October 13, 2021
2 mins read

እባክህ መለኮት ዱባን እሬት አርገው! – በላይነህ አባተ

ስብከት ሽውታ ሰውን የሚነዳው፣
ጭንቅላቱ እንደ ቅል ውስጡ ክፍት ሲሆን ነው፡፡

ሸወዱኝተሸወድኩየዱባጠባይነው፣
እድሜ ልክ ቀቅሎት ቀቃዩን የሚያምነው፣
እንደገና ሰብኮ ተጓሮው ሲተክለው፡፡
ጅላንፎ ቆማሪ በጥበብ በልጧቸው፣
ሕዝብን አሳርዶ አገር ሲሰብካቸው፣
በደንብ ያደምጡታል አፋቸውን ከፍተው፣
ድስኩራም ምሁራን ደም አይከረፋቸው፣
ለሰላሳ ዓመታት ምድርን ያጨቀየው፡፡
አጥንቱ ውልክፋ የዛሬ ዘመን ሰው፣
ቀጥ ብሎ እማይቆም እንደ ሊጥ ልምሾ ነው፡፡

እስተ ቀራኒዮ ብሎ ማዩ ሁሉ፣
ሲሶ መንገድ ሳይደርስ ይሰበራል ቃሉ፡፡

የሰው የበግ መንጋን ምንድን ይለያቸው፣
አሳራጅ እረኛ እኩል ተነዳቸው?

ይብላኝ ለሞተ እንጅ ቋሚንስ ደልቶታል፣
ገዳዩ ሲዘፍን እስክስታ ያወርዳል፡፡

ላባ የሚከብደው የነፋስ ሽውታ፣
ምን ያህል ቢቀለው የሰውነት ገላ፣
አንስቶ አንሳፈፈው እንደ በጋ ትቢያ!

ጣምራ እጅ አያነሳው ሲባል የነበረው፣
የቀጣፊ ትንፋሽ ሲጠርገው አየነው፡፡

እየቀላቀለ ነፋስ ስልነዳው፣
ከባድና ቀላል እኩል ሆነ ዋጋው፡፡

የዚህ ዘመን ነፋስ ከዛር የከፋ ነው፣
እንኳን ገለባውን አለቱን አነሳው፡፡

ታጋዩ በሰለ አፈራ ስንለው፣
ትል የወጋው ዱባ ክፍት ሆኖ አገኘነው፡፡
በአልፎ ሃጂ ነፋስ የተወሰደ ሰው፣
ሰማዩ ሲሰክን ስካሩ ሲለቀው፣
በየ ቁጥቋጦው ሥር ወድቆ እሚገኝ ነው፣
ብርሃን ሲነጋ ወጥቶ መመልከት ነው፡፡
እባክህ ነፋሱ እረፍ አደብ ግዛ፣
በሰማዕት መቃብር አረምን አትዝራ!
እባክህ እግዚአብሔር ለሰው ክብደት ስጠው፣
እንደ ገብስ ገለባ ነፋስ እንዳይጠርግው፡፡
እባክህ መለኮት ዱባን እሬት አርገው፣
ጅላጅሉ ሁሉ ቀቅሎ እንዳይበላው!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ጥቅምት ሰላሳ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop