January 20, 2025
43 mins read

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

                                                      ጥር 12 2017(January 20, 2025)

ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ አካባቢ የተፈጠረው የሀብት ክምችትና፣ በዚህም የተነሳ በአሜሪካን የመንግስት መኪና ላይ ያሳደረውና የሚያሳድረው  ፖለቲካዊ ተፅዕኖ በቀላሉ ሊታይ እንደማይችል ነው። በአሜሪካን ምድር በጣም ጥቂት የሆነ ከመጠን በላይ ሀብትን የሚቆጣጠር የኦሊጋርኪ መደብ ሲፈጠር፣ በዚያው መጠንም በሀብታምና በደሃ መሀከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መጥቷል። ይህ ዐይነቱ የኦሊጋርኪ መደብም በጣም ብዙ የሆነ ሀብትን ከመቆጣጠር አልፎ ስልጣንንም በተዘዋዋሪ እየተቆጣጠረ ነው። ስለሆነም የአሜሪካንን ዲሞክራሲ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ጥሎታል ይሉናል። ይህንን ጉዳይ ፕሬዚደንት ትሩማን በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተናግረውታል። በጊዜው ፕሬዚደንት ትሩማን ያሉት በተለይም የሚሊተሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ ( Military Industrial Complex) ራሱን እያገለለና እየጠነከረ በመውጣት ጠቅላላውን የመንግስት መኪና ሊቆጣጣር የሚችልበት ሁኔታ እንደፈጠረና፣ ይህም ሁኔታ የአሜሪካንን ሊበራል ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል። ስለሆነም የሊበራል ዲሞክራሲያችን አደጋ ላይ ሲወድቅ ዝም ብለን ማየት የለብንም ብለዋል። በሌላ ወገን ደግሞ ራሳቸው ፕሬዚደንት ትሩማን የሚሊተሪ ኢንደስትሪው ውስብስብ እንዲያብጥ ክፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ ናቸው። በአሁኑ ዘመን ደግሞ ይህ የሚሊተሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ  ከትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር በመመሰጣጠር ጥልቅ መንግስት(Deep State) እንደፈጠረና፣ በፎርማል ደረጃም ስልጣኑን በጨበጡት ፓርቲዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እደሚያደርግ ይታወቃል። በተለይም ይህ የሚሊታሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ የአሜሪካንን የውጭ ፖሊሲ ደንጋጊ በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳያቋርጥ ጦርነት እንዲካሄድ ከፍተኛ ግፊት እንደሚያደርግ ግልጽ ነው። ጦርነትም ሲካሄድና በብዙ መቶ ሺህ ህዝብ ሲገደል ብቻ ነው የጦር መሳሪያ ኢንዱስትሪው ከመንግስት በተከታታይ ግዢን የሚያገኘውና ትርፍም በከፍተኛ ደረጃ ሊያካብት የሚችለው። ይህም ማለት አሜሪካ በኦሊጋርኪው መደብ ቁጥጥር ስር የወደቀውና የአሜሪካን የሊበራል ዲሞክራሲም ከፍተኛ አደጋ የተጋፈጠበት ዛሬ ሳይሆን 50 60 ዓመት በፊት እንደሆነ ይታወቃል። ይሁንና ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ይህንን ግልጽና የሚታወቅ ጉዳይ ለመናገር አልፈለጉም። ለሚሊተሪ ኢንዱስትሪው ውስብስብና ለሃይቴክ ኩባንያዎች ማበጥና ከአገራቸው አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃም ለዲሞክራሲና ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገትና ለሰላም ጠንቅ መሆን ራሳቸው የዲሞክራቲክና የሪፓብሊካን ፓርቲዎች አመቺ ሁኔታዎችን እንደፈጠሩ ይታወቃል። ሁለቱም ፓርቲዎች በየአራት ዓመቱ ምርጫ ሲካሄድ ለማስታወቂያና ለልዩ ልዩ የምርጫ ውድድር ወጪ የሚሆን ከፍተኛ የገንዘብ ዕርዳታ የሚያገኙት ከትላልቅ የጦር መሳሪያ አምራቾችና ከሃይ ቴክ ኩባንያዎች ነው። አንደኛው ፓርቲም በውድድር አሸንፎ ስልጣንን ሲይዝ በምንም ዐይነት የጦር መሳሪያ አምራች ኢንዱስትሪውንና የሃይቴክ ኩባንያዎችን ጥቅም የሚነካ፣ ወይም ትርፋቸውን የሚቀንስ ፖሊሲ በፍጹም ተግባራዊ አያደርግም።

ይሁንና ፕሬዚደንቱ በዚህ የማስጠንቀቂያ ንግግራቸው አጉልተው ያሳዩት ግማሽ ዕውነትን እንጂ፣ በተለይም የሚሊተሪ ኢንዱስትሪውን ማበጥ፣ የስለላ ድርጅቱን( የሲአይ ኤን) ሚናና በዓለም አቀፍ ደረጃም ጦርነትን ቀስቃሽና በተለይም በአፍሪካ፣ በማዕከለኛውና በደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ በመንግስት ግልበጣ ላይ በመሳተፍ በየአገሮች ውስጥ አለመረጋጋት እንዲኖርና ተከታታይነት ያለው ስራም እንዳይሰራ የሚሸርበውን ሴራ አልተናገሩም። ሲአይኤይና ሌሎችም ከሲአይኤ በስተቀር ወደ አስራስምንት የሚጠጉ ሌሎች የስለላ ድርጅቶች በየአገሮች ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሸርቡትን ሴራ ይናገራሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ምክንያቱም ለፕሬዚደንትነት የሚወዳደሩ ሰዎችና ፓርቲዎችም ወደ ውጭ የአሜሪካንን የበላይነት ሊያዳክም የሚችል ስራ ስለማይሰሩ ነው። መንፈሳቸውም በኃያልነት ስሜት የታነፀ ስለሆነ ሌሎች አገሮችን ማዳከም፣ በዲሞክራሲ አስተሳሰብ እንዳያብቡና ተቋማትን በመገንባት ህዝባቸውን ማሰባሰብ እንዳይችሉ የውጭ ፖሊሲያቸው ዋና መመሪያ ስለሆነ ከዲሞክራቲክ ወይም ከሪፓብሊካን ፓርቲው በአሸናፊነት የሚወጣው ፕሬዚደንትና የሚያውቅረው አገዛዝ ከዚህ ዐይነቱ በመሰረቱ እርኩስ የሆነ አስተሳሰብና የውጭ መመሪያ ፖሊሲ ብለው ከሚጠሩት ፈቀቅ ሊል አይችልም። በሌላ አነጋገር፣ ይህ አስተሳሰብ የማንኛውም ፕሬዚደንትና የመንግስቱ የውጭ ፖሊሲ ዶክትሪን ነው።

የአሜሪካን የበላይነት የሚገለፀው በዚህ ዐይነቱ የሚሊተሪ የኢንዱስትሪ ውስብስብና በሃይ ቴክ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም በትላልቅ ባንኮችና የሀብታሞችን ገንዘብ በሚያስተዳድሩ እንደ ብላክ ሮክ በመሳሰሉት ነው። ትላልቅ ባንኮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ቪዛና ክሬዲት ካርድን በመቆጣጠርና ዓለም አቀፋዊም በማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ በቀረጥ አማካይነት ወደ አሜሪካን ባንኮች እንዲፈስ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ ዶላርን ተገን በማድረግና አገሮችን የዕዳ ወጥመድ ውስጥ በማስገባት የየአገሮችን ኢኮኖሚ በመቆጣጠር የወለድ ወለደ ከፋይ ለማድረግ በቅተዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ዶላርን በማምለክና ብድር በመበደር፣ በሌላው ወገን ደግሞ በአገራቸው የባንኪንግ ስርዓትና በትናንሽና በማዕከለኛ ኢንዱትሪዎች መሀከል በብድር አማካይነት የጠነከረ ግኑኘት እንዳይፈጠር በማድረግ የየአገራቸው ገንዝበ ማግኘት የሚገባውን ጥንካሬ እንዳያገኝ ለመደረግ በቅቷል። በተደጋጋሚ ለማሳየት እንደሞከርኩት አንድ አገር በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለና ርስ በርሱ የተሳሰረ የውስጥ ገበያ ካላት ሰፊው ህዝብ የመግዛት ኃይሉ ከፍ ይላል። ይህ ሁኔታ ደግሞ የገንዘብ መሽከርከርን ያፋጥነዋል። በዚህም አማካይነት በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና የተሳሰረ የአገር ውስጥ ገበያ ለአንድ አገር ገንዘብ መጠንከር ወሳኝ ነው። ይህንን መሰረታዊ የብሄራዊ ኢኮኖሚና የገበያ ኢኮኖሚ ግንባታ አካሄድ ያልገባቸው፣ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገዛዞች በዓለም አቀፍ የፊናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በመካተትና ጥገኛ በመሆን፤ እንዲሁም ከዓለም የገንዘብ ድርጅት((IMF) ትዕዛዝ በመቀበል በተጨባጭና በተግባር ሲታይ ሰፋ ያለ፣ ለሰፊው ስራ ፈላጊ ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት የሚችል በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ለማድረግ በቅተዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝባችን ከድህነትና ከጥገኝነት እንዳይወጣና እንደሰው እንዳይኖርና በራሱም ላይ ዕምነት እንዳይኖረው ለማድረግ በቅተዋል።

የትላልቅ ሃይ ቲከ ኩባንያዎችንና የሀብታሞችን ገንዘብ፣ ለምሳሌ የአማዞን ባለቤት የሆነውን የቤዞንን፣ ክላውድ ካፒታል በመባል የሚታወቀውን ሀብት የሚያካብት፣ የቢል ጌትንና የኤለን መስክ የመሳሰሉትን ሀብት የሚያስተዳድረውን የብላክ ሮክን ሚና ስንመለከት ደግሞ በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ የጥሬ-ሀብት ማውጫዎችን በመቆጣጠርና የእርሻ መሬትም በመግዛት ልዩ ልዩ ሰብሎችን በማሳረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥሬ-ሀብትንና ስብልን የሚቆጣጠርና የሚሸጥም ነው። በተጨማሪም በአክሲዮን ገበያ ላይ በመሳተፍ ብዙ ትርፍ የሚያገኝ ነው። ከዚህ አልፎ በሬል ስቴት ውስጥ በመሳተፍና፣ ትላልቅ የመኖሪያ አፓርተሜንቶችን በመግዛት በተለይም በራሳቸው የኢንዱስትሪ አገሮች ውስጥም ለመኖሪያ ቤት መወደድ አሉታዊ አስተዋፅዖ የሚያደርግ ነው። ከዚህም አልፎ ትላልቅ የገበያ አዳራሾችን በመግዛትና ኪራዩን በማስወደድ ባህላዊ የሆኑ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ እየሄደ የሚገዛባቸውን ሱፐር ማርኬቶች እንዲዘጉ በማድረግ ባህላዊ ቀውስ እንዲፈጠር በማድረግ ላይ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የአሜሪካን የበላይነት የሚገለፀው በተለያዩ መሳሪያዎችና ዘዴዎች ሲሆን፣ ወደው ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ ዲሞክራሲያዊ ሰርዓት እንዳያብብ፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ሙሉ ነፃነት እንዳይሰማው፣ ወይም ተሸማቆ እንዲኖር፣ በየአገሮች ውስጥ ከአገዛዞች ጋር በመቆላለፍና ለዲሞክራሲ ዕድገትና ለተቋማት ግንባታ ዕንቅፋት በመሆን መረጋጋት እንዳይፈጠር በማድረግ፣ በዚህ መልክ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የጭቆናና የብዝበዛ ሰንሰለትን በመዘርጋት ጥንታዊ አገሮችም እየፈራረሱና ህዝቦችም እንደማህበረሰብ እንዳይኖሩ እያደረገ ነው። ይህም በራሱ የአሜሪካን መንግስትና የፕሬዚደንቶች የውጭ ፖሊሲ ዶክትሪን ነው።

የአሜሪካን የጦርነት ፖለቲካ ስንመለከትም ከዚህ ዐይነቱ የአለመረጋጋትና የፀረ-ሰላምና የፀረ-ዕድገት ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። አሜሪካን የኃያል መንግስት(Super Power) ሚናን መጫወት ከጀመረ ወዲህ እራሱ ሳይወረር፣ ወይም ሌላ አገር ጦርነት ሳይከፍትበትና ድንበሩን ሳይጥስ ጥቅሜን አስጠብቃለሁ በማለት ስንትና ስንት ሺህ ኪሎ ሜትር ዘልቆ በመሄድ በሌሎች አገሮች ላይ ግልጽና ስውር ጦርነቶች አካሂዷል፤ እያካሄደም ነው። የመጀመሪይው ሂሮሺማና ናጋሳኪ ላይ የወረወረው ቦምብና በአንድ ጊዜ ለብዙ ሺሆች መሞት ምክንያት የሆነው ነው። ሁለተኛው የኮሙኒዝምን መስፋፋት መግታት አለብኝ በማለት በቬትናም ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነትና ለብዙ መቶ ሺሆች ህዝብ በአሰቃቂ ሁኔታ መሞት ምክንያት የሆነው ጦርነት ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥም በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ የአሜሪካን ወታደሮች ህይወታቸውን አጥተዋል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩም ቆስለዋል፤ አካለ ስንኩላንም ለመሆን በቅተዋል። ከላይ በአውሮፕላን በሚረጨው ኤጀንት ኦራንዥ በመባል በሚታወቀው መርዝ የተነሳ የእርሻ ሜዳዎች ከመመረዛቸው ባሻገር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቬትናማውያን በመመረዝ ለከባድ ጉዳትና የኋላ ኋላም ላይ ለሞት ተዳርገዋል። የእርሻ ማሳዎችም ከመመረዛቸው የተነሳ ማረስ አይቻልም ነበር። መርዙ እስካሁን ድረስ ስላልጠፋ በዚያ አካባቢ የሚወለዱ ህፃናት አብዛኛዎቹ ጆሮ ወይም አፍንጫ አልባ በመሆን፣ ወይም የተጣመመ በመሆን የሚወለዱ ናቸው። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ህፃናትም ከአካል ጉድለትና ጉዳት ጋር ስለሚወለዱ ህይወታቸው እስካለፈ ድረስ እየተሰቃዩ ይኖራሉ። በልጅነታቸውና በወጣትነታቸው ዘመን እንደልጅ ሳይጫውጡና ሳይዘሉ ተሰቃይተው ይሞታሉ። የሊበራል ዲሞክራሲ ሰፈነበት የሚባለውና በየአራት ዓመቱም ምርጫም የሚካሂድበት አገርና፣ ለሌኦች አገሮችም ምሳሌ ነኝ የሚለው ይህንን ዕይነቱን ወንጀል የፈፀመና የሚፈፅምም ነው።

ሌላው አሜሪካ በስውር የሚያካሂደው በከፋፍለህ ግዛ ላይ የተመሰረተ የውክልና ጦርነት ነው። በስድሳዎቹ መጨረሻና በሰባዎች መጀመሪያ ላይ በአንጎላና በሞዛቢክ ውስጥ በሚካሄደው የርስ በርስ ጦርነት ቀኝ ኃይሎችን በመደገፍና መሳሪያ በማስታጠቅ ግራ ነክ ወይም ሶሻሊስት አገዛዞች የሚላቸውን ለመጣል ሲል ከፍተኛ የሆነ የሰው ዕልቂት እንዲካሄድ አድርጓል። ከዚህም በላይ ፓትሪስ ሉቡምባ እንዲገደል በማድረግ የነፃነቱና የዲሞክራሲ ትግልና መንገዱ እንዲጨልም አድርጓል። በዚያው መጠንም እነ ሞቡቱን በመደገፍና የኮንጎን ሀብት በመበዝበዝ፣ ሞቡቱም ስልጣኑን ከለቀቀ በኋላ እስከዛሬ ድረስ የኮንጎ ህዝብ እረፍት እንዳያገኝ ለመደረግ በቅቷል። አሁንም ቢሆን ትላልቅ የአሜሪካ፣ የካናዳና የአውሮፓ የጥሬ-ሀብት ተቀራማች ኩባንያዎች የውክልና ጦርነት እንዲካሄድ በመገፋፋት የኮንጎንን ህዝብ ርስ በርሱ ያጫርሱታል።

የኋላ ኋላ ላይ ከሰማኒያዎቹ ዐመታት ጀምሮ ከዚያ በፊት ያልታየ የአክራሪ እስላም እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ በተለይም ሶቭየት ህብረትን ከአፍጋኒስታን ማስወጣት አለብኝ በማለት የእስልምና ሃይማኖት መሪዎችን ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብና በማስታጠቅ ኋላ ላይ በቀጥታ ለመውረር የሚያመቸውን ሁኔታ ፈጥሯል። በመጀመሪያ አነሳሱ የሶቭየት ህብረትን ጣልቃ ገብነት ለማስወገድና በራሱ ቁጥጥር ስር የሆነ አገዛዝ ለመፍጠር ነበር። ቀጥሎ ደግሞ እነቢንላዲን ከአፍጋኒስታን ተራራ በመነሳት በአውሮፕላን በመብረር ትላልቅ ታዎሮችን አፍርሰዋል በማለትና ይህንን ሽፋን በማድረግ ከግብረአበሮቹ ጋር በመሆን 20 ዓመት የፈጀ ጦርነት ካካሄደና አፍጋኒስታንን ድምጥማጧን ካጠፋ በኋላ ወደ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚገመት መሳሪያ ለታሊባን፣ ወይም ስልጣንን ለመቆጣጠር ለቻሉት የእስልምና አክራሪ ኃይሎች ጥሎ ወጥቷል። ታሊባኖችም ስልጣንን ሙሉ በሙሉ ከተቀዳጁ በኋላ በተለይም ሴቶች ሙሉ በሙሉ ነፃነታቸውን እንዲያጡና፣ ወጣት ሴቶች ትምህርትቤት ሊሄዱና ሊማሩ የማይችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ተችሏል። ከዚህም በላይ ሴቶች የራሳቸውን ንግድ ማካሄድ አይችሉም፤ ለምሳሌ የፀጉር ስራ ቤትና የቁንጅና ሳሎኖችን መክፈት አይፈቀድላቸውም።

ወደ ኢራክና ሊቢያም ስንመጣ አሜሪካን ሰበብ ፈልጎ ነው  በእነዚህ አገሮች ላይ ወረራ ያካሄደው። እንደተባለው የሊበራል ዲሞክራሲንና የነፃ ገበያን ለማስፋፋት አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ በኢራንና በኢራክ መሀከል ጦርነት እንዲቀሰቀስ ካደረገና ሳዳም ሁሴንን እስከአፍንጫው ድረስ ካስታጠቀ በኋላ ሳዳም ሁሴን ከስምንት ዐመት ጦርነት በኋላ ተሸንፎ ሲወጣ በጦርነቱ ምክንያት የተነሳ የገንዘብ ካዚናው ተሟጦ ነበር። በወቅቱ የኩዌት መንግስት የዘይት ዋጋ ጭማሪ ያደረጋል። ሳዳምም ይህንን ምክንያት በማድረግና በአሜሪካንም በመደገፍ ኩዌትን ይወራል። አሜሪካንም ይህንን ምክንያት ወይም ሽፋን በማድረግና በነገሩ እንደሌለበት በማስመሰል በሳዳም ሁሴን ላይ ጦርነት ይከፍትበታል። የሁለተኛው ጦርነት መነሻና ሳቢያ የሆነው ደግሞ ሳዳም ሁሴን የአቶም ቦምብ ለመስሪያ የሚያገለግል ዩራኒዬም ለመቀመም ችሏል በሚል የውሸት ቅስቀሳ በማካሄድ ነበር ጦርነቱን የከፈተው። በዚህም ጦርነት የተነሳ ኢራክ እንዳለ ሲወድም፣ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሳዳም ሁሴን ሊገደል ችሏል። የሶስት ሺህ ዓመትም የታሪክ ቅርሶችና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ መጽሀፎችና እንዳለ ወድመዋል። አሜሪካ የሚባል አገር ከመፈጠሩ በፊት በስምንተኛው ዓ.ም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ባግዳድ የሳይንስና የፍልስፍና ምርምር መዲና ነበረች። አልጄብራ የሚባለው የሂሳብ አንደኛው ክፍልም በአንድ ኢራካዊ ፈላሳፋ የተፈጠረ ነው። በጊዜው ባግዳድ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ይኖር ነበር። ይህን ዐይነቱን የታሪክ ቅርስና ለሰው ልጅም ያደረገውን አስተዋፅዖ ለመረዳት ያልቻለው ፕሬዚደንት ቡሽና በጠቅላላው የአሜሪካ የሚሊታሪና የፖለቲካ ኤሊት ኢራክን እንዳለ አወደማት።  የሳዳም አገዛዝም ከፈራረስ በኋላ የኢራክ ህዝብ እንደማህበረሰብ ሊኖር በፍጹም አልቻለም። በየጊዜው ስልጣንን የሚቀዳጁት አገዛዞች ቀደም ብሎ ሳዳም ሁሴን ለህዝቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ለመስጠት ባለመቻላቸው ብዙ ህዝብ በኑሮው በስቃይ ላይ ይገኛል።

