ሃሳብን ግልፅ በሆነ ምክንያታዊነት ለመተቸት ካልቻልን…
December 9, 2023
ጠገናው ጎሹ
“የሃይማኖት ጉዳይ ሊያስጨንቀን የሚገባው ለምንድነው?” በሚል ርዕስ በሰጠሁትና በ11/25/2023 በዘሃበሻ በወጣው ሂሳዊ አስተያየት ላይ Lamrot የተሰኙ አስተያየት ሰጭ ለሰጡት አስተያየት የሰጠሁትን ግልፅ የማድረጊያ ምላሽ ለመማማር ይጠቅማል በሚል እሳቤ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ።
በቅድሚያ Lamrot የምታምንበትን/ኝበትን ጉዳይ መግለፅህ/ሽ እና በአስተያየቴም ላይ በገባህ/ሽ መጠንና ችሎታ አስተያየት በመስጠትህ/ሽ አመስጋኝ እንጅ አካኪ ዘራፍ ባይ አይደለሁምና አመሰግናለሁ።
የዚህ ምላሼ ዓላማ አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ለመጋበዝ ሳይሆን ይበልጥ ግልፅ ለመሆን ስለመሆኑ ግልፅ ይሁንልኝ።
እናም ወደ ዚያው ልለፍ፦
1) የምንነጋገረው የጋራ የሆነው እና እጅግ አስከፊና አስፈሪ እየሆነ የመጣው አገራዊ እውነታ (የወገን መከራና ስቃይ) ከሁሉም ሃላፊነታችን ፣ግዴታችንና ሥራችን መቅደም አ ኖርበትም ወይ? እውነተኛው ፈጣሪ የምናስብበት ረቂቅ አእምሮ እና የምናከናውንበት ብቁ አካል የሰጠን እንደዚህ እያሰብንና እያደረግን የእርሱን ድጋፍና በረከት እንድንጠይቅ አይደለም ወይ? እንኳንስ እኛ የደመ ነፍስ እንስሳትም በዚያው የደመ ነፍስ ስጦታቸው የሚሰጡት የቅድሚያ ቅድሚያ ይኖራቸው የለም እንዴ? ሊገድላቸው ወይም ሊያሳድዳቸው የሚሄድባቸውን ሰው ወይም ሌላ አውሬ መምጣቱን ሲያዩ ርቧቸው እየበሉት የነበረውን ነገር ትተው ቅድሚያ ለመሸሽና በህይወት ለመቆየት ይሸሹ የለም እንዴ? ታዲያ አገር ሙሉ ህዝብ (ወገን) በፖለቲካ ሥርዓት ብልሹነትና አረመኔነት ምክንያት በግፍ ሟሟት ፣ በቁም ሞት ፣ በርሃብ ቸነፈር ፣ በመፈናቀል ፍዳ ፣ በአእምሮና የአካል ጤንነት ቀውስ፣ በድንቁርና ክፉ ደዌ፣ ወዘተ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ እየተመታ ባለበት በዚህ ወቅት እድለኞች ከሆን በአካባቢያችን በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን እና ካልሆነም እየተከራየን ወይም በችሮታ እያገኘን እና ያም ካልሆነ በየቤታችን ፈጣሪን እያመሰገንንና እየፀለይን ያልኖርን ይመስል በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት የባህር ማዶ ቤተ ክርስቲያንና ገዳም ካልሠራን በሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ ትክክል አይደለም ብሎ መተቸት ለምንና እንዴት ፀረ ሃይማኖት ወይም ጤና ማጣት ይሆናል? የሚል እንጅ እንኳንስ ቤተ እምነት ሌላም የቅንጦት (ከታደልን) አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አያስፈልግም የሚል በፍፁም እንዳልሆነ ለመግባባት ካልቻልን አስቸጋሪ ነው ።
2) “ውጭ አገር ያሉ ኦርቶዶክሶች ቤተ ክርስቲያን አቋቁመው አምላካቸውን እንዳያመልኩ እሳት ሆነብህ ” የምትይው የምትለው በፅሑፌ ላይ ያልኩትንና ከላይ (ቁጥር 1) ግልፅ ያደረኩትን ወይ ካለመረዳት ወይም ካለመፈለግ ወይም ከስሜታዊነት (ከየዋህነት) የሚነሳ ካልሆነ በስተቀር እንኳንስ ተከታይ የሆንኩበት ታላቅ ሃይማኖት በህዝብና በአገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እስከሌለ ድረስ ወይም የህዝብን ስቃይና መከራ ወደ ኋላው አስቀምጦ ለፅድቅ ይሆነኛል የሚል ከንቱ ውዳሴ እስካልሆነ ድረስ የየትኛውም ሃይማኖታዊ እምነት ቤተ እምነት ወይም ቤተ ፀሎት በዓለም ዙሪያ ቢስፋፋ ከቶ የሚከፋኝ ሰው አይደለሁም። እንኳንስ እሳት ሊሆንብኝ። ይህ አይነት ደምሳሳ የሆነና ከግልብ ስሜት የሚነሳ የሃሳብ ልውውጥ ጨርሶ አይጠቅመንም!
3)”ጥልህ ከኦርቶዶክስ ጋር ነው” ለሚለው የአስተያየት ነጥብህ/ሽ ሁሉንም ነገር ለሚያውቀውና “እውነቱን እውነት እና ሃሰቱን ሃሰት” በሉ ለሚለው ለእርሱ ለእውነተኛው አምላክ እተወዋለሁ። እውነተኛው አምላክ በፖለቲካ ወለድ ጨካኝ ሰይፍ ደሙ የሚፈሰውንና የደም እንባ የሚያነባውን አያሌ ሚሊዮን ወገን ከሁሉም በፊት እንድንታደገው ፈቃዱ ብቻም ሳይሆን የአማኘነት ግዴታ ጥሎብናልና ይህንኑ ሆነንና አድርገን እንገኝ ማለት እንዴት የኦርቶዶክስ ጥላቻ እንደሚሆን አላውቅም።
4) “በእሸቱ ላይ ፍላፃው … “ ለሚለው አሁንም “ለምን እሸቱ ይተቻል” ከሚልና እጅግ እንጭጭ (immature) ከሆነ እሳቤ የሚነሳ ካልሆነ በስተቀር እሸቱ የህዝብ ልጅ የሚያሰኘው ሥራ ፈፅሞ አልሠራምና የህዝብ ልጅም አይደለም የሚል ሃሳብ ፈፅሞ አልወጣኝም። ያልኩትና አሁንም የምለው በፖለቲካ ወለድ ወንጀል እና በሃይማኖት መሪዎች እጅግ አሳሳቢና ልፍስፍስ አቋምና ቁመና ምክንያት አያሌ ሚሊዮን ንፁሃን ወገኖች የገዛ ሰፈራቸውና አገራቸው ምድረ ሲኦል ሆነውባቸው የወገንና የሃይማኖት አባት ያለህ በሚሉበት በዚህ እጅግ አስጨናቂና አስተዛዛቢ ወቅት ምንም እንዳልሆነ በሚያስመስል የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ላይ መጠመድና ለባህር ማዶ ቤ/ክርስትያን ወይም ገዳም ማሠሪያ “ሚሊዮኖች ዶላሮችን ስጡንና የገነትን ቁልፍ ውሰዱ” ማለት እንኳንስ እውነተኛው አምላክ ሚዛናዊ ወይም ጤናማ ህሊና ያለው ሰውም አሜን ብሎ የሚቀበለው አይደለም ብሎ መከራከር ለምንና እንዴት ፀረ እግዚአብሔር ሊሆን ይችላል?
5) “እረፍት ውሰድ፣ ነፍስህን አታስጨንቅ፣ ቀና ቀናውን አስብ” ለሚለው አገርና ህዝብ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ አጥቃላይ ቀውስና ውርደት ውስጥ ናቸውና ከምንም በላይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተን ተስፋ የምናደርገውን ከሞት በኋላ ህይወት እንውረስ፣ የፈጣሪ መቅድሶች የሆኑ የአያሌ ሚሊዮን ንፁሃን ህይወቶች (ወገኖች) እንዳልነበሩ እየተደረጉ ባሉበት እጅግ ግዙፍና መሪር ሁኔታ ውስጥ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባውን የቤተ እምነት ህንፃ “አሁንኑ ካልገነባነው መንግሥተ ሰማያት ሊያመልጠን ነው” በሚል አይነት ዘመቻ ተውኔት መጠመድ ትክክል አይደለም ማለት ረፍት የማይሰጥና ቀናም ነገር ካልሆነ ሌላ ምን? ምነው በስሜት መጋለቡን በቅጡ ብናደርገው ምናለበት? የፈጣሪን (የታላቁን መጽሐፍ ) ሃይለ ቃል ጨምረን ዘቅዝቀን እያነበብን የት ነው የምንደርሰው?
6) “ከአጠገብህ ያለውን/ችውን ወንድምህን/እህትህን በእውን ካላፈቀርክ እኔን እንዴት ለማፍቀር ይቻልሃል/ይቻልሻል “ ተብሎ ተነግሮናል እያልን አይደል እንዴ የምንሰብከው? ታዲያ አገራችን ውስጥ የሆነውና እየሆነ ያለው አጠቃላይና ሁለንተናዊ መከራና ውርደት ይህንን እጅግ ፈታኝ ሃይለ ቃል ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ትከኩረት ሰጥተን ተገቢውን ምላሽ እንድንሰጥ ካላስገደደን ስለ የትኛው እውነተኛ አማኝነት ነው የምናወራው? ይህንን በግልፅና በቀጥታ ከመግለፅና ከመናገር የበለጠ ሌላ ምን ቀናነት አለና ነው ቀና ቀናውን ያሳስብህ የምትይው/የምትለው ወዳጄ???
7) የገዛ ራሳችንን ግዙፉና መሪር እውነት በግልፅና በቀጥታ ከበመጋፈጥ ወደ ትክክለኛው ፍኖተ ድነት ከመመለስ ይልቅ በሃይማኖተኝነት ስም ለማምለጥ ከማይችሉት ግዙፍና መሪር እውነት መሸሽ ምን የሚሉት ኦርቶዶክሳዊነት ነው? እንዲህ አይነቱ አስቀያሚ ወለፈንዲነት (ugly paradox) ታላቁን ሃይማኖት ይጎዳል እንጅ ይጠቅማል እንዴ?
ከመሪሩ እውነታ በመሸሽ የሚደልብ (የሚደነድን) ሥጋ እና ሃሴት የሚያደርግ ነፍስ የትክክለኛ ሰብእና ባህሪያት አይደሉም እኮ! ትክክለኛው ሰብአዊ ባህሪ ለመከረኛው ወገን የሚገደውና ለዚህም እረፍቱን ሰውቶ የሚችለውን የሚያደርግ በመሆኑና ይህም የጤንነት እንጅ የጤና ጉድለት ፈፅሞ እንዳልሆነ በሚገባ እረዳለሁና የሃሳብ ልውውጦቻችንና የትችቶቻችን አስቸጋሪነት አይገርመኝም። ይህ ማለት ግን በእጅጉ ሊያሳዝነንና ሊያሳስበን አይገባም ማለት አይደለም። እንዲያ ከሆነማ ፍኖተ መፍትሄውን ፈልገን ማግኘት አይቻለንም።
8) በመጨረሻም “ተልእኮህ ሌላ …” ለተባለው ያለኝ ምላሽ መሠረታዊ የመረዳት ችሎታ ያለኝ የኦርቶዶክስ ተከታይ ስለመሆኔ መማልና መገዘት የሚያስፈልገኝ አይመስለኝም የሚል ነው። ይህ ተራ ተከታይነቴ ግን ትክክል ያልሆነውን በግልፅና በቀጥታ ትክክል አይደለም ለማለት የሚከለክለኝ ሊሆን አይገባም የሚል ፅዕኑ እምነት ያለኝ ተከታይ ነኝ ። ይህ ደግሞ ማንም የሚለግሰው ወይም የሚነፍገው ሳይሆን ፈጣሪ ራሱ በሰብአዊ ፍጡርነት የሰጠንና የሚሰጠን መብትም ነው።
ለማጠቃለል፦
የየራሳቸው ዓላማ ፣ተልእኮ፣ ዲሲፕሊን፣ አሠራር፣ ወዘተ እንደተጠበቀ ሆኖ ሃይማኖታዊ እምነትን ጨምሮ በማነኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሃሳብ ልውውጥ ስናካሂድ የሃሳቦቻችንን ወይም የመልእክቶቻችንን ይዘት (ለምንነት፣ እንዴትነት እና ከየት ወደ የትነት) ለመረዳትና በዚያው አረዳድ መሠረት የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሃሳቦቻችንን በምክንያታዊነት እያስደገፍን ለመግለፅ ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ካልሆነ መነሻችንም ሆነ መደምደሚያችን ጭፍን ፍረጃ፣ ግለሰባዊ ውረፋ (ዘለፋ)፣ እርግማንና ውግዘት፣ እኛን ፃድቃን ሌላውን ተኮናኝ ማድረግ ፣ ራሳችንን ባለ ሚዛናዊ ህሊና እና ሌላውን ሚዛኑ የተዛባበት አድርጎ ማሳየት፣ እኛን ባለ ጥሩ ህልመኞች እና ሌላውን እረፍት የሌለው ቅዠታም አድርጎ መሳል ፣ ወዘተ ነው የሚሆነው።
ከማሰቢያ አእምሮና ከማከናወኛ አካል ጋር በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር ምድራዊውና ሰማያዊው ህይወቱ የተሳካ እንዲሆን ለማስቻል የተመሠረተው ሃይማኖታዊ እምነት ከላይ በማሳያነት የጠቀስኳቸው ደምሳሳና ልፍስፍስ የሃሳብ አተረጓጎሞችና ፍረጃዎች ሰለባ የመሆኑ ጉዳይ ሊያሳስበን እና ጨርሶ ማስቀረት ባንችልም ለመቆጣጠር የምር ጥረት እንድናደርግ ሊያስገድደን ካልቻለ ከባድ ፈተና ላይመሆናችንን ተድተን የሚነጀንን ማድረግ ይኖርብናልና ልብ ያለው ልብ ይበል!!!