የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በኢትዮጵያ [በትግራይ] ተሰማ…!!

ባያድለን ነው እንጂ ይሄ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ሁሉ ኀዘን፤ የምድሪቱ ልቅሶ መሆን ነበረበት!!
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

“ኢትዮጵያ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው. . . ?!”

እንደ መግቢያ፤

“የኢትዮጵያ ሀገሬ ታጠቂ በገመድ፤
የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፤
ያም ልጅሽ ያም ልጅሽ፤
ያም ዘመድ ያም ዘመድ፤
ለማን ታድያለሽ … ለማንስ ይፈረድ?!

(የባህል ሙዚቃ ንግሥቷ ማሪቱ ለገሠ/እንደው ዘራፌዋ)

የኢትዮጵያና የኢትዮጵያን የታሪክና የሥልጣኔ እምብርት፤ የክርስትና እና የኢስላም ሃይማኖቶች (የርዕሰ አድባራት አክሱም ጽዮን እና የአልነጃሺ) መሠረት/መነሻ ምድር ኢትዮጵያ/አክሱም/ትግራይ፤

ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ጫፍ ተጠራርተው ብሔርና ጎሳ፤ ሃይማኖትና ቋንቋ ሳይለያቸው በአጥንታቸው ብዕርነት በደማቸው ቀለምነት የነጻነትን ክቡር መንፈስ ከፍ ባደረጉበት፤ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ሰንደቅ በተውለበለበባት፤ የኢትዮጵያዊነት የቃልኪዳን ውሉ በተቋጠረባት በዐድዋ/በትግራይ ምድር፤

በወንድማማች ጦርነት በአንድ ጀምበር ለወሬ ነጋሪ አንዱ እንኳን ሳይተርፉላት አምስቱም ልጆቿ/ሁሉም ማለቃቸውን ሰምታ ራስዋን ስላጠፋች፤ ኀዘን አቅሏን ስላሳታት የትግራይ/የኢትዮጵያ ምስኪን እናት ምን ምላሽ፤ ምንስ የማጽናኛ ቃል አለን…?!

በአማራ፣ በአፋር፣ በቤሻንጉል ጉሙዝ፣ በወለጋ… በሁሉም ኢትዮጵያ ምድር በጦርነት ነዲድ እየተለበለቡ በገፍና በግፍ ስላለቁትና እያለቁ ስላሉት የኢትዮጵያ ልጆች ምን እያልን፤ ምን እያሰብን ይሆን…?!

በቤተ መቅደሱ ደጃፍ ስለታረዱት ካህናት፣ ደማቸውን ውሻ ስለላሰው፣ በድናቸውን ለአውሬና ለአሞራ ሲሳይ ስለዳረግናቸው ወገኖቻችን፤ ስለተደፈሩ መነኮሳት፤ የሴትነታቸው ክብር በአደባባይ ስለተዋረደባቸው፣ ስለተጎሳቆለባቸው ምስኪን እናቶቻችና እህቶቻችን ምን ቃል፤ ምንስ አንደበት ይኖረን ይሆን…?!

የጦርነት ነጋሪት ስንጎስም፣ በወንድማማች ሕዝብ፤ በኢትዮጵያውያን መካከል የጥላቻን፤ የመለያየትን ዘር ስንዘራ የነበርን ነፍሰ-ገዳዮች/ቃኤላውያን ሆይ አሁን ገና የደም ግብራችን አልረካ ይሆን…?!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሽምግልናና ድርድር ብሎ ነገር የለም! ጦርነቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ስራ-አስፈጻሚ የሆነውን የአቢይ አህመድ አገዛዝንና ግብረ-አበሮቹን በማስወገድ ፍጻሜ ማግኘት አለበት!

የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በኢትዮጵያ [በትግራይ] ተሰማ…!!

እነዚህ ኃይለ-ቃላት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ጥቅሶች ሲሆኑ፤ በተለያዩ ጊዜያት የእግዚአብሔር ነቢያት ስለ እስራኤል፣ ስለ ኢየሩሳሌም/ስለጽዮን ውርደት፣ መከራና ሰቆቃ የተናገሯቸው ናቸው። ጥቅሶቹ የእናት ምድራችንን የኢትዮጵያን ኀዘን፤ የኢትዮጵያውያን እናቶችን ሰቆቃ/ታላቅ ስብራት የሚገልጽ መስሎ ስለተሰማኝ ነው- ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በመተካት አካፍላችሁ ዘንድ የወደድኹት።

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ [በትግራይ] ተሰማ፤ ራሔል [ኢትዮጵያ] ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን ፈጽሞ እንቢ አለች።”
(ትንቢተ ኤርምያስ ፴፩፤፲፭)።

“ድምፅ በኢትዮጵያ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ የትግራይ እናት ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትንም አልወደደችም።”

ኢትዮጵያ አለቀሰች፥ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የእናቶች ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአልና፤

የኢትዮጵያ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፤ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፤ ደናግላን ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ።

ወደ ዓመት በዓልም የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች [የአክሱም መንገዶች] አለቀሱ፤ በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል ካህናቶችዋም እየጮኹ ያለቅሳሉ፤ ደናግሎችዋም ተጨነቁ፤ እርስዋም በታላቅ ምሬት ውስጥ አለች።

በኢትዮጵያ ሴቶችን፥ በከተሞቿም ደናግልን አጐሰቈሉ፤ አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ በመቅደሱ የካህናት፣ በአደባባይም የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም።

ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ። ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ።

አቤቱ፥ ተጨንቅናል፥ አንጀታችም ታውኮብናልና፤ ተመልከት፤ ልባችን በውስጣችን ተገላበጠብን፤ በሜዳ ሰይፍ ልጆቻችንን አጠፋ በቤታችንም ሞት አለ።

ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን። ስለ ወገናችን ሴት ልጆች ቅጥቃጤ ዓይናችን የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይናችን ሳያቋርጥ ዝም ሳይሉ እንባን ያፈሳሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰሞነኛ ጉዳዮችን በወፍ በረር አንቀጾች ስንቃኛቸው - ከይሄይስ አእምሮ

የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል፤ ዓይናችን በእንባ ደከመች፥ አንጀታችንም ታወከ፤ ስለ ኢትዮጵያ ወገኖቼ ቅጥቃጤ ጉበታችን በምድር ላይ ተዘረገፈ።

ኢትዮጵያ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፤ የሚፈውስሽ ማን ነው?

ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፤ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፤ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል።

እንደ መውጫ፤

አንጋፋው ፖለቲከኛ፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ፣ አዛውንቱ ዶክተር ኃይሉ አርዓያ- በዛን ጊዜው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ/የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት በ1950 ዎቹ ስለኢትዮጵያ የቋጠሩት ስንኝ ለአሁኗ ኢትዮጵያም የሚስማማት ይመስለኛል። እንሆ ከዶ/ር ኃይሉ አርዓያ እንጉርጉሮ/ስንኞች፤

“… ይኸው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት፣
የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት…!!

(ሰቆቃው ኤርምያስ ምዕ. ፭)
———-
፲፯፤ አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ። ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ።

፲፰፤ ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል።

፲፱፤ አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።

፳፤ ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ?

፳፩፤ አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።

፳፪፤ ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቈጥተኸናል።

ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ሰላም ለምድራችን🕊🕊

4 Comments

  1. ወገኖች እግዚአብሄር መጽናናትን ይስጣችሁ፡፡ ይህ እንደሚመጣ እናውቅ ነበር ብዙ ጮህን ሰሚ አላገኘነም ለትግሬ ከኢትዮጵያ በላይ ምን ሊመጣለት ይችል ነበር? ከአማራስ የቀረበው ምን ነበር? ክፉዎች የትግሬን በትረ ስልጣን ያዙ በክፉ አእምሮዋቸው ክፉ ነገር አፍልቀው ማሰብ የማይችለውን አግተለተሉት፡፡ እናንተም ላይ ይህ ሃዘንና ሰቆቃ ተከትሎ መጣ፡፡ በእነዚህ ክፉ መሪዎች በጭፍን የታዘዙት ልጆቻችሁ ወንድሞቻቸውን ጠላት ናቸው ብለው አለ ርህራሄ ፈጇቸው፡፡ የሚያስለቅሰው አጥቶ ነው እንጅ ከእናንተ የመጡት አማራውን ፈጅተውታል ሃብት ንብረቱን የቻሉትን ዘርፈው ቀሪውን አውድመውታል የአማራም እናቶች በናንተ ልጆች ክፋት እያለቀሱ ነው ማን ተጠቀመ ማንም፡፡ ያለፈው አለፈ ካሁን በኋላ አናታችሁ ላይ ፊጥ ብለው የሚያስጨርሷችሁን እምቢ በሏቸው፡፡ ስብሃት ነጋ የት ነው ያለው? ሳሞራ የኑስ የት ነው ያለው ? ጌታቸው ረዳ የት ነው ያለው? ታደሰ ወረደ የት ነው ያለው? ሞንጆሪኖ የት ነው ያለችው?የትግራይ ወጣት ባብዛኛው ያለቀው እነ ደብረ ጽዮንን፤ስብሃት ነጋን ታደሰ ወረደን ሲጠብቅ ነው ከነሱ በፊት እኔን ያድርገኝ ብሎ ነው፡፡የመሪዎቻችሁ ልጆችስ የት ነው ያሉት? ከነሱ አንድ የሞተ አለ? ጎበዝ ከዚህ ሁሉ እልቂት በፊት መጠይቅ ይገባ ነበር፡፡ ሊጠብቃችሁ የሄደውን ስራዊትስ ማረድ ምን ይባላል? በታሪክስ እንዴት ልትታወሱ ነው? የኢትዮጵያ ባንዲራ እየተቃጠለ የቻይና ባንዲራ ሲውለበልብ እንዴት ፈቀዳችሁ? የኢትዮጵያን ባንዲራ ያጠኑት እኮ አጺ ዮሃንስ ነበሩ፡፡ ጥቂት እብዶች ሲያሳስቷችሁ ቀሪዎቹ ረጋ ብላችሁ ማሰብ ይገባ ነበር፡፡ ይህ የማይደበቅ ሊነገር የሚገባ ሃቅ ነው፡፡ አሁንም ጽናቱን ይስጣችሁ የልጅ ሞት በጣም ይጎዳል ይሄ ሁሉ ልጅ ለሞት ተሽቀዳድሞ ሲሄድ ወላጅ ሊከለክል በተገባ ነበር፡፡ አሁንም ደግመን የምንናገረው የመሪዎቻችሁ ልጆች አንዳቸውም አልሞቱም መሪዎቻችሁ የሰላም ሰዎች እየተባሉ ከአብይ መሃመድ ጋር ይሸላለሙ ነበር፡፡ ጻድቃንም ልጆቹን በፈረንጅ አገር ከማስተማሩም በላይ 900 ሚሊዮን ብር በአብይ ፈቃድ ከሃገር አሽሽቷል፡፡ ሳሞራ የኑስም ዛሬ 40 ሚሊዮን ብር በሚገምት ቤት ህጻን አግብቶ ይንፈላሰሳል ተጎጅው ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ነው፡፡ እነ ቴዎድሮስ የርእዮት ሚዲያ ባለቤት፤አሉላ ሰለሞን፤ስታሊን ምናምን የተባሉት ያዘኑ መስለው ወጣቱን ወደ ጥፋት መሩት እነሱም ስሙኒ ሰበሰቡበት እንጅ ለትግራይ ህዝብ ምንም አልጠቀሙትም፡፡ እንግዲህ ካለፈው ተምረን አቅል ገዝተን እንኑር የመጣው እብድ ሁሉ እንዲጋልባችሁ እድል አትስጡት ኢትዮጵያዊነትን አጥኑ ልባችሁ ወደ ውጭ ወደ ውጭ አይበል፡፡ ሰላም ሁኑ

  2. ሰው የሆነ ሰው የትግራይ እናቶችና አባቶችን እንባ እያየ የራሱን እንባ በቅርብም ሆነ በሩቅ የማያፈስ ይኖራል ብዬ አላምንም። የትግራይ ህዝብ ግፍና መከራ ማየት ከጀመረ ቢቆይም እጅጉን ብሶ ዛሬ ላለበት የጉስቁልና ማጥ ውስጥ የከተተው ወያኔ ባርነት ትግራይ ነው። 17 ዓመት ሙሉ ሲታገሉ ወደ 60 ሺህ ሰው አለቀብን ያሉን አሁን በሶስት ጊዜ ወረራው ከህዋላም ከፊትም እየተተኮሰበት የሞተው ቁጥር ወደ አንድ ሚሊዪን ይጠጋል ተብሎ ይገመታል። የሚያሳዝነው ያኔም ዛሬም ወደ ሞት የሚገፉን እኛ እናውቅላችሁሃለን የሚሉን የዘርና የጎሳ ሰካራም ፓለቲከኞች ሃዘን ተቀማጭ መሆናቸው ነው። መሞት የነበረባቸው እነርሱ ነበሩ። ግን ፍትህ በዚህ ዓለም ላይ የት አለና! የድሃ አደግ ልጆችን እያፈሱ ወስደው ያስጨረሱ አሁን እንባ መሳይ ነገር ሲያፈሱ ማየት ይዘገንናል።
    ለህልውና የተከፈለ ክቡር መስዋእትነት በሚል መፈክር በትግራይ በየሥፍራው መርዶ ማስረዳቱ በጎነት አለው። ሰው እርሙን ይዞ ቁጭ ከሚልና አንዴ ወደ ኤርትራ በምርኮ ሄደ፤ ሌላ ጊዜ በፌዴራሉ እስርቤት ይገኛሉ ወዘተ እያሉ የወላጅና ዘመድን ልብ ከማንጠልጠል እንቅጩን ተናገሮ ማረፉ ጥሩ ነው። በዝምባባና በትግራይ ባንዲራ ያሸበረቀው የግጥምና የዘፈን ጋጋታ ግን አላስፈላጊ ነው። ያኔም ዛሬም እየዘፈኑና እየሸለሉ አይደል እንዴ ሰው እንደ እሳት ራት ገብቶ ያለቀው። ፓለቲከኞች እንደ ቦይ ውሃ ናቸው። ያሰቡት ሳይሳካ ሲቀር ሃሳባቸውን ቅይረው ወደ ሌላ አቅጣጫ ይፈሳሉ። ተው ሲባሉ አልሰማ ብለው የእናቶችን እንባ ረግጠው የጫሩት እሳት አሁን እንሆ ትርፍ አልባ የእልፍ ሰዎችን ህይወት አስገብሮ ለነጻነት ነው ይሉናል። ውሸት ነው። ነጻነት ወያኔ እያለ በትግራይ ውስጥ አይኖርም። የሞት ቁማር መጫወት ወያኔዎች ዛሬ የተካኑበት ሳይሆን ድሮ ገና በበረሃ እያሉ የተቃመሱት የግፍ ጽዋ ነው። ስንቶች በረሃ ቀርተዋል? ስንቶች በሱዳን መሬት መጠለያ ፍለጋ ሄደው ረግፈዋል? ግን ለጥቁር ህዝብ ሞትና እርዛት ማን ገዶት። አልቃሽም አስለቃሽም ሁሉም ግን በጊዜ ሂደት አፈር ይመለስባቸዋል። ነጻነት የናፈቀው የትግራይ ህዝብም ራሱ በራሱ በመረጣቸው አመራሮች ቢመራ ወደፊት እንዲህ ያለ እልቂት እንዳይኖር መንገድ ከፋች ይሆናል። ያ ፈሪሃ እግዚአብሄር የተላበሰው አዛኝና ሃገር ወዳድ የትግራይ ህዝብ በእነዚህ አረመኔዎች ይኸው ከ50 ዓመት በላይ መከራውን ያያል። በትግራይ ነጻነት እንዲኖር ከተፈለገ የወያኔ መሪዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ያ እስካልሆነ ድረስ ዝም ብሎ ውሃ ወቀጣ ነው። የሞተውም ይረሳል፤ ዘፈኑና ፉከራውም በሌላ ይተካና እንደገና ከኤርትራና ከአጎራባች ስፍራዎች ጋር ወይም ከኦሮሞው መንግስት ጋር ዳግም ፊልሚያ ሊፈጠር ይችላል። ለመሆኑ የነጻነት መስፈሪያው ምንድን ነው? የመገዳደልና የሞት ፓለቲካ ለማንም አይጠቅምም። ግን ሰው ሆኖ የሰውን ዋይታና ለቅሶ በዝምታ የሚያይ በድን እንጂ እስትንፋስ ያለው አይደለም። በዚህም በዚያም እያላከክን ዝንተ አለም መገዳደላችን መፍትሄ እስካላገኘ ድረስ በትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰው ሃዘን መላው የሃገሪቱን ክፍል ማዳረሱ አይቀሬ ነው። ፈጣሪ ለትግራይ እናቶችና አባቶች ባጠቃላይ በሃዘን ለተመታው ህዝብ መጽናናትን ይስጥ። ወያኔን ከትግራይ ህዝብ ጀርባ ላይ ያውርድ። በቃኝ!

  3. አረ ኮመንቶችን አታንሱ ሰው ይማርበት ሀሳብ አይገደብበት ያልሆነው አልተጻፈም በኛ ልክ አስቡ መልካም አይሆንም።

  4. ያሳዝናል ይህ እንዳይሆን አስቀድመው የሚያዩ ወገኖች ተው ብለው ነበር ማን ይስማ? ይኸው ከአንድ ቤት 5 ልጅ ተንጋግቶ ለሞት መጣደፍ ምን ይባላል? ዛሬ የሰየ አብረሃ የጻድቃን ገ/ተንሳይ፤የደብረ ጽዮንና የሌሎች ጉምቱ ህወአቶች ልጆቻቸው አልሞቱም እነሱም ከአብይ ጋር የሰላም ሰዎች ተብለው ሽልማት በሽልማት ሁነዋል፡፡ አንድ ቤት ውስጥ እንኳን አንዱ ሲያጠፋ አንዱ ተው ይላል ድፍን ትግሬ ከቤተክርስቲያኑ ጋር ሲያብድ ማን ያስታርቅ፡፡ የቀበጡ እለት ሞት አይገኝም ይባላል፡፡ አሁን ከዚህ ትምህርት ወስዶ በፍቅር መኖር ያስፈልጋል ከተቻላችሁ፡፡ የአማራው ሟች ክብር ተሰጥቶት አልተለቀሰለትም እንጅ ረግፏል አሁንም እየረገፈ ነው ንብረቱ ወድሟል በትግሬዎች ተዘርፏል፡፡ የትግሬን ልጆች ያስጨረሱ ዛሬ ገንዘብ አሽሽተው ወደ ባህር ማዶ ከወንጀላቸውና ከደም ገንዘብ ጋር ይኖራሉ ህሊናቸው ይከሳቸዋል አይባል ህሊና የላቸውም፡፡ የትግሬን ወጣት አስፈጅተው አረጋዊ በርሄ፤አርከበ እቁባይ፤ስብሃት ነጋ፤ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፤ጌታቸው ረዳ፤ጻድቃን ገ/ተንሳይ፤ምናምን ወረደ፤ቴዎድሮስ ርዕዮት፤ስታሊን ገ/ስላሴ/አሉላ ሰለሞንና መሰል ወንጀለኞች የትግሬን ወጣት በተለያየ መንገድ አስፈጅተው ተንደላቅቀው ሲኖሩ እነዚህ እናቶች ግን ልጆቻቸውን እስከ ወዲያኛው አጥተዋል፡፡ ለማንኛውም ማስተዋልን ይስጠን

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share