ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
(ሚያዚያ 28፣ 2017) May 6, 2025
ሰሞኑን ዮናስ ብሩ ከመሳይ መኮንን ጋር ያደረገውን የቃለ-መጠይቅ ምልልስ አዳመጥኩት። በመጀመሪያ ደረጃ መሳይ መኮንን በገለጻ መልክ ለዮናስ ብሩ ላቀረበት ጥያቄ ዮናስ ብሩ አዳማጩን ወይም ተመልካቹን ለማሳመን የሚሞክረው በህወሃትም ሆነ በአቢይ የአገዛዝ ዘመን ጥሩ ጥሩ ነገሮች እንደተሰሩ ነው። ሁለቱንም አገዛዞች የሚቃወሙ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ሁለቱም የሰሯቸውን ነገሮች ለመቀበል ወይም ለማመን እንደማይፈልጉ ነው ዮናስ ብሩ ሊነግረን የሞክረው። ይሁንና ግን በተለይም በህወሃት ዘመን ምን ምን ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንደሆኑና ህዝባችንንም እንደጠቀሙ ዮናስ ብሩ በፍጹም አልባራራም። በደፈናው ብቻ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ተሰርተዋል ብሎ ነው ያለፈው።
ወደ ተጨባጩ ሁኔታ ወይም ህወሃት ተግባራዊ ወደአደረገው ፖለቲካዊ ጉዳይ ስንመጣ የጎሳ ፌዴራሊዝም እንደ ጥሩ ነገር በፍጹም ሊታይ የሚችል አይደለም። በመሰረቱ ህወሃት ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር ኢትዮጵያን በጎሳ ሲሸነሽንና ፌዴራሊዝምን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ ሲነሳ ዋና ዓላማውም የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲም ተጨቁነዋል ለሚባሉ ብሄረሰቦች ዕውነተኛ ነፃነትን ያመጣ ሳይሆን ለእሱ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ያሚያመችና በየክልሎች ውስጥ ያሉትን የጥሬ-ሀብቶች ለመቆጣጠርና ለመበዝበዝ የሚያመች ነው። አብዛኛው ብሄረሰብ በአማሮች ወይም ነፍጠኞች ናቸው በሚባሉት ይጨቆኑ ነበር በማለት በተለይም ሌሎች ተጨቁነዋል የሚባሉ ብሄረሰቦች በአማራው ላይ ጥላቻና ጥርጣሬ እንዲኖራቸው ለማድርገ ነው። ይህ ዐይነቱ የጎሳ ፌዴራሊዝምም በመሰረቱ በግለሰብአዊ ነፃነትና ድርጊት ላይ የሚመሰረተውን የሪፑብሊክ አስተሳሰብ የሚቃረንና ለሁለ-ገብ ዕድገትም እንቅፋት የሚሆን ነው። በተለይም የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና ባልዳበረበትና ሳይንሳዊ ዕውቀት ባልተስፋፋበት አገር ውስጥ የጎሳ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ ጥላቻን ነው የሚያስፋፋው፤ መተማመንም እንዳይኖር ነው የሚያደርገው። ከዚህ ዐይነቱ በመሰረቱ የፖለቲካ ፍልስፍናንና የፖለቲካ ሳይንስ አስተሳሰብን ከሚፃረረው በህወሃት የአገዛዝ ዘመን ተግባራዊ ከሆነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ሁኔታ ስንነሳ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ለሁለ-ገብ ዕድገትና ለዕውነተኛ ግለሰብአዊ ነፃነት እንቅፋት የሚሆን ነው። ስለሆነም በህወሃት የአገዛዝ ዘመን ሰለፖለቲካ የጥገና ለውጥ ማውራት በፍጹም አይቻልም። የህወሃት አገዛዝ በውጭ ኃይሎች ታግዞና ተደግፎ ስልጣን ላይ የወጣ ስለሆነ ነፃና የህዝባችንን ንቃተ-ህሊና ሊያዳብር የሚችል ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊመሰረት የቻለ አልነበረም። ከፖለቲካ ሳይንስ ገለፃ ስንነሳም የህወሃት አገዛዝ ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ ዘራፊ መንግስት ነበር(Predatory State) ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ዘራፊ መንግስትም ብሎ የሚያስጠራው የአገሪትን ስትራቴጂክ የጥሬ-ሀብቶችን በመቆጣጠር በዘረፋ ላይ የተሰማራና፣ የራሱን ካድሬዎች ከማደለብ አልፎ የተቀረውን በተለይም እንደ ወርቅ የመሳሰሉን ወደ ውጭ የሚያሽሽ ስለነበር ነው።
ህወሃት ተግባራዊ ወዳደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋም ስንመጣ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በመባል የሚታወቀውና የእነሱ ተጠሪ የሆነው ዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) የጻፈውን ነው ተግባራዊ ያደረገው። ይህም ፖሊሲ ኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል የሚታወቅ ነው። ፖሊሲውም ለአገር ግንባታና ሰፋ ላለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሰረተ ሁለገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመች አይደለም። በነፃ ገበያ ስም ለዘረፋ የሚያመችና ያለውን ሁኔታ የባሰውኑ የሚያዘበራርቅ ነው። ዮናስ ብሩ ኢኮኖሚስት እንደመሆኑ መጠን ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በህወሃት ዘመን በአገራችን ምድር ተግባራዊ እንደሆነ ማብራራት ነበረበት። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ዐይነቱ በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የተደገፈና ተጽፎ የመጣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለተሟላ ዕድገት ያመች አያመች፣ ለግለሰብአዊ የፈጠራ ስራ አመቺ ሁኔታን ይፍጠር አይፍጠር፣ እንዲያም ሲል ለሰፊው ህዝብ ሰፋ ያለ የስራ መስክ ፈጥሮ ወይም አልፈጠረ እንደሆነ ማብራራት ነበረበት። በደፈናው ዝም ብሎ በህወሃትም ዘመን ጥሩ ነገሮች ተሰርተው ነበር ብሎ ነው ሊያሳምነን የሚሞክረው።
ሌላው ዮናስ ብሩ ሊያሳምነን የሞከረው አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ እንደወጣ መሰረታዊ ለውጥ እንዳመጣ ነው። በዮናስ ብሩ ዕምነትም መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ማለት ህወሃት አስሯቸው የነበሩትን እስረኞት መፍታቱ ነው። የእስረኞቹ መፈታት ጥሩ የሆነውን ያህል፣ የእስረኞች መፈታት በራሱ እንደመሰረታዊ ለውጥ ሊታይ የሚችል ነገር አይደለም። መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ማለትም አጠቃላይ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ የግዴታ የተቋማት ግንባታ ማካሄድና የመንግስትንንም ተቋማት የግዴታ ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው። ወደፊትም የመንግስት አሰራር ግልጽ እንዲሆን በኤክስኩቲቭ፣ በህግ አውጭውና በህግ አስፈፃሚው መሀክል ያለውን የስራ-ክፍፍል በደንብ በማስመር ጠቅላይ ሚኒስተሩ ያለውን ስልጣን በመጠቀም ጣልቃ እንዳይገባና የመንግስትን መኪና ለእራሱ በሚስማማው መልክ እንዳያዋቅር ገደብ ማስቀመጥ የግዴታ ከመሰረታዊ ለውጥ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመች የትምህርት ስርዓት ለውጥ ማድረግ የመሰረታዊ ለውጥ አንድ አካል ነው። ከዚህ በመነሳት የህዝቡን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት በቅድሚያ መወሰድ ያለባቸውን ነገሮች መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ የመሰረታዊ ለውጥ ዋናው ዕምብርት መሆን አለበት። ነገሩን ላለማንዛዛት በዚህ ላይ ልገደብና የእስረኞችን መለቀቅ እንደመሰረታዊ ለውጥ አድርጎ የተመለከተውን እንቀበል ብንል እንኳ አቢይ ስልጣን ላይ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ካለበቂ ምክንያት ወደ አስር ቤት እንዲገቡ ተደርገዋል። እየታፈኑ የተወሰዱና የት እንደደረሱም የማይታወቁ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ አሉ። ከዚህም በላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ከቀያቸው እንዲሰደዱ በማድረግ ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቁ ተደርገዋል። በአቢይ አህመድ የአገዛዝ ዘመን ቤተ-ክርስቲያናት ወድመዋል፤ ምመናንም ተገድለዋል። ከዚያም በላይ ሶስት ዓመት የሚያስጠጋ በአማራው ወገናችን ላይ የሚካሄደው ጦርነት ሲደምርበት አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ህዝባችንና አገራችን እጅግ አሰቃቂ በሆነ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ተገደዋል። ስለሆነም ዮናስ ብሩ ያለው የመሰረታዊ ለውጥ ቦታ የሌለውና ራሱም በጥያቄ ምልልሱ ላይ አምኖ የተናገረው ነገር በመሆኑ እዚያው በዚያው የራሱን አስተሳሰብ በመቃረን ሳያስበው መጀመሪያ ላይ የተናገረውን ውድቅ አድርጓል። ስለሆነም ከዚህና ከመጀመሪያው አገላለጼ ስነሳ በአቢይ የአገዛዝ ዘመን ምንም ዐይነት ህዝብን የሚያረጋጋና ወደ ተሻለም ኑሮ እንዲያመራ የሚያደርገው የዕድገት መሰረት አልተጣለም። አገራችንም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊያብባት የቻለች አገር አልሆነችም።
በአጠቃላይ ሲታይ ዮናስ ብሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ስርዓት ባለውና ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ለመተንተን አልቻለም። የህወሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ራሳቸውን ችለው ስልጣን ላይ እንደወጡና “እሱ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው” ብሎ ከሚጠራው አስተሳሰብ፣ ቁጥጥርና ድርጊት ውጭ በአገራችን ምድር ፖለቲካ የሚባል ነገርና የኢኮኖሚ ፖሊሲንም ተግባራዊ እንዳደረጉና እንደሚያደርጉ ነው እየደጋገመ ሊነግረንና ሊያሳምነን የሞክረው። በመጀመሪያ ደረጃ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የሚባል ነገር የለም። እንደዚህም ብሎ መናገር ኢ-ሳይንሳዊ ነው፤ ፖለቲካዊ አጠራርም አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ በደንብ በተቀነባበረና በግልጽም የበላይነትን ያሰፈነና፣ በተለይም በጣም ዝቅተኛ የሆነ የምሁር አስተሳሰብ በሰፈነበት እንደኛ ባለ አገር ውስጥ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችን የበላይነት ያሰፈነና የእነሱንም ትዕዛዝ እንድንቀበልና ተግባራዊ እንድናደርግ የሚያስገድድ ሁኔታ እንደተፈጠረ መታወቅ አለበት። ዮናስ ብሩ የፖለቲካ ተንታኝ ነኝ የሚል ከሆነ ይህንን መሰሪህ አስተሳሰበና የበላይነትን የማስፈንና የጥሬ-ሀብትን የመቀራመት ሴራ በሚገባ መረዳት ነበረበት። ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው የታወቁ የፖለቲካ ተንታኞች የሚስማሙብት ነገር ነው። በመሰረቱ ኢትዮጵያችን በህወሃትና በአቢይ አህመድ የአገዛዝ ዘመን ወደ ቅኝ-አዙር የአገዛዝ ስር(Neo-Colonial Country) የወደቀችና ለውዝግብ ወይም ላለመረጋጋት የምታመመች አገር ለመሆን በቅታለች። ዮናስ ብሩ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ብሎ የሚጠራው በመሰረቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት የሚሰፍንበትና የእሱን ትዕዛዝ የሚቀበሉ ታዛዥና ታማኝ የሆኑ አገዛዞችን ስልጣን ላይ በማውጣት ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታን መፍጠርና ህዝቡም በፍርሃት እንዲኖር ማድረግ ነው። ዲሞክራሲያዊ ተቋማትም እንዳይገነቡና እንዳይስፋፉ በማድረግ በመንግስት የተደገፈና የሚካሄድ ጭቆና ማስፋፋት ነው። የአሜሪካንና የግብረ-አበሮቹም አካሄድ ለአንድ ህዝብና አገር የተሟላ ነፃነትን ማምጣት ሳይሆን የጌታና የሎሌ ስርዓት በመፍጠር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳይመጣ ማድረግ ነው። ስለሆነም ዮናስ ብሩ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው እያለ የሚጠራው አነጋገር በመሰረቱ ኢ-ሳይንሳዊና ፓለቲካዊ ያልሆነ ነው። ግራ የሚያጋባና በተለይም ታዳጊው ትውልድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ያለውን የኃይል አሰላለፍና የሚሸረበውን ሴራ በሚገባ እንዳይገነዘብ የሚያደርግ ነው።
ስለሆነም ወያኔና አቢይ አህመድ የራሳቸው የሆነ ነፃ የፖለቲካ ቲዎሪና የኢኮኖሚ ፖሊሲም የላቸውም። ዓለም አቀፋዊ የሚባሉ እንደነ IMFና የዓለም ባንክም የመሳሰሉ ድርጅቶች በዮናስ ብሩ አጠራር የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው የሚባለውን ጥቅም የሚያስጠብቁና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲስፋፋና ያልተስተካከለ ዕድገት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ናቸው። እንደተቀሩት የአፍሪካ አገሮችም ኢትዮጵያችንም የጥሬ-ሀብት አምራች ብቻ ሆና እንድትቀር ማድረግ ነው። እነዚህም ተቋማት የሚያራምዱት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚባለውን ነው። ይህ ዓይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ፖሊሲ ተብሎ ሊጠራ የማይችል አይደለም። በአንዳቸውም የካፒታሊስት አገር ውስጥ ተግባራዊ ያልሆነ ነው። ከ18ኛውና ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ተግባራዊ ይደረግ የነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ መርከንታሊዝም በመባል የሚታወቅ ነው። ይህም ፖሊሲ ሁለ-ገብ ሲሆን፣ በማንፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተና ለውስጥ ገበያ ዕድገት አመቺ የነበረ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከተማዎች፣ መንደሮች፣ የገበያ አዳራሾች በመንግስታትና በአንዳንድ ሀብታም ነጋዴዎች የሚሰሩ ነበሩ። በተጨማሪም መመላለሻ መንገዶችና፣ የኋላ ኋላ ላይ የባቡር ሃዲድ በመንግስታት ድጎማ ዕውቅ በሆነ መልክ በጣልቃ-ገብነት የሚሰሩና ለንግድ መስፋፋትና ለሰውም እንቅስቃሴ የሚያመቹ ነበሩ። እነዚህ ነገሮች አንድ ላይ ሆነ በመቀነባበር ሲገነቡ ብቻ አንድን ህዝብ ማስተሳሰርና ሁለ-ገብ ዕድገትንም