ከዚህ በታች ያለውን ጽሁፍ ጸሃፊው ቴክስት አድርጎልኝ ለብዙሃን አንባቢዎች እንዲዳረስ ፍቃዱን ጠየቅኩት:: እሱም ፈቃደኛ ሆኖ ኤዲት አድርጎ ላከልኝ:: በሰፊው መነበብ ያለበት ታሪክ ነው:: አንብቡት። አንባችሁም አሰራጩት።
ሰላም ውድ ዶ/ር ዮናስ፣ በቅርቡ ስለ ትግራይ ኤሊቶች ለመጻፍ እንዳሰቡ ሲያሳውቁ እኔስ እንደ አንድ የአካባቢው ተወላጅ ምንድን ነው የሚሰማኝ የሚለውን ሳስብ ለምን ሃሳቤን ጽፌ አላጋራዎትም ብየ የሚከተለውን ጻፍኩልዎ።
እኔ ከኤርትራና ከትግራይ ከተገኙ ቤተሰቦች የተገኘሁና መሀል ሀገር የምኖር ተራ ዜጋ ነኝ። እዛ አካባቢ ካለፉት 30 ዓመታት (እኔ ልብ ብየ መከታተል ከጀመርኩበት ጊዜ) ጀምሮ እየሆነ ያለው ነገር፦ ጦርነቱ፣ ጥላቻው፣ እብሪቱ፣ ፍርሃቱ፣ ጭካኔው፣ ረሀቡ፣ ስደቱ . . . . በአጠቃላይ እብደቱ መጨረሻው ምንድነው? እንዴት ነው ይሄ ሁሉ አልፎ ሰላም የሚመጣው እያልኩ አስብ ነበር።
ይሁንና ትግራይ ላይ ከነበረው ጦርነት በኋላ መጀመሪያ ላይ ቤተሰቦቼን ለማየት በኋላ ደግሞ በስራ ምክንያት አብዛኛውን የትግራይ ከተሞችን ከጎበኘሁ በኋላ ያየሁትና የታዘብኩት ነገር በትግራይና በኤርትራ የወደፊት ሁኔታ ተስፋ እንድቆርጥ እንዲሁም በኢትዮዽያ የወደፊት እጣፈንታ አሁን እየሆነ ካለው ነገር ጋር ተደምሮ ከፍተኛ ፍርሃት እንዲያድርብኝ አድርጎኛል። ጦርነቱ የፈጠረውና ጥሎት የሄደው ጠባሳ እዛው ትግራይ ውስጥ ከነበረው ህዝብ በስተቀር ማንም የተረዳው አይመስለኝም።
ውድ ዶ/ር አሁን አምሳ ዓመት ሞልቶኛል። ከተወለድኩባት ዕለት ጀምሮ እዛ አካባቢ ጦርነት ተለይቶት አያውቅም። ትንሽ ሰላም እንኳ ሰፈነ ቢባል ከጦርነት ስጋት ጋር ነው የነበረው። የመጨረሻው ከአብይ መንግስት ጋር የነበረው ጦርነት ግን ለ17 ዓመታት ከወታደራዊው ደርግ እና በኋላ ላይ ከሻዕብያ ጋር ከተደረገው ጦርነት ጋር በፍጹም የሚወዳደር አልነበረም።
ከጦርነቱ በፊት የትግራይ ኤሊት በህወሃት ላይ የነበራቸው ጭፍን ያለ መተማመን፣ ለአብይ መንግስት እና ለሻዕብያ ያሳዩት የነበረው ንቀት፣ ለራሳቸው የነበራቸው በጣም የተጋነነ ግምት እና ድንቁርና ላይ የተመሰረተው እብሪት ጦርነቱ በጣም የከፋ እንዲሁም የደረሰው አደጋ ማንም ሰው ከሚያስበው በላይ በጣም ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። ብቻ እዛ አካባቢ (በኤርትራም ሆነ በትግራይ) እንዴት፦
_ያ ሁሉ ጦርነት ለምን ተካሄደ?
_ምን ዓላማ ለማሳካት ነበር?
_ጦርነቱስ ምን ውጤት አመጣ?
_ለተፈጠረው ነገር ሁሉ ተጠያቂው ማነው?
የሚሉ ጥያቄዎችን አንስቶ የሚጠይቅ ኤሊት ማየት አለመቻሌ፤ በተቃራኒው አህያውን ትቶ ዳውላውን እንደሚባለው የሁሉም ችግር መንስኤ አንድ ብሄር ላይ ደፍድፈው ለበቀል በከፍተኛ ሁኔታ የተነሳሱና በጥላቻ ያበዱ ኤሊቶችን ማየቴ የወደፊቱ ሁኔታ ተስፋ እንድቆርጥ አድርጎኛል።
በተለይ ትግራይ ላይ 50 ዓመት ሙሉ ለየትኛውም የፖለቲካ ጥያቄዎች አፈሙዝ ብቻ ነው መፍትሄው ብሎ የሚያምንን የፖለቲካ ፓርቲ ለምን ብሎ የሚጠይቅ የተደራጀም ሆነ በግለሰብ ደረጃ አለመኖሩ ምን ያህል የትግራይ ህዝብንም ሆነ ኤሊቶቹን እንደጎዳቸው ገና በደንብ የተገለጠላቸው አልመሰለኝም።
ኤሊቶቹ በትግራይም ሆነ በኤርትራ ህዝብ መካከል በኢትዮዽያ ሀገረ መንግስት እና በቀድሞዎቹ መንግስታት ላይ የነበረውን የተለያየ አመለካከት ወደ አንድ ለማምጣት እና ህዝቡን ሞቢላይዝ ለማድረግ የተጠቀሙበት መንገድ ላለፉት ብዙ አስርት ዓመታት በሀገራችን የማያባራ ጦርነት እንዲነሳ፣ አንድ ብሄርን ታርጌት ያደረገ ጥላቻና ጥቃት እንዲኖር አድርጓል።
በዚህ አጋጣሚ ስሜቴን ስላነሳሱት ተራ ነገሮች የሚመስሉ ነገር ግን የዛን አካባቢ የእብደት ልክ የሚገልጹትንና ሁሌም ሳስባቸው የሚገርሙኝን ነገሮች ላካፍልዎት፡
የመጀመሪያው ደርግ መቀሌን ሲለቅ እዛው ስለነበርኩ የማይረሳኝ ነገር፤ ከእነርሱ በፊት የነበረው መንግስት እነሱንና ሻዕብያን ለማውገዝ በየአደባባዩ አቁሟቸው የነበሩት ቢልቦርዶች በቀለም ጠፍተው በምትኩ ደርግንና አንድን ብሄር ስሙን በመጥቀስ (ኢንተርቼንጄብሊ ሁለቱንም ይጠቀሙበት ነበር) የሚያወግዙ መፈክሮች ይጻፉ ነበር፣ በትግርኛ ቋንቋ በሬድዮ ጣቢያቸውም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ብቻ በተገኘው አጋጣሚዎች ሁሉ ደርግን ጨምሮ የቀድሞ መንግስታትን በአንድ ብሄር ከረጢት ውስጥ ከተውና በጠላትነት ፈርጀው በህዝቡ ዘንድ ፍርሃትን ብቻ ሳይሆን ጥላቻንም ይዘሩ እንደነበር አስታውሳለሁ።
በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ የአባቴ ቤተሰቦች በእብሪት ታውረው ጦርነት ሲጀምሩ በወቅቱ የነበረው ጠ/ሚያችን ”የአይናችሁ ቀለም . . .” ብሎ እነሱን ሲያባርር እዚህ የሚኖሩ ቤተሰቦቼን ጨምሮ ገሚሱ ከዚህ በፊት ወደማያውቋት ኤርትራ ሲባረሩ፣ ገሚሱ ወደዛ ከምሄድ ብሎ ወደ ኬንያና ሱዳን ሸሸ። ቀሪው ግን በሚገርም ሁኔታ የመንግስትን እስር እና ማባረር ለመሸሽ እኔ ኤርትራዊ ሳልሆን የትግራይ ሰው ነኝ እያሉ ይከራከሩ ነበር።
የበለጠ የሚገርመው ኤርትራዊያን ላይ በደረሰው ያልተማሩት እነዚህኛዎቹ ከሃያ ዓመት በኋላ በአብይ መንግስት ላይ በእኔ እድሜ ከማውቃቸው ጦርነቶች ሁሉ የከፋውን ጦርነት አስነሱ። በተለይ ሁለተኛው ዙር ጦርነት ላይ ህወሃቶች ሸዋ ደርሰናል እጃችሁን ስጡ እያሉ ሲያስፈራሩ መንግስታችን ፓኒክ ሁኖ የእናቴን ወገኖች ሰብስቦ ማሰር ሲጀምር የተወሰኑት እንደኤርትራዊያን ወደ ኬንያና ወደ ሱዳን ሲሸሹ ቀሪዎቹ ግን የዛኔ የነበረውን ከፍተኛ የሆነ እስርና ማሳደድ ለመሸሽ እኛ ከትግራይ አይደለንም ኤርትራውያን ነን ይሉ ነበር።
ሶስተኛው የቅርብ ጊዜው ጦርነቱ ከመጀመሩ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ መቀሌ ሂጄ ነበርና ወንድሜ ተከራይቶ ወደሚኖርበት ቤት ለጥየቃ ስሄድ የዋናው መግቢያ የውጭ በር ላይ ቀለም የተቀባ ምልክት ስለነበር እንደዋዛ ይሄ ምልክት የምንድነው ብየ ብጠይቀው የሚገርም ነገር ነበር የነገረኝ። ለካ ወንድሜ ተከራይቶ በሚኖርበት ጊቢ ውስጥ የቤቱ ባለቤት ልጅ አሜሪካ ሲኖር አደጋ ደርሶበት የሚያስታምመው ሲያጡ መሰለኝ እዛ ያሉ ሰዎች ወደዚህ ልከውት እዚህ ከቤተሰቦቹ ጋር እየኖረ እያለ የአካባቢው የቀበሌና የደህንነት ሰዎች ትግራይ ላይ ስላለው አስተዳደርና ስለ ህወሓት ያለው አመለካከት እንደ አደገኛ ነገር ተቆጥሮ ለካ እነርሱ በሚያውቁት መንገድ እዚህ ጊቢ ውስጥ ለህወሓት ስጋት የሆነ ሰው አለ የሚል ምልክት ማድረጋቸው ነበር (ልክ ጀርመኖች በሒትለር ጊዜ የአይሁዳውያንን ቤት በቀላሉ ለመለየት እንዲቻል በር ላይ ያደርጉት እንደነበረው ምልክት ማለት ነው)።
በመጨረሻም ከ14 ወይም 15 ዓመታት በፊት ይመስለኛል ከወታደራዊው ደርግ መንግስት ጋር በነበረው ጦርነት የሻዕብያ ከፍተኛ የጦር መኮንን የነበረ በኋላም ምክንያቱን ባላውቅም በሂደት ሻዕብያን ትቶ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን የተቀላቀለ የአባቴ ቤተሰብ እና የእሱ የልጅነት ጓደኛውን እዚሁ አዲስ አበባ አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ አርፎ በአካል ሂጄ አግኝቸው ነበር።
በወቅቱ መለስ ዜናዊ የኤርትራ ተቃዋሚዎችን አሰባስቦ አንድነት እንዲፈጥሩ የሚጥርበት ጊዜ ስለነበር አዲስ አበባ ይመላለስ ነበር። አንድ ጊዜ ምን አለኝ “እኛ ኤርትሪያውያን እና የትግራይ ብሄርተኞች በዛ ሁሉ መስዋዕትነት አመጣነው የምንለው መልካም ነገር እና ኪሳራው በፍጹም የሚመጣጠን አይደለም። በቀድሞ መንግስታት የተፈጸሙ እና ለትግላችን መንስኤ ናቸው ከምንላቸው ታሪካዊ በደሎች ጋር እንኳ የሚመጣጠኑ አይደሉም። ከአሁን በኋላ ግን ይሄንን እንቀይረዋለን።” ብሎኝ ነበር። ከዛ በኋላ የሆነውን ሁሉ ሲያይ ምን እንደተሰማው ባውቅ ደስ ይለኝ ነበር። ብቻ የእኛ ነገር በጣም ያሳዝናል!
የሚሰማኝን ነገር በዚህ መልኩ እንድገልጽ ስላነሳሱኝ አመሰግናለሁ