በአስከፊ ሁኔታ እራሱን እየደገመ የቀጠለው የፈሪዎችና የጨካኞች የፖለቲካ ሴራ – ጠገናው ጎሹ

May 15, 2021
ጠገናው ጎሹ

ፍርሃትና ጭካኔ ምን አገናኛቸው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል እገምታለሁ። ቢነሳም ተገቢ ነውና ወደ ዋናው የአስተያየቴ ክፍል ከማለፌ በፊት የሚከተውን ልበል።

ፍርሃት (fear) በደምሳሳው አላስፈላጊ ወይም መጥፎ ነገር አይደለም።ይሁን ብንልም አይሆንም። ስላልፈለግነው የማናስቀረው ተፈጥሯዊ እውነታ ነውና።ፍርሃት ባይኖር ኖሮ ጉዳት ሊያደርስብን የሚችል ተፈጥሯዊ ወይም ሰው ሰራሽ ክስትት ሲያጋጥመን ያለንን ሃይል ሁሉ ተጠቅመን ከቻልን ለማሸነፍ ካልሆነም ለማምለጥ ባልሞከርን ነበር። የሰው ልጅ ለህልውናው የሚያሰጋውን የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሠራሽ አደጋ የማይፈራ ቢሆን ኖሮ አደጋውን ቢችል አስቀድሞ ለማስቀረት ካልሆነም አስከፊነቱን ለመቀነስ የሚያስችል ዘዴና አቅም ፍለጋ ባልወጣና ባልወረደ ነበር።

ፍርሃት አላስፈላጊ የሚሆነውና ጉዳት የሚያስከትለው ከልክ ሲያልፍና ተጨባጭነትና በቂ ምክንያት የሌለውን ነገር ሁሉ እንደ ሥጋት በመመልከት ከእራስ አልፎ ሌላውንም እረፍት መንሳት ሲጀምር ነው።

እጅግ ልኩን ካለፈ እራስ ወዳድነት ወይም የግልና የቡድን ጥቅመኝነት የሚመነጭ ፍርሃት ደግሞ በእጅጉ አደገኛ ነው። በተገቢው ጊዜና ሁኔታ ካልተገታ ጭካኔን እየወለደ ማህበረሰብን በእጅጉ ጤና ይነሳል። ትውልድንም በእጅጉ ይበክላል። በእንዲህ አይነት ክፉ ደዌ የተበከለ ትውልድ ደግሞ በጋራና ትክክለኛ መርህ ላይ ቆሞ ለእራሱም ሆነ ለሚኖርበት ማህበረሰብ የሚበጅ ታሪክ ለመሥራት ይሳነዋል።

ስለ ፍርሃት ይህን ካልኩ ወደ ዋናው የአስተያየቴ ክፍል ልለፍ፦

የግልና የቡድን ፍላጎትን ያለ ገደብ እውን በማድረግ ላይ የተመሠረተው የሩብ ምእተ ዓመቱ ህወሃት መራሽ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ዋነኛ መለያው አደገኛ ፍርሃትና ጭካኔ የመሆኑ እውነታ ያለፈ ታሪክ ሳይሆን ዛሬም በመሆን ላይ የሚገኝ ግዙፍና መሪር እውነታ ነው። እንዲያውም ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የግፍና የመከራ ዶፍ እያወረደ ቀጥሏል። ይህ እየሆነ ያለው ደግሞ በዚያው እጅግ አደገኛ በሆነ የፍርሃትና የጭካኔ ሥርዓት ውስጥ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉና በአሽከርነት ያገለገሉ ካድሬዎች “ከውስጥ የተገኘን ለውጥ አራማጆች ነን” በሚል ያንኑ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓታቸውን ለማስቀጠል በመቻላቸው ነው። የኖሩበትና ወደ መንበረ ሥልጣኑ የመጡበት የሸፍጥና የሴራ መጋረጃ እያደር ሲገለጥና መከረኛው ህዝብም “እንዴት ሳይውል ሳያደር ቃላችሁን መልሳችሁ በመብላት ወደ መጣችሁበት ክፉ አዙሪት ትመለሳላችሁ?” ብሎ መጠየቅ ሲጀምር ይበልጥ በፍርሃት ራዱ (ተረበሹ)።

ልክ የሌለው ፍርሃት የአገር መሪነት መንበረ ሥልጣንን የሚቆጣጠሩትን ፖለቲከኞች ሲጠናወት አደጋው በእጅጉ አስከፊ ነውና የመንበረ ሥልጣናቸው የጫጉላ ሽርሽር ገና በቅጡ ሳይጠናቀቅ ልክ የለሹን የፍርሃትና የጨካኔ ሰይፋቸውን በየዋህነት እልል ብሎ በተቀበላቸው ህዝብ ላይ መዘዙበት። ይህ ግን የማይጠበቅ አልነበረም። የፖለቲካ ሥልጣንና ካድሬነትን ከኑሮ ዋስትናነት እና የአገርን አንጡራ ሃብት እየዘረፉ ለግልና ለቡድን ቱጃርነት ማዋል በሚቻልበት እንደ እኛ አይነት አገር ውስጥ ሌላ የተሻለ ነገር መጠበቅ የሚቻል አይሆነም። አዎ! በህዝብ፣ከህዝብና ለህዝብ የሆነ ሥርዓተ ፖለቲካ እውን ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ የተሻለ ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ መጠበቅ ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ወራሪው ማን ነው? ተወራሪዎቹስ? – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት

ሩብ ምእተ ዓመት ሙሉ በዚሁ ክፉ ልክፍት የተለከፈ ባለሥልጣንና የካድሬ ሠራዊት ከእውነተኛ ዴሞክራሲ እውን መሆን ጋር ጨርሶ ዝምድና የለውም።ሊኖረውም አይችልም። ምክንያቱም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሆነ ማለት ገደብ የሌለው የግልና የቡድን ፍላጎት (ጥቅም) ማስፈፀሚያና ማስጠበቂያ የሆነው የፖለቲካ ሥልጣን አለቀለት ማለት ነውና። ለዚህ ነው ህወሃት/ኢህአዴግን በኦህዴድ/ኦሮሙማ/ብልፅግና የተኩት ተረኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች በዴሞክራሲያዊት አገር ውስጥ ተከብሮ፣ ተካባብሮና በጋራ በልፅጎ መኖር ጨርሶ አማራጭ የማይገኝለት መንገድ እንደሆነ በተነገረና በተፃፈ ቁጥር ልኩን ከሳተ ፍርሃት የሚወለድ የጭካኔ ሰይፋቸውን የሚመዙት።

ከሰሞኑ ያስደመጡንና ያስነበቡን “ታላቅ ሴራን የማክሸፍ ገድል ዜናም” ከዚሁ እጅግ አደገኛ የሆነ ፍርሃት ወለድ የጭካኔ ፖለቲካ ተፈጥሮና ባህሪ የመነጨ ነው። ዋነኛ ሥራው የአገርን (የህዝብን) ደህንነት መከላከልና ማስጠበቅ ሳይሆን ሥልጣን ላይ የሚቀመጡ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ልኩን በሳተ ፍርሃት በራዱ (በተረበሹ) ቁጥር የጭካኔ ሰይፋቸውን እንዲመዙ የሚያስችል የፈጠራ መረጃ እየፈበረከና እያቀነባበረ ማቅረብ የሆነው የብሔራዊ ደህንነትና መረጃ መሥሪያ ቤት ከሰሞኑ አከሸፍኩት በሚል ያሰራጨው ዜና እንደ አገር እየዘቀጥን ያለንበትን መሪር እውነት ይነግረናል።

ይህ መሥሪያ ቤት (ድርጅት) የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ያሳሰባቸው ፕሮፌሰር አበራ መሸሻ የተባሉ ምሁር የዛሬ ሦስት ዓመት የክልል ፖለቲካ አገር አፍራሽ እንደሆነ ለማሳያነት የፃፉትንና ባለሥልጣናት ሳይቀሩ በይፉ እንዲያውቁት የተደረገን ፅሁፍ (መጣጥፍ) አገር ለማፍረስ የተዘጋጀ ሰነድ በሚል እጅ ከፍንጅ መያዙን በሰበር ዜናነት አስደምጦናል ። “ስለ አዲስ አበባ ዝም አንልም!” በሚል እራሳቸውን በይፋና በግልፅ አሰባስበው በመንቀሳቀስ አዲስ አበባን በአደገኛ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቅዠት ከሚቃዡ ቁማርተኞች ለመታደግ አስፈላጊውን ሰላማዊ ትግል የማድረግ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ አገር ወዳድ ወገኖችን “አገር የማፍረስ ሴራቸውን በማክሸፍ ታላቅ ገድል ማስመዝገቡን” አስደምጦናል ወይም አስነብቦናል።

ለዘመናት የድንቁርና እና የግፍ አገዛዝ ሥርዓት የበላይ አዛዥ ሆኖ የቆየው ህወሃት ሲጠራቸው አቤትና ሲልካቸው ወዴት በሚል ወራዳ በሆነ የአሸከርነት መንፈስ ሲያገለግሉ የኖሩ ካድሬዎች ህወሃትን አስወግደው የበላይነቱን በተረኝነት በመቆጣጠር ብልፅግና በሚል የለየለት የማጭበርበሪያ ስያሜ የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓት በአስከፊ ሁኔታ እያስቀጠሉት እንደሆነ ከዚህ የተሻለ ማሳያ የለም። ህዝብ ለዘመናት ስለኖረበትና አሁንም ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ እየኖረበት ስላለው የገንዛ እራሱ ህይወት ያለውን እውቀት ወይም ግንዛቤ እርባና ቢስ ከማድረግ የባሰ ድንቁርና እና ጭካኔ የለም።

የዚህ አይነት እጅግ የወረደና የተዋረደ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ እርቃኑን በቀረ ቁጥር የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ቁንጮ የሆነውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመከላከል የሚሞክሩ አንዳንድ ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያሳስቱት አማካሪዎቹ እንደሆኑ ለማሳመን ሲጨነቁ ማየትና መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል።ይህን “ትልቅ ሴራና አደጋ አከሸፍን” በተባልን ማግሥትም ይህንኑ ህሊናን ሽጦ የማሽቃበጥ (የኢትዮ 360ውን የሃብታሙ አያሌውን አገላለፅ ልዋስና ውታፍ የመንቀል ልክፍት) ታዝበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከቶ ማን ነው ህገ ወጡ? - ገለታው ዘለቀ

ለዚህ ልፍስፍስና አሽቃባጭ አስተያየታቸው ማነፃፀሪያ ደግሞ “የሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም ትዝታዎች” መፅሐፍ ፀሐፊ ፀሃፊ ገነት አየለ ለቀድሞው የወታደራዊ አምባ ገነን መንግሥት መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ቃለ መጠይቅ ባደረገችበት ወቅት ኮለኔሉ “ለካስ ብቻየን ነበርኩ” በሚል የገለፀውን አገላለፅ የአማካሪ አጦት ችግር አድርገው በመተርጎም የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፈተናም ይኸው እንደሆነ ለማሳመን የሄዱበት መንገድ ባይገርምም በእጅጉ ያሳፍራል። ያስተዛዝባልም።

አዎ! እውነት ነው አማካሪ በስንፍና ወይም በአድርባይነት ወይም በሌላ ምክንያት ሊያሳስት ይችላል። ይህ ግን አጠቃላይ እውነት እንጅ እንደ እኛ አይነት ግልፅና ግልፅ የሆነውን እውነት አይገልፅም። በወቅቱ ስያሜው አብዮት አደባባይ ይባል በነበረው ሰገነት ላይ ቆሞ ጭራቃዊ መፈክሩን ካስተጋባና ተሰብሳቢውም ለመፈክሩ አፉን አለመክፈቱ ቢታወቅበት ሊያጋጥመው የሚችለውን አደጋ እያሰበ እንዲፎክር ካደረገ በኋላ በቀይ ፈሳሽ ቀለም የተሞላ ጠርሙሱን አሳፋልት ላይ በመከስከስ “ደማቸውን እንደዚህ እናፈሰዋለን!” በሚል የዛተ እና ተግባራዊም ያደረገ የአገር መሪ ምን አይነት አማካሪ ነበር የሚያስፈልገው? እንዴትስ አማካሪ ያቆመዋል? ፖለቲከኞች ሁሉንም ነገር በሚዘውሩበት እና የፍትህ አካል ተብየውም የእነርሱ ሰለባ በሆነበት እንደ እኛ አይነት አገር ውስጥ በብዙ መቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ነፍሶችን “በነፃ እርምጃ” አዋጅ ከመኖር ወደ አለመኖር እንዲለወጡ አድርጎ “እንኳን ሰው ዝምብም አልገደልኩም” ለሚል የአገር መሪ አማካሪ አሳሳተው ማለት እንዴት ስሜት ሊሰጥ ይችላል? ይህንን ሰቆቃ ለማስቆም ሰብአዊነትና ቅንነት ያለው ህሊና እንጅ በእውን የአማካሪ ሊቃውንትን ምክር የግድ ይል ነበር እንዴ? አሁንም የግድ ይላል እንዴ?

አሁንም ንፁሃን ዜጎች ሦስት ዓመታት ሙሉ በማንነታቸው እየተለዩ በገንዛ አገራቸውና ቀያቸው የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ ሰለባ ሲሆኑ በአገር መሪነት ሃላፊነት ወቅታዊና ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ላልቻለ ወይም ላልፈለገ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪዎችን ተጠያቂ የማድረጉ ጉዳይ እንዴት አሳማኝ ምክንያት እንደሚሆን ለመቀበል በእጅጉ አይከብድም እንዴ? የወላድ እናትን ሆድ በስለት ተተርትሮ ለወራት ተሸክማ ወደ ዚህ ዓለም መምጣቱን ስትጠባባቀው የነበረችውን ልጇን የሚያስታቅፍ አረመኔያዊ ተግባር ለማስቆም ወይም ላለማስቆም አማካሪ ያስፈልጋል እንዴ? በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በማንነታቸው የጅምላ ግድያና የጅምላ ግባተ መሬት ሰለባ ሲሆን በቃ ለማለት አማካሪን የግድ ይጠይቃልእ ንዴ? በተፈበረከ መረጃና ማስረጃ የንፁሃን ወገኖችን ስም ማጥፋትና ለእንግልት እንዲዳረጉ ማድረግ ነውር ነው ለማለት አማካሪ ግድ ይላል እንዴ? አገር ለንፁሃን ዜጎቿ ምድረ ሲኦል በሆነችበት መሪር እውነታ ውስጥ የቀን ተቀን ውሎውን ወይ ወደ ውጭ አገራት በመጓዝ ወይም የሚጠላውን የአንበሳ ምስል በሚወዳት ግን ከኢትዮጵያ ታሪካዊውም ሆነ ባህል መስተጋብር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላት ፒኮክ በመተካት፣ የቤተ መንግሥት ግቢ በማስዋብ፣ የመናፈሻ ፕሮጀክት ጥናታዊ ፊልምን በተዋናይነት በመተወን ፣ ለርካሽ ፖለቲካ ማዳመቂያነት ግባእት የሚሆን ፕሮጀክት በመመረቅና ለአዲሱ ደግሞ የመሠረት ድንጋይ በማኖር ፣ በየአጋጣሚው በየሃይማኖት በዓላት መካከል ሽር ጉድ በማለትና የየዋሁን አማኝ ህዝብ ስስ ስሜት ለመሳብ (ለመግዛት) በመሞከር የተጠመደ ፣ እና ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ውጭ በሆነ አስተሳሰብ “የሰው ልጅ የፈለገው መከራና ውርደት ቢደርስበትም ሃሴትን ማሰብና ማድረግ አለበት እንጅ ስለመከፋትና ሃዘን ጨርሶ ማሰብ የለበትም” በሚል አይነት እጅግ የተሳሳተ እምነት እራሱን ላሳመነ ፣ ወዘተ ፖለቲከኛ “አማካሪዎችህ እያሳሳቱህ ነውና ተጠንቀቅ” ማለት የለየለት አሽቃባጭነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህውአት መቀበሪያው የት ይሆን? አንቦ ወይስ ጎንደር ወይንስ አዲስ አበባ ላይ። (ከተማ ዋቅጅራ)

ተዋጠልንም አልተዋጠልን ብልፅግና በሚል የማጭበርበሪያ ስም እራሳቸውን በመሰየም እና የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓታቸውን በተረኝነት በማስቀጠል የባሰ መከራና ውርደት አዙሪት ውስጥ ተመልሰው የተዘፈቁ የኦሮሙማ/ብልፅግና ፖለቲከኞች ከዴሞክራሲ ጋር ጨርሶ ዝምድና የላቸውም። የእውነተኛ ዴሞክራሲን እውን መሆንም ፈፅሞ የሚፈልጉት ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱ ፦ ሀ) አብዛኛውን እድሜያቸውን ያዋገዱበት (ያሳለፉበት) ተፈጥሮና ባህሪ ዴሞክራሲያዊ መሪነትን ጨርሶ አይፈቅድላቸውም ለ) በየጎሳው ጓዳ ተወሽቆ ያለ እቅሙ ወይም ያለችሎታው በመከረኛው ህዝብ ደምና ላብ ኑሮውን ሲገፋ የኖረ ባለሥልጣንና ካድሬ ዴሞክራሲን ተቀብሎ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያሸጋግራል ብሎ ማመን መከራና ውርደትን ተቀብሎ ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆን ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ዴሞክራሲ እውን ሆነ ማለት የኑሮ ዋስትና የሆነው የጎሳ ፖለቲካ ቁማር ጨዋታ አበቃለት ማለት ስለሆነ ሐ) የዴሞክራሲ እውን መሆን የተጠያቂነትን አስፈላጊነት ስለሚያስከትል እና ይህ ደግሞ ከአሮሙማ/ብልፅግና የፖለቲካ ተፈጥሮና ባህሪ ጋር በፍፁም አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ነው።

ለዘመናት የመጣንበትን የመከራና የውርደት ሥርዓት ስያሜ ቀይረው በተረኝነት መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠሩት ገዥ ቡድኖች በከፋ ሁኔታ እንዲቀጥል ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያትም ይኸው ነው። ለዚህ እኩይ የፖለቲካ ሥርዓታቸው ማስፈፀሚያ ካደረጎቸውና ወደ ፊትም ከሚያደርጓቸው ዘዴዎች አንዱ ፖለቲካውን ወደ ህፃናት የሌባና የፖሊስ ጨዋታነት ማውረድ ነው። ህፃናትስ እየተዝናኑ ይማሩበታል ። በአገኙት አጋጣሚ ማለትም በጡጫ ወይም እንደ አሁኑ ገና ከጅምሩ በተበላሸ ምርጫ ተብየ መንበረ ሥልጣን ላይ የተቀመጡና የሚቀመጡ ገዥ ቡድኖች እየገደሉና እያስገደሉ ሥልጣናቸውን ያስጠብቁበታል እንጅ ተምረውበት ወደ በጎ ሥራ አይመለሱም። በፍርሃታቸው ልክ ጭካኔያቸውም እየበረታ ይሄዳል ።

ለዚህ ነው እውነተኛ ዲሞክራሲያዊት አገር እውን መሆን ካለባት የሚያዋጣውና ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት የሚያስችለው የጉልቻና የይምሰል ለውጥ ሳይሆን እውነተኛ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ መሆኑን አውቆ ሰላማዊ ግን አስገዳጅ ትግልን ማስቀጠል በእጅጉ አስፈላ የሚሆነው።

ያለዚያ እየተፈራረቁ የሚገዙን ገዥ ቡድኖችና አሸቃባጮቻቸው ወይም ግብረ በላዎቻቸው ፍርሃት በሚወልደው የጭካኔ ቀንበር ሥር ሌላ የብዙ ዓመታት መከራና ውርደት አይነት ለመቁጠር መዘጋጀት ይኖርብናል። ይኸኛው ሳይሆን ከላይ የጠቀስኩት አማራጭ እውን እንደሚሆን እየተመኘሁ አበቃሁ።

 

 

 

1 Comment

  1. ሰሚ ጠፋ እንጂ ግሩም ትንታኔ ነው! እውነቱ ይሄው ነው። “ይበል ነው!” ብለናል ወንድም ጠገናው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share