የሊቢያም ጉዳይ እንደዚሁ ነው። በተለይም አሜሪካና ፈረንሳይ ጋዳፊን ከስልጣን ላይ ለማስወገድ የፈለጉበት ዋናው ምክንያት ቀደም ብሎ ፕሬዚደንት ጋዳፊ አፍሪካ የኢንዱስትሪ አብዮት ለማካሄድ ከፈለገች የግዴታ የራሷ በወርቅ የተደገፈ ገንዘብ፣ ጎልድ ዲናር በመባል የሚታወቅ መታተምና ለኢንዱስትሪ ተከላ መዋል አለብት ብለው የአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ላይ ስለተናገሩ በዚህ የተቆጩት የአሜሪካንና የፈረንሳይ አገዛዞች ፕሬዚደንት ጋዳፊን ለመጣል ቆርጠው ይነሳሉ። ሰበብም በመፈለግና ወጣቶችን በማነሳሳት ጋዳፊን ለመጣል አመቺ ሁኔታን ያገኛሉ። ጋዳፊም እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ይገደላሉ።ጋዳፊም ከስልጣን ላይ ከተባረሩና መንግስታቸውም ከፈራረሰ በኋላ የሊቢያ ህዝብና ወጣት በጋዳፊ ዘመን ያገኝ የነበረውን እንክብካቤና የኑሮ መሻሻል ለማግኘት በፍጹም አልቻለም። በአሁኑ ወቅት በሊቢያ ውስጥ አንድ ወጥ አገዛዝ በፍጹም የለም። የሊቢያ ዘይትም በፈረንሳይና በአሜሪካን ኩባንያዎች እየተዘረፈ ነው። ባጭሩ ይህ የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች ድርጊትንሃ፣ ሰበብ አስባብ እየፈለጉ አገሮችን ማውደምና የኢንላይተንሜንትን አስተሳሰብ የሚፃረር ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በሁሉም አገሮች ውስጥ የሊበራል ዲሞክራሲንና የነፃ ገበያን እናስፋፋለን ብለው ሲነሱ በመሰረቱ የራሳቸውን ቅምጥ አገዛዞች ስልጣን ላይ በማውጣት የየአገሮችን ዕድል ለመወሰን ብቻ ነው። የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብም ከውጭ የሚመጣ ሳይሆን በየአገሮች ውስጥ በክንውናዊ መንገድ ኦርጋኒካሊ ማደግ ያለበት አስተሳሰብ ነው። የተወሰነው የህብረተስብ ክፍል መንፈስ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ ቀስ በቀስ ልዩ ልዩ ተቋማትንና ይህንን የሚያግዝ የትምህርት ስርዓት ሲዘረጋና፣ ሰፊው ህዝብም የመማርና የመጻፍ ዕድል ሲያገኝ ቀስ በቀስ የሊበራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብን ማዳበር ይቻላል። እንደሚመስለኝ በየጊዜው አሜሪካን ስልጣን ላይ የሚወጡ ፕሬዚደንቶችና የፖለቲካና የሚሊተሪ ኢሊቱ የሊበራል ዲሞክራሲ በክንውናዊ መንገድ ብዙ የውጣ ውረድ ትግል ከተካሄደና፣ የምርት ኃይሎችም ካደጉ በኋላ ቀስ በቀስ ዕውን ለመሆን የቻለ አስተሳሰብና ስረዓ እንደሆነ በፍጹም የገባቸው አይመስለኝም። በሌላ አነጋገር የማቴሬያልና የመንፈስ ሁኔታዎች ባላደጉበት፣ ከተማዎችና መንደሮች በስርዓት ባልተገነቡበትና፣ ልዩ ልዩ መንግስታዊ ተቋማትም ባልተስፋፉበት አገር ውስጥ የሊበራል ዲሞክራሲን ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይቻል ማወቅ ነበረባቸው። በሌላ ወገን የአሜሪካንም ሆነ የአውሮፓ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የስለላ ኤሊት ዋናው ዓላማ በሊበራሊ ዲሞክራሲ ስም አሳቦ አገሮች መበወዝና የጥሬ-ሀብታቸውን መበዝበዝ ነው። በእየአገሮች ውስጥ ያለ ህዝብ አቅጣጫው እንዲጠፋበት ለማድረግ ብቻ ነው።

