ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ ታቅዶብሻል” የሚለውን የአሳየ ደርቤን ቪዲዮ አዳመጥኩ፡፡ አብዛኛው መሃንዲሱ የተናገረው፤ ስራ ላይ ውሏል፤ ቀሪው አስፈሪ ነው፡፡
ዶክተር ማርቲን ሉዘር ኪንግ ባንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ስልጣኔና ሁከት/እልቂት ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ ለአንድ አገር የሚያዋጣው ሰላማዊ ትግል ነው፡፡ ሰላማዊ ህዝባዊ እምቢተኛነት የወቅቱ የሞራል ጥያቄ ሆኗል፡፡ የዚህ መሰረቱ ደግሞ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር ነው፡፡”
ዶር ኪንግ ጨምረው “እኔ ደፍሬ የምናገረው በየትም ቦታ ቢሆን ዜጎች በሙሉ በቀን ሶስት ምግብ በልተው ህይወታቸውን እንዲደግፉ፤ የትምህርት እድል ባህል ኑሯቸው አእምሮዎቻቸውን እንዲጎለምሱ፤ ሰብአዊ ክብር፤ እኩለነት እና freedom ኑሯቸው መንፈሳቸውን እንዲያረኩ ነው፡፡”
ይህ የዶር ኪንግ መልእክት እኛን በቀጥታ ይመለከታል፡፡ እሳቸው የመከሩትን ስራ ላይ ለማዋል መጀመሪያ ራሳችንን መለወጥ አለብን፡፡
የጋራ አገር አለን ካልን የምንጋራቸው መሰረታዊ እሴቶች ከምንለያይባቸው እንዲያመዝኑ የማድረግ ግዴታ አለብን፡፡ የትግራይ፤ የአማራ፤ የሶማሌ፤ የኦሮሞ ወዘተ ህዝብ እየተራበ እኔን አያገባኝም ካልን ማን ይደርስልናል?” የአማራ ህዝብ በድሮን ሌት ከቀን የሚደበደብ ከሆነ የምንጋራው ምንድን ነው? በልማት ስም ወገኖቻችን ከቀያቸው የሚፈናቀሉ ከሆነ አብሮነት እንዴት ይቻላል? ይህ ከልማት ጋር ይዛመዳል? የልማት ዋና ግቡ የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት ነው፡፡
ልንክደው የማንችለው ሃቅ ፊታችን ላይ ተደቅኗል፡፡ ህወሃት የኢትዮጵያን ህዝብ ዘላለም እርስ በእርሱ እንዲናከስ ያበረከተን ህገ መንግሥት በምንን አይነካም የሚሉት ነሃይሎች ዋናው ምክንያታቸው ማንን ስለ ጠሉና ለማምከን ስለ ፈለጉ ነው? ብለን ቢያንስ በችግሩ ላይ ለመግባባት ያልቻልነው ለምንድን ነው? አልበርት አይንስታይን “አንድን ነገር ለመፍታት የሚቻለው መጀመሪያ ችግሩን በሚገባ ስናቀርበው ነው” ያሉትን እጋራለሁ፡፡ የጋራ አገር አለን ካልን የጋራ መፍትሄ መርህ መከተል አለብን፡፡
“ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ” የሚለውን በመረጃ የተደገፈ ትንተና ከሰማሁ በኋላ ራሴን የጠየቅሁት ይህችን ሆነ ተብሎ በመፈራረስ ላይ የምትታይ አገር ማነው የሚታደጋት? የሚለውን ነው፡፡
አንድ አገር ሊከበርና ዘላቂነት ሊኖረው የሚችለው በሚገዛው መንግሥትና በህዝብ ደጀንነት ነው፡፡ ባአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በሁለቱም ዘርፍ እየገጎዳች ነው፡፡ ተቆርቋር የሌላት አገር ሆናለች እላለሁ፡፡
ጉድ የነገሰባትን ኢትዮጵያን ከውርደት ለማዳን ምን ይደረግ?
