22 ማዞሪያ ቁጭ ብሎ ከውጭ የሚመለሱ ወገኖቹን የሚያጭደው ጉራሸትና የ6 ዲያስፖራዎች ገጠመኝ

March 8, 2014

ከዘድንግል ፈንታሁን

ወደ አገራቸው ተመልሰው ለመኖር ወይም ለመስራት በሚሞክሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተዘውትሮ የሚሰማው ቅሬታ፣ በስግብግብነትና በመካካድ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። በአሁኑ ወቅት የእናት ልጅም ቢሆን አይታመንም የሚለው ምክር-አዘል አስተያየት፣ የተጋነነ ላለመሆኑ የብዙ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ገጠመኞች ይመሰክራሉ። ከበርካታ ዓመታት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ወደ እናት ሃገራቸው ጠቅልለው የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ ቆርጠው ወደመጡበት የስደት አገር እንዲመለሱ ከሚያስገድዷቸው ሁኔታዎች አንዱ የስግብግብ ግለሰቦች የማጭበርበር ተግባር ነው። ባልጠረጠሩ የዋሃን የዳያስፖራ አባላት ላይ የማጭበርበር፣ የክህደትና የዝርፊያ ወንጀል የሚፈጽሙ በርካታ ስግብግብ ግለሰቦች ቢኖሩም ትኩረቴን ስለሳበው ስለ አንድ ዘራፊ ለመተረክ እወዳለሁ።

አቶ ጉራሸት ተክሉ ይባላል። ነዋሪነቱ በዚህ በአዲስ አበባ ሲሆን በደርግ ዘመን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ በአጎቱ እርዳታ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ። ደርግ ወድቆ ኢህአዲግ ስልጣን በያዘበት ወቅት ከሙስና ጋር በተያያዘ የእስራትና ከስራ የመባረር እጣ ደርሶት ነበር። ብዙ ሳይቆይ ከእስር ተፈትቶ ወደ ስራ ገበታው ተመለስ። ከወያኔ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ዝምድና እንዳለው በስራ ባልደረቦቹ ዘንድ ጎልቶ እንዲወራ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የስራ እድገት ለማግነት ቻለ። የመምሪያ ሃለፊም ሆነ። ከደሞዙ ጋር የማይጣጣም ሃብትም አፈራ። በዚህ ግለሰብ ዙሪያ፣ በተለይ የመስሪያ ቤቱን ንብረትና ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን በጨረታ በመሸጥ ሂደት ላይ ሃሜት መንሸራሸር ሲጀምርና የፌደራል የስነምግባርና የጸረሙስና ኮሚሽን መቋቋም ጭምጭምታ ተከትሎ ከመንግስት ስራው በራሱ ፈቃድ ተሰናብቶ የአንድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ባለቤት ሆነ። በመቀጠልም ከሌሎች ባለሃብቶች ጋር የሪል ስቴት ኩባኒያ ባለቤትና ቦርድ አባል ሆነ። እነዚህን ሁለት ድርጅቶች እንደ መሳሪያና ሽፋን በመጠቀም በዳያስፖራዎች ላይ አሳፋሪ የክህደትና የማጭበርበር ወንጀል መፈጸሙን ቀጠለበት። ይህ ሰው የመንግስት ስራውን ከለቀቀ ወዲህ ኑሮውን በስራ ሳይሆን በማጭበርበርና በማምታታት ብቻ ለመምራት የወሰነ ዘራፊ ኮን አርቲስት ሆነ።

አቶ ጉራሸት፣ በተለይ በኢንቨስትመንትና ከውጭ አገር ተሽከርካሪዎችን በማስገባት በኩል አገልግሎት እሰጣለሁ እያለ ከጀርመኒ፣ ከኖርዌይ፣ ከስዊድንና ከአሜሪካ የሚመጡ ጓደኞቹንና ዘመዶቹን በማሞኘት በሰው ላብ ለመክበር የሚያደርገው ሙከራ ብዙዎቹን ላልታሰበ እንግልት፣ ብስጭት፣ ሃዘንና ችጋር እንዲጋለጡ አድርጓል። አቶ ጉራሸት ሥራ ሰርቶ ምርታማ ከመሆን ይልቅ ዳያስፖራ ወገኖቹን እያሳደደ ዊስኪ መጨለጥንና ማጭበርበርን ስለመረጠ፣ ኑሮው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መጣ። በተለይም ዳያስፖራው በስደት ላቡን አንጠፍጥፎና ተዋርዶ ያመጣው የላብና የእንባ ገንዘብ ከመሸታ ቤት አልፎ የአቶ ጉራሸትን ህይወት ሊቀይር የሚያስችል በረከት ሊኖረው አልቻለም።

የአቶ ጉራሸት ሰላባ ከሆኑት ብዙ የዳያስፖራ አባላት ውስጥ የጥቂቶቹን እጣ-ፈንታ ለመጥቀስ እሞክራለሁ። ከሰለባዎቹ አንዱ አቶ ቻላቸው መለሰ ይባላሉ። የጀርመኑ አቶ ቻላቸውና አቶ ጉራሸት አዲስ አበባ በተገናኙበት ወቅት፣ አንድ በጣም አትራፊ የሆነ አዲስ የአክስዮን ማህበር እንደተቋቋመና ብዙዎች የአቶ ቻላቸው ጓደኞች አክስዮን እንደገዙ ይነግራቸዋል። ይህ መዝናኛ፣ ሎተሪና ቁማርን ያጠቃለለ ድርጅት፣ በአይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተመሰረተ መሆኑን፣ እንዲሁም አትራፊነቱ በዚያው ልክ በኢትዮጵያ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን ይተርክላቸዋል። ወዲያውኑ ጊዜ ሳያባክኑ ካልገዙ ይህ ወርቃማ እድል እንደሚያመልጣቸው በተለያዩ ዘዴዎች ሊያሳምናቸው ይሞክራል። ሙከራው ተሳክቶለት የአክስዮኑን ገንዘብ ራሱ ይቀበላል። ገንዘቡን በኪሱ ካስገባ በኋላ አቶ ጉራሸትን የበላ ጅብ አልጮህ ይላል። አቶ ቻላቸው መጠራጠር ይጀምራሉ። ከስንት ፍለጋ በኋላ አግኝተውት ጥያቄዎች ያቀርቡለታል።

«የድርጅቱ ጽ/ቤት አድራሻ የት ነው? ሊቀመንበሩና ጸሐፊው እነማን ናቸው? ኤቪደንዱስ የት አለ?» የፈጠራ ድርጅት እንደመሆኑ አቶ ጉራሸት ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ሊሰጥ አልቻለም። አቶ ቻላቸውም ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው ይጠይቃሉ። ገንዘባቸው ተመላሽ እንዲሆንላቸው ከፈለጉ ለድርጅቱ ማመልከቻ መጻፍ እንዳለባቸው በአቶ ጉራሸት ይነገራቸዋል። የማመልከቻው መልስ ይዘገያል። የዘገየበት ምክንያት የድርጅቱ መሪ ለስራ ጉዳይ ወደ መቀሌ ስለተጓዙ ነው ይባላል። ውሸቱ አዲስ ውሸትን እየወለደ አቶ ቻላቸው ክፉኛ ተጉላሉ። ገንዘባቸውን የሰጡት በቀጥታ ለአቶ ጉራሸት እንደመሆኑ አቶ ጉራሸት እንዲሰጣቸው በጓደኞቻቸው ፊት ይጠይቃሉ። በዚህ ወቅት አቶ ጉራሸት ለማይረባ 120,000 ብር ስሜ ተነሳ በማለት በውሸት ቁጣ ቱግ ይላል። አቶ ቻላቸውን መዝለፍና ስብእናቸውን ማዋረድ ይጀምራል። ይህ ሰው የሰውን ንብረት ወስዶ ለመሸሽ ሲፈልግ ወደ ግጭትና ጠብ መሮጥ አመሉ ነው። ተበዳይ ለመምሰል በላይ ሆኖ በእምነት አጉዳይነት ተውነጀልኩ በማለት ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ልማዱ ነው። የአቶ ቻላቸውን ገንዘብ ለማስቀረት ተግባራዊ ያደረገውም ይህንኑ የቅጥፈት ዘዴውን ነው። ገላጋዮች ሁኔታውን ለማብረድ ሲሞክሩ፣ በግርግሩ ወቅት ተበዳይ አካል በመምሰል አቶ ጉራሸት ሹልክ ብሎ ይጠፋል። አቶ ቻላቸውም ገንዘባቸውን ተዘርፈው ቀሩ። «አሁን እኔን ግርም የሚለኝ» ይላሉ አቶ ቻላቸው፣ «መዘረፌ ሳይሆን ከድርጊቱ በኋላ በአንድ ግብዣ ላይ ተገናኝተን ማእድ ቀርቦልን፣ ይህ አይን-አውጣ ስውየ በመካከላችን ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በመቁጠር፣ ቁርጥ ይሻልሃል ክትፎ እያለ በእጁ ሊያጎርሰኝ መከጀሉ ነው።» ይህ የሚያሳየው አቶ ጉራሸት ስለ ሰው ስሜት መጎዳት ደንታ የሌለው ደረቅ ሌባ ዘራፊ መሆኑን ነው።

ሁለተኛው ሰለባ የስዊድኑ አቶ አያልነህ አብርሃ ናቸው። አቶ አያልነህ አንድ ካት የተሰኘ ካተርፒላር ኤክስካቬተር አስመጥተው ማከራየት ይጀምራሉ። ወደ ስዊድን ሲመለሱ ኪራዩን በየወሩ እየተቀበለ እንዲያቆይላቸው አቶ ጉራሸት በተለመደው ጮሌነቱ ያግባባቸዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ ባለንብረቱ ሂሳባቸውን ይጠይቃሉ። አቶ ጉራሸት ገንዘብ አላየሁም ብሎ ይክዳል። ኪራዩን እየሰበሰቡ በየውሩ ለአቶ ጉራሸት እያስፈረሙ ሲያስረክቡ የነበሩት አቶ ንጉሴ ማስረጃ ሰነዳቸውን ይዘው ይቀርባሉ። ገንዘቡ በቦታው የለም። ዊስኪ ሲራጭበት ባጅቶ ከርሟል፣ አቶ ጉራሸት። ከመጠጥ ብዛት ጋር በተያያዘ የተደረገው የጉበት-ሐሞት ቀዶ-ጥገና ወጭ የተሸፈነውም በዚሁ ገንዘብ ነበር። አቶ ንጉሴና አቶ አያልነህ ከረር ያለ እርምጃ ለመውሰድ ቆርጠው ይነሳሉ። አቶ አያልነህ የዋዛ ሰው እንዳልሆኑ ሁሉም ያውቃል። ቤተዘመድ ሁሉ በጭንቀት ይዋጣል። በተከበሩ አዛውንት በአቶ አባተ ጣልቃ-ገብነት የሰው ህይወት ከመጥፋት በፊት፣ አቶ አያልነህ ተዘርፈው እንባቸውን እየጠረጉ፣ ዘራፊውም የዘረፈውን ዘርፎ፣ በለስ ሲቀናው በዘልማድ የሚያፏጫትን ዜማ እያሰማ በየፊናቸው ሄዱ። አቶ አያልነህ ስሜታቸው በእጅጉ ቢጎዳም ኢኮኖሚያቸው በዚህ አልተነካም።

ሶስተኛው ሰለባ የጀርመኒው አቶ ቢትወደድ ናቸው። አቶ ጉራሸት በተለመደው ቅጥፈቱ የአቶ ቢትወደድን አመኔታ ያገኛል። እሳቸውም ጠቅሞ-መጠቀም በሚል ቅን አስተሳሰብ በአቶ ጉራሸት አስመጭ ድርጅት በኩል የሚሸጡ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ፣ ከዚህ የሚገኘውን ትርፍ እኩል ለሁለት እንዲካፈሉ፣ አስፈላጊውን ካፒታል ሁሉ አቶ ቢትወደድ ሊሸፍኑ እንደሚችሉ፣ ስምምነት ላይ ይደረሳል። አቶ ቢትወደድ አምስት መኪናዎች ከጀርመን አገር ይልካሉ። አቶ ጉራሸት በጠየቀው መሰረትም ለጊዜው ስራ ማስፈጸሚያ የሚሆን 340,000 ብር በአቶ ጉራሸት ኩባንያ ባንክ ሂሳብ ይላካል። ድርጅቱ የባንክ እዳ ስለነበረበት ባንኩ ገንዘቡን ውጦ ያስቀረዋል። ባለንብረቱ ይህን ሲሰሙ መኪናዎቹም በተመሳሳይ የተንኮል ስራ ተበልተው እንዳይቀሩ ስጋት ያድርባቸዋል። ባንኩ የወሰደውን ገንዘብ እንደጠፋ በመቁጠር መኪናዎቹን ከበይ ለማዳን ሲሉ አቶ ጉራሸትን በዘዴና በጥንቃቄ በመያዝ አግባብ ካላቸው አካላት ጋር ራሳቸው እየተገናኙ ጉዳዩን እንዲያስፈጽሙ ከአቶ ጉራሸት ውክልና ያገኛሉ። ከጅቡቲ ጀምሮ ያለውን ሂደት እየተከታተሉ ንብረታቸውን በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ቀሪ ገንዘባቸውን ለማግኘት ወደ አቶ ጉራሸት ሽማግሌ ለመላክ ይወስናሉ። አቶ ጉራሸት ጉዳዩ ወደ ሽምግልና ማምራቱን ሲያውቅ፣ በጎን አቶ ቢትወደደን ያስፈራራል። በሚያውቃቸው ደህንነቶችና ከፍተኛ የወያኔ ባለስልጣናት አማካኝነት በፖለቲካ ወንጅሎ ለማሳሰር እንደሚችል ያስጠነቅቃቸዋል። በዚህ ምክንያት በሽምግልናው ቀን ሽማግሌ ጠሪው ራሳቸው አቶ ቢትወደድ ሳይገኙ ይቀራሉ። ከዚያ ወዲህ አቶ ቢትወደድ ብዙ ጊዜ ወደ ኢትዮጲያ ሲመላለሱ አቶ ጉራሸት የሚያዘወትረውን የ22 ማዞሪያ አካባቢ ረግጠው አያውቁም ይባላል።

አራተኛው ሰለባ አቶ መንገሻ አብርሃ ይባላሉ። አቶ ጉራሸት አቶ መንገሻን ወደ ወጥመዱ ያስገባቸው በሪል ስቴት ኩባንያ በኩል በዝቅተኛ ዋጋ ቤት አስገንብቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያስረክባቸው በማባበል ነበር። እሳቸውም በእቅዱ ተስማምተው አቶ ጉራሸት የጠየቃቸውን መቶ ሺህ ብር የቅድሚያ ክፍያ ከፍለው ወደ መኖሪያ አገራቸው ወደ ፍራንክፈርት ይመለሳሉ። በዚህ መካከል የአቶ ጉራሸት ልጅ የውጭ ትምህርት እድል ያገኛል። አሜሪካን አገር ትምህርቱን ለመከታተል የመጀመሪያ ዓመቱን ሁለት መቶ ሺህ ብር ክፍያ አስቀድሞ መጠናቀቅ ነበረበት። ብሩ ከየት ይምጣ? መፍትሄው የቤት ግንባታውን አመካኝቶ 200,000 ብር በአስቸኳይ እንዲልኩ አቶ መንገሻን ማጣደፍ ነበር። ገንዘቡ ቶሎ ካልተላከ በዝቅተኛ ዋጋ ሊያሰሩ የገቡት ውል እንደሚፈርስና የሰጡት የቅድሚያ ክፍያ እንደማይመለስላቸው በተለያዩ ሰዎችና ዘዴዎች ለአቶ መንገሻ መልእክት ይደርሳል። ውትወታው ሲበዛባቸው ጥሬ
ገንዘብ ተሸክመው ወደ ኢትዮጵያ ከመግባት እግረ-መንገዳቸውን የሚሸጡ መኪናዎች ይዘው መሄድን ይመርጣሉ።

በጥድፊያው ምክንያት፣ በጊዜው በኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው የመኪና ገበያና የግብር አከፋፈል ላይ በቂ ጥናት ለማካሄድ ባለመቻላቸው ከመኪናዎቹ አንዷ ኢትዮጵያ ውስጥ የማትፈለግና ቀረጧ 420,000 ብር የሚደርስ ሆኖ ተገኘ። መኪናዋም የመመለሻዋ ወጭ በተጨማሪ ተከፍሎባት ተመልሳ ወደ ጂቡቲ አቀናች። በመሆኑም አቶ መንገሻ ላልተጠበቀ ወጭ ተጋለጡ። በአቶ ጉራሸት ስግብግብነት ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራ ደረሰባቸው። አምስተኛው ሰለባ የስዊድኑ አቶ ሃብተማሪያም ጴጥሮስ ናቸው። አቶ ጉራሸት ከትውልድ ቦታው የሚመጡትን ዳያስፖራዎች አየር ማረፊያ ድረስ ሄዶ መቀበል የዘወትር ልማዱ ነው። አቶ ሃብተማሪያም ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ አቶ ጉራሸት ቦሌ አየር ማረፊያ ድረስ ሄዶ ይቀበላቸዋል። ከቤቱ አድረው የማያውቁ ቢሆንም፣ ያለወትሮው ቤቱ እንዲያርፉ ያግባባቸዋል። አራት ሻንጣዎቻቸውን እንደያዙ አያት ወደሚገኘው ቤቱ አብረውት ይሄዳሉ። በአንዱ ሻንጣ ውስጥ
አድርሱልኝ ተብለው የያዟቸውና ለስጦታ የገዟቸው ጠቅላላ ዋጋቸው ወደ 330,000 የሚደርስ ውድ የእጅ ፖርሳዎች፣ ሞባይሎች፣ ሽቶዎች፣ የእጅ ስዓቶች፣ ቅባቶች፣ ልዩ-ልዩ ጌጣጌጦች፣ የተለያዩ የሙሽራና የሚዜ ልብሶች ነበሩበት። ሲመሽ፣ የሻንጣ ቁልፎቹን ከኮታቸው ኪስ አስቀምጠው ይተኛሉ። ጧት ካደሩበት ክፍል ሲነሱ ላፕቶፑ የለም። እቃዎቹን ለማድረስ ሻንጣቸውን ሲከፍቱ ከላይ የተጠቀሱት እቃዎች በሙሉ ተወስደዋል። አቶ ሃብተማሪያም አቶ ጉራሸትን ከመኝታው ጠርተው ሁኔታውን ሲገልጹለት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ላይ ለማሳበብ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ መደወል ይጀምራል። አቶ ሃብተማሪያም ከመተኛታቸው በፊት ሻንጣውን ከፍተው እቃዎቹን አይተው እንደነበር፣ አየር ማረፊያ ላይ ቢሰረቁ ኖሮ ቁልፉ ይሰበር ነበር እንጂ ሻንጣው እንደተቆለፈ እንደማይገኝ፣ ንብረቱ የጠፋው በእርግጠኝነት ከአቶ ጉራሸት ቤት መሆኑን አስረግጠው ይነግሩታል። በአየር መንገድ ሰራተኞች የማሳበቡ ሙከራ ሲከሽፍበት በትልቁ ልጁ ያሳብባል። በአቶ መንገሻ ኪሳራ ወደ አመሪካ ሄዶ የተመለሰው መከረኛው ልጅ እቃዎቹን ሰርቆ ወስዶ ለተለያዩ ሱቆች እንደሸጣቸው የደረሰበት መሆኑን አቶ ጉራሸት ራሱ በልጁ ላይ በውሸት ይመሰክራል። በተጨማሪም ከተሸጡበት ሱቆች እንደገና በራሱ ገንዘብ ገዝቶ እንደሚተካ ቃል ይገባል። አቶ ሃብተማሪያም በዚህ በጣም ያዝናሉ። ከማዘናቸውም የተነሳ ነገሩን ቸላ ብለው ይተውታል። ያሳዘናቸውም በአደራ እንዲያደርሱ ያመጧቸው እቃዎችና ልብሶች መሰረቅ ሳይሆን፣ በቤተሰቡና በህብረተሰቡ ተከብሮ ሲኖር የነበረው በእድሜ የሚበልጣቸው የራሳቸው የአክስት ልጅ በተራ ስርቆትና ዘረፋ ላይ ተሰማርቶ መገኘቱ ነው።

ስድስተኛውና በቅርቡ የአቶ ጉራሸት ሰላባ የሆኑት አቶ ሃይሉ የሺወንድም ናቸው። አቶ ሃይሉ በስደት ላይ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠሩ ትልቅ ሰው ናቸው። በእድሜ የገፉ እናታቸውን በቅርበት እየተመላለሱ ለመጦር ውጭ አገር ከሚኖሩ ወንድሞቻቸው ጋር ተመካክረው ከኖርዌይ ወደ አገራቸው ለመመለስ ይወስናሉ። የአቶ ጉራሸትን መዋእለ-ክህደት ያላጤኑት አቶ ሃይሉ፣ ገና ከኖርዌይ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ለስራም ለእግራቸውም የምትሆን መኪና በአቶ ጉራሸት አስመጭ ድርጅት በኩል ለመላክ ያቅዳሉ። መኪናዋን ከመላካቸው በፊት የዶላር ወረፋ ላለመጠበቅ 8000 የአሜሪካ ብር እንዲልኩለት አቶ ሃይሉን ይጠይቃል። ያልጠረጠሩና በባንኮች ዘንድ የዚህ ዓይነት አሰራር ፈጽሞ እንደሌለ ገና ያላረጋገጡት አቶ ሃይሉ የተጠየቀውን ገንዘብ ወዲያው ይልካሉ። መኪናዋን ካስጫኑ በኋላ ገና አዲስ አበባ ከመግባታቸው አቶ ጉራሸት ለመኪናዋ ግብር 160,000 ብር ዲፖዚት በባንኬ አስገባ ይላቸዋል። እንደተባሉትም ያደርጋሉ። «መኪናዋ በማን አስመጭነት እንደምትመጣ የነገርኳቸው የቅርብ ጓደኞቸ» ይላሉ አቶ ሃይሉ «ራሳቸው ደንግጠው እኔንም አስደንግጠውኛል። ሁሉም በአንድ ድምጽ ዳያስፖራን በየተራ ሲያስለቅስ የኖረ ጨካኝ የቀን ጅብ መሆኑን ነበር የነገሩኝ» በማለት በቁጭት ያብራራሉ።
አቶ ጉራሸት አቶ ሃይሉን ሳያማክር በሞጆ በኩል እንድትደርስ የላኳትን መኪና ከጅቡቲ ሊረከባት በራሱ መብት ሰነዶችን ይቀይራል። ሳምንታት አልፈው ሳምንታት፣ ወራት አልፈው ወራት፣ ሲተኩ መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም – የመኪናዋ ደብዛ ፈጽሞ ይጠፋል። አብረው ባንድ ላይ ከኖርዌይ የተጫኑ መኪናዎች ሁሉ አዲስ አበባ ከደረሱ ወራት አልፏቸዋል። አቶ ጉራሸት ለመኪናዋ መዘግየት የሚያቀርባቸው ሰንካላ ምክንያቶች እንኳንስ ምሁሩን አቶ ሃይሉ ህጻንን ማሞኘት የማይችሉ ነበሩ። አንዴ ተጭና ስታበቃ ኦሪጂናል ሰነዶች ስለጠፉ ከተጫነችበት አወረዷት ይላል፣ አንዴ ደግሞ የጫነቻት ትልቅ የጭነት መኪና ከጅቡቲ አምስት መቶ ኪሎሜትር ርቀት ስትደርስ ተሰብራ የመለዋወጫ እቃ ልንወስድላት ነው ይላል። ይህ ሁሉ ምክንያት ጊዜ ለመግደል ነበር። ለምን ጊዜ መግደል? ምክንያቱም አቶ ጉራሸት በሌለው አቅም አንድ ቤት ለመስራት ከቤት ግንባታ አክስዮን ማህበር ጋር ውል ገብቷል። በውሉ መሰረት በየደረጃው የሚከፈለውን ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ባለመቻሉ ከኮንትራቱ ሊባረር ስለሆነ ለመኪናዋ የተመደበውን ገንዘብ ለዚሁ ጉዳይ አውሎታል። ለአቶ ጉራሸት ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች እንደሚሉት፣ አሁንም አቶ ጉራሸት ለቤቱ ግንባታ በየወቅቱ መክፈል ስላልቻለ የእሱ ኮንትራት ተሰርዞ በምትኩ ሌላ ባለ ሃብት የመተካቱ እድል በራሱ ላይ እያንዣበበ ይገኛል።

ከብዙ ወራት በኋላ መኪናዋ ክፉኛ ተበላሽታ፣ ውጫዊና ውስጣዊ ብልሽቶች ደርሰውባት አዲስ አበባ ደረሰች። ኢንሹራንሱ የተከፈለው በአቶ ሃይሉ ቢሆንም፣ ይህን ሁሉ ጉድለት ለመሸፈን የተሰጠው ካሳ ወደ ኪሳቸው ያስገቡት ትራንዚተሩና አቶ ጉራሸት ናቸው። መኪናይቱ ከደረሰች በኋላም አቶ ጉራሸት ተጓዳኝ ሰነዶችን ለማውጣት የሚያስፈልገውን ወጭ ቀደም ሲል በባንኩ ገቢ በሆነለት ሂሳብ ለመሸፈን አልቻለም። ምክንያቱም ገንዘቡን ለቤቱ ስራ አውሎታልና። ስለዚህ አቶ ሃይሉ ለትራንዚት፣ ጂቡቲ አራት ወር ለቆየችበት፣ ለቫት፣ ለገቢ ግብር፣ ለመኪና መለዋወጫና ለስም ማዛወሪያ፣ ከዚያ በፊት ለዘራፊው ከሰጡት ገንዘብ እጥፍ ወጭ አድርገው መኪናቸውን በእጃቸው ማስገባት ችለዋል። «መኪናዬን ከዚህ ጅብ መንጋጋ ለማላቀቅ አስር ሰንጋ ማጉረስ ነበረብኝ። ይህን እርምጃ ለመውሰድ ያበቃኝ የኔን ጥቃት የማይወደው ጓደናዬ የአቶ መሳፍንት ፈረደ ምክር ነው።» ይላሉ አቶ ሃይሉ።

በመጨረሻም አቶ ሃይሉ የተዘረፉት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ያደረጉት ሰላማዊ ሙከራ ሊሳካ አልቻለም። ይልቁንስ የዘራፊው ጥረት በአቶ ቻላቸው ላይ እንዳደረገው ሁሉ፣ ከአቶ ሃይሉ ጋር ግጭት በመፍጠር ሁኔታው በጠብ እንዲደመደም ማድረግ ነበር። ዘራፊው ጉራሸት የሰውን ገንዘብ ለመብላት ሲፈልግ እንደ ህጻን ልጅ «ጨዋታ ፍርስርስ ዳቦ ቁርስርስ» በማለት ራሱ ጠብ ጭሮ በሌሎች ማሳበብ የተለመደ የማጭበርበር ዘይቤው ስለሆነ፣ የተገላብጦሽ ራሱ ከሳሽ ወቃሽ ሆኖ ለመታየት በአቶ ሃይሉ ላይ ጥላሸት የመቀባቱን አባዜ ተያይዞታል። ይባስ ብሎ፣ ገንዘባቸውን ለማግኘት ከፈለጉ በራሱ በዘራፊው ንግድ ድርጅት በኩል ማመልከቻ ማስገባት አለባቸው እያለ ትእቢት የተሞላበት ፌዛዊ አነጋገሩን ቀጥሎበታል።

አሁንስ ማነው ባለተራ? እስከ አሁን ድረስ ከጓደኞቹ ጀምሮ ዘመዶቹንና የአክስቱን ልጆች እየበላ ቆይቷል። ቀጣዮቹ ተረኞች ውጭ አገር የሚገኙ ወንድምና እህቶቹ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም። ስለዚህ እያያን ጠንቀቅቅቅቅቅቅ!!!!

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት፣ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት፣ እውቀታቸውን በማካፈል፣ ቴክኖሎጂን በማሸጋገር፣ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ራሳቸውንና ሃገራቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። በግለሰብ ደረጃ የሚደርስባቸው የማጭበርበር፣ የማታለልና የዘረፋ ወንጀል፣ ድርሻቸውን ከማበርከት የሚያደናቅፍ ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ ነው። የአቶ ጉራሸት ዓይነቱ ወንጀል በ22 ማዞሪያ አካባቢ ብቻ ተወስኖ የሚገኝ ሳይሆን፣ በሃገር ደረጃ ጭምር ዳያስፖራው እየተማረረ ያለበት ችግር ነው። ስለዚህ አቶ ጉራሸትንና መሰሎቻቸውን እየተከታተሉ ማጋለጥና ለህግ ማቅረብ የሁሉም የዜግነት ግዴታ ነው።

Latest from Blog

ነገሩ እንዲህ ነው ባሳለፍነው ታህሳስ 15 በተካሄደው ብልጽግና ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አረጋ ከበደ እጃቸውን አውጥተው ተናገሩ እኔ አቅቶኛል የአማራ ክልል ቀውስ ማስተዳደር አልቻልኩም ብለው ተናገሩ በዚህ ጊዜ

“አንተን ለማኝ አደርጋለሁ” አቢይ አሕመድ ለአማራ ክልል ፕረዚዳንት ለአረጋ ከበደ የሰጠው ማስጠንቀቂያ

January 31, 2025
ከቴዎድሮስ ሃይሌ የምናከብራቸው ጀነራል ተፈራ ማሞ ሰሞኑን አደባባይ ወጥተው አድምጠናል:: የጀነራሉ ጤንነትና ደህንነት ሲያሳስበን ለቆየነው ወገኖች ሁሉ በጥሩ ቁመና ላይ ሆነው በማግኘታችን የሕሊና እረፍት ሰጥቶናል:: አሁንም ባሉበት ሰላሞት እንዲበዛ ምኞታችን ዳር የለውም::

እስክንድር ነጋ እና ጀነራል ተፈራ ማሞ ከድል ለዲሞክራሲ እስከ ፉኖ ተሰማራ!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) ዛሬም እንደ ትናንቱ አያሌ ምሁራንና ታዋቂ ነን ባይዎች ስለብሔራዊ ሽምግልና እርቅ ይደሰኩራሉ፡፡ ያለምንም ሐፍረት ቅዱሱን ሽምግልናን ከምእራብ ከተሸመተው ኤፍሬም ይሳቃዊ ድርድር ጋር እያምታቱ የአያት የቅድመ አያቶቻችንን የተባረክ የሽምግልና ሐብት ያበላሻሉ፡፡ ሽምግልና በመለኮት

ፍትህ የሌለው ሽምግልናና እርቅ ሥራ እንደሌለው እምነት የሞተ ነው!

Go toTop

Don't Miss

193265

TEDDY AFRO – ሰዉየዉ (ኅብረ ዝማሬ) | sewuyew – እናንዬ (ኅብረ ዝማሬ) | enanye [New! Official Single 2024] – With Lyrics

TEDDY AFRO – ሰዉየዉ (ኅብረ ዝማሬ) | sewuyew – እናንዬ

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ108 ሚሊዮን በላይ ደረሠ

(ዘ-ሐበሻ) በአለም ባንክና መሠል አለም አቀፍ ተቋማት በዚህ ሳምንት ይፋ