(አሁንገና ዓለማየሁ)
በብሊንከን የሚመራውን ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አማራ የስቴት ዲፓርትመንት ስታፍ ሁላ ማባረሪያው ጊዜ አሁን ነው!!!
ኢትዮጵያ የህልውና አደጋ ተደቅኖባት እለት እለት ወደ መበታተን ጠርዝ እየተገፋች ትገኛለች። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊው መራጭ በአቅራቢያው ፖለቲካ ምቾት የሚሰጡትን ተመራጮች ከመምረጥ ይልቅ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ከፍተኛ አደጋ የማይደቅነውን የፖለቲካ ፓርቲ ቢመርጥ ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ የሚበጅ ሥራ ይሠራል። የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ በአሜሪካ ኢንተረስት ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው የሚባለው ነገር ትክክል ቢሆንም ከዲሞክራቲክ ፓርቲና ከሪፐብሊካን ፓርቲ ጋር የተጣበቁ ኢንዱስትሪዎችና ፖለቲከኞች የተለያዩ ከመሆንም አልፈው የንግድና የፖለቲካ ፍልስፍናቸውና ትስስራቸውም የተለያየ ነው።
ዲሞክራቶች በአፍሪካ በተለይ እጅግ አውዳሚ ፖሊሲዎችን የተከተሉ መሆናቸው በመጽሐፍ የምናነበው ሳይሆን ራሱ የኛው ትውልድ ዋቢ የሆነበት አሳዛኝ ክሥተት ነው። የክሊንተን ዲሞክራት ቡድን ኤርትራን አስገንጥሎ፣ ሱማሊያን ብትንትኗን አውጥቶ፣ የሩዋንዳን ጭፍጨፋ አካሂዶ በተለይ በሱ ዘመን ኢትዮጵያ የመጡ እንቃቅላ የስቴት ዲፓርትመንትና የዲፕሎማሲው ክፍል ወጣቶች ከወያኔ ጋር እየተዳሩ፣ ከዝርፊያውና ዳንኪራው እየተሳተፉ በክሊንተን ስምነት አመት፣ በኦባማ ስምንት አመት፣ ጥርስና ጥፍር ቀንድ አውጥተው በባይደን ፕሬዚደንሲ ግዙፍ የሥልጣን ማማዎች ላይ የሚገኙ አማራ በጅምላ ቢፈጅ፣ በጅምላ ቢቀበር፣ በሚልዮናት አኅዝ ቢፈናቀል፣ መሠረተ ልማቱ ቢወድም ግድ የማይላቸውና እንዲያውም ያንሳል ብለው ያለው መንግስት ከአይ ኤም ኤፍና ወርልድ ባንክ ብድር እንዲያገኝ ያመቻቹ ጸረ ኢትዮጵያ መንጋ ለመሆን በቅተዋል። ብዙዎቹ ከወያኔ ባለሥልጣናት ጋር በአምቻ ጋብቻ፣ በጉዲፈቻ ጭምር የተቆራኙ ናቸው።
ሪፐብሊካን ፓርቲን በመምረጥ ቢያንስ እነዚህ መዥገሮች ለአራት አመት ከሀገራችን ቆዳ ላይ ተነቅለው መጠነኛ እፎይታ እናገኝ ዘንድ እመክራለሁ። “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል። ሁሉም ጸረ አፍሪካ ናቸው” የምትሉ ትኖራላችሁ። ከአንደኛው ግን አንደኛው ይብሳል። ዲሞክራቶች በዘመነ ካርተር ኢትዮጵያን ገንዘብ የተከፈለበት የጦር መሣሪያና የቴክኒክ ድጋፍ በመከልከል በሶማሊያ ወረራ ጭንቅ ውስጥ የገባው ደርግ ወደ ሩሲያ እቅፍ እንዲሄድ ያደረጉ በዚህም በኢትዮጵያ ለተከተለው ምስቅልቅል አንደኞቹ ተጠያቂዎች የሆኑ ናቸው። በክሊንተን ጊዜ የኤርትራን መገንጠል ሲያመቻቹ በተቃራኒው ነጻ መንግሥት የመሠረተችው ሶማሊላንድ እውቅና እንዳታገኝ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ሰሜን እና ደቡብ ፍጹም ተቃራኒ ፖሊሲ በመከተል ጎጂ ሥራ ሠርተዋል። ዲሞክራቱ ክሊንተን የሩዋንዳን ጄኖሳይድ በአርምሞ ያስፈጸመ ብቻ ሳይሆን የጄኖሳይዱ እልቂት ያስከተለው የቀጠናውና የኮንጎ መፍረስ ቀጥታ ተጠቃሚ እና የማእድን ቱጃር ያደረገው ግለሰብ ነው። በኦባማ ስምንት አመት ዘመን ኦባማም የርሱ ኮልኮሌዎችም ኢትዮጵያ እየተመላለሱ በወያኔ የፉገራ ምርጫ ላይ የዲሚክራሲያዊነት ሰርተፊኬት ማኅተም ሲያደርጉ የነበሩ ወራዶች፣ ጸረ ዲሞክራሲና ጨካኞች ናቸው። ካርተርም ከመቃብር ተመልሶ የካርተር ማእከል በሚል የማጭበርበሪያ ድርጅቱ ጭምብልነት ኢትዮጵያ መጥቶ ያንኑ ጸረ ኢትዮጵያ የጥላቻ ሥራውን ደግሞ ለመሥራትና ዳግም ኢትዮጵያን ለመውጋት የወያኔን ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ነው ብሎ የበየነ ሌላው ወራዳ አንጋፋ ዲሞክራት ነው። ብሊንከን የተባለው የባይደን ተሿሚ እና የርሱ ተላላኪ የበሬ ነጋዴ መሳዩ ማይክ ሃመር በወለጋ፣ መተከል፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ፣ አዲስ አበባ ወዘተ በአማራ ላይ የሚደረገውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሳያወግዙ ከዚያ በኋላ በመጣው በትግራይ ጦርነት ጊዜ እጅግ የተወራጩ፣ የዘር ጨፍጫፊዎቹን ከተጠያቂነት አስመልጠው አቅፈው ያሸላለሙ ልክ እንደ ኸርማን ኮህን ከአሜሪካ መንግሥት ሌላ የበላይ አለቃ ያላቸው የሚመስሉ አስነዋሪ ዲሞክራቶች ናቸው። ምክንያቱም የሚጣረሰውን አቋምና ተግባራቸውን በምንም ዓይነት ከአሜሪካ ሕዝብ፣ የንግድ ድርጅቶች ወይም የመንግሥት ጥቅም አኳያ ትርጉም ለመስጠት ስለማይቻል።
ስለዚህ የአማራ ሕዝብ ከነዚህ በጸረ ኢትዮጵያ አቋም ሥር የሰደዱና ቀንድ ያወጡ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ኮልኮሌዎች ቢያንስ የአራት አመት እፎይታ ያገኝ እና የህልውናውን አደጋ ለመቀልበስ ፋታ ይኖረው ዘንድ በዚህኛው ዙር ሪፐብሊካኖችን አንምረጥ። እዚህ ባለንበት ቦታ ፖሊሲያቸው የማይጥመን ይኖራሉ፣ በምሥራቅ አፍሪቃ ላይ ከተደቀነው አደጋ አኳያ ግን እነሱ ይሻሉናል በማለት ነው። የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ሱማሊያ፣ ሩዋንዳ የወደሙት በዲሞክራቶች የበላይነት ዘመን ነው። አሁንም ሱዳን እና ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ የተዘፈቁት በዲሞክራቶች አስተዳደር ነው። አፍሪካ ውስጥ ከሚደርስ የጦርነት ውድመት ጋር የተለየ ቁርኝት አላቸው። በዚህስ አገር ቢሆን ኢትዮጵያውያን ካሉን የቤተሰብና የሃይማኖት እሴቶች ጋር ዲሞክራቶች ምን ያህል ተመሳሳይ ናቸው? በፖለቲካ የዋህነት ወይም በተጠቃሚነት ተገዝተው ተደራጅተው ዲሞክራቶችን ለማስመረጥ የሚንቀሳቀሱ ወገኖቻችን አሉ። ባለፉት አርባ አመታት ዲሞክራቶች በሀገራችን ላይ ያስከተሉትን እና እያስከተሉ ያሉትን አደጋ አጢነው በዚህ ታሪካዊ ወቅት ከተሳስተ አቋማቸው እንዲቀየሩ ጥሪ አቀርባለሁ። ባላፈው ምርጫ ትራምፕን በንግግሩና በብልግናው በመጥላት ከሥልጣን ለማውረድ ብዙዎች ተሯሩጠን፣ ጉዳዩ ተሳክቶ ለሥልጣን የበቁት ዲሞክራቶች ወራት ሳይሆናቸው ክፋታቸውን ተረድተን እነሱን ለመቃወም እንደገና ስንደራጅና ስንባዝን ከርመናል። ያንን መድገም የለብንም። ንግግርን ሳይሆን ተግባርን እንመልከት። የአቢይ አህመድ ሸፍጥ፣ ሽወዳና ክህደት በቂ አላስተማረንም? ስለ አንደበትና ስለተግባር?
“አንመርጥም፣ ሁሉም ያው ናቸው” ብለን እቤት አንቀመጥ። በእንግሊዝኛ “The lesser of two evils” እንደሚባለው አንዳንድ ጊዜ ከሁለት ክፉ በጣም ያልከፋውን ክፉ መምረጥ፣ መጋፈጥ ያለብን የሕይወት ግዴታ ይሆናል።
መልካም ምርጫ