ግብ አንድ፤ ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ ግለሰቦችና ስብስቦች ትችቶችን ወደ ጎን ትተው ይህች አገር ሙሉ በሙሉ ከመፈራረሷ በፊት እንመካከር እና አማራጮች እናቅርብ ብንል፤
ግብ ሁለት፤ በግል የሚደረገውን ጥረት ሳንንቅ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ በአንድነት ሆነን የታፈነውን፤ የተጠቃውን፤ በአደጋ ላይ የሚገኘውን ህዝቧንና ኢትዮጵያን ለመታደግ ብንረባረብ፤
ግብ ሶስት፤ ህወሃትና ኦነግ ከጅምሩ የመገንጠል እቅድና ፍኖተ ካርታ የተቀበሉና እስካሁን ድረስ ከመርሃቸው ፈቀቅ ያላሉ መሆናቸውንና የዚህ አሉታዊ ውጤት የእርስ በእርስ ጦርነት፤ የኢኮኖሚ ውድመት፤ የዜጎች መፈናቀል፤ የኑሮ ውድነት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱን በጥናትና ምርምር ለለጋስ ድርጅቶች ብናቀርብ፤ ለምሳሌ ለዓለም ባንክ፤ አይኤምኤፍ፤ አይ ዲቢ፤ አቤቱታችን በአካል ለነዚህ ተቋማት ብናቀር፤
ግብ አራት፤ አብዝኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ቢጠየቅ በየትኛውም ኢትዮጵያ የአስተዳደር ብልሹነት_ጉቦ፤ ሙስና፤ አድልዎ፤ አፈና፤ እንዳለ ይናገራል፡፡ ይህንን ሃቅ ከተቀበልን፤ የኢትዮጵያ ምሁራን ከብሄራችን በላይ ለሁሉም ወገኖቻችን የቆምን መሆኑ በማሳየት ዛሬ ኢትዮጵያ መንግሥት አልባ መሆኗን በመረጃ ተደግፈን ለማቅረብ ብንደፍር፤
ግብ አምስት፤ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በውጭ እርዳታ የምትደገፍ አገር ናት፡፡ ለኔ አይዋጥልኝ ያለው ከሃያ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ርሃብተኛ ሆኖ፤ በቡግና (ወሎ) ወገኖቻችን በርሃብ እየተሰቃዩ በኮሪዶር ልማት ስም የሚባክነው ብዙ ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ከጀርባ ያለው ማነው? ብለን እንጠይቃለን፡፡
ምንም ልንክደው የማንችለው ከአምሳ ዓመታት የውጭ እርዳታ በኋላ ትውልድ አገራችን በምግብ አቅርቦት ራሷን አልቻለችም፡፡
የቀድሞው የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ዞሊክ እንዳሉት፤ “የህዝብ ድምጽና ተሳትፎ በጎደለበት አገር ዘላቂነትና ፍትሃዊ የሆነ እድገትና ልማት አይቻልም፡፡”
ይህ ማለት ድሃ ሆኖ የተወለደ ኢትጵያዊ ድሃ ሆኖ ይሞታል ማለት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ለሁላችንም አሳፋሪ መሆኑን በመረጃ እናቅርብ፡፡
ለማጠቃለል፤
“ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ” የሚለው ሰነድ ይህች አገር ወደማትመለስበት ደረጃ እያመራች መሆኗን ያሳያል፡፡ ለዚህ አመላካቾቹ፤
- ጦርነትበጦርነት መተካቱ፤ ይህ ጤናማነት አመራር አያሳይም፤ ድንቁርናነት ያሳያል፤
- በባጀት፤ በውጭ ምንዛሬ፤ በሃብት፤ በልማት፤ በሰላም ወዘተ የኢሚንት ያህል እውነት፤ ሃላፊነት፤ ተጠያቂነት ያለው አመራር አለመኖሩ፤ ሃሰተኛነት መንገሱ፤
- ለእርቅ፤ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ ለሰብአዊ መብት፤ ለዲሞክራሲ የሚታገሉት ሁሉ መታሰራቸው፤ መገደላቸው፤ አገር እንዲለቁ መደረጋቸው፤
- የሜድያ ቅቡለነት አለመኖሩ፤
- ምርጫዎች ለይስሙላ እንጅ ለዜጎች መብት ስኬታማነት አለማሳየታቸው፤ የሚቀጠልው ምርጫም በዚህ መንገድ ቢካሄድ ውጤቱ ተመሳሳይ መሆኑ፤
- የተሳሳተ ትርክት በመንግሥት ሜድያና በደጋፊዎች ሲተገበር ለህዝብ እና ለአገር ያለው አሉታዊ ውጤት በተደጋጋሚ መታየቱ፤
- ቀስ በቀስ የአማራውና የኦሮሞው ህዝብ ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲሸጋገር መገደዱ፤ ይህ ሂደት አገር አፍራሽ መሆኑ፤
- የእርቅና ሰላም ኮሚሽኑ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ አለመሆኑ እና የህዝብን እሮሮ ለማስተናገድ የማይችል መሆኑ፤
- የዓለም መንግሥታት፤ በተለይ አሜሪካ’፤ ለይስሙላ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ክማለት ውጭ ሁኔታው አገር ሊያፈርስ ይችላል የሚል ትችት ከማቅረብ መቆጠባቸው፤
- ሰፊው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በዘር እና በጥቅም ምክንያት መለያየቱ ይገኙበታል፡፡
ኢትዮጵያን ከዚህ ከከፋ አጣብቂኝ ለማውጣት በአንድነት የተደገፈ የፍትህ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው፡፡ አንዱ ተጠቂ ሌላው አጥቂ በሆነበት አገር ፍትህ ሊኖር አይችልም የሚሉት ብዙ ናቸው፤ አግባብ ያለው ትችት ነው፡፡
የኛ የመጀመሪያ ግዴታ በወገኖቻችን ላይ የሚካሄደውን አማራን ለይቶ የሚካሄደውን እልቂት (genocide) እንዲቆም ሃቁን ለመላው የዓለም ህዝብ በአንድነት ሆነን ማቅረብ ነው፡፡ አለያ አንድነት፤ አንድነት፤ አንድነት ብንል ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ የህዝብ ህይዎትና ደህንነት መቅደም አለበት፡፡
ሌላው ግዴታችን በጋራ ሆነን ገንቢ የሆኑ አማራጮችን—ስለ ህገ መንግሥት መሻሻል፤ ስለ ህዝብን ያማከለ ልማት፤ ስለ የውጭ ግንኙነት፤ ስለ ወጣቶች የስራ እድል፤ ስለ ሴቶች እውነተኛ እኩለነት ወዘተ ጥራት ያላቸውን ሰነዶች ለህዝብ ማቅረብ ነው፡፡
የችግሩን ክብደትና ጥልቀት ለመገንዘብ የሚከተሉትን ቪዲዎወች አዳምጡ፡፡
December 29, 2024