መኖሩን እያወክ ሞት ቆሞ ተደጅህ፣
ጭራቅ ያገለገልክ ተገዝተህ በሆድህ፣
መሞት ባይኖርማ ባህር ደም በጠጣህ፣
ንጹሑን ፃድቁን በካራ አሳርደህ!
እርጉዝ በጎራዴ በጦቦያ አስመትረህ፣
ፖለቲካ ዝሙት መደመር አጡዘህ፣
አምላክን ህሊናን ልቡናን የጎዳህ፣
ሁሉን የማይተወው እንኳን ሞት አለልህ፡፡
ቲቪና ራዲዮ ዘጋቢ ነኝ እያልህ፣
ግድብ ውሀ ሙላት እየለፈለፍክ፣
ዜጎች በዘራቸው ተቀልተው እያየህ፣
የዘር ማጥፋት ወንጀል ሆን ብለህ የደበክ፣
እንደ ጎርፍ የሚወስድ እንኳን ሞት አለልህ፡፡
አስር ሰላሳ ዓመት የቀጠልክ መስሎህ፣
ሞልተህ የማትመርገው ከርስህ አስገድዶህ፣
ዘሩ እየተጠራ ሲታረድ ወገንህ፣
ለጥ ብለህ የተኛህ እንጀራ እየጎረስክ፣
እንኳንም ሞት አለ ጠርጎ የሚወስድህ፡፡
እርጉዝ ስትመተር ህሊናህ ሳይወቅስህ፣
ሽፍንፍን አድርገህ ማለፍን የመረጥክ፣
በአንተም የሚመጣ እንኳን ሞት አለልህ፡፡
ፒ ኤች ዲ ዲግሪ ማስተርስ አለኝ እያልክ፣
ድስኩር ስትደሰኩር አለሁ ስትል ከርመህ፣
መደመር ግድብን ፈንድ ፈንድዱ እያልክ ፣
ለነፍሰ ገዳዮች ልሙጥ ካድሬ ሆነህ፣
ዘር ፍጅት ሲፈጠም ምላስክን የለጎምክ፣
ተፊትህ የቆመ እንኳን ሞት አለልህ፡፡
እንደ ብፁእ ቅዱስ ቆብ ተራስህ ደፍተህ፣
ተአንገት ተደረትህ መስቀል አንዠርገህ፣
ክርስቲያን ሲታረድ ድሎትህ አታሎህ፣
በሟች አስራት ፍርፍር ክቶፍህን እየዋጥክ፣
በጎችህን ቆመህ በካራ ያሳረድክ፣
እንኳንም ሞት አለ ችሎት የሚያቀርብህ፡፡
በአሪዎስነትህ መጣፍ የሚያወሳህ፣
በአድርባይነትህ ታሪክ የሚከትብህ፣
በሆዳምነትህ ትውልድ የሚወቅስህ፣
የዘር ፍጅት ወንጀል በመሸፈን ያለህ፣
ረስቶ እማይቀረው እንኳን ሞት አለልህ፡፡
አቶ ሞት እያለ ያን ያህል ተከፋህ፣
መሞትማ ባይኖር የት ይደርስ ኃጥያትህ፣
አስቆርቱ ይሁዳ ሰማእትን የከዳህ፣
እንኳንም ሞት አለ ሲው አርጎ እሚወስድህ፡፡
በላይነህ አባተ ([email protected])
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.