August 18, 2013
15 mins read

ለአቡነ ጳውሎስ የመቃብር የነሐስ ሐውልት የተመደበው 1.5 ሚልዮን ብር ነው

የአቡነ ጳውሎስ ሙት ዓመት ትናንት ታስቦ ውሏል። ይህን ተከትሎ በወጡ መረጃዎች የሟቹን ፓትርያርክ የመቃብር ሐውልት በነሐስ ለማሠራት 1.5 ሚልዮን ብር የተመደበ መሆኑ ታውቋል። የሐራ ሙሉ ዘገባ እንደወረደ ይኸው፦
ለሐውልቱ ሥራ የተዋዋለው ተቋራጭ አድራሻውን አጥፍቶ ጀርመን ከረመ
በውሉ መሠረት ከነሐስ የሚሠራውን ሐውልት በ186 ቀን ሠርቶ ማስረከብ ነበረበት
ለጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ‹‹ዝክረ አበው›› እንዲያደርስ ታዝዟል

ነሐሴ ፲ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የተለዩት የአምስተኛው ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኅልፈት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዐት በዛሬው ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማሕሌት፣ በጸሎተ ፍትሐትና በቅዳሴ ታስቦ ውሏል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን የሙታን መታሰቢያ ቀኖና መሠረት በዐጸደ ነፍስ ያሉትን ዕጣን፣ ጧፍ እና መሥዋዕት በማቅረብ ተዝካረ ጸሎት ማድረግ ሥርዐት መኾኑን ከመጽሐፈ ግንዘት እና መጽሐፈ ሢራክ በመጥቀስ ያስረዱት ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ የአቡነ ጳውሎስ ዕረፍት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ የሚካሄደው ‹‹ቅዱስነታቸው በሁሉም አቅጣጫ ያስመዘገቧቸውን የሥራ ውጤቶች በማዘከር›› መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከዐሥራ አንድ ያህል ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ የሙት ዓመት መታሰቢያ ሥነ ሥርዐቱን መርተዋል፤ ንግግራቸውም ‹‹ነፍሰ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያሪክ አባ ጳውሎስን ከማኅበረ መላእክት፣ ከማኅበረ ጻድቃን እንድትደምርልን እንለምንሃለን›› በሚል የተወሰነና የተጠቃለለ ነበር፡፡

ጸሎተ ፍትሐቱ በተከናወነበት የካቴድራሉ ዐጸድ ውስጥ የሚገኘውና ሥራው ያልተጠናቀቀው መካነ መቃብራቸው በእብነ በረድ ተዘግቷል፤ በቆርቆሮ የታጠረው ዐጸድ ዙሪያው ጒንጒን አበባ ተደርጎበት የቀድሞውን ፓትርያሪክ ግዙፍ ምስል በያዘ ባነር ተሸፍኗል፤ ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድያለኹ. . .›› የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ጥቅስ በታላላቅ ፊደላት ሰፍሮበታል፡፡ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዐቱ ተካፋዮች ከጸሎተ ፍትሐቱ በኋላ ወደተቀጸረው የመካነ መቃብሩ ዐጸድ ቢዘልቁም ከዚህ በቀር የሚያዩት ነገር አልነበረም፡፡

የመቃብር ሐውልቱ ሥራ ስለመዘግየቱ የተመለከቱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መድረሳቸውን የገለጹት የጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ሐውልቱ ከነሐስ እንዲሠራ ተወስኖ ሥራውን ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮሚቴ ለክንውኑ በተመደበው ገንዘብ መሠረት ጨረታ አውጥቶ ለአሸናፊው ተቋራጭ ውል ተሰጥቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹በጨረታው ውል መሠረት ተቋራጩ ሥራውን በ186 ቀን ጨርሶ ማስረከብ ነበረበት፤ ባለማጠናቀቁ ለመንፈቅ እንዲያደርስ ተራዘመለት፤ አላደረሰም›› ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ‹‹ስልኩንም አጥፍቶ ነሐሴ 6 ቀን ብቅ ብሎ ጀርመን ነበርኹ ብሎ አረዳን›› ሲሉ እርሱ እየተጠበቀ ሥራው ከውሉ ውጭ እስከ ሙት ዓመት ድረስ መዘግየቱን አስረድተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ለሐውልቱ ሥራ የተመደበው ገንዘብ [1.5 ሚልዮን ብር መኾኑ ተዘግቧል] በባንክ ተጠብቆ እንዳለ መኾኑን ገልጠው÷ ‹‹እብነ በረዱ ተስተካክሎ ተቀምጧል፤ ተቋራጩም ነሐሱን [ከነሐስ የተሠራ ምስላቸውን] አምጥቼ ማቆም ብቻ ነው የሚቀረው ብሎናል፤ በተገባው ውል መሠረት ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሉበት ይመረቃል፤ የዘገየው በእኛ ምክንያት አይደለም፤ ይህን እንድትረዱልን ነው፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በቀድሞው ዘመነ ፕትርክና ይኹን አሁን የፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ገሪማ በንባብ ባሰሙት ዝክረ ፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹በዘመናቸው 49 ኤጲስ ቆጶሳትን አስገኝተዋል›› ብለዋል፡፡ ለአንደኛ ዓመት መታሰቢያ በብፁዕነታቸው ተዘጋጅቶ በሥነ ሥርዐቱ ላይ የተሠራጨውና የፓትርያሪኩን ዜና ሕይወትና ሥራዎች የያዘው ኅትመትም የአቡነ ጳውሎስን ኅልፈት አስመልክቶ የሚከተለውን አስፍሯል፤

ይኹንና ‹‹መኑ ሰብእ ዘየሐዩ ወኢይሬእያ ለሞት፤ ሕያው ሁኖ የሚኖር ሞትንስ የማያይ ሰው ማን ነው?›› /መዝ.88÷48/ ተብሎ በነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በተነገረው መሠረት ቅዱስ ፓትርያርካችን በጾመ ፍልሰታ ለማርያም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመቀደስና ሐዋርያዊ ተልእኮ በመፈጸም አንደኛውን ሱባኤ ካጠናቀቁ በኋላ ነሐሴ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በዐሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ሄደው በመታከም ላይ እንዳሉ ነሐሴ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ከንጋቱ 11፡00 በተወለዱ በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡

ለረጅም ጊዜ የአቡነ ጳውሎስ መጋቤ ሥርዐት ኾነው ያገለገሉት ፕሮቶኮል ሹማቸው ሙሉጌታ በቀለ ስለ ጤንነት ይዞታቸውና ድንገተኛ ኅልፈታቸው ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም በፓትርያሪኩ የቀብር ሥነ ሥርዐት አፈጻጸም ሂደት ላይ ተወያይቶ መርሐ ግብር ለማውጣት ተሰብስቦ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ፊት ቀርበው እንደሰጡት የተነገረው የቃል አስረጅ ደግሞ ፓትርያሪኩ ከተባለው ሰዓት ቀደም ብለው ስለማረፋቸው የሚጠቁም ነው፤

ማክሰኞ [ነሐሴ 8 ቀን] በቅድስት ማርያም አስቀድሰው ነበር፤ ከቅዳሴ ከወጡ በኋላ ከተወሰኑ አባቶችና እንግዶች ጋራ ምሳ በሉ፤ እኔም ወደ ቤቴ ሄድኩ፤ ማምሻውን አመማቸው ተባለና ተጠርቼ መጣኹ፤ ጤንነታቸውን በግል የሚከታተለው ዶ/ር ተጠርቶ መጣና አያቸው፤ ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ብሎ ሄደ፤ ነገር ግን ሕመም ስለጠናባቸው ብዙ ጊዜ ወደሚታከሙበት ባልቻ ሆስፒታል ይዣቸው ሄድኹ፤ ሐኪሞቹ ሲመረምሯቸው ሳምባቸው ውኃ ቋጥሯል፤ ፈቃድዎ ከኾነ ውኃውን እንቅዳው ብለዋቸው ኦፕሬሽን ክፍል ገብተው ተቀዱ፤ ረቡዕ ተሽሏቸው ሰውም ሲያናግሩ ውለው ነበር፤ እኩለ ሌሊት ገደማ ግን ተጫጫነኝ ሲሉኝ ተረኛ ዶክተሮችን ጠርቼ አዩዋቸው፤ ዕረፍት እንዲያደርጉ አዘዟቸው፤ እኔም ከጎን ወደነበረ ማረፊያ ክፍል ሄድኩ፤ ንጋት ላይ ወደ ክፍላቸው ስመለስ ዐርፈው አገኘኋቸው፡፡

በወቅቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ሲናገሩ፣ ‹‹አብረን አስቀድሰን ቢሮም አብረን ቆይተን ነበር፤ ፓትርያሪኩ በስኳር ሕመም ይታወቁ ነበር፤ ጾሙም ሕመማቸውን ሳያከፋው አልቀረም፤ ብቻ ታመው አቅኑኝ ሳይሉ ፃዕር ጋዕር ሳይበዛባቸው ቅዳሴውን ሳያቋርጡ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ነው የሄዱት፤›› ብለው ነበር፡፡

ሌሎች ምንጮች በበኩላቸው የፓትርያሪኩን ሕመም ያከፋው÷ በወቅቱ ይፋ ያልተደረገውን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኅልፈት ሲረዱ በደረሰባቸው ከፍተኛ ድንጋጤና ይህን ተከትሎ ይወስዷቸው የነበሩትን መድኃኒቶች አወሳሰድ ማስተጓጎላቸው ያስከተለባቸው ‘multiple organ failure’ እንደነበረ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡

የፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ቤተ ዘመዶች ‹‹የአቡነ ጳውሎስ ፋውንዴሽን›› ለማቋቋም መንቀሳቀስ መጀመራቸው ከመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች ተሰምቷል፡፡ ይህ ፋውንዴሽን በፓትርያሪኩ ፳ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በሼራተን አዲስ በተከበረበት ወቅት ራእይ ለትውልድ የተሰኘው አካል በስማቸው ‹‹የካንሰር፣ቲቢና ኤድስ የሕክምናና ማገገሚያ ማእከል›› በ200 ሚልዮን ብር ለመገንባት ካቀደበት የበዓለ ሢመት ስጦታ ጋራ ግንኙነት ይኖረው እንደኾነ አልታወቀም፡፡

የፓትርያሪኩ ኅልፈት በተሰማበት ዕለት ረፋድ መኖርያ ቤታቸው፣ በስጦታ ያገኟቸው አይከኖች፣ መስቀሎች፣ አልባሳትና ሽልማቶች የሚገኙበት ሙዝየም ፖሊስና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጠቅላላ አገልግሎት በተገኘበት መታሸጉ ተገልጦ የነበረ ቢኾንም ከአሮጌ አልጋና ካገለገሉ አልባሳት በቀር የተገኘ ነገር አለመኖሩ ተጠቁሟል፤ በምትኩ ፓትርያሪኩ በሽልማት ያገኟቸው አራት መኪኖች የይገባናል ጥያቄ እንደቀረበባቸውና ለዚህም ክሥ እንደሚመሠረት ተሰምቷል፡፡

ቢያንስ ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው በቀድሞው ፓትርያሪክ ንብረት ላይ ለመወሰን የያዘው አጀንዳም በቂ ውይይት እንዳልተካሄደበትና ውሳኔም እንዳልተሰጠበት ነው ለመረዳት የተቻለው፡፡ በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ ፵፭ ንኡስ አንቀጽ (፩) እና (፪) ‹‹ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሀብትና ንብረት›› ግን የሚከተለው ተደንግጓል፤

አንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ከዚህ ዓለም በሞት በሚለይበት ጊዜ የግል የኾነ ገንዘብ ቢኖረው ይረዳቸው ለነበሩ ዕጓለሙታንና ችግረኞች ይሰጣል፡፡ (አብጥሊስ ፴፱)
ኤጲስ ቆጶሱ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ሲያከናውንባቸው የቆዩ መጻሕፍት፣ አልባሳት፣ አርዌ ብርት፣ መስቀሎች፣ መቋሚያዎችና የመሳሰሉት ሁሉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረትነት በስሙ ተመዝግበው በሀገረ ስብከቱ በሙዝየም ይቀመጣሉ፡፡
ነገር ግን እንደ ሕጉ አልኾነም፤ እንዲኾንም ተከታትሎ የሚጠይቅና የሚያስፈጽም አካል ያለ አይመስልም፡፡ እንዲያውም የታዛቢዎች አስተያየት የሚያስረዳው የቀድሞው ፓትርያሪክ ዜና ኅልፈት ከተሰማበት ዕለትና ከዚያም በኋላ የአንዳንድ ጉዳዮች አያያዝ፣ ‹‹ሲደከምበትና በብርቱ ሲፈለግ የቆየው የአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት ብቻ እንደነበረና ሁሉም ነገር ከኅልፈታቸው ጋራ አብሮ ያከተመ የሚያስመስል ነው፡፡››

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop

Don't Miss

eypb

ዋ! እዮብ መኮንን! – ‹‹እግዚአብሔርን ባገኘው የምጠይቀው የዘላለም ሕይወት እንዲሰጠኝ ነው››

በአቤል ዓለማየሁ ጊዜው ከአምስት ዓመት በፊት ነው፤ በሚሊኒየሙ፣ ሚያዚያ ወር