ወደ ሲሪያም ስንመጣ ተመሳሳይ ሁኔታን እናገኛለን። በ2011 ዓ.ም የአረብ የጥቢው አብዮት በመባል የሚታወቀውን አሳበው አሜሪካኖች ወጣቶችን ይቀስቅሳሉ፤ በአሳድ አገዛዝም ላይ እንዲያምጹ ያደርጋሉ። በጊዜው የአሳድ አገዛዝ ችግሩን በብልሃት ፖለቲካዊ በሆነ መንግድ መፍታት ሲገባው መካረር ውስጥ ይገባል። በመሆኑም አገዛዙን የሚቀናቀኑና በአሜሪካንና በቱርክ የሚደገፉ ኃይሎች በመታጠቅ ከአሳድ አገዛዝ ጋር የጦርነት ፍልሚያ ውስጥ ይገባሉ። በመጀመሪያው ወቅት በተደረገው ጦርነት በራሺያ ድጋፍ በአሜሪካንና በቱርክ የሚደገፉ ኃይሎችን የአሳድ አገዛዝ መክቶ መመለስ ቻለ። ይሁንና አሜሪካን የዘይት ማውጫ ሜዳን በመቆጣጠር የሲሪያን የገቢ ምንጭ በማድረቁ የተነሳ ኢኮኖሚው በጣም ይዳከማል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የአሳድ አገዛዝ ኢኮኖሚው እንደገና እንዲያንሰራራ ሊያደርግ የሚችልበት የውጭ ምንዛሪ አልነበረውም። ይህም ጉዳይ የሰፊውን ህዝብ ሞራል ሊያዳክመው ቻለ። ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው ያለውን ውጥረት በመጠቀም፣ በተለይም ኢራን በተለያዩ አቅጣጫዎች ስለተያዘች ለአሳድ አገዛዝ የምትሰጠውን የሚሊተሪ ድጋፍ ልታቀርብ አልቻለችም። ራሺያም እንደዚሁ በዩክሬይን ጦርነት ሰለተወጠረ ኃይሉን ለመከፋፈል አልፈለገም፤ በዚህም ምክንያት የተነሳ አስፈላጊውን ዕርዳታ ለሲሪያ መንግስት ማቅረብ አልቻለም። እነዚህ ነገሮች በመደማመርና አንዳንድ የአሳድ ጄኔራሎች ምናልባትም በሲአይኤ ስለተገዙ ከውጭ እየገፋ የመጣውንና በአሜሪካንና በቱርክ የሚደገፈውን ኃይል ሰተት ብሎ እንዲገባ መንገዱን አመቻችተው ሰጡ። አሳድም ራሺያኖች ባዘጋጁለት አውሮፕላን ከእነቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ሞስኮ ሊገባ ቻለ። ስልጣን ላይ የወጣው አዲስ ኃይልም የእስላም አክራሪ የሆነና አሸባሪም ተብሎ የተፈረጀበት ነው። ይህም ማለት የሊበራል ዲሞክራሲን ሊያራምድ የሚችል አይደለም፤ መንፈሱም በዚህ አስተሳሰብ የታነፀ አይደለም፤ በተለይም ደግሞ ለሴቶች ነፃነትን ሊሰጥ የሚችል ኃይል አይደለም።

ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሀተታ ስንነሳ ጆ ባይደን በአሜሪካን ምድር ለዲሞክራሲ ጠንቅ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ ተፈጥሯል ብለው ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ፣ ይህ ዐይነቱ የኦሊጋርኪ መደብ ለአሜሪካን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ዲሞክራሲያዊና ህዝብን የሚያቅፍ ስርዓት እንዳይመሰረት የሚሸርበውን ከፍተኛ ሴራ በፍጹም አላወሱም። ይህ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውና ከሳቸው በፊትም የነበሩት ሁለቱን ፓርቲዎች ወክለው ፕሬዚደንት የመሆን ዕድል የሚያጋጥማቸው ሁሉ ዋናው አላማቸው ከአሜሪካ በስተቀር ሌሎች አገሮች በሁለት እግራቸው ቆመው መሄድ የለባቸውም የሚል መመሪያ ወይም ዶክትሪን አላቸው። ማንኛውም አገር ካለአሜሪካ ፈቃድ በስተቀር በፈለገውና ለህዝቡ ይስማማል በሚለው መንገድ አገሩን በፀና መሰረት ላይ መገንባት የለበትም። ይህንን ዐይነቱን የአሜሪካንን የውጭ ፖሊሲ ዶክትሪን ለማስፈፀም ደግሞ በየአገሮች ውስጥ ስልጣን ላይ የተቀመጡ ኃይሎች አሉ። የሚሊተሪ፣ የፀጥታና የኢኮኖሚ ኤሊቱም የአሜሪካኖችን ትዕዛዝ ለማስፈፀምና ጥቅም ለማስጠበቅ ተብሎ መንፈሱ ስለታነፀ በቀጥታ የሚሰራው ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ነው ማለት ይቻላል። በአብዛዎቹ አገሮችም ውስጥ፣ የምስራቅ አውሮፓንም ጨምሮ የፖለቲካ ኤሊቱ በከፍፋለህ ግዛው ፖሊሲ የተነሳ ስለተክፋፈለ በማያውቀው ነገር ውስጥ በመግባት ወደ ውስጥ የራሱን አገር እንዳይገነባ ታግዷል። በተለይም የተወሰነው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት የግዴታ የአሜሪካንና የተቀረው የምዕራብ አውሮፓ ካፒታሊስት አገሮች አሽከር ካልሆንኩኝ በማለት የአገሩና የህዝቡ አለኝታ ከመሆን ይልቅ ተላላኪ በመሆን በጦርነት ውስጥ በመሳተፍ የራሱን አገርም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ጥሏል። የዩክሬንንን ሁኔታ መመልከት በቂ ነው። በዚህ ጦርነት ውስጥ ከአሜሪካን ጋር በመሰለፍና መሳሪያ በማቀበል ሰላሳ ሰባት አገሮች ራሺያን ይዋጋሉ። ጦርነቱም የአሜሪካኖችና የተቀሩት የኔቶ አባል አገሮች ጦርነት ነው። ሲሌኒስኪና ግብረአበሮቹ የአሜሪካንን የፖለቲካና የሚሊተር፣ የፀጥታና የኢኮኖሚ ኤሊት ፍላጎት ተግባራዊ ማድረግ አለብኝ በማለት ከራሽያ ጋር እልክ ውስጥ በመግባት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን የዩክሬይን ወታደር እንዲገደል አድርጓል።  በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩም ቆስለዋል። ለወታደርነት አንመለመልም ብለው ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የሸሹ ወጣቶች እስከ 600 ሺህ ይደርሳሉ። ከአስር ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚሆኑ ዩክራኒያኖች አገራቸውን ጥለው ሄደዋል። ወደ አገራቸው የመመለስ ዕድላቸውም ወደ ዜሮ የሚጠጋ ነው። በጣም የሚያማምሩ ከተማዎች ወድመዋል። ብዙ ኢንፍራስትራክቸርና የኃይል ማመንጫዎች ወድመዋል። ራሺያም ወደ 25% የሚሆነውን የዩክሬይንን ግዛት ትቆጣጠራለች።  ይሁንና ይህ ሁሉ ተፈጽሞ አሁንም ቢሆን በባይደንና በብሊንክለን የሚመራው አገዛዝ ራሺያን ማዳከምና ማሸነፍ አለብን በማለት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር መሳሪያ ያፈሳል። በፕሬዚደንተና በውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ በብሊንክነ ዕምነትና አነጋገር የዩክሬን አገዛዝ አንድ ሰው እስኪቀር ድረስ ጦርነቱን መቀጠል አለበት። ይህንን በአፍጢሙ የተደፋ  ሎጂክ ተገንዘቡ። በኃይልነት መንፈስ የተወጠረ ጭንቅላት የሚያስበውንና የሚያደርገውን በፍጹም አያውቅም።

