September 7, 2023
28 mins read

የኢትዮጵያ መንግስት ከአማራ ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት ለምን ፈለገ?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)

አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ አመታት ከረሃብ፣ ከጦርነት፣ ከመፈናቀልና ከፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች ተገላግላ እፎይ ብላ የኖረችባቸው አጋጣሚዎች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ሆኖም ኢትዮጵያ እንዳለፉት አምስት አመታት መሉ በመሉ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የገባችበትና ህልውናዋ እራሱ አደጋ ውስጥ የገባበት ግዜ የለም። የህወሓት አገዛዝ በህዝባዊ ትግል ከሥልጣን ተባርሮ ጠሚ አቢይ አህመድ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ በኋላ ኢትዮጵያን እንደ ደም መጣጭ ተባይ ተጣብተዋት አልላቀቅ ያሏት ብዙ ችግሮች አሉ። ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ የመንግስት ደካማነትና ከህግ በላይ መሆን፣የኤኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች፣የሰላምና መረጋጋት አለመኖር፣ህገወጥነት፣ ብሔር ተኮር ግዲያ፣የብሔር ግጭትና የርስ በርስ ጦርነት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ዕለተ ማክሰኞ ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ቀን ከሱ በፊት ከነበሩትና ከሱ በኋላ ከመጡት ዕለተ ማክሰኞዎች የሚለየው ምንም ነገር የለም። የትግራይን ህዝብ ለአመታት ሲጠብቅ፣ እርሻውን ሲያርስለት፣ መንገድ ሲሰራለትና በተቸገረ ግዜ ሁሉ ሲደርስለት የነበረው የሰሜን ዕዝ ሰራዊት ማክሰኞ ጥቅምት ሃያ አራትን ያሳለፈው ለአመታት ሲያደርግ እንደነበረው የትግራይን ህዝብ ሲረዳ፣ ሲንከባከብና የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ሲያስጠብቅ ነው። ማክሰኞ ጥቅምት 24 ሌሊት ግን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሁሌም ስትታወስ የምትኖር የደምና የክህደት ሌሊት ናት። ጥቅምት 24 ማክሰኞ ወደ ረቡዕ መሸጋገሪያ ሌሊት ላይ ነበር ሰሜን ዕዝ  “የኔ ናቸው” በሚላቸው በራሱ ልጆች ክህደት የተፈጸመበትና በተኛበት እንደ ፋሲካ በግ የታረደው። የትግራይን፣የአፋርንና የአማራን ክልሎች ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት ጦርነት፣መፈናቀል፣ ረሃብ፣ ስደት፣ ሞትና መከራ ውስጥ ይዞ የገባው ይህ ማክሰኞ ጥቅምት 24 ሌሊት የህወሓት ኃይሎች የፈጸሙት ክህደትና ጭካኔ ነው።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት ከህወሓት ጋር ያደረገውና 2 አመት የፈጀው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ዕልባት ያገኘው ዛሬ “የፕሪቶሪያው ስምምነት” እየተባለ በሚጠራው ስምምነት ነው። የዛሬ አመት ጥቅምት ወር ላይ የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት አማጽያን ፕሪቶሪያ ላይ የደረሱት የሰላም ስምምነት 15 አንቀጾች አሉት።-ከ15ቱ አንቀጾች በተለይ በዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ እምነት ከዋና ዋናዎቹ አምስት አንቀጾች ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ተሽቀዳድሞ ተግባራዊ  ያደረገው “የኢትዮጵያ መንግስት ህወሓት የሽብርተኝነት ፍረጃው እንዲነሳለት ያደርጋል” የሚለውን አንቀፅ ብቻ ነው። የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ ይፈታሉ፣ በተለይ ከባድ መሳሪያቸውን የማስፈታቱ ስራ ቅድሚያ ይሰጠዋል የሚለው አንቀፅ ሙሉ በሙሉ ተጥሷል፣ የህወሓት ሰራዊት ትጥቁን ፈትቶ ሰላማዊ ህይወት የሚኖርበት መንገድ ይፈለግለታል የሚለው አንቀፅ ሙሉ በሙሉ ተጥሷል፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ መካከያ ሰራዊት ብቻ ነው የሚኖረው የሚለው አንቀፅ ተጥሷል። የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ተወያይተው ትግራይ ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ያቋቁማሉ የሚለው አንቀፅም ተጥሷል። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ትግራይ ውስጥ የሽግግር መንግስት ተቋቁሟል የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል፣ ነገር ግን ትግራይ ውስጥ የተቋቋመው የሽግግር መንግስት በ”ሃላላ ኬላ” ስምምነት መሰረት ነው እንጂ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት አይደለም። ባጠቃላይ ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ሌሊት ላይ የህወሓት ኃይሎች በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸሙትን አይነት ክህደት የኢትዮጵያ መንግስት ሃላላ ኬላ ውስጥ ከህወሓት መሪዎች ጋር ተሰብስቦ በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ ደገመው። ዛሬ አማራ ክልል ውስጥ ለሚታየው ፍጹም አላስፈላጊ የሆነ የእርስ በርስ ጦርነት አንዱ ምክንያት የሃላላ ኬላ ክህደት ነው!

ባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በነጋ በጠባ እንቆቅልሽ እየተባለ “ምን አውቅልሽ” የሚል አካል ያልተገኘለት ኩነት ቢኖር ኦሮሚያ ውስጥ በተለይ ወለጋ ውስጥ ኦነግ-ሸኔ የሚባለው ሽብርተኛ ቡድን የአማራ ተወላጆችን በነጋ በጠባ ያለምንም መከልከል የመግደሉ ጉዳይ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2013 ዓ.ም ሐምሌ ወር የህወሓት ኃይሎች “ሂሳብ እናወራርዳለን” ብለው እየዛቱ መጥተው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱትም አማራ ክልል ውስጥ ነው። የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ይህንን የሚለው ከማህበራዊ ሚድያ ባገኘው መረጃ አይደለም። ወራሪው የህወሓት ጦር ከደሴና ኮምቦልቻ ከተባረረ በኋላ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት ውስጥ ደብረሲናን፣ሸዋ ሮቢትን፣ደሴን፣ጢጣን፣ኮምቦልቻን፣ ባቲን፣ሚሌን፣የካሳጊታ አካባቢዎችን፣ጭፍራን እና ሰመራን እየተዘዋወረ ከጎበኘና የህወሓት ኃይሎች ጥቃት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን ካናገረ በኋላ ባገኘው የመጀመሪያ መረጃ መሰረት ነው። የሚገርመው የህወሓት መሪዎች ጦርነቱ ከቆመ ከአስር ወር በኋላ ዛሬም ወልቃይትና ራያ የኛ ነውና እናስመልሳለን በሚል ከፍተኛ የጦር ዝግጅት የሚያደርጉት ከአማራ ጋር ለመዋጋት ነው።

የኦሮሞ ኃይሎች በሽመልስ አብዲሳ አጋፋሪነት ሸገር ከተማን ለመመስረት ባደረጉት የቤት ማፍረስ ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ የተጎዳው አማራው ነው። አማራ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይ ወለጋ ውስጥ ባለፉት አምስት አመታት በግፍ ተገድሏል። በተለይ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር አካባቢ ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆች ወለጋ ውስጥ በግፍ ተጨፍጭፈው ዜናው የአለም አቀፍ የዜና ተቋሞችን ትኩረት በሳበበት ቀን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ትኩረት ሰጥቶ ለህዝብ ያሳየው ጠሚ አቢይ አህመድ ችግኝ ሲተክሉ ነው። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የተከበሩ ዶር ደሳለኝ ጫኔ ሟቾችን በብሔራዊ ሀዘን እናስባቸው ብለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሃሳብ ሲያቀርቡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የ200 ሰላማዊ ዜጎችን በግፍ መጨፍጨፍ ከመጤፍ አልቆጠሩቱም፣እንዲያውም በዕለቱ ለዶር ደሳለኝ ጫኔ የሰጡት መልስና መልሱን ሲሰጡ የነበራቸው የሰውነት ቋንቋ ሰውየው የርህራሄ ጠብታ የሌለባቸውና ምን ያክል የህግ አስፈጻሚው አካል ተላላኪ እንደሆኑ ነው ያሳበቀባቸው!

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከቆመ በኋላ ከትግራይ ልህቃን አፍ በየቀኑ የሚወጣው ቃል ወልቃይት ጠገዴን አናስመልሳለን የሚል ቃል ነው። ጌታቸው ረዳ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የትግራይን ክልል ችግር ለመፍታት ከሄደበት መንገድ ይልቅ አገር ቤትና ውጭ አገር ላለው የትግራይ ማህበረሰብ ትግራይ ምን ያክል የታጠቀ ሰራዊት እንዳላትና ወልቃይት ጠገዴን ለማስመለስ በዝግጅት ላይ እንዳሉ ለመናገር የሄደበት መንገድ እጅግ በጣም ይበልጣል። እስካፍንጫቸው የታጠቁ የህወሓት ኃይሎች ወልቃይት ጠገዴን ለማስመለስ አሁንም ከፍተኛ ስልጠና እና የጦር ልምምድ እያካሄዱ እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። በመጨረሻም ከሰሞኑ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶር አብርሃም በላይ የወልቃይት ጠገዴ ተፈናቃዮችና ወልቃይት ጠገዴ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ይመለሳሉ በማለት በ1928 ዓ.ም. የሮማው ጳጳስ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን እንዲወር የሰጡትን አይነት ቡራኬ የመከላከያ ሚኒስትሩም ወልቃይት ጠገዴን ወደ ትግራይ ለማስመለስ ምንም አይነት ስራ መሰራት አለበት የሚል አይነት ቡራኬ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ የክልል ልዩ ኃይል የሚባል ስብስብ አያስፈልግም የሚል ህግና መመሪያ አውጥቶ ህጉን ተግራባዊ ማድረግ ጀምሯል። የክልል ልዩ ኃይል መኖር የለበትም የሚለውን ሃሳብ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ከማንም ሰው በላይ ይደግፋል፣ ይህንን ሃሳብ ባለፉት 20 አመታት በከፍተኛ ደረጃ አራምዷል። ነገር ግን የክልል ልዩ ኃይሎች መፍረስ አለባቸው ብሎ ህግና መመሪያ ማውጣትና ህግና መመሪያውን ተግራባራዊ ማድረግ በጣም የተለያዩ ስራዎች ናቸው። የኢትዮጵያ መንግስት ያልተረዳው ይህንን ቁልፍ ሃሳብ ነው። ግን በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን ሃሳብ አልተረዳውም ወይስ ሌላ ድብቅ አላማ አለው?

ከቅርብና ከሩቅ ከፍተኛ ርብርብ ባይደረግና ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎ አከርካሪውን ባይመታ ኖሮ እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለውና የፌዴራሉን መንግስት ጭምር ማንገዳገድ የቻለ የታጠቀ ኃይል ያለው የትግራይ ክልል ነው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለፌዴራሉ መንግስት መሳሪያ መስጠት የቻለና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የታጠቀ ልዩ ኃይል ያለው ኦሮሚያ ክልል ነው። የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሃላላ ኬላ ውኃ በላው እንጂ የትግራይ ልዩ ኃይሎች በአለም አቀፍ ደረጃም ድርድር ተደርጎ መሳሪያቸውን እንዲፈቱ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ታዲያ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነና እስካፍንጫው የታጠቀ ልዩ ኃይል ያላቸው እነዚህ ሁለት ክልሎች እያሉ የክልል ልዩ ኃይሎች ትጥቅ ይፍቱ የሚል ህግና መመሪያ ሲወጣ መመሪያው የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ መጀመሪያ አማራ ክልል ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን የተፈለገው ለምንድነው? የአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት የለባቸውም እያልኩ አይደለም። የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ትልቁ ጥያቄ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተጠቀሱት የኢትዮጵያ መንግስት በማድረግም ባለማድረግም የፈጠራቸው ውስብስብ ችግሮች እያሉ፣አማራ በየቦታው ያለምንም ከልካይና ጠባቂ እየተገደልኩ ነውና እራሴን መከላከል አለብኝ የሚል እምነት ባደረበት ግዜና፣ የአማራ ህዝብ ከዚህ በፊት ወደ ክልሌ መጥቶ ከፍተኛ በደል የፈጸመብኝ ኃይል አሁንም በህልውናዬ ላይ እየመጣ ነው ብሎ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ በገባባት ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግስት የአማራን ልዩ ኃይልና ፋኖ ትጥቅ ለማስፈታት እሽቅድምድም ውስጥ የገባው ለምንድነው የሚል ነው። የፕሪቶሪያውን ስምምነት ጠጋ ብለን በአንክሮ ካየነው፣ አገር ለማፍረስ ቆርጠው የተነሱትን የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት የትግራይን ክልል የጸጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት ይላልኮ፣ ታድያ ለምንድነው የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖን ትጥቅ የማስፈታቱ ዘመቻ የአማራ ክልል ያለበትን የህልውና ስጋት ከግምት ውስጥ ያላስገባው?

ደግሜ ደጋግሜ መናገር እፈልጋለሁ፣ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከአማራ ኃይሎች ጋር የጀመረው አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ጦርነት የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጠይነት አደጋ ላይ የሚጥል አደገኛ ጦርነት ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት በጦር መሳሪያ፣በዋና ዋና የሜዲያ አውታሮቹና በማህበራዊ ሜዲያ በአማራ ክልል ውስጥ የከፈተውን ዘመቻ በአስቸኳይ አቁሞ ለከሃዲዎቹና አገር ለመበትን ቆርጠው ለተነሱት ህወሓትና ኦነግ – ሸኔ በአለም አቀፍ ደረጃ ያደረገውን የድርድር ግብዣ፣ ከፌዴራል ኃይሎች ጋር ተሰልፈው አገር ላዳኑ የአማራ ኃይሎችም መስጠት አለበት። የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን የማያደርግበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። ስለዚህ የአገር መከላከያ ሰራዊትን በአገራዊ ኃይል ላይ አዝምቼ ኢትዮጵያን እገነባለሁ እያለ የሚነግረን የኢትዮጵያ መንግስት፣ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ ተዋግተን ኢትዮጵያን ማፍረስ እንጂ መገንባት እንደማንችል ተረድቶ ይህንን የጀመረውን ጭፍን የጨለማ ጉዞ በአስቸኳይ ማቆም አለበት።

በቅርቡ አንድ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣን በአሸንዳ በዓል አከባበር ላይ ተገኝቶ ባሰማው ንግግር “የትግራይና የኦሮሞ ህዝብ በጋራ ሆኖ የሚታገልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” የሚል አጅግ በጣም አሳፋሪ ንግግር ተናግሯል። ይህ ሰው የኦሮሞና የትግራይ ልህቃን ከሁለቱ ብሔሮች ውጭ ላለው ከ70 ሚሊዮን በላይ ለሆነው ኢትዮጵያዊ ምን ያክል ንቀት እንዳላቸው በግልጽ በአደባባይ መስክሯል። በእርግጥም እነዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ለብሔር ፖለቲካ ህጋዊ ቅርጽና ይዘት የሰጠውን  ወልጋዳ ህገመንግስት አብረው የጻፉ የትግራይና የኦሮሞ ልህቃን “ብሔር” የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረት ሆኖ እንዲቀጥል የማያደርጉት ምንም ነገር የለም።

ብዙዎቻችን የዚህን  ሳያስበው እውነቱን የነገረንን ሰው ንግግር ንቀን እናልፍ ይሆናል፣ ነገር ግን የታሪክ ባለጸጋዋ መንደር ሃላላ ኬላ ብዙ ትምህርት አስተምራናለችና የኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት የሚጠቅመንና ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵዊነት ውጭ ሌላ ምንም መጠጊያ የሌለን ኢትዮጵያዊያን ይህንን በእኛነታችን ላይ ለመዝመት ቆርጦ የተነሳ አገር አፍራሽ ህብረት ማስቆም አለብን። በረጅም ግዜ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸው የሚታወቁት የትግራይና የኦሮሞ ልህቃን አማራውን ቢቻል ቁጥሩን በግማሽ ለመቀነስ አለዚያም አጎንብሶ እነሱን እየተለማመጠ እንዲኖር ለማድረግ መተባበራቸውና ጥምረት መፍጠራቸው ሊገርመን አይገባም። ወደኋላ ዞር ብለን የቅርብ ግዜውንና የሩቁን ታሪካችንን ብንመለከት፣ ኢትዮጵያን ለመውረር የመጡ ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዢዎችም አልሳካ አላቸው እንጂ፣ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ መጀመሪያ አማራውን መከፋፈል፣ ማዳከምና አቅመ ቢስ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አምነው ምሁራኖቻቸው ስትራቴጂና ዕቅድ ነድፈዋል፣የጦር አበጋዞቻቸውም ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።

ባለፉት 30 አመታት አገራዊ ማንነት (ኢትዮጵያዊነት) ደብዝዞ የብሔር ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ ከፍተኛ የፖለቲካ ስራ በመሰራቱ ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ተዳክሟል፣ ኢትዮጵያ ሲባል የሚያንገፈግፋቸው ኃይሎች የፖለቲካውን መድረክ ተቆጣጥረዋል፣ከሁሉም በላይ ደሞ አማራውን ካጠፋን ወይም ካዳከምን “ኢትዮጵያ” ብሎ የሚነሳ ሌላ ኃይል አይኖርም ብለው ያሰቡ የኦሮሞና የትግራይ ጽንፈኛ ኃይሎች የአላማ አንድነት መፍጠራቸው ብቻ ሳይሆን አማራ ክልል ውስጥ ጦርነት ከፍተዋል። የትግራይና የኦሮሞ ልህቃን ትብብር አላማው ከተቻለ የተዳከመች፣ የእነሱን ጥቅም የምታስጠብቅና በነሱ የበላይነት የምትመራ ኢትዮጵያ መፍጠር ነው፣ ይህ ካልተቻለ ደሞ የየራሳቸውን አገር መፍጠር ነው። ይህ ያልተቀደሰ የኦሮሞና የትግራይ ልህቃን ትብብር የሚያስፈራው አማራውን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ከምትባል አገር ውጭ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ የሚገባውን የአፋርን፣ የሱማሌን፣የጋምቤላንና የደቡብ ኢትዮጵያን ህዝብ ጭምር ነው።

ባለፉት 5 አመታት ጎራ ለይተን ተወነጃጅለናል፣ተሰዳድበናል፣አንዳችን ሌላውን ተለጣፊ፣ ከሃዲ፣ባንዳ ተባብለናል። አንዳንዶቻችን በፍጹም ለአገር የማናስብ ሌሎቻችን ደሞ የኢትዮጵያ ብቸኛ ጠበቃ ሆነን እራሳችንን አይተናል። እነዚህ አንዳንዶቻችን ደጋፊዎች ሌሎቻችን ተቃዋሚዎች መስለን የታየንባቸውና ያደረግናቸውና ያላደረግናቸው ነገሮች ማናችንንም የተሻለ ቦታ ላይ አላስቀመጡንም፣ይልቁንም እኛ ስንኗቀርና ስንባላ አይናችን እያየ አገራችን የመበታተን አደጋ ውስጥ ገብታለች። የጠሚ አቢይን መንግስት ደግፈንም ተቃውመንም ታግለናል፣ግን ማናችንም አገራችንን ዛሬ ከገባችበት እጅግ በጣም አደገኛ ሁኔታ ማዳን አልቻልንም!  ይህ ፍጹም አሌ ልንለው የማንችለው ሃቅ የሚነግረን አንድ ትልቅ ጉዳይ አለ፣ እሱም እኛ ኢትዮጵያዊያን እስካሁን በመጣንበት መንገድ መቀጠል እንደሌለብንና አካሄዳችንን፣የትግል ስልታችንን፣ ስትራቴጂያችንን እና በተለይ የኢትዮጵያን ችግሮች የምንመለከትበትን መንገድና ለችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት የምንሄድበትን መንገድ ፈትሸን መቀየር እንዳለብን ነው።

ኢትዮጵያ እንደ አገር ብትቀጥልም ባትቀጥልም ይብዛም ይነስ አማራ በቆዳ ስፋቱ፣በህዝብ ቁጥሩና በተፈጥሮ  ኃብቱ ትልቅ ህዝብ ነውና ካለ ኢትዮጵያ መኖር ይችላል። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ግን ካለ አማራ መኖር እንደማትችል ኢትዮጵያ ብቸኛ ውሎ መግቢያችን እና ማደሪያ ቤታችን የሆነች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ኢትዮጵያና አማራ ተለያይተው የሚኖሩበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ዛሬ ነገ ሳንል አሁኑኑ ማድረግ ያለብንን ሁሉ ማድረግ መጀመር አለብን። ኢትዮጵያንና አማራን ከፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ ኃይሎች ማዳን የምንችለው ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። ትናንት እና ከትናንት ወዲያ የታገልናቸው ኃይሎች ባህሪይ፣የፖለቲካ ፍላጎትና አላማ  ዛሬ ከምንታገላቸው ኃይሎች ባህሪይ፣የፖለቲካ ፍላጎትና አላማ ይለያልና፣ እኛም ትናንት እና ከትናንት ወዲያ የታገልንበት መንገድና የተከተልነው የትግል ስትራቴጂ ዛሬ መከተል ካለብን የትግል ስትራቲጂና ስልት የተለየ መሆን አለበት። ኢትዮጵያዊያን እባካችሁ የትናንቱን ከስህተታችን ለመማር ብቻ እንጂ ለመሰዳደብ፣ እርስ በርስ ለመካሰስና ለመወነጃጀል አናድርገው። የምናቅደው ዕቅድ፣ የምንሰራው ስራ፣ዘመቻችን፣ውሏችንን፣ አዳራችን እና ፀሎታችን ሁሉ ኢትዮጵያን ከፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ለማዳን ይሁን! ለክሱና ለመወቃቀሱ ኢትዮጵያችን ከዳነች በኋላ ብዙ ግዜ ይኖረናልና ለሱ አንቸኩል!!!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop