እኛ “ትውልደ-ኢትዮጵያውያን” የውጭ አገር ዜጎች – ባይሳ ዋቅ-ወያ

መግቢያ፣

በቅርቡ ፒቱፒ (P2P) በሚባለው የትውልደ-ኢትዮጵያውያን ምሁራን ውይይት መድረክ ላይ “አንድ ጥያቄ አለኝ፣ መልስ እሻለሁ” በማለት የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖሊቲካ ሁኔታ አስመልክተው አቶ በቀለ ገብርኤል የተባሉ የመድረኩ ደንበኛ አጭር ጥያቄ አቅርበው መልስ በማጣታቸው በቅሬታ መልክ ላነሱት ጥያቄ ራሳቸው መልስ ሲያዘጋጁ ሁላችንም አስተውለነዋል። ከዚህ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሑራንን ካቀፈ የውይይት መድረክ ውስጥ እንዴት አንድ እንኳ መልስ ሊሠጥ የሚችል ግለ ሰብ ይጠፋል በማለት አብዛኞቻችን ምናልባት ከራሳችን ጋር ሙግት ገጥመን ይሆናል። እንደ ገመትኩት ከሆነ፣ ጥያቄው መላሽ ያጣው፣ በክብደቱ ምክንያት ሳይሆን፣ ምናልባትም ጥያቄውን ለመመለስ በራሳችን ላይ እምነት ከማጣት ይመስለኛል። በግሌ ለብዙ ዓመታት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስቼ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ የተወያየሁበትና እስከ ዛሬም ድረስ አጥጋቢ መልስ ያላገኘሁበት፣ ሲያዩት ቀላል የሚመስል ሲሸከሙት ግን ከባድ የሆነ ጥያቄ ሆኖ ስላገኘሁት፣ ከፒቱፒ ምርጥ ምሁራን መሃል፣ ለአቶ በቀለ ጥያቄ ደፍሮ መልስ የሚሠጥ አንድም ሰው አለመገኘቱ አልገረመኝም። ዛሬ የደረስኩበት ድምዳሜ፣ ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን መልስ ሊሠጡ የሚችሉት እኛ ባሕር ማዶ ያለነው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገር ዜጎች ሳንሆን እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ፣ በያመቱ ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን የሚወጡና ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውሱ ያስከተለውን ገፈት በየቀኑ የሚቀምሱ የኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ናቸው የሚል ነው። በኔ ግምት አቶ በቀለ፣ አግባብ ያለውን ጥያቄ አግባብ ባልሆነ ቦታ የማያገባቸውን ግለ ሰቦች በመጠየቃቸው አግባብ ያለው መልስ ሊያገኙ አልቻሉም ባይ ነኝ። ትንሽ ላብራራ!

አብዛኞቻችን የዚህ የፒቱፒም ሆነ የሌሎች ተመሳሳይ መድረክ ደንበኞች፣ በተለያዩ ምክንያቶች እናት አገራችንን ለቅቀን፣ በተለያዩ የዓለም ክፍላት “ባክነን” የቀረን ቀድሞ የኢትዮጵያ ዜጎች የነበርን ነን። የአወጣጣችን ዘዴና ምክንያት የተለያየ ቢሆንምና የመጣንበት ማሕበረሰብም ሆነ የትምሕርት ደረጃችን እንደዚያው የተለያየ ቢሆንም፣ ከተወሰኑ የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ሁላችንም የየአገራቱን የዜግነት መሥፈርት አሟልተን ከነባሩ ሕዝብ ጋር “እኩል ዜጋ” ለመሆን የቻልን ነን። የቀድሞ የዜግነት አገራችን ኢትዮጵያን ስንለቅ፣ ግማሾቻችን በፍላጎታችን ለትምሕርት ብለን ሲሆን ብዙዎቻችን ደግሞ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነፍሳችንንም ጭምር ውድ ዋጋ ከፍለን በተለያየ ዘዴና አቅጣጫ የወጣን ነን። በተለያዩ ምክንያቶች እናት አገርን ጥሎ መኮብለል ብዙ የዓለም ሕዝቦችም ሲያደርጉ የነበረና ዛሬም እያደረጉ ያሉት ጉዳይ ስለሆነ ድርጊታችን የሚኮነን አይደለም። የትውልድና የዜግነት አገራችንን ለቅቀን መውጣቱ ወይም የወጣንበት ዓላማ ያን ያሕል አሳሳቢ ባይሆንም፣ ከትውልድ አገራችን ጋር አጋምዶን የነበረውን የዜግነታችንን ገመድ በፈቃዳችን በጥሰን ከጣልን በኋላ፣ በሕጋዊ ሰውነታችን ላይ አንዳችም ለውጥ ያላደረግን ይመስል፣ ዛሬም በቀድሞዋ የዜግነት አገራችን ከአገሬው ዜጋ እኩል በፖሊቲካው ሕይወት “ያገባናል” እያልን በተለያዩ ሚድያዎች እየቀረብን የምናነሳው አቧራ ግን እጅግ በጣም አሳሳቢ ሆኖ አግኝቻለሁ። የአቶ በቀለም ጥያቄ መታየት ያለበት ከዚሁ መሠረታዊ ሃቅ አንጻር መሆን ያለበት ይመስለኛል። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም በቀጥታ ለአቶ በቀለ መልስ ለመስጠት ሳይሆን፣ እሳቸው ላነሱት ጥያቄ መላሾቹ እኛ የውጭ አገር ዜጎች ሳንሆን፣ የኢትዮጵያዊያን ዜጎች መሆናቸውን ለማሳየት ነው። ጉዳዩ ከዜግነት ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለውና!

 

ዜግነት

ዜግነት፣ የአንድ ግለ ሰብ መብት አልፋና ኦሜጋ ነው ይባላል። ምንም እንኳ የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተጎናጸፋቸው አንዳንድ ሰብዓዊ መብቶች ዜጋም ሆነ አልሆነ፣ መከበር ያለባቸው ቢሆኑም፣ ዜግነት ግን በመሠረቱ ሰብዓዊ መብትን ብቻ ሳይሆን ዲሞክራሲያዊ መብትንም ያጎናጽፋል። የአንድ አገር መንግሥትም፣ የሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ጥበቃን በተመለከተ በቅድሚያ ተጠያቂነቱ ማኅበራዊ ውል (social contract) ከተፈራረመው ከአገሬው ዜጋ ጋር ስለሆነ፣ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ በዚህ ማኅበራዊ ውል መሠረት የኢትዮጵያን መንግሥት፣ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲያስከብርላቸው ሊሾሙት፣ አላስከብርም ካለ ደግሞ ሊሽሩት ፍጹማዊ መብት አላቸው። ከኢትዮጵያ ዜጎች ውጪ ግን፣ የሌላ አገር ዜጎች (ብዙዎቻችንን ጨምሮ) የኢትዮጵያን መንግሥት የመሾምም ሆነ የመሻር ሥልጣን የላቸውም ማለት ነው። በሕግም ሆነ በልምድ፣ የውጭ አገር ዜጎች፣ ከምሁራዊ ውይይት ባሻገር በተግባር በሌላ አገር የፖሊቲካ ጉዳይ ጣልቃ መግባትና “ሥርዓቱን ለመናድ” መሞከር ዓለም ዓቀፋዊ ወንጀልም ነው።

 

እኛ ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ቀድሞ የኢትዮጵያ ዜጎች የነበርን)፤

ከላይ በአጭሩ ለማስረዳት እንደ ሞከርኩት፣ ከትውልድ አገራችን ኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘንን ሕጋዊ የዜግነት ገመድ በገዛ ፈቃዳችን ቆርጠን ተለያየን ማለት ስለ ቀድሞው ትውልድ አገራችን አንዳችም ዓይነት ስሜት አይኖረንም ወይም መቆርቆር የለብንም ማለት አይደለም። ምንም ቢሆን፣ ልንለያት እሰክ ወሰንንበት እስከዚያች ክፉ ቀን ድረስ፣ የተወሰነ የሕይወት ዘመናችንን አሳልፈንባታልና፣ ያደግንበት ቄዬና አካባቢው፣ ከብት ያገድንባቸውና ከዕድሜ እኩዮቻችን ጋር የተጫወትንባቸው ቦታዎች፣ የተማርንባቸው ትምሕርት ቤቶችና፣ እንደ እኛ ሳይሳካላቸው ቀርቶ እዚያው እቀድሞ አገራችን የቀሩት ዘመዶቻችንና ጓደኞቻችን በተለያዩ መንገዶችና ሰበቦች ትውልደ አገራችንን እንድናስታውስ ማድረጋቸው አይቀርም። ማንነት በጣም ጥልቅ ነገር ነው። በአገራችን “ዘረኝነት” “ጎጠኝነት” “ጠባብነት” እየተባለ እንደ አሉታዊ ነገር ይታያል እንጂ በመላው ዓለም የሰው ልጅ በሙሉ፣ የማንነቴ መገለጫ ነው ብሎ ከወገነበት አገር ጋር ያለውን ማኅበረ ሰባዊ ቁርኝት በቀላሉ በጥሶ ሊጥለው የማይችል፣ እስከ መጨረሻው ድረስ አብሮት የሚዘልቅ ተፈጥሮያዊ የሆነ ክስተት ነው። ስለሆነም፣ ለምሳሌ ግሪክን ወይም አይርላንድን በእግራቸው ረግጠው የማያውቁ የግሪክ ወይም የአይርላንድ አሜሪካውያን፣ አመጋገባቸውንም ሆነ ባሕላዊ እሴቶቻቸውን በተቻላቸው መጠን ቅድመ አያቶቻቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ጥለውት የወጡትን አገር የሚያስታውሳቸው ይሆናል። በስዊዘርላንድ የሚኖሩ የጣሊያን ዝርያ ያላቸው የስዊስ ዜጎች ለምሳሌ አመጋገባቸውና አኗኗራቸው የጥንት የአያቶቻቸውን የጣሊያን አገር ይመስላል። ፓስታና ፒዛን እንደ ዋነኛ ምግብ ከመቁጠርና፣ የጣሊያንን መኪና ከመንዳት ባሻገር በዓለም ዋንጫ ወቅት እንኳ ስዊዘርላንድና ጣሊያን ቢጋጠሙ ቲፎዞነታቸው ለጣሊያን ቡድን መሆኑን በግሌ ያስተዋልኩት ጉዳይ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የውጭ ጉዳይ ሚ/ሩ ወርቅነህ ገበየሁን ትግሬነት ያጋለጠው ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ ተጨማሪ መረጃዎችን ሰጠ - "የኢትዮጵያ ሕዝብ የጠየቀው ቀለም መቀባት አይደለም"

እኛን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተም፣ በያለንበት አገር የኢትዮጵያን ቅመማ ቅመሞች፣ ቡናና ሻይ፣ ጦስኝና ፌጦ፣ ቡላና ጭኮ፣ እንዲሁም የባሕል ልብሶችን ማስመጣት፣ ወይም ደግሞ በምንኖርባቸው አገራት የኢትዮጵያን ሬስቶራንቶችን ከሁሉም በላይ ማዘውተር፣ የተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናትን ማሠራትንና በቋሚነት ማገልገል፣ በአርባ አራቱ ታቦታት ስም ማሕበራትን ማቋቋምና የመሳሰሉትን በማድረግ፣ ጥለን ከወጣን የዜግነት አገራችን ጋር በመንፈስ ለመቆራኘት ጥረት ስናደርግ እንስተዋላለን። ከኛም አልፎ፣ የቀድሞ የወላጆቻቸውን አገር እንደ ቱሪስት እንኳ ጎብኝተው የማያውቁትን ልጆቻችንን፣ በተቻለን መጠን ኢትዮጵያዊ እንዲመስሉ መጣራችንም የማንነት ጉዳይ ሆኖብን ስለሆነ ድርጊታችን ትክክል ነው ወይም አይደለም ብሎም መፈረጅ አይቻልም። በኔ ግምት፣ ችግሩ ያለው፣ የቀድሞ የዜግነት አገራችንን ባሕልና እሴት ተላብሶ ለመኖር ከመሞከሩ ላይ ሳይሆን፣ የኛ ባልሆነ አገር የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ ለመግባት መሞከሩ ላይ ነው። ይህ በኢትዮጵያ ፖሊቲካዊ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት፣ አብዛኞቻችን በውል ሳናውቀው የተዘፈቅንበት፣ ጥቂቶቻችን ግን ሆን ብለን አገሪቷም ሆነ ዜጎቿ ሰላም እንዳያገኙ በዕቅድ የተሳተፍንበት የተሳሳተ ተልዕኮ ይመስለኛል። አንዳችም ምድራዊ ኃይል ሳያስገድደን በገዛ ፈቃዳችን፣ ኢትዮጵያዊውን ዜግነትን እርግፍ አድርገን ትተን የውጭ አገር ዜጋ መሆናችን እየታወቀ፣ በማያገባን በሰው አገር የፖሊቲካ ጉዳይ ጣልቃ መግባት፣ “መንግሥቱ ይውረድ” “የሽግግር መንግሥት ይቋቋም” ወዘተ እያልን መወትወታችን በምንም መልኩ ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያውያን አይጠቅምም። ትንሽ ላብራራ!

 

የኢትዮጵያን ዜግነት ትተን የሌላ አገር የሆንነው በገዛ ፈቃዳችን ነው፣

“በገዛ ፈቃዳችን እርግፍ አድርገን የተውነው የኢትዮጵያን ዜግነት” የሚለውን ሓረግ የማጠብቀው ያለ ምክንያት አይደለም። የቀድሞ ዜግነታችንን እርግፍ አድርገን ትተን የውጭ አገር ዜግነትን የወሰድነው ማንም ሳያስገድደን መቶ በመቶ በገዛ ፈቃዳችን መሆኑን አጉልቼ ለማሳየት ነው። አብዛኞቻችን፣ የተሰደድንበትን ምክንያት በተቻለ መጠን ውሸትም ቢሆን እየጨማመርንበት ምለን ተገዝተን ባገኘነው የመኖርያ ፈቃድ (ለምሳሌ ግሪን ካርድ) የትውልድ አገራችንን ዜግነት ሳንለቅ በአዲሱ አገር የመኖርና የመሥራት ሙሉ መብት ነበረን። ግን ዜጋ መሆን ደግሞ የተሻለ ጥቅም ስለሚያስገኝ፣ የውጭ አገር ዜግነቱን ለማግኘት ወስነን፣ በየአገራቱ ሕግጋት መሠረት፣ ዜጋ የመሆን ቅድመ-ሁኔታዎችን እንዳሟላን፣ ወዲያውኑ ጠበቃ ገዝተን “ዜግነት ይገባኛል” ብለን ሙግት እንጀምራለን። ለጓደኛና ዘመድም እየወደልን ለኩክ የለሽ ማርያምና ለመድኃኔ ዓለም ምልጃ እንዲያደርሱልን እንጠይቃለን። በለስ ቀንቶን አንድ ቀን “ዜጋ እንድትሆኑ ተፈቅዶላችኋል” የሚል ወረቀት ሲደርሰን ለወዳጅና ዘመድ አዝማድ ሁሉ ደውለን የደስታ መግለጫ እናውጃለን። ያ ስንመኘው የኖርነው “የዜግነት ዲፕሎማ” በጅምላ ወደሚሠጥበት አዳራሽ ተሰልፈን ገብተን “በአዲሱ የዜግነት አገራችን ባንዲራ ሥር ተንበርክከን፣ አንድ እጃችንን ደረታችን ላይ፣ ሌላውን ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ላይ በመጫን፣ “ለባንዲራውና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ እሆናለሁ፣ ይህንን አዲሱን አገሬን ሊያጠቃ የሚመጣን ጠላት አገር (የቀድሞ ትውልድ አገራችንን ኢትዮጵያን ጨምሮ) ያላንዳች ማወላወል ታጥቄ ለመዋጋትና አዲሱን አገሬን ከአደጋ ለማዳን እምላለሁ፣ ለዚህም ታላቁ አምላክ ይርዳኝ” ብለን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ዘመድ አዝማድና የአዲሱ አገራችን መንግሥት ባለ ሥልጣናት በተገኙበት በአደባባይ እናውጃለን። ከዚያች ሰዓት ጀምሮ፣ የአዲሱ አገራችን ዜጋ በመሆናችን ከቀድሞዋ እናት አገራችን ጋር አቆራኝቶን የነበረው ሕጋዊ ገመድ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተበጠሰ ማለት ነው።

እኛንና የቀድሞ አገራችንን አጋምዶን የነበረው ሕጋዊ ገመድ ተበጠሰ ማለት ግን፣ ስለ ቀድሞዋ አገራችን ማሰብ ወይም መቆርቆር እናቆማለን ማለት አይደለም። በተለይም የመጀመርያው ትውልድ ከሆንን። ለቀድሞዋ የዜግነት አገራችን የምንቆረቆርላት ግን እንደ አንድ የውጭ አገር ዜጋ ሆነን ነው እንጂ፣ ግብር ከሚከፍሉ ከኢትዮጵያ ዜጎች እኩል “በያገባናል” መንፈስ ሊሆን አይገባም። ስለ መብታችንም ሆነ ስለ መንግሥታችን የአገር ውስጥና የውጪ ፖሊሲ ደረታችንን ነፍተን ለመወያየትም ሆነ ለማውገዝ የምንችለው ግብር በምንከፍልባቸው አዲሶቹ የዜግነት አገራትና እና ከአዲሱ አገራችን ግብር ከፋዮች ጋር ብቻ ነው። “የከፈለው ብቻ ነው አዝማሪውን የሚያዘው” ይላል የሩሲያ ሕዝብ። ግብር ለማንከፍልበትና በአገሪቷ የመንግሥት አመሠራረትም ሆነ አሠራር አንዳችም ሕጋዊ ሚና ላልነበረንና ለማያገባን መንግሥት ሕልውና ሕጋዊነት ወይም ሕገ ወጥነት ለማውራት ብሎም በአደባባይ ማውገዝ፣ ተፈጥሮያዊ የሆነውን ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብታችንን በተግባር ለመተርጎም ካልሆነ በስተቀር፣ ሕጋዊነትም ተፈጻሚነትም አይኖረውም። ይህ ያገሪቷን የፖሊቲካ ሕይወት በተመለከተ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዜጎቹ ላይ በዓለም አቀፋዊው ማኅበረ ሰብ ዘንድ እንደ ወንጀል የተቆጠሩትን የሰው ልጅ መብቶችን ጥሰት ከፈጸመ ግን፣ የውጭ አገር ዜጎች (እኛን ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ጨምሮ) ድምጻችንን ከማሰማት የሚያግደን አንዳችም እክል አይኖርም። ሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ፣ ማንኛውም የሰው ልጅ ፍጡር፣ (የውጭ አገር ዜጋም ጭምር ማለት ነው) በተለያየ መንገድ የተቃውሞ ድምጹን የማሰማት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበትና! ይህ መብት ዓለም አቀፋዊና ሁሉንም የሰው ልጅ በእኩልነት ለመጥቀም ተብሎ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች የተካተተ በመሆኑና “ሁሉም ሰብዓዊ መብት ለሁሉም የሰው ልጅ” የሚለው መሪህ በሁሉም አገር ተቀባይነትን ስላገኘ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚከሰቱ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ልክ በቤላሩስ ወይም በካምቦዲያ ውስጥ ለሚከሰተው ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የምናሰማውን ጩኸት፣ ያላንዳች ገደብ ድምጻችንን ከፍ አድርገን መጮህ እንችላለን ማለት ነው። የቀድሞ የዜግነት አገራችንን ኢትዮጵያን በተመለከተ፣ የኛ የቀድሞ ዜጎች የጣልቃ ገብነት “መብት” ከዚህ መሪህ የመነጨ ብቻ መሆን አለበት ለማለት ነው። ጭብጥ ጉዳዩ፣ የውጭ አገር ዜጎች ሚና ከኢትዮጵያ ዜጎች ሚና እጅግ በጣም ይለያል ለማለት ነው።

ከሰብዓዊ መብት ነክ ጉዳዮች አልፎ በፖሊቲካ ሥልጣን ጉዳይ ጣልቃ በመግባትና የኢትዮጵያን መንግሥት ድክመት በመጠቆም፣ “ከሥልጣን ይውረድ” “በሽግግር መንግሥት ይተካ” “ሕዝቡ ታጥቆ ይህንን መንግሥት መገልበጥ አለበት” “ሥርዓቱ መቀየር አለበት” “ሕገ መንግሥቱ መፍረስ አለበት” ወዘተ የመሳሰሉትን ፖሊቲካዊ ጥሪዎችና ለዚህም ዓላማ መሳካት የትጥቅ ትግልን ለማበረታታት ግን ቁራጭ ታህል መብት የለንም። ዜጋ ባልሆንንበት አገር፣ (ለዚያውም ያንቺ ዜጋ መሆን አንፈልግም ብለን በገዛ ፈቃዳችን የተውናትን አገር) ፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ለመግባት አንዳችም ሕጋዊ መብት የሌለን እንደ መሆናችን መጠን እንደዚህ ዓይነቱ ጣልቃ ገብነት ነውርም ሕገ ወጥም ነው። የኢትዮጵያ ሕግ እንደ አብዛኛው የዓለም መንግሥታት ሕግ ጣምራ ዜግነትን ስለማይፈቅድ፣ እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጥ ድርጊታችን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአዲሱ የዜግነት አገራችን መንግሥትም ጋር ሊያጣላን ወይም በወንጀልም ሊያስከስሠን ይችላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአንዳርጋቸው አማራ የለምና የወያኔ ቤታማራን መቆጣጠር - መስፍን አረጋ

የውጭ አገር ዜጎች በመሆናችን የምንተዳደረው በአዲሱ የዜግነት አገራችን ሕግ እስከ ሆነ ድረስ፣ የቀድሞ የዜግነት አገራችንን በተመለከተ የምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ የሁለቱ አገሮች ሕግ በሚፈቅደው አኳኋን ብቻ መሆን አለበት። ከላይ እንዳልኩት፣ ዘመድ ቤተሰብን ከመርዳት ባሻገርና ስለ ሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ድምጻችንን ለማሰማት ካልሆነ በስተቀር፣ በቀድሞዋ አገራችን የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ የመግባት ዕድላችን ከአንድ የብራዚል ወይም የአይርላንድ ዜጋ በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ካለው መብት በምንም መልኩ የተሻለ ሊሆን አይችልም። ሁላችንም የውጭ አገር ዜጎች ነንና! አዎ! የሆነ የዕድሜያችን ቁራጭ ከዚያ ከቀድሞ የዜግነት አገራችን ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታን በተመለከተ፣ ለዚያ ለቀድሞ አገራችን ሊኖረን የሚችለው መቆርቆር፣ ከብራዚሊያዊ ወይም ከአይርላንዱ የተሻለ ሊሆን ይችላል። የኢትዮጵያ መንግሥት በገዛ ፈቃዱ፣ ከቀድሞ አገራችን እንዳንቆራረጥና ብሎም ከፖሊቲካ መስክ ውጭ በሁሉም ዘርፎች ከአገሪቷ ዜጎች እኩል እንድንታይ ያደረገንን “የዲያስፖራው ዓዋጅ” ማውጣቱ እጅግ በጣም አስመስጋኝ የሆነውን ያህል፣ አብዛኞቻችን ግን ይህንን የቀድሞ የዜግነት አገራችንን መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት ያጎናጸፈንን መብት፣ እንደ ተፈጥሮያዊ መብታችን በመውሰድና እሱንም እንደ መንደርደርያ ተጠቅመን በቀድሞዋ አገራችን የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ ለመግባት መሞከር በዓለም አቀፍ ሕግም ሆነ በአዲሶቹ የዜግነት አገሮቻችን ሕግም የተከለከለ መሆኑን በውል የተረዳን አይመስለኝም። በዚህ የተሳሳተ እሳቤ ምክንያት ይመስለኛል ዶ/ር ዓቢይ ሥልጣን በያዙ ሰሞን አብዛኛው ዲያስፖራ፣ በተለይም ድሮ ድሮ በአብዮቱ ዘመን የፖሊቲካ ፓርቲ የመሩ ወይም አባል የነበሩ አንጋፋ ፖሊቲከኞች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የተለያዩ የፖሊቲካ ፓርቲዎችን ፈጥረው ወይም የድሮዎቹን አድሰው ለምርጫ ሲዘጋጁ የነበረው። የምርጫ ቦርዱ ግን በውጭ ዜግነታቸው ምክንያት ፓርቲያቸውን ሊመዘግብ እንደማይችል ሲያስታውቃቸው “አገራችንን እናገለግላለን ብለን መጥተን ጉድ ሆንን” “ይህ የማይረባ መንግሥት እንርዳህ ስንለው ወግዱ አለን” ወዘተ ብለው ሻንጣቸውን ቀርቅበው በመጡበት አኳኋን ተናድደው ወደ የዜግነት አገራቸው መመለሳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

 

ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወዳጆቼ፣

ከሁሉም በላይ መገንዘብ ያለብን፣ ኢትዮጵያ ትውልድ አገራችን እንጂ ዛሬ የዜግነት አገራችን አይደለችም። ዜጎችዋ ስላልሆንን ደግሞ እኛ ስለ እሷ ያለን ፍቅር፣ ሳትበደለን ለግል ጥቅማችን ብለን አንዳችም ዋጋ ሳንከፍልበት የቸረችንን ዜግነት ትተን የውጭ አገር ዜጋ ከመሆናችን አንጻር ነው መታየት ያለበት። ይህም ማለት፣ ካሁን በኋላ እሷን ለመውደድ እንኳ የሷ በጎ ፈቃድና ይቅርታ ያስፈልገናል። የኛ ተመልሶ የኢትዮጵያ ዜጋ የመሆን ዕድል፣ የኢትዮጵያ ዜጎች መርጠውትም ሆነ ባልፈለጉት መንገድ ሥልጣን ላይ በተቀመጠው የኢትዮጵያ መንግሥት በጎ ፈቃድ ይወሰናል ማለት ነው። ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት ነው እንግዲህ ወደ አገሪቷ እንድንገባ፣ ከገባንም በኋላ በምን በምን መስክ ተሰልፈን እንደምንረዳት ፖሊሲ የሚቀይስልን። በሌላ አነጋገር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ውጭ ወደ አገሪቷ እንኳ ቪዛ አግኝተን ልንገባ አንችልም ማለት ነው። ታድለን ግን፣ የውጭ አገር ዜጎች መሆናችን እየታወቀ፣ ለኛ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚጠቅም እስከ ዛሬ በጣም በጥቂት አገሮች ብቻ ሥራ ላይ የዋለውን “የመኖርያና የሥራ ፈቃድ” በዓዋጅ ስለ ደነገገልን፣ በጎ ፈቃድ ካለን፣ በዚያ ማዕቅፍ ውስጥ ሆነን ለግል ጥቅማችን ብለን የካድናትን አገር መልሰን ለመካስ እንችላለን ባይ ነኝ። ትንሽ ላብራራ።

ከሁሉ አስቀድሞ፣ የትውልድ አገራችንን ዜግነት አንፈልግም ብለን ኮብልለን በፈቃዳችን የሌላ አገር ዜጋ የመሆናችንን መራራ ሓቅ መዋጥ አለብን። ስለሆነም፣ ወደድንም ጠላንም፣ ካሁን ወዲያ ታማኝነታችን ለአዲሱ የዜግነት አገራችንና ሕገ መንግሥት ብቻ ነው። መጽሓፉም እንደሚለው ደግሞ በአንድ ጊዜ ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይቻልም። የዜግነት መብታችንንም የሚያስከብርልን መንግሥት፣ አላስከብር ካለም ደግሞ ልናወርደውና በሌላ በሚጥመን መንግሥት ልንተካ የምንችለው ይኸው የአዲሱ የዜግነት አገራችንን መንግሥት ብቻ ነው። በዚያው ልክ፣ የፖሊቲካ ሕይወትን በተመለከተ የኢትዮጵያን መንግሥት ሊሾሙትም ሊሽሩትም፣ የሚችሉት የኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ናቸው። ስለዚህ በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ገብተን ለመበጥበጥ አንዳችም መብት የለንም። የለም፣ በጭራሽ ለመቁረጥ አንችልም፣ ምንም ቢሆን የተወለድንበት አገር ነውና በሆነ ዘዴ ከሕዝቡ ጎን መቆም አለብን ካልን ደግሞ፣ በቅንነት ወደ ትውልድ አገራችን ተመልሰን ወይም ከዚሁ ከባሕር ማዶ ሆነን ኢትዮጵያን ልንረዳ የምንችልባቸው ፖሊቲካ ነክ ያልሆኑ እጅግ በጣም ብዙ ዘርፎች ስላሉ እነሱን እንጠቀም። እነዚህንም በተግባር ለመተርጎም ብዙ ምርጫዎች በእጃችን ላይ አሉልን። በዲያስፖራው ዓዋጅም በግልጽ እንደ ተቀመጠው፣ በመደበኝነት ተቀጥሮ ከመሥራት በስተቀር በአገሪቷ የተለያዩ የሥራ መስኮች እንደ ውጪ ዜጋ ሳይሆን እንደ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሕዝባችንን ለማገዝ ሁኔታዎች ተመቻችተውልናል። በሕጋዊ መንገድ ልንወስድ የምንችላቸው እርምጃዎች ከብዙዎቹ በጥቂቱ፣

የመጀመርያውና አንዳንድ ቁርጠኛ የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዳደረጉት፣ የአዲሱ አገራችንን ዜግነትን መልሰን፣ በሕጉ መሠረት መስፈርቱን በማሟላት የቀድሞ የኢትዮጵያ ዜግነታችንን እንደ ገና መጎናጸፍ እንችላለን። ይህ በተግባር ተተርጉሞ አንዳንዶች ግለሰቦች አዲሱን ዜግነታቸውን መልሰው ኢትዮጵያዊ በመሆን የፖሊቲካ ፓርቲዎች አባል በመሆን በአገሪቷ የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ሚና ሲጫወቱ አይቻለሁ። ይህ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ፣ ከንጹህ አገር ወዳድነት መንፈስ የሚመነጭና ብዙዎቻችን (እኔንም ጨምሮ) ልናደርገው የማንፈቅድ ጥልቅ የአርበኝነት መልዕክት ያለው ከባድ ውሳኔ እንደሆነ አውቃለሁ። ስለዚህ ቆራጥ ከሆንን ይህንን እርምጃ መውሰድ እንችላለን።

ሁለተኛው ደግሞ፣ አይ ይህን በብዙ ትግል ያገኘነውን አዲሱን ዜግነታችንን መልሰን እንደ ገና የኢትዮጵያን ዜጋ መሆን አንፈልግም የምንል ከሆነ ደግሞ፣ የውጭ አገር ዜጋ መሆናችንን በጸጋ ተቀብለን፣ እንደ ማንኛውንም የውጭ አገር ዜጋ ፖሊቲካ ነክ ባልሆነ መንገድ የቀድሞ የዜግነት አገራችንን ሕዝቦች በየሙያችን ወይም በገንዘባችን የምንረዳበትን መንገድ መፈለግ አለብን። ገንዘብ ያለን በኢንቬስትመንት መልክ፣ ወይም የልማትና ማሕበረሰባዊ ተቋማትን (ትምሕርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን ወዘተ) ማሠራትን ማጠናከር፣ በአካደሚክ የላቅንና ምሁራዊ ልምድ ያለን ደግሞ፣ ለምሳሌ ሓኪሞች፣ ለጥቂት ሳምንታት እንኳ ቢሆን ወደ ቀድሞዋ አገራችን ተመልሰን ሕዝባችንን በነጻ ማከም፣ ወይም ለአንድ ሴምስቴር እንኳ ሂደን በነጻ የማስተማር፣ ልጆቻችንን ወደ ኢትዮጵያ ልከን በፒስ ኮር መልክ እንዲያገለግሉ ማበረታታት፣ በእርሻ ሙያ ሰፋ ያለ ልምድ ያካበትን ደግሞ ወደየመጣንበት ባላገር ተመልሰን የአርሶ አደሩን ማረሻ ለመቀየር ባንችልም እንኳ፣ ቀለሉ ያሉ የርሻ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ በቦታው ተገኝቶ ማስተማርና ሌሎች ተመሳሳይ እርዳታዎችን በማሕበራዊ ተሳትፎነት መልኩ መርዳት ይቻላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕዝብ ፍርሃትን እያሸነፈ፤ የወያኔም ጀንበር እየጠለቀች ነው! - ያሬድ ኃይለማርያም

ሶስተኛው፣ ማድረግ ያለብን ደግሞ ታዳጊ ልጆቻችንን በምንኖርባቸው አገራት የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲያሳዩና በሂደትም በአገሪቷ የአስተዳደርና የአመራር ተቋማት በተለይም በፓርላማዎቹ ውስጥ ተመራጭ በመሆን፣ እንደኛ በየመዲናዎች አደባባዮች ከውጭ ሆኖ በባዶ ሜዳ ሰሚ የሌለው ጩኸት ከማሰማት፣ ልጆቻችን ከውስጥ ሆነው የወላጆቻቸውን የቀድሞ ትውልድ አገር ጉዳይ ለፓርላማዎቹ ኮሚቴዎች አቅርበው በማወያየት አንዳች ዓይነት ፋይዳ ሊያስገኙ ይችሉ ነበር። ስለዚህ ልጆቻችንም “ሊሆኑ የማይችሉትን” ነገር በግድ “ሁኑ” እያልን ከምናስጨንቃቸውና በሁለት ዓለም መካከል ግራ ከምናጋባቸው፣ በአዲሱ አገራቸው እንደ አንድ ዜጋ በየአገራቱ የፖሊቲካ ሕይወት ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ራሳቸውንም የወላጆቻቸውን የቀድሞ የዜግነት አገር እንዲረዱ ማድረግ ይቻላል።

 

አራተኛውና ብዙዎቻችን ባይዋጥልንም ልንወሰደው የምንችል እርምጃ ደግሞ፣ እኔ አሁን ያለሁበት ሁኔታ ለግሌም ሆነ ለቤተሰቤ ተስማምቶኛል፣ የቀድሞ የዜግነት አግሬን በተቻለኝ መጠን ለመርዳት ሞክሬ አንዳችም ለውጥ ለማየት ስላልቻልኩ ከእንግዲህ አያገባኝም፣ እየተከሰተ ያለው ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ምስቅልቅልም አይመለከተኝም” ብለን ራሳችንን ከቀድሞዋ አገራችን በማግልለ አዲሱን ዜግነታችንን ያጎናጸፈንን ጸጋ ማጣጣም የሚለው ነው። በግሌ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ያልተሳካልኝ ስለሆነ ይህንን እንደ አንድ ምርጫ የወሰድን ወይም ለመውሰድ ሞክረን ያልተሳካልን ግለ ሰቦች ስሜቱን በደንብ ትረዳላችሁ ብዬ አምናለሁ። ምንም እንኳ የግል ጥቅሜን አስቀድሜ በነጻ የቸረችኝን ዜግነት አሽቀንጥሬ ትቼ የባዕድ አገር ዜጋ ብሆንም፣ ሰው ሆኜ የተፈጠርኩበት፣ የልጅነት ዕድሜዬን ያሳላፈኩበትን የትውልድ አገሬን ሕዝብ ችግርና በአገሪቷ ላይ የደረሰው ማሕበረሰባዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ በዓይኔ እያየሁ “አያገባኝም” ብዬ ጀርባዬን ማዞር ግን አልቻልኩም።

 

ለመደምደም ያህል፣

ወገኖቼ፣ በዚህ ቀውጢ ጊዜ ከቀድሞ የአገራችን ሕዝቦች ጎን ለመቆም መወሰናችን ከቅንነት የመነጨ መሆኑን ማንም የሚረዳው ነው። ችግሩ ግን ማን ሆነን እንደ ምን ልንረዳቸው እንደምንችል ቆም ብለን ያሰብንበት አይመስለኝም። ስለሆነም፣ እስቲ እባካችሁ ሰከን ብለን በመጀመርያ ማንነታችንን እንመርምር። በተለይም የውጭ አገር ዜግነት የወሰድን ግለ ሰቦች! እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለቀድሞዋ የዜግነት አገራችን ያለን ፍቅር፣ ለግል ሕይወታችን እና ድሎታችን ካለን ፍቅር እጅግ በጣም ያነሰ ነው። ብዙዎቻችን የተለያዩ ሰበቦችን እንደ ምክንያት እያቀረብን ለጉብኝት እንኳ ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ አንፈልግም። ለመሄድም ከወሰንን ደግሞ፣ ገና ቦሌ አየር ማረፊያ ደርሰን “ለውጭ አገር ዜጎች” በሚለው ልዩ ረድፍ ተሰልፈን የውጭ አገር ፓስፖርታችን ላይ የመግቢያ ፈቃድ ካስመታን በኋላ የሚቀጥለው እርምጃ ወደ ዜግነት አገራችን ኤምባሲ በማቅናት፣ በአገሪቷ ውስጥ “ለጉብኝት የመጣን” መሆናችንን አሳውቀን፣ ድንገት አንድ ነውጥ ቢነሳ ኤምባሲው እንደ ዜጋው የሚገባንን ጥበቃ እንዲያደርግልን ከማለት፣ የምንገኘበትን አድራሻና ስልክ ቁጥር ሰጥተን በቆይታችን እንቀጥላለን። ተማምነን የሄድነው የድሮው የዜግነት አገራችንን መንግሥት ሳይሆን አዲሱን የዜግነት አገራችንን መንግሥት ጥበቃና እንክብካቤ መሆኑ ነው። አያድርስና ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ነውጥ ቢነሳ፣ የዜግነት አገራችን ኤምባሲ በሚያዘን መሠረት በአስቸኳይ ወደ ቦሌ አየር ማረፍያ እናመራለን። ነውጡ “በምንወደው ሕዝብና አገር” ላይ ምን ያህል አደጋ እንደሚያደርስ ከግምት ውስጥ ሳንከት ወይም፣ አብሮ ከመጋፈጥ፣ ሻንጣንችንን ቀርቅበን ኤምባሲያችን በሚመከረን መሠረት በአስቸኳይ ወደ ዜግነት አገራችን እንመለሳለን። ኢትዮጵያውያኖች ችግራቸውን ለብቻቸው ይጋፈጡ ነው ነገሩ!

በፈለገው መሥፈርት፣ ኢትዮጵያ የቀድሞ የዜግነት አገራችን እንጂ የዛሬ አገራችን አይደለችም። እሷ አልፈልጋችሁም ብላን ሳይሆን እኛ አንፈልግሽም ብለን የተውናት ናት። አዎ! ብዙ ከሷ ጋር የሚያቆራኙንና በሕይወት እስካለን ድረስ አሽቀንጥረን ለመጣል የማንችላቸው ተፈጥሮያዊ ግንኙነቶች አሉ። እነዚህ ተፈጥሮያዊ ግንኙነቶች ግን በምንም መልኩ ከኢትዮጵያ ዜጎች ጋር እኩል ሊያደርጉን ወይም ከነሱ እኩል በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ እንድንገባ የሚያስችሉን አይደሉም። ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አንዱ ብሔር “በማንነቴ ምክንያት በደል እየደረሰብኝ” ነው ብሎ በአማጺ ቡድኑ አማካይነት በሚያደርገው የትጥቅ ትግል ከሩቅ ሆነን ለአመጹ መስፋፋት በቃልም ሆነ በተግባር ወገናዊ የሆነ እርዳታ ለማድረግ መደራጀትና ማደራጀት የሕዝቦቻችንን ሰቆቃ ያባብስ እንደው እንጂ አንዳችም ፋይዳ አይኖረውም። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወደዱም ጠሉም ችግሮቻቸውን አቻችለው በአብሮነታቸው መቀጠል አለባቸው። ሌላ ምርጫ የላቸውም። ስለዚህ እኛ ከምቾት ከተማችን ሆነን፣ ለአንዱ ወግነን ሌላው ላይ ጦርነት ስናውጅ፣ ወይም ካወጁት ጎን ስንቆም፣ የግድያውና የማፈናቀሉ ወንጀል ተባባሪ መሆናችንን በውል መረዳት ያለብን ይመስለኛል። ስለዚህ ሕጋዊ ማንነታችንን ጠንቅቀን አውቀን፣ ሕገ ወጥ ከሆኑ የፖሊቲካ ድርጊቶች (ጣልቃ ገብነት) ተቆጥበን፣ የምንወደውን ሕዝባችንን በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ወይም በማኅበረ ሰባዊና ኤኮኖሚያዊ እርዳታ በኩል ብቻ የምንችለውን በማድረጉ ላይ እናተኩር።

ከሁሉም በላይ እና ሁሌም ማስታወስ ያለብን መራራው ዕውነት ግን፣ ኢትዮጵያ የኢትጵያ ዜጎች ብቻ ናት። እኛም ደግሞ፣ እንደ ኢትዮጵያውያኖቹ የኛ የሆኑ የየራሳችን የዜግነት አገራት አሉን። አራት ነጥብ።

 

******

 

ጄኔቫ፣ ሰኔ 5 ቀን 2023 ዓ/

wakwoya2016@gmail.com

 

 

3 Comments

 1. እውነትን እንደዚህ በጥሬው መጋፈጥ ያስፈልጋል። ቢሆንም ታዲያ አብዛኛው ዲያስፖራ “ዝምታን” እንደሚመርጥና ለሃገሩ እንደሚያስብ ማስታወስም ጥሩ ነው። “ነጩ ቤት” ፊት ለፊት መሰለፍ ከቀረ ስንት ጊዜ ሆነው? ሰልፍ ሳይጠራ ቀርቶ ነው? አይደለም! ዲያስፖራ ለራሱ ጥቅም ሲል ኢንቨስት ያድርግ (ብርና እውቀት ካለው!)። የኔ ቢጤ ለፍቶ አዳሪው ካገኛት ላይ ለዘመዶቹ ዶላር በጥቁር ገበያ መንዝሮ ይርዳ (ጥቁሩም አንድ ቀን ይቆማል!)። ከዚያ ዉጭ ምንም የሚመጣ ለውጥ የለም። መንግስት በጉልበት የሚቀየርበት ዘመን አለፈ፣ በቃ አሁን ላይ የፋራ ሆኗል! ባይሆን መንግስትን በደርዝ በደርዙ መገሰጽ፣ ስህተትን ማሳየት ተገቢም አስፈላጊም ነው። ተደራጅቶ ተገዳዳሪ ሆኖ መንግስት ድምጽ እንዳይሰርቅ ማድረግ እና ህዝብ በካርድ እንዲቀጣው ደግሞ የበለጠ ይበረታታል። እንጂ እንደው ኮሽ ባለ ቁጥር “አቢይ ተገኘ” እየተባለ የሚነዛው በዉሽት ላይ የተመሰረተ ፕሮፓጋንዳ ቢያንስ አይጠቅምም። በተለይ በተለይ የመከላከያ ሠራዊታችንን በተመለከተ፣ ምጥህንቃቅ ግበሩ!
  ሰላማችን ይብዛ!

 2. ውድ ወንድሜ አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ “እኛ “ትውልደ-ኢትዮጵያውያን” የውጭ አገር ዜጎች – በሚል አርዕስት ስር የተጻፈውን ሀተታህን አነበብኩት። አንተ እንደምትለው ሳይሆን አቶ በቀለ ገብርዔል ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ ከእኔም ሆነ ከአንዳንድ ተሳታፊዎች ለጥያቄው በቂ መልስ ተስጥቶታል። ይህ ሰው እኔም ሆነ ሌሎች የሰጡትን መልሶች አይ አላነበበም፣ ካነበበ ደግሞ በፍጹም አልገባውም ይመስለኛል ተመሳሳይ ጥያቄ እንደዚሁ አቅርቧል። የአቶ በቀለ ገብርዔልን ጥያቄ በደንብ አንብበህ እንደሆን ለማለት የሚፈልገው የአቢይ አገዛዝ በህዝብ በከፍተኛ ድምጽ ብልጫ የተመረጠ ስለሆነ አገዛዙን ከስልጣን ለማውረድ ከምንሯሯጥ ይልቅ የአገዛዝ ዘመኑ አልቆ አዲስ ፓርቲ እስኪመረጥና ስልጣኑን እስኪረከበ ድረስ ዝም ብለን ማየት አለብን ነው የሚለው። ባጭሩ አቢይ በአብላጫ ድምጽ የተመረጠ ስለሆነ የፈለገውን ነገር ማድረግ ስላለበት በዚህም በዚያም ብለን አናዋክበው ነው የሚለው። ህዝብ ሲጨፈጨፍ፣ አገር ሲበታተን ዝም ብለን መመልከት አለብን ነው የሚለን። በእሱ ዕምነት ምህር ማለት ዝም ብሎ የሚመለከት እንጂ ትክክለኛና ተገቢ ሂስ የማቅረብ ወይንም በህዝብ የተመረጠን አገዛዝ የመክሰስ መብት የለውም ነው የሚለን። የሱን ጥያቄ ሳነብ አቶ በቀለ ገብርዔል በህዝብ መመረጥና የህግ የበላይነት ትርጉማቸው ምን ማለት እንደሆነ አልገባውም ማለት ነው። አንድ አገዛዝ በህዝብ በአብላጫ ድምጽ ሲመረጥ የህዝብ አገልጋይ በመሆን ህዝቡ የሚጠብቅበትን ነግር ተግባራዊ ማድረግ እንደሆነ የተረዳ አይመስለኝም። እነዚህም ሰላምን ማስፈን፣ ድህነት ሊቀረፍና የመጨረሻ መጨራሻ ላይ ሙሉ ለሙሉ ሊወገድ የሚችልበትን ስልት መቀየስ፣ በአገሪቱ ምድር ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲዳብር አመቺ ሁኔታን መፍጠር፤ ለዚህ ደግሞ ግለሰብአዊ መብትንና ነፃነትን ማወቅ፣ ሰራተኛውና ገበሬው በሙያ ማህበር እንዲደራጁ አስፈላጊውን ህግ በመንደፍ መብታቸው እንዲከበር ማድረግ፣ ጎሳዊ አስተሳሰብ እንዲወገድ አስፈላጊውን የንቃተ-ህሊና ትምህርት መስጠት፣ አገዛዙ ራሱ በምንም ዐይነት ለአንድ ጎሳ እንዳያደላ ማረጋገጥ፣ በተለይም ደግሞ ከወንበዴ ድርጅት፣ ከወያኔ ጋር የእርቅ ድርድር ውስጥ አለመግባት፣ ከዚህም በላይ ብሄራዊ ነፃነትን ማረጋገጥ፣ በሌላ አነጋገር የአንድ ኃያል መንግስት ተላላኪ በመሆን በህዝብ ላይ ጦርነት አለማወጅ፣ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚሉትን ትዕዛዝ በመቀበል ድህነትን አለማስፋፋት… ወዘተ. ናቸው ዋና ተግባሩ። የአገራችን ተጨባጭ ሁኒታ እንደሚያረጋግጠው ከሆነ በኢትዮጵያ ምድር ህዝብን የሚያገለግልና የህዝብን መብት የሚያስጠብቅ መንግስት የሚባል ነገር እንደሌለ ነው። አቢይ አህመድ እንደፈለገው የሚያሽከረክራት አገር ነው ዛሬ ያለችን። በድንብ የምትከታተል ከሆነ የዩትቭ ቻናሎች ሁሉ በመዘጋት ሰው ከውጭ የሚመጡ ትንታኔዎች እንዳያነብ ታግዷል። ለማንኛውም ከታች የሰፈረው ጽሁፍ ለአቶ በቀለ ገብር ዔል መልስ የሰጠሁትን ነው። ተሳታፊውን በጅምላ ከመወንጀል በፊት መልስ ተሰጥቶት ወይም አለተሰጠው እንደሆን በደንብ ማየየት አለብህ። እንደመሰለኝ ዘግይተህ ስለገባህ ቀደም ብለው የተካሄደባቸውን ውይይቶች የተከታተልክ አይመስለኝም።

  ውድ አቶ በቀለ ገብረዔል ጥያቄህ በቀላሉ የሚመለስ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ አንድ አገዛዝ በህዝብ ተመረጠም አልተመረጠም ዋና ተግባሩ በአገሩ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሰላምን ማስከበርና ለዜጎቹ የተሟላ የደህንነት ዋስትና መስጠት ነው። እንደምታውቀው የተሟላ ሰላም ሲኖርና ዜጎች ነፃነት ሲሰማቸው ብቻ የመፍጠር ችሎታቸው ያይላል። የተለያዩ የምርት መሳሪያዎችንም ሊሰሩ ይችላሉ። አዳዲስ የምርት ማምረቻ መሳሪያዎች ሲሰሩ የማምረት ኃይል ይጨምራል። በዚህ አማካይነት የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እምርታን ያገኛል። ስለሆነም የአንድ አገዛዝ ዋናው ተግባር የተሟላ ሰላምን ከማስፈን ባሻገር ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመቺ ሁኔታን መፍጠር ነው። ካፒታልና የሰው ኃይል በአገሩ ውስጥ እንደልብ እንዲንቀሳቀሱና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ የተዘረጉ ዕገዳዎች መነሳት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ተባባሪ መሆን አለባቸው። በየክልላቸውም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሊዳብር የሚችለው ማንኛውም ዜጋ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ ሊሰራና ሊያመርት ሲችል ነው። በዚህ አማካይነት በየክልሉ አዳዲስ የስራ መስኮች ሲከፈቱና ተቀጥሮ የሚሰራውም በቂ ደሞዝ ሲያገኝ የየክልሉ አስተዳዳሪዎችም ከሰራተኛውና ከተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል በሚያገኙት ቀረጥ በአንድ በኩል በአስተዳደር ውስጥ ተቀጥረው ለሚሰሩት ደሞዝ መክፈል ይችላሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በክልላቸው ውስጥ ልዩ ልዩ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ይችላሉ። በዚህም አማካይነት አንድ ክልል የማደግና የማበብ ኃይል ያገኛል።
  ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ የዛሬው የአገራችን ሁኔታ ለማንኛውም ነገር አስተማማኝ አይደለም። አገዛዙም ሆነ የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም። ከህዝቡ ጋር እልክ በመጋባት ሰፊውን ህዝብ ሰላም ነስተውታል። ነፃነቱን ሙሉ በሙሉ ነፍገውታል። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ህዝቡ ምን እንደሚሰራ እንዳያውቅ ተደርጓል። ግራ ተጋብቶና ሁሉ ነገር ብዥ ብሎበት ሲሰቃይ ይታያል። እንደምታውቀው አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ሲወጣ ያልተደሰተና ያልደገፈው አልነበረም። ሰፊውም ህዝብ ብሩህ ቀን ይመጣል ብሎ አስቦ ነበር። ይሁንና አቢይ አህመድ ይህንን የህዝቡን ድጋፍ መሰረት አድርጎ የፖለቲካ ስፔሱን ክፍት አድርጎ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲያብቡና የህዝቡም ተሳትፎ እንዲጨምር ከማድረግ ይልቅ አሁን እንደምናየው እንደ አበድ ውሻ በመሆን ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ሁሉ ቀስ በቀስ እየፈጃቸው ነው። በአካባቢውም የተሰበሰቡት በሙሉ ለራሳቸው ከማሰብ በስተቀር ለህዝባቸውና ለመጭው ትውልድ የሚያስቡ አይደሉም። አንድን አገርን ለመምራት የተቀመጡ አይመስልም። በተለይም ክሶስት ዓመታት ጀምሮ በአማራው ወገናችንና በኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ላይ የሚደረገው ክትትልና ግድያ እየጦፈ በመምጣት ይኸው እንደምናየው በተለይም በአማራው ክልል ውስጥ የጦፈ ጦርነት ይካሄዳል። አቢይ አህመድ በገዛ ዜጋው ላይ ጦርነት በመክፈት ማንኛውንም እንቅስቃሴ አግዷል ማለት ይቻላል። ይህ ድርጊቱ በኢኮኖሚው፣ ማለትም በምርት ላይ፣ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ፣ በስነልቦና ላይና፣ ሰው በሰው ግኑኝነት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ማለት ይቻላል። ባጭሩ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይም የአማራው ዜጋችን በአገሩ ባይተዋር ለመሆን በቅቷል። አዲስ አበባ ውስጥ ቤቱ በላዩ ላይ ይፈርሳል። ይህ ዐይነቱ ድርጊት ምን ይባላል? ከፋሺሽታዊ ድርጊት ሊያንስ የሚችል ነው ወይ?
  ወደ አነሳሁ ጥያቄ ልምጣ፤ አንድ ፓርቲ ሲመረጥና ሲያሽነፍ አገሩን በህገ-መንግስቱ መሰረት ለማስተዳደር ነው። ጠቅላይ ሚኒስተሩም ሆነ ሌሎች ሚኒስተሮች ሲሾሙ መሃላ የሚገቡት ቃል አለ። ይኸውም በህዝቤ ላይ ምንም ዐይነት አደጋ እንዳይደርስ የተቻለኝን አደርጋለሁ። በተቻለኝ መጠን ደስታው ከፍ እንዲል አደርጋለሁ በማለት ነው እጃቸውን የህገ-መንግስቱ ላይ ወይም ደግሞ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ አንተርሰው ቃለ-መሃላ የሚገቡት። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም ሆነ ሌሎች ሚኒስተሮች በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተጻፉትን፣ በተለይም ደግሞ የህግን የበላይነት ማክበር አለባቸው። ይህም ማለት እነሱ ስልጣን ስለያዙ ከህገ-መንግስቱና ከህዝብ በላይ ናቸው ማለት አይደለም። እነሱም ራሳቸው እንደማንኛውም ዜጋ ግዴታ አለባቸው። በመሰረቱ እያንዳንዱ ዜጋ መብትም ግዴታም ሲኖርበት፣ ጠቅላይ ሚኒሰተሩም ሆነ ሌሎች ሚኒስተሮች ግዴታ ብቻ ነው ያላቸው። ህዝብ እየሰራና ቀረጥ እየከፈለ ደሞዝ የሚከፈላቸው እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊውን አገልግሎት ለህዝባቸው መስጠት አለባቸው።
  የዛሬውን የአገራችንን ሁኔታ ስንመለከት የህግ የበላይነት እንዳለ ተሰርዟል። ሶስቱም የመንግስት አካላት፣ ማለትም ፓርሊያሜንቱ፣ ዩዲካቲቩና ኤክስኪዩቲቩ እንዳለ አይሰሩም። አገዛዙና የመንግስት መዋቅሩ በአንድ ሰው ብቻ ነው የሚጠመዘዙት። ፓርሊያሜንታሪያን የአገዛዙን የመቆጣጠር መብት የላቸውም። እንደምትመለከተው አብዛዎቹ አፋቸውን ዘግተው የአቢይን ሌክቸር ብቻ ነው የሚሰሙት። በተለይም ለእኛ ኢትዮጵያውያን፣ እዚህ የካፒታሊስት ማህበረሰብ ውስጥና የህግ የበላይነት በሚከበርበት ለምንኖር የአገራችን ሁኔታ በጣም ግራ የሚያጋባ ሆኖብናል። አገራችንና ህዝባችን የኋሊት ጉዞ ነው የሚያድርጉት የሚመስለው። ታዲያ የአገራችን ሁኔታ እንደዚህ ግልጽ ከሆነ አንድ አገዛዝ ስለተመረጠ ብቻ በህዝብ፣ በአገር፣ በታሪክ፣ በባህልና በአጭሩ በሰው ህይወት ላይ የመቀለድ መብት አለው ወይ? መመረጥ ማለት አገርን ማመሰቃቀል፣ ህዝብን ማፈናቀልና መግደል ማለት አይደለም። በማንኛውም ህግ አንድ አገዛዝ ስለተመረጠ ቢገድልም፣ አገርንም ቢያፈራርስም ሌላ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ዝም ብሎ ማየት ነው የሚል የተፈጥሮ ህግ የለም። ሁላችንም በዚህች ዓለም ላይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የምንኖረው። ስንኖርም በተቻለ መጠን ስቃያችንን ለመቀነስና ደስታችንን ለማጎልመስ እንፈልጋለን። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ነው የሚፈልገው። አንድ አገዛዝ ወደ ተራ ውንብድናና ነፍሰ ገዳይነት ከተለወጠ በአንዳች መንገድ ከስልጣን ላይ መነሳት አለበት። ካለበለዚያ የህዝባችን ስቃይ እየጨመረና ችግሩም እየተወሳሰበ ይሄዳል። እንደምታውቀው ችግሩ እየተወሳሰበና እየጠለቀ ሲሄድ አዲስ ኃይልም ስልጣንን ቢይዝ ችግሩን በቀላሉ ሊፈታ አይችልም። ስለሆነም የህዝባችን ሰቆቃ እየጨመረ እንዳይሄድ ከፈለግንና፥ የመጨረሻ መጨረሻም ወደ ህዝብ መተላለቅ እንዳያመራ ይምንመኝ ከሆነ ይህ አገዛዝ የግዴታ መወገድ ያለበት ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን ግን አካሄዳችን ብልሃትን የሚጠይቅ መሆን አለበት። ማንኛውም ነገር በግብታና በችኮላ መካሄድ የለበትም። በጣም የስለጠኑ ሰዎች በመሰባሰብ ሁኔታውን ለመቆጣጠር የሚችሉበት ዘዴ ወይም ስልት መፈጠር አለበት። ባጭሩ ጥያቄህ በዚህ መልክ የሚመለስ ሲሆን፣ ጥያቄህ ሎጂክ ያንሰዋል። የአገራችንን ሁኔታ በቅጡ መከታተልና፣ በተለይም ሰው ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሞክር፡፡ ይህንን ለመመለስ ስትሞክር ነገሮች በሙሉ ግልጽ ሊሆንልህ ይችላል። አንድ ላረጋግጥልህ የምፈልገው ነገር ከአገዛዙና ከጥቂት ግለሰቦች በስተቀር ማንኛችንም ብንሆን አመጽን አንወድም። በተቻለ መጠን በአርቆ አሳቢነት መንገድ የአገራችን ሁኔታ መፈታት እንዳለበት የምናምን ብዙዎች ነን። በተለይም 90% የሚሆነው የአገራችን ህዝብ ሰላምን ነው የሚፈልገው። ህዝባችን በጥቂት ለስልጣን በቋመጡና ስልጣን ባሰከራቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ፍዳውን እያየ ነው። ስለሆነም ጭንቅላታችንን ሰፋ በማድረግና በዕውቀት በመኮትኮት ለአገራችንና ለህዝባችን አንዳች መፍትሄ መስጠት አለብን። መልካም ግንዛቤ!!

  ፈቃዱ በቀለ ከጀርመን ምድር

 3. አቶ ባይሳ ተልእኮህን እየተወጣህ ነው ማለት ነው? ብዙ ንስሮች አሉ የጻፍከውን ሳይሆን ያሰብከውን ቀድመው የሚረዱ ጥንቃቄም ያስፈልጋል አቀራረብንም ረቀቅ ማድረግ ጥሩ ነው ብዙ ስለጻፍክ ስላንተ አንባቢ በቂ ግንዛቤ ያለው ይመስላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share