በመጀመሪያ የአሰቴርን አባት በጉራማይሌ የመጻፌ ምክነያት ፊደሉን ለመጻፍ የሚያስችለኝ የአማርኛ ሶፍትዌር ባለማግኘቴ ስለሆነ እንድትረዱኝ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የአማርኛ ሶፍትዌርን የምትሰሩ ባለሙያዎች ይሄን ነገር ብታስቡበት ጥሩ ነው፡፡ ፊደሉ በደርግ ጊዜ ነበረ፡፡ ኦሮሞን ከኢትዮጵያዊነት ለማራቅ ሆን ተብሎ ሲሰራ ኦሮምኛ ከግዕዝ ፊደል ወጥቶ በላቲን መጻፍ ብቻም ሳይሆን እንደነዚህ ያሉ ድምጾች ፊደል እንደሌላቸው ተደርጎ ሲሴር ስለነበር እነዚህ ሆሄያት አሁንም ድረስ በአማርኛ ሶፍትዌር ውስጥ አለመካተታቸው ያሳዝናል፡፡ ቢያንስ ስሞቻችንን በአግባቡ ለመጻፍ የሚያስችለን ሶፍትዌር ስሩ፡፡
በዚሁ ወደተነሳሁበት
ለታማኝ፡- እያልከን ያለህው እኔን እየገባኝ አደለም፡፡ ሲጀምር ሕወሐት ማለት ላንተ ትግሬ ማለት ነው ወይ? እኛ እኮ ከበፊቱም ትግሬ ወያኔዎች የአገሪቱን መዋቅር ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩበትንና የሚሰሩትን ግፍ ይቁም አልን እንጂ ከትግሬ ወያኔ በዛው ሕገመንግስት፣ በዛው ሰንደቅ፣ በዛው አስተሳሰብ፣ ሥርዓትና አሰራር ለተረኞች ይሰጥ አደለም ጥያቄያችን፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የሆነው እውነት ይሄና ይሄ ብቻ ነው፡፡ ሲጀምር በዋናነት በሥልጣን ላይ ያሉት ወያኔ ሀ ብሎ ከጀመረበት ጀምረው አብረው የነበሩ ዛሬ አንተ ለይተህ በምታወግዘው የወያኔ ትግሬ ዘመን የዘረዘርካቸውን በሕዝብ ላይ የተደረጉ ግፎችን ሁሉ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የኖሩ ናቸው፡፡ አሁን እያየን ያለንው እውነቱ ከትግሬ ወያኔም ዘመን በከፋ የዘረኝነትና ጥላቻ ሥርዓትን በግልጽ ከቤተመንግስት ቁጭ ብለው ሊያጠፉት የፈለጉትን ዘርና ሐይማኖት ላይ ጦርነት የከፈቱ ናቸው፡፡ ወያኔን ከትግራይ ለእገዛ ወደዚህ ሳቡት እንጂ እስኪ ላለፉት ሶስትና ከዚያ በላይ ዓመታት እስካሁንም ዜጎች በማንነታቸው እየተጨፈጨፉ ያሉት እውን በትግሬ ወያኔ ነው? ከቤተመንግስት ስንቅና ትጥቅ በሚሰጣቸው ሰው በላዎች አደለም? አሜሪካ ለኢትዮጵያ በእርዳታ የሰጠቻቸው የጦር መሳሪያዎች ዛሬ እማን እጅ ናቸው? ኦነግ ሸኔ እየተባለ በዳቦ ሥም የሚጠራው ቡድን ማን ነው ሥንቅና ትጥቅ እየሰጠው ያለው? አሜሪካ ለኢትዮጵያ በእርዳታ የሰጠቻቸው መሳሪያዎች በምን ሁኔታ ነው ዛሬ ኦነግ ሸኔ እየተባለ የሚጠራው ቡድን ታጥቋቸው የምናየው? እውነትን እየካድን ዛሬም በዛው ልንኖር ትፈለጋለህ? ከሀያ በላይ ባንክ ተዘረፈ በሚል ገንዘብ ሲተላለፍለት የነበረው ቡድን፣ በይፋ በስቴዲየም ሳይቀር የምርቃት ሥርዓት እየተደረገለት ያየነው አደለ ዞረው ኦነግ ሸኔ ምናምን የሚሉን? እስኪ ከዚህ እውነት ውጭ ያልተረዳንው አንተን የገባህ ነገር ንገረን፡፡
የቀድሞ አባቶች የችግር ጊዜ አንድነታቸውን አንስተሀል፡፡ እውነት ነው፡፡ በውስጥ ጉዳያቸው ችግር ቢኖርባቸው እንኳን በአገራቸው ላይ ጠላት ሲመጣባቸው በአንድ የመሰለፋቸው ነገር ሁሉም ከምንም በላይ የሚወዷት አገራቸው ስለምትበልጥባቸው ነው፡፡ ንጉሱም ሆኑ መሳፍንቱ በአገራቸው ጉዳይ አንድ ስለነበሩ ነው፡፡ ይህ ዛሬ አለ? በኢትዮጵያዊነት የተቀባ መርዝ አገርን ለማፍረስ ቤተመንግስት አደለም ያለው? አይናችን እያየ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነው አንበሳ ተነስቶ ከእነጭርሱ በአገራችን እንኳን በሌለች ወፍ ተክቶ የምታየው መሪ ብለህ የምታስበው ግለሰብ ምን ማድረጉ የምስልሀል? አንበሳው የሌላቸው አገራት ሳይቀር ምልክት ሊያደርጉት የሚፈልጉት ምልክትን ነው ፒኮክ በምትባል በአገራችን እንኳን በሌለች ወፍ የተተካው፡፡ አንድ ግለሰብ ይሄን ሁሉ እንዲያደርግስ ማን ይፈቅድለት ነበር ሥርዓትና ሕግ ቢኖርማ?
ከዚህ በተረፈ እስኪ አንተ የወያኔ ከምትለው ሥርዓት ምንም እንኳ የሥርዓትም የሰዎችም ልይነት ባይኖር የአሁኑ የሚለይበትን ንገረን፡፡ አንተ ከአሜሪካ አዲስ አበባ ስለተንሸራሸርክ? በትግሬ ወያኔ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ብዙ ግፍ ደርሶባቸዋል፡፡ አውቃለሁ፡፡ በአለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ በኦሮሞ ኦነጎች ግን በመቶሺዎች የሚቆጠሩ አልቀዋል፡፡ ከቀን አንድ ጀምረው ነው እኮ ዋና ከተማው አዲስ አበባን ጨምሮ ሰው እየጨረሱ ያሉት፡፡ በቀጥታ አብይ በሚያዘው ሰንሰለት እኮ ነው ከቀን አንድ ጀምሮ ሰዎች ከኖሩበት ቦታ በማንነታቸው በገፍና በግፍ ቤታቸውን እያፈረሰ ሜዳ ላይ የተጣሉት፡፡ ይሄን ያደረጉ ወንጀለኞች ዛሬ በሚኒስቴር ደረጃ ተሹመው እናያቸውዋለን፡፡ በየቀኑ መከራው ሲከፋ አንዱን እየተውን ሰሞንኛ እየሆንን እንጂ፡፡ ከተሞች እኮ ናቸው አይናችን እያየ የወደሙት፡፡ መቼም ሻሸመኔ፣ አጣዬ፣ቡራዩ፣ ዝዋይ….. እያልኩ ልደረድርልህ አትጠብቅ፡፡ ይህን እውነት መጀመሪያ ወደ ውስጥህ ዋጠው፡፡ ከዛ የመረረው እውነት ሲገባህ ሁሉም ይገባሀል፡፡ እየሆነ ያለው ይሄና ይሄ ብቻ ነው፡፡
ዛሬ በወያኔ ትግሬ እየተደረገ ያለውን ወረራና አረመኔያዊ ድርጊት በማን እገዛ እየተደረገ ይመስልሀል? ከቀን እንድ ጀምሮ የሆነውን አስታውስ፡፡ አንተ የኢትዮጵያ መከላከያ እያልክ የምታሞካሸው ተቋም በፊት በትግሬ ወያኔ ተሞልቶ ነበር፡፡ ዛሬስ? በሚያሳፍር ሁኔታ ከወያኔ ትግሬዎች እንደወረደ በተቀዳ አደረጃጀት አደለም ያለው? በኦሮሞ ኦነጋውያን መተካቱ በቀር፡፡ እስኪ ለራስህ የመዋቅሩን ዋና ዋና ሰዎች ልጥቀስልህና ምን ማለት እንደሆነ ንገረኝ፡፡ የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ አብይ አህመድ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር ቀነዓ ያደታ (አሁን ትግሬ ተሰይሟል) የታማጆር ሹም ብርሀኑ ጁላ፣ የአየር ሀይል አዛዥ ይልማ መርዳሳ ሌሎችም እነ ባጫ ደበሌ በልዩ ሚና፡፡ ለመሆኑ ይሄ የኢትዮጵያ መከላከያን የሚያሳይ ነው? እንግዲህ እንዲህ ያለው ተቋም ነው ከኦሮሞ ውጭ ያለውን ሊጠብቅልህ የምትፈልገው? በኮነቮይ ከትግራይ እስከ ሰሜን ሸዋ የሚመጣ ወራሪና ከአማራ ከተሞች እየተዘረፈ የሚወጣ ንብረት የአየር ጥቃት የማይደረግበት ለምን ይመስልሀል? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ደግሞ ከዛሬ ዓመቱ ወያኔ አጠቃችው ከተባለበት ቀን ጅምሮ የነበረው ቁማር እንዴትና በማን ነበር? አንድ የመከላከያ ተቋም ወያኔ አጠቃቸው በተባለበት መልኩ የመጠቃት እድሉ እንዴት እንደሆነ ከገባህ አስረዳኝ፡፡ ለአንድ አገሪቷን ይጠብቃል ለሚባል ተቋም ሰራዊቱ እንቅልፍ ላይ እያል ባልጠበቀው ሰዓት ጥቃት ተፈጸመበት ተብለን ሲነገርን ያመንን እለት ነው ችግሩ የተፈጠረው፡፡ እንቅልፍ ወስዶት? ወያኔ እንዴት እየተዘጋጀች እንደነበር እኮ በድብቅም አልነበረም፡፡ ወያኔ አዲስ አበባ ያሉ አደጋ ጣዮቿን እንኳን በተጠንቀቅ አቁማ ይጎዱብኛል ያለቻቸውን ሰዎቿን ወደ መቀለ ስታሰባሰብ ምን እየተሰራ ነበር? ሰራዊቱስ በምን መልኩ ነበር እየታዘዘ የነበረው? ያን ሁሉ ሲደረግ ተቋሙን እንደፈለገው የሚዘውረው የሥልጣን ልኩን የማያውቀው ግለሰብ ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ምን እየሰራ ነበር?
ለመረጃ ያህል በዛን ወቅት መከላከያው በእርግጥም ሙሉ በሙሉ ተመትቷል፡፡ወያኔን በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ሲጠብቃት የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ነበር የጦርነቱን አቅጣጫ የቀየረው፡፡ ያም በአራት ኪሎው ሰውዬ የእዝ ሰንሰለት ሥር ባለመሆኑ ነው፡፡ ዋናው ግን የእግዝአብሔር ልዩ እጅ ነበረችበት፡፡ ማንም በራሱ የሚመካበት አደለም፡፡ ከዛ በኋላ የአማራ ልዩ ኃይል ምን ሲሰራብት ነበር? ከዛም አሁን ደግሞ በግልጽ በስልታዊ ማፈግፈግ በሚል የሆነውን ሁሉ ሲመራ ቆይቶ በስተመጨረሻ ይባስ ብሎ በአርሲ ማሳ ላይ ቆሞ ታጠቅ ዝመት አትበሉ፡፡ ገዳዮችን እትንኩብኝ አይነት ሲነግረን የነበረው ሰው አደለም ከእነዛ ፒኮኮች በኋላ ያለው ግቢ ውስጥ ያለው?
ታማኝ በዚህ ቁማር ራስህን ባታስገባ ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም የብዙዎች ሴራ ይገለጥ ዘንድ እየሆነ ያለው ሁሉ እየሆነ ስለሆነ አንተም ከዛ እንዳንዱ ላለመሆንህ ማረጋገጫ የለንም፡፡ ስለዚህ ዝም በል፡፡ የአሜሪካን ዛሬ ያለውን የወያኔ እምባ ጠባቂ ቡድን በሚቀጥለው ምርጫ ይወገዳል፡፡ የኢትዮጵያ ዋና ጠላት ያለው እዛው አራት ኪሎ ነው፡፡ ይሄን በተግባር የምናየውን እውነት ለማስተባበል የሚያስችል አቅም ያለህ አይመስለኝም፡፡ ዛሬም እኮ ሕዝብ በሙሉ ጦርነት ላይ ሆኖ እንዲህ እንዲራዘም የሚደረገው ለምን እንደሆነ ብታስረዳን ጥሩ ነበር፡፡ ግን አትችልም፡፡ እስኪ መከላከያ የምትለው የት ጋር ነው እየተዋጋ ያለው?ሥንቅና ትጥቅ የሌለውን ገበሬ አሰልፎ አራት ኪሎ ቁጭ ብሎ ጭራሽ ክርስቶስ ነኝ እያለ ሲሳለቅ ምን ማለቱ እንደሆነ ይገባሀል? እስኪ ይሄ ግለሰብ የኢትዮጵያ የሚያሰኘውን አንዲት በጎ የሰራውን ነገር ንገረኝ?
አስቴር፡ ያንቺም ከታማኝ የተለየ አደለም፡፡ በብዙ ጊዜ ንግግርሽ እውነተኛ ኢትዮጵያውያንን የማረክሽበትን እድል ተጠቅመሽ ዛሬ ከኢትዮጵያ ይልቅ ኢትዮጵያን እያፈረሰ ያለውንየኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን የአራት ኪሎውን ሰው እንዴት ተነካብኝ ብለሽ የሄድሽባቸው ርቀቶች አንችንም ገፍትሮ ያስወጣሽ መሰለኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነት የአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን በመልበስና ምን እልባትም በማስመሰል አደልም፡፡ ለዛማ ይሄው ዛሬ እንዴት ይነካብኛል እያልሽ የዛን ያህል ርቀት ሄደሽ የምትከላከይለት ሰው በቂ ነው፡፡ መሠረታዊ በሆነ አግባብ ለሕዝብ እየሆነ ያለውን የተናገሩትን ለመደለል ባልሞከርሽ ነበር፡፡ ከዛ ይልቅ ስንት አሳሳቢ ነገሮችን በተጋፈጥሽ ነበር፡፡ በሀሌታ ቲቪ ቀርበሽ የተናገርሽው አንችንም ወስዶሻል፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት ያለየንው ክህደታዊ ማንነት የለም፡፡ ያሳዝናል፡፡ ለብዙዎች ለካ የኢትዮጵያ ነገር ከቆማሩ የሚያካፍላቸው እስከሚያገኙ ነበር፡፡ የኢሳትና ጋዜጠኞቹን ዛሬ ያሉበትን እውነት ስናይ እጅግ ይገርማል፡፡ የትግሬ ወያኔን ሰዎች አሰረች አሰቃየች ሲል የነበረ ሁሉ ዛሬ በይፋ ከተሞችን ሲያጠፋና ሲያስጠፋ፣ ሰዎችን በይፋ በማንነታቸው ሲሳርድና ሲያርድ የሚዩትን ከወያኔ የተሻለ ጊዜ መጣልን ብለው ሲነግሩን ከማየት የበለጠ ሕሊናን የሚያደማ ነገር የለም፡፡ ሁላችንም ለውጥ ይመጣል ብለን መጀመሪያ ደግፈናል፡፡ ጉዳዩ ቆየና በሬ ካራቹ ሆነ እንጂ፡፡ ገና ከጅምሩ አብይ አህመድ የጀመረው ከለገጣፉና አካባቢው በሕገ ወጥ ግንባታ ሰበብ ሰዎችን በማንነታቸው ቤታቸውን በማፍረስ ጎዳና ላይ በመጣል ነበር፡፡ በተቃራኒው በአዲስ አበባ ሳይቀር አለ የተባለ ቦታ ሁሉ ለኦሮሞ እየተመረጠ ሲሰጥና አገር ሲወረር በወቅቱ ይሄ አሰራር ሕገ ወጥ ነው ያለው እስክንድርና ጓደኞቹ ዛሬ የት እንደሆኑ እያየን ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ግዙፍ አውነታትን በራስ ጥቀም ለውጦ ሕሊናን ክዶ ለሆድ ከማደር የበለጠ ውርደት የለም፡፡ ወያኔ ትግሬ ስለሆነ አደለም የጠላንው፡፡ ያመጣብን ሥርዓትና እኩይነት እንጂ፡፡ ዛሬስ በተረኞቹ ከወያኔ በከፋ እየሆነ ያለው ሁሉ ሲሆን እንዴት የአገር ጠላትነታቸውን በግልጽ ተረድተን እውነቱን ለመናገር አንደበታችሁ ተያዘ፡፡ ጭራሽ በተቃራኒው ይሄን ከወያኔ ትግሬ የከፋ አረመኔያዊ ቡድን ዘብ ሆናችሁ፡፡ ያሳዝናል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሆይ ኢትዮጵያዊነታችሁን ለኢትዮጵያ ብቻ አውሉት የቁማርተኛ አረመኔዎች መጠቀሚያ አንሁን፡፡ በውጭ ያላችሁ የባይደንን ቡድን የኢትዮጵያ ወዳጅ በሆኑ
የጎንግረስና ሴነት አባላት ሂዱባቸው፡፡ አሁንም ቢሆን እኛ ጸባችን እንደ አገርና ሕዝብ ከአሜሪካ ጋር ሳይሆን ከባይደን ቡድን ጋር ነው፡፡ ሲጀምር ብዙዎቻችሁ አሜሪካ እንደዜግነታችሁ አገራችሁ ነው፡፡ የአሜሪካ የመንግስት መዋቅር እንደ አራት ኪሎ በአንድ ሰው የሚቆመርበት አደለም፡፡ የፕሬዘደንቱ ሥልጣን በተሰጠው ልክ ብቻ ነው፡፡ እሱንም በአግባቡ መጠቀም መቻል ግድ ይለዋል፡፡ በቅርቡ በቨርጂኒያ በተደረገው ምርጫ ያደረጋችሁት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከኢትዮጵያና ኤርትራውያንም በዘለለ የሌሎች አገራት ተወላጆችንም ማንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ አሁን ባለው የአሜሪካ አስተዳደር ብዙዎች ቆስለዋል፡፡ በዚህ ላይ በቋሚነት የሪፐብሊካን ደጋፊ የሚባለው ሕዝብ ቢያንስ እኩሌታው ነው፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ከ60 በመቶ የማያንሰው ነው፡፡ ይሄን ሁሉ በመጠቀም ነው ተደማጭነት ማግኘት የሚቻለው፡፡ እኔ ከጅምሩም ይሄ ዛሬ ያለው በድን ነብይ ሆኜ ሳይሆን አደገኛ እንደሆነ ገብቶኝ ነበር፡፡ ግን ማን ይሰማል?
በዚህ አጋጣሚ በቅርቡ በሲ ኤን ኤን ቀርባ ስለ ኢትዮጵያ የተናገረችውን ብሌኔ ሥዩምን አደንቃለሁ፡፡ ንግግሯ የቋንቋ ችሎታን ሳይሆን የነገሮችን አረዳድና ፍጥነት ያሳየ ነበር፡፡ እንግዲህ ሾልካ አራት ኪሎ ከገቡት ነች እዛ ቦታ እድሜ ካላት ማለቴ ነው፡፡ ሔርሜላ አረጋዊ ሌላዋ ትልቅ ሥራ እየሰሩ ካሉት ነች፡፡ ሚዲያዎች ለገበያቸው ሔርሜላ አረጋዊን የሚራኩቷት ነገር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ነገ የሆነ ነገር ተናግራለች ብለው ሌላ ቁማር ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉም አስቡ፡፡ ይሄ የከሀዲና አስመሳይ ዘመን ነውና፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊና ሐብታም አገር ነበረች ለሁላችንም የሚበቃ ሀብት ነበራት፡፡ ከእኛም ተርፎ ለሌሎች የምንለግሰው፡፡ ምን ያደርጋል በሴረኞች እጅ ወድቃ ይሄው እስከዛሬም መከራዋ ቀጥሏል፡፡ ማንም ሆንክ ማን አገርህን አስብ፡፡ ከመቼውም በከፋ የሚያዋርዱን ናቸው ዛሬ ሥልጣን ላይ ያሉት፡፡ በይፋ ሕዝብንና አገርን ለማፍረስ የሚደነፋ የፓርላማ አባል የሆነባት አገር ነች ዛሬ ኢትዮጵያ፡፡ ይሄ ታስቦበት እየተሰራ ያለ እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ዛሬም ዘንግተዋል፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይቅር ይበል፣ ይጠብቅ፤ ምህረት ያምጣልን፤ በቃችሁ ይበለን!
አሜን