#image_title
የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ አለው፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያውና በመጨረሻው መካከል ያለው ነገር ከሚጠበቀው የሚለይ ከሆነ መጀመርን የሚያስረግም ሁኔታ ይፈጠርና እንደሰው መፈጠርን ጭምር የሚያስጠላ ክፉ ዕጣ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህንን ሃቅ በሀገራችንም በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡
በኦሮሙማ ጽንሰ ሃሳብ እንደሚመራ የሚነገርለት ብልጽግና አጀማመሩ በብዙዎች ዘንድ እልል የሚያስብል ሆኖ ሳለ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ከጊዜ ወደጊዜ ያከናወናቸውና አሁን አሁን ደግሞ በከፋ ደረጃ እያከናወናቸው የሚገኙት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያዩና የሚያጨራርሱ መንግሥታዊ ዕቅዶችና ትግበራዎች ሲታዩ የጅማሮው መጨረሻ አስፈሪ መሆኑን መገመት አይከብድም፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ አካል ኃይልና ጉልበት እንዳለው በተሰማው ጊዜ ከማንም በበለጠ መጠንቀቅ እንዳለበት ካልተገነዘበ ለተሳሳቱ ውሳኔዎችና አጓጉል የዕብሪት ድርጊቶች ይጋለጣል፡፡ ስህተቶች ሲፈጠሩና ቢፈጠሩ ደግሞ ቆም ብሎ በማሰብና የዕርምት እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል ሲቻል “ማንም ምንም አያመጣም” በሚል ልበደንዳናነት ከቀጠሉ በታሪክ የምናስታውሳቸውን እጅግ በርካታ አምባገነን መሪዎችና ቡድኖች የገጠማቸውን የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ወዶና ፈቅዶ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡
እልህና “ማን ምናባቱ ያመጣል” በሚል የምንወስዳቸው ከምክንያታዊነትና ከተጠየቃዊ አመክንዮ ያፈነገጡ እርምጃዎች መጨረሻቸው አያምርም፡፡ የሕዝብን ፍላጎትና ምኞት መናቅም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ብልጽግና ወደ ሥልጣን ከመጣበት በተለይ ከጥቂት ሣምንታት የተስፋ ዳቦ ምገባ ወዲህ እየታዩ ያሉ ስህተቶች ሀገራችንን ወደማትወጣው የችግር አረንቋ እየጨመራት ነውና ወደኅሊናችሁ እየተመለሳችሁና ለመመለስም እያቆበቆባችሁ የምትገኙ ወንድም እህቶቼ ቢመር ቢጎመዝዝም አሁን የምለውን እውነት እንድታዩልኝና ከዚህ አስከፊ ሥርዓታዊ ብልሽት ራሣችሁን አግልላችሁ ወደጤናማ የጋራ ሕይወት እንድትቀላቀሉ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡ መልካም ጥሪ ከየትም ይምጣ መቀበሉ ጉዳት የለውም፡፡ አቢይ የተላከበትን ኢትዮጵያን የማጥፋት ተልእኮ ሲወጣ አጃቢ መሆን የርሱን የመጨረሻ ዕጣ ለመቀበል ሠልፍ እንደመያዝ ይቆጠራልና የኦሮሞ ልሂቃን ፈጥናችሁ ለእውነት ቁሙ፡፡