በአጭሩ ለማለት የምፈልገውና  ስልጣናቸውን ለፕሬዚደንት ትረምፕ የሚያስረክቡት ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ያልተናገሩት ሃቅ አዲሱ ኦሊጋሪክ መደብ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው የአሜሪካ አገዛዝና አወቃቀሩ ለአሜሪካን ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ህዝብ ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማበብ ከፍተኛ ጠንቅ የሆነ ኃይል ነው። በራሱ የአሜሪካን ውስጥ ያለውን ሁኔታም ስንመለከት በተለይም በጥቁሮች ላይ የሚፈፀመው ግፍ በጣም ያሳዝናል። ምንም ማስረጃ ሳይገኝባቸው በወጣትነት ጊዜያቸው እስር ቤት ውስጥ የሚማቅቁና፣ ሰላሳና አርባ ዓመት ከታሰሩ በኋላ ምንም ማስረጃ ስላልተገኘብህ ተለቃሃል በመባል የሚፈቱ አሉ። ከዚህም በላይ በፖሊሶች የሚገደሉና የሚደበደቡ ወጣት አሜሪካኖች ቁጥራችው ትንሽ ነው የሚባል አይደለም። ባጭሩ የአሜሪካን የሊበራል ዲሞክራሲና በየአራት ዐመቱ የሚደረገው የምርጫ ውድድር ተሳትፎ ለሰፊው የአሜሪካን ህዝብ ዕውነተኛ ዲሞክራሲን ለማጎናፀፍ የቻለ አይደለም። ይህንና ብዙ ጥያቄዎችን ሳያነሱ ነው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በአሜሪካን ምድር የሊበራል ዲሞክራሲን የሚቀናቀን አዲስ የኦሊጋርኪ ኃይል ተፈጥሯል ብለው የሚነግሩን። መልካም ግንዛቤ!!

[email protected]

www.fekadubekele.com

https://www.youtube.com/watch?v=VQPsKSeLn7k

https://www.bbc.com/news/articles/c1weqzl3ydro

https://www.youtube.com/watch?v=5nTx_Pi1x9Q

https://www.youtube.com/watch?v=Rg6_tdzH6ho

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop