February 26, 2018
71 mins read

ከመሠረታዊ  ዴሞክራሲያዊ   የሥርዓት ለውጥ ውጭ ሌላ መውጫ መንገድ የለም!

February 25, 2018

ጠገናው ጎሹ

ሰሞኑን በአገራችን የሆነውና እየሆነ ያለው ፖለቲካዊ  እውነታ ሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቅንበት  እጅግ ፈታኝ (  ወፌ ቆመች ሲባል መላልሶ የመውደቅ ) የትግል አካሄድ  በመጠንም ይሁን በይዘት ወደ ላቀና ጨርሶ ወደ ኋላ በማይመለስበት ደረጃ መሸጋገሩን ብዙ ማብራሪያ ሳያስፈልገው ራሱን ግልፅና ግልፅ አድርጎ እያሳየን ስለመሆኑ ለመረዳት ብዙ የሚያከራክረን አይመስለኝም ። እኛው ራሳችን መልሰን ካላበላሸነው በስተቀር በረጅሙ የፖለቲካ ታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እምንመሠርተው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማህበረሰብ ከሚያሸጋግረን ድልድይ የመጨረሻ ጫፍ ላይ የምንገኝ  ስለመሆናችን ጥንቃቄ በተሞላበት  ርግጠኝነት  መናገር እንችላለን ብየ አምናለሁ ።

ይህን የትግል ምዕራፍ በስኬት የማጠናቀቁ ሥራ ከመቸውም በላይ በአብሮነት፣ በፅእኑ ቁርጠኝነትና አስፈላጊውን መስዋትነትም ለመክፈል ዝግጁ ሆኖ በመገኘት ላይ የሚወሰን መሆኑን ከልብ አመኖና ተቀብሎ  መራመድን የግድ ይላል። ያለዚያ ግን የድል ዋዜማ አምባ ላይ የወጣውን   ህዝባዊ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ አምባገነኑ ገዥ ቡድን የለመደውን የጭካኔ በትሩንና የማዘናጊያ ፖለቲካዊና ስነ ልቦናዊ ተውኔቱን እያቀላቀለ በመጠቀም ከአምባው ላይ በማውረድ በመሬት ላይ እንደሚጎትተው ግልፅ መሆን አለበት ። ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የመጣንበት ተሞክሮ ይህ ሊሆን የሚችል ስለመሆኑ መሪር ትምህርት ሆኖን በአስተሳሰብም ሆነ በተግባር ልቀን ካልተገኘን የሩብ ምዕተ ዓመቱ  መከራና ውርደት ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት የማይራዘምበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም።

ህወሃቶች/ኢህአዴጎች የአገርና የወገን መከራና ውርደት አብቅቶ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ እኩልነት፣ የጋራ ብልፅግና እና ዘላቂ ሰላም በሰፈነባት አገር እንኑር ብለው የዜግነታቸውን ድርሻ ለመወጣት ከመንቀሳቀስ ውጭ ሌላ ጥፋት የሌለባቸውን ዜጎች በህዝብ የተቃውሞ ማእበል አስገዳጅነት ከየጠባብ እስር ቤቱ ከለቀቁ ገና ቀናት ሳይቆጠሩ የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጅ (መንግሥታዊ የሽብር አዋጅ) በማወጅ የያንዳዱን ዜጋ ቤት እስር ቤት አድርገው የአፈና እና የዘረፋ መንበረ ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል የሚያደርጉት መወራጨት የሚያስከትለው የጥፋት አስከፊነትን መገመት አያስቸግርም ።  ይህን የእንተላለቅ የፖለቲካ እብደት በጥሞና ለሚታዘብ ሰው ገዥዎቻችን እየረገጡና እየገደሉ በመግዛት ጭራቃዊ ራስ ወዳድነት ህሊናቸው ጨርሶ ስለታወረ የህዝብን በቃኝ ባይነትን ቆም ብለው ለማየት የሚችሉ ሆነው አልተገኙም ።

ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ህዝብን የማዘናጊያ (የማታለያ) ፖለቲካዊ ተውኔታቸውን በህወሃት ዋና አዘጋጅነትና ዳይሬክተርነት ሃያ አራት ሰአት በመተወን ላይ ይገኛሉ ። የትወናው ትረካ ማጠንጠኛውም “ጥልቅ ተሃድሶ  ” የሚል ተረት ተረት ሲሆን የሚጀምረውም የዕለት ኑሯቸውን ለማሸነፍ የማይችሉ ሚሊየኖች ባሉባትና ከደሃም ደሃ በሆነች አገር  ለወራትና ለሳምንታት በተካሄዱና  ገንዘብ ፣ የሰው ኀይል፣ ጊዜና በአጠቃላይ የአገር አንጡራ ሃብት (resource) በባከነባቸው  የሴራ ጉባኤዎች/ስብሰባዎች ማሟሟቂያነት ነው ። የተውኔቶቹን ስኬታማነት ሪፖርቶችና መግለጫዎችን በጥሞና ለሚያነብ (ለሚሰማ) እና የሩብ ምዕተ ዓመቱን የፖለቲካ መሪር እውነታ ከምር ለተከታተለ የአገሬ ሰው እነዚህ ገዥዎቻችን የህዝብን የማሰብና የማገናዘብ እቅም(ችሎታ)ምን ያህል ከደመነፍስ እንስሳ ጋር አውርደው እንደገመቱት ለመረዳት የሚቸገር አይመስለኝም ።ለነገሩ በእነሱ ብቻ የመፍረዱ ነገር በራሱ የእኛን ጥንካሬና ስኬታማነት ጨርሶ አያመለክትም የዚህ ሴረኛና መሰሪ የገዥዎች የሥልጣን አድን ተውኔት አጀንዳ ሰለባ የሆነውንና በተለይም ተማርኩ የሚለውን የአገሬን ሰው ቁጥር ቤቱ ይቁጠረው ገዥዎችን ደንቆሮ እያሉ የድንቁርናቸው ተውኔት ታዳሚ ከመሆን የባሰ ድንቁርና የሚኖር አይመስለኝም

ህወሃት እረፍት እየወሰደና የሦስቱን ቀጥተኛ ሎሌዎቹን (ፈጥሮ ያሳደጋቸውን የግንባሩ አባል ድርጅቶች ) የልብ ትርታና ዝንባሌ እየለካ  የሴራ ስብሰባውን ካካሄደ በኋላ  በኢህአዴግ ስም በዝግ አዳራሽ ሰብስቦ ከወደቅን ተያያዘን ስለምንወድቅ ሁላችንም  ከዚህ የሚታደጉን ስልቶች የሚከተሉት ናቸውና ተመካክረን ለህዝብ የምሥራች እንበለው በማለት ያቀረባቸውና እየተተገበሩ ያሉ  እጅግ መሰሪ ስልቶች :) ህዝብና ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የሚጮኸውን ጬኸት ለማስታገስና ሊያስከትል የሚችለውን የሥልጣን ማጣት አደጋ ለማስቀረት  የፖለቲካ እስረኞችን ጨምሮ ቁጥሩ የማይናቅ እስረኛ መፍታት  ) የተሃድሶውን ተውኔት ከራሱ ከህወሃት  ጀምሮ በእያንዳንዱ ታዛዥ የግንባሩ  አባል  ድርጅት ውስጥ በመተወንና ቤተ መንግሥት (ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበር) ድረስ በመዝለቅ  የተነሳውን የህዝብ የለውጥ ማዕበል ፍጥነቱንና ስፋቱን እንዲቀንስ ለማድረግና ቀስ በቀስም ተውኔቱን አጠናክሮ በመቀጠል ማዕበሉን ማስቆም በሚቻልበት አጀንዳ ላይ መክሮ ተግባራዊ ማድረግ  ሐ) ) አብዮታዊ ዴሞክራሲ ያመጣው ነፃነትና እድገት/ብልፅግና ዓለምን ሳይቀር ያስደመመ ስለመሆኑ እና  መልካም አስተዳደርን የበለጠ ለማጠናከር በሚደረግ ሂደት ውስጥ ግን የተመዘገበውን አንፀባራኪ ድል ፈተና ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ያጋጠሙ በመሆኑ ዙሪያ ተመካክሮ ስለጥልቅ ተሃድሶው ግንዛቤ የሚጎለውን” ህዝብ ማስተማርና ማጥመቅ መ)ለተፈጠረው ቀውስ ( እነሱ ቀውስ አይሉትም ) ኅላፊነትን መውሰድና  ስለመበስበስም  ህዝብን ይቅርታ ጠይቆ አድናቆትን ማግኘት       ሐ) የመበስበሱ ጉዳይ በጥልቅ ተሃድሶ እንደሚቀረፍ  ለህዝቦች ፣ ብሔሮችና ብሔረ ሰቦች ማብሰር  (በነገራችን ላይ ይኸ የመበስበስና የመታደስ መዝሙር አሁን በህይወት የሌለው ታላቁ መሪያቸው አቶ መለስ ዜናዊ መንበረ ሥልጣኑን የሚያሰጋ ነገር በተሰማው ቁጥር ይዘመረው የነበረ መዝሙር ነው ይህም ለጋሲ ሆኖባቸው ነው መሰል አሁንም መዝሙረ መበስበስና መታደስ አድርገው ይዘምሩታል) በተፈጠረው ህዝባዊ አመፅ ( እነሱ ሁከት ይሉታል) በንቃት የተሳተፉትን  (ልብ በሉ የገደሉትንና በጅምላ ሰቆቃ የፈፀሙትን ጨካኝ  ኀይሎቻቸውን  ጨርሶ አይጠቅሱም ) ለህግ አቅርቦ አይቀጡ ቅጣት ማስቀጣት   (መቅጣት) እና  ረ) አፈናውን አጠናክሮ መቀጠል  (እነሆ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ / መንግሥታዊ የሽብር አዋጁ እውን ሆኗል ። )

ወደ ግራም እንውሰደው ወደ ቀኝ ፣ ወደ ላይም እናዉጣው ወደ ታች እናውርደው ፣ ይዋጥልንም ወይም ያስመልሰን በመሬት ላይ ያለውና ተዘርግቶ ፀሐይ የሚሞቀው የገዥዎቻችን አደገኛ የቅዠት ፖለቲካዊ ድርሰታቸው (እየበሰበሱ ታደስን የሚሉት ትራጀዲያቸው) ይኸው ነው ።  የኦህዴድም ይሁን የብአዴን እና የደህዴን  ባለሥልጣናትና ካድሬዎች የፖለቲካ ሰብእናቸው ፈጣሪ ከሆነውና በግንባር (ኢህአዴግ) ስም ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ በደም የቆሸሸውን የፖለቲካ አጀንዳውን አስፈፃሚ ካደረጋቸው የትግራይ ነፃ አውጭ ፈልቀቀው ለመውጣት ከአሁኑ የተሻለ እድል ወይም አጋጣሚ የላቸምም ።   ወኔው ከድቷቸው  ወይም በአድር ባይነት ክፉ አባዜ ተጠርንፈው የአፈና መሳሪያንና የማታለያ (ማዘናጊያ) ፖለቲካዊ ተውኔትን እያቀላቀለ ከሚነጉደው መንኮራኩር ወርደው ወደ ህዝብ የነፃነትና ፍትህ መርከብ እስከ አልተቀላቀሉ ድረስ አልፎ አልፎ በየአጋጣሚው የሚያሰሙት  ህዝባዊ የሚመስል ዲስኩራቸው (populist rhetoric) የትም የሚያደርስ አይደለም ። አይሆንምም።   ይባስ ተብሎ ደግሞ በዚህ ሰሞን የጠቅላይ ሚኒስተርነቱ ወንበር “ለድርጅታችንና ለእኛ ሰዎች  ቢሰጥ ተሃድሶውን ለማሳካት ተአምር እንሠራበታለን የሚል የተውኔቱን የሴራ ጡዘት ከፍ የሚያደርግ ሁኔታ እየታዘበን ነው። በእጅጉ የሚሳስበው ግን የዚህ ድንቅ ፖለቲካዊ ተውኔት ሰለባዎች ለመሆን የሚከጅለን ብዙ የመሆናችን ጉዳይ ነው ። ከልብም ልብ ይስጠን!

ይህ የሰሞኑ የትግል እመርታ በፍፁም መባከን የሌለበት  ወርቃማ የድል ዋዜማ መሆኑን በሚከተሉት  እውነታዎች ማሳየት ይቻላል

  1. ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ እና በተለይ ደግሞ ከ1997ቱ የህዝብ ድምፅ ቅሚያ (ንጥቂያ) በኋላ ውድ ልጆቹን እያስገደለና ወደ ማሰቃያ ማዕከላትና ወህኒ ቤቶች እየሸኘ አርፎ መቀመጥ የእግር እሳት የሆነበት የአገሬ ህዝብ ካለፉት ሁለት/ሶስት ዓመታት ወዲህ ፍርሃት ሲበዛ በቁም መሞት መሆኑን ከምር ተረድቶ መከራና ውርደት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቁ ዘንድ በቃ ብሎ መነሳቱን በማያሻማ መንገድ ግልፅ አድርጓል ።  ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ  የአገሬ  ወጣቶች  በተለይ ደግሞ ቄሮዎችና ፋኖዎች እና  አሁን በዚህ ሰሞን በሚያስደንቅ ሁኔታ የአደባባይ ተቃውሞና ለሰባት ቀናት  ማነኛውንም እንቅስቃሴ የማቆም አድማ የመቱት  የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች ፣  እና በተቃውሞው  የአርበኝነት ጎራ የቆሙ ወገኖች ፋና ወጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ። 
  2.   ከፊታችን ከፍተኛ ሥራ የሚጠይቁ ፈታኝ ጉዳዮች የመኖራቸው እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ የጋራ እጣ ፈንታን በጋራ ለመወሰን በቁርጠኝነት  መንፈስ  በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ  ትግል እያንዳንዱን ነፃነትና ፍትህ ወዳድ ዜጋ እና ከምር ለአገርና ለወገን ቁመናል የሚሉ ባለድርሻ አካላትን (የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችን) ከምር የመደማመጥንና በአብሮነት የመቆምን ወሳኝነት ግልፅ አድርጎታል ።  ይህን ሁኔታ ወደ እሚጨበጥ ውጤት ለማሸጋገር የሚታየው ተነሳሽነትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጥልቀትና ስፋት እያገኘ በሄደ ቁጥር  የመከራና የውርደት ሰለባ የሆንበት የፖለቲካ ሥርዓት የሚያከትምበትን ጊዜ ከአሁን በኋላ ወራትንና አመታትን እየቆጠርን የምንታገሰው አለመሆኑም ይበልጥ ግልፅ እየሆነ ይመጣል። ።
  3. የኢትዮጵያህዝብበባለጌዎችናበግፈኞችእጅወድቀውየሰቆቃአይነትመፈተኛከሆኑትእጅግበርካታንፁሃንልጆቹመካከልየተወሰኑትንናለህዝባዊናዴሞክራሲያዊሥርአትእውንመሆንግንባርቀደምሚናያላቸውንጨምሮከእስርበማስፈታትየአርበኝነትናየጀግንነትአቀባበልየማድረጉንኅያልነትበቅንነትናበእውንለመረዳትለሚፈልግወገንሁሉመልእክቱግልፅናግልፅነው።የገዥውቡድንእየበሰበሰ እያታደስኩ ነው የሚለውን የሴራ ቀልድ በማክሸፍ እና የመከራና የውርደቱን ሥርአተ ህወሃት/ኢህአዴግ  በማስወገድ እውነተኛ ህዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የመመሥረት ብርቱ መልእክት ነው ። አዎ! ይኸው ነው  የአሁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የምርና የማይታጠፍ  መልክት  ። የሚሰማ ሰምቶ ራሱንም ያድናል ፥ የአገርንና የወገንን የመስዋእትነት ዋጋም ከመጠን እንዳያልፍ እና የመከራውና የውርደቱ ጊዜም እንዳይረዝም ያግዛል ። የማይሰማ ካለ ደግሞ ድንቁርናውና እኩይ ባህሪው የሚያስከትልበትን  ውጤት ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለበት ። ያለንበት ገሃዱ ሁኔታ የሚያሳየንና የሚነግረን ይህንኑ የማያወላዳ ሃቅ ብቻ ነው ። ምርጫው የእያንዳንዳችን ነው።በተለይ ግን ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የአገርን ክብር ክፉኛ ያረከሱት እና የዜጎቿን ሁለንተናዊ ህይወት ምስቅቅሉን ያወጡት የገዥው ቡድን ባለጌ ባለስልጣናትና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው አሁን ያሉበት ሁኔታ እስከአሁን የተጠቀሙበትን ታደስን እያሉ የባሰ የመበስበስ ፖለቲካዊ ጨዋታ ጨርሶ የሚያስተናግድ ወይም የሚሸከም አለመሆኑን ተቀብለው ምርጫቸውን ለእነሱም ለአገርም በሚጠቅም አኳኋን ማስኬድ ግድ ይላቸዋል ። ከትናንት ዛሬ የሞራልና የህሊና ዳኝነት ስሜት በትንሹም ቢሆን አድሮባቸው ከሆነ።

4 ) ብርቅየ የአገሬ የቁርጥ ቀን ልጆች ትንሽም እንኳ የሞራል ወይም የህሊና ነውርነት ስሜት በሌላቸው ገዥዎች የግፍ መዳፍ ሥር ሲማቅቁ መኖራቸው አልበቃ ብሎ ያልሰራችሁትን የወንጀል ኑዛዜ ፈርማችሁ ውጡ ሲባሉ ይህ ከግፍም ሁሉ የከፋ ግፍ ነውና ይህን አድርገን ከጠባቧ ማሰቃያችሁ ወጥተን በሰፊዋ እስር ቤታችሁ (ኢትዮጵያ) የምንኖረው ህይወት በአፍንጫችን ይውጣ ማለታቸው ያለንበትን የነፃነትና የፍትህ ትግል ልዕልና ነው አጉልቶ የሚሳየንና የሚነግረን ። እድሚና ጤንነት ለእናት አገር የቁርጥ ቀን ልጆች!!!  

  1. የክሳቸውሂደትተቋርጦየወጡትምገናየወህኒ ቤት ( የህዝብ መሠረታዊ መብቶች በሚረገጡበት ሥርዓት ማረሚያ ቤት ስለማይሆን ) በሮች ተከፍተው ብዙ ሳይራመዱ የአርበኝነትና የጀግንነት አቀባበል ሊያደርግላቸው ይጠባበቅ ለነበረው ህዝብ የእኛ መፈታት ሙሉ ትርጉም የሚኖረው አሳሪዎቻችን አብቅለው ያጎለበቱት የመከራና የውርደት ሥርዓት በማይመለስበት አኳኋን ተወግዶ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ አብሮነት፣ ሰላም ፍቅርና የጋራ ብልፅግና በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ መኖር ስንችል ብቻ ነው በማለት ቃል ኪዳናቸውን ደግመው ሲያረጋግጡ ከማዳመጥና  ከማየት የበለጠ የነፃነት ድል መቃረቡን የሚነግረን አስረጅ ያለ አይመስለኝም ።
  1. በአጠቃላይአምባገነንገዥዎችበተለይደግሞየእኛዎቹከሚጠቀሙባቸው  አይነተኛረግጦየመግዛትዘዴዎችመካከልየኢንፎርሜሽንነፃነትየሌለውህዝብያለበትንየፖለቲካምንነትንናለማንነትየመረዳት  ዉሱንነትን  ፣የገንዘብናየማተሪያልእጥረትንእናየመሰባሰብናየመደራጀትአስቸጋሪነትንበመጠቀምእድሉንከማማረርአልፎአልገዛምእንዳይልማረጋገጥነው።  ህዝብከእንዲህአይነቱችግርለመውጣትየሚያደርገውንትግልየሚመሩናየሚያስተባብሩዜጎችንወይዝምማሰኘትየለዚያበየምክንያቱማዋከብ፣ማሰቃየት፣በህግስምበሃሰትወንጅሎወህኒማጎርናበጎዳናወይምበአደባባላይተኩሶመግደል    ነውየአምባገነኖችበሥልጣንላይየመቆያስልታቸው።በአጭርአገላለፅየህዝባዊ ንቅናቄ አስተባባሪ  ወይም ለተሻለ ሥርዓት የሚሠራ ድርጅት  መሪ ነኝ የሚለውን ሁሉ ከተቻለ  ጨርሶ እንዳይኖር  ካልሆነ ደግሞ በሚገባ  አንዲኮላሽ ከተደረገ  ህዝብ ችግሩንና መከራውን ወደ ውስጥ እያስታመመ ከመኖር አያልፍም የሚል መቀበል ቀርቶ ማሰብ የሚከብድ እርኩስ (እኩይ) የፖለቲካ መሰሪነት ነው የዛሬዎቹን ዘረኛ አምባገነን ገዥዎች የተጠናወታቸው ።

ከዚህ በተቃራኒው ግን  መስዋትነት ከፍሎ ላስፈታቸው ትልቅና ጀግና የአገሬ ህዝብ እና ለእናት አገር የቁርጥ ቀን  ልጆች ክብርና ምስጋና ይድረሳቸውና  ይህ የጨካኝ አምባገነኖች እኩይ ሴራ  ከሰሞኑ መናድ ጀምሯል ። እናም ለዚህ ነው ከአሁን በኋላ ከዘመናት የመከራና የውርደት መውጫ ብቸኛው መንገድ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር እና  ግንባታ የመሆኑ ጉዳይ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ግልፀና የማያሻማ ሆኗል ማለት እውነት የሚሆነው።  ይህን የሚጠራጠርና የአርበኝነቱን የመጨረሻ የፍልሚያ ጎራ ለመቀላቀል የሚቸገር አይጠፋምና ቆም ብሎና ትንፋሹን ዋጥ አድርጎ ራሱን እንዲጠይቅ ማስገንዘቡ አይከፋም። ።

የግማሽ ምዕተ ዓመት ሁለተኛውን አጋማሽ የያዘውን  የህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ  ርዕዮትና የመንግሥትነት አወቃቀር ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖሊሲ አነዳደፍ ፣ የህግ አወጣት ሂደትና አፀዳደቅ  ፣ የአፈፃፀም መመሪያ አወጣትና ሥራ ላይ አዋዋል ፣   ፕሮግራም አነዳደፍና አተገባበር ፣ እና የእነዚህን ሁሉ አስከፊ  ውጤትን ማለትም አገርና  ዜጎቿ  የመከራና የውርደት ቀንበር  እንዲሸከሙ መገደዳቸውን በተመለከተ  ያልተነጋገርንበትና በየፊናችን ይበጃል የምንለውን መውጫ መንገድ  (መፍትሄ) ያልሰነዘርንበት ጊዜና ሁኔታ  ያለ አይመስለኝም ።

ለሩብ ምዕተ ዓመት አብዝተን እንደመናገራችንና እንደመነጋገራችን ከውድቀታችን እየተማርን ይበልጥ ጠንክረን በመነሳት የመከራና የውርደትን አድሜ ማሳጠር የተሳነን  በሚያስማሙን ጉዳዮቻችን እየተስማማን፣ የምንለያይባቸውን ደግሞ በሂደት እየፈታን ፣  ማህበረሰብ የእያንዳችን ባህሪና ፍላጎት ስብስብ እንደመሆኑ ከዚህ ተፈጥሯዊና ማህበረሰባዊ እውነታ የሚመነጩትንና ማስወገድ የማንቻለውን ጉዳዮች ደግሞ እንደአመጣጣቸው ለማስተናገድ  በሚያስችለን የጋራ ዣንጥላ (ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) ሥር መሰባሰብ ስለአልቻልን ነው። ወደ ድል የተጠጋው የነፃነትና የፍትህ ትግል ግቡን ይመታ ዘንድ ተመሳሳይ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀን  የባለጌና ጨቃኝ ገዥ ቡድን ሰለባዎች  እንዳንሆን ከመሪሩ ተሞክሯችን ( the bitter  expereince) መማር የግድ ይለናል ።  ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የጎጠኛና ዘረኛ አምባገነን ገዥዎች መፈንጫ ሆነን የዘለቅነው ማነኛውም ለነፃነትና ለፍትህ የሚደረግ ትግል የሚያጋጥመው መውደቅና መነሳት ስለአጋጠመን  ሳይሆን ከውድቀት ባለመማራችንና  ከመጠን በላይ ደጋግመን በመውደቃችን ነውና የአሁኑ በቃኝ ባይነት ለእውነተኛ ትንሳኤ (ተመልሶ ያለመሞት) መሆን አለበት   የዚህ ዋስትናው (ብቸኛውና አስተማማኝ መንገድ) እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ እንጅ አምባገነኖች የአገዛዛቸውን እድሜ ለማራዘም የሚሸርቡት የሴራ ተውኔት ከቶ ሊሆን አይችልም ። እንዲሆንም በፍፁም መፍቀድ የለብም ።

ይህን ያህል ንፁሃን ታሳሪዎች ሲፈቱ ያንኑ ያህል ወይም የበለጠ  ቁጥር ያላቸው ንፁሃን  ታሰሩ እያልን ዜና ያስነገርንበትና የሰማንበት ፣ የዜግነትና የሰብአዊ መብት ይከበር ማለት ከቁም ሰቆቃ እስከ ህይወት ማጣት (ያውም ጎዳና ላይ በጥይት) የሚያስቀጣ መሆኑን ከመሪር ሃዘን ጋር የታዘብንበት ፣ የእንዴትና ምን እናድርግ  ጥያቄዎቻችን እየመላለስን የጠየቅንበትና መልስ ይሆናል ያልነውን ሁሉ የሞከርንበት ፣ ለድጋፍ ወይም ለተቃውሞ ወደ የአደባባዩ የወጣንበት ፣ የድጋፍ ወይም የውግዘት መግለጫ እያዘጋጀን ያስነበብንበት ወይም ያሰማንበት ፣ የሃዘንና የእግዚአብሔር ያፅናችሁ (ያፅናን)መልክቶቻችን ያስተላለፍንበት ፣ የነፍስ ይማር ፀሎት ያደረስንበት ፣ ከክፉ አድነን ብለን ምህላ የያዝንበት፣ አገራችንና ህዝቧን በሰላም ጠብቅ  እያልን እግዚኦታ ያሰማንበት  ፣ የሃያላን መንግሥታትንና በእነሱ ተፅዕኖ ሥር ያሉትን አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ  ድርጅቶችን የተማፀንበት ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብአዊ መብት ይከበር የሚሉ ድርጅቶች የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ መንግሥታት ባለሥልጣናትን  ትኩረት አገኙ ወይስ የወረቀት መደርደሪያቸው ማሞቂያ ሆነው ቀሩ እያልን የተጨነቅንበት  ዘመን ህወሃት/ኢህአዴግ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ከገባበት ጊዜ ነው የሚጀምረው ። የስፋቱና የጥልቀቱ ደረጃ እየከፋ የመመጣቱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ።

ይኸ ሁኔታ ተገቢ ቁጭትና ፀፀት አሳድሮብን ከመከራና ከውርደት መውጫ ብቸኛ መንገዳችንን (መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታን ) በቀላሉ ልንወጣው ወደ ማንችለው ቀውስ ከመግባታችን በፊት እውን ለማድረግ መረባረቡ ጨርሶ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆን የለበትም ። መንበረ ሥልጣኑን በማነኛውም መንገድ የተቆጣጠረ ሁሉ እያዋከበ ፣ እየገረፈ ፣ እያሰረ ፣ እየገደለና እያስራበ የመግዛቱ አስቀያሚ  ታሪክ በዚህ ትውልድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተዘግቶ ወደ ሙዚየም (ቤተ መዘክር) መውረድ አለበት።  ድንቅየ የአገሬ ወጣቶች ይህን እጅግ ፈታኝ  ነገር ግን  መወጣት የሚቻል ታሪካዊ ተልኮ ለመወጣት እያካሄዱት ያለው ተጋድሎ ወርቃማ ግቡ ይኸው ነው ።

ከዘመን ጋር መዘመኑ ቀርቶብን እንደሰው ያለ ሥጋትና ፍርሃት  በህይወት የመኖር እና እንደ ዜጋ ደግሞ አገር ላይ በነፃነት ሠርቶ የመኖር  ባለመብቶች መሆን ባለመቻላችን (እንድንሆን ባለማድረጋችን) ገዥዎቻችን  ሥልጣናቸውን ከማጣት ሥጋትና ጭንቀት የተነሳ አዘጋጅተው የሚወረውሩልን አጀንዳዎቻቸውና ፖለቲካዊ ተውኔቶቻቸው ሰለባዎች ሆነን እንዳንቀጥል ብርቱ ጥረትና ጥንቃቄ ይጠይቀናል የሚል እምነት አለኝ ።  ይህን ሆኖ ለመገኘት ደግሞ የዕውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማንም ፖለቲከኛ ወደ ሥልጣን በወጣና በወረደ ቁጥር በማይናወጥ መሠረት ላይ ማቆምን ግድ ይላል።  ከሩብ ምዕተ ዓመቱ ጥቂት ዘረኛ አምባገነኖች ከተከሉብን የሰቆቃና የውርደት ሥርዓት ልንወስደው የሚገባን መሪር ተሞክሮ ( bitter expereince) ይኸው ነው ።

እንኳን  እንደ እኛ በረጅም የፖለቲካ ታሪኩ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት እንኳን ጣእሙ ሽታውም ደርሶት ለማያውቅ አገር በአንፃራዊ መልኩ በልፅገዋል በሚባሉ ዴሞክራሲዊ አገሮችም መሳሳት ፣ መውደቅና መነሳት ቢኖር የሚገርም አይደለም ። ይህን አጠቃላይ እውነታ  ግን ለራስ ደካማ አስተሳሰብ ፣ የተግባር ባዶነትና ውድቀት መሸፈኛ ምክንያት (excuse) እየደረደሩ ከገቡበት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ካለመቻል ጋር ጨርሶ ግኑኙነት የለውም ። በእኔ ግንዛቤና አረዳድ ከአለፉት ሁለት/ሶስት ዓመታትና በተለይም በመግቢያዬ ላይ አንደና ሁለት ብየ ለማሳያ ያህል እንደ አስቀመጥኩት በአሁኑ ወቅት በተጨባጭ የምናየውና የምንሰማው የህዝብ አልገዛም ባይነት ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ነው  የምንለውም ይህኑ ክፉ አዙሪት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብሮ  ለመዉጣት የሚደረግ ህዝባዊ የነፃነት ፣የፍትህ ፣ የዜግነትና ሰብአዊ መብት  ተጋድሎ በመሆኑ ነው ።

ከሰሞኑ ገዥው ቡድን በእጁ ላይ ያለውን የማፈኛና የግድያ ኅይሉን ሁሉ ተጠቅሞ ሊገታው ያልቻለውን የህዝብ እምቢተኝነት (በቃኝ ባይነት) አዲስ ባልሆነ ግን በሚመስል የፖለቲካ ጅምናስቲክ ጊዜ ገዝቶ  አይደፈሬነቱን  መልሶ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ከላይ (at face value) ሳይሆን ከተፈጥሮው ፣ ከባህሪውና ከድርጊቱ ይዘት ተነስቶ ለመረዳት ለሚፈልግና ለሚችል የአገሬ ሰው ጨርሶ የሚያስቸግር አይደለም።

የገዥው ቡድን ጊዜ ገዝቶና የተለመደ እኩይ ተግባሩን ይበልጥ አጠናክሮ ለመውጣት በሚተውነው ሴረኛ የፖለቲካ ተውኔት ውስጥ የሚከሰቱ መልካም አጋጣሚዎች (opportunities) ሲኖሩ በአግባቡና በጥንቃቄ ከተጠቀምንባቸው ለነፃነት ትግሉ የማይናቅ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ስለመሆናቸው የጋራ ግንዛቤ ላይ መድረስ የሚያስቸግር አይመስለኝም።

በሌላ በኩል ግን  ከገዥው ቡድን መካከል በግለሰብ ወይም በንኡስ ቡድን ደረጃ አይዟችሁ እናት ድርጅታችንም እየበሰበሰ ነውና አብረን በስብሰን መውደቅ ስለማንፈልግ ከህዝባችንና ከእናንተው ጋር መሆናችን አይቀርም ስንባል ያለምንም ተጨበጭ ፖለቲካዊና ፍትሃዊ የለውጥ መፍትሄ  አሜን ብለን ለመቀበል ሲቃጣን ማየት  ቢያንስ ጥሩ ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም ።  ቆም ብለንና ከመሪሩ ሃቅ (መሬት ላይ ተዘርግቶ ፀሐይ ከሚሞቀው) አንፃር ብናስተውለው በሴራ ተወልዶ ፣ አድጎ እና ጎልብቶ እጅግ በከፋ ሴራ ለሩብ ምዕተ ዓመት ረግጦ ፣ ገድሎና የአገርን አንጡራ ሃብት ዘርፎ  እየገዛ ያለው የገዥ ቡድን የፖለቲካ ተውኔት ጉዳተኞች  (victims of the dirty political game) እንዳንሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ በእጅጉ ያስፈልገናል ።

የዘመናት የመከራና የውርደት ምንጭ ከሆነው አውራ ቀለበት (ህወሃት/ኢህአዴግ) ሰብሮ ለመውጣት የሚደረግ  ተግባራዊ ሙከራ ይቅርና በቃላት ደረጃም እዚህ ግባ እሚባልና ከእናት ድርጅት (ህወሃት/ኢህአዴግ) ብዙ እርቆ የሄደ ዕውነተኛ የለውጥ ፈላጊነትነትንና አድርጎ  መገኘትን  በእርግጠኝነት የሚያመላክት አዲስና ግልፅ የአቅጣጫና የግብ መስመር ባላየንበት ሁኔታ የምናዥጎደጉደው በረከተ ሙገሳ በምንም አይነት መለኪያ የበሳልና የውጤታማነት ፖለቲካ ሥራ አይደለም ። እንዲህ አይነቱ ግልብ ወይም ከአፍንጫ ስር የማያልፍ  ፖለቲካዊ ትንታኔያችንና እና ትንበያችን የሚያሳየው ነገር ቢኖር በገዥው ቡድን በተለይም በህወሃት የሴራ  ተውኔት ቀለበት ውስጥ ሰተት ብለን  እንዳንገባ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን መሆኑን ነው።

እገሌ ስለኢትዮጵያዊነት ደፍሮ ተናገረ  ፥ የመደብ ጭቆና እንጅ የብሔረሰብ ጭቆና የለም ብሎ የፈጣሪውን (የእናት ድርጅቱን- ህወሃትን) ርዕዮተ ፖለቲካ ውድቅ አደረገ ፥  ከተቀዋሚ ድርጅቶች ጋር ለመነጋገር ጥሪ በማድረግ እናት ድርጅቱ ያላደረገውን አደረገ  ፥ በስልጣን መከታነት የሚካሄድ ሙስናን/ኪራይ ሰብሳቢነትን/ኮንትሮባንዲስትነትን እንዋጋለን ሲል በመግለጫው ገለጠ ፥በተያያዝኩት ኢህአዴጋዊ ተሃድሶ ከስህተቴ ተምሬ ተአምር አሠራለሁና ይቅርታ እጠይቃለሁ ብሎ አመነ ፣  የሚናገረው ሁሉ ከእናት ድርጅቱ አለቆች በተለየ ድፋርነት ይታይበታል  ፣ የለውጡ አካል ሊሆን ይችላል ፣ ንግግሩ ሁሉ ማራኪና በይዘቱም በሳል ነው ፥ ወዘተ የሚለው ትንታኔያችንና የአረዳድ አቅጣጫችን ከምንፈልገው   መሠረታዊ ዴሞክራሲዊ  የሥርዓት ለውጥ አንፃር በሚገባ እያሰብንበት መሆኑን ወይም አለመሆኑን ማረጋገጥ አለብን የሚል እምነት አለኝ ። ምክንያቱም ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ አገርና ህዝብ ለማመን በሚያስቸግር አኳኋን የመከራና የውርደት ዶፍ ሲወርድባቸው የራስ ተነሳሽነት የሚባል ነገር ከቶ ያላሳዩን የገዥው ቡድን እድምተኞች የህዝብ የለውጥ ማዕበል አስገድዷቸው ከፖለቲካ መዝገበ ቃላታቸው ያልነበሩ  ቃላትና ሃረጋትን   በአደባባይ የፖለቲካ ንግግራቸው (rhetoric) ውስጥ እየሰካኩ  ስለአሰሙን ከህወሃት/ህአዴግ እቅፍ ወጥተው የህዝብን ተጋድሎ የተቀላቀሉ እስኪመስል ድረስ ሙገሳውን የማዥጎድጎዳችን ነገር ተመልሶ  እኛኑ ራሳችን በወዳጅም በጠላትም ያስገምተናል   ።  በምንም የተግባር ውሎ ያልተፈተነ ቃለ ሠናይነታቸውን ትንሽ ጊዜ ወስደን እንዴትና ወዴት እንደሚያመሩ እንኳ ሳንታዘባቸው የእደጉ ተመንደጉ ልግሥናችን ፖለቲካዊ እውነታን ከየዋህ ሞራላዊ እይታ ለይቶ ለማየት ካለመቻል የሚመጣ ይመስለኛል ።

እያልኩ ያለሁት በራስ መተማመንን ጨርሶ የሚሰልበውን የህወሃት/ኢህአዴግን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ቀለበትን ባይሰብሩም እንኳን በአንፃራዊ እይታ ከሱ ወጣ ያለና ወደ ህዝብ ፍላጎት የተጠጋ ንግግር ለማሰማት እየሞከሩ ያሉ በተለይም ጥቂት የኦህዴድ ባለሥልጣናት  አይበረታቱ ወይም አላስፈላጊና ለአብሮነታችን የማይጠቅም እርስ በርስ የመጠራጠር (ያለመተማመን) ፖለቲካዊ ባህላችንን የሙጥኝ እንበል አይደለም ። በፍፁም !  የአስተያየቴ ጭብጥና አላማ አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ግንዛቢያችንና አረዳዳችን በስሜት በማይነዳ ፣ ግልፅ ቀጥተኛ በሆነ ፣ በሚጨበጥ ምክንያታዊነት ላይ በተመሠረተ ፣ በግለሰቦች የግል ባህሪና አኗኗር ዙሪያ ሳይሆን በሚያሳስበን ጉዳይ ላይ ብቻ ባተኮረ ፣ ብሎም ወደ ጋራ መተማመንና መተባበር በሚያመጣ ጠንካራ ሂሳዊ የሃሳብ ልውውጥ (critical way of exchange of ideas and views) ላይ የተመሠረተ ይሁን የሚል ነው ። ለምን? ቢባል ይህን የማድረግ ፍላጎቱና ወኔው ከሌለን ወደ ህዝብ ፍላጎት እየመጡ ነው የምንላቸው ወገኖችም በዚያው ክፉ የፖለቲካ አባዜያቸው ይቀጥላሉ ፥እኛም እግዚአብሔር ይይላችሁ እያልን በእነሱው ክፉ አገዛዝ ሥር መከራና ውርደቱን እንገፋለን ።   ብንፈራውም ወይም ባንፈልገውም ሐቁ ይኸው ነው ።

እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉ የገዥው ቡድን ባለስልጣናት በአንፃራዊ እይታ ቢያንስ በቃላት ደረጃ ከሌሎች ጓዶቻቸው በተሻለ ሁኔታ ሃሳባቸውን ህዝባዊ ቃና ባለው መንገድ ፈራ ተባ እያሉም ቢሆን መግለፃቸውን ጨርሶ ማጣጣል ትክክል አይሆንም ።  በአብሮነት ነፃ ወጥቶ እኩልነት፣ ነፃነት፣ ፍትህና የጋራ ብልፅግና በሰፈነባት አገር  ለመኖር  የምንመኘው ምኞት እውን ይሆን ዘንድ እንኳን  በጎ ነገር የሚናገሩት  የአቶ ለማ መገርሳ ንግግሮች  እዚህ ግባ የማይባል አስተያየትም ቢሆን መሰንዘሩ መብት ከመሆንም አልፍ የራሱ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ሳይነገር ይቅር ማለት ትክክል አይሆንም ።እነ አቶ ለማም ሆኑ ሌሎች ከህወሃት ትንሽም ብትሆን የተለየች ሃሳብና አስተያየት አለን የሚሉ ኢህአዴጋውያንን ቃለ ሠናይነት ለምን በይሁንታ  እናየዋለን የሚል ደምሳሳ አስተሳሰብም የለኝም።   ከሩብ ምዕተ ዓመት ተሞክሮ ተነስተን እና የአሁኑ ህዝባዊ እምቢተኝነት የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ሲያሳጣቸው የሚከተሉትን የሴራ መንገድ (ስልት) በሰከነ እና ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በሚያግዝ አኳኋን  እናስኪደው ነው አስተያየቴ ።

ጠፍጥፎ የሠራቸውና የእኩይ አጀንዳው አራማጅና አስፈፃሚ ያደረጋቸው የህወሃት የፖለቲካ መንኮራኩር  ተሰባብሮ እንዳይወድቅ  በተሃድሶ(በጥገና)”  እድሜውን ለማራዘም   ሌት ተቀን እየሠሩ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የለውጥ ግቡን እንዲመታ ምን አይነት የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ጨርሶ ግልፅ አይደለም ነው አስተያየቴ። የፖለቲካ እስረኞችን በእኛ ጥረት ስለአስፈታን (የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና ሌሎችም የኦህዴድ ባለሥልጣናት እንደሚነግሩን ) ክሬዲቱም ለእኛ ይገባልየሚል አይነት እወጃም የባሰ ራስን ያስገምታል ። ምክንያቱም የህዝብ የቁጣ ማዕበል የተናጋውን መንበረ ሥልጣን ጨርሶ ይነቅልብናል ከሚል ሥጋት የተወሰደ እርምጃ ስለመሆኑ እንኳን የአገሬ ሰው በአገሬ ሰማይ ላይ የምትበረው የአገሬ ወፍውም ታውቀዋለችና ነው።  

አቶ ለማ መገርሳና መሰሎቻቸው በህዝብ ግፊትም ቢሆን  በአንፃራዊ  እይታ  የህዝብን ስሜት  የሚስብ ንግግርና አስተያየት መሰንዘራቸው ይሁን የሚያሰኝና ተገቢውን እውቅና የሚያሰጣቸው ነው የሚለውን ለመቀበል አያስቸግርም ።በሌላ በኩል ግን እስከአሁንም የፖለቲካውን ትኩሳትና የህዝቡን የለውጥ ማዕበል በጥንቃቄ እየለኩና ለሱም የሚስማማ ቃል እየፈለጉ ከመናገር ያለፈና ዋዉ! የሚያሰኝ የአቋም እደገት (development) አላየንም። አልሰማንምም ።   እንግዴህ ጥያቄው የራስ ተነሳሽነትና አነሳሽነት መነሻ ሳይኖረን የህዝቡ መራር ንቅናቄ በእውን ለእኛና ለድርጅታችን አስጊ ነው ወይስ የተሃድሶ ፍርፋሪ ትንሽ ጠቀም አርጎ በመለገስ የሚረግብ ነው? እያልን የምንደሰኩረው ዲስኩር  እንዴት ነው የህዝብን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ጥያቄን ለመፍታት የምር አስተዋፅኦ የሚያደርገው ?  ነው። ምናልባት ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀለበስ በማድረግ ህዝብ ለመሠረታዊ የሥርአት ለውጥ የሚያደርገውን ትግል በነፃነት እንዲያራምድ ለማድረግ ከቻሉ እና እነሱም ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ዝግጁ ሆነው ከተገኙ  ታሪካዊ የሚባል አድናቆትና ከበሬታ ማግኘት እንዳለባቸው የሚያጠያይቀን አይሆንም። ከዚህ ያነሰ ህዝባዊነት ግን ቀልድ ነው የሚሆነው

አዎ! የሩብ ምዕተ ዓመቱ ጭካኔንና ማጭበርበርን እያፈራረቁ ህዝብን እንደማነኛውም መገልገያ እቃ የመቁጠሩና የአገርን አንጡራ ሃብት ከግል ንብረት ማካበቻ እስከ ተራ የሽርሙጣ ማርኪያ የማዋሉ እጅግ የከረፋ የፖለቲካ ተውኔት ከአሁን በኋላ ጨርሶ መቆም አለበት ።  እንደኔ ግንዛቤና አረዳድ አሁን በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ አልገዛም ባይነት በጥብቅ የሚነግረንና በግልፅ የሚያሳየን ይህ በእጅጉ የከረፋ የፖለቲካ ታሪክ መዕራፍ ነገ ሳይሆን ዛሬ ተዘግቶ አዲስ የነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የእኩልነት ፣ የዜግነትና የሰብአዊ ክብር ፣ የሰላም ፣ የፍቅር ፣ የጋራ ብልፅግና እና ዘላቂነት ያለው ምዕራፍ መከፈት እንዳለበት ነው ።   ያም ምዕራፍ የሚጀምረው ወደ በለፀገ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚወስደን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር (democratization) ነውና ለዚሁ እውን መሆን በማሸነፍ ሂደት ላይ ያለውን ህዝባዊ የለውጥ ማዕበል ይበልጥ በበሰለ ፣በታቀደና በተቀናጀ አካሄድ የማስኬዱ ጉዳይ የሁሉንም ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ ዜጋ ርብርቦሽ ግድ ይላል። በዚህ ረገድ በህዝብ ትግል ከእስር የወጡትን ጨምሮ  በቁም ስቃይ የተቀበሉና በመቀበል ላይ ያሉ ፣ በግፍ ተፈርዶባቸው በየወህኒ ቤቱና በሌላም በማይታወቅ የማሰቃያ ማዕከል የተሰቃዩና የሚሰቃዩ እና የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ አያሌ ንፁሃን ዜጎች የታሪካችን የወርቅ መዝገብ ባለቤቶች ናቸው።  ይህ አሁን ያለንበት የአይቀሬው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ዋዜማ በእነሱ መስዋዕትነትም የተዋጀ ነውና ።

በረጅምና እጅግ አስከፊ ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ የቆየንበት ምክንያት በዋናነት የገዥው ቡድን ሥርዓተ ሰቆቃ የመሆኑን ጉዳይ ከራሳቸው ከገዥዎቻችንና ግብረ በላዎቻቸው በስተቀር በእያንዳንዱ ዜጋ የእለት ከእለት ህይውት ውስጥ ገዝፎና ሥር ሰድዶ የሚታይ ስለሆነ ብዙ የሚያጠያይቅና  ጥናታዊ ማስረጃ ሩቅ የሚያስኬድ አይደለም ።  ጨርሶ መማርና መታረም የማይፈልጉ ወይም የማይችሉ ደንቆሮና አረመኔ  የገዥ ቡድን ስብስቦች በሚቆጣጠሩት ሥርዓት ሥር ሆኖ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈን ይቻላል ብሎ እንኳ ለመቀበል ማሰብም የሚቻል አይመስለኝም ። በመካሄድ ላይ ያለው   የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ  ለውጥ ህዝባዊ ንቅናቄ  በገዥው ቡድን የተሃድሶ ፍርፋሪ (ምፅዋት) ይገታል ብሎ የሚያስብ ወይም የሚያምን ካለ ወይ በሥርዓቱ የተጠቀመ ወይም የሥርዓቱን መቆየት ተማምኖ የጀመረው ፕሮጀክት ያሳሰበው ወይም እንደ ደመነፍስ እንስሳ እየበላና እየጠጣ ከመኖር ውጭ ሰብአዊ ህይወት ትርጉም የማይሰጠው መሆን አለበት ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ለሩብ ምዕተ ዓመት ተሸክሞት የዘለቀው የመለያየትና  በጥላቻ የመተያየት፥ በቁም ስቃይ የመቀበል ፣ በገፍ ወደ የማጎሪያ ማዕከላት (concentration camps) የመጋዝ ፥ መብትን መጠየቅ ከፍተኛ ወንጀል ሆኖበት በየተራ በየወህኔ ቤቱ ፍዳን የመቁጠር ፣ ለነፃነትና ፍትህ ድምፅ በሚያሰማበት ጎዳና እና አደባባይ ላይ የጨካኞች ጥይት ኢላማ የመሆን ፣ እና  በፍፁም የድህነት ማጥ ውስጥ የመማቀቅ የፖለቲካ ሥርዓትን አሜን ብሎ የተቀበለበት ጊዜ ባይኖርም ከአለፉት ሁለት/ሶስት ዓመታት ወዲህ ግን በስፋትና በይዘት ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገሩ  እወነት ነው።

ለብዙ ዓመታት በመከራና በውርደት የፖለቲካ ሥርዓት ሥር እንዲኖር የተገደደ ህዝብ  በሥልጣን አማካኝነት በሚመጣ የጥቅም አግበስባሽነት ጨርሶ ላበዱ የገዥው ቡድን ከፍተኛ አባላትና የጥቅም ሸሪኮቻቸው ግልፅና የማያወላዳ መልክት እያስተላለፈላቸው ይገኛል ።  አዎ!  የሄዳችሁበትና እየሄዳችሁበት ያለው  መንገድ በምድርም በሰማይም ይቅር ለማለት ቢያስቸግርም አገርን ከዚህ ክፉ አዙሪት ለመታደግ እና ለተተኪ ትውልድም የመከራና የውርደት ታሪክ ላለማውረስ ልብ ግዙና ነፃነት ፍትህና እኩልነት በሚሰፍንባት አገር በአብሮነት እንኑር የሚልና ኀላፊነትን ፣ አርቆ አስተዋይነትን ፣ ይቅር ባይነትን ፣ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ለትውልድ አብዝቶ አሳቢነትን አጣምሮ የያዘ መልእክትና ምክር ነው ከህዝብ አደባባይ እያስተጋባ ያለው ።   እንዲህ አይነቱን ምክር አዘል መልክት እንኳን መቀበል መስማትም አንሻም  ብለው በዚያው በለመዱት አጥፍቶ የመጥፋት መንገድ ለመቀጠል የሚንደፋደፉትን ደንቆሮና ጨካኝ   የገዥው ቡድን ባለሥልጣናትንና አጋፋሪዎቻቸውን  በሚገባ ተረድቶ የመታገልን አስፈላጊነት አሁን ካለንበት ሁኔታ  በላይ የሚነግርን ወይም የሚያሳየን ሁኔታ ጨርሶ የለም ። አይኖርምም ። ምናልባት ወደ ደመነ ነፍስ እንስሳነት ወርደንና አገር ፈራርሶ በፍርስራሹ ላይ እርስ በርሳችን እስከ ምንቦጫጨቅ እንጠብቅ ካላልን በስተቀር

ባርነትና ልክ የሌለው ድህነት በቃ! ብሎ የተነሳው ህዝባዊ ንቅናቄ በምናስበውና በምንፈልገው መጠንና ፍጥነት ግቡን ይመታ ዘንድ የሚጠይቀው ዋጋ ከባድነቱን አውቀን ይበልጥ መዘጋጀትን ግድ ከሚለን መስመር ላይ ነው የቆምነው። ከዚህ በላይ የከፋ ሁኔታ እስኪመጣ የሚጠብቅ በተለይ ፊደል የቆጠረና የአገር ጉዳይ በእውን ይገደኛል የሚል የአገሬ ሰው ካለ በአንዳች አይነት ክፉ ብዥታ (delusion) የተለከፈ መሆን አለበት ።

ህዝብ ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ በቁርጠኝነት በሚነሳበት ጊዜና ሁኔታ ሁሉ የከባድነቱ ጥልቀትና ስፋት ይለያይ እንጅ ፈታኝ ሁኔታ  የመኖሩ እውነታ የማይጠበቅ አይደለም ። የአፍራሽነቱን ተፅእኖ ከተቻለ ማስወገድ ካልሆነም መቆጣጠር ካልሆነ በስተቀር ጨርሶ እንዳይኖር ማድረግ አይቻለም ። የገሃዱ ዓለም እውነታም አይደለምና ።

ልንመሠርተው ከምንፈልገው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን አንፃር በእጅጉ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ሴረኛ ገዥዎቻችን  እገሌን ከሥልጣን አንስተን እንቶኔን በመሾም   ፣የአንዳንድ ጉልቾችን ቦታ በመቀያየር፣ አንዳንዶችን ጉልቾች ደግሞ ወደ ባህር ማዶ (ለኢምባሲዎቻችን ጉልቻነት) በመላክ ተሃድሶው ቤተ መንግሥት ድረስ ዘልቆ እንዲገባ በማድረግ ፣ወዘተ ጥልቅ ተሃድሶውን እያጧጧፍነው ነው ” እያሉ የሚነዙት ተራ ፕሮፓጋንዳ  ሰለባዎች እንዳንሆን ነው ።

ላስገኘነው ታይቶ የማይታወቅ ነፃነትና ብልፅግና አገሪቱን ከራሷ ህዝብ አልፎ በክፍለ አህጉርና በዓለም ደረጃ ተአምር የተሰራባት ምድር ተብላ እንድትታወቅ አደረግናት እያሉ ሌት ተቀን ሲያሰለቹን የነበሩት ገዥዎቻችን ዛሬ ጨርሶ እንዳንሄድበት ወደ እምንፈራው የገደል ጫፍ ምን ያህል እየገፉን እንደሆነ ልብ ያለው ልብ ይላል ።

የኢትዮጵያ ህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆቹን ሰብእናቸውን ለሥልጣንና ለሚያስገኘው ጥቅም ለሸጡ አምባገነኖች እየገበረ እዚህ መድረሱ ሳያንሰው አሁን ግን የራሱም  አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ በመውደቁ  መልሶ ማጥቃት ሲጀምር ፀረ ሰላምና  ንብረት አውዳሚ የሚለው ጬኸትና ውንጀላ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት አይነት ኢሰብአዊ ቀልድ ነው ።  በዚህ ላይ የገዥ ቡድኖች ከትርምስ የሚያተርፉ እየመሰላቸው ሊጨምሩት የሚችሉት ቤንዚን ሲጨመርበት ውጤቱ አገር የምንለውን የጋራ ቤት ምን ሊያደርገው እንደሚችል መገመት አያስቸግርምና ተረባርቦ የአደጋውን ምንጭ ሥርአት በማስወገድ የዴሞክራሲያዊ ሥርአት ሽግግር ላይ የመረባረቡ ጉዳይ ጊዜ የሚቀጠርለት ተልኮና ሥራ አይደለም።

ጨካኝ ገዥዎቻችን ሰብአዊ መብትን እየረገጡ ፣ የቁም ስቃይና ሰቆቃ እየፈፀሙ ፣ እንደ ከብት በጅምላ ማጎሪያ ማዕከሎቻው እያጎሩ ፣ ለከባድ ቅጣት የሚስማማ የሃሰት ማስረጃና ምስክር በመፈብረክ በህሊና ቢስ ዳኞቻቸው  እያስፈረዱ ፣ ወይም በቀጥታ በአስቸኳይ የፖለቲካ ችሎት እስከ ይሙት በቃ እየወሰኑ (በየአደባባዩ በነፍሰ ገዳይ ኀይላቸው ጥይት ተመትቶ የሚወድቀውን ልብ ይሏል ) ለሩብ ምዕተ ዓመት የገዙን አልበቃቸው ብሎ አሁንም የሴራ ስልታቸውን አሜን ብላችሁ ተቀበሉን ይሉናል ። የህዝብን የልብ ስብራት የሚያዳምጥ በሚያስመስል ገፅታ (face value)  እየለበዱ (እየሸፈኑ) የመከራና የውርደት አገዛዛቸውን ለማስቀጠል የማይፈነቅሉት ድንጋይ ከቶ የለም።  እኛም የራሳችን የስቃይ ፣ የመከራና የውርደት መጠንና ጥልቀት እያነሳንና እየጣልን ፣ አንዳንዴም  “ድንቅ ትዕግስታችን” እና ልክ የሌለው ድክመታችን እየተደበላለቀብን ለሥልጣን ማራዘሚያ ሴራ ተመቻቼተን ከመገኘት አዙሪት የመውጣቱን ፈተና  ገና አላለፍነውም።

የአምባገነን ገዥዎች አስከፊው ባህሪ ከውድቀት ተመልሶ በመነሳት ሰው ሆኖ መገኝት ሳይሆን በውድቀት ኖሮ በውድቀት መሞት  መሆኑ የፖለቲካ እውቀት ሀሁ ብቻ ሳይሆን አገራችን ጨምሮ በርካታ የዓለም ፖለቲካ ታሪክ መሪር ተሞክሮ ነው ። ህወሃት/ኢህአዴግም የኢትዮጵያ ህዝብ  ለሩብ ምዕተ ዓመት ተሸክሞ የኖረው መከረና ውርደት አሁንስ  በቃ ! ብሎ በተነሳ ቁጥር  የተለመደ የነፍሰ ገዳይ ኅይሉን  እያዘመተ ገደሏል  ፣ በቁም አሰቃይቷል  ፣ ወደ የማጎሪያ ቤቱም አግዟል ። ይህ የበለጠ የህዝብን ምሬትና ቁርጠኝነት ያነሳሳበት መሆኑን ሲረዳ   ደግሞ  ከተቻለ መንደር ለመንደር በሚካሄድ ዘመቻ ህዝብ አብሮ እንዳይቆም (እንዳይተባበር ) ለማድረግና ይህን ሴራውን  ሊያከሽፉ ይችላሉ ያላቸውን ከያሉበት ለመልቀም ያስችለው ዘንድ  የአስቸኳይ ጊዜ (የሽብር) አዋጅ በማወጅ የህዝብ ስሜት በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ለማስገባትና አይደግመኝም ለማሰኘት ሞክሯል ። አሁን ደግሞ አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላው ለሁለተኛ ጊዜ ህዝብን ጨርሶ ከእንስሳነት ባነሰ ደረጃ ሥር የሚያውል አዋጁን ለይስሙላ እንኳ የራሱን ህገ መንግሥታዊ ሥርአት ሳይከተል አውጆት አረፈ ።

የአገሬ ህዝብ የተፈራረቁበት ገዥዎች የጫኑበት የፈላጭ ቆራጭነት ቀንበር እንዳለ ሆኖ ለአያሌ ዘመናት እኛና እነዚያ ሳይል እኛና እኛ ብሎ ተሳስሮ የኖረበትንና የጋራ መስዋዕትነት የከፈለበትን አገራዊ (ብሔራዊ) ማንነት በማይመለስበት ሁኔታ ለመናድ ያልተጎነጎነ ሴራ ያልተሞከረ እኩይ ተግባር የለም ። የኢትዮጵያ ህዝብ በዘረኛ አምባገነን ገዥዎችና አንዳንድ በብሔረሰብ/ጎሳ ወይም በአንድነት ስም በሚነግዱ ፖለቲከኞች ለጊዜው የመታለል ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለአያሌ ዘመን በአብሮነት ገመድ የተያያዘውን አኩሪ ታሪኩንና ማንነቱን ማንም ሊቸረው ወይም ሊነፍገው እንደማይችል ይኸውና ከሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ በማያሻማ ሁኔታ ግልፅ አድርጓል ። የመከራውና የውርደቱ ምክንያት ተከባብሮ በነፃነት የሚኖርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርአት እጦት እንጅ ሴረኛና ክፉ ፖለቲከኞች እንደሚሉት የብሔረሰብ ፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶቹ በፍፁም የእርስ በርስ መጠፋፊያው ሳይሆኑ የሚደምቅባቸው ጌጦቹ እንደሆኑ ማሳየቱን  አሁን እያካሄደ ካለው የጋራ እጣ ፈንታን በጋራ የመወሰን ትግል የበለጠ ማስረጃ የለም ። አዎ! “ደምህ ደሜ በመሆኑ ደምህን የሚያፈሱትን ሁሉ በደሜ መስዋዕትነት እታገላቸዋለሁብሎ ቃል ኪዳንን ከማደስ የበለጠ ማስረጃ የለም ::

ዋነኛው ተጠያቂ የገዥው ቡድን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የመከራውና የውርደቱ  እድሜ  የተራዘመው  በተቃውሞው ጎራ የተሰለፉ   ፖለቲከኞቻችን ( በጣም ከጥቂቶቹ በስተቀር)  የፖለቲካውን ገመድ በአብሮነት ለመተሳሰር ሳይሆን አንዱ ሌላኛውን ጎትቶ (ጠልፎ) ለመጣል ስለተቀሙበት(ስለሚጠቀሙበት) መሆኑን ግልፅ ማድረግ እየተካሄደ ላለው ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ወሳኝነት ይኖረዋል ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኝነቱና ችሎታው የሌላቸውን ፖለቲከኞቻችንን የኢትዮጵያ ህዝብ ከአሁን ወዲያ የሚታገስበት ህሊና እና የሚሸከምበት ትክሻ እንዲኖረው መጠበቅ ወይ ድንቁርና ነው ወይንም አጋጣሚ ጠብቆ የአምባገነንነቱን ዘውድ ለመጫን መፈለግ ነው ። በሌላ አባባል የአገርና የወገን መከራና ውርደት በዕውን አብቅቶ በምትኩ እውነተኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ የተረጋገጠባት  አገር ማየት ከምር የምንናፍቅ ከሆነ አሁን በመካሄድ የሚገኘውና ወደ ድል እየተጠጋ ያለው ህዝባዊ አልገዛም ባይነት ዘረኛ አምባገን መሪዎችና አጫፋሪዎቻቸው ሥልጣንን ለማራዘም ኅይልንና የማታለያ ተውኔትን እያፈራረቁ የሚጠቀሙበት ሥርዓታቸው መወገድ አለበት ። ይህ ነው የአሁኑ ህዝባዊ እምቢተኝነት አቅጣጫና መዳረሻ መሆን ያለበት ።

መልካሙን ሁሉ ተመኘሁ !

Go toTop

Don't Miss

የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከ108 ሚሊዮን በላይ ደረሠ

(ዘ-ሐበሻ) በአለም ባንክና መሠል አለም አቀፍ ተቋማት በዚህ ሳምንት ይፋ

ሲግኒቸር ተዘጋ

(ዘ-ሐበሻ) ሲግኒቸር ለብዙ ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ነው፡፡ እንኳን ለኢትዮጰያዊያን በሙሉ ለአዲስ አበቤውም