ይቅርታ ይደረግልኝና ሲጀመር ብልጽግና የሚባል ፓርቲ አለ ማለት ይቸግራል፡፡ ምክንያቱም ፓርቲው ተመሠረተ ተባለ እንጂ እንኳንስ ፓርቲው ሀገራችን ራሷ በአንድ ሰው እጅ ገብታ ፍዳዋን እያየች ነው፡፡ ይህ ሰው “ንግግሬ ዐዋጅ ነው” ብሎ የሚያምንና ሰሞኑን ባለሀብቶችን ሰብስቦ “የሚያስቸግራችሁ ሚኒስትር ካለ ንገሩኝ – በአንድ ሣምንት ውስጥ ዋጋውን እሰጠዋለሁ” በማለት የሀገሪቱን የህግ አውጪ፣ የህግ ተርጓሚና የህግ አስፈጻሚ የሥራ ድርሻ በማንአለብኝነት ጠቅልሎ የያዘ ነው – ዶናልድ ትራምፕም ከዚህ ሰው ትምህርት እየቀሰመ ይመስላል፡፡ በመሠረቱ ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ በዚህን መሰል አእምሮውን ያጣ ወይም ጤናማ አእምሮውን በአፍራሽ ኃይል የተነጠቀ ግለሰብ ይወከላል ብሎ ማሰብ ይቸግራል፡፡ የነአብዲሣ አጋ፣ የነጃጋማ ኬሎ፣ የነደበላ ዲንሣ፣ የነተፈሪ ባንቲ፣ የነደምሴ ቡልቶ፣ የነአፄ ገላውዴዎስ፣ የነጥላሁን ገሠሠ፣ የነፀጋዬ ገ/መድኅን ዋቀዮ፣ … ብሔር የሆነውና ከሌሎቹ ነገዶችና ጎሣዎች ጋር ኢትዮጵያን በሥልጣኔ ቀጥ አድርጎ ያቆመ ሕዝብ በዚህ አቢይ አህመድ በሚባል የሥነ አእምሮ ህመሞች ሁሉ ጎተራ የሆነ ናርሲሲስት ሰውዬ ሊወከል ይችላል ብዬ በበኩሌ አላምንም፡፡
ስለሆነም ምንም እንኳን አቢይና ብልጽግና ተወራራሽ ስያሜዎች ቢሆኑም እዚያ አካባቢ የምትገኙ ኦሮሞዎች ለዘመናት የተጋመደ ማኅበራዊ ሕይወታችንን በማጤን ቆም ብላችሁ እንድታስቡ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ውጥንቅጥ መውጣቷ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ ግን ይህ ጨለማ ሲነጋ ኪሣራው ቀለል ያለ እንዲሆን ከሁሉም በተለይም ከኦሮሞው ብዙ የሚጠበቅ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ “Everything changes except change itself.” የምትለዋን የፈረንጅኛ ብሂል አንርሳት፡፡
በብልጽግና/በአቢይ አህመድ ምን ምን ክፉ ነገሮች ታዩ? በጣም ጥቂት ናሙናዎችን ብንዳስስ ጥሩ ነው – እንደአብነት፡፡ የአቢይ ኦሮሙማ በኢትዮጵያና በተለይም በአማራ ላይ የሠራው ግፍ በሥነ ቃላዊው አገላለጽ ሰማይና ምድር ብራና፣ ባሕርና ውቅያኖሶች ደግሞ ቀለም ቢሆኑ ተጽፎ አያልቅም፡፡
