July 10, 2023
T.G
ነገረ አስተሳሰባችንና ነገረ ሥራችን ሁሉ ማለቂያ ካጣው ሁለንተናዊ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ እና መነፈሳዊ ውድቀታችን ሰብሮ ለመውጣት በሚያስችል የቅድሚያ ቅድሚያ (the priority of priorities) መርህና አካሄድ ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ እንኳን ዘላቂ ፈውስ ትርጉም ያለው ጊዚያዊ ማስታገሻ ለማግኘት አልቻልንም።
ይህ ደግሞ ከፖለቲካው አልፎ ሃይማኖታዊ እምነትን ሲጠናወት ህመሙ በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ ነው። የባህር ማዶው የገዳም ፕሮጀክት ዘመቻም ከዚሁ በእጅጉ የትኩረት ሚዛንን ከሳተ አስተሳሰብና አካሄድ የመነጨ ነው። መቸም ያፈጠጠውን መሪር እውነት ለመሸሽ የማንደረድረው ምክንያትና ሰበብ የለምና ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን መዓትን እንደመጥራት የሚቆጥሩ ወገኖች እንደሚኖሩ እረዳለሁ። ለዚህ ያለኝ ምላሽ ፀሃይ ስለሞቀው እውነታ ለምን ትተነፍሳላችሁ የሚል እውነተኛ አምላክ የለምና አያስጨንቀኝም የሚል ነው።
እያልኩ ያለሁት ዘመቻችን ሁሉ የህመማችንን መጠንና አስከፊነት በቅጡ ተረድተን ለዚያው በሚመጥን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተግባር ላይ መገኘት ያልቻልንበትን የግልም ሆነ የቡድን ክፉ ደዌ መመርመር አለብን ነው እንጅ ገዳም ወይም ሌላ ለህዝብ የሚያገለግል ተቋም አያስፈልግም ለማለት እንደሆነ ልብ ይባልልኝ።
እናም ልቀጥል፦
ውድ ወገኖቼ፦ ታሪካዊትና የሃይማኖቶኞች አገር እያልን የምንተርክላት አገር ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን እና በተለይም ደግሞ አብይ አህመድና ካምፓኔው የተረኝነት ዙፋኑን ከጨካኝ የአገዛዝ ማስፈፀሚያ ሰይፍፋቸው ጋር ከተረከቡበት ከአምስት ዓመታት ወዲህ የሆነችውንና እየሆነች ያለችውን እጅግ ለመግለፅ የሚያስቸግር መሪር ሁኔታን በአንድ በኩል እና በሌላ በኩል ደግሞ የባህር ማዶ የገዳም ግንባታ ዘመቻ የቅድሚያ ቅድሚያነትን ከእውነተኛ የክርስትና ትርጉምና ዓላማ ጋር ከምር ልብ በሉት (አጢኑት)!!!
እጅግ አያሌ ሚዮኖች እንኳንስ በወጉ የሚያመልኩበት ቤተ አምልኮና ሁኔታ አንጡራ ነፍሳቸውን ለማሰንበት ባልቻሉበት፣ አገር በማያቋርጥ የግፍ ደም በተጥለቀለቀችበት፣ የግፈኞች ሰለባ የሆኑ ሙት አካሎች (አስከሬኖች) አፈር አልባሽ አጥተው የአውሬ መጫወቻ በሚሆኑበት፣ የሃይማኖት አባቶች የምንላቸውን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወገኖች የአድርባይነት ሰለባ በሆኑበት እጅግ መሪር እውነታ ውስጥ “ለባህር ማዶ የገዳም ፕሮጀክታችን ሚሊዮኖች ዶላሮችን ካለገሳችሁ ፅድቁና በረከቱ ያልፋችኋል” በሚል ዘመቻ መጠመድ ምን የሚሉት ክርስትና ነው???
የመከራውና የወርደቱ ዘመን ፍፃሜ ያጣበትን መከረኛ ህዝብ አፍላ ጉልበታቸውንና ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው ትውልዳዊ ድርሻቸውን መወጣት የሚገባቸው እንደ እሸቱ አይነት የዚህ ወጣት ትውልድ አባላት በሃይማኖት ስም በተጀቦነ ርካሽ ዘመቻ ውስጥ ተዋናይ መሆን ከምርና ከትክክለኛ ክርስቲያናዊ አስተሳሰብና እምነት አንፃር ሲታይ በእጅጉ ያሳስባል! ያስፈራልም!
አዎ! ሲሆን በየጊዜው ካልሆነ ደግሞ በተወሰነ ጊዜ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን በአያሌ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖችን በአካል እየተገኘ ማፅናናት ያልቻለና ያልፈለገ የሃይማኖት መሪ ወይም አስተማሪ “የባህር ማዶ ገዳማዊ ፕሮጀክቴን አሁንኑ ለፍፃሜ ካላበቃችሁልኝ ገሃንም ትገባላችሁ” በሚል አይነት ዘመቻ ተጠምዶ ማየት በእውነት ክርስቲያን የሆነን ወገን ህሊና በእጅጉ ያማል!
አዎ! ቀባሪ ያጣንና በቁሙ እየሞተ ያለን አማኝ ወይም ህዝብ በቅርበትና የቅድሚያ ቅድሚያ በሚሰጥ ሁኔታ ከመታደግ ይልቅ በአሜሪካ የሚገኘውን የዳያስፖራ ማህበራዊና የእምነት ህፀፆች እያጋነኑ “ በተወሰኑ ሰዓታት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ካልሰጣችሁ በረከቱ ያልፋችኋል” በሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ እንኳንስ የሃይማኖት አባትና አስተማሪ ነኝ ለሚል መሠረታዊና ሚዛናዊ የሆነ ሰብእና ላለው ወገንም ፈፅሞ አይመጥንም!!!
የሰበብ ድሪቶ ከመደረት ይልቅ ለዘመናት ከመጣንበትና ከአምስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ከቀጠለው ሁለንተናዊ የውድቀት አዙሪት ሰብረን መውጣት ካለብን መነጋገር ያለብን በዚህ ልክ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል!!!