ቅጥረኛ የአብይ አህመድ ጄነራሎች ለሚያፈሱት የአማራና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ደም የክፍያቸው መጠን ጨምሯል፣ – አንዳርጋቸው ጽጌ

የሃገር መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችን ታማኝነት ለመግዛት ሰፋፊ የከተማ መሬት ማደል የተጀመረው በወያኔ ዘመን ነው። በወያኔ ዘመን የሀገር መከላካያ የህዝብና የሃገር ደጀን መሆኑ ቀርቶ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የአንድ ግለሰብ ጉዳይ አስፈጻሚ እንዲሆን የተደረገው የኢትዮጵያ ህዝብ አንጡራ ሃብት የሆነውን የከተማ መሬት ገዥዎቹ ለሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች እንዳሻቸው እንዲሸነሸን እንዲታደል ማድረግ በመቻላቸው ነበር።

በዚህ የመሬት ስጦታ የተነሳ፣ የወያኔ ዘመን ከፈተኛ የጦር መኮንኖች፣ በአንድ ጀንበር ሁሉም ከተራ ሰውነት ወደ ሚሊየነርነት ተቀይረዋል። የኢህአዴግ የቀድሞ መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች ስለነበሩ በብዛት ተጠቃሚ መሆናቸው የሚገርም አልነበረም።

ከትህነግ አባልነት የተባረሩት የትግራይ ከፍተኛ መኮንኖች፣ እነ አበበ ተክለሃይማኖት (ጀቤ) ጻድቃን እንዲሁም ሌሎችም ከህወሃት ጋር ተጣልተው በመጨረሻ ከሰራዊቱ የተባረሩ የሌሎች ብሄር ከፍተኛ መኮንኖች ሳይቀሩ የዚህ የመሬት እደላ ተጠቃሚዎች መሆን ችለው ነበር።

አንዳንዶቹ መሬቱን በጊዜ ሸጠው ወደ ሌላ የንግድ ስራ ሲሰማሩ፣ አንዳዶቹ መሬቱን በመጠቀም ዛሬም በአዲስ አበባ ከተማ ተገትረው የቆሙት ትልልቅ ህንጻዎች ባላቤቶች ሆነዋል። ወያኔዎች መሬት እንዲሰጥ ያደረጉት ለሁሉም ከፍተኛ መኮንኖች እኩል ስፋት ያለው 500 ካሬ ሜትር ብቻ ነበር። እስካሁን መሬታቸው ሳይሸጡ በተሰጣቸው መሬት ላይ ቪላ ቤት ሰርተው እያከራዩ የሚኖሩ የወያኔ ዘመን ከፍተኛ መኮንኖች የተሰጣቸው የከተማ ቦታ በመሃል አዲስ አበባ በመሆኑ ዛሬ እንሽጠው ቢሉ ከ80 ሚሊዮን እስከ 100 ሚሊዮን ብር ያወጣላቸዋል። ይህ ሃቅ መሬት በማደል አንድ ግለሰብ በአንድ ጀምበር እንዴት ሃብታም ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው።

በወያኔ ጊዜ ግን የነበረው የመሬት እደላ አሁን እንደምናየው የአብይ አህመድ ዘመን ጉድ የሚያሰኝ አልነበረም። የአሁኑን ዘመን ጉደኛ ያደረገው የመሬት እደላው አንዱን መኮንን ከሌላው በመጠን ያበላለጠ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአንድ መኮንን የተሰጠው የመሬት ስፋት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታላቅ አገር አቀፍ የማኅበረ ቅዱሳን አጋርነት መረሃግብር እሁድ ጥቅምት 9 ቀን 2007 ዓም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል

በሚቀጥለው ሰነድ እንደምናየው የአብይ ሰራዊት ከፍተኛ ጀነራሎች የሃገሪቱን የደሃ ልጆች እርስበርስ እያጨፋጨፉ፣ ንጹሃንን በድሮን፣ በሮኬት፣ በመድፍና በሞርታር እየፈጁ፣ ከ3500 ካሬ ሜትር አንስቶ እስከ 800 ካሬ ሜትር የሚደርስ የቆዳ ስፋት ያለው የከተማ መሬት ታድሏቸዋል። ብርሃኑ ጁላ ፊልድ ማርሻል ስለሆነ ይመስላል፣ 3500 ካሬ ሜትር ሁለት ቦታ ተከፍሎ፣ የተቀሩት አራት ሙሉ ጄነራሎች 2000 ካሬ ሜትር እያንዳንዳቸው፣ 17 ሌ/ጀነራሎች እያንዳንዳቸው 1500 ካሬ፣ 31 ሜጀር ጄነራሎች (850 ካሬ ሜትር መሬት ከተሰጠው ከኢተፋ ራጋ በስተቀር) እያንዳንዳቸው 1000 ካሬ ሜትር፣ 55 ብርጋዴር ጄነራሎች (650 ካሬ ሜትር መሬት ከተሰጠው ከከማል አቢሶ በስተቀር) እያንዳንዳቸው 800 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተሰጥቷቸዋል።

ከእነዚህ መሬት ከታደላቸው ጀነራሎች ውስጥ አስቀድሞ በወያኔ ዘመን መሬት ተስጥቷቸው የሸጡ፣ ቤት ሰርተው የሚያከራዩ፣ ህንጻ የገነቡ እንደእነ አበባው፣ አለም እሸት፣ ባጫ እና ሌሎችም ጄነራሎች ይገኙበታል። አሁን አዲስ አበባ ውስጥ በሚታየው የመሬት ዋጋ ሲሰላ ብርሃኑ ጁላ በአብይ አህመድ ቅጭን ትእዛዝ በአንድ ጀንበር የ350 ሚሊዮን ብር ጌታ ሲሆን፣ ሙሉ ጄነራሎች መሬታቸውን ቢሸጡ እያንዳንዳቸው የ200 ሚሊዮን ብር ጌቶች መሆን ይችላሉ። ደሃዎቹ ጄነራሎች 800 ካሬ ሜትር መሬታቸውን ሸጠው በትንሹ የ80 ሚሊዮን ብሮች ባላቤቶች መሆን ይችላሉ።

ህዝብ ከወያኔ ጋር ያደረገው ትግል ዘረፋን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም እንጂ አንድን ዘራፊ አስወግዶ በከፋ ሌላ ዘራፊ ለመተካት አልነበረም። የታሪክ ምጸት ሆኖ በመሬት ዘረፋ፣ የወያኔ ዘመን ከአብይ ዘመን ተሽሎ ተገኝቷል። የአብይ አገዛዝ ከቀድሞ ግፈኛ ስርአቶች ጋር ሲነጻጸር፣ በግድያውም፣ በመፈናቀሉም በዘረፋውም ሬኮርድ እየሰበረ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሲድኒ ኢትዮጵያዊያን የተሳካ የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ ( ከአቢይ አፈወርቅ )

ትልቁ ቁም ነገር፣ በሃገሪቱ ለሚያፈሱት የደሃ ልጅ ደም የጄነራሎች ክፍያ ምን ያህል እንደሆነ ህዝብ እንዲያውቅ ማድረግ ነው።

በእነዚህ ጄነራሎች ትእዛዝ ወንድምን እህቱን እየገደለ፣ ራሱም እንደቅጠል እየረገፈ ያለው ሌላው የሰራዊቱ አባል አለቆቹ የሰበስቡትን የደም ግብር አውቆ፣ እነዚህን ደም መጣጭ ጄነራሎችን በቃ እንዲላቸው ነው። ለነጻነቱ ከሚዋደቀው ህዝብ ጎን እንዲቆም ለማሳሰብ ነው።

ድል ለአማራ ህዝብ !

ድል በግፈኞች ላይ በአንድነት ተነስቶ ከአማራ ህዝብ ጎን ለሚሰለፈው የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ !

ዝርዝሩን https://t.me/+UNLX8ZQKVJw0Y2Fk ያንብቡ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share