April 8, 2024
13 mins read

ጠፈርሲን፣ ፀሐይ ግርዶሽና መጽሐፈ ሄኖክ – መስፍን አረጋ

“ጥቁር ነኝ ነገር ግን ውብ ነኝ” (ንጉስ ሰለሞን፣ መኃልየ መኃይል ዘሰለሞን፣ ምዕራፍ 1 ቁጥር 5)

Then I will swear beauty herself is black

And all they foul that thy complexion lack.

ዊልያም ሸክስፒር (William Shakespeare), Sonnet 132

images 5

የውበት ምስል ቀዘባ፣ አባባ የልብ ሌባ

ናት ብየ ጥቁር ደርባባ፣ አፍሪቃዊት ወለባ

ሳልጠራጠር፣ ሳልባባ፣  ይሙት እላለሁ አባባ።  

ይህን ተቃውሞ በያምባ፣ የሚለኝ እሰጥ አገባ

መሆን አለበት ነጫጭባ፣ አለያም ቢጫ ወይባ፣

አለያም ጥቁር ጀዝባ፣ በራሱ ማመን ያልገነባ። 

ጠፈርሲን (astronomy) ማለት የጠፈር ጥናት ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ደግሞ ጠፈር (ሰማይ፣ የምድር ባጥ) እና ስነ ከሚሉት ቃሎች ነው።  ከዚህም ጠፈርሲናዊ (astronomical)፣ ጠፈርሲነኛ፣ ጠፈርሲነኝት (astronomer, astronomist) የሚሉትን ቃሎች እናገኛለን።  ጠፈርሲን የተጀመረው፣ በእብራይስጥኛ ኩሽ ይባል በነበረው የጥቁር ሕዝብ ምድር ነበር።  እብራይስጦች ስያሜውን የወሰዱት ደግሞ ከራሱ ከጥቁር ሕዝብ ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም።

እዚህ ላይ ግን ታሪካዊው ኩሽ በቅርብ ከተፈጠረው ከኦሮሙማው ኩሽ ጋር አንዳችም ግንኙነት እንደሌለው ባጽንኦት ማሳሰብ ያስፈልጋል።  በማንነታቸው ስለሚያፍሩ መልካሙን ነገር ሁሉ የኔ የሚሉት፣ አስተሳሰባቸው ከጨቅላ ሕጻን አስተሳስብ የማይሻል ትናንት መጤ የኦሮሙማ እንጭጮች ኩሽ የሚለውን ቃል የሰሙት (ይህን ፀሐፊ ጨምሮ) ጥቂት አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ኩሽ እና ኢትዮጵያ በሚሉት ስያሜወች ላይ የጻፉትን ተመልከተው ወይም ሲወያዩ ሰምተው ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም።  ቃሉን የመረጡት ደግሞ ወደውት ወይም ታሪኩን አወቀው ሳይሆን ኢትዮጵያ የሚለውን አምርረው የሚጠሉትን ቃል ላለመጥራት ሲሉና ሲሉ ብቻ ነው።  አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ኦሮሙሜወች አቆሸሹት ብለው ማናቸውንም ቃል መጥላት የለባቸውም፣ ኦሮሙሜወች የቀቡትን ቆሻሻ ሙልጭ አድርጎ ማጠብና አቆሻሾቹን ማጋለጥ እንጅ።  የኦሮሙሜወች ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ኩራቶች ሁሉ እያቆሸሹ ኢትዮጵያውያን እንዲያፍሩባቸው ማድረግ መሆኑን መቸም መዘንጋት አያስፈልግም።

ለማንኛውም በእብራይስጥኛ ኩሽ ይባል የነበረው የጥቁር ሕዝብ ምድር ዛሬ ግብጽ የሚባለውን የጥንቱን ከመትን (Kemet) ጨምሮ መላዋን አፍሪቃን፣ ካፍሪቃ ወዲያ ደግሞ አሁን ትናንትን ወደ እስያ የተደመሩትን (ዐረብ ከጥቁር ነጥቆ የሰፈረባቸውን) ሳዑዲያ ዐረቢያን፣ የመንን፣ ኦማንን እና ከነሱ በላይ የሚገኙትን አናሳ አገሮችና ሐከሎች (የበርሐ ገነቶች oasis) የሚያጠቃልል ታላቅ ምድር እንደነበር ከመጽሐፍ ቅዱስ መረዳት ይቻላል፣ ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን በቂ ማስረጃ ባይሆንም።   ለምሳሌ ያህል መዝሙረ ዳዊት (71-9፣ 73-14፣ 87-31)፣ 2ኛ ዜና መዋዕል (14-9፣ 14-12፣ 14-13፣ 16-8)፣ ሁለተኛ ነገሥት (19-9)፣ ትንቢተ ኢሳያስ (37-9)፣ ትንቢተ ሕዝቅኤል (30-4፣ 30-5፣ 30-9)፣ የሐዋርያት ሥራ (8-27) መመልከት ይቻላል።  ለበለጠ መረጃ ደግሞ የታላቁን ሊቅ ያለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን መጽሐፍ ሰዋሰው ወግስ፣ ወመዝገበ ቃላታ ዐዲስ (ግጽ 13 እና 248) መመልከት ይቻላል።

ለምሳሌ ያህል መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ (ምዕራፍ 14) ላይ “ኢትዮጵያዊው (ማለትም ኩሹ) ዝሪ እንድ ሚሊዮን ሰወችና ሦስት መቶ ሠረግሎች ይዞ ወጣባቸው” እያለ አሳ በሚባለው የይሁዶች ንጉስ እና በዘመናቸው በሠረገላ የተራቀቁ በነበሩት በኩሾች መካከል የተካሄደውን ጦርነት በስፋት ካተተ በኋላ ይሁዶቹ ወደ “ኢየሩሳሌም ተመለሱ” ይላል።  ይህ የሚያመለክተው ደግሞ በዚያ ዘመን ኢየሩሳሌምን የከበበው ምድር ብቻ ሳይሆን ራሷ እየሩሳሌም የጥቁሮች ምድር ሳትሆን እንደማትቀር ነው፣ ኩሾች የመጡት የተነጠቁትን ምድር ለማስመለስ ሳይሆን አይቀርምና።

ጠፈርሲን (astronomy) የተጀመረው ኩሽ ይባል በነበረው በታላቁ የጥቁር ሕዝብ ምድር መሆኑን ከመጽሐፈ ሄኖክ የበለጠ ማስረጃ ሊኖር አይችልም።

ራማዊ አካላት (celestial objects) ራማ ሉል (celestial sphere) ላይ የሚያካሂዱትን ራማዊ ሑሰት (celestian motion) እና ባሕሪ ለመጀመርያ ጊዜ በትክክል የተረዳውና የተነተነው ሂኖክ ነው።  (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 21 እስክ 25)

ጨረቃ የራሷ ብርሃን እንደሌላትና የምታበራው የፀሐይን ብርሃን በመፀብረቅ (reflect) መሆኑን ለመጀመርያ ጊዜ የተገነዘበውና የጻፈው ሄኖክ ነው።  (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 22 ቁጥር 5)

የጨረቃና የፀሐይ ዘዌያዊ ገማዘንጎች (angluar diameters) [ከምድር አንጻር] ከሞላ ጎደል እኩል እንደሆኑና ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ (total solar eclipse) የሚከሰተው በዚሁ ምክኒያት እንደሆነ ለመጀመርያ ጊዜ የተረዳውና የገለጸው ሄኖክ ነው። (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 21 ቁጥር 57)

ወደ አድማስ በጭራሽ ሳይጠልቁ ምድርን የሚሖሩ (revolve) [በትክክል ለመናገር ደግሞ ምድርን የሚሖሩ የሚመስሉ] በዘመናዊው አጠራር ሠቅዋልታዊ (circumpolar) የሚባሉ ኮኮቦች እንዳሉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገነዘበውና የዘገበው ሄኖክ ነው። (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 24 ቁጥር 14)

የጨረቃ መልኮች (phases) እየተቀያየሩ ጨረቃ ዐዲስ ጨረቃ (new moon)፣ ሙሉ ጨረቃ (full moon)፣ ሐኔ ጨረቃ (crescent moon)፣ ሰኒም ጨረቃ (gibbous moon) የምትሆነው፣ የፀሐይ ብርሃን የሚያገኘው የጨረቃ ገጽ ከምድር ሲታይ መጠኑ በየጊዜው ስለሚለዋወጥ እንደሆን ለመጀመርያ ጊዜ የተረዳውና ያብራራው ሄኖክ ነው።   (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 26)

ፈለኮች (planets) ፀሐይን እንደሚሖሩ (በፀሐይ ዙርያ እንደሚጓዙ) ለመጀመርያ ጊዜ የተገነዘበው፣ ትናንት መጤ ፈረንጆች እንደሚሉት ኒኮላስ ኮፐርኒከስ (Nicolas Copernicus) ሳይሆን ሄኖክ ነበር።  ፈለኮችን በግእዝ ቅኑይ (ማለትም የተገዛ፣ የተነዳ) ያላቸው ደግሞ ለፀሐይ የተገዙ መሆናቸውን [ማለትም በፀሐይ ሥር ሁነው ጀንበራዊ ስርዓት (solar system)  እንደሚመሠርቱ] ለመጠቆም ነበር።  (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 24 ቁጥር 8)

የራማዊ አካላትን (celestial objects) በተለይም ደግሞ የፀሐይንና የጨርቃን ራማዊ ሑሰት (celestial motion) ለመግለጽ ይረዳው ዘንድ ራማ ሉልን (celestial sphere) በተለያዩ መስኮቶች የከፋፈለው [ማለትም በዘመናዊው አጠራር ቀኝ እርገት (right ascension) እና ዝቅዝቀት (declination) የሚባሉትን የፈጠረው] ሄኖክ ነው።  (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 26)

ዓመት ማለት ምድር ፀሐይን አንዴ ለመሖር (revolve) የሚፈጅባት ጊዜ እንደሆነ በቅድሚያ የተረዳውና፣ እያንዳንዱን ዓመት ለ 364 ዕለታት የከፋፈለው ሂኖክ ነው።  (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 23 ቁጥር 20)

ዕለት ማለት ምድር በዛቢያዋ ላይ አንዴ ለመሾር (spin) የሚፈጅባት ጊዜ መሆኑን በቅድሚያ የተረዳውና፣ እያንዳንዱን ዕለት ለ 18 ሽንሽኖች የሸነሸነው (ማለትም በዘመናዊ አጠራር ለ 24 ሽንሽኖች ተሸንሽኖ ሰዓት የሚባለውን የፈጠረው) ሄኖክ ነው።  (መጽሐፈ ሄኖክ፣ ምዕራፍ 21 ቁጥር 18 እስከ 22)

 

ባጠቃላይ ሲታይ ዘመናዊ ጠፈርሲን (modern astronomy) ማለት ሌላ ምንም ማለት ሳይሆን መጽሐፈ ሄኖክን (በተለይም ደግሞ ከምዕራፍ 21 እስከ 25 ያሉትን ክፍሎች) አምልቶና አስፍቶ፣ ተንትኖና አብራርቶ እንደገና መጻፍ እንጅ ሌላ ምንም አዲስ ነገር የለውም።  በርግጥም ብልሁ ንጉስ (መጽሐፈ መክብብ፣ ምዕራፍ 1 ቁጥር 10 ላይ)  “ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም” ያለው መጽሐፈ ሄኖክን አንብቦ ወይም ስለመጽሐፉ ይዘት ተነግሮት መሆን አልበት።

ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ አንድ ሐርግ ቢመዙ ደን ይወዘውዙ ነውና፣ መጽሐፍ ሄኖክ ተጽፎ የተገኘው በግእዝ ከመሆኑ እንነሳ።  ግእዝን ደግሞ አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፣ ይልቁንም ደግሞ የመጀመርያውን የግእዝ መዘገበ ቃላት የጻፈውን ኦግስቲን ዲልማንን (Augustin Dillmann) ጨምሮ አያሌ የጀርመን ሊቃውንት በሙሉ ድፍረት የአዳም ቋንቋ (የመጀመርያው ሰው ቋንቋ) ይሉታል።  ግእዝን የአዳም ቋንቋ ለማለት የበቁት ደግሞ (ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ቁጥር 1 ላይ)  “ወኮነ ኩሉ ምድር አሐተ ከንፈረ ወአሐደ ነገረ” (ምድር ሁሉ ባንድ ቋንቋና ንግግር ነበረች) የሚለውን ይዘውና ተመርኩዘው ነው።  ስለዚህም፣ ግእዝ የአዳም ቋንቋ ከሆነ፣ ንጉስ ሰለሞን ማን ሊሆን ነው?  ራሱ ንጉስ ሰለሞንስ ቢሆን (መኃልየ መኃይል ዘሰለሞን፣ ምዕራፍ 1 ቁጥር 5 ላይ) ጥቁር ነኝ ነገር ግን ውብ ነኝ ለምን አለ?

 

ጦቢያ ስለሆነ ቀዳሚ የሰው ዘር

ሰውን በአምሳሉ መፍጠሩን ሲናገር

ጌታ ማለቱ ነው ነኝ እንደሱ ጥቁር።

ስለዚህም ሰይጣን የጌታ ባላንጣ

በተቃራኒው መልክ ይሆናል የነጣ።

ለፈረንጅ ስዕል የሚስግድ ሐበሻ

ተዋርዶ አዋራጅ የረከሰ ውሻ።

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop