ዋ! እዮብ መኮንን! – ‹‹እግዚአብሔርን ባገኘው የምጠይቀው የዘላለም ሕይወት እንዲሰጠኝ ነው››

/

በአቤል ዓለማየሁ

ጊዜው ከአምስት ዓመት በፊት ነው፤ በሚሊኒየሙ፣ ሚያዚያ ወር የመጀመሪያ ሳምንት፡፡ ሠራበት በነበረው ጐግል ጋዜጣ ‹‹ጥበብ›› አምድ ላይ እንግዳ ላደርገው ረፋድ ላይ ወደ እዮብ መኮንን የእጅ ስልክ መታሁ፡፡ መልካም ፈቃዱን ገለጾ… አንጃ ግራንጃ ሳያበዛ ‹‹ከተመቸህ ዛሬ መገናኘት እንችላለን›› አለኝ፡፡ ትንሽ መዘጋጀት እንዳለብኝ ነግሬው ዛሬ ከሆነ ምሽት ላይ መገናኘት እንደምንችል ነገርኩት፡፡ ጥያቄዎች ሳሰባስብ እና ሳሰላስል ዋልኩ፡፡ የቀጠሮ ቦታ ስላልቆረጥን ከመገናኘታችን በፊት ልደውልለት ተስማማን፡፡ ደወልኩለት!

‹‹ፒያሳ አካባቢ ነኝ፡፡ እዚህ መምጣት ትችላለህ?›› (እዮብ)
‹‹መልካም ግን ትንሽ እንዳልቆይብህ መገናኛ አካባቢ ነኝ፡፡ መሀል ላይ መገናኘት ከቻልን መልካም ነው፡፡ አለበለዚያ ግን ልምጣ››
‹‹እሺ! የት እንገናኝ? መኪና ይዘሀል?››
‹‹መኪና? ይሄ አራት ጎማ ያለው ነገር?››
‹‹ይስቃል››
‹‹አለኝ ግን butter fly ነው፡፡ (የልብስ ስፌት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ከቤት ውጪ አልነዳውም››
እየሳቀ ‹‹እሺ! የት ልምጣልህ››
‹‹ዑራዔል አካባቢ አማካይ ስፍራ ነው፡፡ ፕላዛ ሆቴል እንገናኝ?›› እውነት ለመናገር እኔ የነበርኩት ፕላዛ አካባቢ ይገኝ የነበረው ቢሯችን ውስጥ ነበር፡፡ የጀመርኩትን ሥራ ሳጠናቅቅ፣ ኮምፒውተር ስዘጋጋ፣ እንዳልቆይበት ብዬ ግርጌዬ ላይ እንዲመጣ ጨከንኩበት፡፡ የሚገርመው እኔ ቢሮ ስድበሰበስ እሱ ቀድሞ ፕላዛ ደረሰ፡፡ ሮጥ ብዬ ስደርስ ሆቴሉ ግቢ ውስጥ ጥቁር ቪታራ መኪናውን እየዘጋጋ ነበር፡፡ ሆቴሉ ምግብ አዳራሽ ውስጥ ገበታ ሳይቆርሱ መስተናገድ ባይፈቀድም ቃለ ምልልስ ለመስራት ሳስፈቅድ ይሁንታ አገኘሁ፡፡ የሆቴሉ ባልደረቦች ድሬድ ጸጉሩን የተሸለተውን እዮብን እያዩ ‹‹እሱ ነው/አይደለም›› እየተባባሉ ነበር፡፡
አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ኦሮምኛና ሱማሊኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ እንደሚናገር የነገረኝ እዮብ ቃለ ምልልሱን ከመጀመሬ በፊት ማስጠንቀቂያ አስቀመጠ፡፡
‹‹በድምጽ መቀዳት ስለማልፈልግ፣ ወረቀት እና እስክሪብቶ አውጣ››
‹‹ለምን››
‹‹ከዚህ በፊት ያላልኩትን ብለው መጽሔት ላይ ስላወጡ ይሄን ስህተት መድገም አልፈልግም፡፡ ስለዚህ እየጠየቅከኝ መልሱን ጻፍ!››
‹‹እኔ እንዲህ እንደማላደርግ ከመቶ ፐርሰንት በላይ ቃል ልገባልህ እችላለሁ››
‹‹ኖ! አይሆንም››
ላሳምነው ሞከርኩ፡፡ ሊዋጥለት አልቻለም፡፡ በዚያው ሰሞን አንድ መጽሔት ያልዘፈነውን ራጋ ‹‹የራጋ ስልት ያለው እንትን የተሰኘ ዘፈኑ›› እያለ አልበሙን ጥንብ ርኩሱን አውጥት ስለነበር ፕሬሱ ላይ ያለው እምነት የበለጠ እንዲሸረሸር አድርጎታል፡፡ የመጨረሻ አማራጭ ልሰጠው ጉሮሮዬን ጠረግኩ፡፡
‹‹እውነት ለመናገር መልስህን በቃል እየጻፍኩ አልዘልቀውም፡፡ በዚህ ላይ እኔ እስክፅፍ ስትጠብቅ ሃሳብህ ይቆራረጣል፡፡ ለዛ ቢስ ቃለ ምልልስ ይሆናል፡፡ ማድረግ ያለብኝ [ተገቢ ነው ብዬ ባላምንም] እስከዛሬም ለማንም አድርገነውም ባናውቅም ድምጽህን ወደ ወረቀት ከገለበጥኩ በኋላ (After transcription) አምጥቼ ላሳይህ እችላለሁ፡፡ አለበለዚያ ግን በቃል…››
አመነታ፡፡ እንደምንም አሳመንኩትና ‹‹ሽጉጤን›› ተረክ አደረግኳት [ለእንደ እኔ አይነት ጋዜጠኛ ተብዬ ሽጉጡ ድምጽ ማስቀሪያው ነች፡፡] አወራን፡፡ በቀጣዩ ቀን ምሽት ላይ ይሰራበት የነበረው ፋራናይት ክለብ (ልምምድ ላይ የነበረ ይመስለኛል) ወስጄ አሳየሁት፡፡ አነበበውና ምንም ሳያንገራግር በደስታ ሸኘኝ፡፡ ከዚያም የሚያዚያ 10/2000 ዓ.ም ጐግል ጋዜጣ ላይ ጨዋታውን ዳርኩት፡፡ ካወራናቸው ውስጥ ጥቂቱን እንካችሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "አስማተኛ ወይም ጠንቋይ አይደለሁም" - የታገዱት መምህር ግርማ ወንድሙ

የተለያዩ አይነት የሬጌ ስልቶች አሉ፡፡ አንተ የምትጫወተው የትኛውን አይነት ነው ትክክለኛ (Pure የሆነውን) ሬጌ ትጫወተዋለህ
ሬጌ የተለያየ አይነት ስታይል አለው፡፡ ሩትስ፣ ስካ፣ ዋን ድሮፕና ሌሎችም አሉ፡፡ የምቱ ሁኔታ ነው ሩት፣ ስካ… ሊያስብለው የሚችለው፡፡ እኔ ሁሉንም የሬጌ ቶን እጫወታለሁ፡፡ ስለ እኔ መናገር ቢከብደኝም ሙዚቃ የሚያውቁ ሰዎች በአብዛኛው በትክክል እንደምጫወተው ይናገራሉ፡፡

‹‹ይዞ የመጣው ለአገራችን አዲስ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያሰልፈው የሚችል አዘፋፈን ነው፡፡ ሬጌ የሚፈልገው ነገር አለው፡፡›› ተብሎ ስለ አንተ የተጻፈ ጽሁፍ አንብቤያለሁ፡፡ በዚህ ትስማማለህ?
ጸሐፊው ያመነበትን ጽፏል፡፡ እኔ ከምናገር አድማጭ ቢፈርድ ጥሩ ነው፡፡

በሙዚቃ ስራህ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረብህ ሰው አለ?
አሊ ቢራ እና ቦብ ማርሌይ በጣም የምወዳቸው ድምጻዊያን ናቸው፡፡ የእነሱ ተፅዕኖ አለብኝ፡፡ የሁለቱንም ዘፋኞች ዘፈን ከልጅነቴ ጀምሮ እሰማም፣ እዘፍንም ነበር፡፡

ሬጌ ሙዚቃ መጫወት ያለበት ሰው ምን ማሟላት አለበት?
መጀመሪያ ሙዚቃውን ማፍቀር አለበት፡፡ ከዚያም በደንብ መስማትና ደጋግሞ ልምምድ መሥራት ይኖርበታል፡፡

በአልበምህ ላይ የሰራሀቸው ዜማዎች ተመሳሳይነት አላቸው ይባላል፡፡
በፍጹም አይመሳሰሉም፡፡ ለአንድ የውጪ አገር ዜጋ የትግሪኛ ዜማ ብታሰማው ሁሉም አንድ ዓይነት ነው የሚመስለው፡፡ የእኔም እንደዚያው ነው፡፡ አሰማማችን ነው እንጂ ዜማዎቹ አይመሳሰሉም፡፡

አልበምህ ያሰብከውን ያህል ተደምጧል?

ገና ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ሰውም በበቂ ሁኔታ የሰማው አይመስለኝም፡፡ የተወሰነ ሰው ግን ሰምቶታል፡፡

ለምሳሌ የሚካያ በኃይሉ አልበም ከወጣ ጀምሮ (1999 ዓ.ም.) የወደዱት ቢሆንም ይበልጥ የተሰማው እየቆየ ሲሄድ ነው፡፡ ያንተም አልበም እንደዚያ…
እመኛለሁ ግን እንደዚያ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ አምላክ ነው የሚያውቀው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: የጎደለው ሊቨርፑል

‹‹እዮብ በአብዛኛው የሚጫወተው የሬጌ ዘፈኖችን ስለሆነ ጸጉሩ መለያው ነበር፡፡ ሲቆረጠው ዘውዱን የተገፈፈ ንጉስ መስሏል ያሉኝ አሉ፡፡

ለእነሱ የሚታያቸው እንዳልከው ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን በመቆረጤ ደስተኛ ነኝ፡፡

መቼና ከማን ጋር ስትሆን ደስ ይልሀል?

ለብቻዬ፣ ከጓደኞቼ ጋር ስሆንና መጽሐፍ ቅዱስ ሳነብ ደስ ይለኛል፡፡ ሁሌም አዲስ ስለሆነ ባነበብኩት ቁጥር ይገርመኛል፡፡ ያነበብከውን መተግበር ስትጀምር ይበልጥ አዲስ ይሆንብሀል፡፡ ሌላ መጽሐፍ ማንበብ ትቼያለሁ፡፡

ትልቁ ራዕይህ ምንድን ነው?
አላውቀውም፡፡ ዛሬን ብቻ መኖሬን ነው የማውቀው፡፡ በፕሮግራም ነገ እንዲህ አደርጋለሁ አልልም፡፡ አስተማሪና መካሪ ዘፋኝ ብሆን ደስ ይለኛል፡፡ ስለ ነገ የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው፡፡

አሁን የምትኖረው ሕይወት እና ያለህበት ደረጃ የምትፈልገውን ዓይነት ነው?

ኑሮዬ ይበቃኛል ማለት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሕይወት ደግሞ የምትጣፍጠው አማራጭ ስታጣ ነው፡፡ በሕይወቴ ከዚህ በላይ ብሆንም ካለሁበትም ዝቅ ብልም ምንም አይመስለኝም፡፡ አማራጩ እግዚአብሄር ብቻ ነው፡፡

በቆይታችንየእግዚአብሄርንስምደጋግመህአንስተሀል፡፡ብታገኘውበቀዳሚነትየምታነሳለትጥያቄምንድንነው?
የዘላለም ሕይወት እንዲሰጠኝ ነዋ!

በደረሰበት ደንገተኛ ህመም ቅዱስ ገብርዔል ሆስፒታል ሲታከም የነበረው ከዚያም ለተሻለ ሕክምና ወደ ናይሮቢ አቅንቶ ሳይነቃ በሳምንቱ መጨረሻ ሕይወቱ ያለፈው ተወዳጁ ድምጻዊ እዮብ መኮንን ጋ ያኔ በተገናኘንበት ወቅት አልበሙ እንዲህ ይገናል ብሎ አላሰበም፡፡ ‹‹ታያለህ እንደ ሚካያ አልበም ነው የሚሆነው›› ብዬ ‹‹ስጠነቁል›› አልመሰለውም ነበር፡፡ ሥራው ከገነነ በኋላ ‹‹አላልኩህም ነበር!›› ብዬ ከመፎከር አልቦዘንኩም፡፡ አንድ ቀን አጋጣሚ ቦሌ አካባቢ አግኝቼው አንድ ካፌ ትንሽ ተቀምጠን አወራን፡፡ አወራን ከማለት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሰብከኝ ነበር ማለት ይቀላል፡፡ ልቡ ተሰብሮ፣ ግንኙነቱ ከአምላኩ ጋር ብቻ ይመስል ነበር፡፡ ዛሬ በ9 ሰዓት በሥላሴ በተፈጸመው የቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ጥቅምት 12/1967 ዓ.ም. መወለዱ የተነገረው እዮብን ሁኔም በማይሰለቹ ዜማዎቹ እናስታውሰዋለን፡፡ በርካታ ሰውም በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በመገኘት ሀዘኑን ገልጿል፡፡ እንደተመኘውም በላይኛው ቤት ‹‹የዘላለም ሕይወት እንዲሰጠው›› እመኛለሁ፡፡ ዋ! እዮብ! ከልቤ አዝኛለሁ! ነፍሱን ይማረው!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሶዶ ፖሊስ ማየት የተሳናቸው ተማሪዎች ላይ ድብደባ ፈጸመ

2 Comments

  1. ልቤ በጣም አዘኗል ኢዪብን የማወቀው ገና ድሬድ ሲጀምር እና ወደ ሙዚቃው አለም ለመግባት ሲያኰበኩብ ነበር በመ፧ቅዱስ መወያየትም ይወድ ነበር አምላክ በምህረት ያስበው።

  2. Zehabesha፣ በጣም አመሰግናለሁ ይህንን ሰው በሞቱም እንኳ ቢሆን ስላስተዋወቃችሁኝ። ስሙን ከዚህ ቀደም ሰምቼው አላውቅም። በጣም አዘንኩ። አበባ ይህን ሊንክ ልካልኝ ተጨማሪ ትምህርት አግኝቼአለሁ። ቤተሰቡን እግዚአብሔር ያጽናቸው። አሜን
    http://www.ethiopianchurch.org/editorial2/177-%E1%8A%A2%E1%8B%AE%E1%89%A5-%E1%88%98%E1%8A%AE%E1%8A%95%E1%8A%95%E1%8A%93-%E1%8A%A5%E1%8C%8D%E1%8B%9A%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%88%94%E1%88%AD.html

Comments are closed.

Share