- የኢሕአዴግ በዘር ከፋፍሎ የመግዛት አስተዳደራዊ ቅኝት ተባብሶ ቀጠለ፡፡ በዚያም ሳቢያ “ተረኝነቱ ለኛ ይገባል” ያሉ ነገር ያልገባቸውና ከነሱ የሞኝነት ድርጊት ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል ያልተገለጠላቸው የዋሃን ሸረኛውን ካሊጉላ ከብበው በሌላው ላይ መዓት ያወርዱበት ያዙ፡፡ ሕወሓት በመጠነኛ ይሉኝታ ይፈነጭባት የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ኦህዲድ “ብልጽግና” በሚል አዲስ ስያሜ አቢይና ጀሌው ይሠራቸውን ባሳጣቸው መልክ ኢትዮጵያ ላይ ቦረቁ፤ ትንሽ ሰው ትንሽ ነውና ሀገርንና ሕዝብን በዓለም ፊት አዋረዱ፤ ከልማት ይልቅ ጥፋትን ወደዱ፡፡ ታሪካዊ ጠላቶቿ ቀደም ሲል ባቀዱላት መሠረትም የፈረደባቸውን አማራንና ኦርቶዶክስን “አጠፉ”፡፡ ለመግደርደር ያህል ካልሆነ በስተቀር በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ሁለት ኅሉያን ጣር ላይ እንጂ በተግባር የሉም፡፡ ወደኅልውነታቸው ለመመለስ ብዙ ሰማያዊ ቸርነትና ከፍተኛ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ምድራዊ ትግል ይጠብቃቸዋል፡፡ ጦርነቱ የሰው ከሰው ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ጦርነት የመናፍስት ነው፤ ሰዎች ምክንያት ናቸው፡፡ ውጊያዎች ሁሉ ዕልባት ሲያገኙ የጦርነቱ አሸናፊ ይታወቃል፡፡ አቢይ በሰው ደም ጥማት እንዲህ የሚንቀዠቀዠው በልዩ መንፈሣዊ ኃይል እየተነዳ እንጂ በራሱ አይደለም፡፡ እሱ ብቻውን ይህን ሁሉ ውርጂብኝ ሊፈጸም አይችልም፡፡
- በሀሰት ንግግር ከዓለም አንደኛ መሆኑ እንዳለ ሆኖ አቢይን የተጠናወተው የገንዘብ ብክነት ይለያል፡፡ ሁላችን እንደምንገነዘበው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እየተራበ፣ የኑሮ ውድነቱ አገር ምድሩን እያናጋ፣ የሥራ አጡ ቁጥር የትዬለሌ ሆኖ፣ ዕድገትና ልማት ቀጥ ብሎ ቆሞ፣ … አቢይ ግን ያለችንን ትንሽዬ ጥሪት እያሟጠጠ ለሥልጣኑ ማስጠበቂያ ጦርነትና ለቅንጦት ወጪዎች እያዋለው ነው፡፡ እንደምንሰማው ከሦስት ትሪሊዮን ብር በላይ የፈጁና እንኳን ሰው ወፍ ዝር የማይልባቸው መናፈሻዎች ተገንብተዋል፡፡ ከሁለት ትሪሊዮን ብር በላይ የሚያስወጣ ቤተ መንግሥት እየተገነባ ነው፡፡ እኛ መቶ ብር ጠርራብን ለጎረቤት ሀገር የ15 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ እንደሰጠም ይነገራል፡፡ እኛ ሁሉ ነገር ጨልሞብን እሱ በሰባትና በሰምንት ቢሊዮን ብር ወደ ጠፈር ሄዶ ሊዝናና ነውም እየተባለ ነው፡፡ የሚዲያው እኛና የእውነቱ እኛ ሰማይና ምድር ሆነውብን የዕንቆቅልሽ ዓለም ውስጥ እየኖርን ነው – መኖር ከተባለ፡፡ይህንን ሕይወታችንን ሌላው ዓለምም ፈጣሪም አይተው እንዳላዩ ሰምተውም እንዳልሰሙ ችላ ብለውናል፤ የሌላው ቢቀር የፈጣሪ ፍርድ መምጣት ግን መቼም ቢሆን አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ሌላ ሌላው በሙስና የሚዘረፈውና በፕሮጀክት ስም እየተመደበ ወደ ባለሥልጣናት ኪስ የሚገባው ገንዘብም በብዙ ትሪሊዮን የሚገመት መሆኑ አይካድም፡፡ ሠራተኛው ግን እየወለደና እየከበደ ልጆቹንም በግል ቀርቶበት በመንግሥት ትምህርት ቤት እያስተማረ በቅጡ መኖር ይቅርና በቀን አንዴም መቅመስ አልቻለም፡፡ የሀኪሞች፣ የመምህራን፣ የወታደሮችና ቅጥር ሠራተኞች ብሶት እየተፍለቀለቀ ነው፡፡
- የአቢይ ጦርነቶች፡፡ ትግራይ ወደመች፡፡ አማራ ወደመ፡፡ ሁለቱ ጠቅላይ ግዛቶች አሁን ሲዖል ሆነዋል፡፡ በሚሊዮኖች ረግፈዋል፡፡ በሚሊዮኖች ተርበዋል፡፡ በመቶዎች ምናልባትም በሚሊዮኖች ተሰደዋል፤ ተፈናቅለዋል፡፡ በብዙ ሥፍራ ትምህርትም፣ ሥራም፣ ማኅበራዊ ግንኙነትም ተቋርጧል፡፡ ይህ ሁሉ የሕዝብ ስቃይና መከራ ለኦሮሙማዎች የደስታ ምንጭ ነው፡፡ በጥላቻና በበቀል ለተመረዘ ሰው የሚጠላው ወገን ሲሰቃይ እንደማየት ጮቤ እሚያስረግጠው የለም፡፡ ይህ ደግሞ ሰይጣናዊ ፍጡር መሆንን ይጠይቃል፡፡ ሰይጣን የአስተዳደር መንበር ሲይዝ ምን ሊከሰት እንደሚችል ኢትዮጵያን በማየት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተያያዘ የሚገርመው ዋና ነገር ትግሬና አማራ በአቢይ ሲወድሙ የቭላድሚር ፑቲን ውሻ መኪና ገጭቷት ብትሞት መክፈቻ ዜና የሚያደርጉ የዓለም ታላላቅ ሚዲያዎች የኛን ሞትና የጦርነት ዕልቂት ከመጤፍ አለመቁጠራቸው ነው፡፡ “በነሱም ደርሶ ይዩት” አይባል ነገር፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ጉዳይ የሰውን ልጅ እንደአጠቃላይ የምንቅበት ትልቁ ነጥብ ነው፡፡ ሰው በሰውነቱ እንጂ በዘርና በቀለሙ ወይ በሀብቱና በዕውቀቱ ሊፈረጅ አይገባም፡፡ ጥቁር በመሆኔ የሚንቀኝ ነጭ ካለ እሱ ፈጣሪን የረሣ በሽተኛ ነው፡፡
- ዘረኝነት ሲነግሥ ሁሉን ነገር በጥርጣሬ ዐይን ማየትና “የኛ” እና “የነሱ” በሚል ልክፍት “የኛ” የሚለውን መጥቀም፣ “የነሱ” የሚለውን ደግሞ መጉዳት፤ ከሀገራዊ ጥቅማ ጥቅሞች ማግለልና በአድልዖ ጦር መውጋት፡፡ ይህ ክስተት በስፋት ይታያል፡፡ የእርሻ ትራክተር ወደ ኦሮሞ – የታንክ ማዕበል ወደትግራይና አማራ፡፡ የድሮን ድብደባና የጥይት ጋጋታ ወደአማራና ትግራይ – ማዳበሪያና የእርሻ ግብኣት ወደ ኦሮሞ፡፡ የሚጠሉትን ሕዝብ በርሀብ ማንጠራወዝ፣ የውጭ ዕርዳታ እንዳይገባለት በወታደር አጥሮ መከልከል፣ እንዳያርስና እንዳይዘራ በዲሽቃና በአየር ማደባየት፣ በጥቅሉ ግልጽ ጄኖሣይድ ዐውጆ ከምድረ ገጽ ማጥፋት፡፡ የሚገርም ደዌ! ሰው ሆኖ ተፈጥሮ እንዴት ሞትን ይረሳል? ሞትን አዝሎ የሚዞር ሰው፣ እንዴት ሰውን ይበድላል? ሁሉንም እኩል ለማገልገል ሥልጣን የያዘ ሰው ለአንደኛው እያዳላ ሲጠቅም እንዴት ሌላኛውን ይጎዳል? ምን ዓይነት አፈጣጠር ነው? የክሮሞዞምና የDNA-RNAችግርማ አለ፡፡ ይመርመሩ፡፡
- የኑሮ ችግሩ ሳያንስ አይፈለጉም የሚባሉ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀል፡፡ ቤታቸውን ማፍረስ፤ ከቀያቸው ማባረር፡፡ ሰላማቸውን ማደፍረስና ሀብት ንብረታቸውን መቀማት፡፡ ከሥራቸውና ባህላዊ ዕሤቶቻው መነጠል፡፡ በገዛ ቀያቸው ባይተዋር ማድረግ፡፡ በምክንያትም አለምክንያትም እሥር ቤት እያጎሩ ማሰቃየት፣ በምግብ ማስራብ፤ በዘር ሐረግ መነሻነት መሳደብና ማሳቀቅ፣ ምሁራንን ተተኪና አንቂ እንዳይሆኑ ደብዛቸውን ማጥፋት፣ መግደል፡፡ አማራን ሰው ማሳጣት፡፡ እሥር ቤቶችን የሞላውን ዜጋ አጢኑ፤ ይበልጡን አማራ ነው፡፡…
አዲስ አበባ ውስጥ ስንቶች ቤታቸው ፈረሰ? ስንቶች ሀብት ንብረታቸው ወደመ? ማንስ ጠበቃ ሆነላቸው? በሰበብ አስባቡ የቤቶች ፈረሳ እንደቀጠለ ስለመሆኑ ጥቂት ምሣሌዎችን እንይና እንሰነባበት፡፡
ከካዛንቺስ፣ ከሽሮ ሜዳ፣ ከተክለ ሃይማኖት፣ ከቤላ፣ ከፒያሣ .. የተነሱ ማለትም ቤት የፈረሰባቸው ሰዎች በፈረንሣይ ሌጋሲዮን አካባቢ የቆርቆሮም የፋይዚትም ጎጆ ቀልሰው ይኖሩ ነበር፡፡ ግፍ አይፈሬው የአቢይ መንግሥት ሰሞኑን ከዚያም ሊያባርራቸው እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግፍና በደል በዕጥፍ ድርብ የሚመለስ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም ይህንን ሰው በቃህ ሊለው የሚገባ ኃይል በተለይ ከኦሮሞው አካባቢ ቢነሳ የነፃነት መስዋዕትነቱን መጠን ይቀንሰዋል፤ ታሪካዊ ጠባሳዎችም በጊዜ ሂደት ሊሽሩ ይችላሉ፡፡ አለበለዚያ ዳፋው ከባድ ነው፡፡ ሀገር እንዳበደች አትቀርምና ስለነገም ማሰብ ደግ ነው፡፡ ነገን ያላሰቡ፣ ስለነጋቸው ያልተጨነቁ ብዙ የዓለማችን ሕዝቦች ጠፍተዋል፡፡ ትናንት ዛሬን እንዳልሆነ ሁሉ ነገም ዛሬን አይሆንምና ስለነገ ሁላችን አብዝተን ብንጨነቅ ጥቅሙ ለጋራችን ነው፡፡ ሕይወት ጤዛ ናት፡፡ ለአቢይ አህመድ ግን ሕይወት ምድር ናት፤ ለርሱ መብለጭለጭና ዱባይን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት በዚያም ሳቢያ ከኢምሬቶችና ከኩዌቶች ጋር በከተማ ውበት መፎካከር ትልቁ የሕይወት ግቡ ነው፤ የተለከፈበት ሌላው ህመሙ ደሞ ራሱን ከአምላክ አስበልጦ ማየቱ ነው፡፡ የ120 ሚሊዮን ዜጎች ሕይወት ተጠበሰ ተገነተረ ለርሱ ጉዳዩ አይደለም፡፡ በርሱ ቤት እርጅናና ሞት ቦታ የላቸውም፡፡ ለዚህም ነው አንጋፋ ዜጎቻችንን ማክበር ሲገባው “አርጅተዋልና በቅርቡ እንደቅጠል ይረግፋሉ” በማለት የሰላ ሂሳቸው የፈጠረበትን የጎፈዬ ስሜት በስላቅ የሚገልጠው፡፡ ስለሆነም ኦሮሞ አቢይን ይርሳው፤ ኦሮሞ አቢይ እንደሚያስጠቃው ይረዳ፡፡ አቢይ ማለት መልኣከ ሞት ነው፡፡ አቢይ እያለ ሰላምና ፍቅር የሉም፡፡ ጥላቻና መለያየት፣ ሞትና ስደት፣ እሥርና ግድያ፣ ጦርነትና ርሀብ … እንደነገሡ ይኖራሉ፡፡
