ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ሰሞኑን በአንድ ክፍለ ከተማ ከሚሠራ ሰው ጋር በሆነ አጋጣሚ ተገናኝተን የመጨዋወት ዕድል ነበረኝ፡፡ ከጭውውታችን እንደተረዳሁት ብልሽትሽቱ የወጣው የአቢይ አህመድ መንግሥት ፀሐይ የሞቀው ሰው ሁሉ የሚያውቀው ገመና በኢትዮጵያ ትንሣኤ ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርጋል፡፡ ኢትዮጵያ ልክ በነዮዲት ጉዲትና በነግራኝ አህመድ ዘመን እንደሆነችው ከውድቀቷና ከሞቷ በኋላ የመነሣት ታሪካዊ ዕድልና መለኮታዊ እገዛ ያላት መሆኑ ባይካድም የአሁኑ ሁኔታዋ ግን እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ አብዛኛው ዜጋዋ ከሞራልና ከሃይማኖት፣ ከባህልና ከወግ ልማድ አፈንግጦ ኅሊናውን ለዕለት ጉርስና ለዓመት ልብስ በሸጠበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ከሞት ብትነሣ ማንኛችን ነን ወደቀደመው አንጻራዊ የጨዋትነና የፍትኅ ሥርዓት የምንመልሳት? ትልቅ ወቅታዊ ጥያቄ ነው፡፡ በቁማችን ሞተናል፡፡ ከዚያ ሰው ጋር ወደነበረኝ ጨዋታ ልመለስ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚሠራ የጊዜው ሰው ነበረ፤ በዚህ ሰሞን ግን ከቦታው ተነስቶ ወደሌላ የሥራ ክፍል ተዛውሯል፡፡ ከላይ እስከታች የታወቀ እጅግ ሲበዛ ሙሰኛ ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ዝምቡን እሽ አይልም፡፡ ሁሉም በተመሳሳይ የሙስና ባቡር የተሣፈረ በመሆኑ ግፋ ቢል በገንዘብ ቅብብሎሽ ይጠቃቀማሉ እንጂ ማንም የማንንም ጫፍ አይነካም፡፡ እናም ሰሞኑን ምን ሆነ – ያ ሰው ከብዙ አቅጣጫ የሚሰነዘር ቅሬታ በዛበት፡፡ በኮሪደር ልማት ስም ከሚነሱ ሰዎችና መንደሮች ብዙ ብር እየተቀበለ ያስነሳና በአዲስ አበባ ዙሪያ ኩርማን መሬት ይሰጣል፡፡ የሚቀበለው ገንዘብ ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡ አሥራ አምስት ሚሊዮን ከፈቀደ ሰባቱ ወይ ስምንቱ በርሱ አካውንት እንዲገባ ተደርጎ ነው – አለበለዚያ ባለጉዳዩ ጨረቃ ላይ መቅረቱ ነው – የትም ቢጮህ ደግሞ ሰሚ የለም፡፡ ሀገራችን ጆሮዎቿንም ዐይኖቿንም ተነጥቃለች፡፡ አሁን ጉዳዩ ወደ ክስ ሲያመራበትና ተቀናቃኞቹም ሲቀኑበት ለፖሊስ 60 ሚሊዮን ብር ሰጥቶ ክሱን አዘጋው፡፡ ያ 60 ሚሊዮን ለስንቱ ከፍተኛና ዝቅተኛ የፖሊስ ወንጀል ምርመራ ባልደረባ እንደሚከፋፈል እዚያው ያሉት ይወቁት፤ ምን አገባን እኛን፡፡ አዲስ አበባ የፈራረሰችውና ገና የምትፈራርሰውም በዚህ መልክ በሙስና በተጠመዱ የፌዴራልና የአዲስ አበባ መስተዳድር የመሬት ይዞታ ባለሥልጣናት የሙስና ትስስር ነው፡፡ የ40 እና የ50 ሚሊዮን ግምት ቤትና መሬት በሁለትና በሦስት ሚሊዮን እየተገመተ፣ ሙስና ካለበት ደግሞ አሥር ተገምቶ ሦስትና አራቱ ለባለሥልጣናት ኪስ እየገባ ሕዝብ በዚህ መንገድ እየተፈናቀለና እየተራቆተ ነው፡፡
በሌላ የሙስና መረጃ – አንድ መርማሪ ፖሊስ ለምሣሌ የአምስት ሚሊዮን ኬዝ (የክስ መዝገብ) ቢይዝ ከተከሳሹ ጋር ይሞዳሞድና አንድ ሚሊዮን በመቀበል ክሱን እንደምንም ብሎ ደብዛውን ያጠፋለታል፡፡ ተከሣሹም በደስታ ሥራውን ይቀጥላል፡፡ ይህ ማለት 1500 ብር ይቀጣ የነበረ ሹፌር ለያዘው ትራፊክ ፖሊስ 500 ብር ጉቦ ከፍሎ ከገንዘብ ኪሣራም ከውጣ ውረድም እንደሚድነው ማለት ነው – በነገራችን ላይ በዚያን ሰሞን አንድ ትራፊክ ፖሊስ 200 ብር ጉቦ ተቀበለ ተብሎ ሲንገላታ አይተን ነበር፤ 200 ብርና 60 ሚሊዮን ብር ምንና ምን እንደሆኑ አስቡት፡፡ አንድም የሀገሪቱ ባለሥልጣን ከሙስናና ከምዝበራ ነፃ ባልሆነበት ሁኔታ ያቺን 200 ብር በተቀበለ ደምብ አስከባሪ ትራፊክ ፖሊስ በዚያ መልክ የሚዲያ ሰዓት ማባከናቸው ይገርማል – ውስጣቸው እውነቱን እያወቀ – አቅራቢው ራሱ እኮ እልል የተባለለት ሌባና ሙሰኛ ነው፤ “አንዱ ባንዱ ሲስቅ ጀምበር ጥልቅ”፡፡ ከዚህ አኳያ የጉቦው ነገር – የሙስናው ደረጃ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ቢሮ የሚፈጸም ሆኖ መጠኑ ደግሞ ድሃ አይነካሽ ሆኗል፡፡ መሬት ይዞታ ላይ ያሉ ሠራተኞች መቶና ሁለት መቶ ሺህ መጠየቅ ካቆሙ ቆዩ፡፡ ዛሬ የሚጠየቀው ሙስና በትንሹ ከ500 ሺህ ብር ጀምሮ ነው – ይህም በትልቅ ሆቴል የሚደረገውን የፍየል ቁርጥና ጮማ በልቶ በአናቱ የሚረፈረፈውን ውስኪ ሳይጨምር ነው፡፡ ሀገራችን ውስጥ የሚታየው የሀብታምና የድሃ ልዩነት ደግሞ ሲሰማ ይሰቀጥጣል፡፡ ለመንግሥት ባለሥልጣናት በየሆቴሎች በሚሊዮኖች እየመደቡ በየቀኑ መሄድና ሒሣብ ማወራረድ ሳይኖርባቸው እነዚህን ነቀዞች የሚቀልቡና የሚያንደላቅቁ ሀብታሞችም አሉ፡፡ ሀገሪቱ ባጭሩ ለ98 መቶኛው ዜጋ የለየላት ሲዖል ስትሆን ለቀሪዎቹ ደግሞ በዘርና በጎሣ፣ በእሽክርናና በባንዳነት ተደራጅተው የናጠጡ ሀብታሞች በሰው ሬሣና የሰው ደምና አጥንት ላይ የሚምነሸነሹባት አኬልዳማ ሆናለች፡፡
በዚህ መልክ የተዋቀረን ማኅበረሰብ ማን ነው ነፃ የሚያወጣው? ከማንስ ነው ነፃ የሚወጣው? በዚያ ላይ ነፃ እናወጣሃለን የሚሉት ወገኖች ራሳቸው የተዘፈቁበት የኢ-ሞራላዊና የኢ-ሃይማኖታዊ ብልሹ ምግባር ሲታይ ዙሪያ ገባው ተስፋ አስቆራጭና አስደንጋጭ መሆኑ አይካድም፡፡ በሃይማኖት ረገድም ያለው ሁኔታ እንደዚሁ ወሽመጥን የሚበጥስ ነው፡፡
ልትወልድ እንደተቃረበች የዘጠኝ ወር ድርስ ሴት ሆዳቸውን አንገፍጥጠው፣ ጫማቸውን ሲያስጠርጉ እንኳን በቀልድ እንደምናውቀው “እኔ ባላይህ እግዚአብሔር ያይሃልና በደምብ ቀለም ቀባልኝ” የሚሉ በ“እክሀደከ ሰይጣን” ሳይሆን በ“እክህደከ ክርስቶስ” አጋንንታዊ ድግምት ወመተት የቆረቡ ዓለማውያን ጳጳሣትና ኤጲስ ቆጶሣት፣ ካህናትና መዘምራን የሞሉባት ቤተ ክርስቲያንም በሣጥናኤል ፈተና ክንዷ ዝሎ እንኳንስ ለሀገር ለራሷም አልሆነችም – በኦሮሙማ ሥልታዊ አካሄድ እየፈራረሰች ነው፤ ከቡና ቤት ጭፈራ ወደ ጵጵስና፣ ከንግዱ ዓለም በቀጥታ አቡነ ዘበሰማያትንና ሰላም ለኪን እንኳን በቅጡ በቃል ሳይዘልቁ በ3 ሚሊዮን ብር የወዲያው ክፍያ ማዕረገ ጵጵስና የሚገኝባት ሀገር ሆናለች፡፡ “ዲቃላ ነውና አማራን ባገኛችሁበት አጥፉ” የሚሉ አባ ሠረቀንና የመሳሰሉ የትግሬና የኦሮሞ ጳጳሣትም እንደተፈጠሩ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ የጉድ መፍለቂያ ሀገር ከሆነች ሰነባበተች፡፡
ይሄውና እንደምናስተውለው ቀደምት ጅላጅል ፖለቲካውያን በ”ቸ” እና በ”ሸ” (እናቸንፋለንና እናሸንፋለን)፣ በላባደርና በወዛደር … ዱላ ሲማዘዙ እንዳልነበር ሁሉ “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” እንዲሉ ሆነና ያሁኖቹ ሥራ ፈት ካህናትም ቅድስት ማርያምን “ቤዛ ናት”፣ “ቤዛ አይደችም” በሚል መወራከባቸውን ቀጥለዋል፡፡ መረገም ነው፡፡ አገር ምድሩ ሰላም አጥቶ በድሮንና በታንክ እየታመሰ፣ አማራ ክልል በርሀብና በጦርነት እየወደመ፣ ትግራይ በበጀትና በነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም በአጓጉል አስተዳደር እየተቃወሰች፣ ኦሮሞውም በገዛ ልጆቹ አላንዳች ርህራሄ እየተመታ፣ ከአዲስ አበባ 50 እና 60 ኪሎ ሜትሮችን መውጣት በሚሊዮኖች የሚገመት ብር ለእገታ ድራማ እያስጠየቀ፣ የኑሮ ውድነቱ ከጦርነትም በልጦ ሚሊዮኖችን በድብቅ ርሀብ እያረገፈ (አንድ ኪሎ ታጥቦ የተቀሸረ ቡና ከ1000 ብር በላይ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ በተስፋ መቁረጥ ዜጎች በየቀኑ ራሳቸውን በገመድ እያንጠለጠሉ፣ በብዙ ቦታዎች በተለይም በአማራው አካባቢ ትምህርት ቆሞ ከ10 ሚሊዮን የማያንሱ ሕጻናትና ልጆች ወደ ድንቁርናው የጨለማ ዓለም እየተገፉ፣ ለዚህ ሁሉ ችግር መዘዝ አንድ “እናቴ ተንብያልኛለች” የሚል ወፈፌ እንደፈለገ ሀገሪቱን ሲጫወትባት እየታዬ፣ ሙስና ከፍ ሲል እንደተገለጸው እግር አውጥቶ በግልጽ እየተራመደ፣ ከዚህ ሁሉ ችግር ጎን ለጎን ደግሞ ይሄው ወፈፌ መሪ ለግሉ መጠቀሚያ በትሪዮን በሚገመት ብር ቅንጡ ቤተ መንግሥት እያሠራ፣ የሀገሪቱ ፋይናንስ ከጦርነትና ከኮሪደር ሥራዎች ባለፈ ደሞዝ መክፈል እንኳን እያቃተው፣ ሚሊዮኖች እየተሰደዱ ለበረሃ ዐውሬና ለባሕር ጉማሬ እንዲሁም ለሰውነት አካላት መለዋወጫነት ሲባል ለጨካኝ በላቾች እየተዳረጉ፣ መንግሥታዊና ቡድናዊ ዝርፊያው ዜጎችን በቁም እየገደለ ባለበት በአሁኑ ወቅት…. አንዳንዱ – የደላው – በቃላት ይጫወታል፤ አንዳንዱ በሰው ስቃይ ይዝናናል፤ አንዳንዱ በሀገር ሀብት ዘረፋ ይሠማራል፤ አንዳንዱ ባልደከመበት የሀገር ሀብት ልጆቹን በአደባባይ ድሮ ይሞሽራል፤ አንዳንዱ ስለሁለት ታዋቂ ሰዎች ትዳር “ተጨንቆ” ሚዲያውን ያጨናንቃል፡፡ የገባንበት አረንቋ ሲታይ “ኢትዮጵያ የት ገባች?” ብለን እንድንጠይቅና በመልስ ፍለጋ እንድንንከራተት ያደርጋል፡፡ በቅርጽ እንጂ በይዘት እኮ የለንም፡፡ ነገ መኖሩ በጄን እንጂ እንደዛሬ ቢሆን ኖሮ ሞትን የሚያስመኘው ብዙ ነው፡፡
ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ይባላል፡፡ የአቢይን “በቅርቡ ይረግፋሉ” ብሎ በዚያን ሰሞን የተናገረውን የጭካኔ አነጋገር ሳላነሳ መጨረስ ግን አልወደድኩም፡፡ ይሄ ዐረመኔ ሰውዬ ኢትዮጵያን መጥላቱን ከምንረዳለት አንዱና ዋናው ስለቀድሞዋ ኢትዮጵያ የሚያቀነቅኑ የየትኛውንም ብሔር የዕድሜ ባለፀጋዎችን አምርሮ የሚጠላና ለሞታቸውም ትልቁን ሚና የሚጫወት መሆኑን ስንረዳ ነው፡፡ ያባቴ አምላክ ራሱን ያርግፈውና ባለፈው ሰሞን ለዚያውም ስብሰባ ላይ በርሱ እሳቤ አገዛዙን የሚያውኩት ትላልቅ ሰዎችን በተመለከተ ጥይት ሳናባክን በዕድሜያቸው ምክንያት “እንደቅጠል ይረግፋሉ” ሲል በልዩ ትዕቢትና ሰዎቹ ላይ ባለው ጥላቻ ተወጥሮ የተናገረው የዚህን ሰው ሰይጣናዊ ተፈጥሮ ለአንድ ሺህኛ ጊዜ ይፋ አድርጓል፡፡ በቤቱ ከዝናሽ ጋር ቢለው የራሱ ጉዳይ በሆነ፡፡ የሁሉም ዜጋ እኩል መሪ ሆኖ ግን በአደባባይ እንዲህ መናገሩ ስለሰውዮው ማንነት በተለይ የማያውቁትን ግራ ያጋባል፡፡ ለነገሩ ከዕብድ ምንም ደህና ነገር አይጠበቅም፡፡ ይህን ሰይጣን የፈጠረ ማሕጸን እስከወዲያኛው የተረገመ ይሁን! መራገም መብቴ ነው፡፡ ጴንጤ ብሆን ኖሮ እንዲያውም “የአቢይን መንፈስ ወጋሁት!” ብዬ በጸለይኩና በገላገልኳችሁ ነበር – የጴንጤ ጸሎት ጴንጤን ካስወገደ፡፡
ሌላው መናገር የምፈልገው ነጥብ – አምባገነኖች በሁለት እንደሚከፈሉ የሚሰማኝን ነው፡፡ ሀገር ወዳድ አምባገነን፤ ሀገር ጠል አምባገነን፡፡ በመሠረቱ አምባገነኖችን የሚያስተሳስሩ ብዙ ባሕርያት አሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ የሚለያዩባቸው ነገሮችም አሉ፡፡ ሀገር ወዳድ አምባገነን በሥልጣኑና በሀገሩ ሲመጡበት ትግስት የለውም፡፡ ሀገር ወዳድ ዜጎችን ግን ያከብራል፤ ይሾማልም፡፡ ሀገር ጠሉ አምባገነን በተቃራኒው በሥልጣኑ ብቻ ሳይሆን እየጠላት በዕውር ድምብር የሚገዛትን ሀገር የሚወዱ ዜጎችን ሳይቀር እያሳደደ ይፈጃቸዋል፡፡ ከያሉበት በመብራት እየተፈለጉ የሚሾማቸው ሰዎች ደግሞ ሀገር ጠልና ያልተማሩ ናቸው፡፡ በዚያም ላይ ሲመረጡ በዘር ሐረግ መሥፈርት የሚጠቆሙ፣ ምንም ነገር የማያገናዝቡና በዕውቀትም በችሎታም ከሀገር ጠሉ አምባገነን በእጅጉ የዘቀጡ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ፍጹም ታዛዥና ሆድ እንጂ አእምሮ የሌላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ሀገር ወዳድ አምባገነን ከሀገር ጠል አምባገነን ባነሰ አጭር የሥልጣን ዘመን ሥልጣኑን የሚያጣው እንግዲህ ለዚህ ነው፡፡ ሀገር ወዳድ አምባገነን ከሚሾማቸው ሀገር ወዳድ ሰዎች መካከል አያያዙን ያዩና አምባገነኑ መሪ ነገር እያበላሸ ሲመጣ በመፈንቅለ መንግሥትም በሌላም መንገድ ያስወግዱታል፡፡ ሀገር ጠሉ አምባገነን ግን የሚኮለኩላቸው ባለሥልጣናት ሁሉ ከሞላ ጎደል በሁሉም ረገድ ከርሱ ያነሱና ምንም ዓይነት የሞራልም ሆነ የሥነ ልቦና ልዕልና ስለሌላቸው ያን ሀገር ጠል አምባገነን በማምለክ እስከወዲያኛው ይጸናሉ – ባጋጣሚ አእምሮ ያላቸው ቢገኙ ራሳቸውን ደብቀው ግን ተመሳስለው ይኖራሉ – ሙስና ውስጥ አለመግባታቸውና ጠቃሚ ሰላማዊ ምክር መሰንዘራቸው በራሱ በሌላ ነገር ሊያስጠረጥራቸው እንደሚችልም የታወቀ ነው፡፡ “ሲጠሩት አቤት፤ ሲልኩት ወዴት” የሚል ባርያ ደግሞ እንደፈጣሪ ለሚቆጥረው ጌታው ታማኝ ነውና የጭንቅ ቀን ካልመጣ እንዲህ በቀላሉ አይከዳም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሰው የሚመለመሉ ወታደሮችም ግደሉ ሲሏቸው “ስንት?” እና “እነማንን?” እንጂ “ለምን?” ብለው አይጠይቁም – ሃራም ነው – ትልቅ ነውር፡፡ የቅጥር ጥያቄዎቹም ለምሣሌ “በግና ፍየል የጓሮ አትክልት ናቸው፤ ሀሰት ወይንስ እውነት?” ተብሎ የተጠየቀ ምልምል ወታደር “ሀሰት” ብሎ ከመለሰ ማሰብ ይችላልና አይቀጠርም፤ “እውነት” ካለ ግን እንደሰው የሚራመድ አእምሮቢስ እንስሳ ተገኝቷልና በደስታ ይቀጠራል፡፡ ከዚያም ብሬንና ዲሽቃ ተሰጥቶት ወደአማራው ክልል ይላካል፤ በዚያ አካባቢ የሚገኝን አማራ ሰደቃውን ያወጣለታል፤ ዜጎችን ወንድ ከሴት፣ ሕጻን ከዐዋቂ ሳይለይ ይደፍራል፤ ደፍሮም ብቻ አይተውም በአሰቃቂ ሁኔታ ይገድላል፡፡ መሠረታዊ የልማትና የአገልግሎት አውታሮችን ያወድማል፤ ክምር ያቃጥላል፤ ዘርፎ መውሰድ የማይችለውን ሁሉ እህልን ጨምሮ በእሳት ያጋያል፡፡ ወይ ኢትዮጵያ! ስንቶቻችንን ይሆን እንደዚህ የምታስለፈልፊ? በቃሽ ይበልሽ፡፡ ፈጣሪ ወደልቦናችን እንዲመልሰን በርትተን እንጸልይ፡፡ የገባንበት አዘቅት ቀላል አይደለም፡፡ እንዴ – “ኢየሱስ ኦሮሞ ነው” ብሎ በልበ ሙሉነት የሚከራከር የጴንጤ ፓስተር ያለባት ብቸኛዋ ሀገር እኮ የኛዋ ኢትዮጵያ ናት! “አሥራ ሁለቱ የዶሮ ብልቶች አሥራ ሁለቱን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚወክሉ ናቸው” ብሎ ዐውደ ምሕረት ላይ ሲሰብክ ቅሽሽ የማይለው የሃይማኖት ሊቀ ሊቃውንት ያለን እኮ እኮ እኛ ብቻ እኮ ነን – (የመንጌ የንዴት አነጋገር እንዴት ትዝ አለኝ በል)፡፡ ይሄን የምልህ እንግዲክ – ሚዲያውን ያጥለቀለቀውን አስማተኛ አጥማቂ፣ ንግሥተ ነገሥታት የማርያም እህት ነኝ ባይ፣ ብሔራዊ ባንክ የማይጠይቀው የተከታዮቹን የባንክ አካውንት በቸርቹ ውስጥ በገንዘብ እንዳንበሸበሸ በመናገር ድህነትን “ወጋሁት” ባይ ሀሰተኛ ጴንጤ፣ አንድ ሚሊዮን ድሆችን በየቀኑ ሁለቴ እንመግባለን ባይ ውሸታም ከንቲባ ….ወደ ጎን ትተን ነው፡፡ ኡፍፍፍ….. ቢበቃኝስ፡፡ ምነው ወሎ!