ማንነቴ አማራ ነው። መገለጫዬም ግብሬም አማራ ነው። እኔነቴን በመንደር ለማጠር ለሚፈልጉ ሰዎች ግን ስለእኔ ማወቅ ስላለባቸው መነሻዬን እነሆ ብያለሁ። በአባቴ በአባቱ 6ኛ ትውልድ በአባ ወልደእግዚእ የሸዋ መንዝ ተወላጅ ነኝ። መንዜው እንጅልሼ ጎጃም ዳሞት ፍኖተሰላም አካባቢ መንዝ የሚባል ስፍራ የቆረቆረ ነው። ዛሬም ድረስ ቦታው መንዝ እየተባለ ይጠራል። በ6ኛ ትውልዴ የመንዝ ውሉድነቴን የተወሰኑ አማራ የሆኑ አማሮች ያውቁታል።
የአባቴ እናት እመት ሙሉነሽ ደስታ ይባላሉ። እመት ሙሉነሽ የደጃዝማች ደስታ ንጉሴ ልጅ ናቸው። ደጃዝማች ደስታ የደጃዝማች ንጉሴ ጎሹ ልጅ ናቸው። ደጃዝማች ጎሹን ከሞላ ጎደል ሁሉም ያውቃቸዋል።
እናቴ እማሆይ የሕዝብዓለም ዘለቀ ጥሩነህ በለጠ መንግስቱ ትባላለች። የልጃንበራ አማራ ናቸው። የልጅ ዘለቀ እናት እመት ፀሐይወርቅ እምሩ ቢሰወር የብላታ እምሩ ልጅ ናቸው። ከሰከላ እስከ ጅጋ ድረስ በዳግማዊ አጤ ምኒልክ ዘመነ መንግስት አጥቢያ ዳኛ ሆነው ያገለገሉ ኩሩ አማራ ናቸው። የዘር ሀረግ ታሪካቸውም በአመዛኙ ከቤተ ክህነት ጋር የተያያዘ ነው። ዛሬም ድረስ አንቱ የተሰኙ ሊቃውንት ጋር የጋራ መነሻ ያላቸው ናቸው። ዝርዝሩ መታበይን ስለሚያክል ዘልየዋለሁ።
ቋሪት፣ ሰከላ፣ ቡሬ፣ ፍኖተሰላም፣ ጎንደርና አዲስ አበባ በተለያዩ የሕይወት እርከኖች ያደግሁባቸው፣ የተማርሁባቸውና የኖርሁባቸው ናቸው። የአማራ ታሪካዊ ርስት ሁሉ ርስቴ የሆነ ሁሉም የእኔ፥ እኔም ለሁሉ መሆናችን ግን ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ መቼውንም አይሆንምም! እኔ አማራ የሆንሁት የምርም ተፈጥሯዊ አማራ ስለሆንሁ ነው። ወደ አማራ ፖለቲካ የገባሁትም ማንም አስገድዶኝ ወይንም ገፍቶኝ አልያም ጎትቶኝ አይደለም። አማራ ስለሆንሁ አማራነቴ ስለተጠቃ ይኽንን ጥቃት መመከት ግዴታዬ መሆኑን ነፍስያዬ ስለነገረኝ ብቻ ነው። የብሔርተኝነት ትግሉንም የጀመርሁት ከአብንም ከቤተአማራም ምስረታ በፊት ነው። ሊያውም እንደዛሬው አንበሳው ጀግናዬ እያለ የሚያሞግስ አልያም ጎጃሜ እያለ የሚናከስ ሳይኖር ለብቻዬ አማራ ሆኜ በወያኔ ደኅንነቶች እየታሰርሁ እየተፈታሁና እየተደበደብሁ ብዙ ዋጋ ስከፍል ኖሬያለሁ።
ዋጋ የከፈልሁት ለራሴ ለማንነቴ ስለሆነ አልመፃደቅበትም። የሚገርመው አሁን እንዲህ ከሚሊዮኖች ጋር ከመሆኔ በፊት አማራ ነኝ እያልሁ በወያኔ ደኅንነቶች ፍዳዬን ስበላ የራሴው ሰዎች ደግሞ የወያኔ ሰላይ እያሉ ይከሱኝ ነበር። አብረን ብዙ ሥራዎችን ሰርተን የጋራ ሥራችንን ለንግድ ያዋሉ ሰዎች በጋራ ተመካክረንና ተስማምተን ለተልዕኮዬ መሳካት ለሽፋን ያደረግኋችውን ፕሮፓጋንዳዎች ዛሬ ለከንቱዎች ክስ ማስረጃነት ሲያቀብሉ ይውላሉ። አማራነታቸውን አሽቀንጥረው ዛሬ የሰፈር ንጉስ ለመሆን የሚፈራገጡት እነዚህ ሰዎች እኮ የሰኔ 15 ክስተትን ተጠቅመው በጥቅሉ አማራነት ላይና በግልም እኔ ላይ የፈፀሙትን ነውር ተዘርዝሮ አያልቅም። የተውነው ለአማራ አንድነት ብለን ነው። ለታሪክ መማሪያ ይሆን ዘንድ ግን አንድ ቀን እውነቱን መፃፌ አይቀርም!
የሰፈር ንጉስ ለመሆን የሚጋጋጡ ወበከንቱዎች ታዲያ ካደረሱብን መጠነሰፊ ግፍ በኋላ እንደነሱው በጭቃ እንድንዋኝ ቢፈልጉም ከአማራነታችን ማማ ወርደን በመንደር አመድ ለመንከባለል የልቡና ውቅራችን አልፈቀደምና እጅጉን ተበሳጭተው ሁሉንአቀፍ ጉንተላዎችን ቢያደርጉም ፈፅሞ አልተሳካላቸውም። መቼውንም አይሳካላቸውም። ለአማራ ከጎጃሜው በላይ ጎጃም ርስቱ ነው። ለአማራ ከጎንደሬው በላይ ጎንደር መናገሻ ምድሩ ነው።
ለአማራ
??❤️
ምንም ማስረጃ አያስፈልገንም ምግባርህ ሁሉ የትልቅ ሰው ልጅ መሆንህን ያስመሰክራል፡፡ እነ አቶ ዳኔል ክብረት፤ብርሃኑ ነጋ (አባ ሞገሴ) ሲያረጠርጡ ለክብሬ ነው የምኖረው ብለህ ስትተጋተግ ኖርክ አብረውህ የነበሩት ሁሉ እጅ ሰጥተው ዛሬ ከህዝብና ከራሳቸው ተሰውረው የሚናገሩት እጅ እጅ እያለ ለሆዳቸው ሲኖሩ አንተ ግን ቅድሚያ ለክብርና አላማ ሰጥተህ ወደ እስር ተጋዝህ ክብርህ ጨመረ ለብዙ ሆድ አደሮች ግን ምሳሌ ሆንክ፡፡ ለህዝቤ እቆማለሁ ብለሃል በእርግጥም ለተገፋው ህዝብህ ቆምክ፡፡