June 14, 2021
2 mins read

አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ! (በላይነህ አባተ)

 

ዘር ልታጠፋ ልትጨርስ እህል ቡቃያን ስትፈጅ ኖራ፣
አልቅጥ ውጣ ሰልቅጣ ሆዷን እንደ ኳስ ቆዝራ፣
ጉዛሙ በስልት አድፍጦ ጪራሮ ይዞ ሲመጣ፣
ተወጣችበት ጉድጓዷ አይጥ ደንብራ ስትገባ፣
ደብቋት የኖረው ዳዋ ተመጠን በላይ ተመታ፡፡

ዳዋ ተልምድህ ተማር አትደብቅ አይጥና ሌባ፣
እርኩስን መደበቅ ትተህ መግብ በግና ኮርማ፡፡

በእህሎች ቅጥናት ወጥሮህ ተአይጥ ጋር ስትሸርብ ደባ፣
የመከራው ቀን ያልፍና የፍርድ ዘመን ሲመጣ!
አንተ ምን መደበቂያ አለህ አይጥ ጉድጓድ ስትገባ?

አረም ይሉኛል በማለት የእህልን ዘሮች ብትከዳ፣
ተአይጥ ጓጉንችር ተሻርክህ ስታስፈጅ ብትውል አዝመራ፣
በቁናህ መሰፈር አይቀር ዳዋ ሆይ የማታ ማታ!

ባይገባህ እንጅ ባትፈትሽ የአይጦችን የቦካ ሴራ፣
ቡቃያን ምች ሲመታው ቀን ክዶት በልግ ሲጠፋ፣
የአይጦች አፍ ዳዋን ጨርጋጅ ነው ታሪክን ፈትሽ አጣራ፡፡

የዳዋ ራስ ቅል መንፈሱ ተዝቅተኝነት ሳይጠራ፣
እርኩስ በውስጡ ደብቆ እህል አዝመራ ሲያስበላ፣
ጭራሮ አይጥን ሲያባርር አይጥም ጉድጓድ ውስጥ ሲገባ፣
ዘመን ዑደቱን ቀጥሏል አይጥ በበላ ዳዋ ሲመታ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ.ም.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop