October 2, 2024
48 mins read

አረንጓዴ ልብ፣ ጥቁር ልብ፣ ሰይጣናዊ መንፈስ!

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

(መስከረም 21 2017) October1,  2024)

በጀርመን፣ በፍራንክፈርት አማይን በሚባል የታወቀ የፋይናንስና የባንክ ከተማ በወጣት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎችና ሰራተኞች የተቋቋመ አረንጓዴ ልብ(Green Heart) የመረዳጃ፣ የባህልና ከዚህም በመሆን አገር ቤት ውስጥ ችግር የገጠማቸውን ሰዎች የሚረዳ በህግ የተቋቋመ ማህበር አለ። ይህ ማህበር በአ.አ በሀምሌ ወር በ7፣ 2024 ቅዳሜ ቀን በተለይም ሙያ ያላቸውን አንዳንድ ኢትዮጵያውያንን   በመጋበዝ ከሙያቸውና ከዕውቀታቸው ልምድ አንፃር አንዳንድ ገለጻዎችን እንዲያደርጉላቸው ይጋብዛል። በተለይም ሰለ ኢኮኖሚክስ ትምህርትና አንድ ሰው ኢኮኖሚክስ ለመማር ከፈለገና፣ ትምህርቱንም ከጨረሰ በኋላ የስራ ዕድል ስለማግኘት ጉዳይ ገለፃ እንዲሰጥ ከተጋበዙት ሰዎች አንዱ እኔ ነበርኩኝ። ሰሚናሩ ከመጀመሩ በፊት ተጋባዥ የነበሩትና እንደዚህ ዐይነት ሰሚናር መካሄዱን የሰሙና እዚያው የተገኙት ታዳሚዎች ከተቀመጡ በኋላ የማህበሩ ሊቀመንበርና ይህንን ሰሚናር ያዘጋጀው አንድ ወንድማችን ሰለማህበሩ አመሰራረትና ዓላማ ከተናገረ በኋላ ንግግር ወይም ገለፃ እንዲሰጡ የተጋበዙት ሰዎች እንደ አቀማመጣቸው ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ መድረኩን ይለቃል።

ንግግር ወይም ገለፃ እንዲያደርጉ ከተጋበዙት ሶስት ሰዎች ውስጥ አንዱ ሃኪምና የራሱም ክሊንክ ያለው ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ በክሊኒኩም ውስጥ ብዙ ሰዎችን ቀጥሮ እንደሚያሰራ ይነግረናል። ክዚያ በፊት እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረድን እንዳሰለፈና፣ በተለይም በጀርመን ምድር ለመማርና ትምህርቱንም ካጠናቀቀ በኋላ ስራ ተቀጥሮ ለመስራት የግዴታ የጀርመንኛ ቋንቋን በሚገባ ማወቅና መረዳት እንደሚያስፈልግ ይነግረናል። በጥሩ የአማርኛ ቋንቋ ሰፋ ያለ ገለፃ ካደረገ በኋላ የጋበዘንን ማህበር ይህንን አረንጓዴ ልብ የሚለውን ስም እንዴት እንደያዘ በመገረም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚመላለስበት ጊዜና አንዳንድ ሆስፒታሎችንና ክሊኒኮችን በጎኘበት ወቅትና፣ ከዚያም አልፎ በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ ሲመለከት ኢትዮጵያ ውስጥ አረንጓዴ ልብ ሳይሆን ጥቁር ልብ ያለው ሰው እንደተስፋፋ በማዘን ይነግረናል። በተለይም በሆስፒታሎችና በክሊኒኮች አካባቢ በሽተኞችን ማመናጨቅና መናቅ የተለመደ መሆኑን ሲነግረን አገራችን በሁሉም አኳያ የዘቀጠች መሆኑን መረዳት ይቻላል። ውድ ወንድማችን ሊለን የፈለገው እሱ እዚህ ጀርመን ምድር ወደ አርባ ዓመት ያህል በትምህርትና በስራ ዓለም ውስጥ በነበረበትና ባለበትም ዘመን ያለመደውን ወይም ያላጋጠመውን እዚያ የመንፈሳውያን አገር ተብላ በምትታወቀው ኢትዮጵያችን አረመኔነት ተስፋፍቶ ሲመለከት እጅግ ያዘነ መሆኑን ካነጋገሩና ከፊቱም ገጽታ መረዳት ይቻላል።

ውድ ወንድማችን የተመደበለትን ሰዓት በጥሩ ማብራሪያ ከደመደመ በኋላ ተራው የእኔ ነበር። ራሴን በመጠኑም ቢሆን ካስተዋወቁኝ በኋላ ወደ ዋናው ቁምነገር ከመግባቴ በፊት ውድ ወንድማችን ጥቁር ልብ ባለው አነጋገር ላይ ትንሽ የራሴን አስተሳሰብ ለማከል ተገደድኩኝ። እንደሚታወቀውና ለማብራራት እንደሞከርኩት ጥቁር የሚባለው ነገር አብዛኛውን ጊዜ ከመጥፎ ነገሮች ጋር ስለሚያያዝ በእኔ ግንዛቤና ዕምነት ጥቁር ልብ ከማለት ይልቅ ሰይጣናዊ መንፈስ ብለን ብንጠራው ይሻላል በማለት፣ በመቀጠልም ይህ ሁኔታ እንዴት በዚህ መልክ ሊገለጽ ወይም ሊታይ እንደቻለ አነስ ያለ ማብራሪያ ለመስጥት ሞከርኩኝ። በተለይም በጀርመን ምድር አንድ ሰው በአውቶቡስም ሆነ በትራም የመጓጓዣ ቲኬት ሳይገዛና ሳያስመታ የሚጓዝ ከሆነ በጥቁር ሄደሃል ተብሎ ብዙ ገንዘብ እንዲከፍል ይቀጣል። የስራ ፈቃድ ሳይኖራቸውም በተለያዩ ቦታዎች፣ በተለይም በግንብ ስራ ተሰማርተው የሚሰሩ ሰዎችም ሲገኙና የስራ ፈቃድም የማያሳዩ ከሆነ በጥቁር ሲሰራ ተያዘ ይባላል። ሌላም በአገራችን የተለመደ አነጋገር አለ። እንደዛሬው ትንሽ “ሰልጠን ባላልነበት ዘመን”  በጥንቱ ዘመን ጥቁር ሁልጊዜ ከመጥፎ ነገር ጋር ነው የሚያያዘው። አንድ ሰው በጣም በጠዋት በሩን ከፍቶ ሲሄድ የመጀመሪያው  የሚያጋጥመው ጥቁር መልክ ያለው ሰው ከሆነ ቀኑን ሙሉ እንደማይቀናው አድርጎ ነው የሚቆጥረው። ቀላ ያለ ሴትም ሆነ ወንድ ልዩ ቦታ ይሰጣቸዋል። ከዚህም በላይ ወደ ቤተክርሲቲያን አካባቢ ስንሄድ  ደግሞ መልአኮች በሙሉ ቀላ ያለ በፈረንጅኛው አጠራር ደግሞ ነጭ መልክ ሲኖራቸው ከስራቸው ያለው እንደሰይጣን ጋደም ብሎ የሚገኘው ደግሞ በጣም የጠቆረ ነው። ሰይጣን የሚባል ነገር ካለ ለብዙዎቻችን ግልጽ ያልሆነልን ነገር ይህን ዐይነቱን ጠቁር የሚባለውን የሰው ልጅ ሰይጣናዊ አስመስሎ መሳል ፈረንጆች የፈጠሩት ነገር መሆኑን ነው። ለቆንጆ ነገር ሳይሆን ለመጥፎ ነገር የተፈጠረ ብቻ ነው እንደማለት ነው። ጥቁር ሲባል ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂዎች፣ ውብ ውብ የሆኑ ከተማዎችን በመገንባት የተሻለ ኑሮ ለመኖር የማይችል የተረገመ ፍጡር ነው። አኗኗሩ ሁሉ የተዝረከረከና ርስ በርሱ ከመገዳደል በስተቀር የሚሰራው ሌላ ፋይዳ ያለው ነገር የለምም እንደማለት ነው።

ወደ መሰረተ ሃሳቡ ጋ እንምጣ። ውድ ወንድማችን በአገራችን ምድር ጥቁር ልብ ያለው፣ ወይም አረመኔያዊ ሰው ተስፋፍቷል ሲል ነገሩን ክሁኔታዎች መለወጥ ጋር በማያያዝ ጠጋ ብለን እንመልከተው። በሰሚናሩ ላይም ለማብራራት እንደሞከርኩት ይህ ዐይነቱ የደነደነ ወይም አረመኔያዊ ልብ ያለው ሰው ሊስፋፋ የቻለው በተለይም አብዮቱ ከፈነዳና አብዛኛዎች ነገሮች በአርቆ አሳቢነትና በምርምር፣ እንዲሁም በመጠናት ሳይሆን በግብታዊነት ተግባራዊ መሆን ከጀመሩ ጊዜ ወዲህ ነው። የተወሰነ የሶስዮሎጂና የሳይኮሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው ሊገነዘብ የሚችለው በተለይም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሰዎች ወይም በአንድ አገር ኗሪ ህዝብ ላይ ሊያስከትሉ የሚያስችሉትን  አሉታዊ ተፅዕኖዎች ሳይጠኑ ዝምብለው በግብረወጥ ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ የሰዎችን አስተሳሰብ አብዛኛውን ጊዜ በመጥፎ እንደሚቀይሩት የታወቀ ጉዳይ ነው። በአንፃሩ በደንብ ተጠንተው ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎች ደግሞ በተለይም የታዳጊውን ትውልድ መንፈስ በጥሩ ወይም በቆንጆ መልክ ሊቀርጹት እንደሚችሉት የታወቀ ጉዳይ ነው።  የሰዎች ባህርይ ወደ መጥፎ መቀየር  በአገራችን ምድር ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች የሚታይና ለህብረተሰብ ውዝግብ መንገድ የከፈተና የሚከፍት ነው። በተለይም ባህላዊ የአኗኗር ዘዴ ወይም ትራዲሽናል ብለን የምንጠራቸው ከካፒታሊዝም በፊት የነበሩ ስርዓቶች በሰፈኑበትና አብዛኛው ሰው በመንደር ውስጥ በሚኖርበት ዘመን የሰውም አኗኗር የተሰበጣጠረ ባለመሆኑና ርስ በርስም ስለሚተዋወቅ አንደኛው ሰው በሌላው ሰው ላይ ይህን ያህልም ጉዳት አያደርስም ነበር ። በተለይም ሃይማኖት በተስፋፋበት አካባቢዎች አብዛኛው ኗሪ ህዝብ እግዚአብሄርን ስለሚፈራና ጭንቅላቱም በሃይማኖት ስለሚያዝ ሰይጣናዊ መንፈስ ወይም ጥቁር ልብ በመስፋፋት መጨካከን አይታይም ነበር። ነገሩ እየተበላሸ የመጣው ነገሮች በግባታዊ መልክ ሲካሄዱና አንዳንዱም የተሻለ ዕድል ለማግኘት ሲል የሚኖርበትን አካባቢ ጥሎ ወደ ከተማዎች ሲሰደድና የተመኘውን ጥሩ ዕድል ቶሎ የማያገኝ ከሆነ ወደ አልባሌ ነገር ላይ ይሰማራል። ይህ ሁኔታ በእንግሊዝ አገር በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን የተለመደና፣ በተለይም እንደለንደን፣ ማንቼስተርና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች የተተከሉባቸው ቦታዎች የተስፋፋ ነበር። እዚህም የምኖርበት የበርሊን ከተማም ውስጥ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ በጊዜው ሰፋ ያለ የኢንዱስትሪ ተከላ ይካሄድ ስለነበር አረመኒያዊ ተግባር የተስፋፋ ነበር። ከሁኔታዎች መመሰቃቀል የተነሳና ራሳቸውም የኢንዱስትሪ ባለቤቶች ከአውሬነት ባህርያቸው ያልተላቀቁ ስለነበሩ አረመኔያዊነት የተስፋፋ ነበር፤ የሰው ልጅ ማድረግ የሌለባቸውን ነገሮች ሁሉ እያደረገ በተለይም በሰላም ለመኖር በሚፈልገው ህዝብ ላይ ብዙ ጉዳት ያደርስ እንደነበር በመጽሀፍ ተመዝግቦ ይገኛል።

ወደ አገራችን ስንመጣ በፊዩዳሊቱ ኢትዮጵያ ዘመን አነሰም በዛም የሰው ከሰው ግኑኘነት ጥሩ ስለነበርና፣ በተለይም አንደኛው ሌላውን በሚያከብርበትና ትላልቅ የሚባሉ ሰዎችም በሚከበሩበት ወይም እንደ ግርማ ሞገስ በሚታዩብት አካባቢ አብዛኛው ነገር ከቁጥጥር ውጭ የወጣ አልነበረም። አንደኛው ሌላውን ስለሚፈራ አንዳንድ ነገሮችን ተሸሽጎ  የሚያደርግ እስካልሆነ ድረስ በይፋ የሚደረግና ህዝብንም ይህን ያህል የሚያስቀይም ወይም የሚያሳዝን ነገር ሲሰራ  አይታይም ነበር። ይሁንና ግን ወደ ከተማዎች ስንመጣ በተለይም ዘመናዊነት የሚባለው በተወሰነ የኢንዱስትሪ ተከላዎች፣ በፍጆታ አጠቃቀምና ዘመናዊ በሚመስሉ ቤቶች የሚገለጸው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ በተለይም የተሻለ ኑሮ አገኛለሁ ብሎ ወደ ከተማ የሚሰደደው የሚፈልገውን ነገር ማግኘት ካልቻለ አንዳንዱ ወደ አልባሌ ስራዎች በመሰማራት በሰው ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በዚያን ዘመን ነው ቀደም ብለው ያልተለመዱ ነገሮች፣ ለምሳሌ ማጅራት መቺነትና ሌብነት እንደ ህብረተሰብአዊ ኖርም መሆን የጀመሩት።  በተጨማሪም ማታለልና መሸወድ የሚባሉት ቃላቶች እየተለመዱ የመጡት ዘመናዊ የሚባለውና በተሳሳተ መልክ የተተረጎመው የዕድገት ፈለግ  ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። እዚህ ላይ ለማለት የፈለግሁት ሁኔታዎች በደንብ ሳይጠኑ አንዳንድ ፖሊሲዎች ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ እንደዚህ ዐይነት ነገሮች መከሰታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይም የፖለቲካ አወቃቀሩ በዘልማዳዊ በሆነ መልክ በተዋቀረበትና ሰፋ ያለና የጠለቀ ዕውቀት የሌላቸው ሰዎች ስልጣን ላይ ቁጥጥ በሚሉበት ጊዜ አንድ ህብረተሰብ ከታች ወደ ላይ በስርዓት እንዴት መገንባት እንዳለበት ስለማያውቁና፣ በተጨማሪም የሰለጠነና የተማረ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበት አገር ውስጥ ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ልዩ ዐይነት የጭካኔ ዐይነት ክስተትን እንዲታዩ ያደርጋሉ። ይሁንና ግን በአጠቃላይ ሲታይ በዘመነ ፊዩዳሊዝም ዘመን አፄው ከስልጣን ላይ እስከተወገዱበት ጊዜ ድረስ ሁኔታው ይህንን ያህልም የከፋ አልነበረም። ሁኔታው እየተበላሽ የመጣውና አረመኔያውነትም ህብረተስብአዊ ኖርም እየሆነ የመጣው በአብዮቱ ወቅት ነው ማለት ይቻላል።

አብዮት የሚባለው ነገር በተበላሸ መልክ በመተርጎሙና አንዳንድ ለስልጣን የሚቋምጡ ሰዎች ሁኔታውን ማራገብ ሰለጀመሩ ያ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ የታሰበው አብዮት በንዑስ ከበርቴው ስግብግብነት የተነሳ በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶችና የተማሩ ሰዎች ህይወታቸው እንዲቀሰፍ ተደረገ። እነዚህ ለስልጣን ይቋምጡ የነበሩ ግለሰቦችና ቡዱኖች ደግሞ ከሰማይ ዱብ ያሉ ሳይሆኑ ባለማወቅ ተግባራዊ በሆነው ፖለቲካዊ፣ ሚሊታራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ክንዋኔ ውስጥ ያደጉና መንፈሳቸውም በደንብ ያልታነፀ ነበር። አንዳንዶችም የውጭ ኃይሎችን ተልዕኮ ለማሟላት ሲሉና በደመነፍስ በመመራት በወንድሞቻቸውና በእህቶቻቸው ላይ በመነሳትና በማሳደድ የብዙ ሰዎችን ህይወት ለመቅሰፍ ችለዋል። በታሪክ ውስጥ እንደታየውና እንደተረጋገጠው በማንኛውም ህብረተሰብ ውስጥ ሰቆቃን የሚያስከትሉ ለስልጣን የሚቋምጡ ኃይሎች ናቸው።  ሲግሙንድ ፍሮይድ በናዚ ዘመን የተከሰተውን የጥላቻ ቅስቀሳና ግድያ ከተመለከተ በኋላ የተገነዘበው ነገር በእንደዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የሰዎች ዕውነተኛ ባህርይ ይታያል። አንዳንዶችም ሁኔታዎችን በመጠቀም ከውስጣቸው ውስጥ የተደበቀውን መጥፎ ነገር ወደ ውጭ በማውጣት አሰቃቂ ስራን ይሰራሉ። በእኔ ዕምነት በተለይም ጭንቅላት በሚገባ ባልተገራበት ጊዜና አንዳንዶችም ከህብረተሰብ ውስጥ ተገልለው በሚኖሩበት ጊዜ መጠጊያ የሚያደርጉት አንዳች ዐይነት ርዕዮተ-ዓለምን  መሸሸጊያ በማድረግና እሱን በማራገብ ነው። ሂትለርና ተከታዮቹ በይሁዲዎች ላይ ለመነሳት የቻሉት የናዚን ርዕዮተ-ዓለም ሽፋን በማድረግና ለማንኛውም ህብረተሰብአዊ ቀውስ በሙሉ አይሁዲዎችን ተጠያዊ በማድረግ ነው። አብዛኛዎች ርዕዮተ-ዓለምንና ወይም ጎሳን ተገነ አድርገው የጥላቻ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሰዎች ጭንቅላታቸው የተበላሸና ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ በጥላቻ አስተሳሰብ የተመረዘ ነው። የሂትለርን ባዮግራፊ ላነበበ ሰውየው በጥሩ ሁኔታ ውስጥ ያላደገና በተለይም ስዕል ለመማር ፈልጎ በጊዜው ለመግባትና ለመማር የፈለገበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ችሎታው የማይፈቅድ ስለነበር የፈለገውን ትምህርት መማር አልቻለም። እንደአጋጣሚ ሆኖ የዴፓርትሜንቱ ኃላፊ ይሁዲ ስለነበር እሱና የእሱ የቅስቀሳ ሚኒስተር የነበረው ጎበል የሚባለው ቂምበቀል በመያዝ የጥላቻ ቅስቀሳን ያካሂዳሉ። ሂትለርም የተጠቀመው በጊዜው የነበረውንና ከትውልድ ትውልድ የተላለፈውን በፕረሺያ አገዛዞች የተዋቀረውን እጅግ ወደ ኋላ የቀረ የመንግስት መኪና፣ የሚሊታሪና የስለላ መዋቅር በመጠቀም ነው አረመኔያዊ ድርጊቱን ሊፈጽም የቻለው። ቬይና ከተማ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንደ አጋጣሚ በሚመላለስበት ጊዜ ስለዘረኝነት ከተጻፈ መጽሀፍም ጋር በመጋጨት የአርያን ዘር የተሻለ መስሎ ታየው። ይሁንና ግን በጊዜው ይሁዲዎች ለጀርመን ስልጣኔ፣ ለአውሮፓውና ለዓለም ህዝብ ሁሉ የሚሆን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፈለጎችን የቀደዱና ብዙ መጽሀፎችንም የጻፉ እንደነበሩ በፍጹም አልተገነዘበም፤ ለጀርመንም የካፒታሊዝም ዕድገት ከፍተኝ አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ አልተረዳም። ከፍልስፍና፣ እስከስነ ጽሁፍ፣ ከሙዚቃና እስከማቲማቲክስና ሌሎች ለዕድገት በሚጠቅሙ ነገሮች ውስጥ ሁሉ የዩሂዲዎች አስተዋፅዖ ከፍተኛውን ቦታ የያዘ ነበር። ይህን ለመረዳትና የስልጣኔንም አመጣጥ ለመገንዘብ ያልቻለው ሂትለርና ተከታዮቹ የይሁዲንና የሌሎችን ዝቅተኛ የሚሏቸውን ዘሮች ሁሉ ለማጥፋት ጨክነው ተነሱ። ከዚያም አልፈው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ሁለተኛውን ጦርነት በማወጅ በአጠቃላይ በአውሮፓ ምድር ብቻ ለሃምሳ ሚሊዮን ህዝቦች መሞት ምክንያት ለመሆን በቅተዋል። በሶቭየትህብረት ብቻ ወደ 27 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ህይወቱን ለማጣት ችሏል። በሂትለር ወረራም ብዙ የአዎሮፓ ከተማዎች ወድመዋል። ሂትለርም እንደዚህ ዐይነት አረመኔያዊ ድርጊት ሲፈጽም የመጨረሻ መጨረሻ በአሸናፊነት በመውጣት የጀርመንን የበላይነት የሚያጸድቅ መስሎት ነበር። ይሁንና ግን በስታሊን የሚመራው የሶቭየት ህብረት አገዛዝ  ያለ የሌለውን ጦር በማዘጋጀትና አዳዲስ ታንኮችን በማምረትና በጊዜው በነበረው ኃይለኛ ክረምት በመታገዝ የሂትለርን ወታደር ሊያዳክመውና ከራሺያም ምድር ሊያሰወጣው ቻለ። የመጨረሻ መጨረሻም በተዘዋዋሪ ስልጣን ላይ ያወጡት የአሜሪካንና የእንግሊዝ አገዛዞች ለእነሱም የማይተርፍ መስሎ ስለታያቸው በመተባበር ሊያሸንፉት ቻሉ። የእንግሊዝና የአሜሪካን የጦር አውሮፕላኖችም አብዛኛውን የጀርመን ከተማዎችና ስታርቴጂክ ቦታዎች እንዳለ አወደሟቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ የጀርመን ህዝብ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንዲወድቅና ለረሃብም እንዲጋለጥ ተደረገ። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳና ታሪክም የሚያረጋግጠው አብዛኛውን ሰው ለመግደል የሚቋምጡና ጭካኔንም የሚያስፋፉት በተለይም ከንዑስ ከበርቴው መደብ የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ሌሎች ሁኔታው አስገድዷቸው ሰተት ብለው በመግባት የጭካኔው አንድ አካል በመሆንና በደመ-ነፍስ በመመራት ለብዙ ሰዎች መቀሰፍ ምክንያት ይሆናሉ። የእነዚህ ሰዎች መንፈስም በሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተለከፈ ስለሆነ ሰውን በመግደልና በማሰቃየት ብቻ ደስታን የሚጎናጸፉ ይመስላቸዋል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ በዛሬው ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተስፋፋባቸው ዘመን ልዩ ዐይነት መልክ ይዞ በመውጣት አብዛኛው ምስኪን የዓለም ህዝብ ሊረዳው እንዳይችል ተደርጓል። በተለይም የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችና የስለላ አውታሮች በመዘርጋት የበላይነትን ማረጋገጫና የሰውንም ህይወት መቅሰፊያ ሊሆኑ በቅተዋል። በአንድ በኩል ቴክኖሎጂያዊ ዕድገት ወይም ምጥቀትና፣ በሌላ ወገን ደግሞ የሰው ልጅ አስተሳሰብ አንድ ላይ በመሆን አብረው ለመሄድ እንዳልቻሉ እንረዳለን። በሌላ አነጋገር፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂያዊ ዕድገት ካለፉት መቶዎች ዓመታት ጋር ሲወዳደር የሰው ልጅ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ቢገኝም በተለይም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ልቡ ርህሩህ ሊሆን አልቻለም፤ አርቆ አሳቢም ለመሆን በፍጹም አልቻለም።

ወደ አገራችን ስንመጣ ከአብዮቱ ጀምሮ በተከታታይ ተግባራዊ የሆኑቱን ነገሮች በሙሉ ስንመለከት በአወቁኝ ባይነትና በደመ-ነፍስ በመመራት የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው። አብዛኛዎቹ ስልጣንን የተቆናጠጡትና ከውጭ ሆነው የግዴታ ስልጣን ላይ ለመውጣት ይታገሉ የነበሩ በሙሉ የጠለቀ የሶስዮሎጂ፣ የስነ-ልቦና፣ የታሪክ፣ የፍልስፍናና የተፈጥሮ ሳይንስ ዕውቀት የሌላቸውና በምሁራዊ የክርክር ሂደት ውስጥ ያላለፉ ስለነበሩ ስለአገርና ስለህዝብ የጠለቀ ዕውቀት አልነበራቸውም። ፖለቲካ የሚባለውንም ነገር ትርጉሙን በፍጹም የተረዱና የማይረዱ ነበሩ። ፖለቲካ ሲባል ሳይንስ መሆኑን ያልተገነዘቡና ማንኛውም ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ፖሊሲ በሙሉ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የእያንዳንዱን ሰው ህይወት እንደሚነካ የሚገነዘቡ አልነበሩም። ስለሆነም ፖለቲካ ሲባል ከፍተኛ የሞራልና የስነ-ምግባር ኃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን በፍጹም አልተረዱም። አብዛኛዎችም ሰው መሆናቸውን ያልተረዱና የማይረዱም በመሆናቸው እንደሰው ልጅ ሊኖራቸው የሚገባቸውን ልዩ ልዩ ባህርዮች በሙሉ በፍጹም አልነበራቸውም፤  የላቸውምም ማለት ይቻላል። ለሌላው ርህራሄን የማሳየትና በመጥፎ ድርጊታቸውም የመጸጸትን ባህርይ የማያውቁ ነበሩ፤ ናቸውም። መንፈሳቸውም ህሊና-ቢስ በመሆኑ የተነሳ ለእነዚህ ዐይነት ሰዎች ሰውን ማሰቃየት፣ መግደልና መናቅ እንደኖርማል ነገር ሆኖ ነው የሚታያቸው።

ስለሆነም አንድ ቦታ ላይ ቆም ብሎ በማሰብ መጥፎ ድርጊታቸውን የመጠየቅ ችሎታ የላቸውም ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ ሲታይ አብዛኛውን ጊዜ ከርዕዮተ-ዓለም ጋር በማያያዝ የሚራባው ወሬ የሰዎችን ባህርይ ካለመረዳት የተነሳ በመሆኑ ነው። አንድ ሰው አንድን ርዕዮተ-ዓለም እከተላለሁ ስላለ ብቻ የእሱን ውስጣዊ ፍላጎት ማየትና ባህርይውንም በማንበብ ፍርድ መስጠት አይቻልም። አብዛኛውን ጊዜ አንድን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወይንም ሃይማኖትን ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በመለወጥ ብዙ ሰዎችን የሚገድሉ ጭንቅላታቸው በጥሩ ዕውቀት ያልተኮተኮተና በልጅነታቸውም ጨወታንና ፍቅርን የማያውቁ ናቸው። አብዛኛዎችም በልጅነታቸው በእግራቸው ያልተጓዙ፣ ዛፍና ተራራ ላይ ያልወጡና ከልዩ ልዩ ጨወታዎች ጋር የማይተዋወቁ ናቸው። በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስልጣንን የተቆናጠጡ ፖለቲከኞች ነን የሚሉ የልጅነት ጊዜያቸውን በሚገባ አጣጥመው ያላደጉና ከችግርም ጋር የማይተዋወቁ በመሆናቸው ጭንቅላታቸው በሚገባ የዳበረ አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ነው በዓለም አቀፍ ደርጃ ጭካኔ ሊስፋፋ የቻለው። ይህንን አረመኔያዊ ድርጊት ደግሞ ካፒታሊዝም በአጠቃላይና በተለይም የአሜሪካን ካፒታሊዝም ጥልቀት በመስጠት አረመኔያዎዊ ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲስፋፋ ለማድረግ ተችሏል። ስለሆነም ትርፍን ማካበትና ለስልጣን መስገብገብ ወደ ርዕዮተ-ዓለምነት በመለወጥ በአሜሪካን የፖለቲካ ኤሊት የሚመራው የልዩ ልዩ አገሮች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት  ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ ማድረግና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ከቀየው ማፈናቀል ስራዬ ብሎ በመያዝ የታሪክን ሂደት በማጣመም ላይ ይገኛል። በአጭሩ የአሰቃቂ ድርጊቶችንና የጦርነቶችን ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ አብዛኛው አሰቃቂ ነገሮችና ግፎች በሙሉ የተፈጹሙት ከሃይማኖትና ከካፒታሊዝም ጋር በመያያዝ ነው። በ17ኛው ክፍለ-ዘመን በፕርቴስታንትና በካቶሊክ መሪዎች መሀከል ለሰላሳ ዓመት ያህል የተካሄደው እልክ አስጨራሽና በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ  ለሁለት ሶስተኛው የአውሮፓ ህዝብ እልቂት ምክንያት የሆነው የርስ በርስ ጦርነት የተቆሰቆሰው ሃይማኖት ዋናው ሽፋንም ቢሆን የበላይነትን ለመያዝ የተደረገ ጦርነት ነው። ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ በማድገና ወደ ሞኖፖሊያዊነት ባህርይ መለወጥ ሲጀምር ጦርነትም ዋናው መገለጫው ሊሆን በቅቷል። ራሱ የካፒታሊዝም አፀናነስ ሰውን በማፈናቀልና በመበዝበዝ ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም ካፒታሊዝምና ጦርነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህም ማለት ካፒታሊዝም ካለጦርነት ሊኖርና የበላይነቱንም ለማስፈን ስለማይችል የሰውን ልጅ ፍዳ እያሳየ ይቀጥላል ማለት ነው።

ዛሬ በአገራችን ምድር የተስፋፋውን አረመኔያውነትና ወይም የጥቁር ልብ መስፋፋት፣ ወይም ደግሞ ሰይጣናዊ ባህርይ  የንዑስ ከበርቴው መገለጫ መሆን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከአሜሪካን ካፒታሊዝም ጋር የተያያዘ ነው። በተለይም የዘመናዊ ትምህርት የሚባለውና መንፈስን እንዳለ የሚሟጥጥ የትምህርት አሰጣጥ በአገራችን ምድር ሰተት ብሎ በመግባት ፈጣሪና አገር ገንቢ፣ እንዲሁም ልበ-ርህሩህና ለሌላው አሳቢ ከመሆን ይልቅ ቀስ በቀስ ዛሬ የምናየውን አረመኔያዊ ባህርይን ለማስፋፍት በቃ። ይህ ሁኔታ በተለይም ሀወሃት ወይም ወያኔ የሚባለው በአሜሪካንና በእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም በመታገዝ ስልጣን ላይ የወጣው  ኃይል የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ሳይሰራ በሀብት የሚያደነድነውና ጭንቅላቱንም እንዲሰለብ የሚያደርገው ኒዎ-ሊበራሊዝም የሚባለው “የኢኮኖሚ ፖሊሲ” ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጀምሮ ጥልቀትን እያገኘ በመምጣት የተወሰነው የፖለቲካ፣ የሚሊተሪ፣ የኢኮኖሚና የስለላ ኤሊት መገለጫ ሊሆን በቅቷል።  ይህ ዐይነቱ ኤሊት የተጎናፀፈውን ኃይል ተገን በማድረግ በሀብት ዘረፋ ላይ በመሰማራትና ይህንን ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ልዩ ዐይነት  የፍጆታ አጠቃቀምን በመልመድ በተለይም ለታዳጊው ትውልድ መጥፎ ምሳሌ እየሆነ በመምጣት በዚያው መጠንም አረመኔያዊነትን ማስፋፋት ዋናው ተግባሩ ሊሆን በቅቷል። መንፈሱ የተሰለበና ልቡም የደነደነ በመሆኑም መደረግና መደረግ በሌለባቸው ነገሮች መሀከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አይችልም።  ባጭሩ በአገራችን ምድር በተለይም በተወሰነውና ተማርኩኝ ወይም ሰለጠንኩኝ በሚለው የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ከሁኔታዎች በተበላሽ መልክ መለወጥ ጋር የሚያያዙ ናቸው። በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲው ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት ስለሌለው አገርን ሁለ-ገብ በሆነ መልክ የመገንባትና ህዝባዊ ሀብትን በመፍጠር ሰፊው ህዝብ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር የሚያደርግ አይደለም። በአንፃሩ ያልተስተካካለ ዕድገትንና ብልጭልጭ የሚሉ ነገሮች እዚህና እዚያ በመትከል የኑሮን ትርጉም የሚያሳጣ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ቀስ በቀስም ባህልን የሚደመስስና በሰዎች መሀከል ያለውን የርስ በርስ ግኑኝነት የሚበጣጥስ በመሆኑ አለመተማመንን የሚፈጥር ነው። ባጭሩ ህወሃት ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ስልጣንን እንዲለቀቅ እስከተገደደበት ጊዜና በአሁኑ ፋሺሽታዊ በሆነው የአቢይ አህመድ አገዛዝ ወቅት ተግባራዊ የሚሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት እንዳለ መንፈስን የሚሰልብና አረመኔያዊነትን የሚያስፋፋ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል። ይህንን  ሂደት ለመረዳት ደግሞ ከባድ አይሆንም። በህወሃት የአገዛዝ ዘመን አንድም ከተማ ጥበባዊ በሆነ መልክ አልተገነባም። በየቦታውም ልዩ ልዩ የህዝቡን መንፈስ የሚያድሱ ባህላዊ ተቋማትና የትምህርት ዘርፍ አልተስፋፋም። በአንፃሩ የምናየው ከቤተ-መጻህፍትና የወጣቱን መንፈስ ከሚያድሱ ተቋማት ይልቅ ቡና ቤቶች፣ ዲስኮቴኮችና የጨአት መቃሚያ ቤቶች ናቸው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከትናንሽና ከማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ይልቅ የሆቴልቤቶች መስፋፋት እንዳለ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል አስተሳሰብ አሉታዊ በሆነ መልክ ሊለውጡት ችለዋል። ይህም ማለት የአንድን ህብረተሰብ የመንፈስ ሁኔታ በመጥፎም ሆነ በጥሩ መልክ መቅረጽ ሊወሰን የሚቻለው ስልጣን ላይ ባለው አገዛዝና በሚያካሂደው ወይም ተግባራዊ በሚያደርገው በተለይም በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ነው። የሚያደርገውን የማያውቅና በውጭ ኃይል እየታዘዘ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲን ተግባራዊ የሚያደርግ አገዛዝ ስልጣን ካለ ደግሞ የግዴታ ከፍተኛ የሆነ የጭንቅላት በሽታን ነው የሚያስፋፋው። ጭንቅላት ሲጋረድ ደግሞ ሁኔታዎችን በግልጽ በማንበብ ሳይንሳዊ ትንታኔም ለመስጠት አይቻልም። በምድር ላይ የሚታዩ አስቀያሚ ነገሮች በሙሉ እንደኖርማል ስለሚወሰዱ ማንኛውም ሰው እያየ ወይም እየዘለላቸው ያልፋል።

በአጠቃላይ ሲታይ ከአብዮቱ ጀምሮ በህዝባችን ላይ የደረሱት ስቃዮች በሙሉ ህዝባችንን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ጥለውታል። አብዛኛዎች በማያውቁት ነገር ውስጥ በመግባት የጥይት ራት ሊሆኑ በቅተዋል። ሌሎች ደግሞ የማምለጥ ዕድል ያገኙት አገራቸውን ጥለው በመሄድ አንዳንዶች በየበረሃው ውስጥ ህይወታቸውን ሲያጡ ሌሎች ደግሞ የማምለጥ ዕድል ያገኙት በየቦታው ተሰደው እንዲኖሩ ተገደዋል። ወያኔም ስልጣን ከያዘ በኋላ ቁጥራቸው የማይታወቅ በመሰደድና፣ አንዳንዶች በአገዛዙ ለአረቦች እንዲሸጡ በመደረግ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቁ ተገደዋል። አልፈው ጥረው ገንዘብ ያጠራቀሙና አንዳንድ ቁም ነገሮችን ለመስራት ያሰቡ ደግሞ በዘመናዊ ቀማኞች ገንዘባቸው እንዲቀማ ተደርጓል። በተለይም ወጣት ወንዶች በሴት እህቶቻቸው ላይ የሚፈጽሙት ወንጀል እጅግ ለጆሮ የሚቀፍ ነው። ይህ ሁሉ አረመኔያዊ ተግባር ሊስፋፋ የቻለው የሁለት ትውልድ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ነው። አብዛኛው ወንጀልና አገርን ማፈራረስና ሰውን መግደል የተፈጸመውና የሚፈጸመው ደግሞ ማሰብ በማይችሉ ወንዶች ነው። አንዳንድ ሴት ልጆችም በመታለል ወንጀል ፈጻሚዎች ለመሆን በቅተዋል። በአጭሩ ባለፈው ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በአገራችን ምድር ሰይጣናዊ መንፈስ የተናወጣቸው ሰዎች እየተበራከቱ ከመምጣታቸው የተነሳ የወንጀሉም ዐይነትና ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሊመጣ ችሏል። እንደዚህ ዐይነቱንም የጭንቅላት መበከል በተራ የፖለቲካ ወይም የአገዛዝ መለወጥ ማሻሻል ወይም ማከም በፍጹም አይቻልም።

እስከምረዳው ከሆነ ድረስ የአረንጓዴው ማህበር ዋና ዓላማና ተግባርም ይህንን መንፈሳዊ ክስረትና የልብን መደንደንና የመንፈስን መሰለብ በመገንዘብ አዲስና ልምላሜን የሚያስፋፋ በሰዎች መሀከል መፈቃቀር እንዲኖርና ለአንድ ዓላማ በመነሳት በጥሩ የመንፈስ ኃይል በመመራት አገርን በጋራ ለመገንባት ነው። ስለሆነም ከመንፈስ አልባነትና ከልብ መደንደን ይልቅ መንፈሳዊ ልምላሜንና ልበ-ርህርሁነትን በማስፋፋት በወንድማማቾችና በእህትማማቾች መሀከል መተሳሰብን ለመፍጠር ነው። በእኔ ዕምነት ለዚህ ደግሞ ጭንቅላትን የሚያድስና በጥሩ መልክ የሚያንጽ የትምህርት ዐይነት መስፋፋት አለበት። ይህ ጉዳይ በዕድሜ ለገፉት በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለማቆየትና ቀስ በቀስም እየገነቡ ጠንከራ አገር ለመገንባት ከተፈለገ የታዳጊ ልጆችን መንፈስ ቀስ በቀስ መኮትኮትና ማሳደግ ያስፈልጋል። በተለይም በህፃናት ላይ ጥሩና ገንቢ ስራ ሲሰራ ብቻ ነው ሰላማዊና ርህራሄነት ያለው ዜጋ ማፍራት የሚቻለው። ይህ ዕድል በሌለበት ወይም ደግሞ በህፃናት አስተዳደግ ላይ ልዩ አትኩሮ ካልተሰጠ አገራችንን እንደ አገር ማቆየትና መገንባትም በፍጹም አይቻልም።  መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de                        

                            www.fekadubekele.com

 

be649390 7cd7 11ef bf4b ef19cfbf3842.jpg
Previous Story

 የረሃብተኞች የጣር ድምጽና የሠማዕታት ደም ጩኸት ለፍትህ ያልቆሙትን ሁሉ ያውዳል – ከበየነ

6667uuhhjjjj
Next Story

የ17 ጀኔራሎቹ አዲስ ዘመቻ ምን ይጨምራል? አስደንጋጩ የአማራ ክልል መረጃ

Latest from Blog

blank

“መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የሚለው የዲያስፖራ ከንቱ አታካራ! – ክፍል ሁለት

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) በአንዳንድ ስብሰባዎችና የሕዝብ መገናኛ መድረኮች የሚታየው የአንዳንድ ዲያስፖራዎች  “መነሻችን እዚህ መዳረሻችን እዚያ” የበከተ ከንቱ አታካራ በልጅነታችን ወላጆቻችን ትምህርት እንዲሆነን ይተርኩልን የነበረውን ከጫጉላ ወጥተው ጎጆ ለመመስረት የታከቱ ሁለት ያልበሰሉ ባልና ሚስትን ታሪክ
blank

መነሻችን አማራ መድረሻችን አማራ እና ወያኔያዊ መሠረቱ

የማይወጣ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል። የዛሬን አያድርገውና የትግሬ ልሂቆች “ትግራይ የጦቢያ መሠረት ናት ።  ጦቢያ ያለ ትግራይ፣ ትግራይ ያለ ጦቢያ ሊታሰቡ አይችሉም” በማለት ጦቢያዊ ከኛ ወዲያ ላሳር እያሉ አለቅጥ ይመጻደቁ፣ ይኩራሩ፣ ይታበዩ ነበር። ወያኔ
blank

ከ”ችርቻሮ” ድል አልፎ ለመሄድ የአንድነት አስፈላጊነት – ግርማ ካሳ

በአሁኑ ጊዜ ሁለት የፋኖ አሰላለፎች አሉ:: መኖር ያልነበረበት:: አንከር ሜዲያ ከሁለቱም አሰላለፎች፣ ሁለት ፋኖ መሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ሁለቱን አደመጥኩ፡፡ በሰማሁት ነገር ተደስቻለሁ:: ትልቅ ተስፋ እንድሰንቅም አድርጎኛል:: የአማራ ህዝባዊ ድርጅት የፖለቲካ
Go toTop

Don't Miss

Mohammed Al Amoudi

ሸህ መሃመድ አላሙዲን ጨክነው ይመለሱ ይሆን?  ሰመረ አለሙ

እኝህ በፎቶግራፉ የሚታዩት ከበርቴው አላሙዲ ከረጂም እገታ በኋላ ለመመለሳቸው በሶሻል
1967-74: Ethiopia's Student Movement

የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴና የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ዋዜማ – ፫ በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

(ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. ከ 1950-1975 ‹‹…