አንዱ ዓለም ተፈራ
ታህሣሥ ፯ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፯ ዓ. ም.
አዲስ አበባ በተኩስ ተናወጠች።
አዲስ አበባ በተኩስ ተናወጠች። ተኩሱ ባንድ ጎኑ፣ ሕጋዊ ነበር። በሌላ ጎኑ፣ ሕገወጥ ነበር። ይሄ እንዴት ሊሆን እንደቻለ አስከትላለሁ። እስካሁን የአገራችን የአስተዳደር መመሪያ የተመሠረተበት፤ ወደ የምትፈራርስ ጎዳና የነዳት፤ “አንድ ሕዝብ አይደለንም!” “የተለያየን ሕዝቦች ነን!” “እናም ተለያይተን፣ ራሳችንን ችለን እና ለትንሽ ጥቅም ብቻ ነው በፌዴሬሺን የምንሰባሰበው!” በሚል የፖለቲካ ፍልስፍና ነው። በ “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ይሄው መመሪያ ተቀንቅኖ፣ ይሄው ድርጅት ይሄን መርኅ የሚያራምድ ሕገ-መንግሥት አስጸድቆ፣ የተለያዩ ክልሎችን ፈጥሮ፤ ያራመደው የአገራችን ፖለቲካ፤ አገር እየፈረሰች የምትሄድበት መንገድ ውስጥ አስገብቷት ነበር። ይህ እስካሁን የሄድንበት መንገድ፤ ዛሬ ወደምንጨራረስበት መንገድ አሸጋግሮናል። በአዲስ አበባ የተካሄደው፤ ለዚህ ደረጃ መብቃታችንን አብሳሪ ነው። እንዴት ለዚህ በቃን?
በአገራችን ያለው የፖለቲካ ቅኝት መንገድ የሳተው፤ የአስተዳደር በደልን፣ ከበዳዮችና ከተበዳዮች፣ ከገዢዎችና ከተገዢዎች አውጥቶ፤ በገዢ ብሄርና በተገዢ ብሔር መካከል ሆኖ የተቀመጠ ጊዜ ነው። ይህ፣ ትልቅ መታለፍ ያልነበረበት ቀይ መስመር ነበር። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ይህን በቦታው ያሳቀመጠበትን ምክንያት፤ ያሳለፍነው ሰላሳ ሶስት ዓመታት በግልጥ አሳይቶናል። ስንት ሰው እንዳለቀ፣ ስንት ንብረት እንደወደመ፣ አገራችን በእድገት ምን ያህል ወደኋላ እንደተጎተተች፤ እያንዳንዳችን የምናውቀው ነው። ያ የፖለቲካ እውነታ፤ እስከዛሬ ገዝቶናል። የዋሆች፤ ይሄ ስርዓት ራሱ ያልፋል! አገራችን ምንም ቢሆን እንዲህ ሆና አትቀጥልም! የሚል ምኞትን እና ተስፋን ይዘው፣ በቀጥታ በትግሉ ከመሰማራት ይልቅ፣ ሁሉን ነገር ለነገ ሠጥተው፤ ለዚህ በቃን። አሁን ወደባሰ አዘቅት ገብተናል።
በአንድ በኩል፤ ይሄ የዘር ክፍፍል አስተዳደር ሄዶ፣ ሄዶ፣ ሊቀጥል የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ፤ የግድ ለውጥ አይቀሬነቱ ገሃድ ሆነ። የብዙዎቻችን ፍላጎት፤ ይስተካከላል ነበር። ክፍፍሉ ይቀርና፤ አንድ እንሆናለን ነበር። የተገነዘብነው ግን ወደባሰ መሄዳችንን ነው። በሌላ በኩል፤ መቆየት የማይችለው፣ አናሳ ብድን ብዙኀኑን መግዛት የማይችልበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ፤ የግድ ማብቃት ነበረበት። ይሄ ግን፤ ወደተስተካከለ መንገድ መመለስ የሚችለው፤ በተፈጥሮ ሂደት ሳይሆን፤ በጉዳዩ ባለቤቶች ጥረት ነው። ዋናው ተጫዋች በቦታው የሚያደርገው ክንውን፤ ወሳኝ ነው። በሥልጣን ላይ ያለው የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን፤ እብሪቱ እያየለ ሲሄድ፤ ከዚህ የገዢ ቡድን የበለጠ አክራሪ የሆነው ሌላው ቡድን፤ ጉልበት ማብጀቱ ግልጥ ነበር። ሲጀመርም፤ የኦነግ ዓላማ፤ ኢትዮጵያን መቀየር እንጂ በደልን ማስቆም አልነበረም። እናም ያ እንዲሆን፤ የሚያራምደው የበለጠ አክራሪዎች ቡድን፤ ራሱን ከገዢው ቡድን የበለጠ አድርጎ አደራጀ። በመካከል የተረዳነው፤ በቦታው የተቀመጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ወሳኝ እንዳልሆነ ነው። በጎን ሌሎች በኦሮሞ አክራሪዎችና ፍጹም አጽናፍ የረገጡት አክራሪዎች መካከል ስምምነት እንዲፈጠር አደረጉ። ይሄም ስምምነት በሥልጣን ላይ ባለው ገዢ ቡድን መሪነት ሳይሆን፤ በፍጹም አጽናፍ በሄዱት መሪነት እየተነዳ ነው። ለዚህ ነው፤ አዲስ አበባ በተኩስ የተናወጠችው። በስምምነታቸው መሠረት ሕጋዊ ሊሆን ይችላል! የስምምነቱን ይዘት ብናውቀው። አዲስ አበባን በምንም መንገድ በተኩስ ማናወጥ ሕጋዊ አይደለም።
ለመሆኑ፤ በአንድ አገር፣ መንግሥታዊ መዋቅር ባለበትና መንግሥታዊ የጦር ሠራዊት ባለበት፤ ከመደበኛ ሠራዊቱ ውጪ የሆነ አካል፤ እንዴት ብሎ ነው ታጥቆ ከተማ በመግባት፣ እንደልቡ ተኩስ በተኩስ የሚፏልለው! ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? የትኛው ሕገ-መንግሥት ነው ይሄን የሚፈቅደው? በስምምነታቸው ላይ ምን ሰፍሯል? ይሄ ተቀምጧል ወይ? ለነገሩ የደቡብ አፍሪካዉን የገዢው አክራሪ ኦሮሞ ቡድን እና የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ስምምነት ዝርዝር መቼ እናውቅና! እንኳንስ የርስ በርሳቸው ስምምነት!
ወደ ዛሬው እውነታ ስንመለስ፤ ለዚህ ያበቃንን ሂደት እንቃኝ። ስምምነቶች!
ሕዝባዊ መሠረት የሌለው ገዢ ክፍል፤ ለአገር ዘለቄታ ሰላምና ትክክለኛ አካሄድ ሳይሆን፤ ዛሬን እንዴት ውሎ እንደሚያድር ስለሆነ የሚጨነቀው፤ አንድም፤ ከማንም ጋር ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ ነው። ሌላው ስምምነቱ ከሥልጣን እስካላወረደው ጊዜ ድረስ፤ ምንም ነገር ላይ ለመፈረም ወደኋላ አይልም። ለዚህ ነው፤ የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን፤ በጣም አገር አሳፋሪ ድርድሮችን ያደረገው። በደቡብ አፍሪካ ከትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር፤ ቀጥሎ ከኦነግ ሸኔ ጋር ስምምነቶችን አካሂዷል። በኒህ ስምምነቶች ውስጥ፤ ምን ያህል የአገሪቱን ጥቅም አስጠባቂ ጉዳዮች ተካተዋል? በኒህ ስምምነቶች ውስጥ፤ ምን ያህል ያፈጠጡ ችግሮችን ቀራፊ መፍትሔዎች ቀርበዋል? ግባቸው እውነት ዘለቄታ ሰላም ነው ወይንስ ጊዜያዊ መተንፈሻ መግዣ? ሌሎችን ጥያቄዎችን ማከል ይቻላል። በዚህ ላቁም።
ምናልባት፤ አሁን ገዢው ኦነግ ሆኖ ሳለ፤ ምን ፈልገው ነው ይሄን የሚያደርጉት? ብሎ ጠያቂ አይጠፋም። ጉዳዩ ግን ወዲህ ነው። ቆርጦ የተነሳ አፍራሽ ቡድን፤ ምንም ዓይነት ድጎማ ቢደረግለት፤ ከተነሳበት ዓላማ ንቅንቅ አይልም። ኦነግ ሸኔ፤ ከሽመልስ አብዲስ ምንም ነገር ቢቀርብለት፤ በቃኝ አይልም። ይሄን በሁለት መንገድ መመልከት ይቻላል። በአንድ በኩል የአክራሪ ባህሪ ነው። አክራሪ ምክንያትና ሠጥቶ መቀበል አያውቅም። በሌላ በኩል፤ ሺመልስ አብዲሳ ራሱ የሚደራደራቸውን ፍላጎት የያዘ ስለሆነ፤ ድርድሩ የወግ ነው። ድርድሩ በማር የተለወሰ የስም መገለጫ ነው።
በማጠቃለሊያ፤ የተያዘው መንገድ፤ አገራችንን ለረሃብ፣ ለድርቅ፣ ለምስቅልቅሉ የወጣ አገር አስተዳደር የሚዳርግ፤ የቂም በቀልና እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ውድድር የሚዳርግ ሂደት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ መለስ ዜናዊን አንበርክኮ እንደሸኘው፤ ዛሬም ያንኑ ለአብይ አሕመድ ሊለግሰው ይገባል።