በዚህ ሣምንት ደግሞ ከኮተቤ አካባቢ የሚሰማ ብልጽግናዊ የማፈናቀል ዜና አለ፡፡ ይሄውም ደኅንነት በሚባለው ደርግ ለሰላዮች ማሰልጠኛነት ይጠቀምበት የነበረውን ግቢ ለማስፋፋት ተብሎ ወደ 300 የሚጠጉ የአካባቢውን ነዋሪዎች ትነሳላችሁ ተዘጋጁ ብሎ እንደነገሯቸው ከአካባቢው ሰዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ግቢው አሁን ያለው ቦታ ጅብና ጦጣ የሚተራመስበት መሆኑ ይነገራል፡፡ ማስፋፋት እንኳን ቢፈለግ ሰዎችን ሳይነካ በአጠገቡ ያለውን ጫካ ሊጠቀምበት በቻለ ነበር፡፡ ነገር ግን የብልጽግና ዓላማ ዜጎችን ማንገላታትና ከባህላዊ ዕሤቶቻው ማቆራረጥ በመሆኑ እነዚህ ለ40 እና 50 ዓመታት በዚያ ቦታ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከሰላማዊ ኑሯቸው ሊባረሩ እንደሆነ ተነግሯቸዋል፡፡ ከነዚህ ሰዎች ጋር በኪራይም በጥገኝነትም በደባልነትም ተጠግቶ የሚኖረው የሰው ብዛት ቢገመት የሚፈናቀለው ሕዝብ ከአንድ የገጠር ወረዳ ሊበልጥ ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ሕዝብ በአንዲት ቀላጤ ትነሳለህ ሲባል የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊና አካላዊ የጤና ጉድለት ከባድ ነው፡፡ የመንግሥት የገንዘብ አቅም እጅጉን ተንኮታኩቶ ደመወዝ እንኳን መክፈል እያቃተው ባለበት ጊዜ ይህን ያህል ሕዝብን የማፈናቀል ፕሮጀክት ማካሄድ ለምን አስፈለገው ብለን ብንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው፡፡ ያም ከፍ ሲል እንደተገለጸው በሕዝብ ልቅሶና ዋይታ ደስታን ለመሸመት እንጂ በዚህ ጦርነትና የኑሮ ውድነት አገርን እያመሰቃቀለ ባለበት ወቅት ጤናማ መንግሥት ዜጋውን አያፈናቅልም፡፡ ብልጽግና ግን ያው የወፈፌዎች ስብስብ በመሆኑ በዕብደት ሥራው ገፍቶበታል፡፡ የዚህ ሁሉ ግፍ ከፋይ ይበልጡን ኦሮሞው ነውና የኦሮሞ ልሂቅና የኦሮሞ ወጣት ቆም ብሎ ማሰብ ይጀምር፤ ሀሰተኛ ትርክት ከፈጠረበት የስሜት ሞቅታም ይውጣና ወንድሞቹ ጋር በፍቅር ይተቃቀፍ፡፡
