ሰሞኑን በየሚዲያው (በይነ- መረቦች) የሚናፈሱ ውል የለሽ ወሬዎች እየተንሸራሸሩ እና ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛሉ።
እነዚህም የኩሸት ወሬዎች እና ሴራዎች “ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ ከአማራ ፋኖ ትግል እራሱን አገለለ” እንዲሁም ወልቃይት እና ራያ ከአማራ ማንነታቸው ተነጥለው እራሳቸውን ችለው ክልል ሊሆኑ ነው” የሚሉ ይገኙበታል።
ከሁለተኛው ፍሬ ፈርስኪ ማለትም “ወልቃይት እና ራያ ከአማራ ማንነታቸው ተነጥለው እራሳቸውን ችለው ክልል ሁነው ሊዋቀሩ ነው” የሚለውን ተልካሻ ወሬ እና ሰማይ እና ምድር ቢደበላለቅ እውን ሊሆን የማይችለውን ትርኪ -ምርኪ ህሳቤ ስንገምግመው።
ወልቃይቴዎች የኖህ ልጅ የሆነው አባታችን አኩኖ -ወሳባ ከክርስቶስ መወለድ በፊት በ224 ምዕተ ዓመት ከወለዳቸው ልጆቹ ማለትም ከበለው ፣ ከከለው ፣ ከአገው ፣ ከኖቫ ፣ ከላካዶን እና ከሳቫዝ መካከል የአማራው ነገድ የሆነው ከላይ ከተጠቀሱት ወንድማማቾች እና እህትማማቾች መካከል “የከለው” ነገድ ወልቃይትን የመነጠረ እና የተፈጠረበት ምድር መሆኑን በታሪክ የተዘገበ እና ተከትቦ የሚገኝ ሃቅ ነው።
ይህን መሰረት አድርገን ይህን አጓጉል እና ፉርሽ የሆነ የአማራ ጠላቶች ልፈፋ ስናየው የአማራ መነሻ እና መሰረት የሆኑትን ወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምት እና ራያን “ምን ብለው ሰይመው ሊከልሏቸው” እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም እነዚህን የአማራ ውብ እና ለም ዐፅመ እርስቶች በማናለብኝነት ፣ ከእውቀት ነፃ በሆነ አካሄድ እና ታሪክን አዛንፈው “ሊበሏት የአሰቧትን አሞራ ዥግራ ናት ይሏታል” እንዲሉ ይህን ቅዠት የተሞላበት ህሳቤያቸውን እነብልፅግና እና አጋሮቻቸው ለመተግበር የሴራ ፖለቲካ እያካሄዱ መሆኑን ቁልጭ ብሎ እየታየ መጥቷል።
የቤተ – ሙከራው እንጭጭ ስሌት እንደሚያሳየው ወልቃይት እና ራያ ራሳቸውን ችለው ክልል ቢሆኑስ የሚል ፉርሽ የሆነ ፅንሰ ሃሳብ በአማራው እና በመላ ኢትዮጵያውያን ልቡና እና አስተሳሰብ ለማስረፅ እንደተፈለገ ቀመረ ስሌቱና ሴራው ቁልጭ እና ግልፅ ሆኖም እየታየ እና አየተለፈፈ ነው።
ያም ሆነ ይህ ፣ ግራ ነፈሰም ቀኝ “ወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምት እና ራያ እንደ ሲዳማ ራሳቸውን የቻሉ ክልሎች ቢሆንስ” የሚልውን ህሳቤ በአማራው ዜጋ ስነ-አዕምሮ ውስጥ ለማስረፅ የሚደረገው መፍጨርጨር እና ሙከራ ሚዛን የማይደፋ እና ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ፣ የብልፅግና መንግስት የተለመደ ዝብረቃ ከመሆኑም ባሻገር የአማራን ህዝብ በዚህ የውዥንብር ንድፈ ሃሳብ ለመነጣጠል እና ለማጋጨት መሞከሩ ከማይወጡበት አዘቅት የሚያስገባ እና ከባድ የሆነ ዋጋም እንደሚያስከፍል እንቅጩን ልንነግራችሁ እንወዳልን።
“ማንን ይዞ ጉዞ” እንዲሉ ወልቃት ጠገዴ ፣ ጠለምት እና ራያን ከአማራ ነጥሎ ማሰብ “አባይን ያለ ጣና ፣ ተከዜ ፣ ርብ እና ገባሪ ወንዞች እንደ ማሰብ” መሆኑን እነ ብልፅግና ሊረዱት ይገባል እንላለን።
የዚህ ፅሁፍ ከታቢ እንደወልቃይት ተወላጅነት በተለያዩ የአማራ አደረጃጀት ስብሰባዎች እየተገኘ የወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምት እና የራያ የአማራ ዕፅመ ዕርስት ባለቤትነት ጥያቄዎች የአማራ ዋና አንኳር ጥያቄ እንደመሆናቸው በየመድረኩ እንደማይነሱ ፣ የመቀዝቀዝ አካሄዶች እንደሚታይ እና በጉዳዩ ላይ ትኩረት ያለመስጠት እዝማሚያ እንዳለ ቢወተውትም ማሳሰቢያው እና ጉትጎታው አድማጭ እንዳላገኘ ትዝብቱን እየገለፀ እና ዝምታው አሳሳቢ እንደሆነም አስረግጦ ያስረዳል።
ህወሃቶች ፣ አፍቅሮት ህወሃት አቀንቃኝ የሆኑ ሚዲያዎች (በይነ-መረቦች) ፣ ወልቃይት እና ራያን በህልማቸው የሚያርዮ ፣ በውንም ፣ በመወለድም ሆነ በመኖር የማያውቋት ትህንጋውያን “ወልቃይት እና ራያን” “ውሸት ሲበዛ እውነት ይመስላል” እንዲሉ ዘወትር ሲያነሷት ፣ ሲኮለታተፉባት እኛ ባለቤቶቿ አማሮች ግን “በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል ” እንዲሉ በየስብሰባው እና መድረኩ ከማንሳት ተቆጥበናል፣ ብዙም ጫና እየፈጠርን አይደለም ፣ የወልቃይት እና የራያን ሕዝብ የትግል አጋርነት ከጎንደር ሕዝብ ባሻገር በሌሎች አካባቢዎች ያሉ አማሮች ችላ ሳይሉ የፋኖን ትግል እያጧጧፉ ሊወተውቱ እና አጋርነታቸውን ሊያሳዩ የግድ የሚላቸው ጊዜ አሁን መሆኑን እናሳስባለን።
የወልቃይትና የራያን ጥያቄ “ ዝም አይነቅዝም” በሚል ትብዕል ዝምታን ካበዛንበት ፣ በንቃት ካልጎተጎትን እና አርማችን አርገን እኛ አማሮች በሚመለከተው ዓለም አቀፍ ሆነ ሃገር አቀፍ መድረኮች ላይ ጥያቂያችንን ካላቀረብን እና ካላሳሰብን “ ጥያቄውን ችላ ብለውታል” በሚል ህሳቤ ተፃራሪዎች እና የጎመጁት ትህነጋዊያን የአማራን ሕዝብ የመለያያ አጀንዳ አድርገው እንደሚጠቀሙበት እና እያደረጉት መሆኑኑ ልንገነዘብ የግድ የሚለን ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ሌላው ጉዳይ ትግል (የፖለቲካ ንቅናቄ) የመሪዎችና የግለሰቦች ጉዳይ ሳይሆን የሕዝብ የደቦ እና የጋራ መፍትሄ ፣ ነፃነት ማስገኛ እና የስልጣን መጨበጫ መሳሪያ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ይህን መሰረት አድርገን የ2005ቱን የአማራ ትግል ጎንደር ላይ ሆኖ ፋና ወጊነቱን ያሳየው ፣ ትግሉ እንዲጎመራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ “ጭቆና ሞት በቃኝ እና እንቢ አልገዛም” ባይነቱን በጋራ አጠንክሮ በማቀንቀን ህወሃት መዲናዋን አዲስ አበባን “ያሁላችው” ብላ ወደ መቀሌ እድትሸሽ ያደረገውን ኮለኔል ደመቀ ዘውዱን የአማራ የቁርጥ ቀን ልጅ “ ከፋኖ ትግል እራሱን አሸሸ” ብሎ መቀባጠር ውሃ የማይቋጥር መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
ለወልቃይት እና ራያ ሕዝብ ስለፋኖ ለመንገር ማሰብ “ ልጅ ለእናቷ ምጥ አስተማረች” እንደማለት መሆኑን አስረግጠን እንናገራለን።
እነ ራስ አዳነ ስዮም ፣ እነ ራስ ውብ ነህ ፣ እነ ራስ አያሌው ብሩ ፣ እነ ደጃች ብሬ ፣ እነ ደጃች ወልደስላሴ እና ወ.ዘ.ተ. ጣሊያንን ያንበረከኩበት የፋኖነትን ትብዕል ተላብሰው ፣ የአንበሳ ገዳይ ጎፈሬያቸውን እጎፍረው እና እንቢ ብለው (ፈንነው) ለድል እንደበቁ ዘንግቶ የወልቃይትን ሕዝብ ከፋኖ ለመነጠል ማሰብ ጣና ያለውን ዓሳ አውጥቶ እንደማምከን ይቆጠራል ፣ ማን ሆነ እና ነው የፋኖው መሰረት እና ፋና ወጊ? አንባቢያን ሆይ።
ስለዚህ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱን “ከፋኖ አጋርነት እራሱን አገለለ” ብሎ ማዘላበዱ አንድምታው “የወልቃይት ሕዝብ በአጠቃላይ ከፋኖ እራሱን አገለለ” ለማለት እንደተፈለገ ልንረዳ የግድ የሚለን እና “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል እና ነቄ ብለናል” ልንላቸው ይገባል።
ይህን ካልን ዘንዳ የአማራ ቀንዲል ፣ የአንድነት ተምሳሌት ፣ ደንበር አስጠባቂ እና እልቆ መሳፍርት የሌለው የባሕል እና የታሪክ ባለቤት የሆነችው ጎንደር በአጠቃላይ ፣ ወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምት “ ቡና የለም እንጂ ቡናማ ቢኖር አይ ሃገር አይ ሃገር አይ ሃገር ጎንደር” ተብሎ ቢቀኙላትም ፣ የቅኔው ፍችአዊ ትርጉም ግን በደንብ ሊፈታ ያስፈልጋል።
ጎንደር የብዙ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ስትሆን በተለይ በወልቃይት ፣ ጠገዴ እና ሰቲት ሁመራ እንደ ጥጥ ፣ ሰሊጥ፣ ሙጫ ፣ እጣን ፣ ቦለቄ ፣ የተፈጥሮ ማዕድናት ወ.ዘ.ተ. በገፍ የሚመረትባት እና ከራስ አልፎ ለመላ ሃገረ ኢትዮጵያ እና ለአማራው ሕዝብ የሚጠቅም ድልብ ምርት አምራች እና የተፈጥሮ ሃብት አፍላቂ ምድር መሆኗ ይታወቃል።
እቺን ወርቃዊት የሆነች ምድር የሚመኟት የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይላት የትየለሌ ሰለሆኑ በሰላም ፣ በዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ማጣቷን ለመግለፅ ( ቡና የሰላም ፣ የመሰባሰቢያ ፣ የአንድነት ምልክት ፣ ዓለም ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ፉት የሚላት ፍሬ በመሆኗ የስንኙ ውስጠ ወይራ ህሳቤ ግን እነዚህ የሰው ልጅ መሰረታዊ መብቶች በቡና አመላካችነት (Symbolism ) ኪናዊ በሆነ አግባብ አገላለፅ ወልቃይት ፣ ጠገዴ እና ጎንደር የመጣው እና የሄደው ሥርዓተ መንግስት ሁሉ ሰላም የሚነሷት ፣ የጦርነት አውድማ ተጠቂ የሚያደርጓት እና የሴራ ፖለቲካ ትብታብ ተጠቂ መሆኗን ለመግለፅ የተደረደረች ስንኝ መሆኗን ልንረዳ ይገባል።
መላ ጎንደር ለረጅም ዘመናት ስላም እና እረፍት እርቋት ስለሰነባበተች በተለይ ከ1966 ዓመተ ምህረት መባቻ ጀምሮ ከራሷ አልፋ ለአማራው ፣ ለጎንደር እና ለሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጥቀም ተስኗታል ለማለት ታስቦ የተቀኘ እና አሁንም ቢሆን የነዚህ የሰው ልጅ መሰረታዊ መብቶቿን ተነጥቃ በጦርነት አውድማ እየታመሰች እንዳለች ልብ ይሏል።
ስለዚህ ማንኛውም የአማራ አደረጃጀት የወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምት እና የራያን ጥያቄ ግንባር ቀደም መፈክሩ ሊያደርገው የሚገባ እና ወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምት እና ራያ የአማራ ዐፅመ እርስት የመሆናቸውን ጉዳይ አንገት ማተባችን ላይ አስረን መንቀሳቀስ የግድ የሚለን ከመሆኑ ባሻገር ፣ እኛ አማሮች ይህ ጥያቂያችን የማንደራደርበት ቀይ መስመራችን መሆኑን ማስረዳት ያለብን ጊዜ ወቅቱ እና ሰዓቱ እንደትላንት ሁሉ አሁንም መቀጠል እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን።
“ወልቃይት ፣ ጠገዴ ፣ ጠለምት እና ራያ ብረሳሽ ቀኘ ትርሳኝ”