደው ልሳኗ እንድትናገር ይዣት ቀርቤያለሁ። የአገዛዙ ጉድ ተነግሮ አያልቅምና ወደ ሰሞነኛው ትዝብቴ ልውሰዳችሁ።
ለብዙ ጊዜያት ከሕዝቡ በኩል የሚቀርቡትን ጥያቄዎች በጉልበትና ባሻጥር ሲያፍን የኖረው አገዛዝ የህክምና ባለሙያዎችን የመብት ጥያቄ በሚታወቅበት ዘዴው ለማድበስበስና ለማፈን ተገቢ መልስ ከመስጠት ይልቅ በማስፈራራትና ሌላ ተጓዳኝ ታሪክ በመፍጠር ተቃውሞው ወደሌላ የህብረተሰቡ ክፍል እንዳይዛመት የተለያዩ አሻጥሮችን በማቅረብ ላይ ተጠምዷል።ከህክምና ሙያ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን በጥቅም የተደለሉና የኔው ወገን ናቸው የሚላቸውን መሃይሞች የሃኪሞች ልብስ (ነጭ ገዋን)አልብሶ ጥያቄያቸው መልስ እንዳገኘና በአድማው ላይ የቀጠሉት ሃኪሞች ሳይሆኑ የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት ናቸው በማለት ጸሃይ የሞቀውን አገር ያወቀውን እውነታ ለመካድ ሲንደፋደፍ ታይቷል።በተመሳሳይም ነጭ ካፖርት የለበሱት መምህራን ለመብታቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ እንዲሁ አዳነች(ገደለች ብትባል ይሻላል) የተባለች ከንቲባ (ቀንጥባ) ምክንያቱም በመሬት ችብቸባው ገበያ ላይ የድርሻዋን በመቀንጠብ ላይ የተሰማራች በመሆኗ) ይህችው በሙስና የደለበች ጎሰኛ በጠራችው ስብሰባ አዳራሽ እንዲገቡ የተደረጉ ያገዛዙ አጋሮች መምህራን መስለው ጥያቄያቸው መልስ እንዳገኘ ሲወሸክቱ በአደባባይ በቴሌቪዥን ታይቷል።የሁለት ነጭ ለባሾች ትግል(ነጩ አብዮት) በመባል የሚጠራው የትግል ጎራ አገዛዙን ገርስሶ የሚጥልና ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የመሰላቸው አካላት በሙሉ ከያሉበት እንደጅብ ተጠራርተው ትግሉን ለማዳፈን በመረባረብ ላይ ሲሆኑ የሕዝቡንም ትኩረት ለመቀዬር አንድ ጊዜ ወደብ ሌላ ጊዜ ወራሪ መጣብህ በማለት እንደ እብድ ውሻ እዬጮሁ ከጎረቤት አገራት ጋር ግጭት በመቀስቀስ ላይ መሰማራታቸውን ታዝበናል።
አገዛዙ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እጅና ጓንት ከነበሩት ወዳጆቹ ከህወሃትና ሻብያ ጋር እሰጥ አገባው ተጠናከሮ ቀጥሏል።ያልታደለው በመከላከያ ስም የተሰለፈው የሕዝብ ልጅ በጎሳ ታፔላ የራሱን ሕዝብ ለመግደል ተሰማርቶ ብዙ ጥቃት ቢያደርስም እራሱም የጥይት እራት ከመሆን አልዳነም።እንደቅጠል እዬረገፈ ነው። ለፋኖ እጁን የሚሰጠው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። የአገሩን ዳር ድንበር ሳያስከብር መሳቂያ መሳለቂያ ሆኗል። የኦነግ-ኦሕዴድ መሪ አብይ አህመድ ኢሱ እያለ ሲያንቆለባብስና እንደፍቅረኛ የጣት ቀለበት ያንገት ሃብል ሲያስርለት የነበረውን አምባገነኑን ኢሳያስ አፈወርቂን ሰብአዊ መብት የማያከብር ተንኳሽና የከባቢው ረባሽ ብሎ ሲከሰው ራሱን ግን የዴሞክራሲ አባት የእድገትና የሰላም ተምሳሌት አድርጎ ይስላል። ጅንጀሮ ከፊቱ የሚሄደውን ጅንጀሮ መላጣ ቂጥ እያዬ ይስቃል እንዲሉ!
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እዬተመላለሱ ሽር ጉድ ይሉባት የነበረዋን ኤርትራን የመከላከያ ሚኒስትር ተብዬዋ አይሻ ሙሃመድ ሳትቀር እንደ አገር ሊቆጠር የማይችል ከመንደር ያነሰ በማለት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባትን ኤርትራን ለማኳሰስ ደፍራለች።ለአንድ አምባገነን ተብሎ ሕዝብን መናቅና ይዞታውን ማጥላላት ትክክል ካለመሆኑም በላይ የእብድ ወይም የደንቆሮ እይታ ነው።አንደኛው ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ ነውና ነገ ደግሞ ከሚሊዮን በታች ዜጋ የሚኖርባትን፣የምዕራባውያን የጦር መሣሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤት የሆነችውን ጅቡቲን ምን እንደሚሉ ሲያስቡት ጅቡቲያውያን ምን ይሰማቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ ይጭራል። ህወሃት በዘመኑ አሁን ደግሞ ኦሕዴድ ኦነግ በተራው የወደዱትን ሚጢጢ ከተራራ በላይ ማግዘፍ የጠሉትን ግዙፍ ደግሞ ከጤፍ በታች ደቃቃ አድርጎ ማኮሰስ ሲታይባቸው ታዝበናል።ይህ የጤና ቢሶችና የአምባገነኖች ጸባይ እንጂ የጤናማፓለቲከኛ ምልክት ነው ተብሎ አይታሰብም።የ40 ሚሊዮን አማራ ሕዝብ የመብት ሠራዊት ፋኖስ በጣት የሚቆጠሩ የቀማኛና ሽፍቶች ጥርቅም ተብሎ ይጠራ የለምን? አለመሆኑን ግን ልባቸው ያውቀዋል፤የላኩት ወታደር አስከሬን ክምርና የምርኮኛው ጋጋታ ምስክር ነው። ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ!!
በኤርትራና በኢትዮጵያ የሰፈኑት አምባገነናው አገዛዞች ሲወገዱ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ በመቀራረብ በጋራ በሰላም ሊኖሩ እንደሚችሉ በታሪክ ታይቷል።ወደፊት በበለጠ ደረጃ ተቀራርበው ሊኖሩ እንደሚችሉ ያለውን ዕድል ማሰብና ማጎልበት ተገቢ ነው።ያ የወደፊት ቀናና ጤነኛ የሕዝብ ግንኙነት በሁለት አምባገነኖች እሰጥ አገባ ሊሸፈን አይችልም።አንዱ ሌላውን ቢተችና ቢያወግዝ ትዝብት አምድ ግን አመድ በዱቄት ይስቃል ወይም ይሉሽን ባልሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ ወይም ስልቻ ቀልቀሎ ቀልቀሎ ስልቻ በማለት የሁለቱንም ከንቱነት ትመሰክራለች።
በትግራይ ውስጥ መሽጎ በሕዝቡ ስም የሚነግድ፣የጎሳ ፖለቲካ ፈጣሪና አራማጅ የሆነው የተልእኮ ሽብርና ጦርነት ለማካሄድ የተሰለፈው የህወሃት ቡድን ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ቢወርድ የከባቢው ዋና ችግር ተወገደ ማለት ነው። አሁን በጥቅምና በዘረፋ ድርሻ ላይ እርስ በርሱ መጋጨቱ ለትግራይ ተወላጅ ጥቅምና መብት አለመሆኑን ትዝብት ትመሰክራለች፤ሕዝቡም ያውቃል።አንደኛው ቡድን ከኦነግ ብልጽግና ጋር ተባብሮ ድንበር ጥሶ የትግራይን ሕዝብ የጨፈጨፈውን ሻብያን ለመቀራረብ ሲጋጋጥ ሌለኛው ቡድን ኦነግ ብልጽግናን ተጠግቶ ትግራይን ለዳግመኛ ችግር ለመዳረግ ከፍ ዝቅ ሲል ይታያል።ከዓላማው ፈቀቅ ያላለም አዲስ ድርጅት መፍጠሩን ይፋ አድርጓል።በቀረው የኢትዮጵያ መሬት ላይ የሰፈነው የኦነግ ኦሕዴድ አገዛዝ እንዲሁ እርስ በርሱ በጥቅምና በዘረፋ ቢባላም የጋራ ዓላማው አንድ ነው፤ኢትዮጵያን አፈራርሶ ኦሮሚያ የተባለች ያልነበረች አገር መመሥረት ነው።ለዚያም በጥቅም ከተጣላቸው ኦነግ ቤተሰብ ድርጅት አባላት ጋር ለመሞዳሞድ ሽማግሌ በመላክ ላይ ነው።ይህም እኩይ ቡድን በሕዝባዊ አመጽ ካልተገረሰሰ ሰላምና አንድነት አይመጣም።የእነዚህ የሶስቱ ፋሽስታዊ ቡድኖች መወገድና መጥፋት ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን ለከባቢው ሰላም ወሳኝ ነው።
ሌላው ምንም እንኳን አምባገነናዊ አገዛዝ በኤርትራ ውስጥ መኖሩ ባይካድም እንደ ኢትዮጵያ የጎሳ ስርዓት አስፍኖ ሕዝብን በጎሳና በክልል ከፋፍሎ ትርምስ ውስጥ አልከተተም።በራሱም ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጆ ጦር አሰማርቶ አልጨፈጨፈም።የነገው ባይታወቅም የዛሬው እውነታ ይህ ነው።ይህ መሆኑ ብቻ ግን ላለፉት ሰላሳ አራት ዓመት የተንሰራፋውን የአንድ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን አገዛዝን መካድና መደገፍ አይደለም።
ወጣም ወረደ ለትዝብት ሰይጣናት መካከል የሚሻለውን ሰይጣን የመምረጥ ያህል ነው።ግን የመጨረሻ መጨረሻ ሁለቱም የትዝብት ምርጫዎች አይደሉም።አምባ ገነን ስርዓቶች ተወግደው ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርዓት እንዲሰፍን ትሻለች።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ተቀራርበው በጋራና በሰላም እንዲኖሩ የብዙዎች ፍላጎት ነው።ሁለቱም እጣ ፈንታቸው የተያያዘ መሆኑ አይካድም።አብረው የኖሩበት ዘመን በደምና ሥጋ ከማስተሳሰሩም በላይ በታሪክ፣በእምነት በቋንቋና በፊደል ፣በልዩ ልዩ ማህበራዊ ሰንሰለቶች የሚጋሩት ብዙ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ አለ።ግንኙነታቸው ከመሬት ድንበር ወይም ከቋንቋ በላይ ነው።ለኢትዮጵያ አገራዊ ምስረታና ከወራሪ ክንድ ጠብቆ ያቆያት ገፈት ቀማሹ ማን ሆነና?ከሌሎቹ ወገኖቹ ጋር ሆኖ የህይወት ዋጋ የከፈለው የኤርትራ ተወላጅ እንዴት ይዘነጋል? ዘርአይ ደረስና ሌሎቹ እንዴት ይረሳሉ?አሁንም ቢሆን ብዙ ዘርዓይ ድረሶች አሉ።
የደቡቡና የመካከል አገሩ ተወላጅ ሲከፋው ወደ ሰሜኑ የሰሜኑም ተወላጅ ሲከፋው ወደ መካከልና ደቡብ እዬሄደ ህይወቱን የሚያተርፈው የጋራ ልማዱ ነው።በክፉ ቀን መጠለያው በደህና ቀን ሥርቶ ማደሪያው በጋራ የመሰረቷት ኢትዮጵያ ነች። ዓለም ለመሰባሰብ በሚጓዝበት ዘመን ውስጥ ሆኖ ስለ ነጠላ ጎሳና ማንነት ጦር በመማዘዝ ከአያት ቅድመአያት የተረከባትን ታሪካዊ አገሩን ለመበታተን መነሳት የዘመኑ እርግማን ብቻም ሳይሆን ያጥፍቼ ልጥፋ ልክፍት ነው።
የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷም ሆነ መሬቷ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ሃብት ነው።ትውልድ ባግባቡ ተጠቅሞ፣ ከባቢውን ሳይበክልና ሳያወድም ለሚመጣው ትውልድ የሚያሳልፈው የጋራ ንብረት ነው።በጎሳና በሌላው መስፈርት ሊቆጣጠሩትና አንዱ ባለቤት ሌላው ባይተዋር የሚሆኑበት አይደለም።ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ጊዜና ቦታ የመኖር የመንቀሳቀስ ሃብት የማፍራት መብት አለው።የመጠበቅና የመንከባከብም ግዴታ አለበት።አንድ ከባቢ ለተወለደበት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ሃብቱ ነው።አሁን በወልቃይትም ሆነ በሌላው አካባቢ ያለው የእኔ ብቻ ነው ግብግብና ትርምስ የጎሳ ፖለቲካ ያመጣው በሽታ ነው። አቅምና ፍላጎት ያለው ኢትዮጵያዊ ሠርቶ የኖረበት አካባቢ ነበር፤ አሁንም ሆነ ወደፊት ያ ልማድ ተመልሶ ተግባራዊ ከሆነ ችግሩ ሁሉ ይወገዳል፤ ለዚያ ግን የችግሩ ወላጅ የሆኑት ጎሰኛ ቡድኖችና አስተሳሰባቸው በአገር ወዳዶችና በኢትዮጵያውያንነት አስተሳሰብ መተካት ይኖርበታል።
የመከራ ሰለባ የሆነው የትግራይ ተወላጅ ለተጋለጠበት የኑሮ ሸክም መከራ፣ ስቃይና እልቂት የዳረገውን የህወሃት ቡድንና አስተሳሰቡን አሶግዶ ከቀረው ወገኑ ጋር በዴሞክራሲና ፍትሕ ጥላ ስር ከመኖር የተሻለ ዕድል አይኖረውም፤ ሌላውም ኢትዮጵያዊ እንዲሁ ባናቱ ላይ ተቀምጦ የመከራ ሰለባ ያደረገውን እርስ በርሱ የሚያጫርሰውን ለመበታተን የቋመጠ ዃላቀር የጎሰኞች ብልጽግና ተብዬ የኦሮሙማ ፋሽስቶች አገዛዝ አሶግዶ ለተሻለች ኢትዮጵያ ተባብሮ ከመነሳት ውጭ የተሻለ መንገድ አይኖረውም። የኤርትራም ሕዝብ እንዲሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ ታሪካዊ ዝምድናና ግንኙነት ያለው አያገኝም።በቀጠናው ላለው እልቂት ስደትና መከራ ድህነትና በሽታ ኻላቀርነትና መበታተን ዋና ምክንያቶቹ ህወሃት ሻብያና ኦነግ ኦሕዴድ ናቸው።እነዚህን አሶግዶ የሰላም የአንድነትና የእድገት ባለቤት ለመሆን በጋራ መምከርና መቆም ያስፈልጋል።የነሱ ተከታይና አገልጋይ መሆን ለባሰ መከራ እልቂትና ድህነት ይዳርጋል።ከጠላት ሰፈር ወዳጅ አፈራለሁ በሚል ጉጉት ማጫፈር ለጊዜው ካልሆነ በቀር ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም።ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው የሚለውን ማስታወስ ይጠቅማል።ሻእብያን ተጠግቶ ወያኔንም ሆነ ኦነግ ብልጽግናን፣ወያኔንም ተጠግቶ ሻብያንና ኦነግ ብልጽግናን ፣ኦነግ ብልጽግናንም ተጠግቶ ሻብያንና ወያኔን ወግቼ ይሳካልኛል ማለት የጅሎች ስልት ነው።በጠላት ሠፈር ማንና ምን አለ? ብሎ እራስን መጠዬቅ ብልህነት ነው። የነዚህ አንድም ሶስትም የሆኑ ጸረ ሕዝብና ጸረ አገር የሆኑ ቡድኖች መኖር የመከራውን ዕድሜ ያረዝመዋል።የነሱ መኖር ከወንበዴዎች ግፍ ቢተርፉም አሁን በገሃድ ለሚታዬው ሰብአዊ መብት ለማይከበርበት የዘረኞች እልህ መውጫ ለሆነው ስደተኛነት ይዳርጋል።አገርንም የውጭ ወራሪዎች መፈንጫ ያደርጋል። ያለው ሁኔታ እንዳይቀጥልና የባሰ እንዳይመጣ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን በያሉበት ተቀራርበው መፍትሔ መፈለግ ይኖርባቸዋል፤ጊዜውም አሁን ነው።የእነሱ በአንድ ላይ መቆም የራሳቸውን ብቻም ሳይሆን የከባቢውን ሕዝብ ሰላም፤አንድነትና እድገት ያረጋግጣል።ለሌላውም የአፍሪካ በተለይም ለምስራቅ አፍሪካ ሕዝብ ምሳሌና ደጀን ይሆናል።
አገሬ አዲስ