መጋቢት 21 ቀን 1953 ዓ.ም
#በዛሬዋ_ዕለት
ከ 63 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን የታኅሣሥ ግርግር በመባል በታሪክ መዝገብ የሚታወቀውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በግንባር ቀደምነት ያካሄዱት የነበሩት የክብር ዘበኛ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ በተቀበሉት ፍርድ መሠረት በስቅላት የተቆጡበት ዕለት ነበር።
የእልፍኝ አስከልካዩ ኮሎኔል አሰፋ ደምሴ (በኋላ ጄኔራል) መጋቢት 20 ቀን 1953 ዓ.ም ከሌሊቱ 9፡00 ስልክ ደውሎ “የጄኔራል መንግሥቱን የሞት ቅጣት ፍርድ ጃንሆይ አጽድቀውታል፡፡ ቅጣቱን በጧቱ እንድታስፈጽም አዘዋል፡፡
አንደኛ ክፍለ ጦር መድፈኛ ግቢ በቶሎ እንገናኝ” አለኝ፡፡ እንዳለኝ ቶሎ ተዘጋጅቼ ከተባለው ቦታ ስደርስ፣ ሽብር የተነሣ ይመስል በአካባቢው የነበረው ግርግር ሌላ ነበር፡፡ ከዚያ ለጄኔራል መንግሥቱን ሰላምታ ከሰጠሁት በኋላ የሞት ቅጣቱ የሚፈጸመው በዕለቱ ጧት መሆኑን ነገርኩት፡፡ ምንም ዐይነት የመደንገጥ ወይም የመናደድ ነገር አላሳየም፤ ምንም አልመሰለውም፡፡ ዝም ብሎ ተቀበለው፡፡
ኮሎኔል አሰፋ ቀለም ከመነከሩ በቀር በጣም ተራ የሆነ ስስ መርዶፍ፣ እጅጌው አጭር ሸሚዝና ቁምጣ ሱሪ የወህኒ ልብስ አምጥቶ ኑሮ “ያን ይልበስ” አለ፡፡ “አይሆንም” ብዬ በመጨቃጨቅ ጊዜ ካሳለፍን በኋላ፣ እኔ “ለጃንሆይ ይነገር እንጂ ይህንን ልብስ አልብሼ ቅጣቱን አላስፈጽምም” ስላልኩ፣ ሌሊት ጃንሆይ እንዲሰሙት ተደርጎ “እሽ የራሱን ልብስ ይልበስ” ብለው ስለፈቀዱ፣ የራሱን ልብስ ከለበሰ በኋላ በስሪ ኳርተር መኪና ላይ “ተሳፈር” ስንለው፣ “እሱን እሺ፤ ነገር ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፤ ብትቀበሉኝ” አለ፡፡ “እሺ ጠይቅ” አልነው፡፡
“እዚህ ያሉት ወታደሮች ባይኔ አጥርቶ አለማየት ምክንያት ወደ ሽንት ቤት ስሄድ እቸገር ስለነበር ደግፈው ወስደው በማድረስ፣ በመመለስና የሚያስፈልገኝን ሁሉ በማድረግ ውለታ ውለውልኛልና እንዳመሰግን ብትሰበስቡልኝ ፈቃዳችሁን እጠይቃለሁ” አለ፡፡ ፈቀድንለትና የተሰበሰቡትን አመሰገናቸው፡፡ ወታደሮቹ ወጣቶች ስለነበሩ በሁኔታው መቆጨትና ማዘናቸው በፊታቸው ላይ ይታይ ነበር፡፡
ከዚያ በስሪ ኳርተሩ ላይ ተሳፍሮ በብዙ ወታደሮች ታጅቦ ተክለሃይማኖት አደባባይ ከመስቀያው ቦታ እንደ ደረስን፣ ወደ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ዞሮ እጅ እንዲነሣ አደረግን፡፡ ከዚያ ገመዱን ከዐንገቱ ላይ ሊያገቡ ሲሉ ኮሎኔል አሰፋ ደምሴ “አላይም” ብሎ መሄድ እንደ ጀመረ፣ [ጄኔራል መንግሥቱ] “ጥሩት” ብሎ አስጠራውና “እባክህ እነዚህ ሰዎች አያውቁትምና የገመዱን ቋጠሮ በተገቢው ቦታ እንዲያደርጉት ንገርልኝ” አለው፡፡
ይህን ያለበት ምክንያት በላይ ዘለቀ ሲሰቀል ገመዱ በትክክለኛው ቦታ ባለመሆኑ የደረሰውን ሥቃይ ዐይቶ ስለነበር ነው፡፡ እሱም “እሺ” ብሎ ለሰዎቹ ነገራቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ገመዱን በተገቢው መንገድ አደረጉለትና መኪናው ወደፊት ሄደ፡፡ ብዙም አልቆየ፣ ነፍሱ ወዲያው ዐለፈ፡፡
#ታሪክን_ወደኋላ