ማምጣት የሚቻለው። አሜሪካንም በእነ አብረሃም ሊንከንና በእነ ሃሚልተን የአገዛዝ ዘመን ይህ ዐይነቱ ወደ ውስጥ ያተኮረ የአገር ግንባታና የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ ነበር ተግባራዊ ይሆን የነበረው። በዚህ መልክ በመንግስታት ጣልቃ-ገብነት ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊስ፣ የከተማዎችና የመንደሮች ግንባታ ሰፋ ካለ የኢፍራስትራክቸር ግንባታ ጋር በመጣመር ነው ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት ሊሆን የቻለውና የኋላ ኋላ ላይም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊዳብር የቻለው።
ወደ እነ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋ ስንመጣ የካፒታሊስት አገሮች በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ ተግባራዊ ያደረጉትን እንዳለ የሚፃረር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት የሚያደርጉት። ሰለ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስለህብረተሰብ ዕድገት ምንም ግንዛቤ የሌላቸው የአፍሪካ መንግስታትም የIMFን ምክር በመቀበል ነው ወደ ውስጥ ያተኮረና የመስራት ዕድል ለሚፈልገው ሰፊው ህዝብ መሰረት የማይሆንና የአገርን የውስጥ ገበያ በሁለመንታዊ መንገድ ሊያሳድግ የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ መቀመቅ ውስጥ የገቡት። የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና አገራችንንም ጨምሮ በዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመመራትና ተግባራዊ በማድረግ ነው የዕዳ ዕዳ ከፋይ ሆነው ለመቅረት የበቁት። በአንዳቸውም የአፍሪካ አገርና አገራችንንም ጨምሮ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆን አይታይም። ከተማዎችና መንደሮችም ስርዓት ባለው መንገድ ሲሰሩ አይታይም። አብዛኛው ነገሮችም ተግባራዊ የሚሆኑት በዋና ዋና ከተማዎችና በአካባቢው ነው። መዋዕለ-ነዋይም የሚፈሰው ሳይንስና ቴክኖሎጂን ለማዳበርና ለሰፊው ህዝብ የሚሆን ሰፋ ያለና ወደ ውስጥ ያተኮረ የአገር ውስጥ ገበያ እንዲገነባ ማድረግ ሳይሆን ሆቴልቤቶችንና የአውሮፕላን ጣቢያዎችን ለመስራትና ለማስፋፋት ነው። እነዚህ መስኮች ደግሞ ምርታማ ያልሆኑ (unproductive) ናቸው። የአገር ውስጥ ሀብትን፣ በተለይም በገበሬው ዘንድ የሚመረተውን በመምጠጥ ለዋጋ ንረት ምክንያት የሚሆኑ ናቸው። የመጨረሻ መጨረሻም በዚህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራሊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ያልተስተካከለ ዕድገት ነው የሚፈጠረው። ሰፊው ህዝብም ወደ ድህነት ዓለም ነው የሚገፈትረው።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ አቢይን ሰለፖለቲካና ስለኢኮኖሚ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም ብሎ ዮናስ ብሩ ሲናገር ነገሩን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማብራራት ነበረበት። በደፈናው ኢኮኖሚ ብሎም መናገር በፍጹም አይቻልም። በአውሮፓ የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ቢያንስ ወደ አምስት የሚጠጉ የተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሆነዋል። እነዚህም ፖሊሲዎች በጊዜው የነበረውን የአውሮፓውን የህብረተሰብ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ነበሩ። በመጀመሪያ ደረጃ ፊዚዮክራቲኪስ የሚባል የኢኮኖሚ ቲዎሪ ነበር። በዚህ ቲዎሪ መሰረት ገበሬው ብቻ ነበር ምርታማ ሆኖ የሚታየውና ትርፍ-ምርትም ያመርት የነበረው። በጊዜው የዕደ-ጥበብ ሙያና ማኑፋክቸሪንግ ያልዳበሩ ስለነበር በእርግጥም አብዛኛው ህዝብ በእርሻ ምርት ውጤት ላይ ነበር የሚመካው። ስለሆነም የፊዚዮክራቶች ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ትክክል ነበር ማለት ይቻላል። የኋላ ኋላ ላይ የዕድ-ጥበብ ሙያ ሲስፋፋና ሲዳብር ይህ ዐይነቱ ተጨማሪ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በእርሻውና በዕደ-ጥበብ ሙያ መሀከል መተሳሰር እንዲፈጠር አደረገ። ከውጭ ንግድና ከዚያ ከሚገኘው ትርፍ ጋር ተደምሮ ቀስ-በቀስ ለካፒታሊዝም የሚሆን መሰረት ተጣለ። አንዳንድ መንግስታትም እነ አዳም ስሚዝ ብቅ ከማለታቸው በፊት ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ ተገደዱ። በተለይም በጊዜው እንግሊዝ ቀድማ የሄደች ስልነበረችና የመርከንታሊዝምን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ጥሩ ውጤት ማማጣቷን የተመለከቱ አገሮች፣ ለምሳሌ እንደፈረንሳይ የመሳሰሉት፣ የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ ጀርመን ከ1871 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግና የባንኪንግን ሲስተም በማስፋፋት ኢኮኖሚውን ማሳደግ ቻሉ። ይህም ለካፒታሊዝም መስፋፋትና መዳበር፣ የኋላ ኋላ ላይ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲኖረው አመቺ ሁኔታ ፈጠረለት። ይህም ሁኔታ ለትላልቅ ኩባንያዎች መፈጠርና ለኢምፔሪያሊዝም መጠንሰስ መሰረት ለመሆን በቁ። ክዚያን ጊዜ ጀምሮ በሶስተኛው ዓለም፣ በተለይም በአፍሪካ አገሮችና እያደገና ወደ ኢምፔሪያሊዝም እየተቀየረ በመጣው የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች መሀከል ልዩ ዐይነት፣ በመሰረቱ የጌታና የሎሌ፣ እንዲሁም ግልጽ የሆነና ግልጽ ያለሆነ የጥሬ-ሀብት ብዝበዛና ግኑኘነት በመፈጠር፣ በዚያው መጠንም የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ለማደግ እንዳይችሉ ተደረጉ። አብዛኛዎችም የአፍሪካ አገሮችም የፖለቲካ ነፃነትን ተቀዳጁ ከተባለ በኋላ የብዝበዛውና የታዛዥነቱ ስርዓት ቀጥሏል። አፍሪካም በርስ በርስ ጦርነት የምትታመስና ሰላምም የማይሰፍንባት አህጉር ለመሆን በቅታለች።
ባጭሩ ለማለት የምፈልገው ዮናስ ብሩ ጊዜ ወስዶ ይህንን ጉዳይ በሰፊው ለማብራራት መቻል ነበረበት። ያለው አስተሳሰብ በጣም ውስን ስለሆነ፣ በተለይም በኒዎ-ሊበራል አስተሳሰብ የሰለጠነ ስለሆነ ዘለቅ ብሎ በመሄድ ነገሩን ለማብራራት አልሞከረም፤ አልቻለምም። ጋዜጠኛውም ችሎታ ስለሌው ጠለቅ ብሎ በመሄድና ጥያቄ በመጠየቅ ማብራሪያ እንዲያደርግ ዕድል አልሰጠውም። ጋዜጠኛው ዝም ብሎ ከመለፍለፍ በስተቀር ነገሮችን በማሳጠር ጥያቄ ብቻ ማቅረብና መልስም እንዲመለስለት ማድረግ ነበረበት። ይህም ማለት ምን ምን ዐይነት ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሆኑና፣ እነዚህም ለምን ለህዝባችንና ለአገራችን አስተማማኝ ሁኔታን ለመፍጠር እንዳልቻሉ እንዲያብራራ መጠየቅ ነበረበት።
ለማንኛውም ዮናስ ብሩ የፖለቲካ አመለካከቱ ምን እንደሆነና በምንስ የፖለቲካ ፍልስፍናና የኢኮኖሚ ሳይንስ እንደሚመራ ሊናገር አልፈለገም። ዝም ብሎ ብቻ በደፈናው ፖለቲካና ኢኮኖሚ እያለ አዳማጩን ግራ አጋብቶ ሄዷል። ቀኝ ይሁን ግራ ወይም ሌላ ነገር ይሁን በፍጹም የሚታወቅ ነገር የለም። ፍልስፍናዊ መሰረትም የሌለው ስለሆነ የሚሆነውን የማይሆነውን ነገር ነው የሚናገረው። ይህም ማለት ስርዓት ያለውና በአንዳች ሳይንሳዊ መሰረትና የአሰራር ዘዴ ላይ የተመሰረተ አተናተን አይደለም። ሰለአንድ አገር ፖለቲካ በሚወራበት ጊዜ በዚያ አገር ውስጥ ስለሰፈነው የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ(Power Relationship) ማንሳትና ከበስተጀርባው ሆኖ የአገራችንን ሁኔታ እንደሚያተረማምስ ግልጽ በሆነ መልክ ማስቀመጥ አለበት። ይህንን በሚመለከት ዮናስ ብሩ አንድ ጥሩ የተናገረው ነገር የአቢይ አህመድ አገዛዝ በጣም ጥቂት የሆኑ የኦሮሞ ኤሊቶችን ጥቅም የሚያስጠብቅና የእነሱን ጥቅም በማስጠበቅ ለብዙ ዓመታት ስልጣን ላይ ለመቆየት እንደሚፈልግ ነው። ይህም ማለት የአቢይ አህመድ አገዛዝ አብዛኛውንና እወክለዋለው የሚለውን የኦሮሞ ብሄረሰብ ጥቅሙን የሚያስጠብቅ አይደለም። ከድህነትና ከኋላ-ቀርነትም የሚያላቅቀውና የተሟላ ግለሰብአዊ ነፃነት እንዲያገኝ የሚያደርገው አይደለም። አቢይ አህመድ በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖርና የሚዝናና፣ በዚህም የመንፈስ ደስታ የሚሰማው ዘመናዊ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ነው። ይሁንና ይህ አገዛዝ ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር በብዙ ድሮች እንደተሳሰረና ሰፋ ያለ ጭቆና፣ በተለይም በአማራው ላይ ጦርነት እንደከፈተ በሚገባ መብራራት ነበረበት። አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣበት ከዛሬ ሰባት ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር ሰፋ ያለ ጭቆና ቢካሄድምና፣ በተለይም በአማራው ላይ ያነጣጠረ ጦርነት ቢካሄድም የአሜሪካን ኢምፔሪሊዝምና ግብረ-አበሮች አፋቸውን ዘግተው ተቀምጠዋል። ይባስ ብለው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አማካይነት በየጊዜው “የኢኮኖሚ ማሻሻያ” እየተባለ በመሰረቱ ጥገኝነትን የሚያባብስ ብድር ይሰጠዋል። በአንፃሩ በኢብራሂም ትራውሬ የሚመራው የቡርኪና ፋሶ አገዛዝ ለህዝቡ ጥሩ ነገር እየሰራ ባለበት ወቅት ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ዘመቻ እያደረጉበት ነው። ከ21 ጊዜ በላይ በተለይም በማክሮን የሚመራው የፈረንሳይ አገዛዝ የግድያ ሙከራ አድርጎበታል። ምግቡም በመመረዙ በስንት ጥረት ነው ከሞት ሊተርፍ የቻለው። ይህንን ያቀነባበረው የፈረንሳይ የስለላ ድርጅት ሲሆን ከተባባሪው ጋርም የቡርኪና ፋሶ ዋና ከተማ ኦጋዱጉ ውስጥ ተይዘዋል። ይሁንና ምግቡን ሰርቶ ያቀረበለት ሰው ካቀረበለት በኋላ በመሸሽ ላይ እንዳለ በተቀነባበረ መልክ ከፈረንሳይ የስለላ ድርጅት ጋር ከሚሰሩ ሰዎች በጥይት ተመቶ ህይወቱ አልፏል።
በአጠቃላይ ሲታይ ጉዳዩ በዚህ መልክ መታየት ሲኖርበት፣ ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ዮናስ ብሩ በእኛ አገር ውስጥ ፖለቲካ የሚባል ነገር እንደማይታወቅ መረዳት ነበረበት። በአገራችን ምድር ፖለቲካ ሲባል መሸወድ፣ ተንኮል መስራት፣ ማምታትና ሲያስፈልግም በአመጽ ላይ የተመሰረተ ዕርምጃ መውሰድ ነው። የከፋፍለህ-ግዛው ፖሊሲም በመከተል ዘለዓለማዊ ውዝግብ መፍጠር ነው። የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚባለው ነገር በመሰረቱ ሰላም እንዳይኖርና መቃቃር እንዲፈጠር በማድረግ የሰለጠነና ሲቪክ የሆነ ስራ እንዳይሰራ ማድረግ ነው። ይህም ዐይነቱ አካሄድ ከዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም ሴራ ውጭ ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም። ምክንያቱም ሰላም ባልሰፈነበት አገር ውስጥ የውጭ ኃይሎች እየገቡ እንደፈለጋቸው ስለሚፈተፍቱ ነው። ያም ተባለ ይህ ዮናስ ብሩ ምን ዐይነት ርዕይ እንዳለው በፍጹም አይታወቅም። አመለካከቱንም ግልጽ ማድረግ አልቻለም። እዚህ አውሮፓ ውስጥ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የየራሳቸው አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ሊበራል ነን ይላሉ። ሌሎች ደግሞ የክርስቲያን ፓርቲ አመለካከት ወይም ኮንሰርቫቲቭ ነን በማለት ይናገራሉ። ሌሎችም ኮሙኒስት ነን በማለት ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ። ሌሎችም እንደዚሁ ቀኝ ወይም ፋሺሽት ነን በማለት ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ። ዮናስ ብሩ የትኛውን መስመር እንደሚያራምድ ግልጽ አላደረገልንም። ይህን ማብራራት ያለበት ይመስለኛል። ምን ዐይነት ፖለቲካ እንደሚያራምድ ወይም ምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም እንዳለው ግልጽ ቢያደርግልን ኑሮ ከዚህም በላይ መተቸት ወይም ገንቢ አስተያየት መስጠት ይቻላል። ዝም ብሎ የፖለቲካ ተንታኝ ነኝ በማለት የሚሆነውን የማይሆነውን መናገርና መዘበራረቅ አዳማጩን ግራ ከማጋበት በሰተቀር የሚሰጠው ትምህርታዊ ጥቅም የለም። አብዛኛው ተመልካች ወይም አዳማጭ የማንበብና የመመራመር ልምድ ስለሌለው እንደ ዮናስ ብሩ የመሰለውን የዶክትሬት ዲግሪ የጨበጠውን ሰው ሲናገርና ሲሰማ ዕውነት መስሎት ሊቀበል ይችላል።
ስለሆነም ዮናስ ብሩም ሆነ ሌሎች የፖለቲካና ሰለኢኮኖሚ ፖሊሲም ትንተና ለመስጠት ሲሞክሩ በምን ፍልስፍናና ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴ ላይ ተመስርተው እንደሚናገሩ ግልጽ ማድረግ አለባቸው። የአሰራር ዘዴንም በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ብቻና ይህንን መሰረት በማድረግ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በተለያዩ ጊዜያት ስልጣንን የጨበጡ አገዛዞች ያራምዱ የነበረውንና የሚያራምዱትን ፖለቲካ የሚባለውንና ተግባራዊ የሚያደርጉትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሚገባ መተንተን ይቻላል። በደፈናው ፖለቲካና ኢኮኖሚ እያሉ ማውራቱ አዳማጩን ግራ ማጋባትና ማሳሳት ነው። የጋዜጠኛው መሳይ መኮንን የዩቱቭ ቻናል ትችት ማቅረቢያ ቦታ ስለሌለው ወይም ስለዘጋው እዚያው ላይ የራስን አስተያየት በፍጹም መስጠት አይቻልም። በተረፈ መሳይ መኮንን አንዳንዶችን ግራ የሚያጋቡትንና ከእሱ አስተሳሰብ ጋር የሚስማሙትን ብቻ እየጋበዘ ውዥንብር እንዲፈጠር እንደሚያደርግ መታወቅ አለበት። በዚህ አቀራረቡና አጠያየቁ አገራችንና ህዝባችንን የሚጠቅም ከመስለው በጣም ተሳስቷል። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
https://www.youtube.com/watch?v=k0Blvfgltdc