- የፍትህ መጥፋትና የሙስና መንሰራፋት፡፡ ትውልዱ ከሞራልና ከሃይማኖት ዕሤቶች እንዲወጣ በተለይ ባለፉት 50 ዓመታት ብዙ ሥራ ተሠርቷል፡፡ አሁን ዓለም አቀፉ ገዢ የጨለማው ኃይል እንደኢትዮጵያ የሚደሰትበት ሀገር ባይኖር አይገርምም፡፡ ገለቴ ቡርቃና ቀነኒ አዱኛ የተባለችው አርቲስት የደረሰባቸውን ማየት ብቻውን ለዚህ ለሞራል መንኮታኮታችን ዋና ማሳያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህግ ብሎ ነገር የለም – ህጋዊነትና ሞራላዊ ስብዕና ይናፍቅሃል፡፡ ሌብነት፣ አጭበርባሪነት፣ ማይምነት፣ ስግብግብነት፣ የሥነ ምግባር ጉድለት፣ ዋሾነት፣ ሆድ አደርነት፣ …. ከራስጌ እስከግርጌ ተንሰራፍተዋል፡፡ የሀገራችን ዋና አዛዥ ከታች ገንዘብ ሲሆን ከላይ ደግሞ አቢይ አህመድ ነው፡፡ ሰው ገድለህ ብትታሰር ገንዘብ ይኑርህ እንጂ እንዲያውም ሟቹ እንዲከሰስልህ ዐቃቤ ህጉን ራሱን ልትቀጥረው ትችላለህ፡፡ በሌላም በኩል ፍርድ ቤቱም፣ ፖሊሱም፣ መከላከያውም፣ ክልሉም፣ዞኑም፣ ክፍለ ከተማና ወረዳውም፣ ሚኒስትሩም፣ ጳጳሱም ሼሁም ፓስተሩም በስልክ የሚታዘዘው በአቢይ ነው – አቢይ ካለ አለ ነው – ውልፊት የለም (“ለ”ዎች ላልተው ይነበቡ)፡፡ አቢይ ከፈለገ በቀን ስንተዜ መተንፈስ እንዳለብህ ሊወስንብህና ለውሳኔው መተግበርም የህክምና ባለሙያ ደምብ አስከባሪ ሊመድብብህ ይችላል – የቤትህን ቀለም የሚመርጥልህ እኮ አቢይ ነው፤ የመብራትህን ዓይነትና የመስኮትህን መጋረጃ ቀለምና ሞዴል የሚመርጥልህ እኮ አቢይ አህመድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትተነፍሰው በአቢይ ሣምባ መሆኑን ካልተረዳህ የአሁኒቷን ኢትዮጵያ አታውቃትም ማለት ነው፡፡ አብዶ አሳበደን፡፡
በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ህጋዊ መሆን ህገወጥ የመሆን ያህል ነው፡፡ ገንዘብ አፍ አውጥቶ ሲናገርና በደናቁርት እጅ የገባው ፖለቲካም ሚሊዮኖችን ሲያሰቃይ የምታየው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ዘረኝነትን መሠረት ያደረገ ሥርዓተ አልበኝነትና ሙሰኝነት የኢትዮያን ነባር ባህላዊና ሃይማኖታዊ ዕሤቶች ድራሻቸውን አጥፍተው በነሲብ እየኖርን ነው፡፡
ይህ አስቀያሚ ትዕይንት መጥፎ አሻራ ጥሎ እንዳያልፍ የአቢይ መንግሥት አደብ ይገዛ ዘንድ የኦሮሞ ልሂቃን ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ አቢይ ሥልጣን ላይ አንድ ሣምንት በቆዬ ቁጥር የሚያስከትለው ጥፋትና የሚነዛው ውሸት አንድ ሌላ መጥፎ መሪ በአሥርና ሃያ ዓመታትም አይፈጽመውም፡፡ ለጥፋትና ውድመት፣ ለበቀልና ቅጣት በዓለማችን እጅግ ፈጣን አእምሮ ያለው ብቸኛ ሰው አቢይ ነው፡፡
- “የበላችው ያስገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንዲሉ አቢይ ነዳጅን ጨምሮ በብዙ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የቫት ግብር መጣሉ እየተነገረ ነው፡፡ ጉዳችን ይበልጥ ሲንተከተክ ይታየኛል፡፡ ይህ ሰው ከአራት ኪሎ እስኪወገድ የምናየው አበሳ መቼም ትንግርት ነው፡፡ …