December 1, 2024
28 mins read

ኢትዮጵያ አንድ የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ እንዳይኖራት የሚያደርገው ሕግ እንዳይፀድቅ እንጠይቃለን – በኢትዮጵያ የባለሙያዎች ድርጅቶች

መጋቢት 24፣ 2015 ዓ.ም.

የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፤

Ethiopia News Language

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ድርጅቶች ይህንን የሕዝብ ማመልከቻ ያፀደቁት ሲሆን እነሱም፣ ‹‹Ethiopiawinnet: Council for the Defense of Citizen Right, People to People (P2P) Inc.፣ Global Ethiopian Scholars Initiative (GESI)፣ Society of Ethiopians Established in Diaspora (SEED)፣ Save Ethiopia Forum›› ናቸው፡፡

የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆይ!

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋና ትክክለኛ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ ነድፎ በሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት የሁሉም ዜጋ እምነት ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝባችን በአንድነት አገራዊ ቋንቋውንና ትምህርትን ተጠቅሞ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቹን ለመፍታትና የአገር አንድነትን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ርብርብ ማድረግ የሚኖርበት ዘመን ነው። ለዚህም የአገር አንድነት፣ ሰላምና ዕድገት ራዕዩ የሆነ የትምህርት ፖሊሲ ያስፈልጋል። መንግሥት ግን አገርን የሚከፋፍልና ሕዝብን የሚያራርቅ፣ ሕዝብ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሲሄድ ባይተዋር የሚያደርግ፣ ተማሪዎች አንድ የጋራ አገራዊ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዳይማሩ የሚያደርግ፣ የትምህርት ፖሊሲ አውጥቶ የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. አፅድቋል። በተጨማሪም ጥቅምት 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ደግሞ ይህ ለዘመናት የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነውን፣ አሁንም ባለው ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛን ከአገራዊ መግባቢያነት እንዲወጣ ክፍተት የሚፈጥር አንቀጽ ያለበት ረቂቅ የትምህርት ሕግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት ቀርቧል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በዕውቀት ላይ ተመሥርቶና የአገርን ጥቅምና አንድነት አማክሎ መቀረፅና መተግበር ይኖርበታል። በባለሙያዎች ከቀረበው የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥና[i] ባፈነገጠ አሠራር መንግሥት እመራበታለሁ የሚለውን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች በመጣስና በዘውግ ፖለቲካ ውሳኔ አደገኛና ከፋፋይ የትምህርት ፖሊሲ አውጥቶ በመተግበር ላይ ይገኛል። በ1986 ዓ.ም. ወጥቶ በነበረው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ[ii] አማርኛ ለአገራዊ መግባቢያነት በአገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መሰጠት እንዳለበት በግልጽ የተደነገገ ነበር። አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ[iii] ግን ይህንን ድንጋጌ ሰርዞታል። ይህ ሕዝብና አገርን ጎጂ የትምህርት ፖሊሲና ተደብቆ የነበረው ረቂቅ የትምህርት አዋጅ እንዳይፀድቅ የሥነ ትምህርት ምሁራን የትምህርትና ቋንቋ ፖሊሲ ውይይት ምክረ ሐሳብን ከማሳወቅ በተጨማሪ፣ ለትምህርት ሚኒስትሩ ግልጽ ደብዳቤ[iv] በመጻፍ ብዙ ጥረት ብናደርግም ምላሽ አላገኘንም። በዕውቀት ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን በፖለቲካ ውሳኔ ይህ ፖሊሲ እንዲፀድቅ ተደርጓል። ይህንን አደገኛ ኢትዮጵያውያንን አንድ የጋራ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ የሚያሳጣ የፖሊሲ አካሄድ በፅኑ በመቃወም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያወግዘውና በሥነ ትምህርት ባለሙያዎች መሪነት አዲስ የትምህርትና የሥልጠና ፖሊሲ እንዲቀረፅና ተግባራዊ እንዲሆን ተግባራዊ ዕርምጃ እንዲወስድ አስቸኳይ ጥሪ አድርገናል። በተጨማሪም በትምህርት ፍኖተ ካርታው ምክረ ሐሳቦች መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛ፣ ለአገራዊ መግባቢያነት በአገሪቱ ትምህርት ቤቶች ሁሉ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ የሚያደርግ ፖሊሲ እንዲወጣ እንዲደረግ አጥብቀን ጥሪ አድርገናል።

የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አንድ አገራዊ የመግባቢያ ቋንቋ የሌለውና ትምህርት ላይ ትኩረት ያልሰጠ አገር ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ አይቻለውም። የዓለም ማኅበረሰብ ዕውቀት መር ወደ ሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት በፍጥነት እየገሰገሰ ባለበት በዚህ ዘመናችን፣ በጥራትና በስፋት የሠለጠነ የሰው ሀብት ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ስለሆነም የአገርን ዕድገትና አንድነት ያማከለ ትክክለኛና አዲስ የትምህርት ፖሊሲ መቅረፅና ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አሁንም በአንክሮ እንጠይቃለን።

ትምህርት ለሥልጣኔና ለአገር ግንባታ መሠረት ነው። ታዳጊ ዜጎቻችን በዕውቀት፣ በአንድነት፣ በአገር ፍቅር፣ ለሕዝብ አገልጋይነት ዝግጁ ሆነው ተገቢው ዝግጅት በተደረገበት፣ በቂ የትምህርት ግብዓትና ድጋፍ እስከተደረገ ድረስ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት የመቅሰም መሠረታዊ መብታቸው ነው። የሕዝባችን ኑሮውና ሕይወቱ እንዲሻሻል የትምህርትና ዕውቀት ሚና ትልቅ ነው። ሆኖም ግን በትምህርት ዘርፍ ውስጥ ገደብ ያልተበጀለት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የመማር ማስተማርን ሥርዓት ከማናጋት አልፎ ተማሪዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዳያገኙ፣ መምህራን በሙያ ዘርፋቸው በነፃነትና በኃላፊነት ሥራቸውን እንዳይሠሩ በማድረግ ብዙ አሠርት ዓመታትን አስቆጥሯል። በዚህ በተበላሸ የትምህርት ፖሊሲ ዜጎች ተገቢውን ዕውቀት መቅሰም ሳይችሉና ለራሳቸውም ሆነ ለአገራቸው ሊያበረክቱ ይችሉ የነበረውን ሁሉ ሳያበረክቱ ቀርተዋል። የዚህ ብልሹ አሠራር ለአገራችንና ለሕዝቧ ከፍተኛ ችግሮችን መፍጠሩን በብዙ መልኩ ለመገንዘብ ችለናል። በመሆኑም የትምህርት ፖሊሲውን በፍጥነት ማስተካከል ይህንን አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ አስመልክቶ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ እንዳይፀድቅ አስቸኳይ ዕርምጃ የሚፈልግ አገራዊ ጉዳይ መሆኑን በፅኑ ለማስገንዘብ እንወዳለን።

አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ስለአገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ጉዳይ ‹‹አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል›› በማለት በአንቀጽ 5 ቁጥር 2 ላይ ደንግጓል። በተጨማሪም የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን በተመለከተ በ1986 ዓ.ም. ያወጣው ፖሊሲ ቁጥር 3.5.4፣ አማርኛ ቋንቋ ለአገራዊ ተግባቦት በትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ትምህርት መሰጠት እንዳለበት ይደነግጋል። ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ላይ ያተኮረና በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥነ ትምህርት ባለሙያዎች የተሳተፉበት የጥናት ቡድን አጽንዖት ሰጥቶ ያቀረበው ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ[v] ለአገራዊ መግባቢያነት አማርኛ በአጠቃላይ በአገሪቱ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ፣ እንደ አንድ ትምህርት ተጠናክሮ መሰጠት እንዳለበት በፅኑ አሳስቧል። በአሁኑ ወቅት በሕገ መንግሥቱ አማርኛ ብቸኛው የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሲሆን፣ ይህንን ቋንቋ በትምህርት ቤቶች በተገቢው ጥልቀትና ጊዜ መማር ያልቻሉ ተማሪዎች ላይ በትምህርትም ሆነ በሥራ ገበታቸው ላይ አሉታዊ ሳንካ ይፈጥራል። የአንድ አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ አስፈላጊነት እየታወቀ፣ ለዚህም ብቁ የሆነው የአማርኛ ቋንቋና ኢትዮፒክ (የግዕዝ) ፊደል ያለን ማኅበረሰብ ሆነን ሳለ፣ አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንኳን ከመፅደቁም በፊት አደገኛና ሕገወጥ ፖሊሲ በሥራ ውሏል። አሁን ደግሞ አማርኛ በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዳይሰጥ ሕጋዊ ክፍተት የሚፈጥር ሕግ ለማፅደቅ የሚደረገው ሒደት እጅግ አሳሳቢና በታሪክ የሚያስጠይቅ ሆኖ አግኝተነዋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውስጣዊና ሥርዓታዊ የፖሊሲ ችግሮችና ተግዳሮቶች ላይ ወድቋል። በመሆኑም የትምህርት ሥርዓቱን ለማሻሻል በጥናትና በትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎች የመሪነት ሚና እንዲጫወቱና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበና ትክክለኛ የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ መተግበር የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የተበላሸ የትምህርት ፖሊሲ ሰለባ የሚሆኑት ተማሪዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ መላው ማኅበረሰብ፣ በተለይም መምህራንና የትምህርት ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ወላጆች፣ በተማሩት ልጆቹ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቹን ለመፍታት ተስፋ ያደረገውን ዜጋ በሙሉ ሲሆን፣ በወልም አገራችን ኢትዮጵያንም ከእርስ በርሰ መገዳደል፣ ከድህነትና ኋላቀርነት አረንቋ እንዳትወጣ የሚያደርግ ነው።

የትምህርት ፖሊሲውን በአደገኛ ፖለቲካ ጣልቃ ገብነትና የኢትዮጵያ ህልውናን ለመሸርሸር የሚታገሉ አካላት በሕዝባችን ላይ ለመጫን ድብቅ እንቅስቃሴ መኖሩ አሳስቦን የትምህርት፣ የታሪክና የፖሊሲ ሙያተኞችን ያሳተፈ ውይይትና የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝባችን እንዲያውቀው ተደርጓል (ውይይት ክፍል 1[vi] ውይይት ክፍል 2[vii])። የትምህርት ሚኒስቴርም እያቅማማም ቢሆን ደብቆት የነበረውን ረቂቅ ሰነድ[viii] ጥር 6  ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ለማድረግ ተገዷል። እንዲሁም የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ይህንን ረቂቅ ሰነድ ፖሊሲ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አፅድቆታል። ሊኖረን ይገባ የነበረውን አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ አስመልክቶ ፖሊሲውና ረቂቅ የትምህርት አዋጁ እንደሚከተለው ብሎ አልፎታል፡፡

‹‹አንድ ተጨማሪ የአገር ውስጥ ቋንቋ ከፌዴራል የሥራ ቋንቋዎች መካከል የተማሪው/የወላጅን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ በየደረጃው ባለው የትምህርት መዋቅር ተወስኖ ከሦስኛ እስከ አሥረኛ ክፍል የሚሰጥ ይሆናል።››

በፖሊሲውም ይሁን በረቂቅ አዋጁ አማርኛን አስመልክቶ ምንም የተጠቀሰ ነገር የለም። ይህ ከመስከረም 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ የዋለው የትምህርና ሥልጠና ፖሊሲ[ix] ሕገ መንግሥቱንም ሆነ የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት ምክረ ሐሳብ በመቃረን የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ለዘመናት የአገራዊ መግባቢያና የሥነ ጽሑፍ ልሳን አድርገው ያቆዩትን ኢትዮጵያውያን በጋራ ያበለፀጉትንና ያሳደጉትን የአማርኛ ቋንቋን እንደ አንድ ትምህርት ዓይነት እንዳይሰጥና ኢትዮጵያውያን የጋራ መግባቢያ እንዳይኖረን ያደርጋል። ይህም በመሆኑም አፍሪቃዊያን የሚኮሩበትን አገራዊ የጽሑፍ ቋንቋ እንደ ትምህርት ዓይነት እንዳይሰጥ ማድረግ ለሺሕ ዓመታት የነፃነት ጮራ ያልደበዘዘባት አገራችንን የመናድ፣ ዜጎቿም እርስ በርስ እንዳይግባቡና የገዛ አገራቸውን የጋራ ልሳን የማሳጣት፣ በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች መካከል የነበረውን ዋና መገናኛ ድልድይ መስበር ነው። እንዲሁም የሕዝባችንን አንድነት የሚያናጋና የአገሪቷ ህልውና መሠረት የሚሸረሽር አደገኛ ፖሊሲና ረቂቅ ሕግ ነው።

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ቀውስና አስቸጋሪ የሰላም ዕጦት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የአገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ ሥርዓት ነፀብራቅ የሆነውና አደገኛው የትምህርት ሥርዓት ነው። በይበልጥም የትምህርቱ ጥራትና ፋይዳ ተሻሽሎ፣ አገሪቱን ከገባችበት ችግርና ማጥ ለማውጣትና ለአገር መግባባት፣ ምክክርና አንድነት ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ሲጠበቅ፣ አሁንም መንግሥት ትምህርትንና ዜጎችን በቋንቋና በብሔር ይበልጥ ለመከፋፈልና ለማጋጨት በመጠቀም አደገኛ ሁኔታን እየፈጠረ ነው።

የምሁራኑ ውይይት፣ አማርኛ ከአገሪቱ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ቋንቋ በመወራረስ፣ ከልጆቿ አብራክ ወጥቶ፣ በኢትዮጵያ ፀንቶ የኖረ፣ በረዥም ጊዜ የዳበረ የኢትዮጵያ የመነጋገሪያና የጽሕፈት ቋንቋ እንደሆነ አስገንዝቧል። ስለዚህም ቋንቋው ከምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ ጥቅሙ አልፎ፣ አገራችንን በአንድነትና በነፃነት በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ቦታ እንዳለው፣ በዚህ ብሔራዊ ሚና አንፃር ሲታይ፣ በትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንዳይሰጥ የወጣውና ተግባራዊ የተደረገው ፖሊሲ የሚያመጣው ጉዳት መጠነ-ሰፊና ለመጪው ትውልድ የተወሳሰበ ችግርን የሚያወርስ ነው። የዳበረውን አገራዊ ቋንቋ ከትምህርት መምርያ መሰረዝ፣ አገርን ይጎዳል፣ ሕዝባችንን ከማቀራረብ ይልቅ ያራርቃል፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ ዜጎች በፈለጉበት በተመቻቸው አካባቢና በሙያቸው ተሠማርተውና ተንቀሳቅሰው የመሥራት መብታቸውን ይነፍጋል፣ እንዲሁም አገር ከመገንባት ይበልጥ ወደ አገር መናድና መበታተን ያመዝናል። እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን የራሳቸውን ቋንቋ በመጣል፣ በቅኝ እንደተገዙት አገሮች እንግሊዝኛን ለአገራዊ መግባቢያነት እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ አዝማሚያ ነው።

ከዚህም የተነሳ በምሁራኑ ዕይታ የአገራችንና የመላው አፍሪካ ኩራት የሆነውን የጽሑፍ ቋንቋችንን አዳብረን፣ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ቋንቋ ማድረግ ሲገባን፣ ለቀመር [ኮምፒዩተር] ቴክኖሎጂ ተመራጭ የሆነውንና የዳበረውን አማርኛን በትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ትምህርት ዓይነት ይሰጥ የሚለውን መመርያ መቀየሩ፣ ‹‹አገር በቀል ዕውቀት እናሳድጋለን፣ አገራዊ መግባባት እንፈጥራል፣›› የሚለው መንግሥትም ሆነ የትምህርት ሚኒስቴር ሕዝቡን የሚያስተባብር፣ አገርን የመገንባት፣ ወደፊት በአንድነቷ የሚያስቀጥልና አስተማማኝና ግልጽ ራዕይ እንደሌለው ያረጋግጣል። ምሁራኑ በውይይቱ በጥልቅ ከተወያዩበትና ታሪካዊና ሥነ ትምህርታዊ አንድምታዎችን በመመርመር የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲን በተመለከተ የሚከተሉት ጉዳዮች ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አስቸኳይ ትኩረትና ማስተካከያ እንዲወሰድ ጥሪያችንን በአጽንኦት እናቀርባለን።

  1. የኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናትን በመመርኮዝ አዲስ የትምህርት ፖሊሲ እንዲቀረፅና በሁሉም ትምህርት ቤቶች ሥራ ላይ እንዲውል። አገሪቱ የዘውግ ፖለቲካ በፈጠረው ችግር ተወጥራ አደጋ ላይ ወድቃ እያለ ሕዝብ ያልመከረበት፣ ከሕገ መንግሥቱና ራሱ ትምህርት ሚኒስቴር ካስጠናው ጥናት ተቃራኒ የሆነ ፖሊሲና ሕግ በድብቅ አዘጋጅቶ ማውጣትና በይፋ ሳይፀድቅ ተግባራዊ ማድረግ አገርን አደጋ ላይ ይጥላል። ስለዚህ በነበረውና በ1986 ዓ.ም. በወጣው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ጥናት መሠረት፣ በሕገ መንግሥቱ የአገሪቱ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ለአገራዊ መግባቢያነት በመላው የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ ራሱን የቻለ ትምህርት ዓይነት ያላንዳች ሕገወጥነት ለሁሉም ዜጎችና ሥፍራዎች እንዲሰጥ እንዲደረግ።
  2. የትምህርት ሥርዓቱ ከማናቸውም የፖለቲካና ሃይማኖታዊ ተፅዕኖዎች ነፃ ሆኖ እንዲዋቀርና ትምህርትን በጥራትና በስፋት በማዳረስ ላይ ማተኮር ይኖርበታል። ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 90 በቁጥር 2 ‹‹ትምህርት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት፣ ከፖለቲካ፣ አመለካከቶችና ባህላዊ ተፅዕኖዎች ነፃ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት›› ሲል፣ እንዲሁም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ሥልጣን አስመልክቶ በሚገልጸው አንቀጽ 77 ቁጥር 6 መሠረት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ይነድፋል፣ ያስፈጽማል›› ይላል። አገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ክልል ተሻጋሪ ስለሆነ፣ ፖሊሲውን የማውጣት ሥልጣኑ ለክልል የሚተው ሳይሆን፣ የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ነው። ስለዚህ የአገራዊ መግባቢያ ቋንቋ ጉዳይ፣ ከተራ የዘውግ ፖለቲካ እንዲለይና የቋንቋ ጉዳይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይበልጥ ማቀራረቢያ፣ ማገናኛ፣ ማስተባበሪያና ማስተሳሰሪያ አገር መገንቢያ እንጂ፣ የመከፋፈያና የጥላቻ መዝሪያ መሣሪያ እንዳይሆን በማስፈለጉ፣ የቋንቋና የትምህርት ፖሊሲ ጉዳዮች በፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣንና ተግባር መማከል ይኖርበታል።
  3. በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በታሪክና በሥርዓተ ትምህርት ጉዳዮች ውስጥ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ጉዳዩ ለዘርፉ ባለሙያዎች ብቻ እንዲተው፤ ለባለሙያዎቹም ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል።
  4. የትምህርት ሥርዓቱ አማርኛ ቋንቋን በማበልፀግ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የቀመር [ኮምፒዩተር]፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት መማሪያና የምርምር ቋንቋ እንዲሆን፣ ሌሎችም የአገራችን ቋንቋዎች ተደጋግፈው የሚዳብሩበትና የሚያድጉበት ሥልታዊ ዕቅድ በባለሙያ በማውጣት ተጨባጭ ሥራ እንዲሠራ።
  5. በቋንቋና በክልል መዝሙር ሰበብ የኢትዮጵያ ለጋ ሕፃናትን በዘውግ መለያየት፣ ወይም በውስጣቸው የጎሳ ጥላቻ ዘር መዝራት እጅግ ነውረኛና አገር የሚያፈርስ አደገኛ ጥንስስ መሆኑ ታውቆ እንዲቆም እንዲደረግ። ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጥላቻንና የጎሳ መለያያ ቦታ ሳይሆኑ መተሳሰብን፣ አካታችነትን፣ አብሮነትን፣ ሕግ አክባሪነትን፣ በምክንያት ማሰብና መወያየትን፣ አንድነትን፣ ኢትዮጵያዊነትን የአገር ፍቅርንና የጋራ አገራዊ ራዕይና አመለካከትን የሚያዳብሩባቸው ተቋማት እንዲሆኑ ተገቢው ሥራ እንዲሠራ እናሳስባለን።

[i]https://planipolis.iiep.unesco.org/sites/default/files/ressources/ethiopia_education_development_roadmap_2018-2030.pdf

[ii]https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy%20of%20Ethiopia.pdf

[iii] https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy-Yekatit-2015%20Final.pdf

[iv] https://shorturl.at/sSoDv

[v]https://planipolis.iiep.unesco.org/sites/default/files/ressources/ethiopia_education_development_roadmap_2018-2030.pdf

[vi] https://www.youtube.com/watch?v=zmemlQs5h_k

[vii] https://www.youtube.com/watch?v=TzR7aIxwuS0&t=14s

[viii]https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy%20Second%20draft%2003-01-2023.pdf

[ix] https://moe.gov.et/storage/Books/Education%20and%20Training%20Policy-Yekatit-2015%20Final.pdf

 

1 Comment

  1. እዚህም ቤት መከራ~ እዛም ቤት መከራ
    የፈጣሪ ያለህ ~~ከማን ጋር እናውራ?
    አማርኛው ቀርቶስ ~~ ሠው በምን ይግባባል?
    ይህን ማመልከቻስ ~~ ምክርቤት ያፀድቃል?
    ብሎ መገመቱ ~~ይቸግራልና
    ወገን ሆይ እንጃልን ~~ፈጣሪ ፈጥነህ ና
    ዘሀበሻ ቤቴ ~~ብሶት መግለጫዬ
    እንዴት ከረምሺልኝ ~~ታውኳል ጤናዬ
    ድፍን 20 ዓመታት ~~ደክሞኝ ለዖሮማራ
    ጭራሽ ፅልመት ወጥቶም ~~ዘምተን በዐማራ
    ታርቀን ሠላም ወርዷል ~~ብለን ከዔርትራ
    እንዳልወደመብን ~~ህዝባችን በጋራ
    እስከመቼ ይሆን ~~በጎጥ ተለያይቶ
    ህይወት የምትተርፈው~~እንኳን ልማት ቀርቶ?
    ህዝባችን የለት ጉርስ ~~ሆኖበት ብርቅዬ
    ለነገ የማይል ~~የዛሬን ሸቅዬ
    የአስፋልት ዳር “ነጋዴ” ን ~~ገፍተህ ወደ ገደል
    እሱ በቆመበት ~~ዘንባባን ብትተክል
    ይህ ከበለጠብን ~~ልማት የኮሪደር
    ፈጣሪ ይፍረደው ~~እንጅ ምን ልናገር?
    ይህን ያህል ካልኩኝ ~~ዛሬን በጠዋቱ
    እንደገባሁ ወጣሁ ~~እኔው አባዊርቱ

    ሠላሙን ለህሊና: ፅናትን ለኢትዯጵያ ያድልልን!
    ይሆናል ብለን ለተመኘነው :ባለመታደላችን ሁሌም ሀዘንተኛ ነኝ:(

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop