በኦነግ ምክንያት የታሰሩ የኦሮሞ ወጣቶችም ይፈቱ | ቡልቻ ደመቅሳ

ኦነግ “ኦሮሞ ነፃ መውጣት አለበት” ብሎ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ሲታገል፣ የረገፉና የታሰሩ ወጣቶች ቁጥራቸው በትክክል ባይታወቅም እስከ አሁን በእስር ቤት የሚማቅቁ ቁጥራቸው አያሌ ነው፡፡ ብዙ የኦሮሞ ወጣቶች፣ የኦሮሞ ነፃ መውጣት ትክክለኛ ጥያቄ ነው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ ያኔ ደግሞ ኦነግና ህውሓት በአንድ ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ይመሩ ስለነበር፣ ካርቱም ላይ አብረው ቡና ይጠጡ ነበር፡፡ የደርግን ሀሳብና እቅድ በቅርብ ያውቁ ስለነበርም፣ ትግሉ ቶሎ አይጠናቀቅም በማለት አሜሪካኖች እርዳታ እንዲያደርጉላቸው ከእነሱ ጋር መፃፃፍ ጀመሩ፡፡ አሜሪካኖቹ ድሮውንም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መቆራረጥን ስለማይሹ ሳይወዱ በግድ አዎንታዊ ምላሽ ለህወሓት ሰጡ፡፡ ከዚያም ታዋቂ ሰዎችና የራሳቸውን ደጋፊዎች በመጋበዝ ኢህአዴግን በዙፋን ላይ አስቀመጡት፡፡

አሜሪካኖቹ የኢትዮጵያን ጉዳይ በጥልቀት ይከታተሉ ስለነበር፣ የኦሮሞ ብዛትና የታገለበትን እድሜ ዘመን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኦነግ በስብሰባው ላይ እንዲጋበዝ አደረጉ፡፡ ኦነጎችም መገንጠል የሚባለውን ሃሳብ ለጊዜው በጉያቸው ሸጉጠው ወደ ስብሰባው መጡ፡፡ ሆኖም ነገሩ ሁሉ በደንብ ስላልታሰበበት ኢህአዴግና ኦነግ ሳይስማሙ ቀርተው ኦነግ ከሃገር ተባረረ፡፡ ኢህአዴግም አምባገነንነቱን አፋፋመ፡፡ ኦነግም የጦርነቱን ጉዳይ ለመቀጠል ወደ ኤርትራ ተጠጋ፡፡ ኢህአዴግ በሃይል ህዝቡን ለመጫን ቢሞክርም ህዝቡ ግን አልገዛም አለ፡፡ (በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ደርግን ማሸነፍ የቻለው የተባበረ የጦር ኃይሎች ድጋፍ ታክሎበት ነው፡፡)

እንግዲህ አሁን የፖለቲካ ጫና በመብዛቱ የተነሳ የኢትዮጵያ መንግስት፣ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችን እፈታለሁ ብሎ ቃል ገብቷል፡፡ የተወሰኑትንም ከሰሞኑ መፍታት ጀምሯል፡፡ ድሮውንስ ቢሆን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችንና ፖለቲከኞችን “ለምን ከእኔ የተለየ የፖለቲካ ሃሳብ አራመድክ” ብሎ ማሰር ተገቢ ነበርን? ለማንኛውም ከእስር የመፍታት እርምጃው መልካም ነው፡፡ የቀሩትም ፖለቲከኞች መፈታት አለባቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  health: ስለኮሌስትሮል ሊያውቁ የሚገባዎት 6 ነገሮች

ከዚሁ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ዜጎች ሁሉ ህሊና ይቀበለዋል ብዬ የማምነው አንድ ነገር አለ፡፡ አያሌ የኦሮሞ ወጣቶች በኦነግ ምክንያት ታስረዋል፡፡ ቁጥራቸውም በጣም ብዙ ነው፡፡ የታሰሩት በፖለቲካ አስተሳሰባቸው ምክንያት ነው፡፡ ምርጫ ማለት የህዝቡን ፈቃድ መፈፀም ነው፡፡ ስለዚህ በኦነግ ምክንያት የታሰሩ ወጣቶችም እንደ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ ይገባል፡፡ መንግስት ይህንን ጉዳይ በጥልቀት ያስብበት ዘንድም እንደ አንድ አገሩን የሚወድ ዜጋ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡

2 Comments

  1. You are an old Person with wide experience. How beautiful it were if you and your co. talk also about the suffer and plight of another people irespective of their ethnicity. By doing though you would have minimized the suffer of your people and lead your people to freedom.

  2. ሰዎች!! ቡልቻ ደመቅሳን የማውቀው በጣም ህፃን ( teen age)ሆኜ እሱ ግን በንጉሱ ጊዜ የገንዘብ ሚኒስቴር ም/ምኒስትር ሆኖ ሲያገለግል ነው። ለሃገሩ ትልቅ ግልጋሎትን ኣበርክቷል። World Bank ደግሞ ለኣፍሪካ ተጠሪ ሆኖ ሰርቷል። ስለ ሃገራችን ጉዳይ ለቡልቻ መንገር ማለት ለቀባሪው ኣረዱት ይሆናል።

Comments are closed.

Share