መንግሥት ያለው ሰላመቢስና ለመፍረስ የሚንደረደር አገርና መንግሥት የሌለው  ጠንካራና  ሰላማዊ አገር

July 10, 2023
20 mins read
Abiy Ahmed Shine OLF 1

Abiy Ahmed Shine OLF 1 480x480 1

ሃምሌ 3 ቀን 2015 ዓም(10-07-2023)

ብዙ ጊዜ መንግሥት ለአንድ አገር ሰላምና እድገት ለሕዝቡም ነጻነትና ደህንነት ዋስትና እንደሆነ ይነገራል።እርግጥ ነው የመንግሥት አስፈላጊነት አይካድም።መንግሥት ሲባል ደግሞ የጥቂት ሹማምንት በሥልጣን ላይ መኖር ብቻም ሳይሆን የአገሪቱን ህልውናና የሕዝቡን መብት የሚያስከብሩ ጠንካራ  ተቋማት መኖራቸው ነው።በአጠቃላይ ሥልጣኑን የጨበጠ ሁሉ መንግሥት ተብሎ ቢጠራም ሁሉም መንግሥት ግን አንድ አይነት ባህሪያትና አመሰራረት አላቸው ማለት አይደለም።በጉልበት ስልጣኑን የሚቀማ የወንበዴዎችና አምባ ገነኖችም ሆነ በሕዝብ ምርጫና ይውንታ ሥልጣኑን የሚረከብ አካል በአጠራር መንግሥት ይባላሉ። በምርጫ የሚሰዬመው መንግሥት በጸና መሠረት ላይ በተቋቋሙ ተቋማት የሚታገዝ ሲሆን እነዚህ ተቋማት ለአንድ አገርና ሕዝብ  ሰላምና ደህንነት ማረጋገጫና ዋስትና ናቸው።ካለነዚህ ተቋማት አገር እንደ አገር ሊቆምና ሊኖር አይችልም።አገር ሲባልም በአምባገነኖችና በወራሪዎች ተጽእኖ ሥር የወደቀውን ማለት ሳይሆን የሕዝብ፣ለሕዝብ በሕዝብ የሆነውን አገር ማለት ነው።ቤት አለመሠረትና ምሰሶ እንደማይቆም ሁሉ አገርም ካለ ተቋማት አይታሰብም።የተቋማቱ የበላይ ተቆጣጣሪና ባለቤት በሕዝቡ የተመረጠ ምክር ቤት ወይም ፓርላማ ነው።ለተቋማቱ ሕግና ደንቦችን የሚያወጣው ይኸው የሕዝብ ምክርቤት ወይም ፓርላማ ነው። የፓርላማ አባላቱ በምርጫ የሚወከሉ ሲሆኑ በዬምርጫው ይለዋወጣሉ።ተቋማቱ ግን አይለዋወጡም።ለዚያም ነው ከነስማቸው ተቋማት(ቋሚ) የሚባሉት።ተቋማት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በትክክል መሥራታቸውን የሚከታተልና ፣አስፈላጊም ከሆነ ማሻሻያ ደንብ የሚያወጣና በሕዝብ ለተመረጠው ምክር ቤት አቅርቦ የጸደቀውን በተግባር የሚተረጉም  የተቋማቱ ተጠሪ የሆነ በሚንስትርነት ደረጃ የሚሰዬም ግለሰብ ወይም የሚመራው ሚኒስትሪ ይኖራል።የያንዳንዱ ተቋም በሚኒስትር የሚወከልና የሚመራ ስለሆነ ያ የተለያዩ ተቋማትን የሚመራው የሚኒስትሮች ቡድን  ካቢኔ ወይም መንግሥት የሚለውን ስያሜ ይይዛል።

ካቢኔው በጽኑ መሠረት ላይ የቆሙትን ተቋማት ተግባር የሚመራና የሚወክል ባለሙሉ ሥልጣን አካል እንጂ የተቋማቱ አድራጊና ፈጣሪ ባለቤት ፣እሱ ሲኖር የሚኖሩ እሱ ሳይኖር የሚፈርሱ አይደሉም።ለተቋማቱ ሕግና ደንብ የሚያወጣው የበላይ አዛዥና ናዛዡ የሕዝቡ ምክር ቤት ብቻ ነው።ካቢኔው ሥራ አስፈጻሚ ነው ማለት ነው።ካቢኔው በተለያዬ ጥያቄዎች ላይ ተስማምቶ የመወሰን መብትና ግዴታ አለበት።የአንድ ፓርቲ ካቢኔ ከሆነ ለመስማማት ብዙም አይቸገርም።ለመፍረስ የሚጋለጠው ካቢኔ ወይም መንግሥት በጥምር ፓርቲዎች የተቋቋመ ሲሆን ነው።በዚህ መልክ የተቋቋመ ካቢኔ ወይም መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው አቋም ከፓርቲዎቹ እምነትና መመሪያ አንጻር ስለሚሆን በክርክር ማሳመን ወይም አለማሳመን ሊከሰት ይችላል።አለመስማማቱ ከገፋ ለካቢኔው(ለመንግሥት) መፍረስ ምክንያት ይሆናል።ሰሞኑን በኔዘርላንድ የተከሰተውም ይህንኑ ይመስላል።ለጽሑፌም መንደርደሪያ የሆነኝ ይኸው ሁኔታ ነው።

ካቢኔው ወይም መንግሥቱ የተዋቀረው ከተለያዩ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለነበር በልዩ ልዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ብዙ ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል፤ለካቢኔው መፍረስ ምክንያት የሆነው ግን የስደተኞችን አቀባበልና አያያዝ የሚመለከተው ጉዳይ ነው።ይህ ጥያቄ ከተከመረው ችግር ላይ የተጨመረ ስለሆነ ቀውሱን አባብሶት በዋናነት ሊታይ ችሏል።

በጠንካራ መሠረት ላይና በጠንካራ ምሰሶ የተደገፈ ቤት ነዋሪው ወይም  በአላፊነት የተሰጠው ሰው ቢቀዬር ወይም  ቢነሳ ይፈርሳል ማለት እንዳልሆነ ሁሉ አንድ አገርም ጊዜያዊ ሃላፊነት የተሰጠው ካቢኔ ወይም መንግሥት ቢቀዬር አገር ይናጣል ወይም ይፈራርሳል ማለት አይደለም።በጠንካራ ተቋማቱ መኖር ምንም ኩሽ ሳይል የአገር አንድነትና ሰላም፣የሕዝቡ ኑሮ ሳይናጋ ይቀጥላል።

ይህንን ሁኔታና ሂደት በሰሞኑ በምኖርበት አገር በኔዘርላንድ ለመታዘብ ችያለሁ።እርግጥ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ሳይሆን በተደጋጋሚ የታዬ ክስተት ነው።በኔዘርላንድም ብቻ ሳይሆን እንደ ኔዘርላንድ ያሉ ጠንካራ ተቋማትና የፖለቲካ ታሪክና ባሕል ባላቸው አገሮችም የታዬ ክስተት ነው።የቅርብ ጎረቤት አገር በሆነችው ቤልጅዬም  በሥልጣን ላይ የነበረው መንግሥት ( ካቢኔ) ፈርሶ ከአንድ ዓመት በላይ አገር ሳትናወጽ ቆይታ ምርጫ ተደርጎ መንግሥት ሃላፊነቱን ተረክቧል።በኔዘርላንድም ውስጥ እንዲሁ መንግሥት ፈርሶ ምርጫ እስኪደረግና የሥልጣን እርክክቦሽ እስኪፈጸም ድረስ ዓመት ወስዷል።ይህ ከዓንድ ዓመት በፊት ሥልጣን የተረከበው መንግሥት (ካቢኔ)ለዳግመኛ ጊዜ ከሁለት ቀናት በፊት ፈርሶ ኔዘርላንድ ያለመንግሥት እዬተንቀሳቀሰች ነው።የሚገርመው ነገር የመንግሥቱን መፍረስ አብዛኛው ሕዝብ ሳይሰማውና ሳያውቀው ከ24 ሰዓት በላይ መቆዬቱ ነው።ተቋማቱ አብረው ስላልፈረሱ በእለታዊ ህይወቱ ላይ ምንም ለውጥ ስላልመጣበት የመንግሥቱን መፍረስ  ከመጤፍም አልቆጠረውም።ለዚህም ይሆናል ህብረተሰብ ከማደጉ ጋር የመንግሥት አስፈላጊነት ስለማይታሰብ እራሱ በኖ ይጠፋል ሲሉ የቀድሞ የግራው ክንፍ የፖለቲካ ፈላስፋዎች የተናገሩት።መንግሥት ፈርሶ ባንኩም፣የጤና፣የሙያና የአገልግሎት ዘርፉም እንቅስቃሴው ሳይዛነፍ ቀጥሏል።የሕዝቡ እንቅስቃሴ አልተገታም።መንግሥት ፈርሷልና ልዝረፍ፣ልግደል ብሎ የወጣም ወንበዴ የለም።ፖሊስና የጸጥታ ሃይሎች መንገዱን አላጥለቀለቁትም፣ሕዝቡን አላሸበሩትም፤የስዓት እላፊ አዋጅም አልተጣለም።ህይወት እንደነበረ ቀጥሏል።ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በጽኑ መሠረት ላይ ያረፈ የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና ማህበረሰብአዊ ተቋማት በመኖራቸው ነው። እንደ ግል ንብረት በባለሥልጣናት ፍላጎትና ትእዛዝ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ባለመኖራቸው ነው።ለዚህ መብቃት ትልቅ ዕድል ሲሆን ምንጭና መሰረቱ ለመብቱና ለአገሩ የሚቆረቆር ሕዝብ በመኖሩና ያላሰለሰ ትግል በማድረግ የጠንካራ ተቋማት ባለቤት በመሆኑ  ነው።የሕዝቡን መብት ለማስከበር ነቅተው የሚከታተሉ ፓርቲዎችና የሲቪክ ድርጅቶች በመኖራቸው ነው። መንግሥትን ሕዝብ እንጂ ሕዝብን መንግሥት ሊፈጥረው አለመቻሉን የሚረዳ ሕዝብ በመኖሩ ነው።የመንግሥቱን መፍረስ ተከትሎ አዲስ ምርጫ መደረግ ይጠበቃል።ምርጫው ግን የዛሬ አምስት ወር በኖቬምበር ይካሄዳል ተብሏል።በተቋማቱ ጥንካሬ ምክንያት ምንም የሚከሰት ችግር እንደማይኖር ተማምኖ ለዝግጅት ረዘም ያለ ጊዜ እንዲኖር በማሰብ የተደረገ ውሳኔ ነው።ምርጫ ተደረገ ማለትም በማግስቱ መንግሥት ተመሰረተ ማለት አይደለም።ከምርጫ በኻላ መንግሥት ለማቋቋም የፓርቲዎች ድርድርና ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።ያ ደግሞ ከሁለት እስከ 6 ወር ሊወስድ ይችላል።ማለትም ለሚመጣው ከ6 ወራት – ዓመት ድረስ መንግሥት አይኖረንም ማለት ነው። በኔዘርላንድ በአንድ ፓርቲ ብቻ መንግሥት ማቋቋም አይቻልም። እስከ አሁን ድረስ በተደጋጋሚ እንደታዬው የሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ  የፓርቲዎች ቅንጅት የሚፈጠር መንግሥት ነው።በነጠላ ወይም በጋራ መንግሥት ለመመስረት በፓርላማ ካሉት 150 መቀመጫዎች ከግማሽ በላይ ቢያንስ(76) መቀመጫ ያገኘ ፓርቲ(ዎች) መኖር አለባቸው።ያ እስኪሆን ድረስ አገር ካለመንግሥት ሰላምና አንድነቷ ሳይናጋ ትቀጥላለች።

እንደ ኔዘርላንድ ለዚህ ደረጃ ለመብቃት ባልቻሉት አገሮች  ደግሞ ሁሉም ነገር፣አገርም ሕዝብም የባለሥልጣኖች ንብረት ሆኖ እንደፈለጉ የሚነዱት፣በወጡ በወረዱ ቁጥር  ግድያና ትርምስምስ የሚፈጠርባቸው አገሮችን መኖራቸውን ሲያስቡ ይዘገንናል።ከነዚያ ያልታደሉ አገራትና ሕዝብ መካከልም አንዷ የተወለድኩባት አገር ኢትዮጵያና ሕዝቧ ናቸው።

በአገራችን መንግሥት ከፈረሰ አገር ይፈርሳል የሚለው ስጋት የቆዬ ስጋት ሲሆን የሚነዛውም የመንግሥትን መወገድ በማይፈልጉት በኩል ነው።ባለፉት ጊዜያቶች መንግሥት ሲወድቅና ሲፈርስ ግን ኢትዮጵያ አልፈረሰችም ።ምንም እንኳን የመጣ የሄደው አምባገነን ቡድንና መሪ ያሻውን ቢያደርግ፣ነጻ ተቋማት ሳይኖሩ የባለሥልጣናቱ መሳሪያዎች ቢሆኑም እዬተንገዳገደች ቢሆንም ኢትዮጵያ ኖራለች።አሁንም ቢሆን ከሌሎቹ ጊዜያቶች ሁሉ የከፋ ጎሰኛ ሥርዓት አገራችንን ለማፈራረስ ሌት ተቀን ቢሠራም ትፈርሳለች የሚል ስጋት ቢኖረኝም ግን ላለመሳካቱም ምልክቶች በመታዬት ላይ ስለሆኑ መንግሥት ይፈርሳል እንጂ ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚል ተስፋ እንዲኖረኛ አድርጓል።ይብዛም ይነስም የሕዝብ በተለይም በአማራው ማህበረሰብ በኩል የሚታዬው መነቃቃትና  እምቢባይነት ለሌሎቹ አገር ወዳዶች የሞራል ስንቅና የጥሪ ደወል ይሆናቸዋል ብዬ እገምታለሁ።ይህ የተነሳሳ ሕዝባዊ እምቢ ባይነት በአምባገነኖች እንዳይጠለፍ ጠንካራ ተቋማዊ ቅርጽ ሊኖረው ይገባል።ሌሎቹን ተቋማት ከመንግሥት መዳፍ እዬፈለቀቁ ነጻ በማድረግ ለቆሙለት ሕዝብ አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባር ነው። የሚታዩ ስህተቶችን በጊዜው ማረምና ማስተካከል ተገቢ ነው።በተለይ ቡድናዊነትን፣ ግለኝነትንና ጎጠኝነትን መጠዬፍ ትኩረት ሊሰጠውና ትግሉ ከነዚህ ድክመቶች የጸዳ ሊሆን  ይገባዋል።ካልሆነ ግን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ይሆንና በአምባገነኖች ፍላጎትና መዳፍ ስር መከራ ሲገፉ መኖር፣ ግፋ ሲልም አገረቢስ መሆን ሊከሰት ይችላል።

ተቋማቱን ነጻ ማውጣት ለዘላቂው አገራዊ ነጻነት መረማመጃና ዋስትና ነው።ይህ የተቋማት ነጻነት በየከባቢው ሊተገበር ይገባል።ከስርዓቱ ጋር የተቆራኘበትን የጎሳ ሰንሰለት እዬበጠሱ በሕዝባዊና ኢትዮጵያዊነት ሰንሰለት መተካቱ አስፈላጊ ነው።

በኔዘርላንድ ውስጥ መንግሥት ሳይኖር ተቋማት በመኖራቸው ሰላምና ዴሞክራሲው ሳይናጋ የመቀጠሉ ተመክሮ ለሌሎቹ አገሮች በተለይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምልክትና አስተማሪ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።ለዚያ ዕድል ብልጽግና የተባለው የጎሰኞች የብልግና ስርዓት መወገድ አለበት። ተቋማት ከመሸጥና ከመለወጥ እንዲሁም ከመፈራረስ መዳን አለባቸው።ያ ሊሆን የሚችለው ደግሞ የተጀመረው ሕዝባዊ እምቢባይነት ሲቀጣጠልና ሕዝባዊ  አገር ወዳድ መንግሥት ሲቋቋም  ብቻ ነው።

አሁን ኢትዮጵያ ያላት የሚያስብላት መንግሥት ሳይሆን የሚያፈርሳት ጠላት ነው።ስለሆነም መንግሥት ከሌላት ኔዘርላንድ ይልቅ መንግሥት ነኝ ባይ አምባገነን ቡድን የተቀመጠባት አገር ለመፍረስዋና ለሰላሟ መናጋት ምክንያት ሆኗል።ለዚያም ነው የጽሑፌን እርእስ “ ጎሰኛ መንግሥት ያለው ለመፍረስ የሚንደረደር አገርና መንግሥት የሌለው ጠንካራና ሰላማዊ አገር” በማለት የሰየምኩት።

ለመፍረሷ መንደርደሪያ ብዙ ምልክቶች ታይተዋል፣እዬታዩም ነው።የኦሮሙማው ቡድን ከባቢዎችን የመዋጥና የመሰልቀጥ ሂደት፣የወያኔ የመሬት ነጠቃ እቅድና በቤተክርስቲያኗ በኩል በሁለቱም አገር አፍራሽ ሃይሎች የሚዘወረው የጳጳሳት አድማና ውዝግብ በቂ ማስረጃዎች ናቸው።በተለይም ለሰላምና ለሰው ልጆች አንድነት ይቆማሉ ተብለው የሚታመንባቸው የእምነት ተቋማት የፖለቲካ ሃይሎች መሳሪያ ሲሆኑ ማዬት ለአገር መፍረሱ ማረጋገጫ ነው።በኦነግ ጳጳሳትና በወያኔ ጳጳሳት በኩል የሚታዬው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ አገር የማፍረሱና አገር የማዋለዱ ተልእኮ አካል መሆኑ አይካድም።የቤተእምነቶች አባቶችና መሪዎች እንኳንስ በውስጣቸው ቀርቶ በማህበረሰቡ መካከል የሚፈጠርን ቀውስና ውዝግብ የሚያሶግዱ የእርቅና የይቅርታ ተምሳሌዎች ነበሩ።አሁን ግን ሻሽ የጠመጠሙ የጦር አበጋዞች ሆነዋል።

ሕዝባዊ ትግሉ ኢትዮጵያን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አገሮች ተርታ ለመቀመጥ ያብቃት!

አገሬ አዲስ

1 Comment

  1. በኔዘርላንድ ውስጥ መንግሥት ሳይኖር ተቋማት በመኖራቸው ሰላምና ዴሞክራሲው ሳይናጋ የመቀጠሉ ተመክሮ ለሌሎቹ አገሮች በተለይም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምልክትና አስተማሪ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Abiy and Getachew
Previous Story

የሰሞኑ የአደባባይ ምስጢር፦ – እውነቱ ቢሆን

Cry Ethiopia 1
Next Story

የእህቴ መከራ የኔም ነው – ከሞሲት የሻነህ

Latest from Blog

አትዮጵያ ያን ዕለት

ግም ሞት 20’ 1983 .ዓ.ም. ለህወሀት /ኢህአዴግ ልደት ለኢትዮጵያ እና ለብዙዉ ኢትዮጵያዉያን የዉድቀት ፣ጥልመት እና ሞት ዕለት መሆኑን ያ ለሁለት አሰርተ ዓመታት ከፍተኛ ዕልቂት እና ደም መፋሰስ የነበረበት ጦርነት አዲስ አበባ በደም

አቢይ አህመድ ታላቁን አሜሪካንና የተቀሩትን የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ማታለል ይችላል ወይ? የአሜሪካ “ብሄራዊ ጥቅምስ ኢትዮጵያ ውስጥ“ እንዴት ይጠበቃል? የአሜሪካ እሴቶችስ(Values) ምንድን ናቸው?

ለመሳይ መኮንና ለተጋባዡ የቀድሞ “ከፍተኛ  ኢትዮጵያዊ ዲፕሎማት” በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን የስቴት ዴፓርትሜንት ውስጥ ተቀጥሮ ለሚስራው ኢትዮጵያዊ ሰው የተሰጠ ምላሽ!   ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ግንቦት 19፣ 2016(ግንቦት 27፣ 2024) መሳይ መኮንን በአ.አ በ17.05.2024 ዓ.ም አንድ እሱ  የቀድሞው “ከፍተኛ የኢትዮጵያ

ጎንደር ሞርታሩን እስከ ጄነራሉ ተማረከ | ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | ብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን

ይልማ ምስጢሩን አወጣ “ብርሃኑ ከሸ-ኔ ጋር በድብቅ ይሰራል” | “ፋኖ ከተማውን ቢቆ-ጣ-ጠር ይሻላል” ከንቲባው |“አብይ ክዶናል ለፋኖ እጅ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ኮ/ሉ |“በድ-ሮን እንመ-ታችኋለን እጅ እንዳትሰጡ” ጄ/ሉ
Go toTop