የእህቴ መከራ የኔም ነው – ከሞሲት የሻነህ

Cry Ethiopia 1በኢትዮጵያ ውስጥ ካለፉት አራት/አምስት አመታት ወዲህ እየባሰ የመጣውና ባሁኑ ጊዜ ደግሞ በጣም ጎልቶ የሚታየው

የሰላም መደፍረስ፣ የሕግ አልባነት መስፋፋት፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር፣ የስብእና መሸርሸርና በእኩልነት የመኖር ተስፋ መመንመን፤ በሴቶች፣ በልጆችና በአቅመ-ደካሞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ለማንም ስውር አይደለም።

 

በኢትዮጵያ ሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ባለብዙ ዘርፍ ቢሆንም ከሁሉም በላይ ኢሰባዊ የሆነው ወንጀል ግን አንዲት ግለሰብ በሴትነቷ ምክንያት የሚፈጸምባት አስገድዶ የመድፈር ወንጀል ነው። ሴትን አስገድዶ የግብረ-ሥጋ ድፍረት መፈጸም ጠላትን የማሸበሪያ፣ የማዋረጃና ሞራሉን የመስበሪያ ስነ-ልቦናዊ መሣሪያ ተደርጎ በመታየት ጦርነት በሚነሳባቸው ወይም ወረራ በሚፈጸምባቸው ቦታዎች ሁሉ እንደሚተገበር ይታወቃል። ይህ ድርጊት የሚያንጸባርቀው፤ ሴት ነጻ የስእብና እውቅና እንደማይሰጣትና ክብሯም ሆነ ህልውናዋ የራሷ ሳይሆን የባሏ፣ የአባቷ፣ የወንድሟ ወይም የወንድ ልጇ፣ ባጠቃላይ የወንድ ዘመዷ ነው የሚል መሠረታዊ አመለካከት መኖሩን ነው። በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በአለም-አቀፍ የሰባዊ መብቶች ህግ መሠረት የጦር ወንጀልነት እውቅና ቢያገኝም የኢትዮጵያ ክልላዊም ሆነ መአከላዊ መንግሥቶች ግን የሚፈጸሙትን ወንጀሎች ለፍትህ ለማቅረብም ሆነ እንዳይፈጠሩም ቅድመ-ሁኔታዎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ አይታዩም።

 

በትግራይ ተጀምሮ፤ የአማራና የአፋር ክልሎችን በመውረር ለሁለት አመቶች በተካሄደው ጦርነት ወቅት በሶስቱ ክልሎች ኗሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈርን ያካተተ ነው። ይህም ሆነ ሌሎች የሰባዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች የተፈጸመባቸው፤ እንዲሁም በፍልሚያ ላይ የተሰውት ዜጎች ቁጥር በትክክል አይታወቅም። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የዜጋ ወይም የግለሰብ ዋጋ በጣም የረከሰባትና አንዱን ብሔር ከሌላው በቁጥር የማበላለጥ እሽቅድድም የሚደረግባት አገር ስለሆነች፤ በጦርነት የሞቱትን ዜጎችም ሆነ በሕይወት ያሉትን ቁጥር፤ የበላይነት ነጥብ ያስገኛል ብለው የሚገምቱ ፖለቲከኞች በብዙ መቶ ሽዎች ክፍም ዝቅም ያደርጉታል። የነጻ ጥናት ለማድረግ የሚነሱ ወገኖች ደግሞ፤ በጸጥታ ችግር የተነሳ ግልጽና በቂ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ስለማይኖሩ ሰነዶቻቸው የተሟሉ ላይሆኑ ይችላሉ። ያም ሆኖ በጥናት ላይ የተመሠረተ መረጃ እንደሚያሳየው በአማራ ክልል ውስጥ በተደረገው ወረራ፤ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከተፈጸሙት የሰባዊ-መብት ጥሰቶች መሀል 13% በሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲሆን፤ ወንጀሉ ከተፈጸመባቸው አንድ አስረኛዎቹ ለአቅመ-ሔዋን ያልደረሱ ሴቶች ወይም ልጆች ናቸው። ሌሎቹ በወረራው ወቅት የተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ መግደል፣ አካላዊ ጉዳት ማድረስ፣ ያለምክንያት ማሰር፣ አስገድዶና አፍኖ መውሰድ ናቸው። የግድያ ወንጀል የተፈጸመባቸው ከጠቅላላው ሰባዊ-መብት ጥሰት 45% ሲሆኑ ከእነሱ መሀል ደግሞ ከአምስቱ አንዷ ሴት ናት።

 

ሴቶች፤ በቀጥታ በራሳቸው ላይ ከሚፈጸሙት ተገዶ የመደፈርና የተጠቀሱት ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከሚፈጥሯቸው ጉዳቶች በተጨማሪ፤ እነኝሁ ጥቃቶች በቤተሰባቸውና በማኅበረሰባቸው ላይ የሚፈጥሩትን ችግርና በጠቅላላው በጦርነትም ሆነ በሌላ ፖለቲካዊ ጥቃት የተነሳ የሚከሰቱትን ማኅበራዊና ቁሳቁሳዊ ጉዳቶች ለመቋቋም ከፍተኛውን ሸክም ማስተናገድ እጣ-ፈንታቸው ነው። ልጆቻቸውንም ሆነ ደካማ ወላጆቻቸውን፤ ከሞት፣ ከመፈናቀል፣ ከረሀብና ከጥም ለመታደግ በሚያደርጉት ጥረት አለመሳካት የተነሳ ጤና የሚጎዳና እድሜ የሚያሳጥር የልብና የመንፈስ ስብራት እንደሚደርስባቸው መገመት አያዳግትም። በባል፣ በወንድም፣ በእህት፣ በአባት፣ በዘመድ በጎረቤት ወጥቶ መቅረትም እንደዚሁ።

 

በአገራችን ውስጥ የሴቶች መከራ የጦርነት ጊዜ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን እለታዊ ክስተት መሆኑ ባለፉት አራት/አምስት አመቶች በገሀድ የሚታይ ነው። ለምሳሌ፤ ወላጆች ሳይደላቸው በችግር ካሳደጉ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት የላኳቸው የአማራ ሴቶች ልጆች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ታፍነው ተወስደው የት እንደገቡ ሳይታወቅ መቅረታቸውን ወላጅ የሆነ ሁሉ ሊረሳው አይገባም። እንዴት መንግሥት አለ ተብሎ በሚታመንበት አገር ውስጥ፣ ራሱን ከውጭ ጠላት ተከላክሎና ነጻነቱን አስከብሮ የመኖር ብቃቱን ያስመሰከረ ሕዝብ መሀል ይህ አይነት ወንጀል ተፈጽሞ፤ ሲሆን መላውን ሕዝብ ሳይሆን ሴቶችን ዳር-እስከዳር በቁጣ ሳያስነሳ ያልፋል? የሴቶችና የልጆች ስቃይ ማንኛውንም ሰብአዊ ህሊና ያለውን ዜጋ በቁጣም በቁጭትም ሊያነሳሳና ሊያነጋግር በተገባ ነበር፤ በመንግሥትም ዘንድ ቀዳሚ ትኩረት በተሰጠው ነበር። የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳየው ግን ይሄንን ሳይሆን፤ በመንግሥት ቸልተኝነት እንዲሁም በቀጥታ ተሳታፊነት ወንጀሎቹ እየበዙና እየባሱ መሄዳቸውን ነው።

 

በአገሪቱ ዙሪያ በተለያዩ ብሔረሰቦች ወይም ማኅረሰቦች ላይ በየጊዜው የሚፈጸመው የማፈናቀል ወንጀል በሴቶችና በልጆች ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ችግር አሌ የማይባል ነው። ለምሳሌ በይፋ እንደሚታወቀው፤ ለሕዝብ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት በመንግሥት ተወስኖና ታውጆ አማራ ክልል ውስጥ እየተወሰደ ያለው ወታደራዊ ጥቃት፤ ሴቶችን፣ ልጆችንና አቅመ-ደካማዎችን በድጋሚ ለተጨማሪ ጉዳትና ለጾታ ተኮር ወንጀል የሚያጋልጥ ነው። በዜና የተነገረው በሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅት ካቀረባቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል።

 

ዋናው ፈተና፤ መንግሥታዊ መስተዳድሩ የሚመራበት የፖለቲካ ሥርአት ለምንኖርበት ዘመን የማይመጥንና የዛሬውን ትውልድ በብዙ መቶ አመታት ወደኋላ የሚጎትት መሆኑ ነው። የሥርአቱ ትኩረት የሰውን ክቡርነት፣ እኩልነትና የዜግነት መብት በሕግ ማረጋገጥ፣ ፍትህን አክብሮ ማስከበር፣ በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የዜጎች አብሮነት፣ ኅብረትና አንድነት እንዲለመልም መዋቅራዊ ድጋፍ መስጠት ሳይሆን፤ በጠባብ ብሔረተኝነት ላይ የተመሠረተ ሥልጣንንና ፍጹም የበላይነትን በሀሰት ትርክት፣ በሽብር፣ በግጭትና በወታደራዊ ኃይል በመታገዝ ከግብ ማድረስ መሆኑን የየቀኑ ክስተቶች ያሳያሉ። ታዲያ፤ በዚህ የፖለቲካ ሥርአት ውስጥ በሴቶችና በልጆች ላይ የሚፈጸመው ወንጀል ልዩ ትኩረት ያገኛል ማለት ዘበት ነው። በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ፈርጀ-ብዙ ስቃይ ትኩረት ሊያገኝ የሚችለው በራሳችን በሴቶች የተባበረ ድምጽ መሆኑን በመገንዘብ በአንድ ድምጽ ስንናገር ነው። በጎሳ፣ በብሔርና በእምነት ሳንከፋፈል ለሰላም፣ ለሰው ክቡርነት፣ ለዜጋዊና ለዲሞክራሲያዊ መብት፣ ለፍትህና ለሕግ የበላይነት በመቆም “የእህቴ መከራ የኔም ነው” ብለን ካልተነሳን ባለብዙ ፈርጁ ስቃያችን ሊገታ አይችልም፤ እየባሰ ይሄዳል እንጅ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop