June 13, 2021
72 mins read

አስከፊው አድርባይነት ዛሬም ከዋነኛ የፖለቲካ ደዌዎቻችን አንዱ ሆኖ ቀጥሏል ! – ጠገናው ጎሹ

June 13, 2021
ጠገናው ጎሹ

በህወሃት የበላይነት እየተመራ ሩብ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው የጎሳ//የቋንቋ አጥንት ስሌት  ሥርዓተ ፖለቲካ በተረኞች ኦህዴዳዊያን/ኦሮሙማዊያን የበላይነት እየተመራ  እና የወራዳነት  ፖለቲካ ጨርሶ በማይሰለቻቸው  ብአዴናዊያን አሽከርነት (አጋሰስነት) እየታገዘ  ይበልጥ አስከፊና አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ  ከቀጠለ  ይኸውና አራተኛ ዓመቱን ይዟል ።

ከሰሞኑ ደግሞ አገር ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የንፁሃን ዟጎቿ ምድረ ሲኦል በሆነችበት መሪር እውነታ ውስጥ “በዴሞክራሲያዊነቱ ታሪካዊ የሆነ ምርጫ “ለማካሄድ  ታሪካዊ ዝግጅት ላይ እንደሆኑ እየነገሩን ነው ።

“እንዲህ አይነት የጭካኔ ፖለቲካ ጨዋታ ለእራሳችሁም ሆነ ለእኛም ብሔራዊ ጥቅም ጨርሶ አይጠቅምምና እብደቱን አቁማችሁ በጋራ በመነጋገር የጋራ መፍትሄ ፈልጉ” ሲባሉ በሰለጠነ እና የአገርን (የህዝብን) ውስጣዊ ልኡላዊነት እየደፈጠጠ የቀጠለውን ሥርዓት በቅጡ ማድረግ በሚያስችል ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከማስተናገድ ይልቅ ይህ አይነቱ የዓለም ፖለቲካ መስተጋብር ወይም ዓለም አቀፍ ግንኙነት አዲስ ግኝት ይመስል  ለምን እንጠየቃለንና የሽርሽር (የባለሥልጣን ሰዎቻችን ጉዞ በእውነትና ከእውነት ለአገር ወይም ለህዝብ ጉዳይ መሆኑ ከቀረ አያሌ ዓመታት አልፎታል)  ጉዞ እገዳ ተጣለብን በሚል አስከፊ አገዛዛቸውን ከአገር ልኡላዊነት መደፈር ጋር አንድ አድርገው በመጮህና በማስጮህ መከረኛውን ህዝብ  ሌት ተቀን ያሸብሩታል።

ይህን አስከፊና ተደጋጋሚ  የፖለቲካ ውድቀት ተከትሎ የሚመጣው ኦኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊና ሥነ ልቦናዊ  ቀውሱም  በአስከፊ  አኳኋን ቀጥሏል። ይህን መሬት ላይ እየሆነ ያለ ግዙፍና መሪር እውነታ ለማስተባበል የሚሞክር ካለ አንድም የሥርዓቱ መሸነፍና መፍረስ የእለት ጉሮሮው መዘጋት ማለት እንደሆነ ሥጋት የገባው ጨካኝ ካድሬ ወይም ለከት የሌለው የማታለል ፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆነ የዋህ ወይም ፅእኑ የነፃነትና የፍትህ ዓላማና መርህ የሌው የአድርባይነት (የልክስክስነት) ልክፍት የተጠናወተው መሆን አለበት ።

በእጅጉ አሳፋሪና አሳዛኝ የሆነው ደጋግሞ የመውደቅ ፖለቲካ ታሪካችን  ዋነኛ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ በመንበረ ሥልጣን ላይ እየተፈራረቁ የፖለቲካ ቁማር ለሚቆምሩ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች   ህሊናቸውን  አሳልፈው ለመስጠት (ለመሸጥ) ፈቃደኛና ዝግጁ የሆኑና ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ወገኖች የመኖራቸው መሪር እውነታ ነው። እናም እነዚህ ወገኖች  ለመከረኛው ህዝብና ለእራሳቸውም ሲሉ ከተለከፉበት የአድርባይነት አዙሪት ሰብረው እንዲወጡ በግልፅና በቀጥታ ከመንገርና ከማነጋገር ይልቅ ዙሪያውን እየዞሩ በማጉረምረምና በመሽኮርመም እንኳን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በቅጡ መኖሪያ የሆነች ኢትዮጵያንም እውን ማድረግ አይቻልም ። ከግፍ አገዛዞች ዋነኛ መሣሪያዎች መካከል አንዱ የሆነውን አድርባይነትንና ባንዳነትን በፅዕኑ ሳንፀየፍና ሳንታገል ዴሞክራሲያዊ ሥርትን መናፈቅ ከቅዠትነት አያልፍም።

አለመታደል ወይም የፈጣሪ ፈቃድ አልሆን ብሎ ሳይሆን ከእኛው ከእራሳችን ዘመን ጠገብ የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ ትምህርት ለመውሰድ እና ከትናንት ዛሬ የተሻለ የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት ባለመቻላችን ምክንያት ዛሬም እራሳችንን ይበልጥ አስከፊ እየሆነ በሄደው የጎሳ/የዘውግ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ቁማር አዙሪት ውስጥ  እንድናገኘው ተገድደናል።  ያዋጣናል በሚሉት በማነኛውም ዘዴ (by hook or crook) ዓላማቸውንና ግባቸውን እውን ለማድረግ የቆረጡ ፖለቲከኞች ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ብልፅግና በሚል የለየለት የማጭበርበሪያ ስያሜ በመሰየም እንዲቀጥል ላደረጉት ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች በአድርባይነት ወይም በባንዳነት እራሳቸውን አሳልፈው የሚሸጡ ደካሞች በቁጥርም ሆነ በአይነት እየጨመሩ የመሄዳቸው ጉዳይ ከምር ካላሳሰበን ዴሞክራሲን መናፈቃችን የለየለት እንቆቅልሽ  ነው።

አዎ! ዛሬም እየደጋገምን ከምንወደቅንባቸውና ከወደቅን በኋላም ፈጥኖ ለመነሳት ካልቻልንባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ በአንድ በኩል በተረኝነት የፖለቲካ መዘውሩን ከሚዘውሩ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ጋር አብረው የሚገለባበጡ እና  በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ ካድሬነት ወይም አድርባይነት ህሊናቸውን በርካሽ የሚሸጡና ለመሸጥ የተዘጋጁ ወገኖችን አደብ የሚያስገዛ የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት ያለመቻላችን ውድቀት ነው።

ይህንን ግዙፍና መሪር ሃቅ ተገንዝበንና እየመረረንም ቢሆን ተቀብለን የተሻለ የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ሆነን እስካልተገኘን ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እስካሁን የምናውቃት ኢትዮጵያንም አስጠብቆ ለመኖር በእጅጉ እንደምንቸገር ከምር መገንዘብ የትክክለኛ መፍትሄ ፍለጋ ግማሽ አካል ነው። ሸፍጠኛ ሴረኛ አድርባዮችን (አሽቃባጮችን) ቢቻል ከክፉ ልክፍታቸው እንዲላቀቁ በመርዳት፣ ካልሆነ ግን ከእኩይ ገዥ ቡድኖች ጋር እየተሻሹ (እየተላላሱ) በአገር (በህዝብ) መከራና ደም የሚቆምሩትን እጅግ ፀያፍና አደገኛ የፖለቲካ ቁማር ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ካላቆሙ ተጠያቂነታቸው ለሦስት አሥርተ ዓመታት እጆቻቸውን በህዝብ መከራና በአያሌ ንፁሃን ደም ከነከሩ ገዥ ቡድኖች ከቶ ዝቅ ሊል እንደማይችል  በግልፅና በቀጥታ መንገር  የግድ ነው ።

