ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
(ሰኔ 10፣ 2017) June 17, 2025
ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ዕውቀት በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ በተለይም ስልጣንን የጨበጡ ሰዎች የሚከተሉትን በአመጽ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስንመለከት ከዘጠና በላይ የሚሆን ህዝብ በስጋት ላይ እንደሚኖር መገመት ይቻላል። በተለይም የሶስተኛው ዓለም ጦርነት ሊመጣ ይችላል ብለው የሚያስፈራሩትን የሚዲያና የሚሊተሪ ሰዎችን አነጋገር ስንሰማ እነዚህ ሰዎች ጭንቅላታቸው በትክክል ማሰብ ይችል እንደሆን መጠያቅችን አይቀርም። ከዚህም በላይ የአንዳንድ አገር የመከላከያ ሚኒስተሮች፣ የሚሊተሪ ሰዎችና የፖለቲካ አማካሪዎች ጦርነት መምጣቱ የማይቀር ጉዳይ ስለሆነ ማንኛውም ዜጋ፣ ልጆችንም ጨምሮ ለጦርነት መዘጋጀት አለባቸው እያሉ በተደጋጋሚ ሲያወሩ ስንሰማ እነዚህ ሰዎች የቱን ያህል ከትክክለኛ ዕውቀት የራቁ መሆናቸውን እንገነዘባለን። በጥቂት ሰዎች በመከበብና ተንኮል በማውጠንጠን ጠቅላላውን ህዝብ ለከፍተኛ አደጋ እንደሚያጋልጡና ጦርነትንም ባክህ ና እያሉ እንደሚተወቱ በየቀኑ የምንሰማው መራራ ሀቅ ሆኗል። ፖለቲከኞች የሚባሉትና በህዝብም የተመረጡት ሰዎች ደግሞ የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል የሚወሰኑት በትላልቅ ወይም በወፍራም ጂኔራሎች፣ የስለላ ሰዎችና በሳይንስ ላይ ያልተመረኮዘና ተጨባጭ ሁኔታዎችን በደንብ ማንበብ በማይችል የፖለቲካ አማካሪዎች የተከበቡና የተሳሳተ ምክር የሚሰጣቸው ናቸው። በተለይም ይህ ሁኔታ በአሜሪካ ፖለቲከኞችና በምዕራብ አወሮፓ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ድርጅት(NATO) ዘንድ የተስፋፋና ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ በማድረግ የዓለምን የጥሬ ሀብትን በመቆጣጠር በየአገሮች ውስጥ ሰላማዊ ኑሮ እንዳይመሰረትና የአንድ አገር ህዝብም የተስተካከለና ህዝቡን ለማሰባሰብና ውስጣዊ ጥንካሬ ሊሰጠው የሚችል ወደ ውስጥ ያተኮረ(Inward Looking Strategy) የኢኮኖሚ ግንባታ እንዳይካሄድ የሚደርግ ነው። ጦርነትም የሚካሄደው ደግሞ በአሜሪካና በምዕራብ አውሮፓ ምድር ሳይሆን በአንዳንድ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ፣ በምስራቅ አውሮፓ፣ አሁን ደግሞ በማዕከለኛው የምስራቅ አገሮች(Middle East) በእስራኤልና በኢራን መሀከል የሚደረገው ጦርነት ነው። በተለይም ሁለቱንም ጦርነቶች፣ ማለትም በራሽያና በዩክሪይን እንዲሁም ደግሞ በእስራኤልና በኢራን መሀከል የሚካሄደውን ጦርነት ስንመለከት ዩክሬይንም ሆነ እስራኤል በአሜሪካና በተቀሩት የኔቶ አባላት አገሮች ዕርዳታ የሚመኩና የእነሱን “የሰለጠነ እሴት”(Western Value) የሚሉትን እናራምዳለን፣ የአረመኔዎችን ባህል እንዋጋለን፣ የመጨረሻም መጨረሻም እናጠፋዋለን ብለው የሚታገሉ ናቸው። ችግሩ ግን ዩክሬንይም ሆነ እስራኤል የጎረቤት አገሮቻቸው፣ ራሽያና ኢራን እስከ አፍንጫቸው ድረስ የታጠቁና ከተማዎችን እንዳለ የሚደመስሱና በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ህዝብ በአንድ ጊዜ ሊጨርስ የሚችል የተወሳሰበ ባሊስቲክ ሚሳይል ብለው የሚጠሩትና አውሮፕላኖችን ከሰማይ እንዳለ የሚመታና የሚበታትን S-300, S-400ና S-500 የመከላከያ መሳሪያዎች የታጠቁ ናቸው። ታዲያ ሀቁ ይህ ከሆነ አንድ አገር ከጎረቤት አገሩ ጋር የሚያጣላው ምን ነገር አለ? ለምን አንድ አገርስ ሌላውን ከመጀመሪያውኑ ጠላቴ ነው ብሎ በመፈረጅ ራሱን በክፍተኛ መሳሪያ በማስታጠቅና የጦር ኃይል በመገንባት የራሱን ህዝብ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ሊጥል የሚችል ጦርነትን ይጋብዛል? ኢራን ከእስራኤል ርቃ የምትገኘው አንድ ሺህ ኪሎሜትር ሲሆን፣ ራሽያና ዩክሬይን ደግሞ በደንበር የሚዋሰኑ፣ ከሰባ ዓመት በላይ አንድ አገር የነበሩና በአንድ ርዕዮተ-ዓለም የሚተዳደሩ ነበሩ። ከሁለተኛውም ዓለም ጦርነት በኋላ በጋራ በመሆን በሂትለር ጦር የፈራረሰባቸውን ከተማዎች እንደገና በመገንባትና ኢንዱስትሪዎችንም በማስተካከልና በመትከል አዲስ ህይወት የጀመሩ ነበር? ታዲያ ከሰባ ዓመት በኋላ ምን ጉድ ቢፈጠር ነው እንደ ጠላት መተያየት የጀመሩት? ችግሩ የአገዛዞች ወይስ በህዝቦች ዘንድ የተፈጠረ ችግር? ሀቁን ለመናገር ከተፈለገ ጦርነቱ የተቀሰቀሰው በጥቅም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በተገዙ ጥቂት ኃይሎችና በአሜሪካኖች የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ አማካይነት ነው። በመሰረቱ የራሽያም ሆነ የዩክሬን ህዝቦች ስላቮች ናቸው። ተጋብተው የተዋለዱና፣ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውም ሁለቱ ህዝቦች የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታዮች ወይም አማኞች ናቸው። ለማንኛውም ጥቂት ፖለቲካ ነን ባዮችና በጥቅም በተገዙና ከራሳቸው ፍላጎት ውጭ አሻግረው ማየት የማይችሉ የታሪክ ወንጀል በመፈጸም በቀላሉ ሊድን የማይችል በሽታ ጥለው ያልፋሉ።
ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሳይታሰብና ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ እስራኤል በኢራን ላይ የከፈተችው ጦርነት ነው። ጦርነቱም የተከፈተው ሮም ላይ በአሜሪካንና በኢራን መሀከል ኢራን የአቶም ቦምብ እንዳታመርት ንግግር ለማድረግ ዝግጅት ላይ ባሉበት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ ነው። እስራኤልም አሜሪካንና ኢራን አንድ ዐይነት ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ በሚል ግምትና፣ ኢራንም ቀድሞ የአቶም ቦምብ ገንብታለች በሚል የውሸት ክስ፣ ቀድሜ የመከላከል እርምጃ(Preemptive Measure) መውሰድ አለብኝ በማለት ከሰማይ እንደወረደ ዱብ ዕዳ ጦረነት በመክፈት አራት የሚሆኑ ከፍተኛ የጄራልነት ማዕረግ ያላቸውና፣ አምስት የአቶም ቦምብ ተመራማሪዎችን ስትገድል ወይም ስታስገድል፣ ከሰባ በላይ የሚሆኑ ንፁህ ዜጋዎች፣ ህፃናትም ጭምር በቦምብ በመደብደብ በመኖሪያ ቤታዎቸቸው ውስጥ ተገድለዋል። አርቆ ማሰብ የጎደለው ወይም ገደብ የሌለው የድንቁርና ፖለቲካ ማለት እንደዚህ ነው። የእስራኤሉ ጠ/ሚኒስተር ኔታንያሁ በሙላሆች የምትገዛውን ኢራንና አገዛዙን ባለኝ ጠንካራና ዘመናዊ የጦር ጄቶች በመጠቀም አንበረክካቸዋለሁ፣ ከስልጣንም አባርራቸዋለሁ ብሉ የከፈተው ጦርነት ሳያስበው ትላልቅና ስትራቴጂክ የሚባሉ ከተማዎቹ እንዲጋዩ ለኢራን አመቺ ሁኔታን ፈጥሯላታል። እንደ ፔንታጎን የሚቆጠረውም የመከላከያ መስራያቤቱና ለሰራዊቱ ጥይት እየሰራ የሚያቀርብ መሳሪያ የሚያምርቱ ፋብሪካዎች ተጎድተዋል፤ አንዳንዶች ወድመዋል። በተጨማሪም የአቶም ቦምብ የመመርመሪያ ጣቢያ የሆነ ከቴላቢብ ወደ 26 ኪሎሜትር የሚገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ በኢራን በተተኮሰ ባሌስቲክ ሚሳይልስ ሊደመሰስና እዚያ ውስጥም ሲሰሩ የነበሩ ሳይንቲስቶች እንዳለ ተገድለዋል። ኔታንያሁና ግብረ-አበሮቹ፣ እንዲሁም ሞሳድ የሚባለው የስለላ ድርጅቱ ከኢራን ጋር ጦርነት መግጠም ማለት ከሃማስና ከሂዝቦላ ፣ የፓለስቲኒያውና የሊባኖኑ የነፃነት ታጋዮች፣ ኔታንያሁና የምዕራብ ሜዲያዎች፣ የፖለቲካ ሰዎችና የጦር ጄኔራሎች አሸባሪ ኃይሎች ብለው ከሚጣሯቸው ጋር እንደመግጠም አድርገው በመቁጠርና በአጭር ጊዜ ውስጥም በድል አድራጊነት በአሸናፊነት እንደሚወጡ በመገመት-የተሳሳተ ግምት- በራሳቸው ህዝብና በአገራቸው ላይ ጦርነትን በመጋበዝ በቀላሉ ሊወጡ የማይችሉት ወጥመድ ውስጥ ለመግባት በቅተዋል። በዚህም የተደናገጠው ኔታንያሁን አሜሪካን የግዴታ ጣልቃ በመግባት የጦርነቱ ተካፋይ በመሆን ከዚህ ዐይነት አሳፋሪ ሁኔታ ውስጥ አውጣኝ በማለት በመለማመጥ ላይ ይገኛል። በቀጥታም ለዶናልድ ትረምፕ በመደወል ተነጋግሯል። ፖለቲካሊ አለማሰብ ማለት እንደዚህ ነው። በኃይል ብቻ የሚመካ የመጨረሻ መጨረሻ ላይ የባሰ እሳት ይነድበታል፤፡ይዋረዳልም።
ኔታንያሁና አገዛዙ በኢራን ላይ ጦርነት ሲከፍቱ ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ህዝብ እንደሚያሰተዳድሩ በፍጹም አልተገነዘቡም ነበር። ቀደም ብለው በተደጋጋሚ በፓሌስቲናውያንና በሊባኖን ህዝቦች ላይ ጦርነት ሲከፍቱ ያልታያቸው ነገር ሊያስከትል የሚችለውን ፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ቀውስ ነበር። እስራኤል እንደ አገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካንና በተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ድጋፍና የቴክኖሎጂ ዕርዳታ በመታገዝ በፓሌስቲናውያኖች ላይ የምታካሂደው ጦርነት ከስትራቴጂያዊ ጥቅሙ ጉዳቱ በጣም ከፍ እያለ መጥቷል። በተለይም ከአጎራባች አገር ጋር የሚካሄድ ጦርነት ልክ አሜሪካ ስምንት ሺህና አስር ሺህ ርቆ በመሄድ አንዳንድ አገሮችን በጀት እንደሚደበድበው ዐይነት ጦርነት ሳይሆን እዚያ በዚያው ከጎረቤት አገርና መግቢያውንና መውጫውን ከሚያውቀው አጎራባች አገር ጋር ነው። ቀደም ብለው የነበሩት የእስራኤል መሪዎችና ከ20 ዓመታት ጀምሮ ደግሞ ኔታንያሁና አገዛዙ በማንአለብኝነት በፓሌስቲናውያንና በሊባኖን ህዝቦች ላይ የሚያካሂደው ጦርነት የእስራኤልንም ህዝብ ጥቅም በፍጹም የሚያስጠብቅ አይደለም። የእሰራኤልን ህዝብ ጥቅም ማስጠበቅ ማለት ከአጎራባች አገሮች ጋር በሰላም መኖር ማለት ነው። ሰፊው የእስራኤል ህዝብ በሰላም ሊኖር የሚችለው በአካባቢው ያለውን ህዝብ ነፃነትና በሰላም የመኖር መብቱንና ፍላጎቱን ሲያከብር ብቻ ነው። አገዛዞቹ ካለምንም ምክንያት እየተነሱና የተወሳሰበ የጦር መሳሪያ እየሰሩና ከተጨባች ሁኔታዎች የራቁና ማሰብ የማይችሉ ወታደሮችና የስለላ ሰዎችን በማሰልጠን በየአካባቢው በሚፈጥሯቸው ጠላቶች የእስራኤል ህዝብ እፎይ ብሎና ተዝናንቶ በዘለዓለም ሊኖር እንዳይችል አድርገውታል፤ ከተለያዩ አካባቢዎች በሚተኮሱ ድሮኖችና በተለይም በድንበር አካባቢ የሚኖሩ እስራኤላውያን ህይወታቸውን ያጡ አሉ። አንድ ህዝብ በሰላም ሊኖር የሚችለው ከጎረቤት አገሮቹ ጋር በንግድና በልዩ ልዩ ነገሮች ጥሩ ግኑኝነት ሲፈጥርና የባህልና የልዩ ልዩ ነገሮች ልውውጥ ሲያካሂድ ብቻ ነው። አንድ ህዝብና የአንድ አገር አገዛዝ ካለበትም ሁኔታ ባሻገር በሰፊው ማሰብ መቻል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ነፃ የሆነና በስለላ ድርጅትና በወታደር ያልተከበበና በኃይል ብቻ የማያምን መንግስት ያስፈልጋል። ኔታንያሁና ግብረአበሮቹ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው አይመስልም። ፖለቲካን ንጹህ በንጹህ ወደ ተንኮል መስራትና በመሳሪያ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ታጥቆ ወደ መገኘት ለውጠውታል። ፖለቲካ ማለት አንድን ህዝብ በሰላም ማስተዳደር፣ ለዚህ ደግሞ የተሟላ ነፃነትን ማጎናፀፍና ከጎረቤት አገሮች ጋር በመከባበርና በመተጋገዝ ላይ የተመሰረተ የውጭ ፖለቲካ ማካዴ ማለት ነው። የእነ ኔታንያሁ ፖለቲካ ግን በብዙ ሚሊዮን ማይልሶች ከዚህ ዐይነቱ ቅዱሳዊ አስተሳሰብ የራቀ ነው። ፖሊሲያቸውም መስፋፋትና የጥሬ-ሀብቶችን መቆጣጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ፖሌስቲናውያንን ማውደም ይፈልጋሉ። በአካባቢያቸው ያሉና ይፎካከሩኛል የሚሏቸውን አገዛዞች በመጣል ለእነሱ በሚስማማ ለመተካት ይፈልጋሉ። በሌላ ወገን ግን የእስራኤል ህዝብ በቁጥር እየጨመረ የሚመጣ አይደለም። ልክ እንደተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች የዲሞግራፊ ችግር አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ሰፋ ያለ አገርን ለመቆጣጠር የግዴታ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ አዳዲስ ህፃናት በፍጥነትና በብዛት መወለድ አለባቸው። ሌላው የህዝብን ቁጥር ለመጨመር ያለው አማራጭ መንገድ ከውጭ ሌሎች የውጭ አገር ዜጎችን በብዛት ማስገባትና የእስራኤልን ዜግነት መስጠት ነው። ይህ ደግሞ በራሱ ችግር አለበት። ከውጭ ቀስ በቀስ ወደ እስራኤል የሚገባ ዜጋ በቁጥር እየጨመረ ሲሄድ የባህልና ሌሎች አስተሳሰቦችና የአኗኗር ስልቶች ይቀየራሉ። ይህም ማለት የይሁዲን የአኗኗር ስልትና ዕምነት እየከለሰውና እያዳከመውም ሊመጣ ይችላል። በሌላ ወገን ደግሞ እስራኤልም ሆነ ሌሎች አገሮች ባለህበት ረግጠው ሊኖሩ አይችሉም። በድሮ የአኗኗር ስልታቸውና በሃይማኖታቸው ፀንተው በፍጹም ሊቆዩ አይችሉም። ማንኛውም ህብረተሰብ በሂደት ውስጥ ይለወጣል፤ ይህም የህብረተሰብ ህግ ነው። ማንም አገር ከዚህ ሊያመልጥ አይችልም። ጥያቄው አንድን ባህልና ዕምነት የማቆየትና ያለማቆየት፣ ወይም ደግሞ የግዴታ የመለወጡ ጉዳይ ላይ ሳይሆን ሰላማዊና ፈጣሪ የሆነና፣ እንዲሁም ስነስርዓት ያለውና የሚከባበር ማህበረሰብ እንዴት መገንባት ይቻላል? የሚለው ነው እንደ ጥያቄ መነሳትና ለክርክርም መቅረብ ያለበት።
ለማንኛውም እነ ኔታንያሁ የሚያካሂዱት ጦርነት በመሰረቱ የአሜሪካንና የተቀሩትን የኔቶ አባል አገሮች ጦርነት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ አንዳንድ የእስራኤል የስለላ ወጥመድ ውስጥ የገቡ አገሮችና ሴሚቶችን የሚጠሉ አገሮች እስራኤልን እየደገፉ እየመሰሉና እየገፋፉም የጂውሽ አገዛዝ እንዲወድም ይፈልጋሉ። አውሮፓውያን በከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ የተካኑ ስለሆኑ አገሮችን ርስ በርስ በማጣላት የራሳቸውን የበላይነት ለዝንተ-ዓለም ለማቆየት ይፈልጋሉ። ይህንን ጉዳይ አክራሪው ኔታንያሁና ግብረአበሮቹ በፍጹም የተረዱት አይመስልም። ባለፉት ሃያና ሰላሳ ዐመታት ኔታንያሁና ግብረአበሮቹ በሚከተሉት የአክራሪነት ፖለቲካ እስራኤል የምሁር አልባ እየሆነች መጥታለች። የቲአትር፣ የስነ-ጽሁፍ፣ የፊልም ደራሲዎችና ቀራጾች፣ እንዲሁም ሌሎች ምሁራን እስራኤልን ለቅቀው አውሮፓና አሜሪካ ተበታትነው እንዲኖሩ ተገደዋል። ይህ ሁኔታ ለቀኝ ወይም ለአክራሪ ኃይሎች እንደልባቸው እንዲፈነጩ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ይሁንና እነዚህ አክራሪዎች ያልተገነዘቡት ነገር የራሳቸውን የመጨረሻ መጥፊያ መንገድ የሚያዘጋጁ መሆናቸውን ነው። ወደ ጦርነቱም ጋ ስንመጣ የመጨረሻ መጨረሻ ኢራን በአሸናፈነት ትወጣለች። የእስራኤልን አየር ካላምንም ገደብ እየጣሱ የሚገቡ ባሌስቲክ ሚሳዮሎችና ድሮኖችም ስላሏት እስራኤል እንደምተመኘው በአሸናፊነት ልተወጣ አትችልም። እስካሁንም ድረስ የኔታንያሁ አገዛዝና የስለላ ድርጁቱ ባልጠበቁት መንገድ ኢራን ድሮኖችን፣ የባሌስቲክ ሚሳይሎችንና በከፍተኛ ኃይል ተስፈንጣሪ የሆኑ ራኬቶችን(Hypersonic Missiles) በመተኮስ የእስራኤልን የመከላከያ ኃይል(Iron Dome) ጥሶ በመግባት ቴላቢብን፣ ሃይፋንና የሩሳሌምንና እንዲሁም ሌሎች ከተማዎችን እንዳለ እያወደሟቸው ነው። በተጨማሪም የየመን ሁቲ የሚባሉ በሩቅ ተስፈንጣሪ መሳሪያ የታጠቁ ከየመን ሆነው በማወፈንጨት እስራኤልን እየደበደቧትና ህዝቡንም ግራ እያጋቡት ነው። ህዝቡም ወደ መከላክያ ዋሻዎች እንዲገባ ሲገደድ፣ የኢንተርኔት ግኑኝነትም እንዳለ ተቁርጧል። ቴላቢብ የሚገኘውም ትልቁ የአውሮፕላን ጣቢያ ተደብድቧል፤ በከፊልም ስራውን እንዲያቆም ተገዷል። ታዲያ እንደዚህ ዐይነቱን ጦርነት መክፈትና በከፍተኛና በአደገኛ መሳሪያ የታጠቀ ኃይል መልሶ እንዲያጠቃ መጋበዝ ምን የሚሉት የፖለቲካ ስልትና የጦርነት ስትራቴጂ ነው? የማይገባኝ ፖለቲካ የጦርነት ስልት። ለምንስ ይህ ዐይነቱ እልክ አስጨራሽ ጦርነት አስፈለገ? ምክንያቱ ምንድነው? ከበስተጀርባውስ ሌሎች ኃይሎች አሉ ወይ? ግልጽ የማይሆን ቢመስልም ኔታንያሁ በኢራን ላይ ይህን ዐይነት ጦርነት ዝም ብሎ አልከፈተም። ወይም የአሜሪካኑ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ወይም ደግሞ የጠለቀው መንግስት የሚባለውና ከመንግስት ስር ሌላ መንግስት ሆኖ ተንኮል የሚሸርብና በዓለም አቀፍ ደረጃም ጦርነትን የሚያካሂድ፣ ከሚሊታሪ የኢንዱስትሪ-ውስብስብ ጋርና ከሌሎች የዓለምን የጥሬ-ሀብቶች ከሚቀራመቱ ትላልቅ ባቅንኮችና የሀብታሞችን ገንዘብ ከሚያስተዳደሩ(Hedge Funds) ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ የውስጥ ኃይሎች በጦርነቱ ግፋበት የሚል የአረንጓዴ መብራት ተሰጥቶት ሊሆን ይችላል። ኔታንያሁን ደግሞ አሜሪካ ተወልዶ ያደገና፣ እዚያውም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተምሮ የሰራና በአሜሪካን የረብሻና በተንኮል አገሮችን የማከረባበት ሰይጣናዊ መንፈስ የሰለጠነ ነው። ይህም ማለት በመሰረቱ ከጂውሽ ህዝብ ጋር የሚያገናኘውና፣ በሰላም እየሰራ ለመኖር የሚፈልገውን ተራውን የጂውሽ ህዝብም ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ ጦርነቱ የውክልናና በጠቅላላው ቀስ በቀስም የአረብ አገሮችን በማከረባበትና ጦርነት ውስጥ አዝፍቆ በማስገባት በአሜሪካንና በኢንዱስትሪዎቹና በባንኮች ቁጥጥር ስር በማምጣት የዘይትንና የጋዝን ሀብት ለመዝረፍ የሚካሄድ ጦረነት ነው። የአሜሪካን ወታደር፣ የስለላ ድርጅቱና ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያ አምራች ፋብሪካዎችና፣ በእነዚህም የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎች ውስጥ የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች በሰው መሞት የሚደሰቱና የሚነግዱ መንፈስ-አልባዎች ናቸው። ሃይማኖታቸውም የጥሬ-ሀብትን መቆጣጠር፣ የትርፍ ትርፍን ማካበትና ጠቅላላው የዓለምን ህዝብ በራስ ቁጥጥር ስር በማምጣት በየአገሮች ውስጥ ያሉ ጥንታዊ ባህሎችንና ሃይማኖቶችን በማውደም ብልግናን ማስፋፋት ነው። ይህም ማለት የዓለም ህዝብ በሙሉ መንፈሰ-አልባ እንዲሆንና እየተንቀዠቀዠ እንዲኖር ማድረግ ነው ዋናው ተግባራቸው። ከኢራንና፣ ከየመን ሁቲስ፣ ከሂዝቦላና ከሃማስ ጋር እልክ ውስጥ የተጋባውና በደመ-መንፈስ በመመራት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በጋዛ አካባቢ የሚኖሩ ወደ ሰማኒያ ሺህ የሚጠጉ ንጹህ ፓሌስቲናውያን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ያስገደለውና፣ በየቀኑ ወደ ሃምሳና ስድሳ የሚጠጉ ዜጎችን ሰበብ አስባብ እየፈለገ የሚያስገድለው ኔታንያሁና የመከላከያ ሚኒስተሩና ሌሎችም የጦር አለቆችን ማንም ኃይል አቁሙ የሚላቸው የለም። አሜሪካንና የተቀሩት የኔቶ አባል አገሮች የሚሰጡት ተደጋጋሚ ምክንያት፣ ያለቀው ሰው አልቆ እስራኤል ለመኖር ወይም እንደ አገር ለመዝለቅ የግዴታ ራሷን መከላከል አለባት የሚል የማፌዝ አባባል ነው። ይህም የሚያረጋግጠው የአሜሪካንና የአውሮፓ ፖለቲከኞች በመሰረቱ ፖለቲከኞች ሳይሆኑ በሊበራልና በብዝሃዊነት ስም ከፍተኛ ውንብድናን የሚያካሂዱ መሆናቸውን ነው። በሊበራሊዝም ስም የሚመፃደቁ፣ እኛ ብቻ ነን የሰለጠንና የግለሰብን መብት የምናውቅ ነን ብለው ቢመፃደቁም የአሜሪካንና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች፣ በተለይም የእንግሊዝና የፈረንሳይ አገዛዞች ዋና ዓላማ አንድና ግልጽ ነው። ማንኛውም አገር ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ሊወጣ አይችልም። የእኛን ትዕዛዝ አልቀበልም፣ የራሴን አገር በመሰለኝ መንገድና ትክክልም ነው ብዬ በማምነበትና ህዝቤንም በሚጠቅም መንገድ አገሬን እገንበላሁ ብሎ የሚነሳ ኃይል በፈለግነው ጊዜ በመጣል ለእኛ አሽከር በሚሆን የመተካት ችሎታ አለን ብለው የሚያምኑ ናቸው። አገሮችንም በወዳጅና በጠላት መሀከል በመከፋፈል፣ እኛ የምንለውን የማይቀበልና ከሌላ ኃይል ጋር የሚሰለፍ ጠላታችን ነው። በሌላ አነጋገር፣ አሜሪካና ግብረአበሮቹ አንድን ከእነሱ ውጭ ያለንና ነጭ ያለሆነውን፣ በተለይም ጥቁርን ህዝብ እንደዝቅተኛ ዘር የሚመለከቱና አሽከርና ለማኝ ሆኖ መቅረት አለበት ብለው የሚያምኑ ናቸው። ይህን ዐይነቱ አስተሳሰብ የሚቃወም፣ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ የሆነና፣ ማንኛውም የሰው ልጅ ነጭ ሆነ ጥቁር፣ ብጫ ሆነ ሌላ ቀለም ይኖረው፣ ይህ ሁሉ ህዝብ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረና ራሱንም በፈለገው መንገድ የማደራጀትና በነፃነትም የመኖር መብት አለው ብለው ያስተማሩ ፈላስፍዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ለማንኛውም የአሜሪካንና የምዕራብ አውሮፓን አገዛዞችና ጠቅላላውን የፖለቲካ፣ የሚሊተሪና የስለላ፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ኤሊት አስተሳሰባቸውን ስንመለከት እጅግ አደገኛና የዓለም ህዝብ በሰላም ተረጋግቶ እንዳይኖር የሚያደርግ ነው።
ያም ሆነ ይህ እኛ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አለብን፣ የዓለምንም ህዝብ ዕድል እኛው ብቻ ነን መወሰን የምንችለው፣ ወይም ያለብን የሚለው የአሜሪካና የተቀሩት የኔቶ አባል አገሮች ፓለቲካ በፍልስፍናም ሆነ በሳይንስ የማይደገፍ የተወላገደ አስተሳሰብ ለዓለም ህዝብ ሰላም አደገኛ እየሆነ መጥቷል። እኛ ነን የሰለጠን፣ በትክክልም ማሰብ የምንችለው እኛው ብቻ ነን ፣ ሌላው ያልሰለጠነና በትክክል ማሰብ አይችልም የሚለው አስተሳሰብ በተለይም የራሳቸውን ዕድል ራሳቸው መወሰን በቻሉና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ተፎካካሪ እየሆኑ በመጡት አገሮች ራሽያ፣ ቻይናና ህንድ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ባለመቻሉ አሜሪካና የተቀሩት የኔቶ አባል አገሮች እንደ አበደ ውሻ ሁሉንም መንከስ አለብን በማለት የሚይዙት የሚጨብጡት ነገር ጠፍቶባቸዋል። ጦርነትንም በየቦታው በመቀስቀስ አንድን ህዝብ በጎሳና በሃማኖት በመከፋፈል ርስ በርሱ እንዲበላላ ያደርጋሉ። በ1989 ዓ.ም እ.አ.አ የኮሙኒስቱ ብሎክ ከፈራረሰና በአንድ ኃያል መንግስት የሚመራ ዓለም(Unipolar World)ተመሰረተ ከተባለ በኋላ አሜሪካንና የተቀሩት የኔቶ አባል አገሮች በአንድ ወጥ ህግ የሚገዛ(Rule based System)ስርዓት የሚለውን የእነሱን የበላይነት የሚያሰፍን ስርዓት ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የቀድሞ የዋርሶ ፓክት አገሮች አባል የሆኑትንና የራሽያም አካል የነበሩትን በራሳቸው ቁጥጥር ስር በማምጣት በቀጥታ ወደ ስምምነት ሳይሆን ወደ ግጭት የሚያመራ የፍጥጫ ፖለቲካ ነው መከተል የጀመሩት። የበላይነታቸውንም ለማስፈን ሲሉ መጀመሪያ ዩጎዝላቪያን፣ ቀጥሎ ደግሞ ኢራክን፣ ቀጥሎ ደግሞ በአፍጋኒስታን ላይ በአሸባሪነት ስም አሳቦ ወረራ መክፈትና፣ 20 ዓመት ያህል በሰው ምድር ላይ ጦርነት ማካሄድ፣ በመሃከሉ ጋዳፊን በመግደል ሊቢያን ብትንትኗን ማውጣትና ወደ ሶሪያም ማምራት የሚያረጋግጠው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው የምዕራቡ ዓለም የሚያካሃደው ፓለቲካ ሳይሆን ዐይን ያወጣ የውንብድና ተግባር ነው። በዚህ ብቻ ሳያቆም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የዩክሪይንን አዞብ በመባል የሚታወቀውን ፋሺሽታዊ ኃይል በማስታጠቅ በራሽያና በዩክሬይን መሀከል ጦርነት በመቀስቀስ ይኸው እንደምናየው ሶስት ዓመት ያህል የፈጀና በቀላሉ መቋጠሪያ የሌለው ጦርነት በመካሄድ ላይ ይገኛል። ዩክሪይንንም መሳሪያ በማድረግ ራሺያን በጦርነት በመያዝና ኃይሏን እንድትጨርስ በማድረግ ቢቻል የመንግስት ለውጥ (Regime Change)ማድረግ፣ ካልተቻለ ደግሞ ብትንትኗን በማውጣት የተትረፈረፈውን የራሽያ የጥሬ ሀብት መቀራመት ነው። እንዳየነው አሜሪካንና ምዕራብ አውሮፓውያን በእነ ፑቲን የጥበብና የጥንካሬ ፖለቲካ ይህንን ግባቸውን ማሳካት አልቻሉም። የመጨረሻ ላይ ግን የአሳድ መንግስትን በመጣል በአሸባሪ ኃይል ተክተዋል። መጨረሻ ላይ የቀራቸው ኢራን ብቻ ነበር። የኢራንንም የእስላም አገዛዝ ለማስወገድ የሚፈልጉት በአካባቢው እስራኤልን የሚፎካከር ኃይል መኖር የለበትም ከሚለው የተሳሳተና ተፈጥሮአዊ ያልሆነ እሳቤ በመነሳት ነው። ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የኢራን መንግስት የአቶም ቦምብ ለመስራት የሚያስፈልገውን የዩራኒየም መጠን በማከማቸት ላይ ነው በማለትና ያለ አግባብ በመወንጀል ነው። በሌላ ወገን ግን አሜሪካ፣ ራሽያ፣ ቻይና፣ ህንድና ፓኪስታን፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ እንዲሁም እስራኤልም የአቶም ቦምብ ባለቤቶች ናቸው። እነዚህ አገሮች ሁሉ አቶም ቦምብ ካላቸው ለምንድነው ኢራን ለመስራት የማይፈቀድላት? እኛ ብቻ ነን መስራት የሚፈቀድልን፣ ሌሎች አገሮች መስራት አይፈቀድላቸውም የሚል በእግዚአብሔር የተደነገገ ህግ አለ ወይ? እንደሚታወቀው አቶም ቦምብ ለሰው ልጅም ሆነ ለተፈጥሮ ጠንቅ የሆነ ነገር ነው። በአንድ አካባቢ ከፈነዳ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመግደል አልፎ የራዲዮ አክቲቭ ንጥረ ነገሮችም አካባቢን በመመረዝ ለብዙ ሺህ ዐመታት ጠንቅ ሆነው የሚቀሩ ናቸው። የሚነቀሉ አይደሉም። በተረጩበትም አካባቢ ምንም ነገር ማብቀል አይቻልም። የአቶም ቦምብ ለሰው ልጅም ሆነ ለተፈጥሮ ጠንቅ መሆኑ እየታወቀ ማንኛውም አገር ኃያል ነኝ ብሎ ቢመፃደቅም መስራት አልነበረበትም፣ የለበትም። አቶም ቦምብ መስራት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሰውን ልጅ ሊገድሉ የሚችሉ መሳሪያዎች በሙሉ መሰራት የለባቸውም። የጦር መሳሪያዎችን መስራት የሚጠቅመው የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ባለቤቶችንና የአክስዮን ድርሻ ያላቸውን ባለሀብታሞችን ነው። ከዚህም በላይ ወታደርና የጦር መሳሪያ በአንድ አገር ውስጥ የሰፈነን የአገዛዝ ኃይል የሚከላከሉ ናቸው። የአንድን አገር ዜጋ የሚከላከሉና ብሄራዊ ነፃነትንም የሚያስጠብቁ አይደሉም። እዚህ ላይ በጣም ቀልዱ ነገር አሜሪካና ግብረ-አበሮች በእንደዚህ ዐይነት የሰውን ልጅ እንዳለ የሚያጠፋና ተፈጥሮንም የሚመርዝ የአቶም ቦምብ ሲሰሩና ሲያከማቹ አንድ ኃይል ሊወረን ይችላል፣ ስለሆነም እንደማስፈራሪያ ነው የምንጠቅምበት እያሉ ነው የሚሰብኩት። ይሁንና አሜሪካንና የተቀሩት የኔቶ አባል አገሮች ራሳቸው ወራሪዎች እንጂ በሌላ ኃይል ተወረው አያውቁም። የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም በመባል የሚታወቁት ጦርነቶች በጀርመን ኢምፔሪያሊስታዊ ኃይል በራሽያ ላይ የተከፈቱ ጦርነቶች ናቸው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ሂትለር ስልጣን ላይ እንዲወጣ የደገፉት የእንግሊዝና የአሜሪካን የትላልቅ ኩባንያዎች ባለቤቶችና ከበርቴዎች ናቸው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነትም በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱት ቀጠተኛና የውክልና ጦርነቶች በሙሉ የአሜሪካንና የግበረ-አበሮቹ ጦርነቶች ናቸው። ታዲያ ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ማንም ኃይል እንዳይደፍረን ተዘጋጅተን መቀመጥ አለብን የሚለው አስተሳሰብ ከየት መጣ? ከጦርነት ይልቅ ተስማምቶ በመኖር የጥሬ-ሀብትን በስነ-ስርዓትና ዘላቂነት ባለው መንገድ መጠቀም የሚያዋጣው መንገድ አይደለም ወይ? በየአገሮች ውስጥ አንድ ትውልድ ብቻ ነው የሚኖረው ወይ? ተከታታይ ትውልድስ አይፈጠርም ወይ? ለተከታታዩ ትውልድስ የተሻለና ሰላም የሰፈነበት ዓለም ጥሎ መሄድ የተሻለና የሰለጠነ አስተሳሰብ አይደለም ወይ? ዛሬ በልቼ፣ ዛሬ ሁሉንም ነገር አግበስብሼና ተቆጣጠሬ ዛሬው አብጬ ዛሬው ልሙት የሚለው የአሜሪካን ፖለቲከኞች፣ የሚሊተሪና የስለላ ሰዎች፣ የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ባለቤቶችና ትላልቅ ባንኮችን የሚቆጣጠሩ ለምን ሰይጣናዊውን መንገድ በመከተልና በሰይጣናዊ መንፈስ በመመራት የዓለምን ህዝብ ፍዳ ያሳዩታል? ለመሆኑ መብት አላቸው ወይ? ራሳቸውንስ መጠየቅ ይችላሉ ወይ? የሚጠይቃቸውስ ኃይል አለ ወይ? የሚያካሂዱት የውስጥና የውጭ ፖለቲካቸው በሙሉ በህገ-መንግስቶቻቸው ውስጥ ተጽፈዋል ወይ? ዝምብለው በራሳቸው ስሜት በመነሳትና በተሳሳተ መረጃ በመሞላትና በመመራት ነው ወይ የዓለምን ህዝብ የሚያዋክቡት?
ያም ተባለ ይህ የአሜሪካና የአውሮፓውያኖች ፖለቲካ ሺህ ጊዜ የሊበራሊዝምን ካባ ቢያጠልቅም ዋናው ዓላማው ሌሎችን አገሮች የራሳቸው አሽከር ማድረግና የጥሬ-ሀብታቸውን በመቆጣጠር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዳይኖራቸው ማድረግ ነው። እነ ሂትለርና ተከታዮቹ ናዚዎች ሲነሱና ወረራ ሲያካሂዱ ጀርመን በሁሉም አገር(Deutschland Überalles)የሚለውን መፈክር ይዘው ነበር። አካሄዳቸውም ግልጽ ነበር። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የበላይነትን የያዘው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ የነፃ ገበያንና ንግድን፣ እንዲሁም ሊበራሊዝምን ሽፋን በማድረግ በስውር የእነ ሂትለርን የወረራና የዘረፋ ፖለቲካ ሲያካሂዱ ከ75 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል። ዋና ዓላማቸውንም ግብ ለማሳካት ቁጥራቸው የማይታወቅ የመንግስት ግልበጣዎች አካሂደዋል። በስድሳዎቹ ዓመታት በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በማዕከለኛውና በደቡብ አሜሪካን አገሮች በህዝብ የተመረጡ ፕሬዚደንቶችን በማስወገድ በወታደር ፋሺሽታዊ አገዛዞች ተተክተዋል። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችም ተገድለዋል። አፍሪካ ውስጥም ከ60 በላይ የሚሆኑ የመንግስት ግልበጣዎች ተካሂደዋል። በዚህም ምክንያት የአፍሪካ አገሮች ነፃ ወጡ ከተባለ በኋላም በተጨባጭ ሲታይ ነፃ አልወጡም።
በአጠቃላይ ሲታይ የአሜሪካንና የግብረአበሮቹ የፍጥጫና የፉክክር ፖለቲካ የዓለምን ህዝብ የሚያሰጋ ነው። ጦርነትን ዓለም አቀፋዊ የሚያደርግ ነው። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ህይወት የሚቀስፍ ነው። የእያንዳንዱም አገር ህዝብ እነሱና ተወካዮቻቸው በሚከፍቷቸው ጦርነቶች መገደልና ታሪክ መበላሽት የለበትም። የኔታንያሁ አገዛዝ በቀጥታ በኢራን ላይ ወደ ከፈተው ጦርነት ስንመጣ ስልጣን ላይ ያለውን በሙላሆች የሚመራውን አገዛዝ በማስወገድና በሌላ በመተካት ዘላቂነት ያለው ሰላም ሊፈጠር አይችልም። በአንድ አገር ውስጥ መሰረታዊና የተሻለ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ጦርነትን በመክፈትና ለውጭ ኃይል ተገዢ በሆነ ኃይል በመተካት አይደለም። የኢራን ህዝብ እዚህ ዐይነቱ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ሊወድቅ የቻለው በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በህዝብ የተመረጠና ሞሳዴ የሚባል ጠቅላይ ሚኒስተር በአሜሪካን የስለላ ድርጅትና በእንግሊዝ እንዲገለበጥ ከተደረገ በኋላና ሻህ በሚባል ንጉስ ከተተካ በኋላ ነው። የሻህ አገዛዝም ከአርባ ዓመት በላይ ለአሜሪካኖች ካገለገለ በኋላ የግራ እንቅስቃሴ እያየለ በመምጣቱና ኢራንም ከአሜሪካን ቁጥጥር ውጭ እንዳትወጣ በማለት በአሜሪካን የስለላ ድርጅት የተከበበና የተዘጋጀ በአያቶላ ሆሜኒ የሚመራ የእስላም አገዛዝ ስልጣን ላይ እንዲወጣ ተደረገ። አያቶላ ሆሜኒም ቴህራን ድረስ ከቦ ከፓሪስ ከስደት ቦታው ያስገባው የአሜሪካኑ የስለላ ድረጅት ነው። የአያቶላህ ሆሜኒም መንግስት ጥቂት ወራት ከቆየ በኋላ ጫማዬን ላሱ በማለት በአሜሪካን አገዛዝ ላይ አመፀ። ይህንን የተገነዘበ የአሜሪካንም አገዛዝን ሳዳም ሁሴንን በማስገደድና በማስታጠቅ በኢራን ላይ ጦርነት እንዲከፍት በማድረግ ስምንት ዓመት ከተከሳከሱ በኋላ ጦርነቱ ሊቆም ቻለ። ከዚያም በኋላ አሜሪካና ኢራን እንደ ዋና ጠላት መተያየት ጀመሩ። ድሮ ግራ የነበሩት ኢራናውያንን በማሰባሰብ የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት የኢራንን የእስላም አገዛዝ ለመጣል ያላደረገው ጥረት አልነበረም። ይሁንና ከአርባ ዓመት በላይ ማዕቀብ የተደረገበት የሙላሆች አገዛዝ ያለ የሌለውን ኃይልና ኢንተለጀንስ በመጠቀም የተወሳሰበና አስፈሪ የጦር መሳሪያዎች በመመስራትና የወታደር ኃይል በመገንባት በአካባቢው ራሱን ችሎ የወጣ ኃይል በመሆን እስራኤልን የሚፎካከር መሆን ጀመረ። ስለሆነም ይህ የእስላም አገዛዝ መወገድ አለበት የሚል አስተሳሰብ በእስራኤል የአክራሪ አገዛዝ፣ በአሜሪካኖች፣ በእንግሊዝና በፈረንሳዮች አገዛዝ መንፈስ ውስጥ በመቋጠር አካባቢው በሰላም እጦት የሚናወጥ ለመሆን በቃ። መቆሚያው መቼና ማንስ ኃይል እንደሚያቆመው የሚታወቅ ጉዳይ አይደለም። ምናልባት በእግዚአብሄር ኃይል ሊቆም የሚችል ይሆናል። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com