“ከባለቤቴ ጋር ስምምነት መፍጠር ተሳነኝ፤ እባካችሁ አንድ በሉኝ”
ዕድሜዬ ሰላሳዎቹ መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ባለቤቴም በዚሁ ክልል አጋማሽ ላይ ናት፡፡ ለአስር ዓመት ያህል በትዳር ህይወት አሳልፈናል፡፡ ደስ የሚሉ ሁለት ህፃናት ያሉን ሲሆን ሁለታችንም ቤተሰባችንን ሊያስተዳድር የሚችል በቂ ገቢ እናገኛለን፡፡ ችግሬ ከባለቤቴ ጋር በነገሮች አለመስማማት ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ተግባቢና ተጫዋች ስሆን ኧረ ለሌላው ችግርም አማካሪ ነኝ፡፡ ሚስቴ እኔ የማደርገው በብዛት አይጥማትም፣ የሆነ ነገር ገዝቼላት ስመጣ እንኳ አመሰግናለሁ በማለት ፈንታ ማሽሟጠጥና ማጣጣል ነው የሚቀናት፡፡ ይቅርታ የሚባል ነገር ፈፅሞ አልፈጠረባትም፡፡ ስህተቷን በጩኸትና ለቅሶ ለመሸፈን ትሞክራለች፡፡ ቤቴን ለማሻሻል ብዙ ነገሮችን ሞከርኩ፣ ከእኔም ችግር እንዳለ ለመፈተሽ ጣርኩ፡፡ አልሆነም፡፡ በዕውነት እንዳሰብኩት እየሆነም አይደለም፤ ደካከምኩኝ፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን እንኳ አብረን እየሄድን ግማሽ መንገድ ሳንጓዝ መጨቃጨቅ እንጀምራለን፡፡ ትዳራችን በሰላምና በፍቅር መዝለቅ ይችል ዘንድ ምን ማድረግ እንደሚገባን ለሌላም ስለሚጠቅም ምክራችሁን ብትለግሱን፡፡ አንባቢያችሁ ኤ ዚ
የኢሳያስ ከበደ ምላሽ፡- መቼም ስለትዳር ብዙውን ጊዜ ብናወጋ በቀላሉ የምንጨርሰው አይመስለኝም፡፡ በተለያዩ አምዳችን ላይ አንስተናል፤ በሰዎች ላይም የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በመረዳት ብዙ መንፈሳዊና አለማዊ ፀሐፍትም በየፊናቸው አውግተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በየትኛው የትምህርት እርከን ላይ እንደምንመድበው ባይገባንም ትዳር በህይወት ዘመናችን በርካታ ጉዳዮችን የምንማርበት መድረክ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዕውነት ልክ እንደሌላው ስርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት ባለትዳሮች በዘመናቸው የሚማሩበት ዕድል ቢኖር ተመሳሳይ ችግሮች ገነው ባልተፈጠሩ፤ ቢፈጠሩ እንኳ በቀላሉ መፍትሄ ባገኙ ነበር፡፡ በቅድመ ጋብቻ ወቅት የነበረውን ለስላሳ ባህሪና ሁሌ የሚናፈቅ መረዋ ድምፅ በድህረ ጋብቻ ጊዜ ሊጎረብጥና ጆሮ ሊያሳምም ይችላል፡፡
በትዳር ህይወት ውስጥ የሚገኙ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ መቼም የአምላክ በረከቱ የትየለሌ ነው፡፡ ‹መባረክ› በገንዘብና ቁሳዊ ነገር ብቻ መስሎን ከመንገድ ወጣ ማለት ጀመርን እንጂ አሰጣጡ በተለያየ መንገድ ነው፡፡ ላንዳንዶቻችን ብዙዎች እንደምናስበው በንብረት፣ ለሌላኛው በሰው፣ ለሌላው ደግሞ በዕውቀት፣ ለሌሎቻችን በመንፈስ ፍሬዎች (ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የዋህነትና ራስን መግዛት) ይባርከናል፡፡ በእርግጥ ብዙዎች ያለንን አናውቅም፤ ያወቅነውም ቢሆን ያለንን በአግባቡ አልተጠቀምንም፣ ለመጠቀምም ፈቃደኞች ያልሆንን ብዙ አለን፡፡ ያልገባን ነገር ምን መሰላችሁ ያለን የሚበዛልን የያዝነውን በመደበቅና ያለጥቅም ቁጭ እንዲል በማድረግ ሳይሆን እያወጣን ለሌላው እያካፈልን ስራ ላይ ስናውለው ነው፡፡
ሌላው ከፅሑፍህ የምንረዳው ከሰዎች ጋር በጣም ተግባቢ መሆንህን ነው፡፡ ስለዚህ ነገር በእውነት ደስ ብሎናል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ ሊኖው ከሚገባ ቁልፍ ማህበራዊ ክህሎት ውስጥ አንዱ ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መኖር ነው፡፡ አየህ እንደነገርከን ከሰው ጋር መልካም ግንኙነት ሲኖርህ የተለያዩ ሀሳባችን መካፈል ያስችልሃል፡፡ ሰዎችን ከጭንቀታቸው እረፍት እንዲያገኙ ስታደርግ፤ ውስጥህ ያለውን ዕምቅ አቅምና ክህሎት በማውጣት ለሌሎች መፍትሄ መሆን ስትጀምር በእርግጥ ደስ ይላል፡፡ ታዲያ አንተም በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ የምትማራቸው ነገሮች እንዳሉ እውን ነው፡፡ ከሌሎች ሰዎች ትማራለህ፤ ከራስህም ድርጊትና ተሞክሮ እንዲሁም በህይወትህ ከሚገጥሙህ መነሳትና መውደቅ ትማራለህ፡፡ ይህን ወደፊት አጠናክረህ ልትገፋበት የሚገባ መልካም ባህሪና ትልቅ ችሎታም ነው፡፡
አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህም ልጆች በመደሰትህ መልካም ነገር ነው፡፡ በህይወታችን ብዙ የምናማርራቸው ነገሮች እንዳሉን ሁሉ ለቁጥር የሚታክቱ ደስ የሚሉና ስለነዛም ነገር ልናመሰግንባቸው የሚገቡ ስጦታዎች አሉን፡፡ አንዳንዴ ስራ ውለህ ደክመህ፣ ቤትህ ውስጥም ከባለቤትህ ጋር በገጠመህ ጊዜያዊ ችግር ተመስጠህ ሳለህ ልጆችህ በደስታ ሲቦርቁ ስታይ ጭንቀትህን ያስረሱሃል፡፡ ከነበርክበትም ጊዜያዊ ቻናል ያወጡህና ወደ ኤፍ.ኤም… ያስገቡሃል፡፡ ልጆችህን ስታስብ ዛሬንና ነገን የተሻለ ነገር እንድትሰራ ያደርግሃል፤ ያበረቱሃልም፡፡ እንግዲህ ወንድማችን በህይወት ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ በቀላሉም አሁን እንደምንላቸው ቶሎ እውን ባይሆኑም መልካም፤ ብሩህና ጥሩ የሆነውን ነገር ባሰብክ ቁጥር መልካምና የተሻለ ነገር ትሰራለህ የሚል እምነት አለን፡፡ መልካም አስብ፣ መልካም ነገር ስራ፣ መልካምም ነገር ይከናወንልሃል፡፡
ወደ ዋናው ቁም ነገሩ ስንመጣ ጥያቄህ ላንተ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ጥንዶችና ባለትዳሮች እንቆቅልሽ የሆነ ነገር ይመስለናል፡፡ በትዳርም ሆነ ማንኛውም ግንኙነት አልጋ በአልጋ የሆነ ምንም ነገር እንደሌለ እናምናለን፡፡ እንዲኖርም የምንጠብቅ ከሆነ የዋህነት ነው፡፡ ነገር ግን በህይወት የሚገጥሙንን ክስተቶች በአግባቡና አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለመመለስ ከሞከርን ትዳራችንን ወደ ፈለግነው አቅጣጫ ልናመጣው እንችላለን፡፡ መሰረታዊ ከሆነው የስሜት ፍላጎቶች (የማፍቀርና የመፈቀር፣ ለራስ ያለን መልካም እይታ፣ ራስን የመቻል…ወዘተ) ባሻገር አንዳቸው የሌላኛውን ፍላጎት ማወቃቸው ለትዳራቸው መጠናከርና መሻሻል ወሳኝ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡
ስለዚህ ጉዳይ በአንድ ወቅት አንዱ ወዳጃችን ሚስቶች ከባሎች ምን ይፈልጋሉ? ባሎችስ ከሚስቶቻቸው ምን ይሻሉ? የሚል ፅሑፍ የላከልንን መነሻ በማድረግና ሌሎችን መፅሐፍት በማጣቀስ የሚከተሉትን ምክሮች ተግባራዊ ብታደርጉ ትዳራችሁን አሁን ካለበት ወደተሻለ ደረጃ ታደርሳላችሁ ብለን እነሆ ብለናል፡፡ አሰጣጣችንም ለአያያዝ ስለሚያመች በአግባቡ በመያዝ በህይወታችሁ እንድትለማመዱ መሞከር የእናንተው ባለጉዳዮቹ ድርሻ ነው፡፡ ለአሁኑ እስቲ ከሚስቶች ፍላጎት እንጀምር፡፡
1. ሁልጊዜ እወድሻለሁ በላት
መቼም ስታገባት ተገደብ እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ ወደህና ፈቅደህ ከሆነ ደግሞ ያገባሃት ልብህ ውስጥ ያለውን በማውጣት እወድሻለሁ በላት፡፡ ይህን ማለት እኮ ወጪ የለውም፡፡ ብላት ሌላ ነገር ይሰማት ይሆናል፣ ወይም ይህ ክብሬ ይቀንስብኛል አትበል፡፡ ከአምላክህ ቀጥሎ ክብርህ እርሷ ናት፤ ለርሷም አንተው ነህ፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ በል ስላልንህ ብቻ ሳይሆን በእርግጥም ስለምትወዳት ነው ማለት የሚገባህ፡፡ መፅሐፉስ ከተደበቀ ፍቅር ግልፅ ዘለፋ ይሻላል… ሲል አላነበብክምን? አየህ እህቶች ሁሌም ቢሆን መወደዳቸውን በንግግርና በድርጊት እንድታረጋግጥላቸው ይፈልጋሉ፡፡ በእርግጥ የሚከብደው በውስጥህ የሌለውን ፍቅር ለማለት ስትሞክር ነው፡፡ ያ ማታለል ነው፣ በራስ ላይ የከፋ የስነልቦና ችግር መፍጠር ነው፡፡ ገባህ የምንልህ?
2. መረዳትና ይቅር መባልን (Understand and forgiveness)
ከሚስቶችም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት አንዳችን ሌሎች የሚሉትን ነገር መረዳት መቻላችን ወሳኝ ነገር ነው፡፡ የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን ካልተረዳን፣ በነርሱም ቦታ ሆነን ካልተመለከትን አተረጓጎማችንም የተሳሳተ ነው የሚሆነው፡፡ ማንም ሰው ፍፁም ስላልሆነ ባለቤትህም ጥፋት ልትሰራ ትችላለች፡፡ ችግሯን በመረዳት ይቅርታ ለማድረግ ወደኋላ ማለት አይገባህም፡፡ እርሷ እንዳልፈጠረባት ብትነግረንም አንተ ግን ሁሌም ቢሆን ይቅር ከማለትና ከመረዳት መቦዘን የለብህም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እርሷን ይቅርታ ማድረግን፣ ትዕግስትን፣ ቻይነትን፣ ታስተምራለህ፡፡
መማር ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በመመረቅ ብቻ ነው ለማለት አንደፍርም፣ ይልቁኑ አብረውን ከሚውሉ ሰዎችም መለወጥ እንዳለ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ የምንልህ ነገር ከገባህ መልካም ግንኙነት መዝለቅ የሚችለው ይቅር በመባባል ነው፡፡ የምድሩ ብቻ ሳይሆን የሰማዩም የሚቀናው ይቅር ከልብ ስንባባል ነው፡፡ ቂም አርግዞ ብዙ መንገድ መጓዝ አይቻልም፡፡ ጊዜው ሳይደርስ ይጨናገፍና ለችግር ይዳርገናል፡፡
3. በቂ ጊዜ ማግኘትን
ብዙዎች ሆዳችንን ለማሸነፍ አሊያም ዝናን ለማቅረብ ስንል አብዛኛውን ጊዜያችንን በስራ ማሳለፋችን አይቀርም፡፡ መድከማችን ለበጎ ቢሆንም የትዳር ህይወታችንን ግን እንዲጎዳ መፍቀድ የለብንም፡፡ ችግራችን በስራ ደክመን ጀርባችንን ከፍራሽ ላይ ለመጣል ስንጣደፍ የትዳር ህይወታችንንም አብረን እናጋድማለን፡፡ በድካም ያተረፍነውን በሽታ ስንተካከም ወንድማን እህት ሆነን እንከርማለን፡፡ የምንልህ፣ ከገባህ ሚስቶች በቂ የሆነ ጊዜ ከባሎች ማግኘትን ይሻሉና የምትወያይበት፣ አብረኻት የምትዝናናበት፣ ዕቅድህን ነጻና ግልፅ በሆነ መንገድ የምታዋይበት ጊዜ በሚገባ ስጣት፡፡ እግዚአብሔርን ባትፈራ ጥላህ ጊዜ ወደሚሰጣት ቦታ በሄደች ነበር፡፡ ነገር ግን እምነቷ ልቧን እንዳተሸፍት ስለሚከለክላት ስሜቷን ብቻ በማራቅና በመነጫነጭ ዕድሜዋን እንድትገፋ ያደርጋታል፡፡ ስሊሊህ ከዚህ አንጻርም ያላችሁበትን ሁኔታ ማጤን አግባብ ነው እንላለን፡፡
4. ከእምቢታ ይልቅ እሺ መባልን
ብዙውን ጊዜ ባለቤትህም ሆነች ልጃችሁ በሚጠይቁህ ነገር ላይ አይሆንም/እምቢታን ካስለመድካቸው አንተን መሸሻቸው እውን ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላም ጊዜ መጠየቅ ቢፈልጉ እንኳ እሺ አይለንም የሚል ግምት ስለሚኖራቸው የጨለመ አመለካከትን ያዳብራሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሳይሆን በፊት በነበሩ ክስተቶች ላይ ይመረኮዛሉ፡፡ የጠየቁህ አይሆንም ከማለትህ በፊት ደግመህ ለማሰብ ሞክር፡፡ ይህን ስንልህ ሁሉንም ነገር እሺ በላቸው እያልን እንዳልሆነ ይታወቅልን፡፡ በእርግጥም ማለት ከተገባህ ለምን እንዳልካቸውና ለሁላችሁም ጥቅም እንደሆነ ግለፅላቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ለምትጠይቀው ነገር አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ግንኙነታችሁን በቀላሉ ሲለወጥ ማየት ትችላለህ፡፡… እሺ ይበልጣል ከሺ… ሲባል አልሰማህም? አየህ ሰዎች እሺ በመባል ከጭንቀት ያርፋሉ፤ የተለያየ መላምቶችን እያሰቡ አዕምሮአቸውን በመጥፎ ነገር ከመሙላት ይተርፋሉ፡፡
5. መደመጥን
ማድመጥ ግንኙነትን ሊያሻሽሉ ከሚችሉ ነገሮች ውስጥ አንዱ እንደሆነ በተለያዩ አምዶቻችን ላይ ያነሳን ይመስለናል፡፡ በንግግራችን ወቅት ሀሳባችንን ሳንከፋፍል ትኩረት ልንሰጥ ይገባል፡፡ ማንኛውም ሰው ሚስቶችንም ጨምሮ ከሚያናግሯቸውና አብረዋቸው ካሉ ግለሰቦች መደመጥን ይሻሉ፡፡ ሚስት ከልቡ እየሰማኝ ነው ብላ የተናገረችውን ቁም ነገር ባለቤቷ እንዳልሰማ ብታውቅ ምንኛ ሊያማትና ባለቤቷ አብሯት እንዳልነበር ስትረዳ እንደሚሰማት መገመት ትችላላችሁ፡፡ ይህ ደግሞ ለርሷ ቦታ እንደማንሰጣት ሊሰማት ይችላል፡፡ በሌላ አነጋገር የምታመጪው ሀሳብ፣ ወሬ የትም የሚገባ አይደለም ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳቱ ከማየሉ በፊት በደንብ አድምጣት፣ እየተከታተልካት ለመሆኑም የምልክት ቋንቋ አሳያት፣ ከዛም ባለፈ ያለችውን በትክክል ለመረዳት ደግመህ በሌላ ቋንቋ ንገራት፡፡ ስለዚህ የምንልህ ከጆሮ በዘለለ ባለቤትህን ከልብህ ልታዳምጣት ይገባል ነው፡፡
6. ፍቅርና ርህራሄን
ሌላው ጋብቻን ከሚያጠናክሩትና ውጤታማ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል አንዳችን ለሌላኛው የምናሳየው ፍቅርና ርህራሄ ነው፡፡ በንግግራችን ወቅት እባክሽን፣ አመሰግናለሁ ቢቻል ደግሞ ለብቻ የምንጠራባቸው ስም ቢኖረን ጥሩ ነው እንላለን፡፡ ሰዎች በኛ ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዳላቸው የሚገነዘቡት በምንለውና በምናደርገው ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡ ችግሩ አንዳንድ ጥንዶች ከተጋቡ በኋላ ይህን ነገር ይዘነጋሉ፡፡ አንዳንዴ ተሳስተው እንኳ ጉንጭ፣ ከንፈር አሊያም ግንባር ላይ ያልተጠበቁ/ድንገተኛ አሳሳም አድርገው አያውቁም፡፡
7. የቤት ውስጥ የልጆች አስተዳደግ ኃላፊነትን መጋራት
ሌላው በጣም ሚስቶች የሚሹትና ባሎች ሊረዷቸው ከሚፈልጓቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የቤት ውስጥ ኃላፊነትን መጋራት ላይ ነው፡፡ ሁለታችሁም ሰራተኞች እንደመሆናችሁ ቤት ስትገቡ ይደክማችኋል፡፡ ይህን ከግምት በማስገባት በቤት ውስጥ የስራ ክፍፍል ታደርጋላችሁን? ልጆችንስ በመንከባከብ በኩል ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ትተጋገዛላችሁን? ይህን ካላደረግን ሚስቶች ሊማረሩ፣ ወደፊት ልጅ ሁሉ ሲባል ላይስቡ ይችላሉ፡፡ ሁሉም የጋራ ፍሬዎቻችሁ እንደመሆናቸው በጋራ ልትንከባከቧቸው የግድ ይላል፡፡ እቤት ውስጥ የሚሰሩ ማናቸውንም ነገሮች እርሷ እስክትልህ ድረስ መጠበቅ የለብህም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፍትሃዊ የሆነ የስራ ክፍፍልን ማድረግ ይጠይቃል፡፡
እንግዲህ የሰው ልጅ ፍላጎት እንዲሁ በቀላሉ የሚገታ ባይሆንም አቅምህ በፈቀደ መጠን ከላይ የጠቀስናቸውን ምክሮች ተግባራዊ ብታደርግ፣ ጋብቻን የሚያፀናው አምላክም ሲፈርስ ማየት ስለማይሻ ይረዳሃል የሚል እምነት አለን፡፡ ሌላው ልታስታውስ የሚገባው… ባሎች ሚስቶቻቸውን እንደገዛ ስጋቸው መውደድ ይገባቸዋል፡፡ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፡፡ የገዛ ስጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው… የሚለውን ነው፡፡
ከላይ የዘረዘርናቸውን ነጥቦች ሚስቶችም ተግባራዊ ልታደርጉት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጎጂ የሚፀናው በሁለታችንም ጥረትና በእግዚአብሔር እርዳታ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ባሎችስ ከትዳራቸው/ሚስቶቻቸው ምን ይሻሉ? የሚለውን አጠር ባለ አገላለፅ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡
– ባሎች ያላቸውን ችሎታና ክህሎት ሚስቶቻቸው እንዲያምኗቸው ይፈልጋሉ፡፡ ይህን ደግሞ እንዲያውቁት በተለያየ መንገድ ግለፁላቸው፡፡ ላከናወኑትም ተግባር በተለያየ መንገድ አበረታቷቸው፡፡ ጀርባ መታ፣ ሳም፣ ባሌ እኮ ባትሆን… የመሳሰሉትን ነገር ማንሳት ተገቢ ይመስለናል፡፡
– ተጨባጭ የሆነ መረጃ ሳታዩ ባላችሁን አትጠርጥሩ፡፡ በሚያደርጉት ነገር እመኗቸው፤ የሞሳድና የሲ.አይ.ኤ ስራ ከመስራትም ይልቅ ልክ እንደዚህ አይነት ምክር የምታገኙበትን ተቋም መጎብኘት መልካም ነው እንላለን፡፡
– ባሎቻችሁን አንዳንዴ በማይፈልጉት አካሄድ ለመለወጥ አትሞክሩ፡፡ በቀላሉ መለወጥ የምትችሉት መጀመሪያ ራሳችሁን ነው፡፡ ባሎቻችሁ ላይ ስህተታችሁን ለመሸፈን አልቅሶ ማታለልና መቆጣት የሚፈጥረው ዘላቂና የተሻለ ነገር የለም፡፡
– ፍቅር የማይለውጠው ነገር የለምና ፍቅራችሁን ሳትሰስቱ ለግሷቸው፡፡ ያለ እናንተ ማን አላቸው ብላችሁ? ይህንንም በተለያየ መንገድ ማለትም በፅሑፍ፣ በመሳም፣ በማቀፍ፣ የተለያዩ ነገሮችን በመስጠት ግለጡላቸው፡፡
– ባሎች መከበርን ይሻሉና ተገቢው ክብር ስጧቸው፡፡ በሚያመጡት አሳብና ምክር ላይ አሉታዊ አስተያየት ለመስጠት አትቸኩሉ፡፡ ለዛሬ ይህንን ካልን የሚበቃ መሰለን፡፡ ጤና ይስጠን እንጂ ወደፊት በዚህ ርዕስ ላይ በሰፊው እናወጋለን የሚል እምነት አለን፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላካችሁ በትዳራችሁ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ጋበዙት፡፡ እርሱ የሌለበት ነገር በሙሉ ከንቱ ነው፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