ይህንን ለማድረግ  ግን ላለንበት ዘመን የሚመጥን የእራስን ትውልዳዊ ታሪክ ሠርቶ ለማለፍ ፈቃደኛና ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል። አዎ! ይህ ትውልድ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት አዋላጅ በመሆን የእራሱን ታሪክ መሥራት ካለበት በእራሱ ውስጥ የተዘራውን እንክርዳድ ከስንዴው ለይቶ የማውጣትን እጅግ አስፈላጊ ሥራ መሥራት ግድ ይለዋል። እንክርዳዱ ደግሞ እራሱን ለአድርባይነት ልክፍት አሳልፎ እየሰጠ ያለውና ከገንዛ እራሱ ጎን ያለው የገንዛ ወገን  ነው ።  ይህን አይነት አስቀያሚ ሁኔታ ጨርሶ ማስወገድ ባይቻልም የነፃነትና የፍትህ ትግሉን ሊጎዳ በማይችልበት ደረጃ ለመቆጣጠር  የጋራ የሆነ አገራዊ  ባለራዕይነትን ፣ ፅዕኑ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ዓላማንና ግብን ፣ ወቅቱና ሁኔታው በሚጠይቀው እውቀት (ንቃተ ህሊና) ታጥቆ መገኘትን፣ ለድል በሚያበቃ ድርጅታዊ ሃይል እራስን አዘጋጅቶ ወደ ፊት መገስገስ ይጠይቃል።

በምሬትና በስሜት የመብከንከን ወይም የመርመጥመጥ ፖለቲካን በአንዴና በፍፁምነት   ማስወገድ ባይቻለንም በቅጡ ከማድረግና በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ወደ ፊት ከመራመድ ይልቅ  መሪሩን እውነታ እየሸሸን  ስለ ዴሞክራሲና ዴሞክራሲያዊት አገር የትንታኔ ድሪቶ በመደረት የትም አንደርስም።

ንፁሃን ዜጎችን እያናቆረ፣ እያጎሳቆለ፣ እየገደለ ፣ እያስገደለና እያገዳደለ የቀጠለውን የጎሳ/የዘውግ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓተ ፖለቲካ በማስወገድ ኢትዮጵያን የመልካም ዜግነት ምድር ለማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ የጋራ ተጋድሎ ለማድረግ አለመቻላችንን ልባችን እያወቀው፦

“እናት ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ ፣

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ። ” የሚለውን መሪርና ጥልቅ አገላለፅ የንግግሮቻችን (የዲስኩሮቻችን) ማድመቂያ እያደረግን የመቀጠሉ ክፉ ልማድ ሊያሳስበን እና አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ እንድንወስድ ሊያስገድደን ይገባል። እያናቆሩ ፣እያጋደሉና እየገደሉ “የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን እየሆነ ነውና ሃሌ ሉያ እያላችሁ ተከተሉን” በሚል ፈጣሪን ጨምረው የሸፍጥና የግፍ ፖለቲካ ቁማራቸው ተባባሪ ሲያደርጉት ህሊናቸውን ጨርሶ ለማይጎረብጣቸው ገዥ ቡድኖች እና እራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የመከራውና የውርደቱ ዘመን ፍፃሜ እንዳይኖረው እያደረጉት ያሉትን የአድርባይነት ፖለቲካ ልክፍተኛ  ወገኖችን በግልፅና በቀጥታ ነውር ነው ማለት የግድ ነው።

በተለይም ተምረናል የሚሉትን እና ከቁማርተኛ ገዥዎች ጋር እየተገለባበጡ (እየተላላሱ) በአቋራጭ የቱጃርነትን ስም ያገኙ ህሊና ቢስ ወገኖችን ከምር በቃችሁ የማለት አስፈላጊነት  ጨርሶ አጠያያቂ ሊሆን አይገባም። አዎ! እየተፈራረቁ መንበረ ሥልጣኑን ከሚቆጣጠሩ ክፉ ገዥ ቡድኖች ጋር በመተሻሸት የህዝብን መከራና ውርደት የሚያራዝም ምሁርነትንና ባለሃብትነትን መፀየፍ ብቻ ሳይሆን አምርሮ መቃወም ወይም መታገል  የነገ ሳይሆን የዛሬ ሥራ መሆን አለበት። እነዚህን ወገኖች ያስተሳሰረውን ሥርዓታዊ መረብ ጨርሶ መበጣጠስ ባይቻልም ለዴሞራሲ በሚደረገው ትግል  ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ትርጉም ባለው አኳኋን ለመቀነስ (ለመቆጣጠር) ካልተቻለ የትም መድረስ እንደማይቻል አውቆ ለዚሁ የሚመጥን የፖለቲካ ሥራ መሥራት የግድ ነው።  ይህ ደግሞ በብዙ ዓመታት አስከፊ የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ተዘፍቀው በኖሩትና አሁንም ያንኑ ሥርዓት ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ባስቀጠሉት ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን ፖለቲከኞች መሪነት በፍፁም ሊሳካ አይችልም። ለዚህ ነው አገራዊ የምክክርና የመግባባት መድረክ አምጦ የሚወልደው የሽግግር ወይም የመሰናዶ  መንግሥት  የግድ ነው ብሎ መከራከር ትክክል የሚሆነው።

አስፈላጊና ተገቢ ሆኖ ሲገኝ አካፋን አካፋ (a spade a spade/call it as it is) ለማለት ዙሪያውን የመዞር ወይም የመሽኮርመም ክፉ ልማድ ተመን የማይገኝለት ዋጋ ለዘመናት  አስከፍሎናልና ዛሬውኑ በቃን ልንለው ይገባል ። ሦስት ዓሥርተ ዓመታት ሙሉ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውና  የከረፋው የህወሃት/ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ኦህዴድ/ኦሮሙማ መራሽ በሆነ “ብልፅግና” እንዲተካ ያደረጉበትን ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ  አደንቁረው ሲገዙት የኖሩት መከረኛ ህዝብ አሁንም  ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ነው ብሎ በድንቁርና የሚቀበላቸው የሚመስላቸው ገዥ ቡድኖች ህሊናቸውን በርካሽ ከሸጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር ከፈጠሩትና እየፈጠሩት ካለው እኩይ የጥቅም ሽርክና ዴሞክራሲ ይወለዳል ብሎ ከማመን የከፋ ድንቁርና የሚኖር አይመስለኝም ።

ይህንን ግዙፍና መሪር  እውነት በአፍ ጢሙ ደፍተው (ዘቅዝቀው) ሊያሳምኑን የሚሞክሩትን አድርባዮች ወይም ሆድ አደሮች ወይም የህሊና ጎስቋሎች  ወይም ወራዳ አሽቃባጮች ያለምንም መሽኮርመም በቃችሁ  ለማለት የሚሳነን ከሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መናፈቃችን ከቅዠትነት አያልፍም።

እውነትን በእውነትነቱ በተግባር ለማሳየት የሚያስችል ሥራ ሳንሠራ “አንድ ቀን እውነት ያሸንፍና አገር አገረ ገነት ትሆናለች” በሚል የምንተርከው ትርክትም አጠቃላይ እውነታ (general truth) እንጅ መሬት ላይ ተዘርግቶ ዘመናት ያስቆጠረውን የእኛን መሪር እውነታ  አይገልፅልንም ። ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከምር እየተነጋገርን ከሆነ ከጅምላና ከደምሳሳ ትርክት አልፈን በመሬት ላይ ተዘርግቶ ከሚነበበውና ከሚጨበጠው የእራሳችን እውነታ ጋር  በግልፅና በቀጥታ ተጋፍጠን ትርጉም ያለው የጋራ መፍትሄ ማበጀት ይኖርብናል።

የእኛ የፖለቲካ እውነታ እኮ በጣም ግልፅና የእያንዳንዱ መከረኛ የአገሬ ሰው የእለት ከለት (በእጅጉ የተለመደ) ህይወት አካል ከሆነ ዘመን ተቆጠረ!

የእኛ የማያወላዳ መሪር እውነት እኮ የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችን እና እራሳቸውን (ህሊናቸውን) በርካሽ አሳልፈው የሚሸጡ ወገኖችን ያጣመረውን ሥርዓተ መረብ በመበጣጠስ አዲስና እውነተኛ ሥርዓት ለመመሥራትና  ለመዘርጋት ያለመቻል ውድቀት መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ከሆነ አያሌ ዓመታት ተቆጠሩ!

አዎ!  እጅግ መሪሩ የእኛ እውነት እኮ የግፍ ግድያ እና የቁም ሰቆቃ ሰለባዎች እያደረገን የቀጠለውን ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ብልፅግና የሚል ስያሜ ሰጥተው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግሩን እያጣደፉት ስለመሆኑ ከገንዛ እራሳችን አይኖች፣ ጆሮዎችና ህሊናዎች በላይ እንድናምናቸው ሲነግሩን ለማመን የሚከጅለን በቁጥር ቀላል ያለመሆናችን አሳፋሪ ፖለቲካዊና ሞራላዊ ዝቅጠት ከሆነ ሰነበተ!

አዎ! የእኛ አስቀያሚ ፖለቲካዊ እውነት እኮ ከዘመናት የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት ከምር ያለመማር ፣ ደጋግሞ የመውደቅ እና ከወደቁበት አቧራን አራግፎ በመነሳት የተነሱበትን ዓላማና ግብ እውን ለማድረግ ወደ ፊት ለመራመድ ያለመቻል አስቀያሚ የፖለቲካ ድህነት ከሆነ ብዙ ጊዜ አስቆጠረ!

አዎ! የእኛ የፖለቲካ እውነታ እኮ ከመሬት ላይ ካለው ወይም በእያንዳንዱ የአገሬ ሰው ጓዳ ውስጥ ከሚስተዋለው እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ይልቅ በሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ባለጌ እና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች የማታለያ (የማደንዘዣ) ዲስኩር ወይም ስብከት ተጠልፎ የመውደቅ ክፉ አባዜ ከሆነ ብዙ ጊዜ ሆነው!

አዎ! የአገሬ ህዝብ መሪር የፖለቲካ እውነታ እኮ  በፖለቲካ ፓርቲ ካድሬዎችና በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ በሚገኙ  አካላት ተባባሪነት አያሌ ንፁሃን ዜጎች በግፍ በሚገደሉበት ፣ በሚፈናቀሉበት እና ለቁም ሰቆቃ በሚዳረጉበት ሁኔታ ውስጥ በፕሮጀክት ጉብኝት ፣ የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ ፕሮግራም ፣  በሰው ሠራሽ ዘዴ ዝናብ ማዝነብ የተቻለ መሆኑን እንደ አዲስ ግኝት በመተረክ፣  ‘ህዝብ ሳይሆን ህዝቦች’ እያሉ መናገር አፓርታይዳዊ አስተሳሰብ ነው በሚል  ማደናገሪያ ወይም አደንዛዥ ዲስኩር ፣ የሃይማኖት ተቋማትን ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ማስገኛ የማድረግ መሠሪ ሙከራ ፣ ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ባህሪ ውጭ  “የፈለገው መከራና ሰቆቃ ቢያጋጥመንም ሁልጊዜና የትም ማሰብ ያለብን ስለ ብልፅግና (prosperity) ነው” በሚል እጅግ የተሳሳተና አደገኛ አተሳሰብ  የተጠመደ  ጠቅላይ ሚኒስትር እመራታለሁ በሚላት አገር ውስጥ መገኘቱ ነው።

የሩብ ምእተ ዓመቱ ህወሃት መራሽ ኢህአዴጋዊ ሥርዓትና ይህንኑ ሥርዓት ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ያስቀጠለው የሦስት ዓመቱ ኦህዴድ/ኦሮሙማ መራሽ የብልፅግና አካሄድ የሚነግረን ይህንኑ የእራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ ነው።

ታዲያ አንድ ቀን እንደሚያሸንፍ  የምጠብቀው እውነት የትኛው ነው? እንዴትስ እውን ይሆናል? ስንት ጊዜስ ይፈጅበታል?  ከእውነት ጋር ተቆራኝተው ለእውነት የቆሙ ወገኖችን ለሃሰተኛና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖችና ግብረበላዎቻቸው ጨካኝ ሰይፍ አሳልፈን የመስጠትን አስከፊ የፖለቲካ ውድቀት ዘላቂነትና አስተማማኝነት ባለው ሁኔታ ፍፃሜ እንዲያገኝ ማድረግ ሳንችል የእውነት አሸናፊነት እንዴት እውን ይሆናል? እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን በአግባቡና በቁርጠኝነት ለመመለስ የሚያስችል አማራጭ የፖለቲካ ሃይል አለመኖሩን የተረዱት ጥቅመኛ አሽቃባጮች (አድርባዮች) ከተረኛ ገዥ ቡድኖች እና ከተለጣፊ የተቃውሞ ፖለቲካ ፖለቲከኞች ጋር የሚያደርጉትን መተሻሸት (መላላስ) በቁጥርም ሆነ በአይነት  አጠናክረው ቢቀጥሉበት ያሳዝን እንደሆን እንጅ ለምን የሚያስገርም ይሆናል

የፖለቲካ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን በአብዛኛው ከቁዘማ እና በግፍ አገዛዝ መንበረ ሥልጣን ላይ የሚፈራረቁ  ገዥ ቡድኖችን እና ግብረ በላዎቻቸውን ከመለማመጥ (ከመማፀን) ክፉ ልማድ ጋር የተያያዘበትን ገመድ በጥሶ የማለፉ ጉዳይ ይኸውና ዛሬም አልትዋጣልንም። በዚህም ምክንያት በአንድ በኩል እኩይ  የቁማር ፖለቲካ ሥርዓቱን በለውጥ አራማጅነት ስም ጉልቻ እየለዋወጡና የማታለያ (የማዘናጊያ) ፍርፋሪ እያሳዩ እንደ ሥርዓት በማስቀጠል ላይ የሚገኙ ገዥ ቡድኖችን እና በሌላ በኩል ደግሞ ህሊናቸውን ለርካሽ ፍርፋሪ ወይም ለሚያልሙት ሌላ “የተሻለ ፍላጎት(ጥቅም)” አሳልፈው የሚሰጡ (የሚሸጡ) ወገኖችን  የሚያገናኘውን ገመድ (የፖለቲካ ሥርዓቱን መረብ) በመበጠስ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር አልተሳካልንም ።

እዚሀ አይነት ክፉ የውድቀት አዙሪት ላይ “መሠረታዊ የሆነ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ በትክክል መልስ ያገኝ ዘንድ የላቀ መስዋእትነት ከፍለናል” ይሉ የነበሩ (አሁንም የሚሉ) እና ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች የዚሁ ክፉ የፖለቲካና የሞራል ድህነት ሰለባ የመሆናቸው መሪር እውነታ ሲታከልበት የሸፍጠኛ ሴረኛ የጎሳ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ቁማርተኞችን ሥርዓት እንዲራዘም ማድረጉ አጠያያቂ አይሆንም።  እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ዋጋ ከፈልንበት የሚሉትን ዓላማና መርህ በአፍ ጢሙ የደፉት በሸፍጥና በሴረኛ ፖለቲካ ጥርሳቸውን ነቅለው ካደጉ ፖለቲከኞች እግር ሥር ወድቀው መንደፋደፍ የጀመሩ እለት ነው። ለዚህ የኢዜማ መሪዎችንና ሂስ አልባ (uncritical or submissive) አባላትን በምሳሌነት መጥቀስ በእውነት በመናገር ወደ እውነት የመቅረብ ደፋርነትን  እንጅ አጉል አሉባልተኛነት በፍፁም ሊሆን አይችልም ።

ታዲያ የትናንቱን መከራና ውርደት ከመቅፅበት እየረሳን ወይም ወደ ጎን እየገፋን፣ ከክስተቶች ትኩሳት ጋር እየሞቅንና እየቀዘቀዝን ፣ ውሸት በእውነት ይሸነፍ ዘንድ አስፈላጊውን ሁሉ ሳናደርግ “እውነት ያሸንፋል!” በሚለው አጠቃላይ አባባል እራሳችንን ብቻ ሳይሆን መከረኛውን ህዝብ ጨምረን እያሳሳትንና እያደነቆርን ፣ በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ዓላማና መርህ ላይ ፀንቶ ከመታገል ይልቅ እገሌ የሚባለው ወይም እገሊት የምትባለዋ የኦህዴድ/ኦሮሙማ/ብልፅግና አባል ወይም ደጋፊ ወይም አሽቃባጭ ለዚህ ወይም ለዚያኛው መሥሪያ ቤት ቢሾም/ብትሾም ይሻላል ወደ እሚል  እጅግ ሰንካላ ወይም የዘቀጠ  አስተሳሰብ እያወረድን ፣ ትርጉም ያለውና ተጨባጭ ሥራ ሳንሠራ ነገን በባዶ ተስፋ እየጠበቅን ፣ የዛሬ  መሪር እውነታችንን የተሸከሙ  አባውራ/እማውራ ፣ጎልማሳ/ወጣት ወገኖችን  እና የነገን እውነት በውስጣቸው የተሸከሙ ህፃናት ዜጎችን የግፍ ግድያ እና የቁም ሰቆቃ ሰለባዎች እያደረግን ስለ የትኛው እውነት ነው የምናወራው (የምንሰበከው) ?  ይህንን መሪር እውነት ከምር ተገንዝቦ “በውስጣቸው እውነትን (truth) ተሸከመው ስለእውነት የተሟገቱንና የሚሟገቱን ንፁሃን ዜጎች መግደል፣ ማስገደል ፣ማሳደድና ለቁም ስቃይ መዳረግ እራሱን እውነትን መግደል፣ ማስገደል ፣ማሳደድና ማቆሳቆል ነውና ሊቆም ይገባል”  ብሎ ከመሟገት ይልቅ በአድርባይነት የወንጀሉ ተባባሪ በመሆን ላይ ያሉ ወገኖች በቁጥርም ሆነ በአይነት (በአይነት ስል አካዳሚሺያን ነኝ ፣ ፖለቲከኛ ነኝ ፣ አክቲቢስት ነኘ  ፣ የሃይማኖት መሪ ነኝ ፣ የኪነ ጥበብ ሰው ነኝ ፣ ባለሃብት ነኝ ባዩን ፣ ወዘተ ማለቴ ነው) እየጨመ ሩበሄዱበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ስለ የትኛው የእውነት አሸናፊነት ነው የምትርከው  እናም ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች እንደ ጉልቻ እየተለዋወጡ የሚቆምሩትን የፖለቲካ ቁማር “ዴሞክራሲን የማዋለድ ሽግግር ነው” በሚል በመከረኛው ህዝብ ላይ ቢሳለቁ  ያሳዝን እንደሆነ እንጅ ምን ያስገርማል?

“ለለውጥ ሐዋርያት” የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ያገለግል ዘንድ በእጅ መንሻነት የተሰጠውን የኢሳት ዋና ሥራ አስኪያጅነትን እና ይፋዊ ባልሆነ (unofficial) የመሥመር ግንኙነት ከቤተ መንግሥት (ጠ/ሚኒስትር) አማካሪነት ጋር አጣምሮ በያዘው በአቶ  አንዳርጋቸው ፅጌ እና ታዋቂ (prominant) እየተባሉ በሚጠሩ ወገኖች አስተባባሪነት “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ!” በሚል መሪ መፈክር ሥር የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ም/ት (senate) ያሳለፈውን ውሳኔ የሚቃወም ገለፃና ሰልፍ ባሳለፍነው ወር (May) መገባደጃ መካሄዱን ተከታትያለሁ።

እንደ አቶ አንዳርቸው ፅጌ አይነት “ለዘመናት መስዋእትነት ከፈልንለት” ከሚሉት እጅግ የተከበረ ወይም የተቀደሰ ዓላማ ፣ መርህ እና ህዝብ ከቸራቸው የከበሬታ ማማ ላይ እራሳቸውን ቁልቁል ያወረዱ (ያዋረዱ) ወገኖች አኳኋን ባይገርመንም ሊያሳስበንና መሪር ትምህርት ሊሆነን ይገባል። በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን እንዲህ አይነት ወገኖች ገና የእሥር ቤት ልብሳቸውን ለመቀየር ጊዜ ሳይኖራቸው የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ በሚጎነጎንበት ቤተ መንግሥት እንዲገኙ የተደረገላቸውን “ታላቅ ጥሪ” ተቀብለው ለርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውል  ምስላቸውን (ፎቶ ግራፋቸውን) ብቻ ሳይሆን ህሊናቸውንም አሳልፈው የሰጡ እለት ነው አሁን ወደ ወረዱበት ቁልቁለት ሊወርዱ እንደሚችሉ ግልፅ የነበረው።

ከዛሬ ሶስት ዓመታት በፊት እንደ አንዳርቸው ፅጌ የመሰሉ ወገኖች እና እንደ የዛሬዎቹ የኢዜማ ከፍተኛ አመር አባላት አይነት ፖለቲከኞች ዛሬ ከሚገኙበት ለሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች (ኦሮሙማ/ኢህአዴግ/ብልፅግና ፖለቲከኞች) ርካሽ የፖለቲካ ባለሟልነት እራሳቸውን አሳልፈው የመስጠት መሪር እውነታ ውስጥ ይገኛሉ የሚል ጥርጣሬ የነበረው የአገሬ ሰው በቁጥር ብዙ የነበረ አይመስለኝም። ግን ሆነ! አድርባይነት እንኳንስ ሊያስተናግደው ፈቃደኛ የሆነን በፍፁም አይሞከርም የሚለውን ህሊናንም የሚፈታተን ክፉ ደዌ ነው ። በአገራችንም  ለዘመናት የሆነውና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ  የቀጠለው መሪር እውነት ይኸው ነው።

ከላይ ለማሳያ ያህል የጠቀስኳቸውን መፈክሮች እና ለዘመናት የመጣንበትንና አሁንም እጅግ አሳፋሪና አስከፊ ሆኖ የቀጠለውን የገንዛ እራሳችንን ሁለንተናዊ ዝቅጠት ከምርና ከቅንነት ማጤን የሚችል ህሊና ላለው የአገሬ ሰው አስተሳሰባችንና አካሄዳችን ሁሉ ምን ያህል ለምንገኝበት ዘመነ ጨርሶ  የማይመጥን እየሆነብን እንደተቸገርን መገንዘብ የሚሳነው አይመስለኝም።

ለሥስት ዓመታት አያሌ ንፁሃን ዚጎቸ በማንነታቸውና በሚያምኑበት ሃይማኖታዊ እምነት ምክንያት የአሰቃቂ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሰለባዎች ሲሆኑ ለምን ዝምታን መረጣችሁተብለው ሲጠየቁ “አይ እኛ እኮ ባለን የውስጥ ለውስጥ ግንኙነት መስመር በጥናት ላይ የተመሠረተ ምክረ ሃሳብ እንሰጣለን እንጅ ጩኸት በተጮኸ ቁጥር መግለጫ አናወጣም” በሚል በህዝብ መከራ ላይ የተሳለቁ የኢዜማ ፖለቲከኞች ዛሬም “ከዴሞክራሲያዊው ምርጫ”  በኋላ ህገ መንግሥት እስከማሻሻል  ወይም እስከ መቀየር የሚያደርስ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ስለሚካሄድ በተስፋ ጠብቁን” ለሚሉንን የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የሚጋሩት ስለመሆኑ እንደ በቀቀን መልሰው ሲያስተጋቡት  ጨርሶ ሃፍረት አይሰማቸውም። ታዲያ ከዚህ የከፋ አጎብዳጅነት ወይም ልጣፍነት የትኛው ነው?

የመውገርገርና የማደናገር ችግር ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ  “ትውልድ እንዳይደናገር” የሚል  ትርክቱን በመጽሐፍ አስጠርዞ ያስነበበን  አንዳርጋቸው ፅጌ ይኸውና የለየለት የአድርባይነት ወይም የባንዳነት (የህዝብ መሠረታዊ ጥያቄ በሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች እንዲኮላሽ መተባበር ባንዳነት ነውና) አሮንቃ (quagmire) ውስጥ ገብቶ ሲዳክር መታዘብ በመርህ ላይ ፀንቶ ለመቆምና ለመዝለቅ የሚችል የፖለቲካ ሰብእና ያለው ፖለቲከኛንና አክቲቪስትን አጥብቆ ለሚፈልግ የአገሬ ሰው በእጅጉ ያማል። እናም ያ ጅግናችን ነው በሚል ያጀገነው አንዳርጋቸው ቁልቁል ተንሸራቶ ህወሃትን ከቤተ መንግሥቱ ፖለቲካ አስወግደው ሥርዓቱን ግን ይበልጥ አስከፊ በሆነ ተረኝነት ካስቀጠሉት ገዥ ቡድኖች ጋር ለምንና እንዴት   በለየለት አድርባይነት ወይም ግብረበላነት ተቀላቀለ?” ብለን መጠየቅ ትክክል ወይም ተገቢ የማይሆንበት አሳማኝ ምክንያት ሊኖር አይችልም ። ይህን ክፉ ልክፍት ጨርሶ ለማስቀረት ባንችልም በነፃነትና በፍትህ ፍለጋ ጥረታችን ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ትርጉም ባለው ሁኔታ መቀነስ  ካለብን እስከ ዚህ ድረስ በግልፅና በቀጥታ መነጋገር ያለብን።

መቸም ነገረ ሥራችን ሁሉ በፅዕኑ ዓላማ፣ መርህና ግብ ላይ ሳይሆን ክስተቶችን እየተከተልን በስሜታዊነት መጋለብ በመሆኑ በተረኝነት የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ  የሚዘውሩ ገዥ ቡድኖችን በአድርባይነት ወይም በአሽቃባጭነት  የተቀላቀሉ እንዲህ አይነት  ወገኖችን “ነውር  ብቻ ሳይሆን ፖለቲካ ወለዱን ወንጀል ማስቀጠል ነውና በአስቸኳይ ወደ ትክክለኛው መንገድ ግቡ” ብለን ከምር ለመቆጣት አልደፈርንም ወይም አልቻልንም ወይም አልፈለግንም። ለዚህም ነው የስም ስያሜና የጉልቻ ልውውጥ እያደረጉ “የሥር ነቀል ተሃድሶ ሂደታችን መዳፈር ማለት የአገርን ልኡላዊነትን መዳፈር ነውና ተጠንቀቁ”  ለሚሉን የጎሳ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ቁማርተኞች እራሳቸውን (ህሊናቸውን) አሳልፈው የሸጡ(የሚሸጡ) ወገኖች በቁጥርም ሆነ በአይነት በመጨመር ላይ የሚገኙት ።

ሦስት ዓመታት ሙሉ በአያሌ ንፁሃን ወገኖች ላይ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ የግፍ ግድያና የቁም መከራ ዶፍ ሲወርድ ፣ ከግድያ ያመለጡ አያሌ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ይኖሩባቸው ከነበሩ ቀየወቻቸው ተፈናቅለው በገንዛ አገራቸው ለአስከፊ ሁኔታ ሲጋለጡ ፣ በርቀት ላይ የሚገኙ ብቻ ሳይሆኑ ከቤተ መንግሥት በጣም ቅርብ የሆኑ ከተሞችና መንደሮችም ሲወድሙ ፣የአገር ልኡላዊነት በጎረቤት አገር (ሱዳን) ሲደፈር፣ የሻእቢያ ወታደር ወደ አገር ቤት ከተሞች ዘልቆ በመግባት በንፁሃን ወገኖች ላይ ዘግናኝ ወንጀል ሲፈፅም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዚህ ሁሉ አስከፊ ወንጀል እጆቻቸው ያስገቡ   ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችን በቃ!  ብሎ በቀጥታና በግልፅ ለመንገር ወኔው ከከዳን ነፃነትና ፍትህ መናፈቃችን ቅዠት  እንጅ እውነት አይደለም ማለት ነው።

እርግጥ ነው በየተሠማሩበት የእውቀት ፣የክህሎት እና ልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ታዋቂነትን (prominence) የሚያተርፉ ወገኖች አሉ ። ታዲያ የእነዚህ አይነት ወገኖች ታዋቂነት ከህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ጋር በተሳሰረ ፅዕኑ ዓላማና መርህ ላይ የቆመ ስለሚሆን  ማንም ፖለቲከኛ ሥልጣን ላይ በወጣ ቁጥር እንደ አንድ የሥልጣን ማስጠበቂያ መሣሪያ (instrument) የሚጠቀምባቸው አይሆኑም። የታዋቂነታቸው መሠረቱና መዳረሻው ከህዝብና ከእውነት ጋር መቆም በመሆኑ ለሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ፈፅሞ አይመቹምና።

ከዚህ በተቃራኒ ግን ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ (ጉልበት ወይም ማታለል) እየተጠቀሙ ፖለቲካ ሥልጣን ላይ የሚወጡ  ሸፍጠኛ ሴረኛ ገዥ ቡድኖች በአገር ልኡላዊነትና ክብር ስም የሚያራምዱትን ርካሽና ጨካኝ የፖለቲካ አጀንዳ አጃቢ (ማራመጃ) ለመሆን ፈቃደኛና ዝግጁ የሆኑ ወገኖች የመኖራቸው አስቀያሚ እውነታ የአስቀያሚው ፖለቲካችን አካል ሆኖ ቀጥሏል።

የዓለም ሃያላን የሚባሉ መንግሥታት እንኳንስ ማስተባበል በማይቻልበት ደረጃ የአደባባይ ምሥጢር ስለ ሆነው የገንዛ እራሳችን የፖለቲካ እብደትና ስላስከተለው ውስጣዊ ቀውስና ሊያስከትል ስለሚችለው አካባቢያዊ ትርምስ ከዚህ መለስ በሚፈጠሩ ጉዳዮችም ብሔራዊ ጥቅማችን ይጎዳል በሚል ያሳስበናል ከማለት ያለፈ እርምጃ ሊወስዱ መቻላቸው በዓለም ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ግኝት አይደለም። ከዚህ መሠረታዊ እውነታ እና አሁን ከምንገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ከአሜሪካም ሆነ ከሌሎች መንግሥታት የቀረቡትን ጥያቄዎችና የተወሰዱትን እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው ከልኡላዊነት መደፈር ጋር ቀጥታ የሚገናኙት? የትኞችስ ናቸው እውነትነት ያላቸውና በዲፕሎማሲ አግባብ ሊፈቱ የሚችሉት? በሚል የበሰለና ሊያስከብርና ሊያከባብር በሚችል ሁኔታ ማስኬድ ሲቻል ልኡላዊነት ተደፈረ በሚል በመንግሥት ደረጃ ሰልፍ አዘጋጅቶ ከተራ ዘለፋና ፉከራ ጋር የተደበላለቀ ጩኸት ማስጪህ  ፈፅሞ የትም አያደርስም ።

እኩይ ፖለቲካቸው ሥጋት ላይ የወደቀ በመሰላቸው ቁጥር ከአገር ልኡላዊነት መደፈር ጋር አንድ እያደረጉ የድረሱልን ነጋሪት ለሚነርቱ (ለሚያስጮሁ) ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች እራስን አሳልፎ መስጠት ከታዋቂነት (prominence) ደረጃ ቁልቁል እንደሚያወርድ ከሰሞኑ እየታዘብን ያለነው ሁኔታ በግልፅ ይነግረናል ። የአገርነትን ትርጉም የተሟላ ከሚያደርጉት አካላት (factors) መካከል ዋነኛ የሆነው የህዝብ መሠረታዊ ልኡላዊነት (በህይወት የመኖርና በነፃነት በመረጠው አካል የመተዳደር መብት) በአስከፊ ሁኔታ የሚደፈጥጡትን ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ትርጉም ባለው ሁኔታ በቃችሁ ለማለት ያልፈለገ ወይም ያልደፈር ታዋቂነት የአገር ልኡላዊነት ተደፈሯልና አብረኸን ጩህ ሲሉት ለምን? እንዴት? እናንተ የደፈጠጣችሁትን ልኡላዊነት ማን እንዲያከብረው ነው ጩኸታችሁን የምንጮኸው? ብሎ ሳይጠይቅ እንደ በቀቀን አብሮ ሲጮህና ሲያጯጩህ መታዘባችን ሊያሳስበንና ተገቢውን ሁሉ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል።

የግዛት አይደፈሬነትን ወይም አገራዊ ልኡላዊነትን እያስደፈረ እና ለዚህ መሠረት የሆነውን የህዝብ ልኡላዊነት እየጭፈለቀ የቀጠለውን የኢህአዴጋዊያን/የብልፅግናዊያን ሥርዓት ተጠያቂ ለማድረግ ያልደፈረ ህሊና እና አንደበት ከውጭ መንግሥታት የቀረበውን በአብዛኛው በእውነትነት ላይ የተመሠረተ ጥያቄን በአግባቡ ከማስተናገድ እና ልኡላዊነትን ይጋፋል የሚባለውን ደግሞ በአግባቡ ለይቶ በሰለጠነ መንገድ ተቃውሞን ከመግለፅ ይልቅ በደምሳሳው ፣ ድብልቅልቁ በወጣ እና በስሜት ትኩሳት በሚናጥ አቀራረብ “ልኡላዊነታችን ተደፍሯልና ተነስ! ድሆች እንጅ ደደቦች አይደለንም! ባንዲራችሁን እስከ ማቃጠል እንሄዳለን! የነቀዘ ስንዴያችሁ ይቅርብን! ኩሩዎች ነን! በእርዳታ አሳባችሁ አታዙንም! ግድቡ የእኛ ነው! ከአባቶቻችን የወረስናትን አገር ለልጆቻችን እናወርሳለን! እብሪት ውስጥ ገብታችኋል! ልኡላዊነታችን ተገፍቷል! አድርጋችሁ የማታውቁትን አደረጋችሁብን! ለእናንተ አሽከር የሚሆን መንግሥት ስለምትፈልጉ ነው! ከውጭ ስንነካ ምን እንደምናደርግ እንተዋወቃለን! ከንፁህ ውሃ በክብር የእለት ውሃ!  ‘እና እድሜ ለቻይና እና ለሩሲያ’ የሚሉ አይነት መፈክሮችን የታዘብንባቸው ሰልፎችንና ዲስኩሮችን ተመልክተናል።

በጥሞና ለታዘበ እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ይህ አይነቱ ትዕይንት የተካሄደው ከእውነተኛ  የአገር ልኡላዊነትና ደህንነት አንፃር ሳይሆን በሸፍጥና በሴራ የተቆጣጠሩት የሥልጣን ዙፋን ከውስጥም ይሁን ከውጭ በሚፈጠር ግፊት (ጫና) ሥጋት ላይ የሚወድቅ በሚመስላቸው ገዥ ቡድኖችና የካድሬ ሠራዊታቸው የታሰበና  የተዘጋጀ መሆኑን ለመረዳት የተለየ እውቀትን ጨርሶ አይጠይቅም

የአገር ልዑላዊነትን  ከእራሳቸው ገደብ የለሽ  የሥልጣን መቀጠል ወይም አለመቀጠል ጋር እያያዙ “አገር ተደፍሯልና በእኛ ላይ ያላችሁን የፖለቲካ ጥያቂ እርሱትና ከጎናችን ቁሙ !” የሚሉንን ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች “ከእናንተ በላይ በዚች አገር (በዚህ ህዝብ) ልዑላዊነት ላይ በቃላት ለመግለፅ የሚያስቸግር ወንጀል የፈፀመና በመፈፀም ላይ የሚገኝ ማነው? ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ በጎረቤት ሱዳን ያስደፈረን ማነው?  የሻእቢያ (የኤርትራ) ወታደር  ቂም በቀል አርግዞ ከድንበር ጥበቃ በማለፍ ወደ ትግራይ ከተሞች ዘልቆ በንፁሃን ዜጎች ላይ እጅግ ዘግናኝ ወንጀል በመፈፀም ልዑላዊነትን እንዲያራክስ የፈቀደለት ማነው? ወዘተ ብለን ሳንጠይቅና ሳንሞግት የምእራቡ ዓለም መንግሥታት  የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት የላቀ ተፅእኖ ፈጣሪነታቸውንና ብሔራዊ ጥቅማቸውን በአሉታዊ ሁኔታ ይጎዳል በሚል የሚያሰሙት ሥጋት  እና ድንበር ተሻጋሪ የሆነው የሰብአዊ መብትም በአስከፊ አኳኋን ተጥሷል በሚል የሚያቀርቡትን ከእውነት የሚነሳ ጥያቄን ልኡላዊነት ተደፈረ በሚል ደምሳሳ ወይም ጅምላዊ በሆነ የአደባባይ ውግዘትና ከገሃዱ ዓለም ጋር በማይሄድ አካኪ ዘራፍነት ለማስተናገድ መሞከር የኢትዮጵያን ረጅምና ጉልህ የዓለም አቀፋዊ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲያዊ ከበሬታ ይቀንሳል ከቶ አይጨምርም።

ከደመነፍስ እንስሳት (አራዊት) በታች ያወረደንን የእራሳችንን የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠት በቅጡ ለማድረግ ሳንችል “የምትሆኑትና የምትሠሩት ሁሉ እራሳችሁን ይበልጥ ቁልቁል ይዟችሁ ከመውረዱም በላይ አካባቢውንም ምስቅልቅሉን ያወጣልና በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጣችሁ ተገቢውን ፖለቲካዊ የጋራ መፍትሄ አምጣችሁ ውለዱ ፤ ይህን ካላደረጋችሁ ግን ከሰብአዊነት አልፎ ለእኛም ብሔራዊ ጥቅም አደጋ አለው”  በሚል የእራሳቸውን እርምጃ የወሰዱትን መንግሥታት ልዑላዊነታችን  ደፈሩብን በሚል የገዥዎች ፍርሃት በሚንጠው ደምሳሳ ( very generalized and somehow distorted ) ስሜት አካኪ ዘራፍ ማለት ጨርሶ የትም አያደርስም።

በመሠረቱ የትኛውም አገር አግባብነት በሌለው ሁኔታ ጣልቃ እየገባ የአገር ልኡአላዊነትን ሲፈታተን አስፈላጊውን መልእክት በግልፅና በቀጥታ ማስተላለፍ ወይም አቋምን ማሳወቅ ትክክል አይደለም የሚል ባለ ጤናማ አእምሮ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

የአንድ አገር ዓለም አቀፍ  ግንኙነት ፖለሲ የሚመሠረተውና የሚወሰነው በውስጥ ፖሊሲዎቹ ጥራትና ጥንካሬ የመሆኑ ጉዳይ የዓለም ፖለቲካና  የዓለም አቀፍ አቀፍ ግንኙነት  ሀሁ ነው። የዚህ መሠረቱ ደግሞ የአገራዊ (የብሔራዊ) ጥቅምን መሠረት ያደረገ ፖለሲ መንደፍና ማራመድ ነው ። ይህ  በአስተማማኝነት እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ አገርን አገር ከሚያሰኙት ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱና ዋና የሆነውን  የህዝብ የሥልጣን ምንጭነትንና ባለቤትነትን (የህዝብ ልኡላዊነትን)  እውን ማድረግን ግድ ይላል። ምክንያቱም አገርን (state) አገር የሚያሰኘው የተወሰነ የግዛት መሬትን (ድንበርን) ፣ በውስጡ የሚኖረውን ህዝብ እና መንግሥታዊ አስተዳደሩን  አጣምሮ  መያዙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ሰው (ህዝብ) ትልቁን ሚና ይይዛልና ነው። ለዚህ ነው ዶ/ር በድሉ ዋቅጀራ (አሁን ያለውን የፖለቲካ አስተሰብና አቋም በትክክል ባላውቅም) “አገር ማለት ሰው ነው” በሚል የግጥም ሥራው የጎሳ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ቁማርተኞች  ሰለባ በመሆን ግራ ለተጋባውና የእራሱን እጣ ፈንታ እያበላሸ ለተቸገረው ለዚህ ወጣት ትውልድ ሃላፊነት እንደሚሰማው አባት ሆኖ  መልእክቱን ያስተላለፈው።

ብዙውን ጊዜ ልኡላዊነትን የምናያይዘው ከአገር ዳር ድንበር አለመደፈር እና በአገር መሪነት ሥልጣን ላይ በሚገኝ መንግሥት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ካለመግባት ጋር ነው። ልኡላዊነት በትክክልና በአስተማማኝ ሁኔታ እውን የሚሆንበትን የውስጥን (የህዝብን) ልኡላዊ የሥልጣን ምንጭና ባለቤትነት አስፈላጊነትን በቅጡ ተረድተን ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን የጋራ ጥረት የማድረጉ ጉዳይ በእጅጉ ይጎለናል። ለዚህም ነው ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች በጉልበት ወይም በማታለል በቁጥጥራቸው ሥር የሚያደርጉት የሥልጣን ዙፋን በውስጥ ትግልና በውጭ ተፅዕኖ ምክንያት  የመነቃነቅ ሥጋት ያጋጠመው በመሰላቸው ቁጥር የአገር ልኡላዊነት አደጋ ላይ ወድቋል ሲሉን ለምን? እንዴት? በማን (በነማን)? እናንተ የፖለቲካ ቁማር መጫዎቻ ያደርጋችሁትን ልኡላዊነት ማን እንዲያከብረው ትጠብቃላችሁ? አሁንስ ይህን አስቀያሚና አደገኛ የፖለቲካ ቁማራችሁን አቁማችሁ ወደ ትክክለኛው ፍኖተ ዴሞክራሲና ፍኖተ ሰላም ለመግባት ዝግጁ ናችሁ ወይ? ብለን ሳንጠይቅ ጩሁ ሲሉን የምንጮኸውና አውግዙ ሲሉን የምናወግዘው።

እራሳቸውን በአድርባይነት ወይም በልጣፍነት  አሳልፈው የሚሸጡ ወገኖች በቁጥርም ሆነ በአይነት ሲጨምሩ እንጅ ሲቀንሱ የማናየውም ለዚህ ነው።

ይበልጥ ግልፅ ለመሆን ቀድም ብየ ከአንዳርጋቸው ፅጌ ጋር በተያያዘ ከጠቀስኩት በተጨማሪ ጥቂት ማሳያዎችን ልጨምር ፦

እነ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ በሚመሩት ምርጫ ቦርድ ተብየ በመካሄድ ላይ የሚገኘው እጅግ አስከፊና አስነዋሪ የምርጫ ተውኔት የሚነገረን በህዝብ መከራና በአያሌ ንፁሃን ደም የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ፖለቲካ ይበልጥ አስከፊ በሆነ ተረኝነት ላስቀጠሉት ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች እራስን በአድርባይነት አሳልፎ  የመስጠትን  ግዙፍና መሪር እውነታ ነው። ይህንን ግልፅና መሪር የሆነ እውነታ በግልፅ፣ በቀጥታና በተገቢው መንገድ ለመጋፈጥ ወኔው ከተሳነን “በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተመርጠናል” በሚል እስካሁን የፈፀሙትንና አሁንም እየፈፀሙ ያሉትን ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የህግ ሽፋን አላብሰው ለመግዛት በተዘጋጁ ገዥ ቡድኖች ቀንበር ሥር ተጨማሪ ብዙ ዓመታትን ለመቁጠር ዝግጁዎች መሆን ይኖርብናል። ይህ እንዳይሆን ግን ቆም ብሎ ለማሰብ ጊዜ የሌላቸው ፣ ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን የተሳናቸው እና እራሳቸውን በርካሽነት አሳልፈው የሚሸጡ ወገኖችን  ያለምንም መሽኮርመም  እውነቱን  መንገር  ግድ ይላል።

እድሜያቸውን እጅግ አሳፋሪና አስከፊ በሆነ የአድርባይነት ፖለቲካ  ልክፍተኝነት የገፉና በመግፋት ላይ የሚገኙ እንደ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አይነት ምሁራን በነፃነትና ፍትህ ፍለጋ ትግሉ ላይ ያሳደሩት፣ እያሳደሩት ያለውና ወደ ፊትም  ሊያሳድሩ አስከፊ ተፅዕኖ የማያሳስበን ከሆነ ስለነፃነትና ፍትህ መጮሃችን በከንቱ ነው ማለት ነው። እናም እንዲህ አይነት ወገኖች የእድሜና የምሁርነት ተሞክሯቸው ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለመጭውም ትውልድ መልካም አርአያነት የለውምና  አደብ በመግዛት ለእራሳችውም ሆነ ለህዝብ የሚበጀውን ያደርጉ ዘንድ  ያለምንም መሽኮርመም  ሃቁ ሊነገራቸው ይገባል። አገር እጅግ አስከፊ በሆነ መከራና ውርደት ውስጥ የመሆኑ መሪር እውነት አሳስቧቸው በታማኝ ባለሟልነት የሚያገለግሏቸውን ገዥ ቡድኖች ለመጠየቅ ወይም እንደ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሀን የአገሩ ጉዳይ ህሊናውን እረፍት እንደሚነሳው ዜጋ ለመቆጣት ያልደፈሩት እንደ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አይነት ወገኖችን  “ጦርነትና ሁለት ተዋጊ ሃይሎች በሌሉበት ተኩስ አቁም ማለት ግራ የሚያጋባ ውሳኔ ነው ፤ ህገ መንግሥቱን ከምርጫ በኋላ ማሻሻል ይቻላል ፣ ወዘተ” የሚሉ የለየላቸው የተራ ካድሬነት የውሸት ትርክቶችን ያለምንም ሃፍረት የሚያናግር የአድርባይነት ክፉ ልክፍት እንጅ ከቶ ሌላ ሊሆን አይችልም።

እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የመሰሉ የቤተ መንግሥት አማካሪ እያጎዎች አስተሳሰብና አካሄድ የማያሳስበን ከሆነ በአያሌ ንፁሃን ዜጎች ላይ ስለ ተፈፀመውና እየተፈፀመ ስላለው የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ የምናሰማው እሪታ (ጩኸት) የምር ሳይሆን ተራ ልማድ ሆኖብናል ማለት ነው።

የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደት ጥንካሬውና ውበቱ የተለያዩ ሃሳቦች (ጠንካራም ይሁኑ ደካማ) በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ፣ የሚፋጩበትና ነጥረው የሚወጡበት በመሆኑ ዲያቆን ዳንኤል ጋር የሚወዳደሩ ወገኖችም በዚሁ መሠረታዊ አስተሳሰብ እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እንደ አንድ ምሁር ነኝ እንደሚል ሰው ከማበረታታት ወይም ሃሳብ ከመስጠት ይልቅ  “ዲያቆን ዳንኤል በሚወዳደርበት የምትወዳደሩ አዘንኩላችሁ “ የሚሉ እንደ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ አይነት ምሁራን ጉዳይ የሚነግረን የፅዕኑ ዓላማና መርህ ድህነትንና ከዚሁ የሚመነጨውን የአድርባይነት ወይም የአሽቃባጭነት ክፉ ልክፍት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል መማር ወይም በፊደል ቆጠራው ብቁ ሆኖ መገኘት ብቻውን ለአገር ወዳድነት ዋስትና የሚሆን ይመስል የሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች የቤተመንግሥት አማካሪ የሆነውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን “ኢትዮጵያን የሚወዳት ዝም ብሎ ሳይሆን በደንብ አውቋት ነው”  በሚል ሊያሳምኑን የሚሞክሩትን  (ግንዛቤያችን ዝቅ ለማድረግ የሚቃጣቸውን ምሁራን) “ምነው እየተስተዋለ እንጅ” ለማለት የምንቸገር   ከሆነ ስለ ዴሞክራሲያዊት አገር ምሥረታ የምናስተጋባው ጩኸት የእውን ሳይሆን የቅዠት ነው ማለት ነው።

እንደ ዮናስ ዘውዴ አይነት ገና ብዙ ረጅም የህይወት ጉዞና ከባድ ሥራ የሚጠብቃቸው  ወጣት ምሁራን በዚሁ ክፉ የአድርባይነት ልክፍት ተጠልፈው  እጅግ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት በተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ትግል ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እንዲቸለስበት የማድረጋቸው አሳፋሪ ተግባር በእጅጉ የማያሳስበንና እራሳቸውን ከዘፈቁበት የፖለቲካ ቁማርተኞች መሣሪያነት እንዲያወጡ በግልፅና በቀጥታ ለመንገር ወኔው የሚከዳን ከሆነ “በገንዛ ወገኖቻችን አስከፊ የባርነት ቀንበር ሥር መኖሩ በቃን!” የሚለው መፈክራችን ባዶ ቃል ነው ማለት ነው።

በዳያስፖራው በኩል ደግሞ በዘመነ ህወሃት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አስፈላጊነትን በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲነግሩን (ሲሰብኩን) የነበሩ እንደ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም አይነት ምሁራን የመለስና የህወሃት የበላይነትን በአብይና በኦህዴድ/በኦሮሙማ ተረኛ የበላይነት ተክቶ የቀጠለውን ሥርዓተ ኢህአዴግ የተቃወመ ሁሉ የተረገመ ነው የሚል አይነት የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠት ውስጥ ሲዳክሩ መታዘብ ህሊናን አሳልፎ የመሸጥ ክፉ ልክፍት እንጅ ሌላ ሊሆን ከቶ አይችልም። “ከለውጡ” ወዲህ የአብይን የፖለቲካ ሰብእና ያላመለከ የተረገመ እንደሆነ አይነት በሚተርኩ እና ከሰሞኑ ደግሞ “አብይንና የሚመራውና ፓርቲና መንግሥት  መድፈር ማለት የአገርን  ልኡላዊነት መድፈር ነው” በሚል አይነት አስተሳሰብ ምእራባዊያን መንግሥታትን በተለይ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናትን በሚኮንኑ (በሚያወግዙ) ፅሁፎች ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የገንዛ አገራቸው ምድረ ሲኦል ስለሆነችባቸው ንፁሃን ዜጎች ጉዳይ  ሂሳዊ አስተያየቶችን ትርጉም በሚሰጥ ሁኔታ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም ።

ከሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ እጅግ እኩይ (evil- driven) የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ በመገላገል ፣ የቡድን መሠረታዊ መብቶች በዜግነት ወይም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር   የሚከበሩበትን ፣ የሰላም ህይወት የሚሰፍንበትን እና የልማት ግሥጋሴ እውን የሚሆንበትን ፍኖተ ካርታ (road map) ሠርተንና ተግባራዊ አድርገን ወደ ፊት ለመገስገስ ያለመቻላችን ውድቀት ነው ዛሬም በአስከፊ አዙሪት ውስጥ እራሳችንን እንድናገኘው ያደረገን ። ለዚህ አስከፊና ተደጋጋሚ ውድቀት ከዳረጉንና አሁንም እየዳረጉን ከሚገኙ ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ደግሞ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ (by hook or crook) እየተጠቀሙ መንበረ ሥልጣን ላይ ለሚወጡ ቁማርተኛ ፖለቲከኞች እራሳቸውን በርካሽነት የሚያቀርቡ ወገኖችን በግልፅና በቀጥታ ነግረን ከቻሉ ወደ ትክክለኛው ህሊናቸው እንዲመለሱ ካልሆነ ግን በሰላማዊ ትግል አስገዳጅነት  ከህዝብ የነፃነትና የፍትህ መንገድ ላይ ገለል እንዲሉ ለማድረግ አለመቻላችን ነው።

ከዚህ እጅግ መሪር ተሞክሯችን ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ተምረን ትክክለኛና ዘላቂ የሆነውን  ፍኖተ ዴሞክራሲ በመከተል እጅግ አስከፊ ከሆነው የፖለቲካ አዙሪት እና እያስከተለ ካለው አጠቃላይ ማለትም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊ እና ሥነ ልቦናዊ  ቀውስ በአሸናፊነት  እንደምንወጣ ያለኝን ተስፋ እየገለፅሁ አበቃሁ!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop

Don't Miss